95072 contract law/ contract of sale/ warranty for defect

አንድ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ ለገዥ የሸጠ ሻጭ የገባው ውል እቃው ቢበላሽ ጥገና ለማድረግ እያለ ሆኖ እያለና ለድብቅ ጉድለቶች ኃላፊነት ሳይኖርበት ከውላቸው ውጭ እና ከህግ ውጭ እቃው ስላልሰራ እቃውን እንዲቀይር ወይም ገንዘቡን እንዲመልስ ሊደረግ የማይችል ስለመሆኑ፡- የፍ/ህ/ቁ 1731፣2266፣2288-2293፣2300

የሰ/መ/ቁ. 95072

ጥር 07 ቀን 2007 ዓ/ም


 

ጉዳዩ የማቀዝቀዣ(ፊሪጅ) ሽያጭን መሰረት አድርጎ የቀረበውን ክርክር የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኗ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ከተጠሪ በብር 16,750.00 የገዙት ፊሪጅ አስፈላጊውን አገልግሎት መስጠት እንደማይችል እንደተረዱ ወደአመልካች ድርጅት አድርስው ድርጅቱ  እቃው እንደሚስተካከልላቸው ነግሯቸው እቃውን ተስተካክሏል በሚል ወደ ቤት ቢመልሱትም በተመሳሳይ ሁኔታ ለሁለተኛ ጊዜ ተበላሽቶ አገልግሎት መስጠት በማቆሙ እቃውን እንዲቀየርላቸው ድርጅቱን ቢጠየቁም ድርጅቱ ፈቃደኛ ያለመሆኑን ዘርዝረው አመልካች ድርጅት እቃውን እንዲቀይርላቸው ወይም የሽያጭ ገንዘቡን እንዲመልስላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም ከተጠሪ ጋር የፊሪጅ ሽያጭ ውል መኖሩን ሳይክድ ማቀዝቀዣው ተጠግኖ እንዲሰራ ማድረጉን፣ ለአንድ አመት ደግሞ የጥገና ዋስትና ግዴታ ከመግባቱ ውጪ ፊሪጁን ለመቀየር ወይም የሽያጭ ገንዘቡን ለመመለስ ግዴታ ያለመግባቱንና ባለው የጥገና ዋስትና መሰረት ማቀዝቀዣውን ጠግኖ  አመልካች ለመውሰድ ፈቃደኛ ያለመሆናቸውን ገልፆ ክሱ ውድቅ ሊሆንይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤትም ፊሪጁ መስራት አለመስራቱን በቦታው ላይ ተገኝቶ ከተመለከተ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ፍሪጁ መስራቱን መመልከቱን ገልፆ አመልካች በውሉ ባለው የጥግና ዋስትና ውል ግዴታውን መወጣቱ መረጋገጡን በምክንያትነት ይዞ ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኗ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱ ፍሪጁ መስራት አለመስራቱ ከሁለት ድርጅቶች ባለሙያ ተመድቦ እንዲጣራ ትዕዛዝ ቢሰጥም አመልካች ድርጅት ከኦሜዳድ ድርጅት የተላከውን ባለሙያ ማቀዝቀዣውን እንዳይመለከት አድርጎ ሳልኔት ከተባለው ድርጅት የተላከው ባለሙያ ብቻ እንዲመለከት አድርጎ ይህ ድርጅት ያቀረበውን ሪፖርት በመመርመር የአመልካች አካሄድ ከቅን ልቦና የሆነ ነው በሚል ድምዳሜ አመልካች ለተጠሪ ተመሳሳይ ሞዴል ማቀዝቀዣ እንዲቀይርላቸው ወይም ዋጋውን ብር 16,750.00 እንዲመልስላቸው ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት  ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ እና


በኦሜዳድም ሆነ በሳልኔት ድርጅት ባለሙያዎች ማቀዝቀዣው መስራት ያለመስራቱ ተጣርቶ እንዲቀርብ አድርጎ ድርጅቶቹ ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት ማቀዝቀዣ መስራቱ ቢረጋገጥም የባለሙያዎቹ አስተያየት እንደ አስገዳጅ ማስረጃ ሊወሰድ እንደማይችል፣እቃው ከሶስት ወራት በኋላ የማይበላሽ መሆኑን እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል፣አዲስ የተገዛ እቃ ሁል ጊዜ እያስጠገኑ መጠቀም አለበት ሊባል እንደማይገባ በምክንያት ይዞ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በድምፅ ብልጫ ሙሉ በሙሉ አንጽንቶታል፡፡በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታውን ያቀረበ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም፡፡የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ለተጠሪ የተሸጠው ማቀዝቀዣ የተበላሸው በተጠሪ የአጠቃቀም ችግር የተከሰተ ሁኖ የሽያጭ ውሉም በአመልካች ላይ ለአንድ አመት የጥገና ግዴታ ከሚጥል በስተቀር እቃውን ለመቀየር ወይም የሽያጭ ገንዘቡን ለመመለስ የማያስገድድ ሁኖ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ ከውሉና ከሕጉ ውጪ ነው የሚል ነው፡፡አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪም ጥሪ ተደርጎላቸው ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በአመልካችና በተጠሪ የተገባውን የሽያጭ ውል ስምምነት መሰረት ያደረገ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል፡፡

አመልካችና ተጠሪ የማቀዝቀዣ ሽያጭ ውል ማድረጋቸው፣አመልካች ማቀዝቀዣውን ቢበላሽ ለአንድ አመት የጥገና ዋስትና ግዴታ መግባቱን፣አመልካች እቃውን ለተጠሪ አስረክቦ ተጠሪ እቃውን በመጠቀም ላይ እንዳሉ መጀመሪያ ሲበላሽ አመልካች ባለው የጥገና ግዴታ እቃውን ጠግኖ ሲመልስ እንደገና በመበላሸቱ ተጠሪ እቃውን ለአመልካች መልሰው አመልካች እንደገና ጠግኖ እቃው እንዲሰራ ቢያደርግም ተጠሪ እቃው ካልተቀየረ አልረከብም ማለታቸው በክርክሩ ሂደት የተረጋገጡት ጉዳዮች ናቸው፡፡

በመሰረቱ ሽያጭ ማለት ሻጭ የሆነው አንዱ ወገን ገዥ ለሆነው ሌላ ወገን ዋጋው በገንዘብ የተወሰነውን አንድ ነገር ገዥው ሊከፍለው ግዴታ በገባበት መሰረት ሊያስረክብና ሀብትነቱን ሊያስተላልፍ የሚገደድበት ውል መሆኑ በፍ/ሕ/ቁ.2266 ተመልክቷል ፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ሻጭ የሆነ ወገን የሽያጩን ገንዘብ ከገዥ ወገን መጠየቅ መብት እንዳለው ሁሉ የተሸጠውን ነገር ደግሞ የማስረከብና ሀብትነቱን የማስተላለፍ ተነጻጻሪ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ሻጭ ያስረከበው ነገር በውሉ መሰረት ትክክል ለመሆኑና ጉድለት ስላለመኖሩ ለገዢው ኃላፊ ነው፡፡ ዕቃው እንደ ውሉ አይደለም የሚባለው ዋቢነት የሚሰጥባቸው ጉድለቶች እና ጉድለት ስለመኖሩ ፣ ጉድለት ያለ ከሆነ ደግሞ ጉድለቱ መቼ መመርመር እንዳለበት ፣ ገዢው የገዛው እቃ ጉድለት ያለበት ስለመሆኑ መቼ ማስታወቅ እንዳለበት እንዲሁም ጉድለትን አለማስታወቅና የሚያስከትለው ውጤትን አስመልክቶ በፍትሐብሔር ህጉ ከቁጥር 2288-2293 ድንጋጌዎች ስር በግልጽ ተመልክቷል ፡፡

ገዢ ጉድለቱን ካወቀበት ወይም ጉድለት ያለበት መሆኑን ካስታወቀበት ግዜ አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ክስ ካላቀረበ መብቱ በይርጋ የሚታገድ ስለመሆኑ በፍ/ሕ/ቁጥር 2298 የተመለከተ ሲሆን ይሁንና ሻጩ የደረሰውን ጉዳት የማስተካከል ወይም በአዲስ የመተካት መብቱ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2300 ድንጋጌ ተጠብቆለታል፡፡


የእቃውን ጉድለት መመርመርን በተመለከተ ህጉ ገዢው ግልፅ ጉድለትን በተመለከተ እቃውን በተረከበበት ግዜ የመመርመር ኃላፊነት እንዳለበት ሲያስቀምጥ ሻጩ ደግሞ ለድብቅ   ጉድለቶች

/በርክክብ ወቅት ሊታዩ ወይም ሊገለጽ የማይችሉ/ ሃላፊነት / let the seller be aware of latent / hidden/ defects/ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ተጠሪ በአመልካች ላይ ክስ ያቀረቡት ጉድለት መኖሩን መሰረት አድርገው ሳይሆን ብልሽቱ እንዲጠገንላቸው ለአመልካች ጥያቄ አቅርበው አመልካች በግራ ቀኙ መካከለ ባለው ውል መሰረት ጠግኖ ከሰጠ በኋላ እቃው እንደገና በመበላሸቱ ምክንያት በድጋሚ ሲጠገን ለታሰበው አገልግሎት ሊውል አይችልም በሚል  ነው፡፡ይሁን  እንጂ ማቀዝቀዣው የሚሰራ መሆኑ በባለሙያ የተረጋገጠ ሲሆን የባለሙያዎች አስተያየት ማቀዝቀዣው እስከመቼ እንደሚሰራ ባይረጋግጥም አመልካች ከተጠሪ ጋር ያለው ውል እቃው ቢበላሽ ጥገና ማድረግ መሆኑ ያልተካደ ጉዳይ ነው፤ስለሆነም አመልካች ለድብቅ ጉድለት ኃላፊነት አለበት ተብሎ ክስ ባልቀረበበትና በህጉ አግባብ የተቋቋመው ውል ደግሞ አድማሱ ለአንድ አመት ያህል አመልካች በነፃ የመጠገን ኃላፊነት ያለበት ስለመሆኑ የሚገልጽ ሁኖ እያለ ከግራ ቀኙ የውል ስምምነት እና ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2300 ድንጋጌ ይዘት ውጪ አመልካች ማቀዝቀዣውን እንዲቀየር ወይም የሽያጭ ገንዘቡን እንዲመልስ ተብሎ የተወሰነው የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1731፣2298 እና 2300 ድንጋጌዎችን የጣሰ ሁኖ አግኝተናል፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ የግራ ቀኙን ስምምነት እና በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጡትን ነጥቦችን ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለአገኘን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

 

1. በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 14450 መጋቢት 05 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 160863 ነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ/ም ፣በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት 174255 ህዳር 03 ቀን 2006 ዓ/ም በትዕዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. የአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.58788 ሰኔ 15 ቀን 2004 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል፡፡

3. አመልካች በውሉ በገባው ግዴታ መሰረት ማቀዝቀዣውን ጠግኖ አግልግሎት እንዲሰጥ ከማድረግ ውጪ ማቀዝቀዣውን የመቀየር ወይም የሽያጭ ገንዘቡን የመመለስ ግዴታ የለበትም ብለናል፡፡

4. ግራ ቀኙ ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡