101890 labor law dispute termnination of contract of apprentice

አንድ አሠሪ ለሙከራ የቀጠረውን ሠራተኛ በቀጠረው በ46ኛው ቀን ለስራው ብቁ አይደለም ብሎ የስንብት ደብዳቤ ቢጽፍለት ድርጊቱ ህገ ወጥ ነው ሊባል የማይችል ስለመሆኑ፣

 

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 11(2)፣(3)

የሰ/መ/ቁ. 101890

ጥቅምት 24 ቀን 2007 ዓ.ም.


 

አመልካች፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ- ጠበቃ አውላቸው  ደሣለኝ ቀረቡ፡፡ ተጠሪ፡- ወ/ት ፍጹም ኃይሉ - የቀረበ የለም፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

በዚህ ጉዳይ የቀረበው ክርክር የሥራ ውሉ ማቋረጡን የሚመለከት ነው፡፡ ለዚህ ሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው ተጠሪ ያቀረቡት ክስ ነው፡፡ የተጠሪ የዳኝነት ጥያቄ አመልካች ከግንቦት 3ዐ ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በዕቃ ግምጃ ቤት ተቆጣጣሪነት በቋሚ ደመወዝ ብር 2,639 የቀጠራቸው መሆኑና ያለማስጠንቀቂያ በ12/11/2005 የተፃፈ የቅጥር ውል ማቋረጫ ደብዳቤ በ15/11/2005 እንዲሰጣቸው በሕገወጥ መንገድ ከሥራ ሰለአሰናበታቸው የተለያዩ ክፍያዎች ተከፍሏቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ እንዲወሰን የሚል ነበር፡፡ የአሁኗ ተጠሪ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በትብብር በሚሰራ ድርጅት ተቀጥረው ሲሰሩ ስለነበር የተቀጠሩት በቋሚነት ነው በማለት ያቀረቡት ክርክር ከቀረበው ማስረጃ አንፃር ተገቢነት የለውም በማለት የታለፈ ሲሆን በግራ ቀኙ የነበረው የሥራ ውል ግንኙነት በ29/09/2005 ዓ.ም በተፃፈው ደብዳቤ ከግንቦት 7 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለ45 ቀናት የሙከራ ቅጥር ተቀጥረው ሲሰሩ እንደነበር መሠረት በማድረግ ታልፏል፡፡

አመልካች በሥር ፍርድ ቤት በተደረገው ክርክር ተጠሪ ሊመደቡበት ላቀደው የዕቃ ግምጃ ቤት የስራ መደብ ተስማሚ መሆናቸውን ለመመዘን ለ45 ቀናት የሙከራ ግዜ ተቀጥረው ለታቀደው ሥራ ተስማሚ ያለመሆናቸውን በማረጋገጥ ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ የሥራ ውል ማቋረጡን ገልጿል፡፡ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የግራ ቀኙ ክርክር እና ማስረጃ በማገናዘብ በሰጠው ውሣኔ ተጠሪ በሰጡት የምስክርነት ቃል የሥራ ውል ማቋረጫ ደብዳቤ የተሰጣቸው እ.ኤ.አ ጁላይ 22/2013 ወይም ወደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ሲመለስ ሐምሌ 15/11/2005 መሆኑን ፤ የአመልካች ምስክርም ደብዳቤው የተሰጣቸው ጁላይ 19 ቀን 2013 ወይም ሐምሌ 15 ቀን 2005 ዓ.ም ነው በማለታቸው የተጠሪ የሥራ ውል ማቋረጫ ደብዳቤ የተሰጣቸው በ46ኛው ቀን ሐምሌ 15/11/2005 ዓ.ም በመሆኑ ስንብቱ የሕግ መሠረት የለውም፡፡ አመልካች ለተጠሪ ያልከፈላቸው የ22 ቀናት ቀሪ ደመወዝ እንዲሁም የካሣ ክፍያ እንዲከፍላቸው የሥራ ልምድ ማስረጃም እንዲሰጣቸውበማለት ወስኗል፡፡ በይግባኝ ሥልጣኑየተመለከተው ከፍተኛ ፍ/ቤትም የአመልካችን ይግባኝ ሰርዞታል፡፡

አመልካችም በሥር ፍ/ቤቶች ፍርድ ላይ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን የቅሬታ ነጥቡም ሲጠቃለል፡- በአመልካች እና ተጠሪ የነበረው የሥራ ግንኙነት ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ ጁላይ 19 ቀን 2013 እ.ኤ.አ በተፃፈ ደብዳቤ መቋረጡ፤ ይህ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ሲመለስ ሐምሌ 12 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም መሆኑን እየታወቀ የውል መቋረጫ ደብዳቤ በ43ኛው  ቀን


ተድፎ ሳለ ስንብቱ በ46ኛው ቀን የተደረገ በመሆኑ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ በሥር ፍርድ ቤት መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡ ተጠሪ በበኩላቸው በሰጡት መልስ ከአሁን በፊት ለ5ወር ከ6 ቀን በማቴሪያል ኢንቨንተሪ ኮንትሮል ሥራ በአመልካች መስሪያ ቤት መሥራታቸው እየታወቀ ድጋሚ በዚያው ሥራ በሙከራ የቅጥር ውል መሥራታቸው ሕጋዊ አለመሆኑን

፤የሥር ፍ/ቤት ማስረጃዎች በመመዘን ውሣኔ መስጠቱ ፤የተጠሪ ምስክሮች የሥራ ውል ማቋረጫ ደብዳቤ እ.ኤ.አ ጁላይ 22 ቀን 2013 እንደተሰጣቸው ማስረዳታቸውአመልካች በሕግ የተቀመጠውን 45 ቀን አሳንሶ በ43ኛው ቀን የስንብት ደብዳቤ መስጠት እንደማይችል፤ ደብዳቤውም ከሥራ ሰዓት ውጭ የተሰጣቸው መሆኑንበመግለጽ የሥር ፍ/ቤት እንዲፀና አመልክቷል፡፡ አመልካችም ተጠሪ ላቀረቡት መልስ የመልስ መልስ በማቅረብ አቤቱታውን በማጠናከር ተከራክሯል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙ ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማዛመድ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

ከሥር ፍርድ ቤት መዝገብ መረዳት እንደተቻለው በአመልካች እና ተጠሪ በሙከራ ጊዜ ላይ የተመሰረቱ የሥራ ቅጥር ውል መፈፀሙን ነው፡፡ ተጠሪ ከድርጅቱ ጋር ግንኙነት ባለው ሌላ ድርጅት በዚህ የሥራ መደብ ላይ ሲሰሩ እንደነበር በድጋሚ በተመሳሳይ የሥራ መደብ ለሙከራ መቀጠራቸው ሕጋዊ አለመሆኑን በመጥቀስ ቢከራከሩም የሥር ፍርድ ቤት  ለሙከራ የተቀጠሩበት ደብዳቤ በማስረጃነት በመውሰድ ክርክራቸው አግባብነት የሌለው መሆኑን በውሣኔው አስፍሯል፡፡ ተጠሪ ይህንን ውሣኔ በመቃወም ያቀረቡት ይግባኝ ይሁን መስቀለኛ አቤቱታ የለም፡፡ በዚህ ረገድ በሰበር አቤቱታቸው በሥር መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ውድቅ የተደረገው ክርክር በሰበር ደረጃ ማቅረባቸው ሥነ-ስርዓታዊ አካሄድ የተከተለ አይደለም፡፡

አንድ ሠራተኛ ሊመደብበት ለታቀደው ቦታ ተስማሚ መሆኑና አለመሆኑን ለመመዘን ለሙከራ ጊዜ ሊቀጠር እንደሚችል፤ ይህ የግራ ቀኙ ስምምነትም በጽሑፍ መደረግ እንዳለበት፤ የሙከራ ጊዜውም ከ45 ተከታታይ ቀናት መብለጥ እንደሌለበት ከአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 11(1) ፣(2) እና (3) አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ነው፡፡ አመልካች ተጠሪን ለሙከራ ጊዜ መቅጠሩ በሥር ፍ/ቤት የታመነበት ጉዳይ ነው፡፡ አመልካች ተጠሪን በግዜ ገደቡ ውስጥ ማሰናበቱን ሲከራከር ተጠሪ ደግሞ በ46ኛው ቀን የተሰናበቱ መሆናቸው በመግለፅ ስንብቱ ህገ ወጥ እንዲባልላቸው አመልክተዋል፡፡ በስር ፍ/ቤት የአመልካች ምስክሮች ስንብቱ እ.ኤ.አ. ጁላይ 19 ቀን 2013 መሆኑን ይህ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር ሲመለስ ሐምሌ 15 ቀን 2005 ዓ.ም መሆኑን በሥር ፍርድ ቤት መዝገብ ሰፍሯል፡፡ ተጠሪ በሰጡት የምስክርነት ቃል የስንብት ደብዳቤው እ.ኤ.አ. ጁላይ 22 ቀን 2013 መሆኑ፤የጊዜ ስሌቱ ሲሰራ ከተቀጠሩበት ጊዜ ጀምሮ በ46ኛው ቀን መሆኑን ገልጿል፡፡ የሥር ፍርድ ቤቱ የአመልካች ድርጊት ሕገወጥ ነው ለማለት እንደመነሻ የወሰደው ተጠሪን በ46ኛው ቀን ከሥራ አሰናብቷል በሚል ነው፡፡ አመልካች ተጠሪን ያሰናበታቸው በ43ኛ ቀን ነው?ወይስ በ46ኛው ቀን?በ46ኛው ቀን ሲሰናበቱ ሕጋዊ ውጤቱስ የተለየ ሊሆን ይችላል? የሚለው መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ የሥር ፍ/ቤት በአመልካች ተሰጠ የተባለው ደብዳቤ እ.ኤ.አ አቆጣጠር ጁላይ 19 ቀን 2013 ዓ.ም የተጻፈ መሆኑ ወደ ኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር ሲመለስ                         ደግሞ ሐምሌ 15 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም  መሆኑን በውሣኔው አስፍሯል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት እ.ኤ.አ. ጁላይ 19 ቀን 2013 ወደ ኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር ሲመለስ  ሐምሌ  15  ቀን 2ዐዐ5  ዓ.ም  በማለት በውሣኔ  የተጠቀሰው  ተቀባይነት

/conventional/ ካልሆነው የጊዜ አቆጣጠር ቀመር አኳያ ሲታይ አግባብነት ያለው አይደለም፡፡ ከላይ የተገለፀው ጁላይ 19 ቀን 2ዐ13 ወደ ኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር ሲመለስ ሐምሌ 12  ቀን


2ዐዐ5 ዓ.ም መሆኑን ተቀባይነት ካለው የጊዜ አቆጣጠር /ካላንደር/ አንፃር በማዛመድ በቀላሉ ግንዛቤ የሚወሰድበት ነው፡፡ በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤት ጁላይ 19 ቀን 2ዐ13 እ.ኤ.አ ወደ ኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር ሲመለስ ሐምሌ 15 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ነው፡፡ በማለት ማስፈሩ አግባብነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ አመልካች ተጠሪን ሐምሌ 12 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ የሙከራ ግዜ ቅጥር ውል እንዲቋረጥ የተደረገ ከሆነ በ45 ቀን ጊዜ ገደብ ውስጥ የተፃፈ ደብዳቤ መሆኑ መረዳት ይቻላል ፡፡ አመልካች ተጠሪ ሊመደቡበት ለታቀደው ቦታ ተስማሚ መሆኑን አለመሆናቸው በ45 ቀን ውስጥ ውሣኔ ማስተላለፍ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ካለው ሕግ ጋር የሚቃረን ውሣኔ አይደለም፡፡

የሥር ፍርድ ቤት የአመልካች ድርጊት ሕገወጥ ነው በማለት ለመወሰን እንደ መነሻ የወሰደው ስንብቱ በ46ኛው ቀን ተከናውኗል በሚል ነው፡፡አንድ አሠሪ የሙከራ ጊዜ ውል ያለአግባብ በማሳጠር ይሁን ከሚገባው በላይ ጊዜው በማራዘም የሠራተኛው የተረጋጋ የሥራ ዋስትና እንዳይኖር ማድረግ እንደሌለበት ከአጠቃላይ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅቁ. 377/96 ድንጋጌዎች የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ይሁንና አሠሪው በ45ኛው ቀን መጨረሻ ይሁን በ46ኛው ቀን መጀመሪያ ሠራተኛው ለተመደበበት የሥራ ቦታ ተስማሚ አይደለም በማለት ከወሰነ የፈጠነ ወይም በጣም የዘገየ ውሣኔ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ የሙከራ ግዜው በ45ኛው ቀን መጨረሻ የሚጠናቀቅ ከሆነ በ46ኛው የመጀመሪያ ቀን የስንበት ደብዳቤ መፃፉ የሠራተኛው የሥራ ዋስትና አደጋ ውስጥ አስገብቷል ለማለት የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት የለውም፡፡ በሥር ፍ/ቤት ተረጋግጧል የተባለው ፍሬ ነገር ተወስዶ ደብዳቤው በ46ኛው ቀን ነው የተፃፈው ቢባል እንኳ የአሠሪው የማሰናበት መብትና ሥልጣን ዘግይቶ ተግባራዊ የተደረገ ነው ሊባል አይችልም፡፡ የሙከራ ጊዜ ውል ለ 45 ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል ከሆነ ግለሰቡ በመጨረሻው ቀን በመገምገም ለታቀደው ቦታ ተስማሚ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ውሣኔ ለማስተላለፍ የመጨረሻ ቀን የሥራ አፈፃፀም ውጤት ጭምር ታሳቢ መደረግ ያለበት በመሆኑ በ46ኛው ቀን የስንብት ደብዳቤ መፃፉ የሕጉን ይዘትና መንፈስ የሚቃረን አይደለም፡፡ ስለሆነም የሥር ፍ/ቤቶች ግራ ቀኙ እያከራከረ ያለውን ጉዳይ በአግባቡ ሳያገናዝቡ የሙከራ ጊዜ ከ45 ቀናት መብለጥ የለበትም የሚለውን የሕጉ ይዘት ከአጠቃላይ የሕጉ ዓላማና ግብ ሳያገናዝቡ መወሰናቸው በአግባቡ አይደለም ብለናል፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት የሥር ፍ/ቤቶች የአመልካች ድርጊት ሕገወጥ ነው በማለት መወሰናቸው መሠረታዊ የሕግ አተረጓጐም ስህተት ፈጽመዋል፡፡ በመሆኑም ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ት ዕ ዛ ዝ

1. የፌዴራል የመ/ደ/ፍ/ቤት በኮ.መ.ቁ.85529 በ18/07/2006 ዓ.ም እንዲሁም የፌ/ከ/ፍ/ቤት በኮ.መ.ቁ. 139947 በ19/07/2006 የሰጡት ፍርድ እና ትዕዛዝ ተሽሯል፡፡

2.  አመልካች ተጠሪ ያለማስጠንቀቂያ ማሰናበቱ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡

3. ለዚህ ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸው ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

ብ/ግ                                     የማይነበብ   የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡