93772 extra-contractual liability/ contract law/ independent contractor/ waiver of liability

የአንድ ግንባታ ባለቤት ግንባታውን ለሚያከናውነው የስራ ተቋራጭ ግንባታው ሲከናወን ለሚደርሱ ከውል ውጪ ኃላፊነቶች ወይም በህጉ የተጣለበትን ፍትሐ ብሄራዊ ግዴታዎች ለስራ ተቋራጩ በማስተላለፍ የሚያደርገው ስምምነት በህግ ጥበቃ የሚደረግለት ስለመሆኑ፡-

 

የፍ/ሕ/ቁ.2027(1)፣2130፣2132(1)፣2131(1)፣2035(1)፣2141

የሰ/መ/ቁ 93772

 

የካቲት 30 ቀን 2007 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ

 

አልማው ወሌ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶ ሁሴን አመዴ - ጠበቃ ጌታቸው ቅጣው ቀረቡ ተጠሪዎች፡- 1.ኢትዩ ቴሌኮም - ነ/ፈጅ ዘለቀ ሰይፉ ቀረቡ

2 ድርባን ሚድሮክ ሲሚንቶ ኃ/የተ/የግ/ማ…ጠበቃ ጋዲሳ ጉታ-ቀረበ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የኮንስትራክሽን ስራ በኮንትራክተር ሲሰራ ደረሰ ለተባለ የቴሌኮሚኒኬሽን ኬብል መበጠስ ጉዳት የጉዳት ካሳ ክፍያን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ከሳሽነት፣ በአሁኑ አመልካች ተከሳሽነት እና ለአሁኑ 2ኛ ተጠሪ ጣልቃ ገብነት በምስራቅ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ እና ይዘትም ባጭሩ የሚከተለው ነው፡፡

 

1ኛ ተጠሪ በስር ተከሳሽ ላይ ባቀረበው ክስ ተከሳሹ የአመልካች ንብረት በሆነው የአለም አቀፍ ግንኙነት በተሸከመ የኦፕቲካል ፋይበር ኬብል ላይ በሕግ የተጣለበትን ግዴታ በመጣስ ህዳር 30 ቀን 2002 ዓ/ም የብር 123,710.7234፣ ታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ/ም ደግሞ የብር 374,754.2334 ጉዳት የ2ኛ ተጠሪን ፋብሪካ አጥር ግንባታ ሲያከናውን አድርሷል በሚል በድምሩ ብር 498,465.10(አራት መቶ ዘጠና ስምንት ሺህ አራት መቶ ስልሳ  አምስት ብር ከአስር ሳንቲም) ከተለያዩ ወጪዎች ጋር እንዲከፍል ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት ጠይቋል፡፡ የአሁኑ አመልካችም የሲሚንቶ ፋብሪካ አጥር ግንባታውን ያከናወኑት ከአሁኑ 2ኛ ተጠሪ ጋር ባደረጉት የግንባታ ውል መሆኑን፣ አሰሪ የሆነው 2ኛ ተጠሪ በሰጣቸው ንድፍ  መሰረት ስራውን በማከናውን ላይ እያሉ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ጉዳት እንደደረሰና ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው ሲሰሩ ለደረሰው ጉዳት በሕግም ኃላፊነት የሌለባቸው መሆኑን፣ ታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ/ም ደረሰ ለተባለው ጉዳትም የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ሠራተኛ የሆኑት ከ23 ሜትር በኋላ ቆፍሩ ብለው ምልክት አድርገውላቸው 25.10 ሜትር ርቀት ላይ ሲቆፍሩ ጉዳቱ የደረሰ በመሆኑ ኃላፊ ሊሆኑ የሚችሉበት ሕጋዊ ምክንያት የሌለ መሆኑን ጠቅሰው ክሱ ወድቅ እንዲሆን ከመከራከራቸው በተጨማሪ 2ኛ ተጠሪ ወደ ክርክሩ እንዲገባም ጥያቄ አቅርቧል፡፡


የአሁኑ ሁለተኛ ተጠሪ በጣልቃ ገብነት ወደ ክርክሩ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ በሰጠው መልስም ለክሱ ኃላፊነት የለብኝም የሚል ሁኖ ለዚሁ መልሱ መሰረት ያደረጋቸው ምክንያቶችም ከአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ጋር ያደረገው የግንባታ ውል ኃላፊነቱን ለ1ኛ ተጠሪ ማስተላለፉንና የግንባታ ፈቃድን ከሚመለከታቸው አካላት አግኝቶ ተገቢውን የፈፀመ መሆኑን የሚገልጹትን ነጥቦችን ነው፡፡

 

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም አመልካችንና የአሁኑን 2ኛ ተጠሪ ለክሱ ኃላፊ አድርጎ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ብር 498,465.10(አራት መቶ ዘጠና ስንምት ሺህ አራት መቶ ስልሳ አምስት ብር ከአስር ሳንቲም) ከመስከረም 10 ቀን 2004 ዓ/ም ጀምሮ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲሁም ለክርክሩ የወጡትን ወጪና ኪሳራ በአንድነትና በነጠላ ሊከፍሉ ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአሁኑ አመልካችየአሁኑ 2ኛ ተጠሪ ለአሁኑ 1ኛ ተጠሪ የሚከፈላቸውን የጉዳት ካሳ ገንዘብም ሆነ ወጭና ኪሳራ በሙሉ የአሁኑ አመልካች ለጣልቃ ገብ ሊሸፍኑ እንደሚገባ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው የአሁኑ ተጠሪዎች በመልስ ሰጪነት ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ አመልካችና 2ኛ ተጠሪ በህዳር 30 ቀን 2002 ዓ/ም ከአመልካች ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት በአንድነትና በነጠላ ኃላፊ መሆናቸው በአግባቡ ነው በማለት ሙሉ በሙሉ ያጸናው ሲሆን የታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ/ም ጉዳትን በተመለከተ ግን የአሁኑ አመልካች ሰራተኛ ቁፋሮው ከመንገዱ ከሃያ ሶስት ሜትር ርቀት በኋላ መቆፈር እንደሚችል ለአሁኑ አመልካች እስከቦታው ሂዶ በገለጸው መሰረት ቁፋሮው ከመንገዱ ከሃያ አምስት ሜትር ርቀት በላይ ሲከናወን የደረሰ መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል በሚል ምክንያት የ1ኛ ተጠሪ ሰራተኛ ለጉዳቱ መድረስ አስተዋፅኦ ነበረው ወደሚለው ድምዳሜ ደርሶ በዚህ ቀን ደረሰ ከተባለው የብር 374,754.3734 ጉዳት ውስጥ የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ለግማሹ ብር 187,377.19(አንድ መቶ ሰማንያ ሰባት ሺህ ሶስት መቶ ሰባ ሰባት ብር ከአስራ ዘጠኝ ሳንቲም) ኃላፊነት አለበት በማለት ወስኗል፡፡የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ በሁለቱም ቀናት ደረሰ ለተባለው ጉዳት አመልካች ኃላፊነት የለብኝም በማለት በመቃወም ውሳኔውን ለማስለወጥ ነው፡፡

 

የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አመልካች በታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ/ም ለደረሰው የንብረት ጉዳት ግማሽ ኃላፊነት አለበት በማለት የሰጠው ውሳኔ ለጉዳቱ መድረስ አስተዋጽኦ አደረገ የተባለው የ1ኛ ተጠሪ ሠራተኛው መሆኑን ተቀብሎ እያለ ሰራተኛው መስሪያ ቤቱን በመወከል በአመልካችና  በ1ኛ ተጠሪ መካከል ስራውን እንዲያከናውን ስምምነት መግለጽ የሚያስችል  የስልጣን ውክልና የለውም ብሎ አመልካች በከፊል ኃላፊነት አለበት በማለት የሰጠው ውሳኔ ተገቢነት የሌለው መሆኑን፣ እንዲሁም አመልካችና 2ኛ ተጠሪ አደረጉ የተባሉት  ስምምነት የተተረጎመበት አግባብም የግራ ቀኙን ውል፣እንዲሁም የኮንስትራክሽን መመሪያውን  ይዘትና ተፈፃሚነትን ባግባቡ ያላገናዘበ መሆኑን ዘርዝረው አመልካች ለጉዳቱ ኃላፊነትአለባቸው ተብሎ የወሰነው ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ችሎቱም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡እንደመረመረውም የዚህን ችሎት  ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ ሁኖ የተገኘው አመልካች በሁለቱም ቀናት በ1ኛ ተጠሪ ንብረት ላይ


ለደረሱት ጉዳቶች ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ በተሰጠው ውሳኔ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለ ለማለት ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለው ጭብጥ ሁኖ አግኝቶታል፡፡

 

በዚህም መሰረት የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ከሳሽ ሁኖ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የብር 498,465.10 የንብረት ጉዳት ካሳ ክስ ያቀረበው ጉዳቱ በተለያዩ ቀናት መድረሱንና በእያንዳንዱ ቀን የደረሰውን የጉዳት መጠን ለይቶ ክስ ያቀረበ ሲሆን የስር ተከሳሽ የነበሩት የአሁኑ አመልካች በእያንዳንዱ ቀን ደረሰ ለተባለው ጉዳት ኃላፊ የማይሆኑባቸውን ምክንያቶችን ጠቅሰው የተከራከሩ ሲሆን 2ኛ ተጠሪ ደግሞ ወደ ክርክሩ ጣልቃ እንዲገባ ተደርጎ ከአሁኑ አመልካች ጋር ባደረገው የግንባታ ውልም ሆነ ለጉዳዩ አግባብነት ካላው ሕግ አንጻር በ1ኛ ተጠሪ ንብረት ላይ ደረሰ ለተባለው ጉዳት ኃላፊነት የሌለበት መሆኑን ጠቅሶ ተከራክሮ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶ አመልካችንና 2ኛ ተጠሪን በሁለቱም ቀናት በአመልካች ንብረት ላይ ለደረሱት ጉዳቶች በአንድነትና በነጠላ ኃላፊ አድርጎ ለክሱ መሰረት የሆነውን ገንዘብ በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ወስኖባቸዋል፡፡በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኃላ የስር ፍርድ ቤት በሃላፊነት ላይ የሰጠውን የውሳኔ ክፍል አሻሽሎአል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዞም የጉዳት ካሳ መጠኑን ቀንሶ አመልካችና 2ኛ ተጠሪ ለአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ሊከፍሉ የሚገባው የጉዳት ካሳ መጠን ብር 311,087.91 (ሶስት መቶ አስራ አንድ ሺህ ሰማንያ ሰባት ብር ከዘጠና አንድ ሳንቲም) ነው ሲል ወስኗል፡፡ ይህ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ይዘት የሚያስገነዝበው አመልካች የሕዳር 30 ቀን 2002 ዓ/ም ጉዳትን በ2ኛ ተጠሪ በተሠጣቸው ንድፍ መሰረት ስራውን ሲሰሩ ጉዳት ደርሷል ብለው ያቀርቡት ክርክር በማስረጃ ያለመደገፉን፣ ታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ/ም ደረሰ ለተባለው ጉዳት ለአመልካች የስራ ትዕዛዝ አስተላለፉ የተባሉት ሰራተኛ ሕጋዊ ውክልና ሳይኖራቸው መሆኑ ተረጋግጦ የተወሰነ መሆኑን ነው፡፡ እንግዲህ ይህ የበታች ፍርድ ቤቶች ድምዳሜ የተያዘው በሕጉ የተሰጣቸውን ስልጣን መሰረት በማድረግ የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመስማትና ፍሬ ነገሩን በማጣራት ስለመሆኑ የውሳኔው ይዘት ያሳያል፡፡ በመሆኑም ይኼው የበታች ፍርድ ቤቶች የፍሬ ነገር ማጣራትና የማስረጃ ምዘና ድምዳሜ በዚህ ችሎት የሚለወጥበት አግባብ የሌለ ስለመሆኑ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው በመሆኑ ይህንኑ የበታች ፍርድ ቤቶችን ድምዳሜ በመያዝ በበታች ፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ በሕጉ አተረጓጎም ወይም አተገባበር ረገድ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት መኖር ያለመኖሩን ተመልክተናል፡፡

 

ከክርክሩ መገንዘብ የተቻለው አመልካች የግንባታው ባለቤት የሆነው የአሁኑ 2ኛ ተጠሪ ከሚመለከተው የመንግስት አካል በወሰደው የኢንቨስትመንት ቦታ ላይ አጥር ለማጠር ቁፋሮ ሲያካሂድ የ1ኛ ተጠሪ ንብረት የሆነው ፋይበር ኬብል መበጠሱን ነው፡፡ አመልካች በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት አጥብቆ የሚከራከረው ታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ/ም ደረሰ ለተባለ ጉዳት የ1ኛ ተጠሪ ኃላፊነት ነው፣ 2ኛ ተጠሪ ደግሞ የግንባታው ባለቤት ሁኖ በአዋጁ መሰረት ፈቃድ ባለማውጣቱ የደረሰ ጉዳት በመሆኑ አመልካች በውልም ሆነ በሕግ ለጉዳቱ ኃላፊ የሚሆኑበት አግባብ የለም በማለት ነው፡፡ እኛም እነዚህን በአመልካች የቀረቡትን ክርክሮች ሕጋዊ መሆን ያለመሆናቸውን ከቴሌኮሙኒኬሽንና የኤሌትሪክ ሐይል አውታሮችን ደህንነት ለመጠበቅ ከወጣው አዋጅ ቁጥር 464/1997 እና አግባብነት ካላቸው የፍትሐ ብሔር ህግ ድንጋጌዎች አንጻር መመርመሩ ተገቢ ሆኖ አግኝተናል፡፡ በመሰረቱ አዋጅ ቁጥር 464/1997 በአንቀጽ 3(3) ሥር የፌዴራልና የክልል ከተማ  አስተዳደር  አካላት  የግንባታ  ፈቃድ  ከመስጠታቸው  በፊት  የቴሌኮሙኒኬሽን ወይም


የኤሌትሪክ ሀይል አውታር ስለመኖሩ እና ፈቃድ ጠያቂው አካልም ግንባታ ከማካሄዱ በፊት በቴሌኮሙኒኬሽን ወይም በኤሌትሪክ ሀይል አውታር ላይ ጉዳት የማይደርስ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ ድንጋጌው በቴሌኮሙኒኬሽንና በአሌትሪክ ሀይል አውታሮች ላይ በግንባታ ወቅት ጉዳት እንዳይደርስ አስቀድሞ እንዲያረጋግጡ ግዴታ የጣለው በፌዴራልና በክልል አስተዳደር አካላት ብቻ ሳይሆን የግንባታ ፈቃድ ጠያቂ ላይ ጭምር ነው፡፡ 2ኛ ተጠሪውም በዚህ የህግ ድንጋጌ መሰረት በቴሌኮሙኒኬሽን አውታር ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የማድረግና በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት አስቀድሞ የማረጋገጥ ግዴታ በመወጣት ቦታውን ላይ ተገቢው ስራ እንዲሰራ ማድረግ ያለበት መሆኑን የድንጋጌው ይዘት ያስገነዝባል፡፡

 

በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት በቴሌኮሙኒኬሽንና በኤሌትሪክ ሀይል አውታሮች ላይ እያወቀም ሆነ በቸልተኝነት ጉዳት ያደረሰ ሰው የሚቀጣ ስለመሆኑም ተደንግጓል ፡፡ ወደ ፍትሐብሄር ህጉ ስንመለስ አንድ ሰው በራሱ በኩል ምንም የገባው ግዴታ ሳይኖር በራሱ ጥፋት(አስቦ ወይም በቸልተኝነት) በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ኃላፊ እንደሆነ  በቁጥር 2027(1) ከተደነገገው መገንዘብ ይቻላል፡፡ እንዲሁም በህግ በትክክል ተገልጾ የተመለከተውን ልዩ ድንጋጌ፣ ልዩ ደንብና ሥርዓት የጣሰ ሰው ደግሞ ጥፋተኛ ሊሆን እንደሚገባ በፍ/ህ/ቁ 2035(1) ተመልክቷል፡፡ በአዋጁም ሆነ በፍትሐብሔር ህጉ የተዘረጋው ስርዓት ከላይ የተጠቀሰው ሲሆን አመልካች በዚህ ችሎት በሕግ ረገድ የሚያቀርቡት ክርክር ሶሰት አበይት ምክንያቶችን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይኼውም ታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ/ም ደረሰ የተባለው ጉዳት በ1ኛ ተጠሪ ሰራተኛ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ስራው ሲከናወን ጉዳቱደርሷል፣ የሕዳር 30 ቀን 2002 ዓ/ም ጉዳትም 2ኛ ተጠሪ የግንባታ ፈቃድ ባላወጣበት ሁኔታ የተከናወነ በመሆኑ ጉዳቱ ሙሉ በሙሉ የሚመለከተው 2ኛውን ተጠሪ ነው፣2ኛ ተጠሪ ግዴታውን በውሉ ለአመልካች ማስተላለፍ አይችልም የሚሉ ናቸው፡፡

 

ይሁን እንጂ አመልካች ስለታህሳስ 30 ቀን 2002 ዓ/ም ጉዳት የሚያቀርቡት ክርክር የስር ፍርድ ቤቶች ከአረጋገጡት ፍሬ ነገር ውጪ የቀረበ በመሆኑ ተቀባይነት የሚያገኝበት አግባብ የለም፡፡ ምክንያቱም ለአመልካች የስራ ትዕዛዝ ሰጠ የተባለው የ1ኛ ተጠሪ ሰራተኛ በሕግ አግባብ ያከናወነው የሰራተኛ ግዴታ ስለመሆኑ ካለመረጋገጡም በላይ አመልካች ራሳቸው ሰራተኛው ሰጠ ካሉት ርቀት ውጪ ሂደው ቁፋሮውን ሊያከናውኑ የቻሉበት ሕጋዊ ምክንያትም በተገቢው ማስረጃ ያልተደገፈ ስለመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በግልጽ ያሳያልና፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ የቀረበው የአመልካች ክርክር የሕግ መሰረት የሌለው ሁኖ አግኝተናል፡፡ 1ኛ ተጠሪ በአሰሪነቱ ሰራተኛው በሰራው ጥፋት ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂነት የሚኖርበት ሰራተኛው ስራውን በሚሰራበት ጊዜ ጥፋት የሰራ የሆነ እንደሆነ ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2130 ድንጋጌ በግልጽ ያሳያል፡፡ አመልካች የ1ኛ ተጠሪ ሰራተኛ የሆኑት ግለሰብ የሥራ ተግባሩን ሲያከናውን ጥፋቱ የተፈፀመ መሆኑን በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2131/1/ እና በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2032/1/ መሰረት ሊያረጋገጥ የሚገባው መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2141 ድንጋጌ ይዘት የሚያስገነዝብ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ደግሞ ሰራተኛው የስራ ተግባሩን ሲያከናውን ያደረሰው ጥፋት የሌለ መሆኑን ማስረዳት እንደሚጠበቅበት የድንጋጌዎቹ ይዘት ያስገነዝባል፡፡ ከላይ እንደተገጸው የ1ኛ ተጠሪ ሰራተኛ የሆነው ግለሰብ ለአመልካች ሰጠ የተባለው የስራ መመሪያ ተገቢውን ስራ እንደደንቡ ለማከናወን ተብሎ ስራው ሲሰራ የደረሰ አለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም አመልካች የታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ/ም ጉዳት ኃላፊነቱ የ1ኛ ተጠሪ ነው በማለት ያቀረቡትን ክርክር አልተቀበልነውም፡፡


አመልካች ከ2ኛ ተጠሪ ጋር የግንባታ ውል ያላቸው መሆኑን ሳይክዱ በውሉ በግንባታው ጊዜ ለሚደርሰው ጉዳት ኃላፊነቱ የአመልካች ተብሎ ስምምነት መደረጉ በ2ኛው ተጠሪ ላይ አዋጅ ቁጥር 464/97 አንቀጽ 3(3) ድንጋጌ የጣለውን ግዴታ በግለሰቦች ስምምነት እንደመለወጥ የሚቆጥር ነው በማለት ተራክረዋል፡፡ ሆኖም አዋጅ ቁጥር 464/97 አንቀጽ 3(3) ተጠሪ የግንባታው ባለቤት በመሆኑ ምክንያት ግንባታውን ከማከናወኑ በፊት በቴሌኮሚኒኬሸን ወይም በኤሌትሪክ ሀይል አውታር ላይ ጉዳት የማይደርስ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት የሚያሳይ ቢሆንም ግንባታው የተከናወነው በሕግ አግባብ በተቋቋመ የአመልካችና የ2ኛ ተጠሪ ስምምነት መሰረት በአመልካች ስራ ተቋራጭነት ነው፡፡ አመልካች በስራ ተቋራጭነቱ ግንባታውን የሚያከናውን ከሆነ ደግሞ ጉዳቱ እንዳይደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ በአመልካችና በ2ኛ ተጠሪ ሐምሌ 09 ቀን 2001 ዓ/ም የተደረገው የግንባታ ውሉም በአንቀጽ 12.1.5. ሀ እና 12.1.6 ስር አመልካች ግንባታ ከማከናወኑ በፊት ከመብራት ኃይል ባለስልጣናትና ከ1ኛ ተጠሪ ፈቃድ መውጣት እንዳለበት ግራ ቀኙ መስማማታቸውን፣ በውሉ በግንባታው ጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግም አመልካች ከ2ኛ ተጠሪ ጋር የተስማማ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን 2ኛ ተጠሪ አመልካች ስራውን በሚያከናውንበት ጊዜ የሕዝብ መጠቀሚያ የሆነ ንብረት ኬብል እንደማይነካ፤ እንክብካቤ እንደሚደረግለት፣ ንብረቱ ያለባለቤቱ ፈቃድ በምንም ሁኔታ እንደማይነካ፣ በንብረቱ ላይ ምንም አይነት ጉዳት ቢደርስ ተጠያቂው ኮንትራክተሩ ስለመሆኑም ስምምነቱ ያስገነዝባል፡፡ እንዲሁም የቁፋሮ ስራ ሲካሄድ ኬብሉን ሊነካ ስለሚችል የ1ኛ ተጠሪን  ፈቃድ አመልካች ማግኘት እንደአለበት፣ ኬብሉ ላይ ጉዳት እንዳይደረስ ጥንቃቄ የማድረግ ኃላፊነትም የአመልካቹ መሆኑንና ማንኛውም ጉዳት ከደረሰ ተጠያቂ ኮንትራክሩ ስለመሆኑም የግራ ቀኙ የግንባታ ውል ስምምነት ያስረዳል፡፡

 

አመልካች ይህን የግራ ቀኙን የሥምምነት ይዘት መኖሩንና በነፃ ሐሳቡና ፈቃዱ መፈረሙን ሳይክድ ስምምነቱ ሕገ ወጥ ነው በሚል ያቀረበው ክርክር የአዋጅ ቁጥር 464/97 አንቀጽ 3(3) ድንጋጌን ሙሉ ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ የግንባታው ባለቤት በቴሌኮሚኒኬሸን ወይም በኤሌትሪክ ሀይል አውታር ላይ ጉዳት የማይደርስ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት የሚያሳይ ከመሆኑ ውጪ ይኼው ግዴታ ግንባታውን ለሚያከውነው የሥራ ተቋራጭ በስምምነት እንዳይተላለፍ ግልፅ ክልከላ የሚያስቀምጥ አይደለም፡፡ የድንጋጌው መሰረታዊ አላማም የሕዝብ መጠቀሚያ የሆነ ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደረስ ግንባታ ሲከናወን ሊወሰዱ የሚገባቸውን ቅድመ ጥንቃቄዎችንና ጥንቃቄውን ሊያደርጉ የሚገባቸው ወገኖች  የትኞቹ እንደሆነ የሚያመላክትና ጥንቃቄ ባለመደረጉ በንብረቱ ላይ ለሚደረስ ጉዳት ደግሞ ካሳ ሊከፍል የሚችልበት አግባብ መኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡ ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈፃሚነት ያለው አዋጅ ቁጥር 464/97 የግንባታው ባለቤት ግንባታውን ለሚያከናውነው የስራ ተቋራጭ ግንባታው ሲከናወን በሕጉ የተጣሉበትን ፍትሓ ብሔራዊ ግዴታዎች ለስራ ተቋራጩ የሚያስተላልፍ ስምምነት አድርጎ ቢገኝ ሕጉ ስምምነቱን ጥበቃ የማያደርግበት ምክንያት የሌለ መሆኑን ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1675፣ 1716 እና 1731 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ጋር አጣምረን በማየት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም 2ኛ ተጠሪ ግዴታውን ለአመልካች በስምምነት ማስተላለፉ ተቀባይነት ያለው ሲሆን ጉዳቱ በ2ኛ ተጠሪ ወይም ሰራተኛ ወይም ወኪሉ ስለመድረሱም እንዲሁም አመልካች ጉዳቱን ለመከላከል በማይችልበት ሁኔታ የደረሰ መሆኑም በማስረጃ ያልተረጋገጠ በመሆኑ አመልካችና ተጠሪ ሐምሌ 09 ቀን 2001 ዓ/ም በአደረጉት የግንባታ ውል የውሉ አካል በሆነው  በስራና ከተማ  ልማት  ሚኒስቴር  በወጣው  መመሪያ  (Standard  Conditions of


Contract for Construction of Civil Work Project) አንቀጽ 22 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መሰረት አመልካች ለጉዳቱ ኃላፊ የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡

 

ሲጠቃለልም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካችን ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ ያደረጓቸው በሕጉ አግባብ ነው ከሚባል በስተቀር ውሳኔያቸው የሚነቀፍበትን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ስላላገኘን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሣ ኔ

 


 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ት/ጌ


1.  በምስራቅ ጎጃም አሰተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር1914 መስከረም  10 ቀን 2004 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 32796 ሰኔ 03 ቀን 2005 ዓ/ም ተሻሽሎ የተሰጠው ውሳኔ    በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር

348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

2. የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካችን ለጉዳቱ ኃላፊ አድርገው በሰጡት ውሳኔ ላይ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል፡፡

3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና  ኪሳራ  የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::