90121 Family law/ filliation/ DNA test/ Evidence law

የDNA ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ መሰጠቱ አንደኛው ወገን አሉኝ የሚላቸውን የመከላከያ ማስረጃዎች የማሰማት መብት የማይከለክል ስለመሆኑ፣

 

የDNA ምርመራ እንዲረግ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ስለሚሠጥበት አግባብ፣

 

የሰ//.90121 ቀን 28/01/2007 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ሱልጣን አባተማም መኮንን ገ/ህይወት ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመለስ

አመልካች፡- አቶ ………ጠበቃ ሀይልዬ ሰሀለ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ …………- ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ በመዝገብ የቀረበው ክርክር የአባትነት ይረጋገጥልኝ ጥያቄ የሚመለከት ነው፡፡ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ጉዳይ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአሁን ተጠሪ ከሳሽ በመሆን በአመልካች ላይ ያቀረቡትን ክስ እናታቸው ወ/ሮ ….. ከአመልካች ጋር ከጥር ወር 1973 ዓ/ም እሰከ ህዳር ወር 1974 ዓ/ም ድረስ ጋብቻ ሳይኖር እንደባልና ሚስት አብሮው በመቂ ከተማ ድግዳቦራ ወረዳ ቀበሌ 02 የቤት ቁጥር 190 ወስጥ ሲኖሩ መቆያታቸውን ገልጸው በዚህ ግንኙነታቸው መሰረት ተጠሪ በጋንዲ ሆስፒታል ሚያዝያ 02 ቀን 1974 ዓ/ም የተወለዱ መሆናቸውን በመግለጽ አመልካች የተጠሪ አባት ነው ተብሎ እንዲወሰን የሚጠይቅ ነው የአሁን አመልካች በስር ፍርድ ቤት በሰጡት መልስ ልጅነት የሚረጋገጠው የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀፅ 154 እና 155 ላይ እንደተመለከተው የልደት ምስክር ወረቀት በማቅረብ መሆኑን፤ተጠሪ ያቀረቡትማስረጃ አለመኖሩ አመልካች መቂ  ከተማ  ኑረው እንደማያወቁ ተጠሪም አንድም ቀን እራሳቸውም ሆነ በሰው የአመልካች ልጅ መሆናቸው ጠይቀው እንደማያውቁ በመጥቀስ ክሱ ውድቅ ተደርጐ እንዲሰናበቱ አመልክተዋል፡፡

 

የስር ፍርድ ቤት የተጠሪ ሁለት ምስክሮች በማዳመጥ በሰጠው ውሳኔ በአሁን አመልካች እና የተጠሪ እናት እንደ ባልና ሚስት አብረው ይኖሩ ነበር በሚል ስላልተረጋገጠ የአመልካች ምስክር መስማት አያስፈልግም፡፡ የአመልካች እና የተጠሪ እናት ግንኙነት በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 143 በሚያዘው አግባብ ሳይረጋገጥ የደም ምርመራ (የDNA ምርመራ) ማድረግ ተገቢ ስላልሆነ ፍ/ቤቱ የተጠሪ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን በመግልጽ አመልካች በነጻ ይሰናበቱ በማለት ፍርድ ሰጥቷል፡፡ የአሁን አመልካች በዚህ  ውሳኔ  ቅር በመሰኘት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታውን ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙ በማከራከር በሰጠው ውሳኔ ተጠሪ በቃል ክርክር የድኤንኤ ምርመራ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ የስር ፍርድ ቤት ምርመራውን ለማዘዝ የልጅ አባት ነው የሚያሰብል ግምት መያዝ አለበት በማለት መደምደሙ ከሰ/መ/ቁ.63195 አኳያ ተገቢነት የለውም፡፡ የአሁን ተጠሪ በስር ፍ/ቤት በማስረጃነት


የጠቀሰውን የዲ.ኤን.ኤ ምርምራ ጥያቄ ሳይቀበለው አልፎ የሰጠው ውሳኔ  የህግ አግባብ ባለመሆኑ ምርመራ ተደርጎ በምርምራው ውጤት የመስለውን እንዲወሰን ውሳኔውን በማሻር በነጥብ መልሶታል፡፡

 

የከፍተኛውን ፍ/ቤት ውሳኔ በመቃወም አመልካች ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡትን ይግባኝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.337 መሰረት ተሰርዟል፡፡ አመልካች በስር ፍርድ ቤቶች ተፈጽሟል ያሉትን የህግ ስህተት እንዲታረም ግንቦት 13 ቀን 2005 ዓ/ም የተጻፈ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ የአመልካች አቤቱታ ዋና ፍሬ ነገሩ፡- የሰበር ውሳኔው ለዚህ ጉዳይ አግባብነት የለውም ፤ የስር ፍርድ ቤት የዲ.ኤን.ኤ ምርመራ ጥያቄ የተቀበለው ስርዓቱን ጠብቆ አይደለም ፤ ከአመልካች ስለመወለዱ አልተረጋገጠም በማለት ስር ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲሻር አመልክቷል፡፡ ተጠሪ በበኩላቸው በስጡት መልስ በአመልካች እና የተጠሪ እናት ግንኙነት መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ የዲኤንኤ ምርመራ በመጀመሪያ ቀጠሮ መጠየቃቸው፤ ምርመራውም ጉዳዩን ግልጽ የሚያደረግ መሆኑ በመጥቀስ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲጸና ጠይቋል፡፡ አመልካች የመልስ መልስ ያቀረቡ ሲሆን አቤቱታቸውን የሚያጠናክር ክርክር አቅርበዋል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ህዳር 05 ቀን 2006 ዓ/ም ግራ ቀኙ በችሎት በቃል አከራክሮ ውጤቱን መዝግበዋል፡፡

 

የክርክሩ አጭር ይዘትና አመጣጥ ከላይ የተመለከተው ነው፡፡ እኛም መዝገቡን በአጣሪ ችሎቱ ያስቀርባል ከተባለው ጭብጥ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አኳያ ጉዳዩን መርምረናል፡፡ እንደመረመርነውም የአሁን ተጠሪ በአመልካች እና እናቱ መካከል የነበረው ግንኙነት ለማስረዳት ምስክሮች በማቅረብ ያስማ መሆኑ ከመዝገቡ መገንዘብ ተችሏል፡፡ የስር ፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የዲኤንኤ ምርምራ ጥያቄ ውድቅ ያደረገው በአመልካች እና የተጠሪ እናት ነበረ የተባለው ግንኙነት በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 143 መሰረት ከተመለከቱት ግምት የሚያሰጡ ምልክት ሰጪ ነገሮች በአንዴ አልተረጋገጠም የሚል ነው፡፡ የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዲኤንኤ ምርምራ በተጠሪ በቃል ክርክር ወቅት የተጠየቀ በመሆኑ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.259(1) መሰረት እንዲሁም ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ.መ.ቁ. 63195 ከሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ አኳያ ዲኤንኤ ምርመራ ይደረግ ጥያቄ ተቀብሎታል፡፡ የአባትነት ይረጋገጥልኝ ጥያቄ በአንዱ በኩል አባት የማግኘት መብት ሲያረጋግጥ በሌላ በኩል ደግሞ አባት ያልሆኑ ግለሰቦች አባት ነህ ተብሎ እንዳይወሰን ለመከላከል የተበጀ ህጋዊ ስርዓት ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪ የዲኤንኤ ምርመራ ይደረግልኝ ጥያቄ በስር ፍርድ ቤት ማቅረቡ አልተካደም፡፡ የዲኤንኤ ምርመራ እንደ አንድ የማስረጃ ይዘት እንዲታይለት መጠየቁ እና ይህንን ጥያቄም ስርዓቱን ጠብቆ ማቅረቡ በስር መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትም የተካደ ጉዳይ አይደለም፡፡ የስር ፍርድ ቤት ጥያቄውን ውድቅ ለማድረግ መነሻ ያደረገው የደም ምርመራ ለማድረግ አመልካች የዲኤንኤ ምርምራ እንዲያደርጉ ለማስገደድ ተጠሪ እናትና አመልካች በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 143 መሰረት ግንኙነት የነበራቸው መሆኑ እና ተጠሪም በዚህ ግንኙነት የተወለደ መሆኑ በቅድሚያ መረጋገጥ አለበት በሚል ምክንያት ነው፡፡ ይሁንና ይህ የስር ፍርድ ቤት ድምዳሜ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የስር መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፍሬ ነገር ማጣራትና ማስረጃ ምዘና ስርዓት ተገቢ አይደለም ተብሎ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱ ከተሻረ በሰበር ችሎቱ የማስረጃ ምዘና ሂደቱ የሚታይበት ስርዓት አይኖርም፡፡

 

በአመልካች እና ተጠሪ እናት መካከል ግንኙነት ነበረ ወይስ አልነበረም የሚለው የፍሬ ነገር ክርክር የስር ፍርድ ቤቶች የየራሳቸው አቋም የወሰዱበት መሆኑ ከስር ፍርድ ቤት ውሳኔ መገንዝብ ይቻላል፡፡ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት መሰረታዊ የህግ ስህተት መኖር አለመኖሩን መርምሮ


ውሳኔ ከመስጠት ውጪ ፍሬ ነገርን በማጣራትና ማስረጃ ምዘና ረገድ የስር ፍርድ ቤቶች የደረሱበት ድምዳሜ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለመመርመር የሚያስችል ስልጣን የሌለው ስለመሆኑ ከኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 80(3)(ሀ) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 መሰረታዊ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ነው፡፡ የቤተሰብ ህጉ የአባትነት ይረጋገጥልኝ ጥያቄ የሚቀርብበት የጊዜ ገደብ በግልጽ አልተገደበም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አመልካች ከ30 ዓመት በኃላ የአባትነት ይረጋገጥልኝ ጥያቄ ማቅረቡ የጥያቄውን ህጋዊነት ከወዲሁ ውድቅ ለማድረግ የሚያስችል ምክንያት ሆኖ አልተገኘም፡፡ የሰበር ችሎቱ በመ/ቁ. 63195 የዲኤንኤ ምርመራ ወጪ ከመሸፈን ጋር በተያያዘ የሰጠው ትርጉም በስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደ አስገዳጅ ውሳኔ መጠቀሱ የክርክር ምክንያት ቢሆኑም በዚህ ጉዳይ በዋናነት መታየት ያለበት ይህ ሰበር ችሎት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የዲኤንኤ ምርመራ እንዳይደረግ የክልከላ ውጤት ያለው ውሳኔ ከመስጠቱ አንፃር ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሰበር ችሎቱ ከኤክሰፐርት ምርመራ ውጤትና የማሳረዳት ብቃቱ በተያያዘ የተሰጠ ትርጉም መኖሩ ግልጽ ቢሆንም በእጃችን ከተያዘው ጉዳይ ጋር በፍሬ ነገርና በጭብጥ ረገድ አንድና ተመሳሳይ የሆነ ምርምራ የሚከለክል ውሳኔ ያልተሰጠ ከመሆኑ አንፃር የስር ፍርድ ቤት ከላይ የተጠቀሰው መዝገብ በአስገዳጅ ውሳኔ መመዝቡ የውሳኔውን ህጋዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከተው ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አባትነት የሚረጋገጥባቸውን መንገዶች አስቀምጧል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቀሱት አባትነት በህግ ግምት የሚወሰድባቸው ሲሆኑ በጋብቻ ውስጥ የተወለዱ ልጆች እንዲሁም እንደባልና ሚስት ሆነው ከኖሩ ግለሰቦች የተወለደው ህፃን የሚመለከት መሆኑ ከቤተሰብ ህግ አንቀጽ 126 እና 130 ድንጋጌዎች መሰረታዊ ይዘትና መንፈስ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ወጪ አባትነት እውቅና በመስጠት ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ የአባትነት ይረጋገጥልኝ ጥያቄ ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች ማረጋገጥ በማይቻልበት ሁኔታ በፍርድ ቤት ክስ በማቅረብ እንደሚታይ ነው፡፡ በፍርድ ቤት አባትነት ለማረጋገጥ መነሻ ነጥቦች በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 143 የተዘረዘሩት ሲሆኑ በዚህ ረገድ የሚነሳው ክርክር ወይም ግምትና ምልክት ሰጪ ግምቶች ለማስተባበል የሚያስችሉ ምክንያቶች በዚህ ህግ አንቀጽ 144 በዝርዝር ተመልክቷል፡፡ በስር ፍርድ ቤት በተጠሪ የቀረበው የአባትነት ይረጋገጥልኝ ጥያቄ በአመልካች ተክዷል፡፡ ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት የዲኤንኤ ምርመራ እንዲታዘዝለት ጠይቋል፡፡ የስር የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጥያቄውን ውድቅ ቢያደረገውም ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት የጥያቄው ተገቢነት በመቀበል ምርመራው እንዲደረግ አዟል፡፡ የስር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የተጠሪ የዲኤንኤ ምርመራ ይታዘዝልኝ ጥያቄ በወቅቱ የቀረበ መሆኑ በማረጋገጥ የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንዲመለከተው መልሶ መላኩ በህግ አተረጓጎም ረገድ የፈጸመው ስህተት አለ ማለት አልተቻለም፡፡ የዲኤንኤ ምርመራ ውጤት በማንኛውም ሁኔታ እንዲደረግ የሚጠይቅ አለመሆኑ ችሎቱ የሚገነዘብ ቢሆንም የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስር የመጀመሪያ ደረጃ የፍሬ ነገር ድምዳሜና የማስረጃ ምዘና ባለመቀበል ምርምራ እንዲደረግ ማዘዙ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህግ የተደነገጉት የክርክር አመራር መሰረታዊ የስነ ስርዓት ድንጋጌዎች በአግባቡ አልተተረጎሙም ለማለት የሚያስችል ነገር አልቀረበም፡፡ በአመልካች እና ተጠሪ መካከል ያለው የአባትነት ይረጋገጥልኝ ጥያቄ የዲኤንኤ ምርመራ ተደረጎ የስር ፍርድ ቤት የመሰለውን  እንዲወሰን መታዘዙ ፤ የምርመራ ወጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መተንበይ በማይቻልበት ሁኔታ አመልካች ለመጉዳት ታስቦ የተደረገ ነው የሚያስብል የህግ ምክንያት የለውም፡፡ በመሆኑም የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአመልካች እና ተጠሪ መካከል ያለው አባትነት ይረጋገጥልኝ ጥያቄ ለመወሰን የዲኤንኤ ምርምራ አስፈላጊ መሆኑ በስር ፍርድ ቤት ከታመነበት የፍ/ቤቱ    ትእዛዝ


ተፈጻሚ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ አንጻር የስር ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የዲኤንኤ ምርመራ እንዲደረግ ማዘዛቸው በአግባቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል አመልካች በስር ፍርድ የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚችሉ ግልጸዋል፡፡ የስር ፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክሱን ውድቅ በማድረግ የመከላከያ ማስረጃ አለማዳመጡን ከስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተገንዝበናል፡፡ በመሆኑም አመልካች የዲኤንኤ /DNA/ ምርምራ ቢደረግም አለኝ የሚሉትን የመከላከያ ማስረጃ የማስማት መብታቸው የሚከለክል አይሆንም፡፡

 

በማጠቃለል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትን ውሳኔ በመሻር የዲኤንኤ ምርመራ እንዲደረግ ማዘዙ እና ውሳኔው በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት መጽናቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በዚህ መሰረትም ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳኔ

 

1. የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ. 57163 በ1/09/2004  ዓ/ም የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ. 126002 ጥር 30 ቀን 2005 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔና ፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ.87769 የሰጠው ውሳኔ ጸንቷል፡፡

2. የስር ፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የዲኤንኤ ምርመራ እንዲደረግ ማዘዙ በአግባብ ነው ብለናል፡፡

3. የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትም በትእዛዙ መሰረት ይፈጸም ብለናል፡፡ አመልካችም አለኝ የሚሉትን መከለከያ ማስረጃ የማሰማት መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡

4. በዚህ ጉዳይ ክርክሩ ለጊዜው እንዲቆም ግንቦት 28 ቀን 2006 ዓ/ም የተሰጠው ትእዛዝ ተነስቷል፡፡

5. በዚህ የሰበር ጉዳይ ክርክር የተነሳ የግራ ቀኙ ላወጡት ወጪና ኪሳራ የየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 


 

 

ሃ/ወ


 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::