105962 jurisdiction of court/ jurisdiction of federal courts

በክልል በተነሳ ግምት በሌለው የመንገድ ይከፈትልኝ ጥያቄ ላይ ከተከራካሪ ወገኖች መሃል አንደኛው በፌዴራል መንግስት የተመዘገበ ማህበር ከሆነ ጉዳዩ በፌዴራል የፍ/ቤቶች ስልጣን ስር፣በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የስረ ነገርሥልጣን ስር የሚወድቅ ሲሆን የክልሉ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በውክልና ስልጣኑ ጉዳዩን የሚመለከት ስለመሆኑ፣

 

አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 5(2) እና 5(6)፣ አንቀፅ 14

 

በኦሮሚያ ክልል ህገ መንግስት አንቀጽ 64(3) እንዲሁም በክልሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 141/2000 አንቀጽ 27(4)

 

የሰ/መ/ቁ 105962 ቀን የካቲት 19/2007 ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል

አመልካች፡- 1. ቢ.ኤም.ጂ ኃ.የተ.የግል ማህበር              ጠበቃ ሰለሞን እምሩ ቀረቡ፡፡ 2. ዜድ ኤ.ዲ.ኤስ ኃ.የተ.የግል ማህበር

ተጠሪ፡- ፕሮፌሰር ባደግ በቀለ - ወኪል ተካልኝ በቀለ ቀረቡ፡ መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ርድ

 

ጉዳዩ ከመንገድ ይከፈትልን ጥያቄ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል የተነሳን ክርክር የሚመለከት ሲሆን ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ የቀረበው በአመልካቾችና በተጠሪ መካከል የተነሳውን ክርክር ለመዳኘት የስረ ነገር ስልጣን ያለውን ፍርድ ቤትን ለመለየት እና ስልጣን ሳይኖር ዳኝነት ተሰጥቶ ሲገኝ ውሳኔው ሊኖረው ስለሚኖረው ዋጋ ለመወሰን ይቻል ዘንድ ነው፡፡

 

ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካቾች ባሁኑ ተጠሪ ላይ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ አዋስ ወረዳ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው፡፡ የአመልካቾች ክስ ይዘትም፡- ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰበታ ከተማ ወስጥ አንደኛው  አመልካች 7939 ካ/ሜትር፣ ሁለተኛው አመልካች ደግሞ 8589 ካሬ ሜትር ቦታ ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዲስትሪ ልማት በኢንቨስትመንት መወሰዳቸውን፣ በዚህ ቦታ ላይ ለመውጫና መግቢያ የሚጠቀሙበትን መንገድ የአሁኑ ተጠሪ በመዝጋት መንገዱ እንዲከፈትላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ሲሆን የአሁኑ ተጠሪም ለክሱ በሰጡት መልስ በሕግ አግባብ ለኢንቨስትመንት ቦታውን መውሰዳቸውንና የዘጉት መንገድ ያለመኖሩን ጠቅሰው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡ በዚህ መልክ ጉዳዩ የቀረበለት የወረዳው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመስማትና ተገቢ ነው ባለው መንገድ ሁሉ ከአጣራ በኋላ ተጠሪ አመልካቾች በኢንቨስትመንት በወሰዱት ቦታ ላይ ያለውን መውጫና መግቢያ መንገድ መዝጋታቸው ተረጋግጧል በሚል ድምዳሜ ተጠሪ ለመኪና ተቆፍሮ በተሰራው መንገድ ላይ የሰሩትን አጥር አንስተው መንገዱን እንዲከፍቱ በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ ጉዳዩን


ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ተጠሪ አቅርበው ግን ችሎቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ጉዳዩ መንገድ ይከፈትልኝ የሚል በመሆኑ ይህንን አይነት ክርክር በመጀመሪያ ደረጃ አይቶ የመወሰን የስረ ነገር ስልጣን ያለው የወረዳው ፍርድ ቤት ሳይሆን የቀበሌ  ማህበራዊ ፍርድ ቤት ስለመሆኑ በክልሉ የቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 128/1999 ተደንግጓል በሚል ምክንያት የበታች ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ሽሮታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- አመልካቾች በፌዴራል መንግስት የተመዘገቡ የንግድ ድርጅቶች በመሆናቸው ክርክሩ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር የሚወድቅ ነው፣ ጉዳዩ በመጀመሪያ ደረጃ ለክልሉ የቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት አግባብ የሌለ ከመሆኑም በላይ ጉዳዩ ወረዳ ፍርድ ቤት መጀመሩ ስህተት ነው ቢባል እንኳን በይግባኝ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ታይቶ የጸና በመሆኑ ውሳኔው ሙሉ በሙሉ ዋጋ የለውም ተብሎ ውድቅ ሊሆን የሚችልበት የህግ አግባብ የለም በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

 

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካቾች በፌዴራል መንግስት የተመዘገቡ የንግድ ድርጅቶች መሆናቸውን፣ ተጠሪም ከክልሉ መንግስት ለኢንቨስትመንት በወሰዱት ቦታ ላይ በሕግ አግባብ ስራቸውን ከማከናወናቸው ውጪ የዘጉት መንገድ የሌለ መሆኑን ጠቅሰው የሚከራከሩ መሆኑን፣ ክርክሩ የመንገድ ይከፈትልን የዳኝነት ጥያቄን የሚመለከት ቢሆንም ከተከራካሪ ወገኖች መካከል በፌዴራል መንግስት የተመዘገቡ የንግድ ድርጅቶች ያሉበት መሆኑንና በክልሉ የቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 128/1999 መሰረት የመንገድ ይከፈትልኝ ጥያቄን በመጀመሪያ ደረጃ የስረ ነገር ስልጣን አይቶ ዳኝነት መስጠት የሚችሉት የቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች መሆናቸው በግልጽ የተደነገገ መሆኑን ነው፡፡

 

በመሰረቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በፌዴራል መንግስትና በክልሎች መዋቀሩን መሰረት በማድረግ የዳኝነቱም ስልጣን በፌዴራል መንግስቱ እና በክልል መንግስታት መካከል እንደተከፋፈለ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 50 እና 51 ስር ተመልክቷል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 80 "የፍ/ቤቶች ጣምራነትና ስልጣን" በሚል ርእስ በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ስልጣኑ በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፤ በክልል ጉዳዮች ላይ በክልሉ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት ስልጣኑ የተደነገገ ሲሆን የክልል ፍ/ቤቶች በህገ-መንግስቱ በተሰጣቸው የውክልና ስልጣን መሰረት ካልሆነ በቀር የፌዴራልን ጉዳይ ለማየት ፤ እንዲሁም የፌዴራል ፍ/ቤቶች የክልልን ጉዳይ ለማስተናገድ የሚያስችል ስልጣን የሌላቸውም መሆኑን በዚሁ ድንጋጌ ስር የተቀመጡት ንዑስ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያሳያል፡፡ አንድ ጉዳይ የፌዴራል ነው? ወይስ የክልል? የሚለውን ለመለየትም መሰረቱ የአዋጅ ቁጥር 25/88 ሲሆን፤ በዚሁ ህግ አንቀጽ 5 ስር በተመለከቱት ጉዳዩች ላይ ብቸኛ ስልጣን ያላቸው የፌዴራል ፍ/ቤቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የክልል ፍ/ቤቶች ስልጣን የሚኖራቸው በህገ-መንግስቱ በተሰጣቸው የውክልና


ስልጣን አግባብ ብቻ ነው፡፡ ይህ በግልጽ የሚያሳየው በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 5 መሰረት የፍርድ ቤቶች ስልጣን በጉዳዩ ባለቤትነት (subject matter) የስልጣን ክፍፍል እንደተጠበቀ ሆኖ ክሱም መቅረብ ያለበት ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን የስረ-ነገር ስልጣን ላለው ፍ/ቤት ስለመሆኑ ነው፡፡ የፌዴራል ፍ/ቤቶችን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8፣11፣14 እና 15 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ደግሞ አንዳንድ ጉዳዮች ሊያስነሱ በሚችሉት የክርክር ባህርይ ምክንያት ለተወሰኑ ፍ/ቤቶች እንዲቀርቡ በህግ ተለይተው ከተመለከቱት በቀር የስረ-ነገር ስልጣን የተደለደለው በክሱ በተመለከተው የገንዘብ ወይም የንብረት ግምት መነሻ እንደሆነ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 14 እና 15 ስር ከተመለከቱት ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ እና የክልል መንግስታት ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ ሕጎች ያስረዳሉ፡፡

 

አመልካቾች በፌዴራል መንግስት የተመዘገቡ የንግድ ማህበራት እንደመሆናቸው መጠን ጉዳዩ በፌዴራል ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 5(2) እና 5(6) መሰረት በፌዴራል ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ስር የሚወድቅ ነው፡፡ ጉዳዩ የፌዴራል ጉዳይ ሆኖ ክርክሩ የተነሳው በክልል ሲሆን የክርክሩ መሰረት ግምት በሌለው የመንገድ ይከፈትልኝ ጥያቄ ላይ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 14 መሰረት ጉዳዩን የማየት የመጀመሪያ ደረጃ የስረ ነገር ስልጣን ያለው የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን የሆነውን ጉዳይ በውክልና ስልጣን በመጀመሪያ ደረጃ የስረ ነገር ስልጣን የሚመለከተው የክልሉ የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለመሆኑ በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀጽ 80(4) ድንጋጌ ተመልክቷል፡፡ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ህገ መንግስት አንቀጽ 64(3) እንዲሁም በክልሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 141/2000 አንቀጽ 27(4) ድንጋጌዎችም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስልጣንን የክልሉ የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በውክልና የማየት ስልጣን እንደአለው ተመልክቷል፡፡

 

የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣኑ መሰረት በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የሚቀርበው ይግባኝ በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስለመሆኑ  የህገ መንግስቱ አንቀጽ 80(5) በግልጽ ያሳያል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግስትም በአንቀጽ 64(4) ይህንኑ አስቀምጧል፡፡ ይህ በአዋጅ ቁጥር 322/95 መሰረት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ባልተቋቋሙባቸው ክልሎችም የሚሰራ ስርዓት ነው፡፡

 

ይህንኑ በህግ የተዘረጋውን ስርዓት መሰረት አድርገን ጉዳዩን ስንመለከተው በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን ስር የሚወድቁ ጉዳዩች በቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤት ወይም በወረዳ ፍርድ ቤት የሚታይበት አግባብ የለም፡፡ በክልሉ መንግስት ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው የመንገድ ይከፈትልኝ  ክርክር ከሚያነሱ ወገኖች መካከል አንዱ በፌዴራል መንግስት የተመዘገበ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ይኼው አካል/ተቋም/ የክርክሩ ተካፋይ መሆኑ ብቻውን ጉዳዩን የፌዴራል ጉዳይ የሚያደረገውበመሆኑ በክልሉ የቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ጉዳዩ እንዲታይ የሚደረግበት የህግ አግባብ የለም፡፡ ጉዳዩ የፌዴራል መንግስት አወቃቀርን መሰረት አድርጎ ያልታየ መሆኑና በስርዓቱ መሰረት በክርክር ላይ ባለበት ሁኔታ የስረ ነገር ስልጣን ሳይኖር የተሰጠ ውሳኔ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ጉዳዩን በመጀመሪያ የስረ ነገር ስልጣን የሚመለከተው ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ አጽንቶታል በሚል ምክንያት ብቻም ውሳኔው ዋጋ እንዲኖረው ማድረግ ከይግባኝ መብት እንዲሁም የፍርድ ቤቶች የስልጣን ድልድል መነሻ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች አንጻር ሲታይም ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ አይደለም፡፡


ስለሆነም አመልካቾች በፌዴራል መንግስት የተመዘገቡ መሆኑ በተረጋገጠበት  ሁኔታ እና ክርክሩን ያስነሳው ጉዳይም ግምት የሌለው ሁኖ እያለ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ የመንገድ ይከፈትልኝ የሚል ነው በሚል ምክንያት ብቻ የቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ነው በማለት የደረሰበት ድምዳሜ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ቢሆንም ከላይ እንደተመለከተው ጉዳዩ የፌዴራል ጉዳይ ሁኖ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የስረ ነገር ስልጣን የሚወድቅ ሲሆን በህገ መንግስቱ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት በመጀመሪያ ደረጃ መታየት ያለበት በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሆኑ የወረዳው ፍርድ ቤትና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት መሻሩ በውጤት ደረጃ የሚነቀፍ ሁኖ አላገኘነውም፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1.  በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር

180394   ነሐሴ    12   ቀን   2006ዓ.ም    የተሰጠው    ውሳኔ   በውጤት    ደረጃ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

2. ጉዳዩን በቀጥታ አይቶ የመዳኘት ስልጣን ያለው የክልሉ የቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤት አይደለም ብለናል፡፡ ጉዳዩ የፌዴራል ጉዳይ በመሆኑ በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(4) ፣ አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 14፣ በኦሮሚያ ክልል ህገ መንግስት አንቀጽ 64(3) እንዲሁም በክልሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 141/2000 አንቀጽ 27(4) ድንጋጌ መሰረት በመጀመሪያ ደረጃ አይቶ የመወሰን ስልጣን ያለው የክልሉ የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው ብለናል፡፡

3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመልስ ብለናል::

 

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት