99375 court jurisdiction/ jurisdiction of federal courts/ Addis Ababa city court

የአዲስ አበባ መስተዳደር አስፈፃሚ አካላት በሌላ ሰው ንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ካሳ ይክፈሉ ተብሎ የሚቀርብ ክስን በተመለከተ የማየት የስረ-ነገር ስልጣን ያላቸውየፌዴራል  ፍ/ቤቶች ስለመሆናቸው፡-   አዋጅ ቁጥር 361/1995፣ አዋጅ ቁጥር 408/1996

 

አዋጅ ቁጥር 25/88

 

የሰ//.99375 መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ/ም

ዳኞች፡- አልማዉ ወሌ

 

ዓሊ መሀመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አምባቸዉ አለሙ - ጠበቃ ፋሲል ቀረበ ተጠሪዎች፡-1ኛ የካ/ክ/ከ/ወ/01/አስተደር - የቀረበ የለም

2ኛ አቶ አሸናፊ መንገሻ

 

3ኛ አቶ ኦገስት አድነዉ

 

4ኛ አቶ አድማሱ አንጀሎ

 

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ  ር ድ

 

ጉዳዩ የተጀመረዉ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሾች ነበሩ፡፡ አመልካች ባቀረቡት ክስ በተለምዶ ፈረንሳይ ለጋሲዩን ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ በግምት 5 ሄክታር የተጎዳ መሬት በ 1985 ዓ/ም ተረክቤ የተለያዩ የዉጭ እና የሀገር ዉስጥ ዛፎች አልምቼ ዙሪያዉን በግንብና በሽቦ አጥር በመከለል፤ በርካታ የንብ፤ እንስሳት እርባታ፤ የእንግዳ መቀበያ እና መዝናኛ ቤቶች የሚገኙበትን የተሟላ መናፈሻ አቋቁሜ እያለሁ ተጠሪዎች እኔ በማላዉቀዉ ሁኔታ በመምጣት መናፈሻዉን በዉስጡ የነበሩትን ንብረቶችን አዉድመውብኛል

፤ግምቱንና የተቋረጠ ገቢ ብር 30,822,160.00(ሰላሳ ሚሊዩን ስምንት መቶ ሃያ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ስልሳ ብር) ከፍለዉኝ ድርጅቱን እንዲያስረክቡኝ ሲል ጠይቋል፡፡

 

1ኛ ተጠሪ በሰጠዉ መልስ አመልካች ይዞታዉን በህጋዊ መንገድ አልተረከበም፣  በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር

1195 እና በደንብ ቁ.14/96 መሰረት ያቀረበዉ ማስረጃ የለም፣ ወደመ የተባለዉም ንብረት ስለመኖሩም አልተረጋገጠም፣ አመልካች ይዞታን አለቅም የሚል ሲሆን ተጠሪ በህግ በተሰጠዉ ስልጣን መሰረት ያከናወነው ተግባር በመሆኑ ሊከስ መብት የለዉም፣ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለዉም በማለት ተከራክሯል፡፡ ፍርድ ቤቱም ከክርክሩና ከቀረበዉ ማስረጃ አመልካች ድርጅቱን በእጃቸዉ አድርገዉ የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩበት የነበረ መሆኑ አልተካደም፣ ንብረት መዉደም ያለመዉደሙ በፍሬ ነገር ክርክር ወቅት የሚታይ በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ የሰረ ነገር ስልጣን ያለዉ መሆኑን ስናይ በአዋጅ ቁ.361/1995 አንቀጽ 41(1)  ((ረ))


መሰረት የአዲስ አበባ መስተዳድር አስፈጻሚ አካላት በህግ በተሰጣቸዉ ስልጣንና ተግባር ጋር በተያያዙ ለሚነሱ ክርክሮች ስልጣን ያላቸዉ የአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች በመሆኑ የስረ ነገር ስልጣን የለኝም በማለት በፍ.ብሥ.ሥ.ህ.ቁ 244(2)((ሀ)) መሰረት ሳይቀበለዉ ቀርቷል፡፡የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚዉ ችሎትም የአመልካችን ቅሬታ ባለመቀበል ይግባኙን ሰርዞታል፡፡

 

የአመልካች አቤቱታም የቀረበዉ ይህንኑ ዉሳኔ ለማስቀየር ነዉ  ፡፡በመሆኑም አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ ቅሬታቸዉን ሲገልጹ፡- ለደረሰብኝ ጉዳት ካሳ ገንዘቡን ገምቼ አቅርቤ እያለሁ ፍርድ ቤቱ የአዲስ አበባ አስተዳደር አስፈጻሚ አካል ጋር የዳኝነት ጥያቄዬን በማገናኘት በአዋጅ ቁ. 361/95 41(1)( ሀ) መሰረት የስረ ነገር ስልጣን የለኝም ብለዋል ፤የአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች በዚህ አዋጅ አንቀጽ 41 ስር ከተዘረዘሩት ዉስጥ አስተዳደሩ በግለሰቦች ላይ ለሚያደርሰው የንብረት ጉዳት ላይ የሚቀርብየካሳይከፈለኝ ጥያቄ አይቶ ለመወሰን ስልጣን እንዳላቸዉ አይገልጽም፤ በመሆኑም የደረሰብኝንጉዳት ገልጨ ያቀረብኩትን ክስ ተጠቃሹን አዋጅ መሰረት በማድረግ ስልጣን የለኝም ማለቱ አግባብነት የለዉም፤ ጉዳዩን የማየት የስረ ነገር ስልጣን በአዋጅ 25/88 መሰረት የፈደራል ፍርድ ቤቶች በመሆኑ የቀረበዉ የዳኝነት ጥያቄን የማየት ስልጣን የለኝም በማለት የተሰጠዉ ብይን መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

 

በዚህም መሰረት ችሎቱም የቀረበዉን ካሳ ክፍያ ጥያቄ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማየት ስልጣን የለኝም ብለዉ የመወሰናቸዉን አግባብነት በጭብጥነት በመያዝ 1ኛ ተጠሪ እና አመልካችን በጽሁፍ መልስና የመልስ መልስ በማቀባበል አከራክሯል፡፡ከ2ኛእስከ 4ኛ ተራ ያሉትን ተጠሪዎችን አስመልክቶ ጥሪ ቢደረግላቸዉም ባለመቅረባቸዉ በጽሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸዉ ታልፏል፡፡

 

ተጠሪ በሰበር በሰጠዉ መልስ የሚለዉ ጉዳዩ በቀጥታ ከተጠሪ ጋር ግንኙነት ያለዉና የክርክሩም መሰረት መሬት በመሆኑ ከአንድ ስረ ነገር የሚመነጩትን  ጥያቄ በአንድ ቦታ መቅረቡ እና ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ብይኑ የሚነቀፍበት ምክንያት የለም፡፡ አመልካች መሬቱን የያዙት በህጋዊ መንገድ ባለመሆኑ በፍ.ብ.ህ.ቁ.1178 መሰረት ካሳ ሊጠይቁ አይገባም፣ በህግ ባልተፈቀደላቸዉ ቦታ ላይ ያሰፈሩትን መጠየቅ መብት የላቸዉም፡፡ የተሰጣቸዉን ማስጠንቀቂያ ወደጎን በማለት ሲጠቀሙበት የነበረ በመሆኑ የወሰድነዉ እርምጃ  ሊነቀፍ አይገባም፤ ስለዚህ የተሰጠዉ ብይን ተገቢ ነዉ ይባልልን በማለት ተከራክሯል፡፡ አመልካች በበኩላቸዉ ይዞታዉን እንድለቅ ሳልጠየቅ ደብዳቤ ሳይደርሰኝ ለ16 አመታት ስገብርበት የያዝኩትን ድርጅትና ንብረት አዉድሞብኛል ፤ጉዳዩ የቦታ ማስለቀቅ ጉዳይም አይደለም፤ ስለዚህ በስር ፍርድ ቤት ጉዳዩ መታየት ያለበት በአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ነዉ መባሉ ሊታረም ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

 

እኛም ጉዳዩን አቤቱታ ከቀረበበት ዉሳኔ እና አግባብነት ካላቸዉ የህግ ድንጋጌ አንጻር መዝገቡን መርምረናል፡፡

 

ከዚህ አንፃር ስንመረምረው የአዲስ አበባ ከተማ ነክ ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን በአዋጅ ቁ.361/95 በአንቀጽ 41 የተዘረዘረ ሲሆን ከከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት የመቆጣጠር ስልጣንና ተግባር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችን አይቶ የመወሰን ስልጣን እንዳለው በአዋጁ አንቀጽ 41/1/ለ/ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አኳያ ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ ተጠሪዎች ከሕግ ውጪ  ተያዘ


የተባለውን ቦታ በሕግ በተሰጠው ስልጣን አግባብ መቆጣጠር፣ተገቢውን ክትትል ማድረግና አስፈላጊ ሁኖ ሲገኝም ተገቢውን እርምጃ መውሰድ የሚችሉ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ጉዳይ የቀረበውን ክርክር ይዘቱን እንዳየነዉ የአመልካች ጥያቄ የነበረዉ ተጠሪዎች ተረክቤ በይዞታዬ ስር የሚገኘዉን እና አልምቼ የምገለገለልበትን መናፈሻ እና በዉስጡ የሚገኙትን የተለያዩ ንብረቶች እኔ በሌለሁበት ከሕግ ውጪ አዉድመውብኛል፣ በመሆኑም በግምት ብር 30,822,160 ያለው ንብረት የወደመብኝ በመሆኑ ገቢዬ ተቋርጧል፣ ከውል ውጪ ኃላፊነትን በሚገዙ ድንጋጌዎች አግባብ ካሳ ይክፈሉኝ የሚል መሆኑን ከመዝገቡ የምንረዳዉ ነው፡፡ይሁንና ጉዳዩ የቀረበለት ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፤አዋጅ ቁ 361(41) ለ በመጥቀስ የአዲስ አበባ አሰተዳደር አስፈጻሚ አካላት በህግ በተሰጣቸዉ ስልጣንና ተግባር ስር የሚቀርቡትን ጉዳዮች የመዳኘት የስረ ነገር ስልጣን የለኝም በማለት በብይን መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ ስለዚህ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነዉ የአመልካች ዋና የዳኝነት ጥያቄ የነበረዉ በንብረታቸዉ ላይ ለደረሰዉ የጉዳት ካሳና የቀረ ጥቅም ይከፈለኝ የሚል ነው፡፡በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤቶች የአዲስ አበባ ከተማ የአስተዳደር አካል የክርክሩ ተሳታፊ በመሆኑ ብቻ በተጠቃሹ አዋጅም ሆነ የአዋጁ ማሻሻያ በሆነው በአዋጅ ቁጥር 408/1996 ድንጋጌዎች ስር በግልጽ እንዲህ አይነት የካሳ ጥያቄ ለመዳኘት ለአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ስልጣን መሰጠቱ ሳይደነገግ የቀረበለትን ጉዳይ ተጠቃሹን አዋጅ በመጥቀስ ስልጣን የለኝም ሲል በብይን መዝገቡን መዝጋታቸው ሊታረም የሚገባዉ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ባጠቃላይ የከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ጉዳዩ በአዋጅ 25/88 መሰረት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን መሆኑን አዉቆ በፍሬ ነገር ደረጃ መርምሮ አስፈላጊዉን ዉሳኔ መስጠት ሲገባዉ በብይን መዝጋቱና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚዉ ችሎትም  ሳይታረም መቅረቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነዉ ብለናል፡፡ በመሆኑም ተከታዩ ዉሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ዉሳ ኔ

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ.ቁ.108063 በቀን 08/05/2006 ዓ/ም  የተሰጠዉና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚዉ ችሎት በመ.ቁ. 97764 በቀን 26/6/2006 ዓ/.ም የጸናው ውሳኔ ተሽሯል፡፡

2. የፌዴራል ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማከራከር (ማየት) ስልጣን እንዳለዉ አዉቆ አግባብነት ካላቸዉ ማስረጃዎች ጋር በማገናዘብ ተገቢውን እንዲወስን ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 341(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል፡፡ይጻፍ፡፡

3.      የግራቀኙ የዚህን ችሎት የወጪ ኪሳራ ይቻቻሉ ብለናል:: መዝገቡ ዉሳኔ በማግኘቱ ተዘግቷል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡