95638 labor law dispute jurisdiction of court

በስራ ክርክር የተከራካሪ ወገኖች ማንነት የፍርድ ቤቶችን ስልጣን (የክልል ወይም የፌዴራል)ብሎ ለመወሰን እንደወሳኝ  መለኪያ ሊወሰድ የማይገባ ስለመሆኑ፤

 

የአሰሪው እርምጃ ህገ ወጥነት የተረጋገጠ እንደሆነ  የክፍያ መጠኑ ሊሰላ የሚገባው አዋጁ ባስቀመጠው ስሌትና በማስረጃ በተረጋገጠ የደመወዝ መጠን መሆን ያለበት ስለመሆኑ፣

 

አዋጅቁጥር377/1996አንቀፅ 35(1(ለ))፣39(1(ለ))፣40(1)(2)፣43(4(ሀ)፣68፣71

የሰ/መ/ቁጥር 95638

 

መስከረም 29 ቀን 2007 ዓ/ም

 

ዳኞች፡-አልማው ወሌ ሡልጣን አባተማም መኮንን ገ/ሕይወት ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

አመልካች፡-ኢስት ሲሜንት አክሲዩን ማህበር - ጠበቃ ዓለሙ ደነቀው - ቀረቡ ተጠሪ፡-አቶ ዘላለም ታደሰ  - ጠበቃ ገናናው ተሾመ ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ  ር ድ

 

ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የቀረበውን የግል የስራ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረበት ፍርድ ቤት የሂደቡ አቦቴ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው፡፡በዚህ ፍርድ ቤት ከሳሽ የአሁኑ ተጠሪ ሁኖ የክሱ ይዘትም፡-በተጠሪ ድርጅት በአስተዳደር ኃላፊነት እና ጉዳይ አስፈፃሚነት አምስት አመት ከዘጠኝ ወር ብር 6,410.90 በወር እየተከፈላቸው ማገልገላቸውንና የስራ ውሉ ከሕግ ውጪ መቋረጡን ገልጸው ልዩ ልዩ ክፍያዎች እንዲከፈላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡የአሁኑ አመልካች ተከሳሽ የነበረ ቢሆንም መጥሪያ ደርሶታል፣ግን አልቀረበም ተብሎ በሌለበት ጉዳዩእንዲታይ ተደርጓል፡፡የሥር ፍርድ ቤትም ጉዳዩን መርምሮ የአሁኑ አመልካች ለክሱ ኃላፊ ነው ተብሎ ለከሳሽ ብር 277,294.00 ( ሁለት መቶ ሰባ ሰባት ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና አራት) ብር እንዲከፈል ወሰኗል፡፡

 

የአሁኑ አመልካች በሌለሁበት ታይቶ የተወሰነው ውሳኔ ተነስቶ ባለሁበት ይታይልኝ በማለት ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተጨማሪ ከሳሹ የአሰሪ ወገን ስለሆነ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ሊዳኙ አይገባም፣በአዋጁ መሰረት ሊዳኝ ይገባል ከተባለም የስራ ውሉ የተቋረጠው በሕጋዊ መንገድ ስለሆነ ሊፈጸም የሚገባ ክፍያ የለም፣ክፍያ ሊፈፀም ይገባል ከተባለም ከሳሽ ደሞዜ ነው ብሎ ያቀረበው መጠን ትክክል አይደለም፣በትክክል ደመወዙ ላይ ተመስርቶ ሊከፈል የሚገባውም የደመወዙን

     ኛውን ያህል ብቻ ነው ብሎ ተከራክሯል፡፡የስር ፍርድ ቤት በአመልካች በሌለሁበት ታይቶ

 

የተወሰነው ውሳኔ ይነሳልኝ ጥያቄ ላይ የአሁኑ ተጠሪ (የስር ከሳሽ) አስተያየት እንዲሰጡበት  ያደረገ

ሲሆን ተጠሪው በሰጡት አስተያየትም ለአመልካች መጥሪያውን ባቀረቡት የቃለ መሓላ አቤቱታ የተዘረዘሩ ምስክሮች የሚያረጋገጡ መሆኑን እና የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈሏቸው የተወሰነውም በአግባቡ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡የወረዳው ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ጉዳዩ ባለሁበት ይታይልኝ በማለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፣በቃለ መሐላ ተረጋግጧል በማለት ውሳኔ ሰጠ ፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ


ፍርድ ቤት አቅርቦ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ከዚህም በኋላ አመልካች የሰበር አቤቱታውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርቦ ችሎቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ መጥሪያው በሕጉ መሰረት ለአሁኑ አመልካች የደረሰው መሆንያለመሆኑን የግራ ቀኙን ምስክሮችእንዲሰሙና ተገቢው እንዲወሰን በማለት ጉዳዩን ለወረዳው ፍርድ ቤት መልሶታል፡፡ በዚህ አግባብ ጉዳዩ የተመለሰለት የወረዳው ፍርድ ቤትም በ18/03/2004 ዓ/ም የአሁኑ ተጠሪ ለወረዳው ፍርድ ቤት ባቀረቡት ቃለ መሃላ ላይ ያሉትን ምስክሮችን ከሰማ በኋላ የአሁኑ አመልካች ደግሞ የቀረቡት ምስክሮች ይበቁናል ስላለ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ መጥሪያው ለአመልካች መድረሱ ተረጋግጧል በማለት በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ውሳኔ አይነሳም ሲል በ24/05/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት ወሰኗል፡፡በዚህ ውሳኔ ላይ ለሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአሁኑ አመልካች ይግባኙን አቅርቦ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ መሰማት የሚገባቸው ምስክሮች በ18/03/2004 ዓ/ም በተጻፈ የተጠሪ ቃለ መሃላ ላይ ያሉት ምስክሮች ሳይሆኑ በ26/03/2004 ዓ/ም በተጻፈ ቃለ መሃላ ላይ ያሉት ምስክሮች ናቸው በማለት በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት መመሪያ መሰረት የወረዳው ፍርድ ቤት አልፈጸመም ሲል በዚህ ረገድ የተሰጠውን ውሳኔ በ28/06/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት ሽሮ በ26/03/2004 ዓ/ም በተጻፈ ቃለ መሃላ ላይ ያሉት ምስክሮች እንዲሰሙ ሲል ጉዳዩን ለወረዳው ፍርድ ቤት መልሶ ልኮለታል፡፡.የአሁኑ ተጠሪ በዚህ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ችሎቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ችሎቱ መሰማት የሚገባቸው በ18/03/2004 ዓ/ም በተፃፈ ቃለ መሃላ ላይ የተዘረዘሩት ምስክሮች ናቸው? ወይስ በ26/03/2004 ዓ/ም በተጻፈ ቃለ መሃላ ላይ የተገለፁት ምስክሮች ናቸው? የሚለውን ጭብጥ ይዞ ጉዳዩን በመመርመር የወረዳው ፍርድ ቤት በ12/03/2004 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ የተከሳሽን መልስ ለመቀበል ብሎ ለ18/03/2004 ዓ/ም መቅጠሩን፣በዚህ ቀን ከሳሽ ለተከሳሽ መጥሪያ ማድረሱን በመግለፅ በቃለ መሃላ የተከሳሽ መልስ የመስጠት መብት መታለፉን፣በ26/03/2004 ዓ/ም ደግሞ ከሳሽ ደመወዝ ሲበላበት የነበረ ፔሮል ለተከሳሽ ድርጅት እንዲያቀርብ የታዘዘ መሆኑን ከመዝገቡ መረዳቱን ጠቅሶ መሰማት ያለባቸው ምስክሮች በ18/03/2004 ዓ/ም በተፃፈው ቃለ መሃላ ያሉት ምስክሮች እንጂ በ26/04/2004 ዓ/ም በተጻፈ ቃለ መሃላ የተገለፁ ምስክሮች አይደሉም በማለት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ በ20/01/2006 ዓ/ም በዋለው ችሎት የተሠጠውን ውሳኔ ሽሮ የወረዳ ፍ/ቤት ውሳኔን አጽንቷል፡፡

 

የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም በዚሁ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ሲሆን የአመልካች የሠበር አቤቱታ ቅሬታ መሰረታዊ ነጥቦችም፡-የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለወረዳው ፍርድ ቤት የመለሰው በ26/03/2004 ዓ/ም በተፃፈ ቃለ መሃላ የተገለፁትን ምስክሮች እንዲሰሙ ሁኖ እያለ መልሶ መሰማት ያለባቸው በ18/03/2004 ዓ/ም በተጻፈ ቃለ መሃላ የተገለፁትን ምስክሮች ናቸው ማለቱ ተገቢነት የለውም፣የተጠሪው ደመወዝ ተጠሪው እንደገለፀው ብር 6,410.00 ሳይሆን ብር 3,230.70 ብቻ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ የስራ ስንብት ክፍያ ብር 47,383.60 እንዲሆን መወሰኑ ያላግባብ ሲሆን የስራ ስንብት ክፍያው ብር 8,348.00 ብቻ ነው፣የካሳ ክፍያ ብር 19,384.00 መሆን ሲገባው ብር 25,849.60 መሆኑ ያላግባብ ነው፣የሳምንት የእረፍት ክፍያ ሊተመን በማይችል ስሌት ብር 188,784.57 ሁኗል፣የአምስት አመት በዓል በማለት ብር 16,357.00 እንዲከፍል መወሰኑ ያላግባብ ነው፣የአመልካች እርምጃ ሕገ ወጥ ነው የሚባል ከሆነም ሊከፈሉ የሚገባቸው ክፍያዎች፤- የአገልግሎት ክፍያ ብር 8,384.30፣የሁለት ወር ማስጠንቀቂያ ብር 6,461.40፣የካሳ ክፍያ ብር 19,384.20 በድምሩ ብር 34,229.90 እንጂ ብር 277,294.00 እንዲከፈል መወሰኑ ያለአግባብ ነው በማለት በዚህ ችሎት እንዲወሰን የጠየቀው ዳኝነትም የአመልካች የመከራከር መብቱ እንዲጠበቅለት፣ይህ  የሚታለፍ  ከሆነ  በአዋጁ  መሰረት  ክፍያዎቹ  መወሰን  አለባቸው  የሚል


ነው፡፡የሠበር አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት ጉዳዩ እንዲታይ የተደረገው ከአመልካች ማንነት አንፃር ይህንኑ ጉዳይ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ተቀብሎ ማየቱ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ተብሎ ሲሆን ተጠሪ ቀርበው በሰጡት መልስም ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ስለሆነ አዋጁ ከወጣበት ጊዜ አንጻር በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የማይታይበት ምክንያት የለም፣ጉዳዩ የማስረጃ ምዘና ጉዳይ ስለሆነ በዚህ ችሎት የሚታይ አይደለም፣በሌለበት በታየ ጉዳይ በስንብቱ እና በደመወዝ መጠኑ ሊከራከርአይችልም፣ተጠሪ የአሰሪ የአስተዳደር አካል ያለመሆናቸው በማስረጃ ተረጋግጧል፣በቃለ መሃላ ጉዳይ ላይ ማስተባበያ ማስረጃ አላቀረበም፣የተጠሪ ምስክሮች የእኔም ምስክሮች ናቸው በማለት መግለፁን የስር ፍርድ ቤት መዝገብ ያሳያል፣የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ራሱ የሰጠውን ውሳኔ አልሻረም፣በ26/03/04 በተጻፈ ቃለ መሃላ የተገለጹት ምስክሮች የሚሰሙበት ምክንያት የለም፣በዚህ ቀን የቀረበው ቃለ መሃላ የስር ተከሳሽ ከሳሽ የሚበላውን ደመወዝ መዝገቡን እንዲያቀርብ በ22/03/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ አዞት ስለነበር ተከሳሹ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አልፈፀመም፣የፍርድ ቤቱን መጥሪያአልወስድም ማለቱን ለማረጋጋጥ ነው፣ በማለት ዘርዝሮ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 163369 በ20/01/2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ እንዲፀናላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡የአሁኑ አመልካችም ያስቀርባል የተባለበትን ነጥብ በመደገፍና በሰበር አቤቱታው ላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦችን በማጠናከር የመልስ መልሱን ሰጥቷል፡፡

 

ከዚህም በኋላ ይህ ችሎት ጉዳዩን መርምሮ አመልካች መጀመሪያ በሌለበት ታይቶ የተሰጠው ውሳኔ እንዲነሳለት ለወረዳው ፍርድ ቤት አመልክቶ ተቀባይነት ካጣ በኋላ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን ሲያቀርብ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ስርዓቱን ጠብቆ እስከ ክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት መከራከሩን ለማወቅ ይረዳ ዘንድ የወረዳው ፍርድ ቤት መጀመሪያ በፍሬ ጉዳዩ ላይ የሰጠው ውሳኔ ግልባጭ፣አመልካች ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበው የይግባኝ እና የሰበር አቤቱታ ግልባጮችን እንዲያያይዝ ትዕዛዝ ሰጥቶ አመልካችአሉኝ ያላቸውን ውሳኔዎችን አያይዟል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክርና ለሰበር አቤቱታው መነሻ የሆነውን ውሳኔ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩመርምሮታል፡፡እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልጋቸው አበይት ነጥቦች፡-

 

1.  የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለማየት ስልጣን አለው ወይስ የለም?

2.  የአመልካች የመከራከር መብት የታለፈው በሕጉ አግባብ ነው ወይስ አይደለም?

3. የአመልካች እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ የተለያዩ ክፍያዎችን ለተጠሪ እንዲከፍል በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለ ለማለት ይቻላል ወይስ አይቻልም?

 የ መጀ መሪያ ውን ጭ ብጥ በተመለከተ ፡-በመሰረቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በፌዴራል መንግስትና በክልሎች መዋቀሩን መሰረት በማድረግ የዳኝነቱም ሥልጣን በፌዴራል መንግስቱ እና በክልል መንግስታት መካከል እንደተከፋፈለ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 5ዐ እና 51 ሥር ተመለክቷል፡፡በኢ.ፌ.ዲ.ሪሕገ መንግስት በአንቀጽ 8ዐ “የፍ/ቤቶች ጣምራነትና ሥልጣን” በሚል ርዕስ በፌዴራል ጉዳዩች ላይ የበላይና የመጨረሻየዳኝነት ሥልጣኑ በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፤በክልል ጉዳዮች ላይ በክልሉ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት ሥልጣኑ የተደነገገ ሲሆን የክልል ፍ/ቤቶች በህገ- መንግስቱ በተሰጣቸው የውክልና ሥልጣን መሠረት ካልሆነ በቀር የፌዴራልን ጉዳይ ለማየት፤እንዲሁም የፌዴራል ፍ/ቤቶች የክልልን ጉዳይ ለማስተናገድ የሚያስችል  ሥልጣን የሌላቸው  መሆኑን  በዚሁ  ድንጋጌ  ስር  የተቀመጡት  ንዑስ  ድንጋጌዎች  ይዘትና    መንፈስ


ያሳያል፡፡አንድ ጉዳይ የፌዴራል ነው? ወይስ የክልል? የሚለውን ለመለየትም መሰረቱ የአዋጅ ቁጥር 25/88 ሲሆን፤በዚሁ ህግ አንቀጽ 5 ሥር በተመለከቱት ጉዳዮች ላይ ብቸኛ ሥልጣን ያላቸው የፌዴራል ፍ/ቤቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የክልል ፍ/ቤቶችስልጣን የሚኖራቸው በህገመንግስቱ በተሰጣቸው የውክልና ሥልጣን አግባብ ብቻ ነው፡፡ይህ በግልፅ የሚያሳየው በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 5 መሰረት የፍርድ ቤቶች ስልጣን በጉዳዩ ባለቤትነት (Subject matter) የሥልጣን ክፍፍል እንደተጠበቀ ሆኖ ክሱም መቅረብ ያለበት ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን የሥረ-ነገር ሥልጣን ላለው ፍ/ቤት ስለመሆኑ ነው፡፡የፌደራል ፍ/ቤቶችን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8፣11፣14 እና 15 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ደግሞ አንዳንድ ጉዳዮች ሊያስነሱ በሚችሉት የክርክር ባህርይ ምክንያት ለተወሰኑ ፍ/ቤቶች እንዲቀርቡ በህግ ተለይተው ከተመለከቱት በቀር የሥረ-ነገር ሥልጣን የተደለደለው በክሱ በተመለከተው የገንዘብ ወይም የንብረት ግምት መነሻ እንደሆነ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 14 እና 15 ስር ከተመለከቱት ድንጋጌች ጣምራ ንባብ እና የክልል መንግስታት ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ ሕጎች ያስረዳሉ፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አዋጅ ቁጥር 25/1988"ን" ያወጣው የፌዴራል መንግስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ክርክሮች የሚመሩበትን ስርኣት የዘረጋውን አዋጅ ቁጥር 377/1996 ከየካቲት 18 ቀን 1996 ዓ/ም ስራ ላይ ያዋለ ሲሆን በዚህ አዋጅ የስራ ክርክር ስልጣን ድልድል የተደረገው የግል የስራ ክርክርና የወል የስራ ክርክር የሚሉትን ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ ሲሆን የተከራካሪ ወገንን ማንነትን ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ አይደለም፡፡በመሆኑም ክርክሮቹ ክልል የተነሱ ቢሆንም ጉዳዩን የክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወይም አግባብነት ያላቸው የቋሚ ወይም ጊዜአዊ ቦርዶች ሊመለከቱ እንደሚችሉ አድርጎ ሕጉን ሕግ አውጪው አውጥቷል፡፡ይህ አዋጅ ከአዋጅ ቁጥር 25/1988 በኋላ ከመውጣቱም በላይ ለስራ ክርክሮች ልዩ ሕግ ነው፡፡እንዲህ ከሆነ አዋጅ ቁጥር 377/1996 ለስራ ክርክሮች ከሕገ መንግስቱ በመለስ ባሉት ማናቸውም ሕጎች የበላይ ተፈፃሚነት ያለው ስለመሆኑ ተቀባይነት ያላቸው የሕግ አተረጓጎም ደንቦች የሚያስረዱን ጉዳይ ነው፡፡በመሆኑም በስራ ክርክር ተከራካሪ ወገኖች ማንነት የፍርድ ቤቶችን ስልጣን (የክልል ወይም የፌዴራል) ብሎ ለመወሰን እንደወሳኝ መለኪያ ሊወሰድ የሚገባው አይደለም፡፡ከዚህ አንጻር ሲታይ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ተቀብሎ ማየቱ ከላይ የተመለከተውን የህጉን ማዕቀፍ እና በዚህ ረገድ ይህ ችሎት በመ/ቁጥር 95298 እና በሌሎች በርካታ መዛግብት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በአከራካሪው የህግ ነጥብ ላይ ከሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ጋር የተጣጣመ ነው ከሚባል በስተቀር የሚነቀፍበትን አግባብ አላገኘንም፡፡

 

 ሁ ለተ ኛ ውን ጭብጥ በተ መለ ከተ ፡- በመሰረቱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር94 ስር እንደተመለከተው መጥሪያ በቅድሚያ መድረስ ያለበት ለተከሰሰው ሰው ሲሆን የተከሰሰው ሰው የንግድ ድርጅት ከሆነ ደግሞ ከድርጅቱ ጸሃፊ ወይም ለድርጅቱ ኃላፊ መሰጠት ያለበት መሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 97(1) ስር ተመልክቷል፡፡ሕጉ መጥሪያ አሰጣጥ ዘዴና ቅደም ተከተሉ እንዲሁም መጥሪያው ለማን እንደሚሰጥ የሚመለከተው የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ክፍል ዓይነተኛ ዓላማ ከሆኑት መካከል አንዱ ተካራካሪ ወገኖችን እኩል የመከራከር መብት እንዲኖራቸው በማድረግ ጉዳዩን ፍትሐዊ በሆነ አኳኋን ለመወሰንማስቻል መሆኑን ይታወቃል፡፡በመሆኑም ፍርድ ቤቱ መጥሪያ የሚደርስበትን ተገቢ መንገድና ለማን መድረስ እንዳለበት ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡

 

መጥሪያ በተገቢው መንገድ ደርሶት ተከራካሪ ወገን ካልቀረበ ወይም መጥሪያን አልቀበልም ካለ ፍርድ ቤቱ ሊከተለው የሚገባው ስርዓትም በሕጉ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ከእነዚህም ድንጋጌዎች መካከል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 70(ሀ)፣103፣104፣105፣ 106 እና 107 ስር የተመለከተው ሊጠቀሱ


የሚችሉ ሲሆን በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት ተከሳሽ በሌለበት ክርክሩ ታይቶ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው መጥሪያው በአግባቡ የደረሰው መሆኑ ሲረጋገጥ ወይም መጥሪያውን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ ወይም ሊገኝ ያልቻለ መሆኑ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ድንጋጌዎቹ መጥሪያው በትክክል ያልደረሰው መሆኑ ከተረጋገጠ ጉዳዩ ተከሳሽ በሌለበት እንዲታይ የማይታዘዝ ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ፡፡በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 70(ሀ) ድንጋጌ ስር ላይ "መጥሪያው በትክክል  መድረሱ" የሚለው ሐረግ መኖሩም የሚያሳየው ስለመጥሪያ አሰጣጥና አደራረስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 94 እስከ 110 ድረስ የተመለከቱት ሁኔታዎች በአግባቡ መሟላታቸውን የሚያስገነዝብ ነው፡፡አንድ ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ ታይቶ ውሳኔ ከተሰጠውም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 78 መሰረት መፍትሔ መጠየቅ የሚችል ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡በዚህ ድንጋጌ መሰረት መፍትሔ ሊጠየቅ የሚችለው አቤቱታ አቅራቢው በሚያቀርበው አቤቱታ ላይ የጥሪው ትዕዛዝ "በሚገባ ያልደረሰው" መሆኑን በመጥቀስ ይህንኑ ማረጋገጥ ሲችል ነው፡፡ከእነዚህ ሁሉ ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚቻለው አንድ ሰው የመከራከር መብቱን እንደተወው የሚቆጠረው መጥሪያው በሕጉ በተዘረጋው ሥርዓትና ቅደም ተከተል መሰረት ደርሶት ክርክር ያለው መሆኑን እያወቀሳይቀርብ ሲቀር ብቻ መሆኑን ነው፡፡ፍርድ ቤቱ በሕጉ የተዘረጋውን ስርዓት ተከትሎ አማራጭ የመጥሪያ አደራረስ ሥርዓት  ከፈጸመ መጥሪያው ለተከሳሹ እንደደረሰ እንደሚቆጠርና በቂና ሕጋዊ ምንክያት ካለው ብቻወደ ክርክሩ እንዲገባ የሚፈቀድ መሆኑን ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያስገነዝባል፡፡ስለሆነም ማንኛውም ውሳኔ መሰጠት ያለበትም በሕጉ በተዘረጋው ሥርዓት መሰረት መጥሪያው መድረሱ በሚገባ የተረጋገጠና የተከሳሽ የመከራከር መብት የተጠበቀ መሆኑ ሲታወቅ ሊሆን ይገባል፡፡

 

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም በወረዳው ፍርድ ቤት በነበረው ክስ ተጠሪ ለአመልካች ድርጅት መጥሪያውን እንዲያደርሱ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ መጥሪያውን ይዘው "ለድርጅቱ ኃላፊ ልሰጥ ስል ኃላፊው አልቀበልም ብለውኛል" በማለት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 103 መሰረት በቃለ መሃላ አረጋግጠው መጥሪያውን የመለሱ ሲሆን ለዚህም ምስክሮች ያላቸው መሆኑን ጭምር ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ተጠሪ ለስር ፍርድ ቤት በ18/03/2004 ዓ/ም እና በ26/03/2004 ዓ/ም የተጻፉ  ሁለት ቃላ መሃላዎችን ያቀረቡ ሲሆን አሁን በዚህ ረገድ ግራ ቀኙን እያከራከረ ያለው በየትኛው ቀን የተዘረዘሩት ምስክሮች ናቸው ስለመጥሪያው አደራረስ ሊመሰክሩ የሚገባቸው? የሚል ነጥብ ነው፡፡ከላይ እንደተገለጸው የተጠሪ የመጥሪያ አደራረስ በቃለ መሃላ ተደግፎ የቀረበ ቢሆንም መጥሪያውን ለአመልካች ድርጅት ያደረሱ መሆን ያለመሆኑን በተመለከተ ምስክሮች እንዲሰሙ በማለት በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 148159 ጥቅምት 26 ቀን 2005 ዓ/ም ተወስኖ ጉዳዩ የተመለሰለት የወረዳው ፍርድ ቤትም በ18/03/2006 ዓ/ም በተፃፈው ቃለ መሃላ የተጠቀሱትን ምስክሮች የሠማና ምስክሮቹ መጥሪያውን ተጠሪ ለአመልካች ድርጅት ማድረሳቸውንና የአመልካች ድርጅት ኃላፊ አልቀበልም ማለታቸውን ማረጋገጣቸውን ምክንያት አድርጎ የአመልካችን በሌለሁበት ታይቶ የተወሰነ ውሳኔ ይነሳልኝ ጥያቄን ሳይቀበለው የቀረ ሲሆን ይኼው የወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ በክልሉ የሰበር ሰሚ ችሎትም ተቀባይነት አግኝቷል። እንግዲህ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 148159 በ26/02/2005 ዓ/ም በተሰጠው ውሳኔ ስለመጥሪያው አደራረስ የግራ ቀኙ ምስክሮች እንዲሰሙ ተብሎ ለወረዳው ፍርድ ቤት ከመመለሱ ውጪ በ26/03/2004 ዓ/ም በተጠሪ ለወረዳው ፍርድ ቤት በቀረበው ቃለ መሃላ የተጠቀሱት ምስክሮች እንዲሰሙ በግልጽ የተሰጠ ውሳኔ የለም፡፡በ26/03/2004 ዓ/ም ቀረበ በተባለው ቃለ መሃላ ያሉት ምስክሮችም አመልካች የተጠሪን ደመወዝ መጠን ለማወቅ ይቻል ዘንድ መዝገቡን እንዲያቀርብ የወረዳው ፍርድ ቤት በ22/03/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቶ ስለነበር አመልካች የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አልፈፀምም፣የፍርድ ቤቱን መጥሪያአልወሰድም ማለቱን ለማረጋጋጥ የቀረቡ ስለመሆኑ የክርክሩ ሂደት የሚያሳይ   ሁኖ


አግኝተናል፡፡እንዲህ ከሆነ በ26/03/2004 ዓ/ም በቀረበው ቃለ መሃላ የተጠቀሱት የተጠሪ ምስክሮች ስለመጥሪያ አደራረስ የሚሰሙበት የሕግ አግባብ የለም፡፡አንድ ማስረጃ መሰማት የሚገባው ለጉዳዩ አግባብነት ሲኖረው ስለመሆኑ ተቀባይነት ያላቸው የማስረጃ ሕግ ደንቦች የሚሳዩት ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነምአመልካች በዚህ ረገድ የሚያቀርበው ክርክር ተቀባይነት የሚሰጠው ሁኖ አልተገኘም፡፡በ18/03/2004 ዓ/ም በተጻፈ የተጠሪ ቃለ መሃላ የተጠቀሱት ምስክሮች መሰማታቸው ተገቢ ነው ከተባለ እነዚህ ምስክሮች አመልካች መጥሪያ ደርሶት አልቀበልምበማለት ተጠሪን የመለሳቸው መሆኑን ያረጋገጡት የፍሬ ነገር ጉዳይ በመሆኑ የተጠሪ የመከራከር መብቱ መታለፉ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 97(1)፣103፣70(ሀ) እና 78 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ተገቢ እንጂ የሚነቀፍበት አግባብ የለም፡፡

 

 ሦ ስተ ኛውን ጭብጥ በተመ ለከተ፡ -አመልካች ተጠሪን ያሰናበተበትን ሕጋዊ ምክንያት በዋናው ክርክር ያለበቂ ምክንያት ባለመቅረቡ አላስረዳም፡፡ይልቁንም ተጠሪ አመልካች ከህግ ውጪ ያሰናበታቸው መሆኑን በወረዳው ፍርድ ቤት ባቀረቡት ማስረጃ ያረጋገጡት ጉዳይ መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡በመሆኑም የአመልካች እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ በዚህ ችሎት የሚለወጥበት አግባብ የለም፡፡በመሰረቱ አንድ ተከሳሽ በሌለበት ታይቶ በተሰጠው በዋናው ጉዳይ ላይ ለበላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሲያቀርብ የይግባኝ አቀራረብ አድማሱ በተወሰኑት ነጥቦች ላይ ብቻ መሆን እንዳለበት የይግባኝ አቀራረብን በተመለከተ የተደነገጉት ድንጋጌዎች መንፈስ እንደሚያስረዳና ጉዳዩ በሌለበት ታይቶ የተወሰነበት ተከሣሽ ለበላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሲያቀርብ በስር ፍ/ቤት በተከራካሪነት ቀርቦ ያላነሣውን ነጥብ ማንሳት እንደማይችል፣እንደዚህ ዓይነት ተከራካሪ በፍ/ቤቱ የውሣኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ክሱን፣የማስረጃዎችን አግባብነት ተቀባይነት እና ጥንካሬ ባግባቡ ያላገናዘበ ሁኔታ አለ የሚል ከሆነ ይግባኝ ሊያቀርብ እንደሚችል ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 36412  በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ስለሆነም ፍ/ቤት ከሣሹ ያቀረበው ክስ አባሪ ሆነው ከቀረቡት ማስረጃዎች አግባብነት፣ተቀባይነትና ጥንካሬ አኳያ በመመርመር ተገቢውን ዳኝነት አልሰጠም በሚል ይግባኝ የማቅረብና ወደ ቀጣዩ የሰበር ደረጃም ቅሬታውን ማድረስ ጉዳዩ በሌለበት ታይቶ ውሳኔ ለተሰጠበት ወገን በሕግ የተጠበቀለት መብት መሆኑ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡

 

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም የወረዳው ፍርድ ቤት በ29/03/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት ስንብቱ ህገ ወጥ ነው ብሎ ሲወሰን በዚህ ውሳኔ ተጠሪ የሚከፈለኝ ገንዘብ በግልጽ አልተቀመጠልኝም በማለት ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን አይቶ ለስር የተጠሪ ደመወዝ ተጣርቶ ሊታወቅ ይገባል፣ከዚህ በኋላ የማስጠንቀቂያ፣የስራ ስንብት ክፍያ እና ካሳ፣የሳምንት፣የአመት እና የበዓል ቀናት ክፍያዎች እንዲሁም ያልተከፈለው ደመወዝ ታስቦ በግልጽ መቀመጥ አለበት በማለት በመ/ቁጥር 33824 በ17/05/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት ለወረዳው ፍርድ ቤት መልሶለት የወረዳው ፍርድ ቤትም ተከሳሽ ግብር ሲከፍልበት የቆየበት ቦታ በደገም ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት እና በተከሳሽ ድርጅት እንዲቀርብ አዝዞ ደመወዝንና የትርፍ ሰዓት ክፍያ በጠቅላላው ብር 6410.92 መሆኑ በድጋሚ እንደቀረበለት ጠቅሶ እንዲሁም ከደገም ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ከሳሽ ደመወዝ ሲበላበት የነበረው እና ወሩ ያልታወቀ ፔሮል ቀርቦ በሁለቱም ወገኖች ስምምነት መደረሱን ገልፆ ውሳኔውን ወደ ገንዘብ ለውጦ ማስቀመጥ የአፈፀጸም ክስ ቡድን እንጂ የፍርድ ቤት ተግባር አይደለም፣ግን የይግባኝ ሰሚውን ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መከተል ተገቢ ነው ብሎ ተጠሪ በሰዓት የሚያገኘው ደመወዝ ብር 13.46.00፣በቀን ደግሞ 107.69 መሆኑን ማረጋገጡን ጠቅሶ የወር


ደመወዙን ብር 3230.70 ይዞ ክፍያዎችን አስልቶ በጠቅላላው ብር 277,294.04 እንዲከፈለው ሲል በመ/ቁጥር 03756 የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት ወስኗል፡፡አመልካች በሌለበት ጉዳዩ በመታየቱ ላይ የይግባኝ ቅሬታና የሰበር አቤቱታ ለክልል ፍርድ ቤቶች ሲያቀርብ ለተጠሪ እንዲከፈሉ በተወሰኑ ክፍያዎች መጠን ላይም በሕግ አግባብ ያልተሰሉ መሆኑን ጭምር በመጥቀስ ቅሬታ ሲያቀርብ የነበረ መሆኑን የክርክር ሂደት የሚያሳይ ሲሆን ተጠሪ በዚህ ረገድ የሚያቀርቡት ክርክር አመልካች በሌለበት በታየው ውሳኔ ላይ ይግባኝና የሰበር ክርክር ማቅረብ አይችልም የሚል መሆኑን ተረድተናል፡፡ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለጸው አመልካች በሌለበት ጉዳዩ ቢታይም ተጠሪ ያቀረቡት ክስ አባሪ ሆነው ከቀረቡት ማስረጃዎች አግባብነት፣ተቀባይነትና ጥንካሬ ያለመመርመሩንና እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 377/1996 ከአስቀመጠው የክፍያ ስሌት ውጪ መሆኑን በሚያሳዩት ነጥቦች ላይ በዚህ ችሎት ክርክር ከማቅረብ የሚያግደው የሥነ ስርዓት ህግ የሌለ በመሆኑ በዚህ ረገድ ተጠሪ ያቀረቡትን ክርክር የምንቀበለው ሁኖ አልተገኘም፡፡

 

አመልካች ከተጠሪ ጋር ያለውን የሥራ ውል በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 አግባብ ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ ለማሰናበት የሚያስችል ሁኔታ ሣያጋጥመው ካቋረጠ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀፅ 39(1/ለ) መሠረት በአንቀፅ 40 ንዑስ አንቀፅ 2፣ በአንቀፅ 44 እና በአንቀፅ 43 ንዑስ አንቀፅ 4(ለ) የተደነገጉትን ክፍያዎች ለተጠሪ የመክፈል ኃላፊነት አለበት፡፡ከዚህ አንጻር የስር ፍርድ ቤት አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል በማለት የዘረዘራቸው የክፍያ አይነቶች  የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣ካሳ፣የስራ ስንብት ክፍያ፣የሳምንት እረፍት ክፍያ፣የአምስት አመት በዓላት ክፍያ ናቸው፡፡የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣የስራ ስንብት ክፍያና የካሳ ክፍያዎች የሚሰሉበት አግባብ በሕጉ ተለይቶ የተቀመጠ ሲሆን ይህንኑ በሕጉ የተቀመጠውን ስሌት ተግባራዊ ለማድረግ ሰራተኛው በወር ሲከፈለው የነበረው ደመወዝ በሕጋዊ ማስረጃ መረጋግጥ የግድ ይላል፡፡ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው የወረዳው ፍርድ ቤት የተጠሪ የወር ደመወዝ ብር 3230.70(ሶስት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ ብር ከሰባ ሳንቲም) መሆኑን በመ/ቁጥር 03756 የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ አረጋግጧል፡፡በመሆኑም የተጠሪ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣የስራ ስንብትና የካሳ ክፍያዎች መሰላት ያለባቸው በዚሁ የተጠሪ ወርሃዊ ደመወዝ የተባለው መጠን መሰረት ተደርጎ በሕጉ የተቀመጠው ስሌት ባገናዘበ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡

 

ይህንኑ መሰረት አድርገን እያንዳንዱን የክፍያ መጠን ስንመለከትም ተጠሪ በአመልካች ድርጅት ያላቸው የአገልግሎት ዘመን አምስት አመት ከዘጠኝ ወርበመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 35(1)(ለ)) መሰረት ሊከፈላቸው የሚገባው የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ የሁለት ወር ደመወዝ ብር

6,461.40 (ስድስት ሺህ አራት መቶ ስልሳ አንድ ብር ከአርባ ሳንቲም) ሁኖ አግኝተናል፡፡የስራ ስንብት ክፍያን በተመለከተም በአዋጁ አንቀጽ 39(1(ለ)) እና 40(1)(2) ድንጋጌዎች መሰረት የሚመጣው ውጤት ብር 8,384.30 (ስምንት ሺህ ሶስት መቶ ሰማንያ አራት ከሰላሳ ሳንቲም) እንጂ ብር 47,383.60 ያለመሆኑን ተረድተናል፡፡እንዲሁም የካሳ መጠኑ በአዋጁ አንቀጽ 43(4(ሀ)) መሰረት ሲሰላ የወረዳ ፍርድ ቤት የተጠሪን አማካይ የቀን ደመወዝ ብር 107.69 ያደረገው በመሆኑ ይኼው የቀን አማካይ ደመወዝ በመቶ ሰማንያ ሲባዛ የሚመጣው ውጤት ብር 19,384.20(አስራ ዘጠኝ ሺህ ሶስትመቶ ሰማንያ አራት ብር ከሃያ ሳንቲም) እንጂ ብር  25,849.60 ያለመሆኑን ተገንዝበናል፡፡ሌላው የስር ፍርድ ቤት በአዋጁ አንቀጽ 71 እና 68 መሰረት የሳምንት እረፍት ክፍያ በማለት ያስቀመጠው ብር 188,784.57(አንድ መቶ ሰማንያ ስምንት ሺህ ሰባት መቶ ሰማንያ አራት ብር ከሃምሳ ሳንቲም) የስሌቱ መነሻ እና የመብቱ አድማስ ለጉዳዩ አግባብነትና ጥንካሬ ያላቸውን ማስረጃዎችን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ የክርክሩ ሂደት አያሳይም፡፡በመሆኑም በዚህ ረገድ የተሰጠው


የውሳኔ ክፍል ሕግና ማስረጃን መሰረት ያደረገ ሁኖ አላገኘነውም፡፡የአምስት አመት በዓል ክፍያን በተመለከተ ግን አመልካች በስር ፍርድ ቤት በሌለበት የታየ በመሆኑና የይርጋ ክርክር ተነስቷል ለማለት ስለማይቻል እንዲሁም ፍርድ ቤቱ ደግሞ ይርጋውን በራሱ ሊያነሳ የሚችልበት አግባብ የሌለ በመሆኑ የገንዘቡ መጠን ብር 16,357.00(አስራ ስድስት ሸህ ሶስት መቶ ሃምሳ ሰባት ብር) ተብሎ በስር ፍርድ ቤት መቀመጡን የማንቀበልበትን አግባብ አላገኘንም፡፡ በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1.  በኦሮሚያ ብሔራዊ  ክልላዊ  መንግስት ጠቅላይ  ፍርድ  ቤት  ሰበር  ሰሚ  ችሎት በመ/ቁጥር

163369 በ20/01/2006 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ ተሻሽሏል፡፡

2. በሂደቡ አቦቴ ወረዳ በመ/ቁጥር 03756 የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት የአመልካች የስንብት እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል የፀና ሲሆን ውጤቱን በተመለከተ የሰጠው የውሳኔ ክፍል ግን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

3. የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው፣የአመልካች የመከራከር መብት የታለፈው ባግባቡ ነው፣የአመልካች እርምጃ ህገ ወጥ ነው በማለት መወሰኑም ተገቢ ነው በማለት ውጤቱን ግን አመልካች ለተጠሪ ሊከፍል የሚገባው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በተቀመጠው ስሌትና በማስረጃ በተረጋገጠው የደመወዝ መጠን በመሆኑ፡-

3.1  የስራ ስንብት ክፍያ ብር 8,384.30፣

3.2  የሁለት ወር ማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ብር 6,461.40፣

3.3  የካሳ ክፍያ ብር 19,384.20 እና

3.4 የአምስት  አመት   የበዓል   ቀናት   ክፍያ  ብር   16,357.00   ሁኖ  በድምሩ   ብር

50,586.90(ሃምሳ ሺህ አምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ብር ከዘጠና ሳንቲም) ነው በማለት ወስነናል፡፡

4. የሳምንት ዕረፍት ቀናት ክፍያ ብር 188,784.57 በተመለከተ ግን በሕግ እና በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ  አመልካች ለተጠሪ ሊከፍል አይገባም በማለት ወስነናል፡፡

5. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ት/ጌ