97683 unlawful enrichment/ government houses/ liability of government

የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ያልተወረሰ ቤትን በህገወጥ  መንገድ በመያዝ የተጠቀመበት ከሆነ የኪራይ ገንዘብና ያለአግባብ የበለፀገበትን ያህል ሊከፍል የሚገባ ስለመሆኑ፡-

 

ያለአግባብ በመንግስት ተይዞ ለቆየ ቤት የታጣ ጥቅም አይከፈልም ሊባል የማይችል ስለመሆኑ፡-

 

የፍ/ሕ/ቁ 2162

 

አዋጅ ቁጥር 193/92 አንቀፅ 7(3) አዋጅ ቁጥር 192/92 አንቀፅ 3

የሰ/መ/ቁ. 97683

 

መጋቢት 18 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሀመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኸሊት ይመሰል

አመልካች፡- አክበር አሊ ካምሩዲን ኩባንያ ተጠሪዎች ፡- 1) የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ

2) የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ የቀጠና 4 ጽ/ቤት

 

3) በመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ የአ/አ ቅ/ጽ ቤት

 

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካች ከሳሽ ተጠሪዎች ተከሳሽ ነበሩ፡፡ አመልካች ባቀረቡት ክስ 1ኛ ተጠሪ የቤት ቁ.868 እና 872 ሁከት በመፍጠር በመያዝ 2ኛ ተጠሪ በቤት ውስጥ የነበሩትን ልዩ ልዩ ዕቃዎች እና ሰነዶች በ3ኛ ተጠሪ መጋዘን የተቀመጠ ሲሆን 2ኛ ተጠሪ ዕቃውን እንዲመልስ ቢጠየቅ ለመመለስ ፍቃደኛ አልሆነም በተጨማሪም 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የአመልካችን ቤት ለተለያዩ ግለሰቦች እያከራዩ ብር 149,294,00 (አንድ መቶ አርባ ዘጠኝ ሺ ሁለት መቶ ዘጠና አራት ብር) ተጠቅመውበታል፡፡ አመልካች ቤቱን ስረከብ 5000 ብር ወጪ አድርጌያለሁ ፡፡1ኛ እና 2ኛ ተጠሪ ቤቱን አከራይተው አለአግባብ የበለጸጉበትን እና ቤቱን ለማሳደስ ያወጣሁትን ወጪ በድምሩ 154,294,00 (አንድ መቶ ሀምሳ አራት ሺ ሁለት መቶ ዘጠና አራት ብር) የስር 4ኛ፣5ኛ ፣6ኛ ተከሳሾች ጭምር የአሁን ተጠሪዎች የአመልካችን ንብረት ይመልሱ ፣ካልሆነ ግምቱን ብር 124,786.(አንድ መቶ ሀያ አራት ሺ ሰባት መቶ ሰማንያ ስድስት ብር) እንዲከፍሉኝ ባጠቃላይ ተጠሪዎች 279,080.00(ሁለት መቶ ሰባ ዘጠኝ ሺ ሰማንያ ብር) ከእነወለዱ እንዲከፍሉ፣ወጪና ኪሳራ እንዲተኩ ተብሎ ይወሰንልኝ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በማየት የስር 4ኛ፣5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ከክሱ በማሰናበት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉት ተጠሪዎች በሰጡት መልስ አመልካች ተጠሪዎች ያለአግባብ የበለጸጉበትን ኪራይ ገንዘብ ይከፈለኝ በማለት  መጠየቅ አይችሉም መጠየቅ ቢችሉም በመንግስት እጅ የቆየን ንብረት የሚጠየቅ ጉዳትም ሆነ ኪራይ የለም ተጠሪ ንብረት ተረክቧል ቢባል እንኳ ንብረቶቹ  ያልተመዘገቡና  እርጅና ያልተቀነሰ እንዲሆን ቁሳቁሶቹን በመጋዘን ለማስቀመጥ የፈጀው ጊዜ ከቀረበው ዋጋ በላይ ነው ሌላው አመልካች 5000 ብር ወጪ አደረግኩ የሚሉት ቤቱን ለማበላሸታችን ባለ ማስረዳታቸው ጥያቄው


ባጠቃላይ ውድቅ ሊሆን ይገቧል በማለት ተከራክረዋል ፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ግራቀኙን በማከራከር አመልካች ያቀረቡትን የታጣ ገቢና የኪራይ ጥቅም አስመልክቶ በአዋጅ ቁ.192/92 በአንቀጽ 3 ላይ በመንግስት እጅ በቆየበት ጊዜ ለታጣ ጥቅም(ገቢ) ማናቸውም የጉዳት ካሳ መጠየቅ እንደማይቻል የሚደነግግ በመሆኑ የተጠየቀው የቤት ኪራይ ይከፈለኝ በማለት አመልካች የጠየቁትን ዳኝነት ውድቅ በማድረግ የንብረትን ጥያቄ በተመለከተ ተጠሪ እርጅናቸው አልተቀነሰም በማለት ተከራክረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የአመልካችን የንብረት መጠየቅ መብት አያስቀረውም፡፡ሌላው አመልካች ቤቱን ቀለም ለማስቀባት አወጣሁት የሚሉት  5000 ብር ተጠሪዎ በቤቱ ላይ ጉዳት ያድርሱ ወይም በራሱ ጊዜ ቀለም የፈለገ ስለመሆኑ የሚያሳይ አይደለም በማለት አልፎታል፡፡

 

በአጠቃላይ ንብረትን በተመለከተ በተጠሪ ተዘርዝረው የቀረቡትን የንብረት በአይነቶች እነዲያስረክቡ ካልሆነ ግምቱን 124,786.000(አንድ መቶ ሀያ አራት ሺ ሰባት መቶ ሰማኒያ ስድስት ብር) ከነወለዱ ክስ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ይክፈል በማለት ወስኗል፡፡ በቀጣይነት ጉዳዩን ያየው ከፍተኛው ፍርድ ቤትም መዝገቡን በመመርመር ክርክር የተነሳበት ቤት በተመለከተ የተወረሰ አይደለም ከህግ ውጭ ተይዟል በሚል ምክንያት ሁከት ይወገድ ተብሎ አመልካች ቤታቸውን የተረከቡ መሆኑን የበፊት መዝገብ ያመላክታል ይህ ከሆነ ደግሞ የአዋጅ ቁጥር 193/92 አንቀጽ 7/3 ከአዋጅ ውጭ በመንግስት እጅ የቆየ ንብረት ለታጣ ገቢ ወይም ለደረሰ ጉዳት ካሳ ክፍያ መጠየቅ አይችልም ስለሚል በዚህ ረገድ የተሰጠው ውሳኔ የሚነቀፍ  አይደለም

፡፡ ንብረትን አስመልክቶ ግምቱን ወይም በአይነት ያስረክቡ የሚለው የውሳኔ ክፍልም ስህተት የለበትም በማለት ባጠቃላይ አጽንቶታል፡፡

 

የአመልካች አቤቱታም የቀረበው ይህንኑ ውሳኔ ለማስለወጥ ነው በመሆኑም አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ ቅሬታቸውን ሲገልጹ፡- የአመልካች ጥያቄ ተጠሪዎች ቤቱን ሁከት በመፍጠር ይዘው አከራይተው የተቀበሉትን ገንዘብ ሊከፍሉኝ ይገባል የሚል ሆኖ ሳለ ለአዋጅ ቁጥር 193/92 የተሳሳተ ትርጉም በመስጠት ሊከፈልህ አይገባም ተብሎ መወሰኑ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡ ተጠቃሹ አዋጅ ቁ.193/92 የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ለሚያስተናግደው ክርክር የወጣን ወጪን እንጂ በፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበት ውሳኔያገኘ አይነት ባለመሆኑ ውድቅ ሊሆን ይገባል በአጠቃላይ መንግስት (ተጠሪ) ማከራየታቸውን ባልካዱበት የሰበሰቡትን ገንዘብ  ሊመልሱ አይገባም መባሉና ብር 5000 ጥያቄ ውድቅ መደረጉም መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው በማለት አመልክቷል፡፡

 

በዚህም መሰረት ችሎቱም የአዋጅ ቁጥር 193/92 ተጠቅሶ ተጠሪ የአመልካችን ቤት ሁከት በመፍጠር ይዞ አከራይቶ እየተጠቀመበት ሊመልሱ አይገባም ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት በጭብጥነት በመያዝ የግራቀኙን በጹሁፍ በማከራከር መልስ እና የመልስ መልስ በማቀባበል አከራከሯል፡፡

 

ተጠሪዎች በሰበር መልሱ የሚሉት በአዋጅ 47/67 የተወረሰ ቤት አይደለም ሁከት ፈጥራችው የያዛችሁት ነው ተብሎ ተወስኖ የነበረ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት በእጁ ይዞ ሲያስተዳድር በነበረበት ጊዜ አመልካች ያጣውን ገቢ ወይም ጥቅም በአዋጁ ቁጥር 193/92 አንቀጽ 3 መሰረት ሊጠይቅ አይችልም ተብሎ መወሰኑ የሚነቀፍ አይደለም ሌላው በስር ፍርድ ቤት ሁከት ፈጥሮ መያዝና ወርሶ መያዝ አንድ ናቸው አላለም ስለዚህ በዚህ ረገድ የተነሳው ክርክር ተቀባይነት የለውም፡፡ ባጠቃላይ ተጠቃሹ አዋጅ በአግባቡ የተተረጎመ በመሆኑ የአመልካች


ጥያቄዬ አግባብነት የለውም፡፡ ሌላው አመልካች ለእድሳት አወጣሁ የሚሉት 5000 ብር(አምስት ሺ) ብር ውድቅ መደረጉ የሚነቀፍ ባለመሆኑ የስር ውሳኔ ሰህተት የለበትም ተብሎ ሊጸና የሚገባው ነው በማለት ተከራክረዋል አመልካች በበኩሉ የስር ክርክሩን በማጠናከር ተጠሪዎች ለ 11 አመታት ቤቶቹን አከራይተው የተጠቀሙበትን እና ያሳደስኩበትን ወጪ ነው የጠየቅኩት እንጂ የጉዳት ካሳ ከገንዘባቸው ክፈሉኝ የሚል ክስ የቀረበበት ሁኔታ የለም ስለዚህ ጉዳይ በማይመለከተው አዋጅ ቁ.193/92 ተጠቅሶ ገንዘብህን ሊከፈልህ አይገባም ተብሎ መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

በአጠቃላይ የክርክሩ አመጠጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሰውን ይመስላል፡፡ እኛም የግራቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካለው የህግ ድንጋጌ አንጻር መዝገቡን መርምረናል ፡፡ በመሆኑም ከተያዘው ጭብጥ አንጻር የክርክሩን አመጣጥ አንዳየነው የአመልካች ጥያቄ የነበረው ተጠሪዎች ሁከት ፈጥረው የያዙትን ቤት ለቀው ሁከት ይወገድ በመባሉ ለቀዋልና ያለአግባብ ይዘው በነበሩበት ወቅት ለግለሰቦች ቤቱን በማከራየት የሰበሰቡትን ገንዘብ ይመልሱልኝ በውስጡ የነበረውን ንብረት እና ያሳደስኩበትን ይተኩልኝ የሚል መሆኑን ከመዝገቡ መረዳት የሚቻል ነው፡፡

እንግዲህ በተያዘው ጉዳይ ያከራከረው ተጠሪ አዋጅቁጥር 193/92 ጠቅሶ በመንግስት የቆየን ንብረት ጥቅም ወይም ጉዳት መጠየቅ ስለማይቻል ልንጠየቅ አይገባም በማለቱ እና የስር ፍርድ ቤቶችም በዚህ ረገድ የቀረበውን የተጠሪን መከራከሪያ በመቀበል በተጠቃሹ አዋጅ መሰረት አመልካች መጠየቅ አይገባውም በማለት በመወሰናቸው እና የእድሳት ገንዘቡን ውድቅ በማድረጋቸው ነው፤ይህ ችሎትም አመልካች በተጠቀሰው አዋጅ መሰረት በኪራይ ተጠሪዎች የሰበሰቡትን ገንዘብ ሊመልሱ ይገባል? ወይስ በተጠቃሹ አዋጅ መሰረት መከፈል የለበትም? የሚለው ነጥብ ምላሽ ሊያገኝ የሚገባው ሆኖ አግኝቷል፡፡ በመሆኑምከስር  ክርክር እንደተገነዘብነው ተጠሪ ያልተወረሰ ቤት በመያዙ ምክንያት በፍርድ ሀይል ሁከት መፍጠሩ ተረጋግጦ ቤቱን መልቀቁ የተረጋገጠና በግራቀኙ ያልተካደ ነው በተጨማሪም  ተጠሪም ተጠቃሹን ቤት አላከራየሁም በማለት የተከራከረው ነገር የለም በስር ፍርድ ቤቶች የፍርድ ሀተታም ቢሆን ቤቱ አልተከራየም በሚል የተጠቀሰ ነገር የለም ፡፡ በመሆኑም መከራየቱ ያላከራከረ ፍሬ ነገር በመሆኑ በዚህ ረገድ ተጠሪም የዚህ ችሎት መከራከሪያው አላደረገም ፡፡ ይልቁንም የተጠየቀውን ገንዘብ ልንከፍል አንገደድም የሚል መሆኑን አጉልቶ የሚከራከረው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ከተጠቃሹ አዋጅ ቁ.193/92 ድንጋጌ በመንግስት እጅ በቆዬ ንብረት ለታጣ ገቢ ወይም ለደረሰ ማንኛውም ጉዳት ካሳ ክፍያ መጠየቅ አይቻልም የሚል ነው፡፡ እንግዲህ ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው ቤቱ በተጠሪ በመያዙ ብቻ ሊያገኙ የነበሩትን ጥቅም በማጣታቸው የደረሰባቸውን ካሳ ከምንም ተነስቶ ተጠሪ እንዲከፈላቸው ሳይሆን በህገወጥ መንገድ ቤቱን ይዞ በእውነቱ ሲያከራየው የነበረውን እና ቤታቸው የፈጠረላቸውን የራሳቸውን ገንዘብ እንጂ ቤቱ ተወርሶ ተይዞ በመቆየቱ በካሳ መልክ ከመንግስት የሚከፈላቸው ማካካሻ አይደለም። ስለዚህ ተጠሪ ያልተወረሰ ቤት በህገወጥ መንገድ በመያዝ የበለጸገበትንና አላከራየሁም በሚል ያላስተባበለውን የኪራይ ገንዘብ ለመክፈል አልገደድም ማለቱ እና ፍርድ ቤቶቹም ተጠሪዎች ያቀረቡትን መቀበላቸው የአዋጁን አላማ እና ሊያሳካ የፈለገውን ግብ ያገናዘበ አይደለም አዋጅ ቁጥር 193/92 ለዚህ ጉዳይ ተፈፃሚ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት የለም ፡፡ በመሆኑም ተጠሪዎች ቤቱን ይዘው ለሰበሰቡት ኪራይ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2162 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሰረት ኃላፊ ሊሆኑ ይገባል ብለናል ፡፡ ይህን ካልን በስር ፍርድቤት ተጠሪዎች በምን ያህል እንዳከራዩ፤ቤቱ  ለስንት  አመታት  እንደተከራዬ  ጭብጥ  ተይዞና  በማስረጃ  ተለይቶ ክርክር


ያልተደረገበት በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ያሉት ነጥቦች ተጣርተው ሊወሰኑ የሚገባቸው በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ስር ፍርድ ቤት መመለሱ ስነ ስርዓታዊ ሁኖ አግኝተናል ፡፡

ሌላው የአመልካች ቅሬታ ቤቱ የታደሰበትን 5000 ብር አስመልክቶ የስር ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ሊከፍል አይገባም ሲሉ የሰጡትን ውሳኔ ተገቢ አይደለም ብለው አመልካች ያቀረቡትን አቤቱታ በተመለከተ የስር ፍርድ ቤቶች ፍሬ ነገሩን አጣርተውና ማስረጃውን መዝነው ውድቅ ያደረጉት ስለሆነ ይህ ችሎት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ.ሕግ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ከተሰጠው ስልጣን አንፃር የሚታይ ባለመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበውን ቅሬታ አልተቀበልነውም፡፡

በአጠቃላይ የፌዴራል የመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 193/92 መሰረት በማድረግ በመንግስት እጅ ለቆዬ ንብረት ተጠሪዎች የሰበሰቡትን ኪራይ ሊከፍሉ አይገባም በማለት የደረሱበት ድምዳሜ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ብለናል ፡፡ በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥተዋል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ.ቁ 175802 በቀን 04/08/2004 ዓ/ም እና የከፍተኛ ፍርድ ቤት በ125972 በቀን 25/03/2006 ዓ.ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

-   አመልካች ያቀረቡት የ 5000 ብር የእድሣት ክፍያ እና ንብረትን አስመልክቶ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ፀንቷል፡፡

2. ተጠሪዎች ከአከራካሪው ቤት ላይ የሰበሰቡትን የኪራይ ገንዘብ የመመለስ ሀላፊነት አለባቸው ብለናል ፡፡ በመሆኑም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አከራካሪው ቤት በምን ያህል የኪራይ ገንዘብ ሲከራይ እንደነበር ፤ እና ከመቼ ጀምሮ ሲከራይ እንደነበር በጭብጥነት ይዞ የግራ ቀኙን ማስረጃዎችን በመስማትና እና አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነም ፍርድቤቱ በራሱ አነሳሽነት በሚያስቀርባቸው ማስረጃዎች አጣርቶ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ውሳኔ እነዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.343(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል ፡፡ ይፃፍ፡፡

3.  የግራቀኙ የወጪኪሳራቸውን ይቻቻሉ ብለናል፡፡  መዝገቡ ውሳኔ በማግኘቱ ተዘግቷል፡፡

 

 

 

 

ት/ጌ                               የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡