95797 contract law/ administrative contract/ non performance/ interest

-ከአስተዳደር ውሎች አለመፈፀም ጋር ተያይዞ የወለድ ጥያቄ ሊቀርብ የሚችለው የአስተዳደር መስሪያ ቤቱ በውሉ በተመለከተው መሠረት ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ለተዋዋዩ ስለ ገንዘቡ አከፋፈል የሚያስፈልገውን የማረጋገጥ ሥራ ሳይፈጽም የቀረ እንደሆነ ወይም የአስተዳደር መስሪያ ቤቱ የሚፈለግበትን ገንዘብ የማረጋገጥ ሥራ በተፈፀመ በ3 ወር ውስጥ ሳይከፍል የቀረ እንደሆነ ስለመሆኑ፣

 

-ተቃራኒ የውል ቃል ቢኖርም እንኳን ከአስተዳደር መስሪያ ቤት ጋር የተዋዋለው ሰው መስሪያ ቤቱ ሳይከፍል  ለቆየበት  ገንዘብ ወለድ ወይም ኪሣራ ለመጠየቅ የሚችለው ሳይከፈል የቆየበት ጊዜ ከ6 ወር በላይ ሲሆን ወይም ውሉን ያደረገው የአስተዳደር መስሪያ ቤት ተዋዋዩን ለመጉዳት ብሎ ያደረገው ወይም ከባድ በሆነ ቸልተኝነትና ወይም ጥፋት ያደረገ ስለመሆኑ፣

 

የፍ/ህ/ቁ. 3196፣3197

የሰ/መ/ቁጥር. 95797

 

ጥር 20 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኸሊት ይመሰል

አመልካች፡- ደበበ ድርሪሳ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ -ስራ አስኪያጆች ባለቤት ደበበ ድሪርሣ ቀረቡ ተጠሪ፡- የፈንታሌ ወረዳ ውሃ ማእድን ኢነርጂ ፅ/ቤት - የቀረበ የለም፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ርድ

 

ጉዳዩ ከንጹህ ውሃ ግንባታ ጋር ተያይዞ የተነሳውን የወለድ ክፍያ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ እና በፈንታሌ ወረዳ ገንዘብና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት ላይ በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም አመልካች ከአሁኑ ተጠሪ ጋር በ17/08/2002 ዓ/ም በተደረገ የውል ስምምነት መሰረት የንጽህ ውሃ ግንባታ በፈንታሌ ወረዳ ከኒፋ ቀበሌ ውስጥ ለማከናወን ግዴታ ገብቶ በውሉ  መሰረት ስራው ተሰርቶና በባለሙያ ተለክቶ የ1ኛ የ2ኛ እና የ3ኛ ዙር የምስክር ወረቀት ተዘጋጅቶ ክፍያ የተፈፀመለት መሆኑን ከዚህ በኋላ የተሰራው ስራም ተለክቶ የ4ኛዙር ላይ ብር 239,828,88 የ5ኛ ዙር ሰርተፊኬት ላይ ብር 131,975,13 ለአመልካች ሊከፈል ይገባል በማለት በባለሙያ ሰርተፊኬት ተዘጋጅቶ ለሥር ከሳሾች ቢደርስም ክፍያውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆኑም በማለት የብር 371,803,88 ከተለያዩ የወጪና ኪሳራ ክፍያዎች እንዲሁም ከ20%ቅጣት ጋር ሊወሰንልኝ ይገባል በማለት ዳኝነት ጠይቋል ፡፡ የአሁኑ ተጠሪም አመልካች ስራውን እንደውሉ ያለመፈጸሙንና ውሉን በጊዜ ገደቡ ያለማጠናቀቁን ጠቅሶ ለአመልካች ክፍያ ለመፈጸም የሚገደድበት አግባብ ያለመኖሩን ዘርዝሮ ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የወረዳው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የአመልካችን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደረገው ሲሆን የአሁኑ አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዪን መርምሮ የአሁኑን አመልካች ለክሱ ኃላፊ አድርጎ ብር 412,668,41(አራት መቶ አስራ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስምንት ብር ከአርባ አንድ ሳንቲም)ተጠሪ ለአመልካች ሊከፍል ይገባል በማለት ወስኗል፡፡ወጪና ኪሳራን በተመለከተ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ያለ ሲሆን ወለድና ቅጣትን በተመለከተ ግን የአሁን አመልካች ጠይቆ ውሉ የተደናቀፈው በተጠሪ ስላልሆነ መክፈል ያለበትን ገንዘብ አለመክፈሉ ቅጣትን ወለድን የሚያስከፍለው አይደለም በማለት ወስኗል፡፡ ወለድና ቅጣትን እንዲሁም ወጪና ኪሳራን በተመለከተ በተሰጠው የውሳኔ ክፍል የአሁኑ አመልካች ቅር


በመሰኘት የሰበር አቤቱታውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርቦ ችሎቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ወጪና ኪሳራን በተመለከተ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተሰጠውን የውሳኔ ክፍል በመሻር ይግባኝ ሰሚው ችሎት ወጪና ኪሳራውን በተመለከተ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 462 እና ተከታይ ድንጋጌዎች አግባብ ግራቀኙ አከራክሮ እንዲወስን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 343(1)መሰረት መልሶለታል የአሁኑ የአመልካች የሰበር  አቤቱታ የቀረበው የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ወለድን በተመለከተ ዳኝነት ያለመስጠቱ ያላግባብ ነው በሚል ሲሆን ጉዳዩ ተመርምሮም የአመልካች የወለድ ይከፈልኝ ጥያቄ መታለፉ ባግባቡ መሆን ያለመሆኑ በጭብጥነት ተይዞ ጉዳዩ በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ተጠሪ ቀርቦ በሰጠው መልስ ተጠሪ ከአመልካች ጋር በገባው የውል ግዴታ መሰረት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ዙር ያሉትን ክፍያዎችን በአግባቡ የከፈለ ሁኖ በ4ኛ እና 5ኛ ዙር ክፍያዎች ግን ከአመልካች ጋር በውል በተቀመጡ መሰረታዊ ጉደዮች ላይ ወደ ክርክር የተገባ በመሆኑና የሥራው ጊዜም ከ72 ቀናት ያለፈ በመሆኑ ሳይከፈል ለቆየው ገንዘብ ወለድ የሚከፍልበት የሕግ ምክንያት የለም ሲል ተከራክሯል አመልካችም የሰበር አቤቱታውን በማጠናከር የመልስ መልሱን ሰጥቷል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው  ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል ፡፡

 

አመልካች ለሰራው ስራ 4ኛ እና 5ኛ ዙር ክፍያ እንደሚገባው  በባለሙያሰርቲፊኬት የተረጋገጠለት ቢሆንም ተጠሪ ጋር ውሉ በአግባቡ አልተከናወነም በሚል ወደ ክርክር የገቡ መሆኑ የክርክሩ ሂደት ያሳይል አመልካች በዚህ ሰበር ደረጃ የሚከራከረው ተጠሪ ሕጋዊ ወለድ የማይከፍልበት አግባብ የለም በሚል ሲሆን ለዚህም እንደ ሕጋዊ ምክንያት የሚያቀርበው ክርክር የተነሳበት ገንዘብ መጠን ከተሰራው ስራ ጋር በማመዛዘን የመስሪያ ቤቱ ባለሙያና ምድብ ሰራተኛ የክፍያ ሰርተፊኬት አዘጋጅቶ ካቀረበው ጊዜ ጀምሮ የሚታወቅ እዳ ነው የሚል ነው፡፡

 

ይሁን እንጂ በውሉ መሰረት ስራው መሰራት ያለመሰራቱ ላይ ግራ ቀኙ ሊተማመኑ ባለመቻሉ ወደ ክርክር የገቡ መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል ፡፡ ይህ ደግሞ በአመልካች ላይ የጥቅም መቀነስን የሚያስከትል መሆኑ ግልፅ ቢሆንም ስራው በውሉ መሰረት መሰራት ያለመስራቱ አከራካሪ እስከሆነ ድረስ የታወቀ እዳ እያለ ተጠሪ ለአመልካች ሳይከፍል ዘግይቷል ሊባል የሚችል አይደለም ፡፡ አመልካች ላይ በተጠሪ ያልተገባ የውል ተግባር ቀጥተኛ የሆነ የገንዘብ ኪሳራ የደረሰባቸው መሆኑ በሚገባ የተረጋገጠ ጉዳይ አይደለም፡፡

 

ወለድ በሕጉ አግባብ የተዘረጋው ስርዓት እንደተጠበቀ ሁኖ በስምምነት ወይም ያለስምምነት ሊከፍል የሚችል ገንዘብ ነው፡፡ወለድ ተበዳሪ የወሰደውን ገንዘብ ወይም እቃ በወቅቱ ባለመመለሱ የተነሳ የሚከፈል የገንዘብ ካሳ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ስራ ውልም ወለድ ሊጠየቅበት የሚችል አግባብ ያለ ሲሆን አላማውም የገንዘብ ኪሳራን ማካካሻ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ምክንያቱም ከላይ ከተገለጸው የወለድ አይነት ሌላው አይነት ወለድ አንድ ሰው ግዴታውን ባለመፈፀሙ ወይም በማዘግየቱ የተነሳ የሚከፈለው ካሳ እኩያ መሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1803 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የምንችለው ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ወለድ ለገንዘብ ብድር ብቻ እንዲከፈል የሚደረግ የካሳ የአይነት ሳይሆን ለግዴታ ባለመፈጸም ወይም ማዘገየት የተነሳ የሚከፈል ካሳ በመሆኑ ይህ ሲረጋገጥ ብቻ የሚከፈል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የተያዘውን ጉዳይ ስንመለከት አመልካች የንጹህ ውሃ ግንባታ ውል ስምምነት ያደረገው ከአስተዳደር መስሪያ ቤት ጋር   ነው፡፡


ከአስተዳደር ውሎች ያለመፈፀም ጋር ተያይዞ የወለድ ጥያቄ የሚቀርብበት አግባብ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 3196 እና 3197 ድንጋጌዎች የሚታይ ነው ፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 3196 ድንጋጌ ይዘት ሲታይ የወለድ ጥያቄ ማስጠንቀቂያ መስጠት ሳያስፈልግ ተገቢነት የሚኖረው የአስተዳደር መስሪያ ቤቱ በውሉ በተመለከተው መሰረት ከአስራ አምስት ቀን በኃላ ለተዋዋዩ ስለ ገንዘቡ አከፋፈል የሚያስፈልገውን የማረጋገጡ ስራ ሳይፈጽም የቀረ እንደሆነ ወይም  የአስተዳደር መ/ቤት የሚፈለግበትን ገንዘብ የማረጋገጡ ስራ በተፈፀመ በሶስት ወር ውስጥ ሳይከፈል የቀረ እንደሆነ ስለመሆኑ ያስገነዝባል የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 3197 ድንጋጌ ደግሞ ተቃራኒ የውል ስምምነት ቢኖርም እንኳን ሳይከፈል የቆየበት ጊዜ ከስድስት ወር በላይ ሲሆን ወይም ውሉን ያደረገው የአስተዳደር መስሪያ ቤት ለመጉዳት ብሎ ያደረገው ወይም ከባድ በሆነ ቸልተኛነት ወይም ጥፋት ያደረገው የአስተዳደር መስሪያ ቤት ለመጉዳት ብሎ ያደረገው ወይም ከባድ በሆነ ቸልተኛነት ወይም ጥፋት ያደረገው ሲሆን ወለድ ሊጠየቅና ተቀባይነት ሊሰጠው እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ እንዲሁም ከወለድ አላማ አንፃር አሁን የተያዘውን ጉዳይ ስንመለከተው አመልካች ግዴታውን በውሉ በተቀመጠው አግባብ አልፈጸመም በሚል ምክንያት ተጠሪ ክፍያውን ሳይፈጽም የዘገዬ መሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ አመልካች የካሳ እኩያ የሆነውን ወለድ የሚያገኙበት የሕግ ምክንያት አላገኘንም ፡፡

 

ሲጠቃለልም ከላይ በተገለፁት ሕጋዊ ምክንያቶች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ፍርድ ቤት ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስላላአገኘነው ተከታዩን ወስነናል ፡፡

 

 ው ሳኔ

 

1. በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 159905 ጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

2. የአመልካች የወለድ ክፍያ ጥያቄ በመታለፉ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የለም ብለናል፡፡

3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ፤ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት ፡፡