95440 criminal law/ retroactive law/ sentencing guideline

አንድ በወንጀል የተከሰሰ ሰው ወንጀል የሰራው አዲሱ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ከመውጣቱ በፊት ሲሆንና ቅጣቱ  በሚወሰንበት ጊዜ ወንጀሉን በፈፀመበት ጊዜ ከነበረው የቅጣት አወሳሰን ማንዋል ይልቅ አዲሱ የቅጣት አወሳሰን ማንዋል(መመሪያ) ቅጣቱን የሚያቀልለት ሲሆን ተፈፃሚ መደረግ የሚገባው አዲሱ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ስለመሆኑ፡-

የወ/ሕ/ቁ. አንቀፅ 88(4)፣6

የሰ//.95440 ሰኔ 4 ቀን 2006 ዓ.ም.

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ

ሙስጠፋ አህመድ

 

አመልካች፡- አቶ ሰሚር ኢብራሂም ሂቡ ጉዳይ ተከታታይ ነኝ በማለት አቶ ኢብራሂም ሂቡ ቀረቡ

ተጠሪ፡- የፌዴራል ዐ/ሕግ የቀረበ የለም

 

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

በዚህ መዝገብ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ተጠሪ ያቀረበባቸውን ሁለት የወንጀል ክሶች የተመለከተው የፌ/ከ/ፍ/ቤት የሰጠባቸው እና በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት በውሳኔ የጸናው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡

 

ተጠሪ በአመልካች ላይ ያቀረባቸው ሁለት ክሶች ይዘት ባጭሩ፡- አመልካች የሚያዝበት ገንዘብ ሳይኖር ቼክ ለመስጠት አስቦ በአንደኛ ክስ በ28/09/2005 ዓ.ምእና በሁለተኛ ክስ በ30/09/2005 ዓ.ምበየክሶቹ ላይ በተመለከተው ጊዜ እና ቦታ የግል ተበዳይ ለሆኑት አቶ አሩቅ ሙሐባ አባድር ቁጥሮቻቸው በየክሶቹ ላይ የተመለከቱትን በአጠቃላይ ብር 520,000 የያዙ ከሕብረት ባንክ የሚመነዘሩ ሁለት ቼኮችን በመስጠቱ እና ሁለቱም ቼኮች እንደቅደም ተከተላቸው በ06/10/2005 ዓ.ም.እና በ05/10/2005 ዓ.ም. ለክፍያ ለባንኩ ሲቀርቡ በቂ ስንቅ የላቸውም ተብሎ ክፍያ ሳይፈጸምባቸው በመቅረቱ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 693(1) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ የሚያዝበት ገንዘብ ሳይኖር ቼክ የመስጠት ወንጀል አድርጓል  የሚል ሲሆን አመልካች ተጠይቀው በሁለቱም ክሶች የተመለከተውን ወንጀል ማድረጋቸውን ሙሉ በሙሉ ማመናቸው በመረጋገጡ ፍ/ቤቱ ማስረጃ መስማት ሳያስፈልግ በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ.134 (1) መሰረት ላይ በሁለቱም ክሶች የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል፡፡

 

በመቀጠልም ፍ/ቤቱ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 መሰረት የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከተቀበለ በኃላ ለሁለቱም ክሶች በመመሪያው መሰረት የተሰላው መነሻ ቅጣት 11 ዓመት ጽኑ እስራት እና የብር 16,000 መቀጮ መሆኑን፣ ይህ የእስራት ቅጣት እና የመቀጮ መጠን በአባሪ አንድ እና ሁለት እንደቅደም ተከተሉ በእርከን 29 እና 7 ላይ የሚወድቅ


መሆኑን፣ ወንጀሎቹ ተደራራቢ በመሆናቸው ምክንያት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 85 መሰረት እርከኑ በአንድ ማክበጃ ምክንያት ወደ 30 ከፍ የሚል መሆኑን፣ በሌላ በኩል አመልካች የቀረበባቸው ሪከርድ አለመኖሩ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸው እና በችሎት ቀርበው ክሶቹን ማመናቸው በሶስት የማቅለያ ምክንያትነት ሲወሰዱ እርከኑን ከ30 ወደ 24 ዝቅ የሚያደርጉ መሆኑን፣ በአባሪ አንድ እርከን 24 ስር የተመለከተው ፍቅድ ስልጣን ከ6 ዓመት ከ6 ወር  እስከ 7 ዓመት ከ8 ወር መሆኑን እና በአባሪ ሁለት በእርከን 2 የተመለከተው የመቀጮ መጠንም እስከ ብር 2000 መሆኑን በመግለጽ በመጨረሻ አመልካች በስድስት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እና በብር 700(ሰባት መቶ) መቀጮ እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

አመልካች ለዚህ ችሎት አቤቱታ ያቀረቡት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት የስር ፍ/ቤት ውሳኔን በማጽናቱ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ አመልካች የተከሰሱበትን ወንጀል አምነው የግል ተበዳይን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ መመለሳቸው፣ የወንጀል ሪከርድ ያልቀረበባቸው መሆኑን እና የቤተሰብ አስተዳዳሪነታቸውን የስር ፍ/ቤቶች በማቅለያ ምክንያትነት መያዛቸውን በገለጹበት ሁኔታ በአመልካቹ ላይ የጣሉት የቅጣት መጠን ተመዛዛኝ መሆን አለመሆኑን ከቅጣት አወሳሰን መመሪያው አንጻር ተጠሪው ባለበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር ጉዳዩን መርምረናል፡፡

 

በዚህም መሰረት ቀደም ሲል እንደተገለጸው አመልካች የቀረቡባቸውን ሁለት የወንጀል ክሶች ሙሉ በሙሉ በማመናቸው የጥፋተኝነት ውሳኔው የተሰጠባቸው በወ.መ.ሕ.ስ.ስ.ቁ. 134(1) መሰረት በሰጡት የእምነት ቃል መሰረት ነው፡፡ አንድ ተከሳሽ የጥፋተኝነት ውሳኔው የተሰጠበት የተከሰሰበትን ወንጀል ሙሉ በሙሉ በማመኑ በሆነ ጊዜ ስለቅጣቱ ልክ ወይም ስለቅጣቱ ሕጋዊነት ካልሆነ በስተቀር በጥፋኝነት ውሳኔው ላይ ይግባኝ ማቅረብ የማይችል ስለመሆኑ በወ/መ/ሕ/ስ/ስ/ቁ.185(1) ተደንግጋል፡፡በተያዘው ጉዳይ አመልካች የተከሰስኩባቸውን ወንጀሎች በተመለከተ ክሱን በሰማው ፍ/ቤት የእምነት ቃል አልሰጠሁም ወይም ያስመዘገብኩት ቃል በወ/መ/ሕ/ስ/ስ/ቁ.134(1) መሰረት የእምነት ቃልን የሚያቋቁም አይደለም በማለት በሰበር አቤቱታቸው ላይ ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ለሰበር ክርክሩ በጭብጥነት የተያዘውም የቅጣት ውሳኔው አግባብነት ነው፡፡ በመሆኑም አመልካች የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ሊሻርልኝ ይገባል በማለት ያቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ ሕጋዊ መሰረት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

የቅጣት ውሳኔውን በተመለከተ አመልካች ጥፋተኛ የተባሉበት ወንጀል በቅጣት አወሳሰን መመሪያው ደረጃ ከወጣላቸው ውስጥ የሚካተት ሲሆን የፌ/ከ/ፍ/ቤት ቅጣቱን የወሰነው በቼኮቹ ላይ ከተመለከተው የገንዘብ መጠን አንጻር በሁለቱም ክሶች የተመለከቱት ወንጀሎች በደረጃ 7 የሚወድቁ ሆኖ የእስራት ቅጣቱ እና መቀጮው እንደቅደም ተከተላቸው በአባሪ አንድ በእርከን 22 እና በአባሪ ሁለት በእርከን 6 ስር የሚወድቁ መሆኑን በመግለጽ፣ አንድ የማክበጃ ምክንያት እና ሶስት የማቅለያ ምክንያቶችን ተቀብሎ ቅጣቱን በመመሪያው መሰረት በማስላት መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡ ፍ/ቤቱ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 "ን" መሰረት በማድረግ የተከተለው ይህ የቅጣት አወሳሰን ስርዓት በመሰረቱ ተገቢ ቢሆንም በሌላ በኩል ግን አሁን በስራ ላይ ያለው የተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 ከወንጀል ደረጃው አመዳደብ አንፃር በቅጣት  አወሳሰኑ ላይ የሚያስከትለው ለውጥ መኖር አለመኖሩ እና    ካለም


ተፈጻሚ መደረግ የሚገባው የትኛው መመሪያ እንደሆነ ማየቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሰረቱ የፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤት የቅጣት አወሳሰን መመሪያዎቹን ያወጣው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 88(4) ድንጋጌ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በመሆኑ ምክንያት መመሪያዎቹ እንደ ሕግ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አመልካች ጥፋተኛ የተባሉባቸውን ወንጀሎች ያደረጉት መመሪያ ቁጥር 1/2002 ስራ ላይ በነበረበት ጊዜ ሲሆን ይህ መመሪያ ከጥቅምት 1 ቀን 2006 ዓ.ም.ጀምሮ በተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 ተተክቷል፡፡ በሌላ በኩል አዲሱ የወንጀል ህግ እንዲጸና ከተደረገ በኃላ አድራጊው ህጉ ከመጽናቱ በፊት ላደረገው ወንጀል ሲፈረድበት ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ በስራ ላይ ከነበረው ሕግ ይልቅ አዲሱ ሕግ ቅጣትን የሚያቃልልለት ሲሆን ተፈጻሚ መደረግ የሚገባው በአዲሱ የወንጀል ሕግ የተመለከተው ቅጣት ስለመሆኑ በወንጀለኛ ሕግ አንቀጽ 6 ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 ከቀድሞው መመሪያ ይልቅ ለአመልካቹ የሚጠቅም መሆኑ ከተረጋገጠ በወ/ሕ/ አንቀጽ 6 የተመለከተው ድንጋጌ በዚህ ጉዳይ ተፈጻሚነት እንዲኖረው መደረግ ይኖርበታል፡፡

 

ለአመልካቹ ቅጣቱን የሚያቀለው የትኛው መመሪያ ነው? የሚለውን ነጥብ በተመለከተ ለ1ኛ ክስ ምክንያት በሆነው ቼክ ላይ የተመለከተው የገንዘብ መጠን ብር 120,000 በቀድሞው መመሪያ መሰረት በደረጃ 7 ስር ይሸፈን የነበረ ሲሆን በአዲሱ መመሪያ ግን በደረጃ 6 ስር እንዲሸፈን የተደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ በፍቅድ ስልጣን አወሳሰን ረገድም አዲሱ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ለተከሳሹ ቅጣትን የሚያቃልልለት በመሆኑ ለቅጣት አወሳሰኑ መሰረት ተደርጎ መያዝ የሚገባው አዲሱ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ በዚሁ በአዲሱ መመሪያ መሰረት በ1ኛ ክስ ስር የተመለከተው ወንጀል በደረጃ 6 ስር የሚወድቅ ሆኖ የእስራት ቅጣቱ እና መቀጮው እንደቅደም ተከተሉ በአባሪ አንድ በእርከን 15 እና በአባሪ ሁለት በእርከን 4 ስር የሚሸፈን መሆኑን፣በ2ኛ ክስ ስር የተመለከተው ወንጀል በደረጃ 7 ስር የሚወድቅ ሆኖ የእስራት ቅጣቱ እና መቀጮው እንደቅደም ተከተሉ በአባሪ አንድ በእርከን 17 እና በአባሪ ሁለት  በእርከን 5 ስር የሚሸፈን መሆኑን፣ በአባሪ አንድ በእርከን 15 እና በአባሪ አንድ በእርከን 17 ስር ከተመለከተው ፍቅድ ስልጣን ውስጥ አነስተኛው የቅጣት መጠን ተወስዶ ሲደመር በሁለቱ ወንጀሎች የሚጣለው መነሻ ቅጣት 6 ዓመት መሆኑን፣ ይህ የቅጣት መጠንም በአባሪ አንድ በእርከን 21 ስር የሚወድቅ መሆኑን፣ ይህ እርከን በስር ፍ/ቤት ተቀባይነት ባገኙት አንድ የማክበጃ እና ሶስት የማቅለያ ምክንያቶች ሲሰላ ወደ እርከን 19 ዝቅ የሚል መሆኑን መሰረት በማድረግ ተፈጸሚ መደረግ የሚገባው የቅጣት መጠን በአባሪ አንድ በእርከን 19 ፍቅድ ስልጣን ስር የተመለከተው የቅጣት መጠን መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

 

ሲጠቃለል በሁለቱም ክሶች በተመለከቱት ወንጀሎች በፌ/ከ/ፍ/ቤት ተሰጥቶ በይግባኝ ሰሚው ፌ/ጠ/ፍ/ቤት በውሳኔ የጸናው የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ እና በቅጣት ውሳኔው ላይ ግን ከላይ በተገለጸው ምክንያት ተገቢው ማስተካከያ ሊደረግበት የሚገባ ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።


 ው ሳ ኔ

 

1. በፌዴራል ከ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 136445 በ13/10/2005 ዓ.ም. እና በ25/10/2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 92629 በ20/01/2006 ዓ.ም. የጸናው ውሳኔ በወ.መ.ሕ.ስ.ቁ. 195(2)(ለ)(2) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2. በተ.ቁ.1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ በአመልካቹ ላይ በሁለቱም ክሶች የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ፀንቷል፡፡

3. በተ.ቁ. 1 ከተጠቀሰው ውሳኔ ውስጥ በአመልካቹ ላይ በሁለቱም ክሶችበድምሩ ተጥሎ የነበረውን የስድስት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ በማሻሻል አመልካቹ በዚህ ጉዳይ የታሰሩት የሚታሰብላቸው ሆኖ በአራት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስነናል፡፡

4. ይህንኑ ተገንዝቦ በተሻሻለው የቅጣት ውሳኔ መሰረት እንዲያስፈጽም አመልካቹ ለሚገኙበት የአዲስ አበባ ማረሚያ ተቋም የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ይላክ፡፡

5.  የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለፌ/ከ/ፍ/ቤት እና በማረሚያ ቤት በኩል ለአመልካቹ ይላክ፡፡

6.  በፌ/ከ/ፍ/ቤት የተሰጠው የብር 700(ሰባት መቶ)  የመቀጮ ውሳኔ አልተነካም፡፡

7.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ብ/ይ