104294 labor law dispute/ breach of duty by employee/ termination without notice

አንድ ሠራተኛ የስራ ግዴታውን በአግባቡ ባለመወጣት በአሰሪው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ ጉዳት ያደረሰ ከሆነ የስራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ በቂ ምክንያት ሥለመሆኑ፣

 

አዋጅ ቁጥር 377/96 (1)(ሸ)፣ 12(2)(7)

የሰ/መ/ቁ. 104294 ቀን 29/07/2007 ዓ/ም

ዳኞች፡-  አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- ሐግቤስ ኃ/የተ/የግል/ማህበር - ነ/ፈጅ ፀጋዬ መካሻ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ በላይ ገ/ማሪያም - ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው በፌዴደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአመልካች የስንብት እርምጃ ህገ ወጥ ነው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመጽናቱ በውሳኔው ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልካች ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 “ን” መሰረት ያደረገ የግል የስራ ክርክር ሁኖ አንድ ሰራተኛ ከአሰሪው ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል ተብሎ ከስራ ያለማስጠንቀቂያ የሚሰናበትበትን የህግ አግባብ ነው፡፡

በስር ፍርድ ቤት የቀረበው የተጠሪ ክስ አመልካች ተጠሪን በጨረታ እንዳይሳተፍ የተደረገውን ጥፋት ሳይፈጽም ይህንኑ ጥፋት ፈጽመሃል በሚል ምክንያት የስራ ውል አላግባብ ያቋረጠ በመሆኑ የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲከፍል ይወሰንልኝ የሚል ነው፡፡ የአሁኑ  አመልካች በተከሳሽነቱ ቀርቦ በሰጠው መልስ የተጠሪ የስራ መዝርዝር በግልጽ የሚያሳየው የጨረታ ሰነድ አዘጋጅተው የጨረታውን ሂደት በመከታተል ሪፖርት ማቅረብ መሆኑን ፣ ተጠሪ ይህንኑ የስራ ግዴታ በመተላለፍ የጨረታ ሰነድ ሳያስገቡ በቀሩት የማሽን ጉልበት አመልካች ድርጅት ከጨረታ እንዲሰረዝ በመደረጉ ለተጠሪ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ቢሆንም አመልካች ድርጅት ተሳታፊ እንዲሆን በወሰነበት የትግራይ የውሃስራዎች ኮንስትራክሽን መጋቢት 05 ቀን 2005 ዓ/ም ባወጣው ጨረታ ጨረታውን ሳይከታተሉ በመቅረታቸው ድርጅቱ በጨረታው እንዳይሳተፍ አድርገው የጥቅም ማጣት እንዲደርስበት ያደረጉ መሆኑን ዘርዝሮ ስንብቱ በህጉ አግባብ የተደረገ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡

የስር ፍ/ቤት ተጠሪ በፈጸሙት ከባድ ቸልተኝነት ምክንያት አመልካች ድርጅት በጨረታው ላይ ሳይሳተፍ የቀረ መሆኑ ቢረጋገጥም በዚህ ጥፋት ምክንያት በአመልካች ድርጅት ላይ የደረሰ ጉዳት መኖሩ አልተረጋገጠም የሚል ምክንያት አስፍሮ የአመልካች የስንብት እርምጃ ህገ ወጥ ነው በማለት አመልካች ለተጠሪ የተለያዩ ክፍያዎችን ሊከፍል ይገባል በማለት የክፍያዎችን


አይነትና መጠን በመዘርዘር በድምሩ ብር 72,000.00 (ሰባ ሁለት ሺህ) እንዲከፍል፣ የስራ ልምድ የምስክር ወረቀት አዘጋጅቶ እንዲሰጠው ሲል ወስኗል፡፡

አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ሲሆን የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ተጠሪ በስራ መዘርዝራቸው መሰረት ግዴታቸውን ያለመወጣታቸውና ከባድ ቸልተኝነት የነበረባቸው መሆኑን የስር ፍርድ ቤት አረጋግጦ ጉዳት ስለመድረሱ አልተረጋገጠም በሚል ምክንያት ብቻ ስንብቱ ህገ ወጥ ነው በማለት የወሰነው ከህጉ ይዘትና መንፈስ ውጪ ነው ፣ አመልካች በጨረታው ላይ ባለመሳተፉ ከብር ሃያ ሶስት ሚሊዮን በላይ የጥቅም ማጣት ደርሶበታል በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በጽሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡ ተጠሪ በፅሁፍ በሰጡት መልስም በአመልካች ድርጅት ላይ ጉዳት ያለመደረሱን ፣ በስራቸው የፈጸሙት ጥፋትም የሌለ መሆኑን ዘርዝረው ተከራክረዋል፡፡

ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም ጉዳዩን መርምረናል፡፡ ጉዳዩን እንደመረመርነው የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች የተጠሪን የስራ ውል ያቋረጠው ከህግ ውጭ በመሆኑ ፣ ለተጠሪ የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲከፍል የሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ጭብጥ መታየት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ጉዳዩን እንደመረመርነው የተጠሪ የስራ መዝርዝር በግልጽ የሚያሳየው የጨረታ  ሰነድ አዘጋጅተው የጨረታውን ሂደት በመከታተል ሪፖርት ማቅርብ መሆኑንና ይህንኑ የስራ ግዴታ ባለመወጣታቸው አመልካች ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንደገና አመልካች ድርጅት ተሳታፊ እንዲሆን በወሰነበት የትግራይ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን መጋቢት 05 ቀን 2005 ዓ/ም ባወጣው ጨረታ ጨረታውን ሳይከታተሉ በመቅረታቸው ድርጅቱ በጨረታው እንዳይሳተፍ ያደረጉ መሆኑ በበታች ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል፡፡ ተጠሪም ይህንን ጥፋት ያልፈጸሙ መሆኑን በማስረጃዎቹ ያላስረዱ መሆኑን ከስር ፍርድ ቤቶች የውሳኔ ይዘት ተገንዝበናል፡፡ ተጠሪ በዚህ የሰበር ክርክር ደረጃ ባቀረቡት መልስ በአመልካች ድርጅት ላይ በጨረታ ባለመሳተፉ የደረሰ ጉዳት የለም በማለት ከገለፁ በኋላ በአማራጭ ደግሞ ከባድ ቸልተኝነት እንዳልነበራቸውና ጥፋት እንዳልፈጸሙ ዘርዝረው በዚሁ በአማራጭ ባቀረቡት ክርክር መሰረት የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ሊጸና ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡ ሆኖም ተጠሪ ከባድ ቸልተኘነት እንዳልነበራቸው ፣ ጥፋት እንዳልፈጸሙ የሚያቀርቡት ክርክር በሰበር መልሳቸው የተገለፀ እንጂ ስርዓቱን ጠብቆ  የቀረበ ነው ሊባል የሚችል ካለመሆኑም በላይ የስር ፍርድ ቤት ፍሬ ነገሩን አጣርቶና ማስረጃን መዝኖ የደረሰበት ድምዳሜ በመሆኑ በዚህ ችሎት ሊለወጥ የሚችል ሆኖ አልተገኘም፡፡ በመሆኑም ተጠሪ በከባድ ቸልተኝነት አመልካች ድርጅት በጨረታው ላይ እንዳይሳተፍ ያደረጉ መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ ነው በሚል የምንቀበለው ነጥብ ነው፡፡

አመልካች ተጠሪን ለቀደመው ጥፋታቸው በማስጠንቀቂያ ያለፋቸው ቢሆንም መጋቢት 05 ቀን 2005 ዓ/ም በወጣው ጨረታ እንዳይሳተፍ የተደረገው በተጠሪ ጥፋት መሆኑ በመረጋገጡ ተጠሪን ከስራ ሊያስናብታቸው ችሏል፡፡ አመልካች በዚህ ጨረታ ያልተሳተፈው በተጠሪ ከባድ ቸልተኝነት መሆኑ በበታች ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል፡፡ ተጠሪ የሚሰሩበት የስራ ባህርይ የጨረታ ሰነድ አዘጋጅተው የጨረታውን ሂደት በመከታተል ሪፖርት ማቅረብ መሆኑንም በስር ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠ በመሆኑ ተጠሪ አመልካች ድርጅትን ጥቅም ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥንቃቄና ትጋት በማድረግ ግዴታቸውን መወጣት የሚገባቸውና የድርጅቱ ኢኮኖሚ ጥቅም ጉዳት  እንዳይደርስበት  የማድረግ  የስራ  ግዴታ  አለባቸው፡፡  ተጠሪ  ይህንን  የስራ ተግባሩን


በአግባቡና በጥንቃቄ ባለመፈጸማቸው አመልካች ድርጅት ከጨረታ መሰረዙ  በድርጅቱ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ ጉዳት አላደረሰም ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ተጠሪ ጉዳዩን ጨረታን መሰረት ያደረገና በውድድር ላይ የተመሰረት መሆኑን ግልጸው የአመልካች ድርጅት የጨረታ ሰነድ ከሌሎች ተጫራቾች ጋር ሲነጻጸር ጨረታውን ሊያሽነፍ ይችል ያልነበረ መሆኑን ጠቅሰው ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ በጨረታው ውደድር በአመልካች ድርጅት ጥቅም የሚገኝበት አግባብ መኖሩ ግልጽ ከሆነና አመልካች በተጠሪ የስራ ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት ከውድድሩ ውጪ መሆኑ ከተረጋገጠ በአመልካች ድርጅት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ ጉዳት ያለመደረሱን የማስረዳት ግዴታ የተጠሪ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ግን ተጠሪ በአመልካች ላይ ጉዳት አልደረሰም ከማለት ውጪ ይህንኑ የሚያስረዳ ማስረጃ ያለማቅረባቸውን ከክርክሩ ሂደት ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ተጠሪ የፈጸሙት ጥፋት በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1/ሸ/ የሚሽፈንና የተጠሪን የስራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የሚያስችል በቂ ምክንያት ሆኖ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች በተጠሪ ከባድ ቸልተኝነት ምክንያት በአመልካች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም በማለት ስንብቱ ህገ ወጥ ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1)ሸ እና አንቀጽ 12(2)(7) ድንጋጌ መሰረታዊ ይዘት ፣ መንፈስና አላማ ያላገናዘብ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ከዚህ አንጻር ሲታይ አመልካች የተጠሪን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ በድጋሚ ጥፋት ሲፈጽሙ የስራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጡ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1)(ሸ) እና 12(2)(7) ድንጋጌዎች መሰረት ህጋዊ እንጂ ህገ ወጥ ተግባር ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች የተጠሪን የስራ ውል ያቋረጠው ከህግ ውጭ ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ ስለአገኘነው ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

1. በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 10206 ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 140042 ሐምሌ 25 ቀን 2006 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. የአመልካች እርምጃ ህጋዊ ነው፣ አመልካች ለተጠሪ ካሳም ሆነ የሰራ ስንብት ክፍያ ሊከፍል አይገባም ብለናል፡፡ የስራ ልምድ ምስክር ወረቀት ግን ይስጣቸው ብለናል፡፡

3.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

 

 

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት