97203 criminal law/ participation in the commission of crime/ individuation of guilt

ከአንድ በላይ ሰዎች በወንጀል ተሳታፊ በሚሆኑበት ጊዜ ለወንጀሉ ድርጊት ኃላፊ ናቸው የተባሉት ወንጀለኞች የእያንዳንዳቸውን ተሳትፎ ህጉ ባስቀመጠው የማስረጃ መለኪያ መሰረት መለየት ያለበት ስለመሆኑ-

የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 141፣ የወ/ህ/ቁ. 40

የሰ/መ/ቁ 97203

 


 

ዳኞች፡-አልማው ወሌ ሡልጣን አባተማም መኮንን ገ/ሕይወት

ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል


መስከረም 30 ቀን 2007


 

አመልካች፡- 1.አቶ ታምራት ደምሴ

2.አቶ በሪሁን ደምሴ       የቀረበ የለም

3.አቶ ታደለ ሽቱ

ተጠሪ፡- የቤንሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ቢሮ ዐቃቤ ሕግ - የቀረበ የለም፡፡ መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ  ር ድ

 

ጉዳዩ የወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በመተከል ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ነው፡፡ በዚህ ፍ/ቤት የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካቾች እና አቶ አለኽኝ ጋሻው በተባሉት ግለሰብ ላይ የመሰረተው ክስ:- በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)(ሀ) እና 539/1/ሀ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ታህሳስ 29 ቀን 2002 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 3፡00 በሚሆንበት ጊዜ ግልገል በለስ ከተማ ከወ/ሮ አለምፀሐይ ጌታሁን ሻይ ቤት አረቄ እየጠጡ በፈጠሩት ፀብ ለምንድን ነው የሰደብከን? በማለት የአሁኑ 1ኛ፣2ኛ አመልካቾች እና የስር 3ኛ ተከሳሽ የነበሩት አቶ አለኸኝ ሟች ኤርሚያስ ኃይሉን ሊደበድቡት ሲሉ በገላጋይ ከቤት ከወጡ በኋላ ከስር ሶስተኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን ተከታትለው በመሄድ ኤርሚያስ ኃይሉን በአንድ ላይ ተባብረው በዱላና በድንጋይ ግንባሩንና መላ ሰውነቱን ደብድበው በግፍ ገድለዋል የሚል ነው፡፡አመልካቾች ክሱ ተነቦላቸው እንዲረዱት ከተደረገ በኋላ ስለእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቁ በክሱ ላይ ተቃውሞ የሌላቸው መሆኑን ገልፀው የድርጊቱ አፈጻጸሙን በተመለከተም ክደዋል፡፡ ተጠሪ በበኩሉ አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎችን ያሰማ ሲሆን የስር ፍ/ቤትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን መርምሮ አመልካቾች ድርጊቱን መፈፀማቸው በበቂ ሁኔታ ተረጋግጧል በሚል ምክንያት የአሁኑ አመልካቾችን እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ የስር 3ኛ ተከሳሽ የነበሩትን ግለሰብ ግን በነፃ አሰናብቷል፡፡በዚህ ብይን መሰረትም አመልካቾች የመከላከያ ማስረጃዎችን አቅርበው አሰምተዋል፡፡

 

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን መርምሮ የአመልካቾችን የመከላከያ ማስረጃነት ቃል ክብደት የማይሰጠው ነው በማለት ውድቅ ከአደረገ በኃላ አመልካቾችን በዓቃቤ ሕጉ በኩል ተጠቅሶ በቀረበው ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ በማድረግ እያንዳንዳቸውን በ17 (አስራ ሰባት አመት) ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡ከዚህም በኃላ አመልካች በጥፋተኝነትና በቅጣት ውሣኔው ላይ ቅር በመሰኘት ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኛቸውን፣የሰበር አቤቱታቸውን ደግሞ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ  ውሣኔ በመቃወም ለማስቀየር ነው፡፡


አመልካቾች ህዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ ሁለት ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ ላይ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱንም ባጭሩ፡- የበታች ፍርድ ቤቶች በአመልካቾች ላይ የሰጡት የጥፋተኛነት ውሣኔ አግባብነት የሌለውን ማስረጃ መሰረት ያደረገ ከመሆኑም በላይ ማስረጃውም ተገቢውን የማስረጃ ምዘና ስርዓት ተከትሎ ያልተመዘነ መሆኑን፣አድራጎቱ በአመልካቾች ተፈፅሟል ከተባለም አግባብነት ያለው ድንጋጌ ተራ በሆነ የሰው መግደል ወንጀል የሚሸፍን ነው እንጂ በግፍ ሰው መግደልን በሚሸፍነው ድንጋጌ ስር የሚወድቅ ያለመሆኑን፣ እንዲሁም የቅጣት ውሳኔውም የአመልካቾችን የእድሜ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባና የበዛ መሆኑን በመዘርዝር ውሣኔው ሊለወጥ ይገባል በማለት ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሣይ ነው፡፡አቤቱታቸው ተመርምሮም አመልካቾች ለወንጀል ድርጊቱ ተጠያቂ የመደረጋቸውን አግባብነት ከወ/ሕ/አንቀጽ 23(2) ድንጋጌ አንፃር ለመመርመር ሲባል ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ባለመቅረቡ በፅሑፍ መልስ የመስጠት መብቱ ታልፏል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልጉት አበይት ነጥቦች፡-

 

1. ከአመልካቾች ውስጥ ለሟች ሕልፈት ተጠያቂነት ያለበት የትኛው ነው?፣

 

2. ተጠያቂነት አለበት ሊባል የሚችለው አመልካች አለ ከተባለ አድራጎቱ የሚሸፈነው በየትኛው አንቀፅ ስር ነው? እና ቅጣቱስ ስንት ሊሆን ይገባል የሚሉት ሁነው ተገኝተዋል፡፡

 

 የ መጀ መሪያ ውን ጭብጥ በተመ ለከተ፡ - ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው በዓቃቤ ሕግ የክስ ማመልከቻ ለህልፈት ተዳርገዋል የተባሉት ግለሰብ ለህልፈት የተዳረጉት በአመልካቾችና በስር 3ኛ ተከሳሽ በነበሩት ግለሰብ በግብረአበርነት በተፈፀመባቸው አድራጎት መሆኑን የተጠሪ ክስ የሚገልጸው ጉዳይ ሲሆን ተጠሪ በሟች ላይ ለህልፈተ ሕይወት መድረስ ምክንያት የሆነውን አድራጎት የፈፀሙት አመልካቾች መሆናቸውን ለማስረዳት አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎችን ማቅረቡን የውሳኔው ግልባጭ የሚያስገነዝብ መሆኑን ነው፡፡በዚህ ረገድ የተሰሙት ምስክሮች የሰጡት የምስክርነት ቃል ሲታይም፡-1ኛው ምስክር ድርጊቱ የተፈፀመው በአቃቤ ሕግ የክስ ማመልከቻ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ መሆኑን ጠቅሰው አመልካቾችና ሟች የምስክሩ ጎረቤት በሆኑት በወ/ሮ አለምፀሐይ ጌታሁን ሻይ ቤት ሲጠጡ እንደቆዩና ጎረቤታቸው ወደ ምስክሩ ቤት እራት ሊበሉ ሂደው አመልካቾችና ሟቹ እንደተጣሉና ምስክሩ እንዲያገላግሏቸው ለምስክሩ ሲነግሯቸው ምስክሩም ወደ መጠጥ ቤት ሂደው ሲመለከቱ ሁሉም ቁጭ ብለው እንደአገኟቸው፣ከዚያ በኋላ ሟቹ ቀድሞ ከቤቱ ሲወጣ አለኽኝ ጋሻው የተባለው የስር 3ኛ ተከሳሽ ሟችን ተከታትሎ መውጣቱንና ከአምስት ደቂቃ ቆይታ በኋላም የአሁኑ አመልካቾች ተከታትለው እንደወጡ፣በወቅቱ በመጠጥ ቤት ውስጥ ሟቹና የስር ተከሳሾች ሲጨቃጨቁ ምስክሩ መስማታቸውን፣ተከሳሾች ከቤት ከወጡ በኋላ ምስክሩ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ሂደው ከተኙ በኃላ ከምሽቱ 7፡00 አከባቢ ጩኸት እንደሰሙና በበነጋታውም 2፡00 አከባቢ ሟቹ ሞተ ሲባል መስማታቸውን መስክረዋል፡፡አለምጸሐይ ጌታሁን የተባሉት 2ኛ የዓቃቤ ሕግ ምስክር በበኩላቸው ድርጊቱ የተፈፀመው በዐቃቤ ሕግ የክስ ማመልከቻ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ መሆኑን ጠቅሰው በሻይ ቤታቸው ሶስት  ሰዎች ቀድመው  ገብተው  በብርሌ አረቄ  ገዝተዋቸው  እየጠጡ  እያለ


የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማውራት እንደጀመሩና ከቆይታ በኋላ ስድብ ሲጀምሩ ምስክሯ ነገሩ ጠብ መሆኑን በመረዳት ጎረቤታቸው ለሆኑት ለዓቃቤ ህግ አንደኛ ምስክር ከሻይ ቤታቸው ወጥተው በመሄድ ስለጉዳዩ እንደነገሯቸውና ጎረቤታቸውም ወደ ምስክሯ ቤት መጥተው በመጠጥ ቤት የነበሩትን አመልካቾችን "ሌላ ሰው ለምን ትረብሻላችሁ?" በማለት ሲናገሯቸው ከመጠጥ ቤት የነበሩት ሰዎች ተከታትለው እንደወጡና ምስክሯም ከዚህ በኋላ የመጠጥ ቤቱን በር ዘግተው የተኙ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ሦስተኛው የዐቃቤ ሕግ ምስክርም የአቃቤ ሕግ 1ኛ ምስክር ባለቤት መሆናቸውን ጠቅሰው የሰጡት የምስክርነት ቃል በይዘቱ ከ1ኛው ምስክር ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡4ኛው የአቃቤ ሕግ ምስክር ደግሞ ድርጊቱ ተፈፀመ በተባለበት ጊዜ በግልገል በለስ ከተማ 02 ቀበሌ ግብርና ፅ/ቤት ወደታች ባላቸው የግል ሻይ ቤት የሥር 3ኛ ተከሳሽ አለኽኝ እና ኤርምያስ የተባሉት ሰዎች ሂደው የሚጠጣ ሻይ ከአዘዙ እና ሻሂውን ከጠጡ በኋላ ከምሽቱ 3፡00 አከባቢ ከቤት ወጥተው እንደሄዱ፣ከምሽቱ 4፡30 ሲሆን ደግሞ አለኽኝ የተባለው ተከሳሽ ተመልሶ ወደ ሻሂ ቤታቸው ገብቶ ጅን አረቄ እንዲሰጠው ሲጠይቃቸው ምስክሯ የለኝም የሚል ምላሽ ሲሰጡት ይሄው ግለሰብ ሻሂ ጠጥቶ ለብቻው ተመልሶ መሄዱን መስክረዋል፡፡5ኛው የአቃቤ ህግ ምስክር በሰጡት የምስክርነት ቃል፡-በዓቃቤ ሕግ የክስ ማመልከቻ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ እንዳልነበሩ፣ድርጊቱ ከተፈፀመ በኃላ የወንጀል ክትትሉን እንደጀመሩ፣ከወንጀሉ መፈፀም በኃላ የደምሴ ልጆች መሰወራቸውን፣አባታቸውም ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ታስረው እንደነበር፣አቶ ደምሴ የተባሉት ግለሰብም "አይ እኔን ከእስር ቤት ፍቱኝና ሌሎች ልጆች ስላሉ አፈላልጌ ላምጣ!" ብለው ለፖሊስ አቤቱታ እንደአቀረቡ፣ከዚያም ሰውየው ፖሊስ ይሰጠኝ በማለታቸው ፖሊስና ልዩ ኃይል ተሰጥቷቸው ታምራት የተባለው ልጃቸው ከስራ ቦታ ተይዞ እንደመጣ፣በወቅቱ "ድርጊቱን ከወንድሜ በሪሁን ጋር የፈፀምኩት እኔ ነኝ፣ ታደለና አለኽኝም በድብደባው ላይ አሉ፤ድርጊቱን የፈፀምነው እኛ ነን!" በማለት ለፖሊስ መናገሩን፣ድርጊቱን አራት ሁነው የፈፀሙት መሆኑንና ሟቹ ይሞታል በሚል ሃሳብ እንዳልፈፀሙ፤ሟችን የመቱትም ታምራት በዱላ ግንባሩን፣ሌሎች በቡጢ እና በድንጋይየመቱት መሆኑን መግለፁንና ከዚያም እንደሸሹና እንደተበታተኑ እንዲሁም ጥዋት ወደ አዝመራ ቦታ ሂዶ ቆይቶ በልዩ ኃይል መያዙን ሲናገር መስማቱን የመሰከረ ነው፡፡6ኛው ምስክር በበኩሉ በወቅቱ በሟች ለቅሶ ላይ እያሉ "የእናተ ቤተሰብ ነው!" በሚል ምክንያት ተይዘው በፖሊስ ጣቢያ እንደነበሩ፣ምሽት ላይ ታምራት የተባለውን ተከሳሽ ፖሊሶች ይዘው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እያለ አንድ የፖሊስ አባል ታምራትን "ለምንድነው እንዲህ አድርጋችሁ የምትማቱት?" በማለት ሲጠይቀው ታምራት ጭንቅላቱን አልመታሁትም፤እኔ ጀርባውን ነው የመታሁት፣ጭንቅላቱን የመታው ሰው ሌላ ነው ብሎ ሲመልስለት መስማቱን መስክሯል፡፡

 

እንግዲህ የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካቾችን ጥፋተኛ ለማድረግ በዓቃቤ ሕግ በኩል የቀረቡት ምስክሮች ቃል ይዘት ከላይ የተጠቀሰው መሆኑን በውሳኔው ላይ የገለፁት ጉዳይ ሲሆን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍርድ ሐተታው በግልጽ ያስቀመጠው ድምዳሜውም  ከዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል አመልካቾች ሟችን ሲመቱትና ሲገድሉት አየሁ በሚል ያልተገለጸ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካቾችን ለወንጀል ድርጊቱ ኃላፊ ያደረጋቸው በክሱ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ በሟቹና በአመልካቾች መካከል ጠብ ተፈጥሮ ሟቹ ከስር ሶስተኛ ተከሳሽ ጋር በአንድ በኩል፣አመልካቾቹ ደግሞ በሌላ በኩል ተቀምጠው ሟቹ ምራቅ ሲተፋ አመልካቾች "ይህች ምራቅ ዛሬ ደም ትሆናለች!" በማለት ተናገረው ወዲያውኑ ሟቹና የስር 3ኛ ተከሳሽ ከአረቄ ቤቱ ወጥተው ሲሄዱ ወዲያውኑ የወንጀል ድርጊቱ መፈፀሙን ተረጋግጧል በሚል ድምዳሜ ነው፡፡


አመልካቾች ከሚከራከርባቸው ነጥቦች ውስጥ የአመልካቾችን የድርጊት ፈፃሚነት በተገቢው መንገድ አቃቤ ሕግ በማስረጃ ያለማስደገፉንና የአቃቤ ሕግ የአይን ምስክሮች  ድርጊት ፈፃሚዎችን በወቅቱ ስለመለየታቸው ሳይመሰክሩ ሰምተናል በማለታቸው ብቻ ጥፋተኛ መባላችን ያላግባብ ነው የሚለውን በወንጀል ጉዳይ የሚቀርብ ማስረጃ ከሚመዘንበት መርህ ጋር በማጣቀስ ነው፡፡

 

በመሰረቱ በአንድ የወንጀል ጉዳይ የሚቀርብ ማስረጃ በቂና አሣማኝ በሆነ ሁኔታ የወንጀል ድርጊቱ መፈፀሙንና የወንጀል ድርጊቱን ፈፃሚውን ማንነት በትክክል ለይቶ ማሳየት ያለበት ስለመሆኑ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 141 ድንጋጌ ይዘትንና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡አንድ ሰው ለወንጀል ድርጊት ኃላፊ ተብሎ ቅጣት ሊወሰንበት የሚገባው ወንጀል መስራቱ ወይም መፈፀሙና ተሰራ ወይም ተፈፀመ የተባለው ወንጀል ደግሞ በተከሳሹ መፈፀሙ በበቂና በአሳማኝ ሁኔታ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23(4)፤32፣40፤57፣ 58(1) እና ከወ/መሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 141፣142 እና 149 ድንጋጌዎች አገላለፅና መንፈስ መመልከት የምንችለው ጉዳይ ነው፡፡ማንም ሰው በዋና ወንጀል አድራጊነት ወንጀል እንዳደረገ የሚቆጠረው ወንጀሉን እርሱ ራሱ በቀጥታ ቢያደርግ ወይም በቀጥታ ባያደርግም እንኳን በመላ ሀሳቡና አድራጐቱ በወንጀሉ ድርጊትና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተከፋይ በመሆን ወንጀሉን  የራሱ ያደረገ ሆኖ ሲገኝ እንደሆነ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ለ/ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ከሳሽ የሆነው አቃቤ ሕጉም ይህንኑ በሕጉ የተጣለበትን ግዴታ መወጣት አለበት፡፡

 

አመልካቾች ሟችን በቀጥታ መትተው ስለመግደላቸው አይተናል የሚል የአቃቤ ሕግ ምስክር ባይኖርም ሟች ጋር በእለቱ በአረቄ ቤት ሲጨቃጨቁ እንደነበር፣ሟች ምራቅ ሲተፋም ምራቁ ደም እንደሚሆን ተናግረው እንደነበር በአቃቤ ሕግ ምስክሮች ተገልፆአል፡፡ይሁን እንጂ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች በወቅቱ ከሟች ጋር ጠብ አስነስተው የነበሩትን ሰዎች ማንነት የገለፁ ቢሆንም ለሟቹ ህልፈተ ሕይወት እያንዳንዱ አመልካች የነበረውን ተሳትፎ ያልተናገሩ ከመሆኑም በላይ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል በሁሉም አመልካቾች ላይ እንደ አከባቢ ማስረጃ የሚወሰድ ነው ቢባልም ማስረጃው በ2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች ላይ ግን ጥንካሬ የሌለው ሁኖ ተግኝቷል፡፡በሌላ አነጋገር የተጠሪ ምስክሮች በወቅቱ ስለነበረው አጠቃላይ ሁኔታ /Circumstantial Evidence/ የምስክርነት ቃል ሰጥተው የተመለሱ ቢሆንም ከጠቡ መነሻ ውጪ ከጠቡ በኋላ 2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች የነበራቸውን ሚና በግልጽ የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ በአገራችን የህግ ሥርዓት ምስክሩ ስለአጠቃላይ ሁኔታዎች በአይኑ የታዘበውን በጆሮው የሰማውንና የሚያውቀውን ፍሬ ጉዳይ ሊመሰክር እንደሚችልና የምስክሩም ቃል ህጋዊ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 137 ንዑስ አንቀፅ 1 ድንጋጌ ይዘት መንፈስና ዓላማ ለመረዳት ይቻላል፡፡ይሁን እንጂ በ2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች ላይ በአቃቤ ምስክሮች የተሰጠው የምስክርነት ቃል በአረቄ ቤት የነበረውን ጠብ እና ሟች ምራቅ ሲተፋ ይህ ምራቅ ደም ሊሆን እንደሚችል አመልካቾች ከመናገራቸው ውጪ በድርጊቱ ወቅት ወይም በኋላ 2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች የፈፀሙትን አድራጎት የሚያሳይ አይደለም፡፡ስለሆነም በ2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች ላይ የቀረበው የአቃቤ ሕግ ማስረጃ በወንጀል ሕግ የሚቀርብ ማስረጃ ስለጉዳዩ ለማስረዳት በቂና አሳማኝ ማስረጃ ነው ብሎ ለመደመድም የሚያስችል ሊሆን ይገባል የሚለውን መለኪያ ያሟላ ነው ለማለት አልተቻለም፡፡ስለሆነም በእነዚህ አመልካቾች የተሰጠው የጥፋተኛነት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡


1ኛውን አመልካች ታምራት ደምሴን በተመለከተ ግን 1ኛ፣2ኛ እና 3ኛ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች አመልካቹ በወቅቱ ስለነበረው አጠቃላይ ሁኔታ ከሰጡት የምስክርነት ቃል በተጨማሪ አመልካቹ ከወንጀል ድርጊቱ በኋላ በፖሊስ ተይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተይዞ ከገባ  በኋላ ወንጀሉን መፈፀሙንና እንዴት እንደፈጸመ ጭምር ሲገልፅ እንደነበር 5ኛ እና 6ኛ የአቃቤ ምስክሮች ከመሰከሩት ቃል መረዳት የሚቻል ሁኖ ስለተገኘ አመልካቹ በሟቹ ህልፈተ ሕይወት ተሳትፎ እንደነበረው በዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ተደጋጋፊነትና ተመጋጋቢነት ባለው ጠንካራ የአከባቢ ማስረጃ የተረጋገጠ ሁኖ አግኝተናል፡፡በመሆኑም አመልካች ታምራት ደምሴ በቀጥታ የወንጀሉ ተሳታፊ ሁኖ በመላ ሀሳቡ የወንጀሉን ድርጊት እንዲሁም ውጤቱን የራሱ ያደረገ ስለሆነ አመልካቹ ለወንጀል ድርጊቱ ኃላፊ ልባል አይገባም በማለት ያቀረበው ቅሬታ ተቀባይነት ሊሰጠው የሚገባ ሁኖ አልተገኘም፡፡

 

አንደኛውን ጭብጥ በተመለከተ ስናጠቃልለው 2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች ለወንጀሉ ድርጊት ኃላፊ የተባሉት ዓቃቤ ሕግ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 141 በሚያስቀምጠው የማስረጃ መለኪያ መሰረት የአመልካቾችን ተሳትፎ ባላስረዳበትና በሕጉ የተጣለበትን ግዴታ ባልተወጣበት ሁኔታ በመሆኑ በእነዚህ አመልካቾች ላይ የተሰጠው የጥፋተኛነት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሲሆን 1ኛ አመልካች ግን ሟች ከመሞቱ በፊትና ሲሞት የነበረው የወንጀሉ ተሳትፎ በሚገባ የተረጋገጠ በመሆኑ በሰው ግድያ ወንጀል ተጠያቂ መደረጉ የሚነቀፍ ሁኖ አይደለም ብለናል፡፡

 

 ሁ ለተ ኛ ውን ጭብጥ በተመለ ከተ፡ - የስር ፍርድ ቤቶች 1ኛ አመልካችን ተጠያቂ ያደረጉት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 539(1(ሀ)) ስር ነው፡፡

 

በመሰረቱ የሰው ግድያ ወንጀል በወንጀል ሕግ አንቀፅ 539(1(ሀ)) መሰረት ድርጊት ፈጻሚውን ሊያስጠይቅ የሚችለው ድርጊቱ ሆነ ተብሎ አስቀድሞ በማሰብና በመዘጋጀት ሲፈፀም ወይም በአንቀጽ 84 ወይም 86 ስር የተመለከቱት አክባጅ ሁኔታዎች በተገኙበት ሁኔታ የወንጀል አድራጊው በተለይ ጨካኝ፣ነውረኛ ወይም አደገኛ መሆኑን ሲያመለክቱ ስለመሆኑ ተጠቃሹ ድንጋጌ በግልጽ ያሳያል፡፡ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው በድንጋጌው ስር የተመለከቱት የወንጀሉ ማቋቋሚያ ነጥቦች በየራሳቸው መቆም የሚችሉ ነጥቦች ስለመሆናቸው ነው፡፡

 

የወንጀል ህግ አንቀጽ 540 ድንጋጌ ሲታይ ደግሞ፡-

”ማንም ሰው አገዳደሉ በአንቀጽ 539 የተመለከተውን ያህል ከባድ ወይም በአንቀጽ 541 የተመለከተውን ያህል ቀላል ባልሆነ ሁኔታ አስቦ ሌላ ሰውን የገደለ እንደሆነ፤ ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል በሚል አስቀምጧል፡፡

 

በመሠረቱ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 539 እና 540 መሠረት የሚፈፀሙ ግድያዎች ሆነ ተብሎ ወይም በማወቅ /አስቦ/ የሚሰሩ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ሁለቱ አንቀፆች ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ነገር ግን ሁለቱን አንቀፆች የተለያዩ የሚያደርጓቸው መሰረታዊ ነጥቦች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው በወ.ህ.አንቀጽ 539/1/ሀ/ መሠረት ጥፋተኛ ሆኖ እንዲገኝ በዚሁ አንቀጽ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ተሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡እነዚህን ሁኔታዎች ደግሞ ሰውየው ድርጊቱን ለመፈፀም ካነሣሣው ሃሣብ እና ከድርጊቱ አፈፃፀም አንፃር በመመርመር የድንጋጌውን ትክክለኛ አፈጻጸም መለየት ይቻላል፡፡በድንጋጌው ስለሃሳብ ሁኔታ የሚገልጹትን ሁኔታዎች ስንመለከትም አስቀድሞ የማሰብ ሁኔታ፤ ቂም በቀል፤ጥላቻ፤ ቅናት ወዘተ----የሚሉ የሚገኙ ሲሆን ከባድ የድርጊት አፈፃፀም መኖርን የሚያመላክቱ ነጥቦች ደግሞ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 84


ስር የተመለከቱትና በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ በአንቀጽ 86 መሠረት ከባድ ምክንያቶች ናቸው ብሎ የሚቀበላቸውን ሁኔታዎች የሚያካትቱ ናቸው፡፡

 

አንድ ሰው ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት የሃሣብ ሁኔታዎች ወይም የድርጊት አፈፃፀም አንዱን እንኳ ፈጽሞ ቢገኝ እና ይህም ሁኔታ ሲታይ ገዳዩ “በተለይ” ጨካኝ፤ ነውረኛ ወይም አደገኛ የሚያሰኝ አይነት ሆኖ ከተገኘ በአንቀጽ 539/1/ሀ/ መሠረት ጥፋተኛ ሊሰኝ እና ለዚሁ አድራጎት በሕጉ የተመለከተው ቅጣት ውሳኔ ሊተላለፍበት ይገባል፡፡

 

አንቀጽ 539/1/ሀ/ በቅድሚያ እንዲሟላ የሚፈልገው መሰረታዊ ነጥብ የአገዳደሉ ሁኔታ አድራጊው በተለይ ጨካኝ፤ ነውረኛ ወይም አደገኛ መሆኑን የሚገልጽ ሆኖ መገኘትን ነው፡፡በድንጋጌው ስር “በተለይ” የሚለው ቃል የሚያስገነዝበው ከተራ አገዳደል ወይም የሃሣብ ሁኔታ ውጭ በሆነ አድራጐት ወይም ለጥቃት መገልገያ የተደረገው መሣሪያ በሟች ላይ ስቃይና መከራ ማሣደር እንዳለበት፣ ግድያውም ከተራው ሁኔታ የተለየ እንደነበር የሚያመለክት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡፡ በህጉ በተለይ ጨካኝ ነውረኛ ወይም አደገኛ መባሉ የአገዳደሉ ሁኔታና የመግደያው መሣሪያ አደገኛነት፣ ፍፁም ጨካኝነትን፤ ነውረኛነትን ወይም የተጋነነ አደገኛነትን ማሳየት እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው፡፡ስለሆነም የወ.ሕ.አንቀፅ 539(1(ሀ)) የማክበጃ ልዩ ሁኔታዎች በመኖራቸው ምክንያት ሆን ተብሎ የተፈፀመው ግድያ “ከባድ የሰው ግድያ” የሚባልበትን ምክንያቶች የያዘ ነው፡፡እነዚህ ልዩ ሁኔታዎች በሌሉበት አንድን ተከሣሽ በዚህ አንቀጽ ስር ጥፋተኛ ሊባል የማይችል መሆኑን የሕጉ ይዘትና መንፈስ ያሳያል፡፡ ከእነዚህ እና በተጠቃሹ አንቀፅ በፊደል "ለ" እንዲሁም "ሐ" ስር ከተመለከቱት የድንጋጌዎቹ ማቋቋሚያዎች ውጪ ሆን ተብሎ የሚደረግ ሰው የመግደል ወንጀል የሚያስቀጣው በአንቀጽ 540 ስር ነው፡፡

 

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመጣም አመልካች ሟችን ለመግደል አስቀድሞ ሐሳብ ያልነበረው መሆኑ ግልጽ ሲሆን አፈጻጸሙ ሲታይም በተለይ ጨካኝነት ያለበት ነው ለማለት የሚያስችል ስለመሆኑ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል አያሳይም፡፡እንዲሁም የአገዳደሉ ሁኔታና የመግደያው መሣሪያ አደገኛነት ፍፁም ጨካኝነትን፤ ነውረኛነትን ወይም የተጋነነ አደገኛነትን አያሳይም፡፡እንዲህ ከሆነ ደግሞ አድራጎቱ በእለቱ በተፈጠረው ያለመግባባት በቀላሉ ለህልፈት የሚዳረግ የሰውነት ክፍል በዱላ በመምታት የሆነው ይሁን በማለት የፈፀመውና በተራ የሰው ግድያ ወንጀል ስር የሚሸፈን እንጂ በግፍ ሰው የመግደል ወንጀል በሚያስጠይቅበት የወንጀል ሕግ አንቀፅ 539(1(ሀ)) ድንጋጌ መሰረት የሚጠየቅበትን አግባብ አላገኘንም፡፡ስለሆነም የበታች ፍርድ ቤቶች 1ኛ አመልካችን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 539(1ሀ) ስር ጥፋተኛ ያሉት አጠቃላይ የድርጊቱን አፈፃጸም ከድንጋጌው ይዘትና መንፈስ ጋር ሳያገናዝቡ ሁኖ ስለአገኘነው በዚህ ረገድ የተሰጠውን ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195(2)(ለ-2) ድንጋጌ መሰረት በመለወጥ 1ኛ አመልካች(ታምራት ደምሴ) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 ድንጋጌን የተላለፈ ጥፈተኛ ነው በማለት ወስነናል፡፡

 

ቅጣትን በተመለከተ 1ኛ አመልካች ሊቀጣ የሚገባው በዚህ ችሎት ጥፋተኛ በተባለበት የሕግ ድንጋጌ መሰረት ነው፡፡አመልካች ተራ የሆነ የሠው ግድያ ወንጀል መፈፀሙ በሚገባ ተረጋገጧል፡፡በወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 ስር ጥፋተኛ የተባለ አጥፊ ደግሞ ሊቀጣ የሚገባው ከአምስት አመት እስከ ሃያ አመት ጽኑ እስራት ነው፡፡

 

በመሠረቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ የወንጀል ህግ የአገሪቱን  የወንጀል ህግ ግብ በአዋጅ ቁጥር 414/1996 አንቀጽ 1 ስር ሲደነግግ “የወንጀል ህግ ግብ ወንጀል


እንዳይፈፀም መከላከል ሲሆን ይህንን የሚያደርገው ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ እርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው በማድረግ ነው” በማለት ያስቀምጣል፡፡ ህጉ በአንቀጽ 87 ላይ ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎች ህጉ ሊደርስበት ያሠበውን ዓላማ ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ በህጉ መንፈስ መሠረት መፈፀም እንዳለባቸው በመርህ ደረጃ ይደነግጋል፡፡ይኸው አንቀጽ ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎቹ ምን ጊዜም ሠብዓዊ ክብርን በሚጠብቅ መንገድ መፈፀም እንደሚኖርባቸው ያስገነዝባል፡፡  የወንጀል ህጉ አንቀጽ 88 ሲታይም የቅጣቶች እና የጥንቃቄ እርምጃዎች አወሣሠንን በተመለከተ ዘርዘር ያሉ ንዑስ ድንጋጌዎችን አካቶ ይዟል፡፡ በዚህ አንቀጽ ስር ያሉ ንዑስ አንቀጾች የሚያሣዩት ፍርድ ቤቱ ቅጣቶችንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን የሚወሰነው የወንጀል ህጉን ጠቅላላ ክፍል ድንጋጌዎችን እንዲሁም ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው የሚደነግጉትን የልዩ ክፍሉ ድንጋጌዎች መሠረት በማድረግ መሆኑን፣ ቅጣት ሊወሰን የሚገባው የወንጀል አድራጊውን ግላዊ የአደገኛነት መጠን ያለፈ የህይወት ታሪኩን ወንጀል ለማድረግ ያነሣሡትን ምክንያቶችና የአሣቡን ዓላማ የግል ኑሮውን ሁኔታ፣ የትምህርቱን ደረጃ፣ እንዲሁም የወንጀሉን ከባድነትና የአፈፃፀሙን ሁኔታዎች በማመዛዘን መሆኑን፣ የወንጀል ህግ ልዩ ክፍል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ፍርድ ቤቱ እጅግ ቀላል ከሆነው ቅጣት አንስቶ እስከ ከባዱ ድረስ ያለውን በጥንቃቄ በመመርመር ለእያንዳንዱ ጉዳይ ተገቢ የሆነውን ቅጣት እንደሚወስን የቅጣት አወሳሳን ደንቡ በግልፅ ያሳያል፡፡ከላይ እንደተገለጸው የወንጀል ቅጣት የሚወሰነው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 88(2)ስር የተመለከቱትን ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ይህ ችሎትም እነዚህ ሁኔታዎችን ተመልክቷል፤አመዛዝኗልም፡፡ አመልካች ጥፋተኛ የተባለበት ድንጋጌ ድርጊቱ በተፈጸመበትና ክርክሩ በስር ፍርድ ቤት ታይቶ ዳኝነት በተሰጠበት ጊዜ በነበረው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ደረጃ ያልወጣለት የነበረ ሲሆን በተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ደግሞ ደረጃ የወጣለት ነው፡፡እኛም ጉዳዩን ከዚሁ ከአዲሱ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ አንፃር ተመልክተናል፡፡

 

ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው አመልካች ከሟች ጋር ለጠብ የተዳረገው በሟቹ ስድብ ምክንያት ሲሆን ይህም ለወንጀል ድርጊቱ መንስኤው ሟቹ መሆናቸውን የሚያሳይ  ሁኖ ለድርጊቱ አፈጻጸም አመልካች የተጠቀመበት መሳሪያም ዱላ የነበረ ሁኖ የዱላው አይነትና አደገኛነትም በማስረጃ ያልተረጋገጠ መሆኑ ሲታይ አፈፃፀሙ የራሱ የሆነ የተለየ ዘዴ የነበረው መሆኑን የማያሳይ በመሆኑ በመመሪያው መሰረት የወንጀሉ ደረጃው 2 ሁኖ ይሄው ደረጃ በእርከን 23 ስር የሚወድቅ ነው፡፡በዚሁ እርከን ደግሞ የፍርድ ቤቱ የፍቃድ ስልጣን ከስድስት አመት እስከ ሰባት አመት ከሁለት ወር ነው፡፡ከዚሁ ፍቅድ ስልጣን ውስጥ የመነሻ ቅጣቱን ይዘን የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶችን ባለመኖራቸው እርከኑን ከፍ ማድረግ ያለመቻሉን ተገንዝበናል፡፡በሌላ በኩል አመልካች ጠቅላላ የቅጣት ማቅለያም ሆነ ልዩ የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ያሉት መሆኑን በስር ፍርድ ቤት በማስረጃ ተደግፎ የተመዘገበለት ያለመሆኑን ከውሳኔው ግልባጭ ተገንዝበናል፡፡በመሆኑም በእርከን 23 ስር ካለው የፍርድ ቤቱ ፍቅድ ስልጣን ውስጥ 1ኛ አመልካችን (ታምራት ደምሴን) ያርማል፣መሰል ወንጀለኞችን ያስጠንቅቃል ያልነው የቅጣት መጠን ሰባት አመት ሁኖ ስለአገኘን አመልካች በጉዳዩ ላይ የታሰረው ካለ የሚታሰብለት ሁኖ በዚሁ የቅጣት መጠን እንዲቀጣ በማለት ከላይ በዝርዝር በተመለከቱት ህጋዊ ምክንያቶች የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት በማሻሻል ተከታዩን ወስነናል፡፡


 

 

 ው ሣኔ

 

1. በመተከል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 04545 ሚያዚያ 5 እና 6 ቀን 2003 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 02856 ግንቦት 02 ቀን 2003 ዓ/ም፣በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 03200 መስከረም 11 ቀን 2004 ዓ/ም በትዕዛዝ የፀናው የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195(2)(ለ-2) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2. 2ኛ አመልካች በሪሁን ደምሴ፣3ኛ አመልካች ታደለ ሽቱ ሟች ኤርሚያስ ሃይሉን ስለመግደላቸው በበቂና አሳማኝ ሁኔታ ስላልተመሰከረባቸው በእነዚህ አመልካቾች ላይ የተሰጠውን የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195(2)(ለ-1) መሰረት ሙሉ በሙሉ በመሻር አመልካቾቹን በነጻ እንዲሰናበቱ በማለት ወስነናል፡፡አመልካቾቹ በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ መሆኑ ከተረጋገጠ ወዲያውኑ ከእስር እንዲፈቱ ተገልፆ የመፍቻ ትዕዛዝ ለክፍሉ ማረሚያ ቤት ይድረሰው ብለናል፡፡ይጻፍ፡፡

3. 1ኛ አመልካች ታምራት ደምሴ በሟች ኤርሚያስ ኃይሉ ህልፈት ተጠያቂ መደረጉ በአግባቡ ተመስከሮበት ሲሆን የአመልካቹ አድራጎት የሚሸፈነው ግን በወ/ሕ/አንቀጽ 539(1(ሀ) ሳይሆን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 540 ስር ነው በማለት በዚሁ የሕግ ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ በማድረግ በጉዳዩ ላይ የታሰረው ማናቸውም ጊዜ የሚታሰብለት  ሁኖ በሰባት አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስነናል፡፡

4. በ1ኛ አመልካች በዚህ ችሎት ተሻሽሎ በተወሰነው የቅጣት ውሳኔ መሰረት ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ለክፍሉ ማረሚያ ቤት ይድረስ ብለናል፡፡ይጻፍ፡፡

 

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡