92296 criminal law/ concurrent offences/ aggravating punishment/

የወንጀል አድራጊው በአንድ ድርጊት ከአንድ ጊዜ በላይ አደራርቦ የህግ ድንጋጌዎችን የጣሠ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የአካባቢ ሁኔታዎችን ሲመረምር በተለይም ወንጀለኛው አስቦና አቅዶ ህግ መጣሱን ወይም ግልጽ የሆነ መጥፎፀባይ ማሣየቱን ባመነ ጊዜ ቅጣቱን አክብዶ መወሠን ሥለመቻሉ፣

 

ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመው በተገኙ ጊዜ ፍርድ ቤቶች የድምር ውጤት የቅጣት አወሣሠን መርህን ተፈጻሚ ማድረግ ያለባቸው ሥለመሆኑ፣

 

በተደራራቢ ወንጀሎች የሚወሠነው ቅጣት ድምር ውጤት ከሃያ አምስት አመት ጽኑ እስራት ሊበልጥ የማይችል ሥለመሆኑ፣

 

የወ/ህ/ቁ. አንቀጽ 184/1/ለ/፣ 108/1/፣ 187/1/፣65

የሰ//.92296 ህዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካቾች፡- 1. አንዱዓለም አራጌ

 

2. ናትናኤል መኮንን     ጠበቆች አቶ ደርበው ተመስገንና አቶ አበበ ጉታ ቀረቡ

 

3. ክንፈሚካኤል ደበበ

 

ተጠሪ፡- የፌደራል ዓቃቤ ህግ አቶ ወንድምአገኝ ብርሃኑ ቀረቡ

 

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች በየግላቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወንጀል መዝገብ ቁጥር 112546 የሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔና፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 83593 ጉዳዩን በይግባኝ ካየ በኋላ የሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ሥህተት ያለበት ሥለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልን በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ ተጠሪ አመልካቾች  የሽብርተኝነትና ከፍ ያለ የመክዳት ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ያቀረበውን የወንጀል ክስና ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ በሥር ፍርድ ቤት በቀረበው የወንጀል መዝገብ ቁጥር 112546 ተጠሪ ከሳሽ፣አንደኛው አመልካች አንደኛ ከሳሽ፣ሁለተኛው አመልካች ሁለተኛ ተከሳሽ እና ሶስተኛው  አመልካች አምስተኛ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡

 

1. ከሥር የክርክሩን አመጣጥ ከመዝገቡ እንደተረዳነው፣ተጠሪ በሥር ፍርድ ቤት አመልካቾችና ሌሎች ተከሳሾች በአራት ወንጀል ክሶች የጠቀሳቸውን የወንጀል ሕግና የአዋጅ ቁጥር 652/2001 ድንጋጌዎች በመተላለፍ ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ክስ አቅርቧል፡፡ ተጠሪ አመልካቾችና በሌሎች ተከሳሾች ላይ ካቀረባቸው አራት ክሶች ውስጥ፣ አመልካቾች በዚህ ክርክር ተሳታፊ ካልሆኑት ተከሳሾች ጋር በመሆን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1/ሀ/፣ አንቀጽ 38 እና በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 252 ንዑስ አንቀጽ 1/ሀ/ በመተላለፍ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሚስጥሮችን በመሰብሰብ ለኤርትራ መንግስት አሳልፈው በመሰጠት የስለላ ወንጀል ፈጽመዋል በማለት በአምስተኛው ተራ ቁጥር ያቀረበውን የወንጀል ክስ የሚያስረዳ በቂ ማስረጃ ባለማቅረቡ በሥር ፍርድ ቤት አመልካቾችና ሌሎቹ   ተከሳሾች


በነጻ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት የተጠሪን ክስና ማስረጃ፣ የአመልካቾችን የመከላከያ ማስረጃ በመስማት፣በመመርመርና በመመዘን በአመልካቾች ላይ ጥፋተኛኝነትና የቅጣት ውሳኔ የሰጠው ተጠሪ ባቀረበባቸው በሶስት የወንጀል ክሶች የተገለጹትን የወንጀል ድርጊቶች መፈጸማቸው በበቂ ማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል በማለት ነው፡፡

2. የሥር ፍርድ ቤት አመልካቾች ከሌሎቹ በዚህ ክርክር ተሳታፊ ካልሆኑ ተከሳሾች ጋር በመሆን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀፅ 1 እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 4፣ የተመለከተውን በመተላለፍ፣የሥር ፍርድ ቤት አመልካቾች ከሌሎቹ በዚህ ክርክር  ተሳታፊ ካልሆኑ ተከሳሾች ጋር በመሆን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀፅ 1 እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2፣የተመለከተውን በመተላለፍና በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) እና አንቀጽ 248(ለ) የተመለከተውን በመተላለፍ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል ክሱ የዘረዘራቸውን የወንጀል ድርጊቶች ዋና ወንጀል አድራጊና ተካፋይ በመሆን የፈጸሙ መሆናቸው በበቂ ማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል በማለት የጥፋኝነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

3. የሥር ፍርድ ቤት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው የቅጣት መመሪያ ቁጥር

1/2002ን  መሰረት በማድረግ አንደኛው አመልካች ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘባቸው፣

ሀ) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4፣ በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ መካከለኛ ነው ብሎ አስልቶ ያገኘው የቅጣት መነሻ አሥራ ዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት፣

 

ለ) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና ስለ ጸረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2፣ በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ  መካከለኛ ነው ብሎ  አስልቶ ያገኘው የቅጣት መነሻ ሰባት ዓመት ጽኑ እስራትና፤

 

ሐ) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና አንቀጽ 248 (ለ) በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ መካከለኛ ነው ብሎ አስልቶ ያገኘው  የቅጣት መነሻ አሥራ ሶስት ዓመት ጽኑ እስራት፣በወንጀል ሕግ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) መሰረት ሲደመር ሰላሳ ዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚሆን በቅጣት ውሳኔው አመላክቷል፡፡ የስር ፍርድ ቤት የጽኑ እስራት ቅጣት ከሃያ አምስት የማይበልጥ መሆኑን በመግለጽ፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው የቅጣት መመሪያ ቁጥር 1/2005 ከፍተኛው ጣሪያ ሃያ አምስት ዓመት እርከን 37 ላይ ይወድቃል፡፡ አንደኛ አመልካች ከዚህ በፊት በጽኑ እስራት ተቀጥቶ የነበረ በመሆኑ አንድ እርከን ከፍ ብሎ እርከን 38 ላይ እንደሚወድቅ በውሳኔው አስፍሯል፡፡ የስር ፍርድ ቤት አንደኛ አመልካች ተቀባይነት ያለው የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ያላቀረበ በመሆኑ በእርከን 38 ከተቀመጠው ቅጣት በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

4. ሁለተኛው አመልካች በተመለከተ፣ የሥር ፍርድ ቤት ሁለተኛ አመልካች ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘባቸው፤

ሀ) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ4፣ በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ መካከለኛ ነው ብሎ  አስልቶ ያገኘው የቅጣት መነሻ  አሥራ ዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት፣


ለ) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና ስለ ጸረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2፣ በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ብሎ  አስልቶ ያገኘውን ቅጣት ስምንት ዓመት ፅኑ እስራትና፣

 

ሐ) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና አንቀጽ  248(ለ) በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ መካከለኛ ነው ብሎ አስልቶ ያገኘው  የቅጣት መነሻ አሥራ ሶስት ዓመት ጽኑ እስራት፣ መሆኑን በቅጣት ውሳኔው አመላክቷል፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(1) መሰረት ሲደመር አርባ ዓመት እንደሆነ ነገር ግን የጽኑ እስራት ከሃያ አምስት የማይበልጥ መሆኑን በመግለጽ፤የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው የቅጣት መመሪያ ቁጥር 1/2002 እርከን 37 ላይ የሚወድቅ መሆኑን፣ በዓቃቤ ሕግ በኩል የቅጣት ማክበጃ ያልቀረበ መሆኑንና፤ሁለተኛ አመልካች ወንጀል ፈጽሞ የማያውቅ  በመሆኑ አንድ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ያለው መሆኑን ገልጾ ሶስት እርከን ተቀንሶለት እርከን 34 ላይ ይወድቃል፡፡ በዚህ እርከን የተመለከተው የቅጣት ሬንጅ ከ 15 ዓመት እስከ 18 ዓመት የሚደርስ መሆኑን አስፍሮ ሁለተኛ አመልካች 18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

5. ሶስተኛው አመልካች በተመለከተ፣ የሥር ፍርድ ቤት ሶስተኛ አመልካች ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘባቸው፣

ሀ) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4፣ በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ብሎ አስልቶ ያገኘው የቅጣት መነሻ ሃያ ሁለት ዓመት ጽኑ እስራት፣

 

ለ) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2፣ በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ መካከለኛ ነው ብሎ አስልቶ ያገኘው  የቅጣት መነሻ ሥምንት ዓመት ጽኑ እስራትና፣

 

ሐ) የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣እና አንቀጽ 248(ለ) በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ብሎ አስልቶ ያገኘው የቅጣት መነሻ አሥራ ዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት መሆኑንና፣በወንጀል ሕግ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) መሰረት ሲደመር አርባ ዘጠኝ ዓመት መሆኑን ቅጣት ውሳኔው አመላክቷል፡፡ ነገር ግን የጽኑ እስራት ከሃያ አምስት ስለማይበልጥ፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው የቅጣት መመሪያ ቁጥር 1/2002 እርከን 37 ላይ ይወድቃል፡፡ ሶስተኛ አመልካች በችሎት መድፈር ስምንት ወር በመቀጣቱ የዘወትር ጸባዩ መልካም ነው ብሎ ለመያዝ የማይቻል መሆኑን ገልጾ በእርከን 37 የተቀመጠው የቅጣት ሬንጅ ከሃያ ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ነው፡፡ ሶስተኛ አመልካች  የፈጸማቸው የወንጀል ክብደቶችና ግላዊ ሁኔታ በማየት በሃያ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

6. አመልካቾች የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን የጥፋተኝነትና የቅጣት  ውሳኔ  በመቃወም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርበዋል፡፡ይግባኝ ሰሚው ችሎት የአመልካቾችን ይግባኝ በዚህ ክርክር ተሳታፊ ካልሆኑት ሌሎች ይግባኝ ባዮች ጋር በማጣመር አይቷል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የሥር ፍርድ ቤት አመልካቾች ከሌሎቹ በዚህ ክርክር ተሳታፊ ካልሆኑ ተከሳሾች ጋር በመሆን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2፣የተመለከተውን  በመተላለፍ


ወንጀል ፈጽመዋል በማለት የሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ስህተት ያለበት ነው በማለት የጥፋተኝነት ውሳኔውን ሽሮ አመልካቾች በነጻ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሥር ፍርድ ቤት አመልካቾች የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣እና ስለ ጸረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4፣ እና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣እና አንቀጽ 248(ለ) በመተላለፍ ወንጀል ፈጽመዋል በማለት የሰጠውን የጥፋተኝነት ውሳኔ አጽንቶታል፡፡

7. ይግባኝ ሰሚው ችሎት አንደኛ፣ሁለተኛና ሶስተኛ አመልካቾች የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4፣ እና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና አንቀጽ 248(ለ) በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል  የነበራቸው ተሳትፎ መካከለኛ ነው በማለት ወስኗል፡፡

ሀ) አንደኛ አመልካች በሁለቱ ወንጀሎች መካከለኛ ደረጃ ላይ ተመድቦ በሥር ፍርድ ቤት የተወሰነበት 32 ዓመት ጽኑ እስራት መነሻ ቅጣት በወንጀል ሕጉ ከተመለከተው ከሃያ አምስት ዓመት በላይ በመሆኑ ቅጣቱ ከእርከን 37 እንደሚሆንና አንደኛ አመልካች ተቀባይነት ያለው የቅጣት ማቅለያ ያላቀረበና አንድ የቅጣት ማክበጃ ያለበት በመሆኑ በእርከን 38 መነሻ ተደርጎ ቅጣቱ ሲሰላ የሥር ፍርድ ቤት በአንደኛው አመልካች ላይ የሰጠውን የእድሜ ልክ ጽኑ እሥራት የቅጣት ውሳኔ የሚያስለውጥ አይደለም በማለት  ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ለ) ሁለተኛ አመልካችን በተመለከተም የሥር ፍርድ ቤት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና ስለ ጸረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ4፣ በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ መካከለኛ ደረጃ እንደሆነና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ እና አንቀጽ 248(ለ) በመተላለፍ በተፈጸመው ወንጀል የነበረው ተሳትፎ መካከለኛ ደረጃ ነው በማለት ያስቀመጠውን የቅጣት መነሻ እንዳለ በመቀበል፣ በሁለቱ ወንጀሎች የስር ፍርድ ቤት የወሰነው መነሻ ቅጣት ሲደመር ሰላሳ ሁለት ዓመት በወንጀል ሕጉ ከተደነገገው 25 ዓመት በላይ በመሆኑ የስር ፍርድ ቤት ቅጣቱ እርከን 37 መነሻ በማድረግ ሁለተኛው አመልካች ያቀረበውን አንድ ቅጣት ማቅለያ በመቀበል በእርከን 34 ከተቀመጠው የቅጣት ሬንጅ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የስር ፍርድ ቤት የወሰነውን የቅጣት ውሳኔ የሚያስለውጥ አይደለም በማለት ወስኗል፡፡

ሐ) ሶስተኛ አመልካች በተመለከተ በችሎት መድፈር መቀጣቱ አመልካች የወንጀል ሪኮርድ የሌለበብኝ በመሆኑ በቅጣት ማቅለያነት ሊያዝለት እንደሚገባ ያቀረበውን ጥያቄ፣ የሥር ፍርድ ቤት ሶስተኛው አመልካች በችሎት መድፈር ወንጀል ተቀጥቷል በማለት በቅጣት ማቅለያነት አለመያዙ ስህተት መሆኑን ገልጾ ይህ ማቅለያ ሲያዝ ደረጃው ከእርከን 37 ወደ እርከን 34 የሚቀንስ በመሆኑ የስር ፍርድ ቤት የወሰነውና ሃያ አምስት ዓመት ጽኑ እሥራት ቅጣት ተገቢ አይደለም በማለት ወስኗል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን የሃያ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ተሻሽሎ ሶስተኛው አመልካች በአሥራ ስድስት ዓመት ጽኑ እሥራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በሌላ አነጋገር ይግባኝ ሰሚው ችሎት በአንደኛና ሁለተኛ አመልካቾች ላይ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ አጽንቶ፣ በሶስተኛው አመልካች ላይ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ አሻሽሎ ወስኗል፡፡

8. አመልካቾች ሐምሌ 22 ቀን 2005 ዓ.ም ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ ዝርዝር ይዘት ከላይ የተገለጸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት የሚል ነው፡፡ አመልካቾች በጋራ ባቀረቡት የሰበር ማመልከቻ ጥፋተኛ ተብለን የተቀጣነው የግዙፍ ተግባር፣ ሃሳብና የህግ ሁኔታዎች  ባልተሟሉበትና በዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ባልተረጋገጠበት  ሁኔታ     ነው፡፡


ወንጀሎቹን ለመፈጸማችን ከሳሽ በበቂ ማስረጃ ባላስረዳበት ሁኔታ የስር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡት የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ተብሎ ሊሻር ይገባዋል፡፡አመልካቾች በይግባኝ ሰሚው ችሎት ጥፋተኛ የተባልንባቸው ሁለት የህግ ድንጋጌዎች በአንድ ወንጀል የመፈጸም ሃሳብ የተፈጸሙ መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ክስና ማስረጃ የሚያሳይ በመሆኑ በሁለት ወንጀል ጥፋተኛ መባላችን የወንጀል ሕጉን መሰረታዊ መርህና ይህ ሰበር ችሎት የሰጠውን አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሚጥስና መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሥር ፍርድ ቤት አመልካቾች ከሌሎቹ በዚህ ክርክር ተሳታፊ ካልሆኑ ተከሳሾች ጋር በመሆን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2፣ በመተላለፍ ወንጀል ፈጽመዋል በማለት የሰጠውን የጥፋተኝነት ውሳኔ ከሻረ በኋላ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ አጽንቶታል፡፡ አመልካችዎች በስር ፍርድ ቤት በሶስት ወንጀሎች ጥፋተኛ ናቸው ተብለን የተወሰነብን የቅጣት ውሳኔ፣በይግባኝ ሰሚው ችሎት በአንደኛው ወንጀል ነጻ ተብለን በሁለት ወንጀሎች ብቻ ጥፋተኛ በተባልንበት ሁኔታ ሳይሻሻል እንዳለ የሚጸናበት ህጋዊ ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጠው ውሳኔ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት አመልክተዋል፡፡

9. ተጠሪ በበኩሉ አመልካቾች ላቀረቡት የሰበር አቤቱታ የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም የተጻፈ መልስ ሰጥቷል፡፡ ተጠሪ አመልካቾች ከሌሎቹ በዚህ ክርክር ተሳታፊ ካልሆኑ ተከሳሾች ጋር በመሆን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4፣ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) እና አንቀጽ 248(ለ) የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል መፈጸማቸው ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ የግዙፍ ተግባር፣ ሀሳብና የህግ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ጥፋተኛ ተብለናል በማለት ያቀረቡት ክርክር የህግ መሰረት የለውም፡፡ አመልካቾች በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ስለ ጸረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 የፈጸሙት ወንጀል፣ አመልካቾች ከሌሎቹ በዚህ ክርክር ተሳታፊ ካልሆኑ ተከሳሾች ጋር በመሆን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) እና አንቀጽ 248(ለ) የተመለከተውን በመተላለፍ ከፈጸሙት ከፍ ያለ የክዳት ወንጀል የተለያዩ ናቸው፡፡ ሁለቱም ወንጀሎች ራሳቸውን ችለው የሚቆሙ ወንጀሎች በመሆናቸው አመልካቾች በአንደኛው ወንጀል ብቻ ጥፋተኛ  ልንባል  ይገባል በማለት ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ የህግ መሰረት የለውም፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት አመልካቾች ለፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2፣ በመተላለፍ ጥፋተኛ መባል የለባቸውም በማለት  ቢወስንም፣ይግባኝ ሰሚው ችሎት በአመልካቾች ላይ ባጸናቸው ሁለት የወንጀል ድርጊቶች በአንደኛና ሁለተኛ አመልካቾች ላይ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ የሚያስለውጥ አይደለም፡፡ ሶስተኛውን አመልካች በተመለከተ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ አሻሽሎታል፡፡ ስለዚህ የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግልን በማለት  ተከራክሯል፡፡ አመልካቾች መጋቢት 11 ቀን 2006 በተጻፈ የመልስ መልስ በሰበር አቤቱታቸው ያነሷቸውን ነጥቦች በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡

10. ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት፣የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካቾች ላይ ካስተላለፋቸው ሶስት የጥፋተኝነት ውሳኔዎች ውስጥ ለፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን    አዋጅ


ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 1፣ በመተላለፍ ወንጀል የፈጸሙ ጥፋተኞች ናቸው በማለት የሰጠውን የጥፋተኝነት ውሳኔ ሽሮ፤ አመልካቾች ጥፋተኛ መባል የሚገባቸው በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ)፣ አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ1 እና ስለ ፀረ ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4፣ የተመለከተውን በመተላለፍ በማሴር፣ በማነሳሳት፣በማቀድና በማዘጋጀት ወንጀልና በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) እና አንቀፅ 248(ለ) የተመለከተውን በመተላለፍ ከፍ ያለ የክዳት ወንጀል ነው በማለት የጥፋተኝነት ውሳኔ ከሰጠ በኋላ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሶስተኛው አመልካች የሰጠውን ቅጣት ከማሻሻልና ከማስተካከል ውጭ በአመልካቾች ላይ የሥር ፍርድ ቤት በሰጠው የቅጣት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ሳያደርግ መወሰኑ ሕጋዊ መሰረት አለው ወይስ የለውም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

11. ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካቾች በኢ.ፊ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጀውና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ የጦርነት፣የአመጽና ሌሎች የወንጀል ተግባራትን የሚፈጽመው የግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት ውስጥ አመራርና አባል በመሆን፣ በአገር ውስጥ ካሉት የድርጅቱ አመራሮች ጋር በሕቡዕ በመገናኘት፣ የሽብር ተልዕኮ በመቀበል ፣ለዚሁ የሽብር ተግባር አጋዥ የሚሆኑ ሰዎችን በመመልመል፣ ወደኤርትራ ለወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና በመላክ እንደዚሁም ስለ ግንቦት 7 የፖለቲካ ዓላማ፣ጉዞ መመሪያና ወታደራዊ አደረጃጀት ለአባላት ገለጻ በመስጠት፣ የታቀደውን የሽብር ተግባር በቀጥታ በመምራት፣ በህቡዕ የሚተላለፈውን ገንዘብ ተቀብሎ የሽብር ወንጀል ፈጻሚዎች ያስተላለፉና የሽብር ዓላማ ያላቸውን ስብሰባዎችን በመጥራት፣ በመምራትና በተለያዩ የሽብር ተግባሮች ላይ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ዋና ወንጀል አድራጊና ሙሉ ተካፋይ በመሆን፣በማሴር፣ በማነሳሳት፣በማቀድና በማዘጋጀት ወንጀል የፈጸሙ ስለመሆናቸው ፍሬ ጉዳይ ማጣራትና ማስረጃ የመመዘን  ሥልጣን  ባላቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት ተረጋግጦባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አመልካቾች ወሩና ቀኑ  ተለይቶ ከማይታወቅበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ የጦርነት፣ የአመጽና ሌሎች የወንጀል ተግባራትን የሚፈጽመው የግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት ውስጥ አመራርና አባል በመሆን፣ ኢትዮጵያ ጋር በሰላማዊ ሁኔታ ሳይሆን በጦርነት ሁኔታ ከሚኖረውና በጠላትነት በመሰለፍ በማናቸውም መንገድ ኢትዮጲያን የማተራመስ አጀንዳ ካለው የኤርትራ መንግስት ጋር በህቡዕ በመገናኘት፣ለኤርትራ መንግስት የሚጠቅሙ የተለያዩ ተግባራትን ይፈጽሙ እንደነበር ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት ተረጋግጦባቸዋል፡፡

12. እኛም አመልካቾች ከላይ የተገለጹትን ሁለት ወንጀል ድርጊቶች የፈጸሙ ስለመሆናቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የደረሱበትን የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና መደምደሚያ ሙሉ በሙሉ እውነት ናቸው በማለት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 3(ሀ) እና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 መሰረት በመቀበል እነዚህ አመልካቾች የፈጸሟቸው ሁለት ድርጊቶች ጥፋተኛ የሚያስብሉት በአንድ ወንጀል ነው ወይስ በሁለት ወንጀል የሚለውን ነጥብ መርምረናል፡፡ አመልካቾች በአሸባሪነት የተፈረጀው የግንቦት 7 ድርጅት  ውስጥ  አመራርና  አባል በመሆን፣ በአገር ውስጥ ካሉት የድርጅቱ አመራሮች ጋር በሕቡዕ በመገናኘት፣የሽብር ተልዕኮ በመቀበል፣ለዚሁ የሽብር ተግባር አጋዥ የሚሆኑ ሰዎችን በመመልመል፣ ወደ ኤርትራ


ለወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና በመላክ እንደዚሁም ስለ ግንቦት 7 የፖለቲካ ኣላማ፣ ጉዞ መመሪያና ወታደራዊ አደረጃጀት ለአባላት ገለጻ በመስጠት ፣ የታቀደውን የሽብር ተግባር በቀጥታ በመምራት፣ በህቡዕ የሚተላለፈውን ገንዘብ ተቀብሎ የሽብር ወንጀል ፈጻሚዎች ያስተላለፉና የሽብር ዓላማ ያላቸውን ስብሰባዎች በመጥራትና በመምራት በተለያዩ የሽብር ተግባሮች ውሳኔ በማሳለፍ የፈጸሙት የማሴር፣ የማነሳሳት፣የማቀድና የማዘጋጀት ድርጊት ራሱን የቻለ ወንጀል ድርጊት እንደሆነና ከአሥራ አምስት ዓመት በማያንስ ጽኑ እስራት፣ በእድሜልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ መሆኑን ከአዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 4፣  ድንጋጌዎች ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡

13. አመልካቾች ኢትዮጵያ ጋር በሰላማዊ ሁኔታ ሳይሆን በጦርነት ሁኔታ ከሚኖረውና በጠላትነት በመሰለፍ በማናቸውም መንገድ ኢትዮጵን የማተራመስ አጀንዳ ካለው የኤርትራ መንግስት ጋር በህቡዕ በመገናኘት፣ ለኤርትራ መንግስት የሚጠቅሙ የተለያዩ ተግባራትን መፈጸማቸው ራሱን የቻለ የወንጀል ድርጊትና በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) እና አንቀጽ 248(ለ) መሰረት ከአምስት ዓመት በማያንስ ጽኑ እስራት፣ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ አመልካችዎች ሁለቱም የወንጀል ድርጊቶች የተፈጸሙት በአንድ ወንጀል የመፈጸም ሃሳብ ማለትም ሕገ  መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል የመናድ ኃሳብ በመሆኑ በሁለቱ ወንጀሎች ጥፋተኛ መባላችንና የቅጣት ውሳኔ መሰጠቱ ሕጋዊ አይደለም በማለት ተከራክረዋል፡፡ የአመልካችዎች ጥፋተኛ ሆነው የተገኙባቸው ተደራራቢ የወንጀል ሕግ ድንጋጌ የመጣስ አድራጎት በወንጀል ህጉ አንቀጽ 61(ሀ) የተደነገገው መሰረታዊ መርህ ተፈጻሚ የሚሆንበት ሁኔታ የለም፡፡ በአንጻሩ ወንጀል አድራጊው በአንድ ድርጊት በአንድ ጊዜ አደራርቦ የህግ ድንጋጌዎችን የጣሰ እንደሆነ ቅጣት የሚወሰነው በወንጀል ሕግ አንቀጽ 187(1) መሰረት እንደሆነ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 65 በግልጽ ይደነግጋል፡፡

14. በወንጀል ሕግ አንቀጽ 187(1) ወንጀል አድራጊው በአንድ ድርጊት በአንድ ጊዜ  አደራርቦ የህግ ድንጋጌዎችን የጣሰ እንደሆነ (አንቀጽ 65 ) ፍርድ ቤቱ የአካባቢ ሁኔታዎችን ሲመረምር በተለይም ወንጀለኛው አስቦና አቅዶ ሕግ መጣሱን ወይም ግልጽ የሆነ መጥፎ ጸባይ ማሳየቱን ባመነ ጊዜ በአንቀጽ 184 መሰረት ቅጣቱን አክብዶ ለመወሰን እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) ድንጋጌ ይዘት ስንመለከተው ከሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ  ነጻነትን የሚያሳጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመው በተገኙ ጊዜ እያንዳንዱ ተደራቢ ወንጀል ቅጣት ተወስኖ፣ ቅጣቱ እንደሚደመርና የቅጣቱ አይነት በሕጉ ከተመለከተው ከፍተኛ ቅጣት ሊበልጥ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንጻር አመልካቾች የወንጀል ህጉ አንቀጽ  61(ሀ) በመጥቀስ ያቀረቡት ክርክር ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 65፣ አንቀጽ 187(1) እና በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) የተደነገገውን የቅጣት አወሳሰን መርሆች ያላገናዘበና የህግ መሰረት የሌለው በመሆኑ አልተቀበልነውም፡፡

15. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጠው የቅጣት ውሳኔ ህጋዊነት በተመለከተም አመልካቾች ጥፋተኛ በተባሉበት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4፣ ሕጉ መነሻ ቅጣት አድርጎ በደነገገው አሥራ አምስት ዓመት ጽኑ እስራትና በሃያ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት መካከል ያለው ልዩነት አስር ዓመት ነው፡፡ ይህም በዝቅተኛ ደረጃ የሚመደበው የቅጣት ሬንጅ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ አሥራ ሥምንት ዓመት ከአራት ወራት፣ በመካከለኛ ደራጃ የሚመደበው የቅጣት ሬንጅ አሥራ ሥምንት ዓመት ከአራት  ወራት፣ እሰከ ሃያ አንድ አመት ከስምንት ወር፣ በከፍተኛ ደረጃ የሚመደበው የቅጣት ሬንጅ ሃያ


አንድ አመት ከስምንት ወር፣ እስከ ሃያ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ካወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 ለመረዳት ይቻላል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት ሶስቱም አመልካቾች በዚህ ወንጀል ያላቸው ተሳትፎ በመመካከለኛ ደረጃ የሚመደብ መሆኑን በውሳኔው አስፍሯል፡፡

16. አመልካቾች ጥፋተኛ ሆነው በተገኙበት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) እና አንቀጽ 248(ለ) የቅጣት ዝቅተኛው መነሻ ሆኖ በተደነገገው አምስት ዓመት ጽኑ እስራትና እና ከፍተኛ በሆነው ሃያ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት መካከል ያለው ልዩነት ሃያ ዓመት ነው፡፡ይህም በዝቅተኛ ደረጃ የሚመደበው የቅጣት ሬንጅ ከአምስት ዓመት እስከ አሥራ አንድ ዓመት ከሥምንት ወራት፣ በመካከለኛ ደረጃ የሚመደበው የቅጣት ሬንጅ  አሥራ አንድ ዓመት ከስምንት ወራት እሰከ አሥራ ሥምንት ዓመት ከአራት ወር፣ በከፍተኛ ደረጃ የሚመደበው የቅጣት ሬንጅ አሥራ ሥምንት ዓመት ከአራት ወር፣ እስከ ሃያ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን የቅጣት አወሳሰን መመሪያውን መሰረት በማድረግ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ  ሰሚው ችሎት ሶስቱም አመልካቾች በዚህ ወንጀል ያላቸው ተሳትፎ በመመካከለኛ ደረጃ የሚመደብ መሆኑን በውሳኔው አስፍሯል፡፡

17.  የጽኑ እስራት ቅጣት ከሃያ አምስት አመት ሊበልጥ እንደማይችል በወንጀል ሕግ   አንቀጽ

184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) የመጨረሻው ፓራግራፍ እና ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 108 ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌዎች ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህ በመሆኑ የሶስቱም አመልካቾች ከፍተኛ የቅጣት ጣሪያ 25 ዓመት ጽኑ እስራት ሲሆን ይህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 መሰረት እርከን 37 ላይ የሚወድቅ ይሆናል፡፡በይግባኝ ሰሚው ችሎት ውሳኔ መሰረት ሁለተኛና ሶስተኛ አመልካቾች አንድ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ያላቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡  አንደኛ  አመልካች የቅጣት ማቅለያ ምክንያት የሌለው መሆኑንና አንድ የቅጣት ማክበጃ የቀረበበት በመሆኑ በእርከን 38 ላይ የሚወድቅ መሆኑን የስር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት ተስማምተዋል፡፡ በእያንዳንዱ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ሶስት እርከን የሚቀንስ መሆኑን፣የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት በውሳኔያቸው አስፍረዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት ሁለተኛና ሶስተኛ አመልካቾች ሶስት እርከን ተቀንሶላቸው እርከን 34 ላይ በማሳረፍ ፈቃደ ሥልጣናቸውን ተጠቅመዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት የስር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት በቅጣት አወሳሰን መመሪያው የተሰጣቸውን ፈቃደ ሥልጣንና በወንጀል ሕግ አንቀጽ 88(2) የተደነገገውን መሰረት በማድረግ አንደኛ አመልካች በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣና ሁለተኛው አመልካች በአስራ ሥምንት ዓመት ጽኑ እስራት ያስተላለፉት የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የስር ፍርድ ቤት በሶስተኛ አመልካች ላይ ያስተላለፈውን የሃያ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ አንቀጽ 2(ለ)2 መሰረት በማሻሻል በአስራ ስድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የሰጠው ውሳኔ  የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አላገኘነውም፡፡

18. የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) የመጀመሪያው ፓራግራፍ ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመው በተገኙ ጊዜ ፍርድ ቤቶች የድምር ውጤት የቅጣት አወሳሰን መርህን ተፈጻሚ ማድረግ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ይህም አንድ ሰው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ተደራራቢ ወንጀሎችን ከፈጸመና ወንጀሎቹ ነጻነትን በሚያሳጣ ቅጣት የሚያስቀጡ ከሆነ ለእያንዳንዱ ወንጀል ሊቀጣ የሚገባውን ቅጣት በመወሰንና ቅጣቱን በመደመር  በወንጀለኛው


ላይ የሚወሰነውን ቅጣት ለማስላት የሚያስችል ቅጣት አወሳሰን መርህ ነው፡፡ በሌላ በኩል ድንጋጌው ድምር ውጤት የቅጣት አወሳሰን መርህ የሚገድብና ውጤት አልባ የሚያደርግ ደንብ የያዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በያዝነው ጉዳይ በጽኑ እስራት ቅጣት የሚያስቀጡ ሁለት ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ እደዚህ በሆነ ጊዜ ፍርድ ቤቶች ለሁለቱ ተደራራቢ ወንጀሎች የሚወሰኑት ቅጣት የድምር ውጤት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 108 ንዑስ አንቀጽ 1 ከፍተኛ የጽኑ እስራት ቅጣት ሆኖ ከተደነገገው ሃያ አምስት አመት ጽኑ እሰራት ሊበልጥ እንደማይችል የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) ሁለተኛው ፓራግራፍ ገደብ ያስቀምጣል፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) ሁለተኛው ፓራግራፍ የተቀመጠው ገደብ ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመው በተገኙ ጊዜ ፍርድ ቤቱ፣በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) የመጀመሪያው ፓራግራፍ መሰረት  በጥፋተኛው ላይ ሊወሰን የሚገባው ድምር የቅጣት ውጤት ከሃያ አምስት ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ፍርድ ቤቶች የቅጣት ድምር ውጤቱን ወደ ሃያ አምስት ዓመት ዝቅ በማድረግ እንዲወስኑ የሚያስገድድና ሕግ አውጭው በአዲስ መልክ በወንጀል ሕጉ ያስገባውን የድምር ውጤት የቅጣት አወሳሰን መርህን  ውጤት አልባ የሚያደርግ ገደብ ነው፡፡

19. ይህም ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመው በተገኙ ጊዜ ፍርድ ቤቶች የድምር ውጤት የቅጣት አወሳሰን መርህን እንዲተገብሩ በሚደነግገው የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ1(ለ) የመጀመሪያው ፓራግራፍና የቅጣቱ ድምር ውጤት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 108 ንዑስ አንቀጽ 1 ከተደነገገው ሃያ አምስት አመት ጽኑ እስራት ሊበልጥ እንደማይችል አስገዳጅ ገደብ በሚጥለው በወንጀል የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) ሁለተኛው ፓራግራፍ መካከል በይዘትም ሆነ በተግባራዊ አፈጻጸማቸው ክፍተትና አለመጣጣም ያለ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሆኖም ህጉ ባለው ክፍተትና አለመጣጣም አመልካቾች ተጠቃሚ እንጅ ተጎጅ አይደሉም፡፡ ስለሆነም የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) በመጀመሪው ፓራግራፍ የደነገገውን የድምር ውጤት የቅጣት አወሳሰን መርህ ዋጋ በማያሳጣ ሁኔታ ለተደራራቢ ወንጀሎች ፍርድ ቤቱ የሚወስነው ድምር የቅጣት ውጤት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 108 ንዑስ አንቀጽ 1 ከተደነገገው ሃያ አምስት ዓመት መብለጥ የለበትም በማለት የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) ሁለተኛው ፓራግራፍ የጣለውን አስገዳጅ ገደብ ማሻሻል ለህግ አውጭው የስራ ኃላፊነትና ተግባር ነው፡፡ በያዝነው ጉዳይ ካላይ በገለጽናቸው ወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች የሚታየው ክፍተት አመልካቾችን መብት የሚያጣብብ ሳይሆን እነርሱን በሚጠቅም መልኩ የተተረጎመና ሥራ ላይ የዋለ በመሆኑ አመልካቾች ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ የህግ መሰረት ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በመሆኑም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአንደኛ አመልካችና ሁለተኛ አመልካች ላይ የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ ማጽናቱና በሶስተኛው አመልካች ላይ የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ በማሻሻል የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት ወስነናል፡፡


 

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195 ንዑስ አንቀጽ 2(ለ)2 መሰረት ጸንቷል፡፡

2. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 83593 በአመልካቾች ላይ የወሰነው የቅጣት ውሳኔ የጸና መሆኑን አውቆ ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ለክፍሉ ማረሚያ ቤት ይተላለፍ፡፡

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡