95587 civil procedure agency death of principlal

በሞተ ሰው ስም ቀደም ብሎ የተሰጠን ውክልና በመያዝ  የሚቀርብ ክስ ፣የሚደረግ ክርክር እና የሚሰጥ ውሣኔ እንዳልቀረበ እና ውሣኔም እንዳልተሰጠ የሚቆጠር ስለመሆኑ፣

የፍ/ብ/ህ/ቁ. 2232(1)

 

የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 57

 

ሰ/መ/ቁ. 95587

 

ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል

አመልካች፡- ወ/ሮ ሐዋ በከር አቶ ጀማል የሱፍ ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- 1. አቶ ቶፊቅ መሀመድ        ጠበቃ አቶ ፋይሶ ከድር ቀረቡ 2. አቶ አብዱሰላም መሀመድ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለው ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

1. ጉዳዩ የቀረበው አመልካች በሐዋ በከር የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 164559 ጥቅምት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይወሰንልኝ በማለት የሐዋ በከር ጠበቃ ነኝ በማለት አቶ ራጅ ገመቹ በአመልካች ስም ፅፈውና ፈርመው ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በሐሮማያ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው፡፡ የአውዳይ ፍርድ ቤት ጥር 30 ቀን 2004 ዓ.ም በሀዋ በከር ስም የቀረበለት ክስ ላይ የተከሳሾችን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶ ተከሳሾች በከሳሽ የይዞታ ቦታ ላይ ግንባታ በማከናወን ሁከቱ የፈጠሩበት ስለሆነ ሀከቱ እንዲወገድ በማለት በመዝገብ ቁጥር 24494 ታህሣሥ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

2. ተጠሪዎች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካችን (ሀዋ በከርን) በመልስ ሰጭነት በመሰየምና መልስ ሰጭ በወኪሏ በኩል መልሷንና ክርክሯን እንዳቀረበች በማስፈር የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ በመዝገብ ቁጥር 34942 ግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. በሰጠው ውሣኔ አፅንቶታል፡፡ ተጠሪዎች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ሀዋ በከርን በተጠሪነት በመሰየምና ተጠሪ በወኪል በኩል እንደተከራከረች በውሣኔው ውስጥ በማስፈር የወረዳው ፍርድ ቤትና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ ሽሮታል፡፡

3. ይህንን ውሣኔ በማስለወጥ በሀዋ በከር ስም ህዳር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. የተፃፈ የሰበር አቤቱታና መጋቢት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. የተፃፈ የመልስ መልስ ለዚህ ሰበር ችሎት ጠበቃው ራጅ ገመቹ ያቀረቡ ሲሆን ሐምሌ 15 ቀን 2006 ዓ.ም ሀዋ በከር በህይወት


የሌለች መሆኑ ለፍርድ ቤቱ በመግለፅ፣የሀዋ በከር ወራሽ የወራሽነት ማስረጃውን እንዲያያይዙ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ትዕዛዝ መሰረት አቶ ጀማል ዮሱፍ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ ማመልከቻ የሃረሚያ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 25234 መጋቢት 6 ቀን 2004 በተፃፈ መሸኛ ሀዋ በከር ህዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየች መሆኑን በማረጋገጥ የሰጠውን ፍርድና የወራሽነት ማስረጃ ቀርቧል፡፡ ተጠሪዎች በበኩላቸው ለወረዳው ፍርድ ቤት ክስ የቀረበውና እስካሁን ክርክሩ በሀዋ በከር ስም የቀጠለው ሟች ከሞተች በኋላ በመሆኑ ጉዳዩ ሊሰረዝልን ይገባል በማለት ጥቅምት 18 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ ማመልከቻ ጠይቀዋል፡፡

4. ይህችሎትሀዋበከር ህዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም በሞት ከተለየች በኋላ በሀዋ በከር ስም ከወረዳ ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ሰበር እንዴት ክርክር እንደ ቀረበ ለማጣራት ግራ ቀኙን በቃል እንዲከራከሩ በማድረግ አጣርቷል፡፡ ጠበቃው አቶ ራጅ ገመቹ በመጀመሪያ ፋይሉን የከፈተው ጀማል ዮሱፍ ነው፡፡ እኔ ክርክሩ ከተጀመረ በኋላ ነው ጉዳዩን የያዝኩት በማለት መልስ የሰጠ ሲሆን አቶ ጀማል ዮሱፍ በሟች ስም ለወረዳው ፍርድ ቤት ክስ ያቀረብኩት እኔ ነኝ፡፡ ባለማወቅ ነው ክሱን ያቀረብኩት በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡

5. አጠቃላይ የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተገለፀ ሲሆን፤ እኛም ጉዳዩን እንደመረመርነው በሀዋ በከር ስም ከወረዳ ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ እዚህ ሰበር ችሎት ክርክር ሲደረግ  የነበረው ሀዋ በክር ከዚህ አለም በሞት ከተለየች ከህዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም በኋላ ነው፡፡ ሀዋ በከር በህይወት እያለች ለአቶ ጀማል ዮሱፍ የሰጡት ውክልና ሀዋ በከር ህዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ውጤት እንደማይኖረውበፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2232(1) ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አንፃር ጀማል ዮሱፍ ሟች ሀዋ በከር በሕይወት እያለች የሰጠችውን ውክልና በመጠቀም ጠበቃ ወክሎ ሟች በህይወት እንዳለች በማስመሰል ለወረዳው ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስና ክፍያ ከዚያም በኋላ በይግባኝና በሰበር ያቀረበው ክርክር የሞተችው ሀዋ በክር በህይወት እያለች ሆኖ የቀረበ፣እስከ ሐምሌ  15 ቀን 2006 ድረስ ለሌሎች ፍርድቤቶችም ሆነ ለዚህ ችሎት ያልተገለፀና፣ ሀዋ በክር በህይወት እንዳለች ጀማል ዮሱፍ ወኪሏ እንደሆነና ወኪሏ ደግሞ ጠበቃ እንደወከለ ተደርጐ የቀረበ መሆኑን በመዝገቡ የቀረቡ ውሳኔዎችንና ሌሎች ክርክሮችን በመመርመር ተገንዝበናል፡፡

6. በአንድ ሰው ስም ፍርድ ቤት ቀርቦ ክስ ለማቅረብና ለመከራከር የሚችለው ዋናውባለጉዳይ ወይም ለዋናው ባለጉዳይ የወኪልነት፣የጠበቃነት ወይም የነገረ ፈጅነት ሥልጣን ያለው ሰው እንደሆነ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 57 ይደነግጋል፡፡በያዝነው ጉዳይ ጀማል የሱፍ የሟች ወራሽ መሆኑን ገልፆ በወራሽነቱ ያቀረበው ክስና  ክርክር የለም፡፡ጀማል የሱፍ ሀዋ በከር በህይወት እያለች የሰጠችውን የውክልና ሰነድ በመጠቀም የሀዋ በከር ወኪል በመሆንና ጠበቃ በመቅጠር በሀዋ በከር ሥም ሟች ከሞተች በኃላ ክስ አቅርቧል፡፡ይህም ጀማል የሱፍ ሀዋ በከር በመሞቷ ምክንያት  የተሰጠው የውክልና ሥልጣን ቀሪ ከሆነ በኃላ በወኪልነት ሥልጣኑ በመጠቀም ጠበቃ ያቆመ በመሆኑና ጠበቃውም ሀዋ በከርን በመወከል ጠበቃ ለመወከል ሥልጣን በሌለው ሰው ተወክሎ ክርክሩ ያቀረበ በመሆኑ ከወረዳው ፍርድ ቤት ጀምሮ በሀዋ በከር ስም እስከዚህ ችሎት ያቀረቡት ክርክር የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2232/1/ እና የፍታሐብሔር ሥነ -ሥርዓት ሕግ ቁጥር 57 ድንጋጌዎችን የሚጥስና ህጋዊ ዕውቅናና ውጤት ሊሰጠው የማይገባው ነው፡፡


7. በመሆኑም ህዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት በተለየችው ሀዋ በከር ስም ለሥር ፍርድ ቤት የቀረበ ክስና ከዚያም በኃላ ፍርድ ቤቶቹ ሀዋ በከር በህይወት እንዳለች በመገመትና በውሣኔያቸው በመግለፅ የሰጡት ውሣኔና ህጋዊ ዕውቅና ውጤት ሊሰጠው የማይገባ በመሆኑ በአመልካች ስም የቀረበውን ክርክርና የተሰጠውን ውሣኔ ሙሉ በሙሉ ሠርዘናል፡፡

 ው ሣ ኔ

 

1.  ክሱ የተጀመረውና እስከዚህ ሰበር ችሎት ክርክሩ የተደረገው ሀዋ በከር ህዳር 15   ቀን

2004 ዓ.ም በሞት ከተለየች በኃላ በሀዋ በከር ስም በመሆኑ ይህም የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2232/1 እና የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 57 ድንጋጌን የሚጥስ በመሆኑ በሟች ሀዋ በከር ስም የቀረበውን ክርክርና በየደረጃው ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ ሙሉ በሙሉ ተሰርዟል፡፡

2. ሀዋ በከር በሞት ከተለየች በኃላ በስሟ የቀረበው ክስ፣ክርክር እንዳልቀረበና በየደረጃው የተሰጡት ፍርዶች ሁሉ እንዳልተሠጡ ይቆጠራሉ ብለናል፡፡

3. በሞት በተለየችው ሃዋ በከር ሥም ክርክር በማቅረብ በተጠሪዎች ላይ ለደረሰው መጉላላትና ኪሣራ አቶ ጀማል የሱፍ ብር 2000/ሁለት ሺ ብር/ ኪሣራ ተጠሪዎች ይክፈል በማለት ወስነናል፡፡

 

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::

 

እ/ኢ