96309 banking/ ATM/ damage to account

አንድ የባንክ ደንበኛ ከባንኩ ጋር በገባው ውል መሰረት  የቁጠባ ሂሳቡን በኤ.ቲ.ኤ.ም ካርድ ሲያንቀሳቅስ ቆይቶ ነገር ግን በአጋጣሚ ካርዱ ቢጠፋ እና ይሄንኑ በፅሁፍ ለባንኩ ካሳወቀ ከዚያ በኋላ በሂሳቡ ላይ ለሚደርስ ጉድለት ባንኩ ኃላፊ ስለመሆኑ፡-

አንድ የባንክ ደንበኛ ከባንኩ ጋር በገባው ውል መሰረት  የቁጠባ ሂሳቡን በኤ.ቲ.ኤ.ም ካርድ ሲያንቀሳቅስ ቆይቶ ነገር ግን በአጋጣሚ ካርዱ ቢጠፋ እና ይሄንኑ በፅሁፍ ለባንኩ ካሳወቀ ከዚያ በኋላ በሂሳቡ ላይ ለሚደርስ ጉድለት ባንኩ ኃላፊ ስለመሆኑ፡-

ሰ/መ/ቁ 96309

 

መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም

 

 

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ ሡልጣን አባተማም መኮንን ገ/ህይወት ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

አመልካች፡- ዳሽን ባንክ አ/ማ - ነ/ፈጅ ሠለሞን አያኖ - ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ አበባየሁ ግርማ - ቀረቡ፡፡

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

የሰበር አቤቱታቸው የቀረበው የፌዴራሉ መ/ደ/ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ. 189176 የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት በይግባኝ አይቶ በኮ/መ/ቁ/132422 ህዳር 23 ቀን 2006 ዓ.ም ማፅናቱን በመቃወም ነው፡፡ ጉዳዩም ባጭሩ እንደሚከተለው ነው፡፡

 

በሥር ከሳሽ የነበሩት የአሁን ተጠሪ የሥር ተከሳሽ በነበረው የአሁኑ አመልካች ላይ ባቀረቡት ክስ በባንኩ ደንበኛ ሆነው በማጠራቀሚያ ሂሳብ ቁጥር 50100055 02016 ገንዘብ በባንኩ ተቀማጭ አድርገው የቁጠባ ሂሳቡን በኤ.ቲ.ኤም ካርድ ሲያንቀሳቅሱ ከቆዩ በኃላ  የኤቲ.ኤም ካርዱ ጥር 23 ቀን 2003 ዓ.ም የጠፋ በመሆኑ ለባንኩ ጥር 25/2003 ዓ.ም በፅሑፍ ያሳወቁ ቢሆንም ባንኩ ሂሳቡን መዝጋት እያለበት ባለመዝጋቱ ሪፖርት ከተደረገበት ከ25/5/2003 ዓ.ም እስከ 09/6/2003 ዓ.ም ድረስ ለማይታወቁ 3ኛ ወገኖች 40,300.00 (አርባ ሺህ ሶስት መቶ) ወጪ ሆኖ የተከፈለ በመሆኑ ይህን ገንዘብ ከነወለዱ ወጪና ኪሣራ ጋር ይከፈለኝ በማለት ጠይቀዋል፡፡

 

ተከሳሽ በሠጠው መልስ ካርዱ የጠፋ መሆኑን ማሳወቃቸውን ሳይካድ ነገር ግን የጠፋ መሆኑን ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን በባንኩ አሠራር መሠረት ሂሳቡ እንዲዘጋ የመጠየቅ ግዴታ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ግራ ቀኙ በገቡት ውል መሠረት የሚስጥር ቁጥሩን  ለሌላ  ወገን እንዳያሳውቁ ግዴታ ያለባቸው በመሆኑና የሚስጥር ቁጥሩ ካልታወቀ ደግሞ ገንዘቡ ወጭ ሊሆን የማይቻል በመሆኑ እንዲሁም የሂሳብ ይዘጋልኝ ጥያቄ ባልቀረበበት ሁኔታ ተከሳሽ ሂሳብ ሊዘጋ የማይችል በመሆኑ ላቀረበው ክስ ኃላፊነት እንደሌለበት በመግለፅ መልስ አቅርበዋል፡፡


ጉዳዩ በቅድሚያ የተመለከተው ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ከሳሽ እና ተከሳሽ በገቡት የካርድ ክፍያ አገልግሎት ውል አንቀፅ 2(2) መሠረት ካርዱ መጥፋቱን በጽሁፍ ከማሳወቁ በፊት ለተደረገ ማንኛውም የክፍያ ትዕዛዝ ባለካርዱ ኃላፊነት እንዳለበት የሚያመለክት በመሆኑና የዚህ የውል ክፍል ተቃርኖ ትርጉም ባለካርዱ በፅሑፍ ካሳወቀ በኃላ በተደረገ የክፍያ ትዕዛዝ ባንኩ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የሚያስገነዝብ በመሆኑ፤ የውሉ ድንጋጌዎች የመብት እና ግዴታ ዝርዝር ውስጥ ኃላፊነት ለመውሰድ ባለካርዱ ሂሳብ እንዲዘጋለት ማመልከት እንዳለበት ያልተካተተ በመሆኑ ከሳሽ ካርዱ መጥፋቱን ለባንኩ ባሳወቀበት እለት ባንኩ ባዘጋጀው ፎርም ላይ የሚስጥር ቁጥሩን መፃፉ የታመነ በመሆኑ የካርዱን የሚስጥር ቁጥር የተከሳሽ ሰራተኞች በቀላሉ የማያውቁበት ምክንያት ባለመኖሩ የተከሣሽ መከራከሪያ ተቀባይነት የለውም ስለሆነም የክሱን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲከፍል በማለት ተወስኗል፡፡

 

የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም ግራ ቀኙን ካከራከረ እና ተጨማሪ የሙያ ምስክሮችን ከሰማ በኃላ የሥር ፍ/ቤትን ውሳኔ አፅንቷል፡፡

 

አመልካች ይህን ውሳኔ በመቃወም ታህሳስ 23 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ ክርክር የሰበር ቅሬታቸውን አቅርበዋል ቅሬታቸው ተመርምሮ ክርክር ያስነሳውን ገንዘብ አመልካች እንዲከፍል መወሰኑን አግባብ ለማጣራት ሲባል ለሠበር እንዲቀርብ ተደርጎ ተጠሪ በቅሬታው ላይ መልስ ሰጥተዋል ተጠሪ ጥር 27/2006 ዓ.ም የሰጡት መልስ የስር ክርክራቸውን የሚያጠናክር እና የሰበር ቅሬታው ውድቅ ተደርጎ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲጸና የሚጠይቅ  ነው፡፡ አመልካችም የካቲት 21/2006 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

 

ከላይ በአጭሩ ለመግለፅ የሞከርነው የነገሩን አመጣጥ ሲሆን የሥር ፍ/ቤቶች ባሳለፉት ውሳኔ የተፈፀመው የህግ ስህተት ቢኖር መርምረናል፡፡

 

እንደመረመርነው ተጠሪ ካርዱ የጠፋ መሆኑን በፅሑፍ ለአመልካቾቹ ማሳወቁ፤ክርክር ያስነሳው ክፍያ የተፈፀመው ካርዱን መጥፋቱን ካሳወቀ በኃላ መሆኑ ግራቀኙ ባደረጉት ውል ካርዱ ከጠፋ በኃላ ለሚደረግ ክፍያ ባንኩ ኃላፊነት ይኖርበት ዘንድ ደንበኛው (ተጠሪ) ሂሳቡ በሙሉ እንዲዘጋለት የመጠየቅ ግዴታ እንደሌለበት፤ ተጠሪ ካርዱ መጥፋቱን በፅሑፍ ባሳወቀ ጊዜ በፎርሙ ላይ የሚስጢር ቁጥሩን መጻፉ ሁሉ ግራ ቀኙ የሚካካዱበት አይደለም፡፡

 

ከዚህም ሌላ ፍሬ ነገር ለማጣራትና ማስረጃ ለመመዘን ስልጣኑ የተሰጠው የስር ፍ/ቤት የሙያ ምስክሮችን በመስማት ተጠሪ በስህተት እንኳ የሚስጢር ቁጥሩን በፎርሙ ላይ ጽፎ ቢገኝ ይህ ቁጥር የተመዘገበበት ፎርም መቀመጥ እንደሌለበት ሙያዊ ምስክርነት እንዲሠጡ አረጋግጧል፡፡

 

አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው የሂሳብ ይዘጋልኝ ጥያቄ ባልቀረበበት ሁኔታ የተጠሪ ሂሳብ ሊዘጋ የማይችል መሆኑን እና ተጠሪ የሚስጥር ቁጥሩን በመግለፅ ግዴታውን መጣሱን በማንሳት ነው፡፡ነገር ግን ካርዱ መጥፋቱን ካሳወቀ በኋላ የሂሳብ ይዘጋልኝ ጥያቄ አልቀረበም በሚል ከኃላፊነት መዳን ስለመቻሉ በግራ ቀኙ ውል ካለመመልከቱም በላይ ተጠሪ በባንኩ ፎርም ላይ የሚስጥር ቁጥሩን ከሞላ በኋላ ሚስጥርነቱ ስለሚቀር ተገቢ ያልሆነ ተግባር እንዳይፈፀምበት በባንኩ በኩል ስለተደረገው ጥንቃቄ በአመልካች በኩል የቀረበ ክርክርም ሆነ ማስረጃ የለም፡፡

 

ከባንኩ የሚጠበቀው በተለመደው የባንክ ሥራ አካሄድ ጥንቃቄ ማድረጉን እና ጥፋት አለመሰራቱን ማሳየት ነው፡፡ይህን ሳያሳይ ደንበኛው የሂሳብ ይዘጋልኝ ጥያቄ አላቀረበም   በሚል


ከኃላፊነት የሚድንበት የህግም ሆነ የውል አግባብ ባለመኖሩ የሥር ፍ/ቤቶች ውሳኔ የሚነቀፍበት ምክንያት የለም ብለናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌ/መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ. 189176 የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ያሳለፈው ውሳኔ እንዲሁም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ. 132422 ህዳር 13/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 348(1) መሠረት ፀንቷል፡፡

2.  በዚህ ችሎት ስለተደረገው ክርክር ግራ ቀኙ ወጪያቸውን ይቻሉ

3. የተጀመረው አፈፃፀም እንዲታገድ በዚህ ፍ/ቤት ታህሳስ 28/2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል፡፡ይፃፍ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ት/ጌ