98283 criminal law/ criminal responsibility of judges/ corruption

ከዳኝነት ስራ ጋር ያልተያያዙ እና የአስተዳደር ስራ ሲያከናውኑ የሚፈፀሙ የወንጀል ጥፋቶች ዳኛውን ከተጠያቂነት የማያስቀሩ ስለመሆኑ፣

የወ/ህ/ቁ. 402(1) እና (2)

በትግራይ ክልል ዳኞች እና ሬጂስትራሮችን ለማስተዳደር ተሻሽሎ የወጣው ደንብ ቁጥር 1/2003

የሰ/መ/ቁ. 98283

 

መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

መኮንን ገ/ህይወት ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ ተኸሊት ይመስል

አመልካች፡- አቶ ሐጐስ ገ/ሄር መኮንን

 

ተጠሪ፡- የትግራይ ክልል የስነ/ፀ/ሙ/ኮ - ዐ/ሕግ መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ፍ ርድ

 

የአሁኑ አመልካች በወንጀል ህጉ አንቀጽ 407(2) የተመለከተውን በመተላለፍ የማይገባውን ብልፅግና ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በትግራይ ክልል በደቡብ ዞን አሰላ ወረዳ ፍ/ቤት ዳኛ ሆኖ ሲሰራ ሥልጣኑን አላግባብ በመጠቀም የመንግስት የአበል አከፋፈል ሥርዓት በመጣስ ለራሱና ለሥራ ባልደረቦች ሊከፈል የማይገባውን ብር 7653.4 እንዲከፈል በማድረጉ በፈፀመው በሥልጣን ያለአግባብ መጠቀም ወንጀል ተከሷል ሲል የአሁን ተጠሪ  ክስ አቅርቦበታል፡፡

 

ጉዳዩን በቅድሚያ የተመለከተው የአላማጣ ማዕከላዊ ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃ ከሰማ በኋላ አመልካች በተዘዋዋሪ ችሎት ስም ከሥራ ቦታዬ ወደ ቀበሌዎች ሄጃለው በማለት በተሞክሮ ልውውጥ ስም፤ በመሀበራዊ ፍ/ቤትና የመሬት ዳኞች ሥልጠና ስም አበል አላግባብ መውሰዱ ፤ዳኞች ስልጠና ሰጥተዋል በማለት በፔሮል ወደ ቀበሌ እንደወጡ አሰመስሎ አበል መክፈሉ ፤ የሂሳብ መደብ በማይፈቅድበት ሁኔታ በራሱ ስም አበል ወጪ በማድረግ የፅሕፈት መሣሪያ መግዛት እና ከፋይናንስ ደንብ እና መመሪያ ውጭ ስለመስራቱ በራሱ በዝርዝር የተመለከተውን እና የቀረበበትን የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ እንደ ክሱ አቀራረብ ጥፋተኛ ነው በማለት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶችን ተቀብሎ በ1(አንድ) ዓመት ፅኑ እስራት እና በብር 2000 /ሁለት ሺህ /መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

 

ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤትም ሆነ የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔው የሚነቀፍበት ምክንያት የለም በማለት ቅሬታውን ውድቅ አድርገዋል፡፡


የሰበር አቤቱታው ለዚህ ፍ/ቤት የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ አመልካቹ የካቲት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በተፃፈ 5 (አምስት) ገጽ ዝርዝር ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ተጠቃሎ ሲታይ የፍርድ ቤቱ ሥራ እንዳይጐዳ ብሎ የፈፀምኩት መሆኑ እየታወቀ፤በአግባቡም ሣይጣራ ተድበስብሶ የታለፈ በመሆኑ፤የቀረቡት ማስረጃዎች ከሚመለከታቸው ህጐች ሳይገናዘብ የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑና ፤ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በሰበር መዝገብ ቁጥር 33075 ባሳለፈው ውሳኔ የዳኝነት ሥራ በሚያከውኑበት ጊዜ የሚፈፅሙ ጥፋቶች እና ስህተቶች ዳኞች በስልጣን ያለ አግባብ መጠቀም በሚል ወንጀል ሊከሠሱ አይገባም በማለት የሰጠው ውሳኔ ተሻሽሎ ተተርጉሞ የሥር ፍ/ቤቶች ውሣኔ ተሽሮ በነፃ ልሰናበት ብለዋል፡፡

 

ቅሬታቸው ተመርምሮ ፈፀሙት የተባለው ድርጊት ጥፋተኛ በተባሉበት የህግ አንቀጽ ሥር የሚወድቅ መሆኑን ወይም ጉዳዩ ከዳኝነት ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን አኳያ የሚታይ መሆኑን ለማጣራት ተብሎ ተጠሪ መልስ እንዲሠጡበት ተደርጓል፡፡

 

ተጠሪ ሚያዚያ 9/2ዐዐ6 ዓ.ም በተፃፈ መልስ በወ/ህ/ቁ.407(2) መከሰሱ እና ጥፋተኛ መባሉ የህግ ስህተት የሌለበት በመሆኑ፤አስቀድሞ በሰ/መ/ቁ. 33075 የተሰጠው ውሳኔም የዳኝነት ሥራ በመከናወን ላይ እያለ የሚፈፀሙ ጥፋትና ሥህተትን እንጅ መሠል ተግባርን የሚመለከት ባለመሆኑ የሥር ፍ/ቤቶች ያሳለፉት ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት አልተፈፀመበትም ተብሎ እንዲፀና ጠይቀዋል፡፡ አመልካቹም ግንቦት 2/2006 ዓ.ም የተፃፈ ክርክራቸውን የሚያጠናክር የመ/መልስ አቅርበዋል፡፡

 

ከላይ ባጭሩ ለመግለፅ የሞከርነው የጉዳዩን አመጣጥ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ያስቀርባል የተባለበትን ጭብጥ ይዘን መዝገቡን መርምረናል፡፡

 

እንደመረመርነው ፍሬ ነገሩን የማጣራት እና ማስረጃ ለመመዘን ሥልጣኑ የተሰጠው የሥር ፍ/ቤት አመልካቹ መንግስት የፋይናንስ ህጐች እና ደንቦች ከተፈቀደው ውጭ በአጠቃላይ ብር 7,650.40 እንዲወጣ በማድረግ ለራሱም ሆነ ለሥራ ባልደረቦቹ መጠቀሚያ በማድረግ በኃላፊነቱ አላግባብ መገልገሉን አረጋግጧል፡፡

 

ይኸው በማስረጃ ተረጋግጧል የተባለው አድራጐት በመንግስት ሥራ ላይ የተፈፀመ ከዳኝነት ሥራ ጋር ተቀላቅሎ ሊታይ የማይገባ የወንጀል ጥፋት ነው፡፡

 

አመልካቹ በዳኝነት ተሹመው በቋሚት የዳኝነት የመንግሰት ሥራን የሚሰሩ የመንግስት ሠራተኛ በመሆናቸው እና ይሠሩበት የነበረው የወረዳ ፍ/ቤትም በመንግስት በጀት ተመድቦለት የዳኝነት መንግስታዊ ሥራ የሚከናወንበት መስሪያ ቤት በመሆኑ በመንግስት ሥራ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን የሚመለከቱ የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች በመሠል ጥፋቶች ላይም በተመሳሳይ ተፈፃሚነት የሚሆኑ ናቸው፡፡ /የወ/ህ/ቁ. 402(1) እና (2) ይመለከታል፡፡

 

ሌላው መከራከሪያ እና የሰበር አቤቱታው ያስቀርባል ለመባሉ ምክንያት የሆነው ጉዳዩን ከዳኝነት ሥነ ምግባር እና ዲሲፕሊን አኳያ የሚታይ መሆኑን የተመለከተ ነው ፡፡

 

በትግራይ ክልል ዳኞች እና ሬጅስትራሮችን ለማስተዳደር ተሻሽሎ የወጣው ደንብ ቁጥር 1/2003 በመንግስት  ገንዘብ  ወይም  ንብረት  በዳኞች  የሚፈፀምን  ያላግባብ  መጠቀም  እና መውሰድ


የዲስፒሊን ጥፋት አድርጐ ይዟል፡፡ ነገር ግን የዲስፒሊን ደንቡ መሠል ድንጋጌ መያዙ በወንጀል ገረድ የሚኖረን ኃላፊነት የሚያስቀር አይደለም፡፡

 

የዲስፕሊን ጉዳዩች የሚቋቋሙበት፣ የሚመሩበት ሥርዓት እና ከሚሠጠው ውሳኔ የወንጀል ጥፋቶች ከሚቋቋሙበት፣ከሚመሩበት ሥርዓት እና ከሚሰጠው ውሣኔ ተለይቶ ሊታይ ይገባል፡፡ ስለሆነም የተፈፀመው ጥፋት የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆን አለመሆኑ ከዲስፒሊን ጉዳዩ ጋር ሊያታይ አይገባም፡፡

 

የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 33075 ዳኛ ብርቁ ባላዬ እና የአማራ ክልል ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተከራከሩበት ጉዳይ ጥር 13/2001 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ የዳኝነት ሥራን በሚያከናውኑበት ወቅት የሚፈፅሙ ስህተቶች እና ጥፋቶች ሁሉ ዳኛን በሥልጣን አላግባብ መገልገል ወንጀል ሊያስጠይቁ  የማይችሉ ስለመሆናቸው መወሠኑ የዳኞችን ህገ መንግስታዊ የውሳኔ ነፃነት ለማጠናከር እንጅ በእጃችን እንዳለው ጉዳይ ከዳኝነት ሥራ ጋር ያልተያያዙ እና የአስተዳደር ስራ ሲያከናውኑ የሚፈፀሙ የወንጀል ጥፋቶች ሁሉ ተጠያቂነትን የሚያስቀር ትርጉም የሚሠጠው ባለመሆኑ አመልካቾች ይኸው ውሳኔ በማመሳሰል ለተያዘው ጉዳይ ተፈፃሚ እንዲሆን ያቀረቡት ጥያቄ በህጉ ተቀባይነት የለውም ብለናል፡፡

 

በአጠቃላይ አመልካቾች በነበራቸው የሥራ ኃላፊነት ምክንያት ሊጠብቅ እና ሊከላከሉት የሚገባን የህዝብ እና የመንግስት ንብረት ከህግ ውጭ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ለፈፀሙት ጥፋት በስር ፍ/ቤቶች የተላለፈባቸው ውሣኔ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት አይደለም ብለናል ተከታዩንም ወስነናል፡፡

 

 ው ሳኔ

የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በሰጠው መ/ቁ. 6111/06 ታህሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ያሳለፈው ትዕዛዝ ፤የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.58434 ግንቦት 13 ቀን 2005 ዓ.ም ያሳለፈው ትዕዛዝ እና በደቡባዊ ዞን ማዕከላዊ ፍ/ቤት የአላማጣ ምድብ ችሎት በወ/መ/ቁ.02867/05 የካቲት 26/2005 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.195(2)(ለ)(2) መሠረት ፀንቷል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

 


 

ብ/ግ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡