99717 jurisdiction of court/ jurisdiction of federal courts

የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህራን ትምህርት ለመማር ከአሰሪያቸው ተቋም ጋር የሚያደርጉትን ውል አፈፃጸምና ከውሉ ጋር ተያያዥ ባላቸው ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ክርክሮችን ለማየት ስልጣኑ ያላቸው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ስለመሆናቸው፣

 

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 79(1)

 

የፌድራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515//1919 አንቀፅ 75(5)(6)

የሰ/መ/ቁ. 99717

 

ጥር 20 ቀን 2007 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሀመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል

አመልካች ፡- አቶ ሲሳይ ይማነ - ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነገረ ፈጅ አቶ መስፍን ጌታቸው - ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል ፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁጥር 41105 ህዳር 30 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ  ቁጥር

143053 ጥር 13 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ትእዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የዳኝነት ስልጣን ጥያቄን የሚመለከት ነው፡፡ በስር ፍ/ቤት አመልካች ከሳሽ ተጠሪ  ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡

1. የክርክሩ መነሻ አመልካች ያቀረበው ክስ ነው፡፡ አመልካች  /ከሳሽ/  ከተከሳሽ ጋር የአካዳሚክ ሰራተኛ የነበረ መሆኑን ገልፆ፣ ግንቦት 9 ቀን 2001 ዓ/ም ከሳሽና ተከሳሽ ባደረጉት ስምምነት መሰረት በሌክቸረርነት አገልግያለሁ፣ ከሳሽ የማስተርስ ድግሪ ትምህርት በመማር ውጭ ሃገር ሄጄ ተመልሻለሁ፡፡ ከዚያም የዶክትሬት  ድግሪ ትምህርት ለመከታተል ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ተከሳሽ ከነሀሴ 19 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ለሶስት ዓመታት የሚታሰብ ፍቃድ ሰጥቶኝ የዶክተሬት ትምህርቴን በመከታተል ላይ እገኛለሁ ትምህርት ፍቃድ የተሰጠኝ ሀምሌ 4 ቀን 2001 ዓ/ም ባወጣውና ህዳር 7 ቀን 2002 ዓ/ም በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ነው፡፡ በመመሪያው መሰረት በሁለት የትምህርት ፈቃዶች መካከል አንድ አመት አገልግሎት የመስጠት ግዴታ  እንዳለ የተገለጸ ሲሆን ይህን የማያሟላ የአካዳሚክ ተቀጣሪ ፈቃዱን ማግኘት የሚችለው ፈቃድ በሚሆንበት ጊዜ ጥቅማ ጥቅሞቹን መብቶቹን /ደመወዙን ጨምሮ/ ላለመጠየቅ ሲስማማ


ነው ሆኖም የአካዳሚክ ሰራተኛው የተሰጠው ፈቃድ ከመጠናቀቁ በፊት  ወደ ዩኒቨርስቲው ተመልሶ ያላሟላውን የአንድ አመት አገልግሎት ከሰጡ፣ ቀደም ሲል በስምምነት መነሻነት የተዋችው ጥቅማ ጥቅም የማግኘት መብት እንደሚኖረው በመመሪያው ተደንግጓል ፡፡ በዚህ መሰረት ከሳሽ የተሰጠኝ የትምህርት ፈቃድ ከማለቁ በፊት ተመልሼ የአንድ አመት አገልግሎት የሰጠሁት ግዴታን የተወጣሁ በመሆኑ ተከሳሽ በስምምነታችን መሰረት ሊከፍለኝ የሚገባውን ደመወዝ ጥቅማ ጥቅም የአየር መጓጓዧ ወጭ እንዲከፍል ብጠይቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ እነዚህን ክፍያዎች ከህጋዊው ወለድ ጋር እንዲከፍል ይወሰንልኝ በማለት ክስ አቅርቧል ፡፡

2. ተጠሪ በተከሳሽነት ቀርቦ ተከሳሽ በአዋጅ ቁጥር 515/99 እና በደንቡ ቁጥር 77/94 የሚተዳደር በመሆኑ ፍ/ቤት ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን የሚያስችለው የስረ ነገር ስልጣን የለውም የሚል የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቅርቧል ከሳሽ ተከሳሽ ባቀረበበት ጥያቄ መሰረት ከነሀሴ 19 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ የሶስት ዓመት ተሰጥቶ የስራ ውል ተቋርጧል፡፡ ከሳሽ ከተከሳሽ ጋር ያለው ስምምነት ከጥር 6 ቀን 2003 ዓ/ም ጀምሮ የተቋረጠ በመሆኑ ክስ ለማቅረብ የሚያስችለው መብትና ጥቅም የለውም  የሚልና ሌሎች መከራከሪያዎቹን አቅርቧል፡፡የስር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙ ክርክር የመነጨው በቅጥር ላይ ከተመሰረተ ግንኙነት ነው የስራ ውሉም የተደረገው የመንግስት ተቋም ከሆነው አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጋር ነው፡፡ ተከሳሽ መንግስት በሚበጅትለት የሚተዳደር ነው፡፡ ከሳሽና ተከሳሽ ያደረጉት ውል፣ የውሉን አፈጻጸም አስመልክቶ ያለመግባባት ቢፈጠር በፍርድ ቤት ቀርቦ እንደሚታይ የሚገልጽ ቢሆንም ይህ አገላለጽ የግራ ቀኙ ክርክር የሚዳኘው በአስተዳደር ፍ/ቤት መሆኑን የሚያሳይ እንጂ ጉዳዩ ለመደበኛ ፍ/ቤት የሚቀርብ መሆኑን የሚያመላክት አይደለም ስለዚህ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለኝም በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡አመልካች ይግባኙን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአመልካች ይግባኝ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 337 መሰረት ሰርዞታል፡፡

3. አመልካች አከራካሪው ጭብጥ የአካዳሚው ሰራተኛ የትምህርት ፈቃድ የሚያገኝበትንና የትምህርት እቅድ በተሰጠው ጊዜ መፈጸም የሚገባውን የአንድ ዓመት አገልግሎት የፈጸመ በሆነ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲው ሊከፈለው ስለሚገባው ደመወዝ ፤ ጥቅማ ጥቅምና የትራንስፖርት ወጭ የሚመለከት በሌላ አነጋገር የውል አፈጻጸም የሚመለከት ሆኖ እያለ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለኝም በማለት ብይን መስጠቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ሚያዝያ 7 ቀን 2006 ዓ/ም የተጻፈ የሰበር አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ተጠሪ በበኩሉ ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓ/ም በተጻፈ መልስ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለው የስቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍ/ቤት እንደሆነ የሚገልጽ መከራከሪያ አቅርቧል፡፡አመልካች ሰኔ 2 ቀን 2006 ዓ/ም የተጻፈ የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

4. ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት የጽሁፍ ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የበታች ፍ/ቤት ጉዳዩን በዳኝነት አይቶ ለመወሰን ስልጣን የለንም በማለት የሰጡት ብይን የህግ መሰረት አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል ፡፡

5. ከላይ የተያዙት ጭብጥን ለመወሰን፣ በመጀመሪያ አመልካች ተጠሪ የሚያከራክራቸው መሰረታዊ ጉዳይ ባህሪና ይዘት የግራ ቀኙ ክርክር የሚፈታበትን መንገድ መመርመር አስፈላጊ  ነው፡፡  ጉዳዩን  እንደመረመርነው  አመልካች  ለስር  ፍ/ቤት  ክስ ያቀረበው


ከተጠሪው ጋር በተዋዋልነው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት የተሰጠኝ የትምህርት ፈቃድ ከማለቁ በፊት፣ ተመልሼ መጥቼ አንድ አመት አገልግሎት የመስጠት ግዴታዬን ተወጥቻለሁ፡፡ተጠሪም በውሉ የገባውንና ደመወዝ፣ጥቅማ ጥቅምና የአየር ትራንስፖርት ወጭ የመሸፈን ግዴታውን እንዲወጣ በፍርድ ተጣርቶ ይወሰንልኝ በማለት ነው፡፡ ይህም

/ሀ/በተጠሪ ፈቃድና ይሁንታ የዶክትሬት ድግሪ ትምህርቱን ለመከታተል የተፈቀደለት አመልካች፣ ደመወዝ ጥቅማ ጥቅምና የአየር ትራንስፖርት ወጭ ክፍያ ሳይጠይቅ የትምህርት ፈቃድ እንዲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ በመቀበል ተጠሪ የሰጠው የትምህርት ፈቃድ መሰረታዊ ይዘትን ባህሪ እንደዚሁም ህጋዊ ውጤት ምንድን ነው

/ለ/ አመልካች ተጠሪ የሰጠው የትምህርት ፍቃድ ከመጠናቀቁ በፊት ተመልሶ በመምጣት በመመሪያው የተገለጸውን አገልግሎት የሰጠ በሆነ ጊዜ ቀደም ብሎ ላለመጠየቅ ተስማምቶ የተወውን ደመወዝ ጥቅማ ጥቅም  እና የአየር የትራንስፖርት ወጪ ክፍያ ለመጠየቅ የሚችልበት ሁኔታ አግባብነት ባለው መመሪያ አመልካችና ተጠሪ ባደረጉት የመግባቢያ ስምምነት ተደንግጓል ወይስ አልተደነገገም?

/ሐ/ ተጠሪ አመልካች የትምህርት ፈቃድ በነበረበት ጊዜ ደመወዝ ጥቅማ  ጥቅም እና አየር ትራንስፖርት ወጭ ክፍያ የመክፈል ከውል ወይም ከህግ የመነጨ ግዴታ አለበት ወይስ የለበትም? የሚሉትን ጭብጦች መርምሮና በማስረጃ አጣርቶ መወሰን የሚጠይቅ መሆኑን ከግራ ቀኙ ክርክር ለመረዳት ይቻላል፡፡

6. አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩባቸው በላይ የተገለጹበት መሰረታዊ የፍሬ ጉዳይ እና የህግ ጭብጦች አመልካችና ተጠሪ የትምህርት ፈቃድንና አመልካች በትምህርት ፈቃድ ባለበት ጊዜ ተጠሪ ለአመልካች የደመወዝ ጥቅማ ጥቅምና የአየር ትራንስፖርት ወጭ የሚከፍልባቸው ቅድመ ሁኔታዎችና ቅደመ ሁኔታዎቹ ባልተሟሉ ጊዜ ተጠሪ እነዚህን ክፍያዎች ከመክፈል ነፃ የሚሆንባቸውን ሁኔታዎች የሚመለከት ነው፡፡  ከዚህ በተጨማሪ አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩበት ጉዳይ አመልካች በትምህርት ፈቃድ ለቆየበት ደመወዝ ጥቅማ ጥቅምና የአየር ትራንስፖርት ወጭ ክፍያ ለማግኘት የሚያስችሉትን ቅድመ ሁኔታዎች አመልክቷል፡፡ ወይስ  አላመለከተም? አመልካች ቅድመ ሁኔታዎቹን አሟልቷል የሚባል ቢሆን ተጠሪ ለአመልካች መክፈል ያለበትም ምን ያህል ነው? የሚሉትን ጭብጦች የሚያካትት ነው፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩት በመካከላቸው ስላለው የሥራ ቅጥር ውል፣እድገት ወይም ዝውውር ሳይሆን ተጠሪ ለአመልካች የትምህርት ፈቃድ ሲሰጠው በተዋዋሉት የመግባቢያ ስምምነት ተዋዋይ ወገኖች ያላቸው መብትና ግዴታን ተዋዋይ ወገኖች በውል የገቡትን ግዴታ በአግባቡ የፈጸሙ መሆን አለመሆናቸውና ውል የሚተረጎምበትንና የሚፈጸምበትን አግባብ የሚመለከት ነው፡፡

7. ከዚህ አንጻር የሲቪል ሰርቪስ የአስተዳደር ፍ/ቤት አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩባቸውን ከላይ የተገለጹትን የህግና የፍሬ ጉዳዩን ጭብጦች በመመስረት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመስማት በመመርመርና በመመዘንና በማጣራት ውሳኔ የመስጠት የዳኝነት ስልጣን አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ መመርመር ይጠይቃል፡፡ የፌዴራል የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/1999 አንቀጽ 75 የሚታዩ ጉዳዮችን በዝርዝር ደንግጔል በዚህ ድንጋጌ መሰረት በአስተዳደር ፍ/ቤት ታይተው ውሳኔ የሚያገኙት ከህግ ውጪ ከስራ መታገድ ወይም አገልግሎት መቁረጥ ጉዳይ ከባድ የዲስፒሊን ቅጣት


የተወሰነባቸው ጉዳዮች ሰራተኛው ከህግ ውጭ ደመወዝ ወይም ሌሎች ክፍያዎች የተያዘበት ወይም የተቆረጠበት የሚመለከት ሲሆን በእንግሊዘኛው “an illegal attach ment or deduction of his salary or other payment” ሰራተኛው በስራው ምክንያት በደረሰበት ጉዳት ጋር በተያያዘ መብቱ መጓደልን የሚመለከቱ ጉዳዮች እና ሌሎቹ በአዋጅ አንቀጽ 75 ንዑስ ከአንቀጽ 5 እና ንዑስ አንቀጽ 6 የተመለከቱትን ጉዳዬች እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

8. ይህም የአዋጅ ቁጥር 515/99 አንቀጽ 75 ድንጋጌዎች ይዘት  ተጠሪ አካዳሚክ ሠራተኞች የትምህርት ፈቃድ የሚሰጥበት ሁኔታ፣በትምህርት ፈቃድ የወሰዱ የአካዳሚክ ሰራተኞች ጋር ባደረገው የመግቢያ ውልና ይህንን በሚመለከት በወጣው መመሪያ መሰረት ለአካዳሚክ ሰራተኞች ስለሚከፍለው ደመወዝ ጥቅማ ጥቅምና የትራንስፖርት ውጭ እና እነዚህን ክፍያዎች ለማግኘት የአካዳሚክ ሰራተኛው ማሟላት ስለሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች የተሟሉ መሆናቸውን በማጣራት  በአካዳሚክ ሰራተኛው የሚቀርበውን ክስ በቀጥታ ተቀብሎ ማስረጃ ሰምቶ መርምሮ፣ መዝኖና ፍሬ ጉዳይ አጣርቶና አግባብነት ያለውን የውል ስምምነትና የህግ ድንጋጌዎች በመተርጎም የአስተዳደር ፍ/ቤት ውሳኔ የሚሰጥ መሆንን የሚደነግግ አይደለም የክርክሩ ይዘት ባህሪ ክርክሩ የሚያቀርብበትና የሚወስንበት ስርዓት የአስተዳደር  ፍ/ቤት የአመልካችና የተጠሪን ጉዳዩ ተቀብለው ለማየትና  አከራክሮ  ለመወሰን የሚያስችለው አይደለም፡፡

9. ከዚህ አንጻር ሲታይ አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩበትን ጭብጥ በዳኝነት አይቶ የመወሰን ስልጣን ያላቸው በህግ መንግስቱ አንቀጽ 79 ንዑስ አንቀጽ 1 የዳኝነት ስልጣን የተሰጣቸው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ የበታች  ፍርድ ቤቶች በተጠሪና በአመልካች መካከል የሚደረገውን ክርክር መሰረታዊ ይዘትና ባህሪ ሳይመረምሩ፣ ተጠሪ የመንግስት ተቋምና በመንግስትን በጀት የሚተዳደር መሆኑን በመመልከት ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለንም በማለት የሰጡት ውሳኔ ከላይ የገለጽናቸው የህግ ድንጋጌዎች ያላገናዘበና መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል ፡፡

 

 ው ሳ ኔ

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትና የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጡት ውሳኔ ተሸሯል

2. የአመልካችንና የተጠሪን ክርክር በዳኝነት አይተው የመወሰን  ስልጣን  ያላቸው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ናቸው በማለት ወስነናል፡፡

3. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአመልካችና የተጠሪ ክርክርና ማስረጃ ሰምቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 341/1/ መሰረት መልስን ልከንለታል፡፡

4.  በዚህ ፍ/ቤት ግራ ቀኙን ያወጡትን ውጭና ኪሳራ በየራሳቸው ይቻሉ

መዝገቡ ወደ መዝገቡ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::