95267 Extra-contractual liability (tort)/strict liability/ collusion of cars

ሁለት የሞተር ተሽከርካሪዎች ሲጋጩ እያንዳንዱ ተሽከርካሪ በየራሱ አንዱ ከአንዱ ላይ ጉዳት እንዳደረሱ  የሚቆጠረውና የእያንዳንዱ መኪና ባለሀብት ለአደጋው ኃላፊ የሚሆነው አደጋው የደረሠው ከአንደኛው መኪና አሽከርካሪ ስህተት መሆኑ በማስረጃ ያልተረጋገጠ እንደሆነ ብቻ ስለመሆኑ፡-   የፍ/ሕ/ቁ 2084

የሰ/መ/ቁ. 95267

ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም.


 

አመልካች፡-ናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማህበር ነገረ ፈጅ ይነበብ ደርሰህ-ቀረቡ ተጠሪዎች፡-

1.   አቶ ካሣሁን ወንድሙ- ቀረቡ

2.  አቶ  ግርማ ታጳኖ- ከክርክሩ ውጭ ተደርገዋል

3. ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማህበር- ነገረ ፈጅ ዮሴፍ ገብሬ ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥ~ል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ክርክሩ በተጀመረበት የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሳሽ የነበረው የአሁኑ አመልካች በዚህ መዝገብ አቤቱታውን ያቀረበው በተሽከርካሪዎች ግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰበትን የደንበኛውን ተሽከርካሪ አስጠግኖ ወደ ነበረበት ለመመለስ ያወጣውን ወጪ ለማስተካት ያቀረበውን ክስ ውድቅ በማድረግ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡

 

የጉዳዩን አመጣጥ በተመለከተ አመልካች ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ24/04/2004 ዓ.ም.አዘጋጅቶ ባቀረበው ክስ ንብረትነቱ የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ ሆኖ በአሁኑ 2ኛ ተጠሪ በመሽከርከር ላይ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ 3-02598 ደ/ሕ. የሆነ ተሽከርካሪ በሾፌሩ ጥፋት  ንብረትነቱ የአድቫንስድ ኢንጂነርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሆኖ በአመልካች የኢንሹራንስ ሽፋን የተሰጠውን የሰሌዳ ቁጥሩ 3-3277 የሆነ ተሽከርካሪ ገጭቶ ያደረሰበትን ጉዳት አስጠግኖ ወደ ነበረበት ለመመለስ አመልካች ያወጣውን ወጪ ብር 441,213.17 (አራት መቶ አርባ አንድ ሺህ ሁለት መቶ አስራ ሶስት ከአስራ ሰባት) 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ይወሰንለት ዘንድ የጠየቀ መሆኑን፣1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች እንዲሁም ለ1ኛ ተጠሪ ተሽከርካሪ የመድን ሽፋን የሰጠው እና በተጠሪው ጠያቂነት ወደ ክርክሩ የገባው 3ኛ ተጠሪ ከመቃወሚያ በተጨማሪ በኃላፊነት እና በመጠን ረገድ ተገቢ ነው ያሉትን ክርክር ማቅረባቸውን፣ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርከር ከሰማ በኃላ 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎችን ለክሱ ኃላፊ በማድረግ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ውሳኔ መስጠቱን፣በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ባቀረቡት ይግባኝ ሳቢያ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የተጠሪዎቹ ማስረጃ ሳይሰማ ውሳኔ መሰጠቱ እና የ3ኛ ተጠሪ ኃላፊነትም ተለይቶ አለመወሰኑ ተገቢ አለመሆኑን ገልጾ ውሳኔውን በመዝገብ ቁጥር 51395 በ30/11/2004 ዓ.ም. በመሻር ጉዳዩን በነጥብ የመለሰው መሆኑን፣ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በተመለሰለት መሰረት የተጠሪዎችን ማስረጃ ከሰማ በኃላ የግራ ቀኙን ማስረጃ መዝኖ የሁለቱ ተሽከርካሪዎች ግጭት የደረሰው


በአመልካች ደንበኛ ተሽከርካሪ ሾፌር ስህተት መሆኑ ተረጋግጧል ከሚል  ድምዳሜ ላይ በመድረስ ተጠሪዎቹ ለክሱ ኃላፊነት የለባቸውም ሲል በነጻ ያሰናበታቸው መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡

 

አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔን በማጽናቱ ነው፡፡የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ የስር ፍርድ ቤት እንደደረሰበት መደምደሚያ ለጉዳቱ መንሰኤ ለሆነው ጉዳት የሁለቱም ወገኖች ጥፋት የለም፣የመኪኖች ግጭት ጉዳይ ነው ከተባለ የአሁኑ አመልካች ያቀረበው የጉዳት ካሳ ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2084(2) ድንጋጌ አንጻር ተጠሪዎች ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ ተደርጎ አመልካች ከ1ኛ እና ከ3ኛ ተጠሪዎች ጋር የጽሁፍ ክርክር የተለዋወጡ ሲሆን ለ2ኛ ተጠሪ መጥሪያውን ተከታትሎ ማድረስ ባለመቻሉ አቤቱታውን እንደተወው ተቆጥሮ 2ኛ ተጠሪ ከክርክሩ ውጪ እንዲሆን በ15/08/2006 ዓ.ም.ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል፡፡

 

በዚህም መሠረት አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው የግጭት አደጋው የደረሰው በ1ኛ ተጠሪ ተሽከርካሪ ሾፌር ጥፋት ምክንያት አይደለም በሚል በስር ፍርድ ቤቶች የተደረሰበት ድምዳሜ እና ይህንን ድምዳሜ መሰረት በማድረግ የተሰጠው ውሳኔ በግራ ቀኙ የቀረበውን አጠቃላይ ክርክርና ማስረጃ ያገናዘበ አይደለም፤የ1ኛ ተጠሪ ተሽከርካሪ ሾፌር ጥፋት አልነበረውም ቢባል እንኳ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2084(1) እና (2) ድንጋጌዎች መሰረት ተጠሪዎቹ ያወጣነውን ወጪ አጋማሽ የመክፈል ግዴታ አለባቸው በማለት መሆኑን የክርክሩ ይዘት ያመለክታል፡፡እንደተባለው ሁለት ባለሞተር ተሽከርካሪዎች ሲጋጩ እያንዳንዱ ተሽከርካሪ በየራሱ አንዱ በአንዱ ላይ አደጋ እንዳደረሰ የሚቆጠር ስለመሆኑ በፍትሐብሔር ሕግ በቁጥር 2084 (1) ስር፣የእያንዳንዱ ተሽከርካሪ ባለሀብት ወይም ለአደጋው ኃላፊ የሆነው ሰው በአደጋው ምክንያት ከደረሰው ጠቅላላ ጉዳት ገሚሱን መክፈል የሚገባው ስለመሆኑ በዚሁ ሕግ በቁጥር 2084 (2) ስር እና አደጋው የደረሰው በተለይ ወይም በጠቅላላው በአንደኛው መኪና ነጂ ስህተት መሆኑ በማስረጃ በተገለጸ ጊዜ ግን ከዚህ በተጠቀሱት ሁለቱ ንዑሳን ቁጥሮች የተመለከተው ደንብ የማይጸና ስለመሆኑ በቁጥር 2084 (3) ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ ክርክሩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በግራ ቀኙ ወገኖች የቀረቡትን የሙያ እና የዓይን ምስክሮች ቃል እንዲሁም የትራፊክ ፕላንን ጨምሮ የቀረቡለትን ሰነዶች አገናዝቦ ከመረመረ እና ከመዘነ በኃላ ተጠሪዎቹ  ኃላፊነት የለባቸውም በማለት ውሳኔ የሰጠው አመልካች እንደሚከራከረው ጥፋቱ የ1ኛ ተጠሪ ተሽከርካሪ ሾፌር መሆኑ አልተረጋገጠም በማለት ሳይሆን ይልቁንም የግጭት አደጋው የደረሰው የአሁኑ አመልካች የመድን ሽፋን በሰጠው ተሽከርካሪ ሾፌር ስህተት ነው በማለት መሆኑን የውሳኔው ይዘት በግልጽ ያመለክታል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው ቁጥር 2084 (1) እና (2) ድንጋጌዎች ስር የተመለከተው ጉዳቱን የመጋራት ደንብ ተፈጻሚነት የማይኖረው ስለመሆኑ በድንጋጌው ንዑስ ቁጥር (3) ስር በግልጽ የተመለከተ በመሆኑ አመልካች ያወጣውን ወጪ አጋማሽ ተጠሪዎቹ እንዲሸፍኑ መወሰን ነበረበት በማለት አመልካች የሚያቀርበው ክርክር ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ለማለት የሚቻል አይደለም፡፡


በሌላ በኩል 1ኛ ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት ለቀረበባቸው ክስ በሰጡት መልስ ለጉዳቱ መንስኤ ሁለቱም ተሽከርካሪዎች በመሆናቸው የየራሳችንን ጉዳት እንድንችል መደረግ ይገባዋል በማለት ተከራክረው እያለ አመልካች ያወጣውን ወጪ አጋማሽ እንዲጋሩ ሳይወሰን የቀረው አላግባብ ነው በማለት አመልካች ያቀረበውን የክርክር ነጥብ በተመለከተ 1ኛ ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት ባቀረቡት መልስ ላይ ለጉዳቱ መንስኤ ሁለቱም ተሽከርካሪዎች በመሆናቸው የየራሳችንን ጉዳት እንድንችል መደረግ ይገባዋል በማለት የተከራከሩት በራሳቸው ተሽከርካሪ ላይም በተመሳሳይ ሁኔታ ጉዳት መድረሱን እና ለጥገና ወጪ ማውጣታቸውን ለመግለጽ እንጂ ጥፋቱ በራሳቸው ተሽከርካሪ አሽከርካሪ ነው በሚል  የቀረበባቸውን ክስ በማመን ካለመሆኑም በላይ በመልሳቸው  መጨረሻ ላይ ለክሱ ኃላፊነት የሌለባቸው መሆኑን በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ የተከራከሩ መሆኑን አመልካች አቅርቦ ያያዘው የ1ኛ ተጠሪ መልስ ይዘት የሚያመለክት በመሆኑ እና ቀደም ሲል እንደተገለጸው ግጭቱ የተከሰተው አመልካች የመድን ሽፋን በሰጠው ተሽከርካሪ ሾፌር ስህተት መሆኑ በማስረጃ የተረጋጠ እስከሆነ ድረስ በቁጥር 2084(1) እና (2) ድንጋጌዎች ስር የተመለከተው ጉዳቱን የመጋራት ደንብ ተፈጻሚነት የማይኖረው በመሆኑ አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረበው የክርክር ነጥብም ሕጋዊ ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ አልተገኘም፡፡

ሲጠቃለል ከላይ ከተመለከተው አጠቃላይ የክርክሩ ይዘት መገንዘብ የሚቻለው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ የቀረበበትን ውሳኔ የሰጠው ፍሬ ነገርን በማጣራት እና ማስረጃን በመመዘን ረገድ በሕግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት መሆኑን ሲሆን ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ማስረጃ የመዘነበት አግባብ ደግሞ በይግባኝ ሰሚው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 80(3)(ሀ) እና በአዋጅ ቁጥር 25/88  በአንቀጽ 10 እንደተመለከተው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ስልጣን መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበትን የመጨረሻ ውሳኔ መርምሮ በማረም የተገደበ በመሆኑ ፍሬ ነገርን የማጣራት እና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን የተሰጣቸው የመጀመሪያ ደረጃ እና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ የሰጡት ውሳኔ አግባብነት በዚህ ሰበር ችሎት ሊመረመር የሚችልበት ስርዓት የለም፡፡ በሕግ ረገድ ደግሞ ውሳኔው መሰረታዊ ስሕተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 ው ሳ ኔ

 

1. የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 24449 በ26/07/2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 59437 በ23/12/2005 ዓ.ም. በውሳኔ የጸናው ውሳኔ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ  ቁጥር

348(1) መሰረት ፀንቷል፡፡

2.  እንዲያውቁት የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍርድ ቤቶች ይተላለፍ፡፡

3.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

 

4.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡