የፍርድ ባለዕዳ ንብረት የሆነ ለፍርድ ማስፈፀሚያ ተብሎ በጨረታ ከተሸጠ በኋላ በሐራጅ ላይ ጉድለት አለ፣የጨረታ ሽያጩ ይሰረዝ የሚል አቤቱታ በሚቀርብበት ጊዜ ሽያጩ ሊሰረዝ ይገባዋል? ወይስ አይገባውም? በሚለው ላይ መከራከር ያለባቸው የፍርድ ባለዕዳና ባለገንዘብ ብቻ ሳይሆኑ ንብረቱን በሐራጅ አሸንፎ የገዛው 3ኛ ወገንም ጭምር ስለመሆኑ፡
የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 32፣39፣40፣79 እና 370(3)
የሰ/መ/ቁጥር 97332
መጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ/ም
ዳኞች፡- አልማው ወሌ
ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል
አመልካች፡- አቶ አይመረ በላይ - ጠበቃ ሙሉአለም ዘውዴ ቀረቡ ተጠሪ፡- 1. መሪጌታ ኮነ ንጋቱ - ጠበቃ ተሾመ መኮንን ቀረቡ
2. አቶ አንዷለም አሻግሬ - ታልፏል
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ጉዳዩ አንድ በፍርድ ቤት የተደረገ የጨረታ ሽያጭ ውድቅ የሚሆንበትን አግባብ የሚመለከት ነው፡፡ የሰበር አቤቱታው የቀረበው አመልካች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 14450 በሆነው ህዳር 4 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እንዲነሳላቸው አመልካች ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት በማጣቱ ነው፡፡
የክርክሩ አመጣጥ ሲታይም የአሁን1ኛ ተጠሪ ለአሁኑ 2ኛ ተጠሪ በነበረባቸውና በወረዳው ፍርድ ቤት በተወሰነው የብር 15,000.00 ዋና ገንዘብ፣ የዚሁ ገንዘብ ወለድና የተለያዩ ወጪዎች ዕዳ መክፈያ እንዲሆን በአሁን አመልካች ስም ይታወቅ የነበረው በአዴት ከተማ ቀበሌ 02 ክልል ውስጥ የሚገኘው ቤት በምስራቅ መንገድ፣ በምእራብ 16 ቁጥር፣ በሰሜን 15 ቁጥር፣ በደቡብ 19 ቁጥር በሚያዋስኑት መካከል የሚገኝ ቤት ባለሙያ ተገምቶ በአከባቢ ማስታወቂያ ጨረታ እንዲወጣ ተደርጎ የአሁኑ አመልካች የሃራጁ አሸናፊ ሁነው ከተሸጠ በኋላ የ1ኛ ተጠሪ እዳ ለ2ኛ ተጠሪ እንዲከፈል፣ የተረፈው ገንዘብ ደግሞ ለአሁኑ 1ኛ ተጠሪ እንዲቀመጥላቸው የወረዳው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሲሰጥ የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ በሐራጅ ሽያጩ ጉድለት እንደአለ ገልጸው አቤቱታ ቢያቀርቡም የወረዳው ፍርድ ቤት ጥያቄአቸውን ባለመቀበል መዝገቡን የዘጋባቸው ሲሆን በዚህ ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ተቀባይነት ስለአጡ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን አቅርበው ችሎቱ በ1ኛ ተጠሪ አመልካችነት የቀረበለትን የሰበር አቤቱታ የአሁኑ 2ኛ ተጠሪ (የስር የፍርድ ባለመብትን) ብቻ ተጠሪ አድርጎ ክርክሩን ከመራ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ለፍርድ ማስፈፀሚያነት የዋለው የ1ኛ ተጠሪ ንብረት የጨረሻ መነሻ ግምቱ ብር 76,354.30 ሁኖ
በጨረታ የተሸጠው ግን በብር 76,358.60 መሆኑ ቤቱ በአከባቢ ማስታወቂያ ለሰላሳ ቀናት ማስታወቂያው አየር ላይ ሳይውል መሸጡ በሽያጭ አካሄዱ ላይ ጉድለት መኖሩን የሚያሳይ ነው የሚል ምክንያት ይዞ በወረዳው ፍርድ ቤት ትእዛዝ የተካሄደውንና የፀደቀውን የጨረታ ሽያጭን እንዲሰረዝ በማለት ወስኖታል፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የጨረታው አሸናፊ የሆኑትን አመልካች ሳይጠራና የሐራጅ ሽያጩም ጉልህ ጉድለት ያለበት ስለመሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ አመልካች በግልጽ ተወዳድረው አሸናፊ የሆኑበትን የጨረታ ውጤት መሰረዙ ያላግባብ ነው፣ንብረቱም በሕግ አግባብ ለሶስተኛ ወገን ተሸጦ የሀራጅ ሽያጩ ወደ ነበረበት ቦታ ሊመለስ በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል የሚል ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ 2ኛ ተጠሪ መጥሪያ ደርሷቸው ሊቀርቡ ባለመቻላቸው በፅሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸው የታለፈ ሲሆን1ኛ ተጠሪ ግን በመቅረባቸው ከአመልካች ጋር በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡እንደመረመረውም የችሎቱን ምላሽ የሚያስፈልገው አቢይ ነጥብ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የአሁኑን አመልካች ወደ ክርክሩ ሳያስገባ ክርክሩን መርቶ ዳኝነት መስጠቱና አመልካች ጉዳዩ ባሉበት እንዲታይላቸው ያቀረቡትን አቤቱታ የማስረጃ ምዘና ጉዳይ ነው በማለት ያለመቀበሉ በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነው፡፡
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የአሁኑ አመልካች በጨረታው አሸናፊ መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን ሽያጩ የሽያጭ ስነ ስርዓት ጉድለት አለበት ተብሎ እንዲፈርስ ጥያቄ የቀረበው የፍርድ ባለእዳ በሆኑትና ለእዳው ማስፈጸሚያ ተብሎ የተሸጠው ቤት ባለንብረት የሆኑት የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ መሆናቸውን፣ይኼው ተጠሪ በወረዳው ፍርድ ቤት ያቀረቡት የሽያጭ ይፍረስልኝ ጥያቄ ተቀባይነት ሲያጣ ይግባኙን ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲያቀርቡ ተጠሪ ያደረጉት የአሁኑን 2ኛ ተጠሪ ወይም የስር የፍርድ ባለመብት መሆኑን፣በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው የ1ኛ ተጠሪ ይግባኝ የተሰረዘው ተጠሪዎች ክርክር ሳያደርጉበት መሆኑን፣ከዚህ በኋላ 1ኛ ተጠሪ የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ሲያቀርቡ ተጠሪ ያደረጉት የአሁኑን 2ኛ ተጠሪ ሁኖ የሰበር ችሎቱ ጉዳዩን አከራክሮ ተገቢ ነው ያለውን ውሳኔ የሰጠው የጨረታውን አሸናፊ የሆነውን የአሁኑን አመልካች ወደ ክርክሩ ሳያስገባ መሆኑን ነው፡፡
በመስረቱ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ለ)) እና እና በክልሉ ሕገ መንግስት አንቀጽ 67(2(ሐ)) ተለይቶ የተሰጠው ስልጣን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ማረም እንጂ ፍሬ ነገርን ማጣራት ወይም ማስረጃን መመዘን ያለመሆኑ ተጠቃሽ የሕግጋተ መንግስታት ድንጋጌዎች የሚያስገነዝቡ ሲሆን የክልሉን ፍርድ ቤቶችን ያደራጀው የክልሉ አዋጅ ቁጥር 153/2000 በአዋጅ ቁጥር 169/2002 እንደተሻሻለ በአንቀጽ 8 ስር ሰበር ችሎቱ ያለው ስልጣን መስረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የማረም ስልጣን እንጂ ፍሬ ነገርን ማጣራትና ማስረጃን መመዘን ስልጣን ያለመሆኑን ያስረዳል፡፡የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሚመራው ከላይ በተጠቀሰው የክልሉ የፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅና በ1958ቱ የፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት መሰረት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
በመሆኑም ችሎቱ የተለየ የክርክር አመራር ስርዓት የሌለው እስከ ሆነ በ1958ቱ የፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ሕጉ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች መሰረት አድርጎ ክርክሩን መምራትና ዳኝነት መስጠት ያለበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በ1958ቱ የፍትሃ ብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ከተካተቱት ጉዳዮች መካከል ደግሞ የአፈፃፈም ክርክር የሚመራባቸው ድንጋጌዎች በግልጽ ተቀምጠዋል፡፡ እንዲሁም ይኼው ሕግ በአንቀጽ 32 እና 79 ድንጋጌዎች ስር የፍትሃ ብሔር ድንጋጌዎች በሕጉ በተመለከቱት ሁሉም ጉዳዮች ተፈጻሚነት ያላቸው መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን እነዚህ ድንጌጌዎች የቀጥታ ክስና የይግባኝ ክርክሮች ላይ በስነ ስርኣቱ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት ያላቸው መሆኑን፣ የይግባኝ መብት ደግሞ በፍርድ አፈፃጻም ፍርድ ቤቱ በሚሰጣቸው ትዕዛዛት ላይ በፍርድ አፈፃፀም ደንብ መሰረት ሌሎቹ ትዕዛዞች ይግባኝ እንደሚባልባቸው ሁሉ ስለ አፈጻጸሙ በሚሰጠው ትዕዛዝ ይግባኝ ማለት የሚቻል መሆኑን በአንቀጽ 370(3) ስር ደንግጓል፡፡ የቀጥታ ክስ ወይም ይግባኝ ክርክር ሲመራ ተግባራዊ መሆን ከአላባቸው የስነ ስርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች መካከል ደግሞ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 39 እና 40 ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረታዊ አላማ በአንድ ጉዳይ ላይ ክስ ሲቀርብና የክሱም ምክንያት የብዙ ሰዎችን መብትና ጥቅም የሚነካ ሆኖ ከእነሱ አንዱ ወይም ከፊሉ ክስ በቀረበ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በጉዳዩ ላይ በሚሰጠው ውሳኔ ወይም ፍርድ መብትና ጥቅም የሚነካ ሲሆን በክሱ ውስጥ ተካፋይ ያልሆኑ ሰዎች የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ መብታቸውን ለማስጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም ይኼው በሕጉ የተቀመጠው መመዘኛ መሟላቱ ከተረጋገጠ በክሱ ውስጥ ተካፋይ ያልሆኑ ሰዎች የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆኑ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ መስጠት ያለበት ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 39/1/ እና 40/2/ ድንጋጌዎች ይዘት ያስገነዝባል፡፡
እነዚህ ወገኖች ተካፋይ ሳይሆኑ የሚሰጠው ውሣኔ ወይም ፍርድ ውጤት የማይኖረው ስለመሆኑም የተጠቃሽ ድንጋጌዎች መንፈስ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም በክሱ መግባት ያለበት ተከሣሽ የሆነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የክርክር ተካፋይ እንዲሆንና በቀረበው ክስና መልስ መከላከያውን እንዲያቀርብ ሊያዘው የግድ የሚል ስለመሆኑ ሥነ ሥርአቱ ያሳያል፡፡ በክርክሩ ውስጥ የግድ ተካፋይ መሆን የሚገባቸው ወገኖች ማለት ደግሞ ክስ በቀረበበት ጉዳይ ላይ በሚሰጠው ውሳኔ ጥቅማቸው፣መብታቸው ወይም ግዴታቸው የሚነካ፣በክርክሩ ውስጥ ተካፋይ ያልሆኑ ሰዎች ስለመሆናቸውም ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 40 ድንጋጌ ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡በይግባኝ ደረጃ በሚደረገው ክርክርም ይግባኝ በቀረበበት የበታች ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ ውስጥ ተካፋይ የነበረ ማናቸውም ሰው በይግባኝ ክርክሩ ላይ ተካፋይ ሳይሆን የቀረበ እንደሆነ የይግባኝ ውጤት የሚመለከተው መሆኑን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ሲረዳው የይግባኝ ክርክር መስሚያ ቀነ ቀጠሮ በማስተላለፍ ተካፋይ ያልሆነውን ሰው በመልስ ሰጪነት አባሪ ሆኖ እንዲቀርብ ትዕዛዝ መስጠት ያለበት መሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 40(5) በግልጽ የተመለከተ ሲሆን የሰበር ችሎት የሚመራው በዚሁ በይግባኝ ሰርዓት የክርክር አመራር በመሆኑና በዚህ ድንጋጌ የተቀመጠው መመዘኛ ደግሞ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 447(4) ድንጋጌ ይዘት ጋር ሲታይ በጨረታ አሸናፊ የሆነ ሰውን ወደ ክርክሩ እንዲገባ ሳያደርግ ዳኝነት የሚሰጥበት አግባብ የሌለ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በፍርድ ቤት የሚደረግ ጨረታ በሕግ አግባብ የሚቋቋም ውል በመሆኑ የጨረታ አሸናፊ የሆነ ሰው የክርክሩ ተካፋይ ሳይሆን ውሉ ፈራሽ የሚሆንበት አግባብ ከውል አመሰራረት መሰረታዊ መርሆዎችም ሆነ ከፍርድ አፈጻጸም ስርዓት ጋር የማይሄድ ከመሆኑም በላይ የፍርድ ቤት ክርክሮች በግልጽ ታይተው መወሰን ያለባቸው ስለመሆኑ ሕገ መንግስቱ ስል
ገልፅነትና ተጠያቂነት ከተደነገገው መርህ ጋርም አብሮ የማይሄድ በመሆኑ ተቀባይነት ያለው የክርክር አመራርና የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓት አይደለም፡፡ በሕጉ አግባብ የተቋቋመ ውል መኖሩ በፍርድ ቤት የጸደቀለት ሰው ይኼው ውል በሕግ አግባብ ያልተደረገ ነው ተብሎ ፈራሽ ነው የሚል ውሳኔ ሲሰጥበት በዚሁ ላይ የሚያቀርበው ክርክር የማስረጃ ምዘና ብቻ ነው ተብሎ አቤቱታዋው በሰበር ሰበር ስርዓት የማይስተናገድበት አግባብ የለም፡፡ችሎቱ የጨረታ አሸናፊ የሰበር ክርክር የመሰረታዊ ሕግ ስህተት መመዘኛን የማያሟላ ነው የሚለውን ዳኝነት መስጠት ያለበትም ክርክሩን በሕጉ አግባብ ከመራ በኋላ ሊሆን ይገባል እንጂ አቤቱታ አቅራቢው ወደ ክርክሩ ገብቶ ተገቢውን ክርክር ሳያሰማ ሊሆን አይችልም፡፡ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አምስት ዳኞች ተሰይመው የሰጡት ዳኝነት የጨረታውን አሸናፊ የክርክሩ ተካፋይ ያላደረገ ነው የሚለውን የአመልካችን ክርክር የማስረጃ ምዝና ነው በማለት የደረሰበት ድምዳሜ የአመልካችን የመሰማት መብትንም የጎዳ መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡
በአጠቃላይ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የአመልካች የሰበር አቤቱታ የፍሬ ነገር እና የማስረጃ ምዘና ቅሬታዎችን መሰረት ያደረገ እንጂ የመሰረታዊ ህግ ስህተት መመዘኛን የሚያሟላ አይደለም በማለት ትዕዛዝ መስጠቱ ከመነሻውም ተገቢውን የክርክር አመራር ስርዓት ተከትሎ ባልተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የተሠጠው ውሳኔም ሆነ ትዕዛዝ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ተከታዩን ወስነናል፡፡
ው ሳ ኔ
1. በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 14450 ህዳር 04 ቀን 2006 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ እና በዚሁ መዝገብ ቀኑ ሳይጠቀስ የአመልካች አቤቱታ ማስረጃን መስማትን የሚጠየቅ ነው ተብሎ የተሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 348(1) መሠረት ሙሉ በሙሉ ተሸርዋል፡፡
2. የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የአሁኑን አመልካች የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆኑ አድርጎ በ1ኛ ተጠሪ በቀረበው የሰበር አቤቱታ ላይ ግራ ቀኙ በሕጉ አግባብ እንዲከራከሩ በማድረግ ተገቢውን ዳኝነት ሊሰጥበት ይገባል በማለት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 343(1) መሰረት ጉዳዩን መልሰን ልከንለታል፡፡ ይፃፍ፡፡
3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት