97948 law of succession/ government houses/ justiceable matters

አንድ የቀበሌ ቤትን ተከራይቶ የነበረ ሠው ከዚህ አለም በሞት ሲለይ ወራሾቹ ወይም ቤተሠቦቹ የተከራይነት መብቱ ይተላለፍልን ብለው በሚጠይቁበት ጊዜ ከሕግ አኳያ ዳኝነት የሚሠጥበት እንጂ በፍርድ ቤት የሚያልቅ ጉዳይ አይደለም ብሎ ጥያቄውን  አለመቀበል አግባብነት የሌለው ስለመሆኑ፣

የኢ.ፌ.ዲ.ሪፕብሊክ ህገ መንግስት አንቀጽ 37 የፍ/ህ/ቁ. 826/2/ እህ 2928

የሰ/መ/ቁ. 97948

 

ታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ/ም

 

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡-ወ/ሪት ሄለን ተክሌ - ቀረቡ ተጠሪ፡-ወ/ሮ ዘይድ አብርሃ - የቀረበ የለም

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የውርስ ንብረት ይጣራልኝ ጥያቄን የሚመለከት ነው፡፡ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች የሟች አባታቸው የአቶ ተክሌ ነጋሽ የውርስ ንብረት እንዲጣራላቸው ባቀረቡት አቤቱታ መነሻ ነው፡፡ የውርስ አጣሪው በፍርድ ቤቱ ተቋቁሞ የማጣራት ስራውን ከአጠናቀቀ በኋላ ሪፖርቱ ለፍርድ ቤቱ ቀርቦ ግራ ቀኙ አስተያየት ከሰጡበት በኋላ የውርስ አጣሪው ሪፖርት ተሻሽሎ በስር ፍርድ ቤት ፀድቋል፡፡በዚህ ውሳኔ የአሁኗ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፅንቶታል፡፡የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡የአመልካች የሠበር አቤቱታ መሰረታዊ  ይዘትም፡- አመልካች ሶፋውን ከእነ ሙሉ ጠረጴዛ የግል ንብረቴ ነው በማለት ጠይቀው እያለ በንብረቱ ላይ የግል ወይም የጋራ ነው ተብሎ ዳኝነት ሳይሰጥበት መታለፉ እና የቀበሌ ቤት የተከራይነት መብትን በተመለከተም አመልካች በወራሽነታቸው የሚገባቸው ስለመሆኑ በፍርድ ቤት መወሰን ሲገባው በቤቱ አካራይ የሚወሰን ነው ተብሎ መታለፉ ያላግባብ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡አቤቱታቸው ተመርምሮም በዚህ ችሎት ሊታይ የሚገባው ነው ተብሎ ተጠሪ እንዲቀርቡ ተደርጎ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም የችሎቱን ምላሽ የሚያስፈልጋቸው አበይት ነጥቦች፡-

 

1. ሶፋውን ከእነ ሙሉ ጠረጴዛ ዳኝነት ሳይሰጥ መታለፉ ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም?፣


2. በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ክልል ውስጥ በሚገኘውና በቁጥር 009 በሚታወቀው የቀበሌ ቤት የሟች አባት የነበራቸው የተከራይነት መብት ለአመልካች ሊተላለፍ የሚችል መሆን ያለመሆኑ በፍርድ ቤት ሊወሰን የሚችል ነው? ወይስ አይደለም? የሚሉ ሁነው ተገኝተዋል፡፡

 የ መጀ መሪያ ውን ጭ ብጥ በተመ ለከተ ፡-አመልካች የሟች አቶ ተክሌ ነጋሽ ወራሽ መሆናቸውን ጠቅሰውና የሟቹ ንብረት እንዲጣራ የውርስ አጣሪ በፍርድ ቤት እንዲሾም ጠይቀው ፍርድ ቤቱም የውርስ አጣሪው እንዲቋቋም አድርጎ አመልካች ሊጣራ የሚገባቸውን የውርስ ንብረቶች ህዳር 05 ቀን 2005 ዓ/ም በፃፉት ማመልከቻ ዘርዝረው ያቀረቡ መሆናቸውን፣በዚህ የንብረት ዝርዝርም ከሟቹ መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ንብረቶች ናቸው በሚል ወደ 48 የሚሆኑ የቤት መገልገለያ እቃዎችን መጥቀሳቸው የውርስ አጣሪው ከአቀረበው የውርስ ማጣራት ሪፖርት መጠቀሱን ከስር ፍርድ ቤት የውሳኔ ግልባጭ የተመለከተን ሲሆን በዚህ የንብረት  ዝርዝር ውስጥ አመልካች በሟቹ መኖሪያ ቤት ሶፋ ከእነ ሙሉ ጠረጴዛ አለ በማለት የጠቀሱት ነገር እንደሌለ ግልባጩ የሚያሳይ ሁኖ አግኝተናል፡፡ከዚህም መረዳት የሚቻለው አመልካች ይህንኑ ንብረት የውርስ ንብረት ነው በማለት በዚህ ረገድ ተገቢው መጣራት እንዲደረግላቸው የማጣራት ስራውን እንዲያከናውን በፍርድ ቤት ለተሾመው የውርስ አጣሪ ጥያቄ ያላቀረቡ ከመሆኑም በላይ የማጣራት ስራውን ሲከታተል ለነበረው ፍርድ ቤትም በተገቢው ጊዜ በዚህ ረገድ ያቀረቡት ጥያቄ ያለመኖሩን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡እንዲህ ከሆነ አመልካች ሶፋው ከእነ ሙሉ ጠረጴዛ ዳኝነት ተጠይቆበት የግል ወይም የጋራ ነው ተብሎ ውሳኔ ሳያርፍበት ቀርቷል በማለት የሚያቀርቡት ቅሬታ በስር ፍርድ ቤት የዳኝነት ጥያቄ ያልቀረበበት በመሆኑ እና የስር ፍርድ ቤት ደግሞ ባልተጠየቀ ጉዳይ ዳኝነት የሚሰጥበት አግባብ የሌለ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 182 (1) ድንጋጌ ስር የተመለከተ በመሆኑ ይህ ችሎት በዚህ ረገድ አመልካች የሚያቀርቡትን ቅሬታ የሚቀበለው ሁኖ አልተገኘም፡፡

 

 ሁ ለተ ኛ ውን ጭ ብጥ በተመ ለከተ ፡- አመልካች የሟች አቶ ተክሌ ነጋሽ ወራሽ መሆናቸውንና ሟቹ ከቀበሌ ተከራይተው ይኖሩበት የነበረ መኖሪያ ቤት እንዳላቸው ጠቅሰው የሟች አባታቸው የተከራይነት መብት እንዲተላለፍላቸው ዳኝነት እንዲያርፍበት ጥያቄ ማቅረባቸውን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡የበታች ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካችን የዳኝነት ጥያቄ ያለፉት ጉዳዩ በቤቱ ባለቤት የሚወሰን እንጂ በፍርድ ቤት የሚወሰን አይደለም በሚል ነው፡፡ይሁን እንጂ የቀበሌ ቤት የተከራይነት መብት ተከራይ ሲሞት ለወራሾቹ ወይም ለቤተሰቦቹ የሚተላለፍ መሆን ያለመሆኑ በፍ/ብ/ሕጉ ስለማይንቀሳቀስ ንብረት የኪራይ ውል የተመለከቱትን ድንጋጌዎች፣የቀበሌ ቤትን የኪራይ መብትና ግዴታ ለመግዛት በሚመለከተው አካል በወጡት ደንብና መመሪያዎች አንጻር ታይቶ በፍርድ ቤት ዳኝነት የሚሰጥበት እንጂ የቤቱ አስተዳዳሪ የሆነ ቀበሌ ለፈለገው ሰው የሚያከራየው ነው ተብሎ በፍርድ እንዳያልቅ የሚደረግ ጉዳይ አይደለም፡፡የቀበሌ ቤት የተከራይነት መብት የሚሰጥበት አግባብ በሕግ ስርዓት የሚዘረጋለትና የራሱ የሆነ አስራር ያለ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡መብቱ በሕጉ በተዘረጋው ስርዓትና አሰራር መሰረት መፈፀሙ ያለመፈፀሙ ላይ ክርክር ሲነሳ ደግሞ ነፃና ገለልተኛ በሆነ አካል፤በፍርድ ቤት ታይቶ አግባብነት ያላቸውን ማስረጃዎችን፣ህጎችንና አሰራሮችን መሰረት በማድረግ ዳኝነት የሚሰጥበት እንጂ ጉዳዩ የቤቱ አስተዳዳሪ ለሆነው አካል የሚተው አይደለም፡፡የቀበሌ ቤት የተከራይነት መብት ላይ ክርክር ሲነሳ ጉዳዩ ለቤቱ አስተዳዳሪ ለሆነው ለቀበሌ የሚተው ነው ከተባለ የቀበሌ ቤት የተከራይነት መብት ማግኘት ያለባቸው ግለሰቦችም መብታቸውን በአግባቡ ለማስከበር የሚችሉበት አግባብ ይኖራል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም፡፡በመሆኑም የበታች  ፍርድ


ቤቶች አንድ የቀበሌ ቤትን ተከራይቶ የነበረ ሰው ከዚህ አለም በሞት ሲለይ ወራሾቹ ወይም ቤተሰቦቹ የተከራይነት መብቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አግባብ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀጽ 37፣ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 826(2) እና 2928 ድንጋጌዎች እንዲሁም በዚህ ረገድ የወጣውን መመሪያና ተቀባይነት ያለውን አሰራር በመመልከት የራሳቸው በቂ መተዳደሪያ የሌላቸው ዜጎች ከመንግስት ሊደረግላቸው ከሚገባው ድጋፍ ጭምር በመመርመር ዳኝነት መስጠት  ሲገባቸው ጉዳዩ በፍርድ ቤት የሚያልቅ አይደለም በማለት የአመልካችን የቀበሌ ቤቱን የተከራይነት መብት የውርስ ጥያቄ ማለፋቸው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡በአጠቃላይ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሣ ኔ

 

1. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 75418 መጋቢት 10 ቀን  2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 135521 ታህሳስ 22 ቀን 2006 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2. በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ 06 ክልል ውስጥ በሚገኘው ቁጥሩ 009 በሆነው የቀበሌ ቤት ላይ አመልካች ተከራይ የነበሩትን ሟች አባታቸውን አቶ ተክሌ ነጋሽ መብት ለመውረስ ያቀረቡት ጥያቄ በፍርድ ቤት የሚወሰን አይደለም ተብሎ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ተሸሯል፡፡በቤቱ ላይ የቀረበው የተከራይነት መብት የውርስ ጥያቄ በፍርድ ቤት የሚያልቅ ነው በማለት በዚህ ነጥብ ላይ የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክርክሩን ቀጥሎ በፍርድ ሐተታው ላይ በተመለከተው አግባብ ጉዳዩን አጣርቶና ተገቢውን የክርክር አመራር ሁሉ በመከተል ተገቢውን ዳኝነት ሊሰጥበት ይገባል በማለት ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 341(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡ይጻፍ፡፡

3. ሶፋን ከእነ ሙሉ ጠረጴዛ በተመለከተ የበታች ፍርድ ቤቶች ማለፋቸውም ሆነ በሌሎች ንብረቶች ላይ የሰጡት የውሳኔ ክፍል ላይ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል፡፡

4.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውንወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

 

መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::