103781 Family law interdiction divorce

በፍርድ የተከለለከለ ሰው የፍቺ ጥያቄ ስለሚያቀርብበት አግባብ

 

የሰ/መ/ቁ. 103781 ቀን መጋቢት 17/2007 ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኸሊት ይመስል

አመልካች ፡- ወ/ሮ አስካለ አሽኔ - ጠበቃ በርታ በቀለ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ታምራት ተስፋዬ - ጠበቃ አሸናፊ ቦሻ ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች በመዝገብ ቁጥር 197469 ጥር 12 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 150493 ግንቦት 5 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የፍች ውሳኔን በመቃወም የቀረበ ጥያቄን የሚመለከት ነው፡፡

1. የክርክሩ መነሻ ተጠሪ የአባቱ የአቶ ተስፋዬ ጉልማ አሳዳሪና ሞግዚት መሆኑን ገልፆ፣የአቶ ተስፋዬ ጉልማና አመልካች 1964 ዓ.ም ጀምሮ በጋብቻ ተሣስረው ኖረዋል፡፡በትዳራቸው ልጆች አላፈሩም ፡፡ አባቴና ሞግዚት አድራጊና በእድሜ በመግፋታቸው ምክንያት የአእምሮና የጤና መታወክ አጋጥሟቸዋል፡፡ ተጠሪ ባላቸውን ሊንከባከቡዋቸው አልቻለም በዚህ ምክንያት ሁለቱ ተለያይተው መኖር ከጀመሩ ረዥም ጊዜ ሆኋቸዋል ፡፡ ስለዚህ ሞግዚት አድራጊዬ ከተጠሪ /አመልካች /ጋር ያላቸው ጋብቻ በፍች እንዲፈርስ ውሣኔ ይሰጥልኝ በማለት አመልክቷል፡፡ የአሁን አመልካች /በሥር ተጠሪ/ለፍች የሚያበቃ ምክንያት የለንም በማለት ተከራክረዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት አቶ ተስፋዬ ጉልማ  በአካል በተደጋጋሚ እያስቀረበ ካነጋገረ በኃላ በአቶ ተስፋዬ ጉልማና በአመልካች መካከል በፍች እንዲፈርስ ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ አመልካች ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የአመልካችን ይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሠረት ሰርዞታል፡፡

2. አመልካች ተጠሪ ፍች እንዲወሰን የማመልከት ስልጣን የለውም ፡፡ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው የፍች ውሣኔ ህግን መሠረት ያደረገ አይደለም በማለት ነሐሴ 5 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ የሰበር አቤቱታ አቅርበዋል ፡፡ ተጠሪ በበኩሉ አመልካች ከሞግዚት አድራጊዬ ጋር የባልና የሚስት ግዴታ እየተወጡ አይደለም፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ውሣኔ የሰጠው ሞግዚት አድራጊዬን በተደጋጋሚ አስቀርቦ ሁኔታውን ከተረዳ በኃላና በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ መሠረት ነው በማለት ተከራክሯል፡፡ አመልካች የመልስ መልስ አቅርበዋል ፡፡


3. የሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች የተጠሪን የፍች ጥያቄ በመቀበል የሰጡት የፍች ውሳኔ ሕግን መሠረት ደረገ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳይን መርምረናል፡፡

4. በመርህ ደረጃ የፍች ጥያቄ ለማቅረብ የሚችሉት ባል ወይም ሚስት ወይም ሁለቱም በጋራ ጥያቄ በማቅረብ እንደሚሆን በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/992 አንቀፅ 81 ተደንግጓል ፡፡ ሆኖም አንድ ሰው ጋብቻ ፈፅሞና በጋብቻ ተሣሥሮ ከኖረ በኃላ በፍርድ ክልከላ የተደረገበት በሆነ ጊዜ የፍች ጥያቄ የሚያቀርበው በምን ሁኔታና  እንዴት ነው የሚለው ጥያቄ ሲነሳ በፍታብሔር ሕግ በፍርድ ስለሚደረግ ክልከላና ክልከላው ስለሚያስከትለው ውጤት ከፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 351 እስከ ፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 389 የተደረጉትን ድንጋጌዎች መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 370 ንዑስ አንቀፅ 1 ፍች ወይም ከሕግ ውጭ የሚያደርገው የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲቀር ጥያቄ ለማቅረብ የተከለከለው ሰው ፈቃድ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ የአሳዳሪውም ፈቃድ የግድ አስፈላጊ ነው በማለት ይደነግጋል ፡፡

5. ከዚህ አንፃር የአቶ ተስፋዬ ጉልማ አሳዳሪና ሞግዚት ሆኖ የተሾመው ተጠሪ ሞግዚት ሆኖ የሚያስተዳድራቸው ወላጅ አባቱ ፤በእድሜ በመግፋታቸው ምክንያት ራሳቸውን ችለው ህጋዊ ተግባራት መፈፀም እንደማይችሉ በፍርድ ተረጋግጦ ክልከላ የተደረገባቸው መሆኑንና አመልካችና አቶ ተስፋዬ ጉልማ ተለያይተው ለረጅም ጊዜ መኖራቸውን በመግለፅ ፍች እንዲወሰን ጠይቋል፡፡ ይህም ተጠሪ የፍታብሔት ህግ ቁጥር 370 ንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት ጋብቻው በፍች አንዲፈርስ ጥያቄ ያቀረበ መሆኑን ያሳያል ፡፡ የሥር ፍርድ ቤትም ፤አቶ ተስፋዬ ጉልማ በተደጋጋሚ ቸሎት በማስቀረብና ካናገረ በኃላ አመልካችና አቶ ተስፋዬ ጉልማ በቤተሠብ ህጉ በባልና ሚስት ላይ የተጣለውን እርስ በእርስ የመተጋገዝ  የመረዳዳት

፣የመደጋገፍና የመተሳሰብ ግዴታ እየተወጡ አለመሆኑን በማረጋገጥ ጋብቻው በፍች እንዲፈርስ ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ ይህ የሥር ፍርድ ቤት ውሣኔ አመልካችና አቶ ተስፋዬ ጉልማ በሕግ ፊት ባልና ሚስት ናቸው ቢባልም በዕውኑ ግን በባልና ሚስትነት የመፈፀማቸውን ተግባራትን ግዴታዎች እየፈፀሙ የማይኖሩ መሆኑንና የጋብቻው በፍች መፍረስ በፍርድ ክልከላ የተደረገባቸውን አቶ ተስፋዬ ጉልማ መብትና ጥቅም ለማስከበር አስፈላጊ መሆኑን በማረጋገጥ የሰጠው ውሳኔ መሆኑን በውሣኔ ተረድተናል ፡፡ በመሆኑም የበታች  ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ ፀንቷል ፡፡

2. ይህ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 103781 ህዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል ፡፡ ይፃፍ፡፡

3. ግራቀኙ በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭ ለየራሳቸው ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስትዳኞች ፊርማ አለበት ፡፡