96607 criminal law/ legality

በማስረጃ በተረጋገጠ የወንጀል ፍሬ ነገር መፈፀሙ የተረጋገጠው የወንጀል ተጠያቂነትን በሚያስከትለው የህግ ድንጋጌ መሰረት የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ መሠጠት ያለበት ስለመሆኑ፡-

 

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መንግስት የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 56/1995 አንቀጽ 98(2)(ሀ)

የሰ/መ/ቁ. 96607

 

መስከረም 29 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ተኽሊት ይመሰል

 

አመልካቾች፡- 1ኛ.አቶ ኤርሚያስ ካጢሶ

 

2ኛ. አቶ ዮሐንስ ላምቤቦ     ጠበቃ ፀጋዬ አሰፋ ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- የከምባታ ጠምባሮ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ  ር ድ

 

በዚህ መዝገብ አመልካቾች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ገቢን አሳንሶ የማስታወቅ ወንጀል መፈጸማቸው በማስረጃ ተረጋግጧል በማለት በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠብን የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡

 

ክርክሩ በተጀመረበት በቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ፍርድ ቤት ተጠሪ በአመልካቾቹ ላይ በ08/8/2005 ዓ.ም አዘጋጅቶ ባቀረበው ክስ ተከሳሾቹ በከምባታ ጠምባሮ ዞን በቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ጊዜ ደበኦ በተባለ ቀበሌ አሸዋ እና ድንጋይ ለማምረት ከመንግስት ጋር ውል አድርገው ስራውን እያከናወኑ በነበረበት ከ2004 ዓ.ም እስከ ህዳር ወር 2005 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ትክክለኛ የገቢ ግብር ላለመክፈል ሆን ብለው በማሰብ በኤንትሬ ገልባጭ መኪና በቢያጆ ከብር 300 እስከ ብር 360 ይሸጡ የነበረውን ነጭ ድንጋይ ከብር 40 እስከ ብር 100 የሸጡ አስመስለው፣እንዲሁም በፊያት ገልባጭ መኪና በቢያጆ ከብር 140 እስከ ብር 250 ይሸጡ የነበረውን ነጭ ድንጋይ ከብር 30 እስከ ብር 60 የሸጡ አስመስለው በመመዝገብ እና ገቢያቸውን በማሳነስ የመንግስትን እና የሕዝብን ጥቅም የሚጎዳ አድራጎት የፈጸሙ በመሆኑ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መንግስት የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 56/1995 በአንቀጽ 97 የተደነገገውን በመተላለፍ ግብር አሳንሶ የማስታወቅ ወንጀል አድርገዋል በማለት ክስ የመሰረተ ሲሆን ተከሳሾቹ ድርጊቱን አልፈጸምንም በማለታቸው ተጠሪ ሁለት ምስክሮችን አቅርቦ ያሰማ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ሰነዶችን በማስረጃነት አቅርቧል፡፡

 

ፍርድ ቤቱም የተጠሪን የሰው እና የጽሁፍ ማስረጃ መርምሮ በአመልካቾቹ ላይ በክሱ መሰረት ያስረዳ መሆኑን በመግለጽ ተከሳሾቹ መከላከያቸውን እንዲጀምሩ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 142 መሰረት ትዕዛዝ ከሰጠ እና የተከሳሾቹን የሰው እና የጽሁፍ መከላከያ   ማስረጃ


ከሰማ በኃላ የግራ ቀኙን አጠቃላይ ክርክር በመመርመር ዐቃቤ ሕግ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ያስረዳባቸውን ፍሬ ነገር ተከሳሾቹ በመከላከያቸው ያላስተባበሉ መሆኑን ገልጾ  በክሱ በተመለከተው ድንጋጌ ስር በሁለቱም ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡በመቀጠልም የግራ ቀኙን የቅጣት አወሳሰን ክርክር ከሰማ በኃላ የጥፋተኝነት ውሳኔው የተሰጠበት ድንጋጌ የሚያስቀጣው ከአምስት ዓመት በማያንስ እስራት መሆኑን በመግለጽ፣ተከሳሾቹ ወንጀሉን የፈጸሙት ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው መሆኑን በማክበጃ ምክንያትነት በመያዝ እና የቀረበባቸው የቀድሞ የወንጀል ሪከርድ አለመኖሩን ደግሞ በማቅለያ ምክንያትነት በመያዝ እንዲሁም የቤተሰብ ኃላፊዎች መሆናቸው በቅጣት ማቅለያ ምክንያትነት እንዲያዝላቸው ተከሳሾቹ ያቀረቡትን ጥያቄ ባለመቀበል እያንዳንዳቸው በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

ተከሳሾቹ በተሰጠባቸው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ ቅር በመሰኘት፤ዐቃቤ ሕግ ደግሞ በተሰጠባቸው የቅጣት ውሳኔ መጠን ቅር በመሰኘት ሁለቱም ወገኖች ይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን የከምባታ ጠምባሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሳሾቹን ቅሬታ መሰረት አድርጎ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ዐቃቤ ሕግ ክሱን ያቀረበው በተሻረ ሕግ መሆኑን እና ተከሳሾቹ ለነጭ ድንጋይ የዋጋ ተመን ከወጣ በኃላ ከተመን በላይ ሽያጭ ስለማከናወናቸው ዐቃቤ ሕግ ያላስረዳባቸው መሆኑን በምክንያትነት በመጥቀስ የጥፋተኝነትም ሆነ የቅጣት ውሳኔውን ሽሮ ተከሳሾቹን በነጻ በማሰናበት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

ዐቃቤ ሕግ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ባቀረበው ይግባኝ ሳቢያ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ በክሱ የተጠቀሰው የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መንግስት የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 56/1995 በአዋጅ ቁጥር 136/2003 በከፊል የተሻሻለ ከመሆኑ ውጪ ሙሉ በሙሉ ያልተሻረ እና ለክሱ መሰረት የሆኑት ድንጋጌዎችም በማሻሻያ አዋጁ ያልተነኩ ሆኖ እያለ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ ክሱ የቀረበው በተሻረ ሕግ መሆኑን መግለጹ ተገቢነት የሌለው መሆኑን እና የተመን ጉዳይም በክርክሩ ሂደት በግራ ቀኙ ምስክሮች እግረ መንገድ የተነገረ ከመሆኑ ውጪ ለክሱም ሆነ ለወንጀሉ የማቋቋሚያ ምክንያት ባልተደረገበት ሁኔታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተመንን ጉዳይም በምክንያትነት የጠቀሰው አላግባብ መሆኑን ገልጾ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔን በመሻር እና የወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔን በማጽናት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡አመልካቾቹ ይህ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ችሎት ያቀረቡት አቤቱታ የተሰረዘ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በወረዳው ፍርድ ቤት የተሰጠው የቅጣት ውሳኔ አንሷል የሚለውን ቅሬታ እስከ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በማድረሱ ሰበር ችሎቱ በዚህ ረገድ በሌላ መዝገብ በቀረበለት አቤቱታ ሳቢያ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ በስር ፍርድ ቤቶች የተወሰነውን የቅጣት መጠን ከፍ በማድረግ ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

አመልካቾቹ አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት ተሻሽሎ እና ከፍ ተደርጎ የተሰጠባቸውን የቅጣት ውሳኔ ጨምሮ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠባቸው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮ ገቢያችንን አሳንሰን ያሳወቅንበት የግብር መጠን በገቢ ማስታወቂው ላይ በሌለበት ሁኔታ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መንግስት የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 56/1995 በአንቀጽ 97 ስር ጥፋተኛ መባላችን የሕግ ስህተት ነው በማለት አመልካቾቹ ያቀረቡትን ቅሬታ ተጠሪው ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ


በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል፡፡

 

በዚህም መሰረት አመልካቾቹ ሲጠየቁ ወንጀሉን አላደረግንም በማለታቸው ተጠሪ አቅርቦ ያሰማቸው የውሃና ማዕድን ሀብት ጥናት የስራ ሂደት አስተባባሪ መሆናቸውን የገለጹት 1ኛ ምስክር እና የድንጋይ ግዥ ከአመልካቾቹ ሲፈጽሙ እንደነበረ የገለጹት 2ኛ ምስክር አመልካቾቹ በሽያጭ ደረሰኞች ላይ የሚጽፉት ዋጋ ድንጋዩን ከሚሸጡበት ዋጋ እጅግ ዝቅ ያለ መሆኑን፣ ግብር ይከፍሉ የነበረውም በደረሰኙ ላይ በተመለከተው መሰረት ከሽያጩ ዋጋ 3% መሆኑን፣ በደረሰኞቹ ላይ የሽያጩን ትክክለኛ ዋጋ እንዲሞሉ በተደጋጋሚ ሲነገራቸው የቆየ ቢሆንም ፈቃደኞች ሳይሆኑ መቅረታቸውን፣በኃላ ግን በተደረገ አጠቃላይ ውይይት ድንጋዩን የሚሸጡበት ተመን ወጥቶ ተግባራዊ መደረጉን፣ተመን ከወጣ በኃላ የተከሰተ ችግር ስለመኖሩ የቀረበ ሪፖርት አለመኖሩን እና መሰል ፍሬ ነገሮችን በመግለጽ በተመሳሳይ ሁኔታ የመሰከሩ መሆኑን እና ተጠሪ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎችም የሽያጭ ደረሰኞችን ጨምሮ ይህንኑ ምስክርነት የሚያጠናክሩ መሆናቸውን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡አመልካቾቹ እንዲከላከሉ በተሰጠው ብይን መሰረትም ድንጋዩን ለማምረት እና ለማስጫን ይወጣ የነበረውን ወጪ በአዋጁ አንቀጽ 20 በተመለከተው መሰረት ከአጠቃላይ የሽያጩ ገንዘቡ ላይ በመቀነስ በደረሰኙ ላይ ይጽፉ የነበረው የተጣራ ትርፋቸውን ወይም ገቢያቸውን ብቻ እንደነበረ ያውቁልናል በማለት እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ምስክሮችን ያሰሙ እና የተለያዩ ሰነዶችን በማስረጃነት ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ አመልካቾቹ በተጠሪ ማስረጃ የተመሰከረባቸውን የወንጀል ፍሬ ነገር በመከላከያቸው አላስተባበሉም በማለት የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላለፈባቸውም ሕጋዊ ወጪዎችን ተቀናሽ የማድረግ መብት ተግባራዊ የሚደረገው ገቢያቸውን በስርዓቱ መሰረት እያስታወቁ ግብር ለሚከፍሉ ነጋዴዎች እንጂ ገቢያቸውን አሳንሰው ለሚያስታውቁ ነጋዴዎች ጭምር አይደለም የሚል ነጥብ በዓቢይ ምክንያትነት በመያዝ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡

 

በመሰረቱ በአመልካቾቹ ላይ የቀረበው ክስ መሰረታዊ ይዘት ግብር የሚከፈልበትን ገቢ አሳንሰው አስታውቀዋል የሚል ሲሆን"ግብር የሚከፈልበት ገቢ" ለሚለው ሐረግ ለክሱ በተጠቀሰው የክልሉ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 56/1995  የተሰጠ  ትርጉም የለም፡፡በሌላ በኩል  በአዋጁ  ውስጥ የተለየ ትርጉም በግልጽ ካልተሰጣቸው በስተቀር በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጎች ትርጉም የተሰጣቸው ቃላት በተተረጎሙበት ሕግ የተሰጣቸውን ትርጉም የሚይዙ ስለመሆኑም በአዋጁ አንቀጽ 2 መግቢያ ላይ የተመለከተ ሲሆን ለጉዳዩ አግባብነት ባለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 በአንቀጽ 2(11) ስር "ግብር የሚከፈልበት ገቢ" ማለት በአዋጁ እና በአዋጁ መሰረት በሚወጡ ደንቦች መሰረት ማናቸውም ወጪ እና ሌሎች ተቀናሽ ሂሳቦች ከተቀነሱ  በኃላ የሚቀረው የገቢ መጠንስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡በተያዘው ጉዳይ አመልካቾች አጥብቀው የሚከራከሩት በእነዚህ የአዋጆቹ ድንጋጌዎች መሰረት ለምርት እና ለአገልግሎት ያወጣነውን ወጪ ከአጠቃላይ የሽያጭ ገንዘቡ ላይ ቀንሰን ግብር የሚከፈልበትን ገቢ በደረሰኝ ላይ ከማስፈር ውጪ ግብር የሚከፈልበትን ገቢያችንን አሳንሰን አላስታወቅንም በማለት ነው፡፡ በሽያጩ ዋጋ እና አመልካቾቹ በሽያጭ ደረሰኞቹ ላይ በሚሞሉት የዋጋ መጠን መካከል ልዩነት  መኖሩን ከማስረዳት ውጪ አመልካቾቹ ወጪዎቻችን ናቸው የሚሏቸውን የተለያዩ ሂሳቦች በመቀናነስ በደረሰኞቹ ላይ ይሞሉት የነበረው የገቢ መጠን ከእውነተኛው ገቢያቸው መጠን በታች ስለመሆኑ


ተጠሪው ባለበት የማስረዳት ግዴታ መሰረት በማስረጃ ያረጋገጠው ፍሬ ነገር ስለመኖሩ የመዝገቡ ግልባጭ አያረጋግጥም፡፡

 

አመልካቾቹ መግለጽ ይገባቸው የነበረው ከተቀናሽ ወጪዎች በኃላ የሚገኘው እውነተኛው የገቢ እና በገቢው ላይ መከፈል ይገባው የነበረው የግብር መጠን ምን ያህል እንደነበረ በመወሰን ተጠሪው በአዋጁ በተሰጠው ስልጣን እና በተዘረጋው የግብር አጣጣል ስርዓት መሰረት በአመልካቾቹ ላይ የጣለው ግብር ስለመኖሩም የቀረበ ክርክር እና ማስረጃ የለም፡፡ተጠሪው በሕግ በተጣለበት የማስረዳት ግዴታ መሰረት እነዚህን መሰረታዊ የወንጀሉን ፍሬ ነገሮች ማስረዳቱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ደግሞ አመልካቾቹ በተከሰሱበት እና ጥፋተኛ በተባሉበት የወንጀል ሕግ አነጋገር መሰረት ግብር አሳንሶ የማስታወቅ ወንጀል አድርገዋል ከሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱ ሕጋዊ መሰረት አለው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

በሌላ በኩል አመልካቾቹ ለምርት እና ለአገልግሎት አውጥተናል የሚሏቸውን ወጪዎች የግብር አስገቢው መስሪያ ቤት በማያውቀው ሁኔታ በራሳቸው በመቀነስ በሽያጭ ደረሰኞቹ ላይ የተጣራ ነው የሚሉትን ገቢ ብቻ በመሙላት መፈጸማቸው የተረጋገጠው ድርጊት ራሱን ችሎ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ ቀጥሎ መታየት እና ምላሽ ማግኘት የሚገባው ጥያቄ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ ግብር የሚከፈልበትን ከንግድ ስራ የሚገኝ ገቢ በሚመለከት በአዋጁ የተመለከቱት ገደቦች እንደተጠበቁ ሆነው ግብር ከፋዩ ወጪዎችን ማረጋገጥ እስከቻለ ድረስ ለንግድ ስራው ገቢ ለማግኘት፣ለንግድ ስራው ዋስትና ለመስጠት እና እንቅስቃሴውን ለማስቀጠል የተደረጉ ወጪዎች ተቀናሽ የሚደረጉ ስለመሆኑ ከላይ በተጠቀሰው የክልሉ መንግስት የገቢ ግብር አዋጅ በአንቀጽ 20 ስር ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ግብር የሚከፈልበት የንግድ ስራ ገቢ ተቀባይነት ያገኘውን የሂሳብ አያያዝ መርህ በመከተል የሚዘጋጀውን የትርፍና ኪሳራ ሂሳብ ወይም የገቢ መግለጫ ፣ አዋጁን እና የግብር ባለስልጣን የሚያወጣውን መመሪያ መሰረት በማድረግ በእያንዳንዱ የግብር ዘመን የሚወሰን ስለመሆኑ በዚሁ አዋጅ በአንቀጽ 18 ተመልክቷል፡፡

 

ከእነዚህ የአዋጁ ሁለት ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ መገንዘብ የሚቻለውም ግብር ከፋዩ ለንግድ ስራው ገቢ ለማግኘት፣ለንግድ ስራው ዋስትና ለመስጠት እና እንቅስቃሴውን ለማስቀጠል ተደርገዋል የሚባሉት ወጪዎች ተቀናሽ የሚደረጉት በራሱ በግብር ከፋዩ ውሳኔ ሳይሆን ሕጋዊ ወጪዎቼ ናቸው የሚላቸውን ወጪዎች ጨምሮ አጠቃላይ የሂሳብ መግለጫውን ለባለስልጣኑ ካቀረበ እና የወጪዎቹ ሕጋዊነትና ተገቢነት በግብር ባለስልጣኑ  ተረጋግጦ ተቀባይነት  ካገኘ በኃላ ብቻ መሆኑን ነው፡፡አንድ ግብር ከፋይ ለግብር ባለስልጣኑ በሚያቀርበው መግለጫ ውስጥ መካተት የሚገባቸውን ነጥቦች ያለበቂ ምክንያት ሳያካትት ያስቀረ በሆነ ጊዜ የዚህ ዓይነቱ ድርጊት ራሱን ችሎ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 98(1)(ለ) ስር የተደነገገ ሲሆን ለወንጀሉ የሚጣለው ቅጣትም ሳይካተት በቀረው ነጥብ ምክንያት ሳይከፈል የቀረውን የግብር መጠን መሰረት በማድረግ በአንቀጽ 98(2) በፊደል(ሀ) እና (ለ) ስር በተለያየ መጠን ተደንግጎ ይገኛል፡፡በተያዘው ጉዳይ አመልካቾቹ ሕጋዊ ናቸው የሚሏቸውን ወጪዎች ዝርዝር ለባለስልጣኑ ሳያቀርቡ በመቅረታቸው ምክንያት ሳይከፈል የቀረውን የግብር መጠን ተጠሪው ለይቶ ያላስረዳ በመሆኑ በአመልካቾቹ ድርጊት ምክንያት አንሶ እንዲከፈል የተደረገው የግብር መጠን በአንቀጽ 98(2)(ሀ) ስር የተመለከተው አነስተኛ መጠን ማለትም ከብር አንድ ሺህ የማይበልጥ ተደርጎ መወሰድ የሚገባው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡በመሆኑም በአመልካቾቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሊሰጥ የሚገባው በዚህ ድንጋጌ ስር ሲሆን ሊጣልባቸው የሚገባው   የቅጣት


መጠንም በስር ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ያገኙትን የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ምክንያቶች መሰረት በማድረግ በድንጋጌው ስር የተመለከተው ከብር ሃያ ሺህ የማይበልጥ መቀጮ እና ከአንድ ዓመት የማያንስ እና ከሶስት ዓመት የማይበልጥ እስራት ነው፡፡በአመልካቾቹ የወንጀል ድርጊት ምክንያት ሳይከፈል የቀረው የግብር መጠን ቀደም ሲል እንደተገለጸው አነስተኛ ነው ተብሎ ግምት የሚወሰድበት በመሆኑ ውሳኔው በተሰጠበት ጊዜ በስራ ላይ በነበረው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 አንቀጽ 13(2) እና (3) መሰረት መፈጸሙ የተረጋገጠው ወንጀል በክብደቱ እና በአፈጻጸሙ ሊመደብ የሚገባው በዝቅተኛ ደረጃ መሆኑንም ተገንዝበናል፡፡ የጥፋተኝነት ውሳኔው በተሰጠበት ድንጋጌ ስር በዝቅተኛ ደረጃ ለተመደበ ወንጀል በቅጣት አወሳሰን መመሪያው የተቀመጠው ፍቃድ ስልጣን ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ከሶስት ወር የሚደርስ እስራት ሲሆን ይህም በመመሪያው አባሪ አንድ በእርከን ሰባት ስር የሚወድቅ ነው፡፡የገንዘብ መቀጮ መጠኑም በአባሪ ሁለት መሰረት እስከ ብር 20,000 (ሃያ ሺህ) የሚደርስ ነው፡፡

 

ሲጠቃለል በማስረጃ በተረጋገጠው የወንጀል ፍሬ ነገር መሰረት በአመልካቾቹ መፈጸሙ የተረጋገጠው ወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትለው በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መንግስት የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 56/1995 አንቀጽ 98(2)(ሀ) ድንጋጌ ስር ሆኖ እያለ በአመልካቾቹ ላይ በክሱ በተጠቀሰው የአዋጁ በአንቀጽ 97 ስር የተሰጠው በጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት እና ሊሻሻል የሚገባው ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥ~ል፡፡

 ው ሳ ኔ

1. በቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 06021 በ11/07/2005 ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ችሎቶች እንደቅደም ተከተሉ በመዝገብ ቁጥር 01611 በ01/02/2006 ዓ.ም እና በመዝገብ ቁጥር 02314 በ29/02/2006 ዓ.ም በውሳኔ እና በትዕዛዝ የጸናው የጥፋተኝነት ውሳኔ እና በቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 06021 በ11/07/2005 ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ  ቁጥር

01612 በ29/02/2006 ዓ.ም. የተሻሻለው የቅጣት ውሳኔ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ  ስነ ስርዓት ቁጥር 195(2)(ለ)(2) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2.  አመልካቾቹ የወንጀል ተጠያቂነት አለባቸው መባሉ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡

3. በአመልካቾቹ ላይ በአዋጁ አንቀጽ 97 ድንጋጌ ስር ተሰጥቶ የነበረውን የጥፋኝነት ውሳኔ በማሻሻል የወንጀል ተጠያቂነታቸው የሚወድቀው በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መንግስት የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 56/1995 አንቀጽ 98(2)(ሀ) ድንጋጌ ስር ነው በማለት ወስነናል፡፡

4. በተራ ቁጥር 1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ በአመልካቾቹ ላይ በክልሉ ሰበር ችሎት ተሻሽሎ የተሰጠው የአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት ተሻሽሎ በዚህ በጉዳይ የታሰሩበት የሚታሰብላቸው ሆኖ አመልካቾቹ እያንዳንዳቸው በአንድ ዓመት እስራት እና በብር 1,000 (አንድ ሺህ) መቀጮ እንዲቀጡ ወስነናል፡፡

5. በዚህ ውሳኔ መሰረት እንዲያስፈጽም የውሳኔው ግልባጭ አመልካቾቹ ለሚገኙበት ማረሚያ ተቋም ይላክ፡፡ውሳኔው ዛሬ ጥቅምት 4 ቀን 2007 ዓ.ም ተነገረ፡፡

6.  የውሳኔው ቅጂ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::                             እ/ተ