89676 criminal law/ evidence law/ fundamental principle of evidence law

የማስረጃ ምዘና    መሰረታዊ      መርሆችን       መሰረት  ያላደረገ  ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለመሆኑ

የሰ//. 89676

 

ጥር 22 ቀን 2007 .

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሀመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል

አመልካች፡- የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ - /ሕግ ምርምር ጥጋቡ ቀረቡ ተጠሪ፡- ሳሙኤል ፍቃዱ ኃይሌ - ቀረቡ

መዝገቡን የተቀጠረው የቅጣት ውሳኔ ለመሰጠት ነው፡፡ በዚህም መሰረት መዝገቡን መርምረን ተከታዩን የቅጣት ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

 

 ቅ ጣ ት

 

1. አንድ ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ሁኖ ከተገኘ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ያለበት ሲሆን ቅጣቱ የሚወሰነው ደግሞ ስራ ላይ በዋለው በፌዴራል ጠቅላይ  ፍ/ቤት የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ታይቶ ነው፡፡ ተጠሪ ጥፋተኛ የተባሉት የወንጀል ሕግ አንቀፅ 627/1/ ድንጋጌ የሚያስቀጣው ከአስራ አምሰት አመት እስከ ሃያ አምስት ለሚደርስ በሚችል ጽኑ እስራት ነው፡፡

2. በመሰረቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ የወንጀል ህግ የአገሪቱን የወንጀል ህግ ግብ በአዋጅ ቁጥር 414/1996 አንቀፅ 1 ስር ሲደነግግ "የወንጀል  ህግ ግብ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ሲሆን ይህንን የሚያደርገው ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው በማድረግ ነው" በማለት ያስቀምጣል ህጉ በአንቀፅ 87 ላይ ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎች ህጉ ሊደርስበት ያሰበውን ዓላማ ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ በህጉ መንፈስ መሰረት መፈፀም እንዳለባቸው በመርህ ደረጃ ይደነግጋል፡፡ ይኽው አንቀፅ ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎቹ ምን ጊዜም ሰብዓዊ ክብርን በሚጠብቅ መንገድ መፈፀም እንደሚኖርባቸው ያስገነዝባል፡፡ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 88 ሲታይም የቅጣቶች እና የጥንቃቄ እርምጃወች አወሳሰን በተመለከተ ዘርዘር ያሉ ንዑስ ድንጋጌዎችን አካቶ ይዟል፡፡ በዚህ አንቀፅ ስር ያሉ  ንዑስ አንቀፆች የሚያሳዩት ፍርድ ቤቱ ቅጣቶችንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን የሚወስነው የወንጀል ህጉን


ጠቅላላ ክፍል ድንጋጌዎችን እንዲሁም ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው የሚደነግጉትን የልዩ ክፍሉ ድጋጌዎች መሰረት በማድረግ መሆኑን፣ ቅጣት ሊወሰን የሚገባው የወንጀል አድራጊውን ግላዊ የአደገኛነት መጠን ያለፈ የህይወት ታሪኩን ወንጀል ለማድረግ የነሳሱትን ምክንያቶችና የአሳቡን አላማ የግል ኑሮውን ሁኔታ፣ የትምህርቱን ደረጃ፣ እንዲሁም የወንጀሉን ከባድነትና የአፈፃፀሙን ሁኔታዎች በማመዛዘን  መሆኑን፣ የወንጀል ህግ ልዩ ክፍል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ፍርድ ቤቱ እጅግ ቀላል ከሆነ ቅጣት አንስቶ እስከ ከባዱ ድረስ ያለውን በጥንቃቄ በመመርመር ለእያንዳንዱ ጉዳይ ተገቢ የሆነውን ቅጣት እንደሚወስን የቅጣት አወሳሰን ደንቡ በግልፅ ያሳያል፡፡ ከላይ እንደተገለፀዉ የወንጀል ቅጣት የሚወሰነው በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 88/2/ ስር የተመለከቱትን ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ይህ ችሎትም እነዚህ ሁኔታዎችን ሁሉ ተመልክቷል፤ አመዛዝኗልም፡፡

3. እንደ ቅጣት መመሪያው መወሰን እንዲቻል ደግሞ በተጠሪ ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ከግራ ቀኙ ማክበጃ እና ማቅለያ ምክንያቶች ጋር ተገናዝቦ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ በዚህ አግባብ ቅጣቱ ከመሰላቱ በፊት ግን ተጠሪ ጥፋተኛ የተባሉበት ድንጋጌ ክሱ ሲመረትም ሆነ በበታች ፍርድ ቤቶች ክርክር ሲካሄድ ደረጃ ያልወጣለት ቢሆንም በዚህ ችሎት ጉዳዩ በመታየት ላይ እያለና የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠበት ጊዜ በስራ ላይ ያለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 በመሆኑ በዚሁ መመሪያ መሰረት የወንጀል ህጉ አንቀፅ 627 ደረጃ የወጣለት ድንጋጌ ነው፡፡ ተጠሪ ድርጊቱን የፈፀሙት እድሜዋ ዘጠኝ አመት ካልሞላት ሴት ህፃን ላይ በመሆኑ የወንጀሉ ደረጃ 2 ሁኖ የእስራት ቅጣት መነሻ እርከን 35 ነው፡፡ በዚህ እርከን ለፍርድ ቤቱ የተተወው ፍቃደ ስልጣን ከአስራ ስድስት አመት ከስድስት ወር እስከ አስራ ዘጠኝ አመት ከስድስት ወር ነው፡፡ መነሻ ቅጣቱም በዚሁ ሬንጅ ውስጥ የሚያዝ ሲሆን በተጠሪ ላይ መጨረሻ ላይ የሚጣለው የቅጣት መጠን የሚታወቀው ግን የማክበጃ እና የማቅለያ ምክንያቶች ታይተው ስሌቱ ከተሰራ በኋላ ነው፡፡ በዚህም አግባብ የቅጣት መጠኑን ማስላት የግድ ሲሆን በተጠሪ ላይ በዓቃቤ ሕግ በኩል ቅጣቱን ሊያከብዱ ይገባል ተብለው የተጠቀሱት ምክንያቶች የድርጊቱ አፈፃፀም በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 84/1// የተጠቀሰው መጥፎ አመልንና ወራዳነትን ያሳያል እንዲሁም በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 84/1/// መሰረት ድርጊቱ የተፈፀመው የተለዬ እንክብካቤ በሚያስፈልጋት ህፃን ልጅ ላይ ነው የሚሉት ናቸው፡፡ ይሁን እንጅ እነዚህ ምክንያቶች ከወንጀል ሕጉ አንቀፅ 627 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ እንዲሁም የቅጣት አወሳሰን መመሪያው ደረጀውን ሲያወጣ እድሜን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ከመሆኑ አንፃር የወንጀሉ ድርጊት ማቋቋሚያ ነጥቦች ሊባሉ የሚችሉ በመሆኑና በወንጀል ህጉ አንቀፅ 82/2/ ድንጋጌ አንፃር በቅጣት ማክበጃ ምክንያትነት መያዙ ተገቢ ሁኖ አልተገኘም፡፡ በመሆኑም አቃቤ ሕግ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት ባቀረበው የቅጣት አስተያየት ተጠሪ የወንጀል ሪኮርድ አለባቸው የሚል ግልፅ አስተያየት አላቀረበም፡፡ ይህም ተጠሪ ሪኮርድ ያልቀረበባቸው መሆኑን የክርክሩ ሂደት የሚያሳይ በመሆኑ ይኼው ምክንያት በማቅለያነት እንዲያዝላቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ሌላም ተጠሪ ያቀረቡት የቅጣት ማቀለያ የቤተሰብ አስተዳዳሪነት ሲሆን ከራሳቸው ልጆች በተጨማሪ የዘመድ ልጅ የሆኑትን ሁለት ህፃናትን የሚያስተዳድሩ መሆናቸውን ገልፀው በቅጣት ማቅለያነት እንዲያዝላቸው የጠየቁ ሲሆን አቃቤ ሕግ በዚህ በኩል ክርክር ካለማቅረቡም በላይ ችሎቱም እነዚህ ምክንያቶች የቤተሰብ አስተዳዳሪነት በጠቅላላ ቅጣት ማቅለያነት፣ የዘመድ ልጆችን በመንከባከብ የማስተማር ሰብዓዊነት ተግባር መፈፀማቸው ደግሞ በልዩ


ቅጣት ማቅለያነት ሊያዝ የሚገባ ሁኖ አግኝቷል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ተጠሪ ሶስት ህጋዊ የሆኑ የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ያሏቸው ሁኖ አግኝተናል፡፡

ከላይ እንደተገለፀው ተጠሪ ጥፋተኛ የተባሉበት ድንጋጌ ድርጊቱን በተፈፀመበት የካቲት 08 ቀን 2ዐዐ4 እና ክሱ የካቲት 19 ቀን 2ዐዐ4 .ም ተመስርቶ ክርክሩ በስር ፍርድ ቤት ታይቶ ዳኝነት በተሰጠበት ጊዜ በነበረበት የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ደረጃ ያልወጣለት የነበረ ሲሆን በተሻሻለውየቅጣት አወሳሳን መመሪያ ደግሞ ደረጃ የወጣለት ነው፡፡ እኛም የቅጣት ማቅለያ ዋጋ አያያዝን ከወንጀል ሕጉ አንቀን 6 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ አንፃር ለተጠሪ የተሻለ ሁኖ ያገኘነው ነባሩ የቅጣት አወሳሳን መመሪያ በመሆኑ የቅጣቱን መጠን ከዚህ አንፃር ተመልክተናል፡፡

ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው ተጠሪ እንዲቀጡ በመነሻነት የሚያዘው እርከን 35 በመሆኑ በዚህ እርከን መነሻ ሲያዝ የቅጣት መጠኑ ከሰባት አመት በላይ በመሆኑ ተጠሪ ያላቸው ሶስት የቅጣት ማቅለያዎች በመመሪያው ቁጥር 1/2002 አንቀፅ 13/8/ ድንጋጌ መሰረት እያንዳንዳቸው ሶስት እርከን የሚያስቀንሱ በመሆኑ ከእርከን 35 ወደ እርከን 26 መውረድን፣ በዚህ እርከን ውስጥ ተገቢውን ቅጣት መወሰን የሚጠይቅ ነው፡፡

በዚሁ መሰረት ቅጣቱን ስናሰላው ተጠሪ ሊቀጡ የሚገባው በእርከን 26 ስር ለፍርድ ቤቱ በተተወው የፍቅድ ስልጣን ማለትም ከሰባት አመት ከስምንት ወር እስከ ዘጠኝ አመት ከሁለት ወር ፅኑ እስራት ውስጥ ነው፡፡ ከእነዚህ የእስራት ጊዜያት ተጠሪን ያርማል፣ ሌሎች መሰል አጥፊዎችን ከወዲሁ ያስጠነቅቃል ብለን ያመነው ሰባት አመት ከስምንት ወር ፅኑ እስራት ሁኖ አግኝተናል፡፡ ሲጠቃለልም ከላይ በዝርዝር በተመለከቱት ህጋዊ ምክንያቶች ተጠሪ በጉዳዩ ላይ የታሰሩት ማ ና ቸ ው ም ጊዜ ካለ የሚታሰብላቸው ሁኖ ተጠሪ በ ሰ ባት አመት ከ ስምን ት ወር ጽኑ

 እ ስ ራት ሊቀጡ ይገባል በማለት በድምፅ ብልጫ ወስነናል፡፡

 

የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤትም በተጠሪ ላይ በዚህ ችሎት የተሰጠውን የቅጣት ውሳኔ ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ብለናል፡፡ ይፃፍ፡፡መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የሶስት ዳኞች ፊርማ አለበት

 የ ሃ ሳ ብ  ል ዩ ነ ት

በአብላጫ ድምፅ በተሰጠው የቅጣት ውሳኔ ላይ የተጠሪው የዘወትር ፀባይ መልካምነት በማቅለያ ምክንያትነት ሊያዝ ይገባል የተባለው ዐ/ሕግ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት እያለ ተጠሪ የወንጀል ሪኮርድ ያለባቸው ስለመሆኑ ያቀረበው ክርክር የለም በማለት ነው፡፡ በርግጥ አመልካች ባቀረበው የቅጣት አስተያየት ላይ ተጠሪ የወንጀል ሪኮርድ ያለባቸው ስለመሆኑ የቀረበው ክርክር የለም፡፡ ይሁን እንጅ ተጠሪው ከሌሉ ውጤቱ የታወቀ /የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠበት/፣ ከፊሉ ደግሞ የመጨረሻ ውጤቱ ያልታወቀ የኋላ የወንጀል ታሪክ የነበራቸው ስለመሆኑ የፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት መዝገብ በግልፅ ያመላክታል፡፡ ተጠሪው በኋላ የወንጀል ታሪክ የነበራቸው ሲሆን ደግሞ ይህ የኋላ የወንጀል ታሪክ ሕጋዊውን ስርዓት ተከትሎ የተሰረዘ መሆኑ ሳይረጋገጥ የተጠሪው የዘወትር ፀባይ መልካም ነበር የሚል ግምት መያዙ ተገቢነት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በመሆኑም የተጠሪው የዘወትር ፀባይ መልካምነት በቅጣት ማቅለያነት እንዲያጣ ከመደረጉ በፊት የፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት መዝገብ የሚያረጋግጠው የተጠሪው የኋላ የወንጀል ታሪክ ሕጋዊውን ስርዓት ተከትሎ የተሰረዘ መሆን አለመሆኑ አሰቀድሞ ሊጣራ ይገባው ነበር በማለት ስማችን በአራተኛ እና በአምስተኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰው ዳኞች ይህንን የልዩነት ሀሳብ አስፍረናል፡፡

 

የማይነበብ የሁለት ዳኞች ፊርማ አለበት