101913 labor law dispute priority of payment to employees

ከአሠሪና ሠራተኛ ክርክር ጋር በተነሳ ማንኛውም የሠራተኛ ክፍያ ጥያቄ ከማናቸውም የክፍያ ወይም የዕዳ ጥያቄ ቅድሚያ የሚኖረው ለሠራተኛ እንጂ ለስራ መሪዎች ስላለመሆኑ፣

 

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 2(2)(ሐ) (3)፣167

የሰ/መ/ቁ.101913 የካቲት 17 ቀን 2007

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶ መላከ ሙሉጌታ - ጠበቃ ሙሉጌታ ወንድምአገኘሁ ቀረቡ፡፡ ተጠሪ፡- አቶ አበበ አቡራ - አልቀረቡም

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 11115 ታህሳስ 21 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝና ታህሳስ 28 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ እንደዚሁም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 139436 ሰኔ 6 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠውየአፈፃፀም ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ በአፈፃፀም ሂደት የቀዳሚነት መብት ጥያቄን የሚመለከት ነው፡፡

 

1. የፍርድ ባለዕዳ የሆነው ዲማክዶ መስማት የተሳናቸው የተባለ ድርጅት በመክሰስ አመልካችና ተጠሪ የፍርድ ባለመብት ሆነዋል፡፡ ተጠሪ የድርጅቱ የሥራ መሪ ስለነበረ በፍትሐብሔር ሕጉ መሠረት የፍትሐብሔር ክስ አቅርቦ የፍርድ ባለመብት ሆኗል፡፡ የፍርድ ባለዕዳውንም ንብረት አስቀድሞ በማስከበር በአፈፃፀም እንዲሸጥ አድርጓል፡፡ አመልካች በፍርድ ባለዕዳው ላይ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሠረት ክስ አቅርቦ የፍርድ ባለመብት ሆኗል፡፡ አመልካች በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 167 መሠረትየቀዳሚነት መብት ያለኝ ስለሆነ በቅድሚያ ለእኔ ሊከፈለኝ ይገባል የሚል ጥያቄ አንስቷል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት አመልካችም ሆነ ተጠሪ የፍርድ ባለዕዳው ሠራተኞች በመሆናቸው የቀዳሚነት መብት ያለው ንብረቱን ቀድሞ በአፈፃፀም የሸጠው /ተጠሪ/ ነው በማለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ሁለቱም የፍርድ ባለመብቶች የፍርድ ባለዕዳ ሠራተኞች በመሆናቸው ከይግባኝ ባይ /አመልካች/ የቀዳሚነት መብት የለውም በማለት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ አፅንቶታል፡፡

2. አመልካች የፍርድ ባለዕዳው ንብረት ተሽጦ ከተገኘው ገንዘብ በቀዳሚነት ሊፈፀምልኝ ሲገባ የበታች ፍርድ ቤቶች በሕግ የተሰጠኝን ልዩ የቀዳሚነት መብት አሳጥተውኛል በማለት የስር


አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን ተጠሪ በበኩሉ እኔም የፍርድ ባለዕዳው ተቀጣሪ ሠራተኛ በመሆኔ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡትን አፈፃፀም ትዕዛዝ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል፡፡ አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡

3. ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ትዕዛዝ የሕግ መሠረት ያለው ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡

4. ጉዳዩን እንደመረመርነው ተጠሪ የፍርድ ባለዕዳውን ትምህርት ቤት ከስድስት ዓመት በላይ በወር 250 /ሁለት መቶ ሀምሳ የአሜሪካ ዶላር/ እየተከፈለው ያገለገለ መሆኑን፣ ተጠሪ የድርጅቱ የሥራ መሪ በመሆኑም ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቄራ ምድብ 2ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ክስ አቅርቦበመዝገብ ቁጥር 01892 ግንቦት 29 ቀን 2004 ዓ.ም የፍርድ ባለዕዳው 12,000 /አስራ ሁለት ሺ የአሜሪካን ዶላር/ እንዲከፍለው ውሣኔ የሰጡለት መሆኑን ተረድተናል፡፡ አመልካች በበኩሉ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቄራ ምድብ የሥራ ክርክር ችሎት ክስአቅርቦ የፍርድ ባለዕዳው ብር 28,173.33 /ሃያ  ስምንት ሺህ አንድ መቶ ሰባ ሦሰት ብር ከሰላሳ ሦስት ሣንቲም / ለአመልካች እንዲከፍል በመዝገብ ቁጥር 09226 ሐምሌ 8 ቀን 2005 ዓ.ም ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

5. ከላይ እንደተገለፀው በተጠሪና በፍርድ ባዕዳው መካከል የሥራ ቅጥር ውል መኖሩ ግልፅ ቢሆንም የፍርድ ባለዕዳው አመልካችን የቀጠረው በሥራ መሪነት  በርዕሰ መምህርነት እንደሆነ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ተረጋግጧል፡፡ በሌላ በኩል በአመልካችና በፍርድ ባለዕዳው መካከል የነበረው ግንኙነት በአዋጅ ቅጥር 377/1996 መሠረት የተመሠረተ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ አንድ የሥራ መሪ የሆነ ሰው በአሠሪው ድርጅት በፍትሐብሔር ሕጉ መሠረት ሊከፍለው የሚገባውን ክፍያ እንዲከፍለው ክስ አቅርቦ የፍርድ ባለመብት መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሠረት አሠሪው የሚያስተዳድራቸው ሠራተኞች በፍርድ እንዲከፈላቸው ያስወሰኑት ክፍያ ከመክፈሉ በፊት ፍርድ ተፈፃሚ ሊሆንለት ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለው የህግ ጥያቄ መታየት ያለበት ነው፡፡

6. ይህም ጥያቄ በቅጥር ላይ ከተመሠረተ የሥራ ግንኙነት የሚመነጭ ማናቸውም የሠራተኛ ክፍያ ጥያቄ ከማናቸውም የክፍያ ወይም የዕዳ ጥያቄ ቅድሚያ ይኖረዋል በማለት የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 167 ድንጋጌ አንፃር መታየት ያለበት ነው፡፡  በአዋጅ ቁጥር 377/1996 ሠራተኛ ማለት በአዋጅ አንቀጽ 4 በተመለከተው መሠረት ከአሠሪው ጋር በቅጥር ላይ የተመሠረተ የሥራ ግንኙነት ያለው እንደሆነ በአዋጅ አንቀጽ 2 ንዑስ  አንቀጽ 3 የተደነገገ ሲሆን የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 2/ሐ/ በተገለፁት የሥራ መሪዎች ላይ ተፈሚነት የሌለው መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አንፃር ተጠሪ የሥራ መሪ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 167 የተደነገገው ልዩ የቀዳሚነት መብት የለውም፡፡ በመሆኑም ልዩ የቀዳሚነት መብት ያለው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሠረት ከፍርድ ባለዕዳው ጋር የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ያለው አመልካች እንጅ ተጠሪ አይደለም፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ የቀዳሚነት መብት አለው  በማለት የሰጡት የአፈፃፀም ትዕዛዝ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀጽ 2፣ የአንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 2 እና አንቀጽ 167 የሚጥስና መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡


 

 ው ሣ ኔ

 

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ ተሻሽሏል፡፡

2. በአፈፃፀም የቀዳሚነት መብት ያለው ተጠሪ ነው በማለት የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት የውሣኔ ክፍል ተሽሯል፡፡

3. በአፈፃፀም የቀዳሚነት መብት ያለው አመልካች ነው በማለት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 167 መሠረት ወስነናል፡፡ የፍርድ ባለዕዳው ንብረት ተሽጦ ከተገኘው ገንዘብ፣ አመልካች በቅድሚያ ሊከፈለው ይገባል በማለት ወስነናል፡፡

4.  በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡

5.  በዚህ ፍርድ ቤት ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል፡፡

 


መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡ ብ/ግ


 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡