97217 civil procedure evidence law appeal procedure cassation procedure relevant evidence

civil procedure

evidence law

appeal procedure

cassation procedure

relevant evidence

 

 

አንድ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት (ሰበር ሰሚ ችሎት )የሥር ፍ/ቤት ጉዳዮን አግባብነት ባላቸው ማስረጃዎች ሁሉ አጣርቶ እንዲወስን ብሎ አንድን ጉዳይ ሲመልስ ስለማስረጃ አቀራረብ በህጉ የተመለከቱትን ድንጋጌዎችን ሁሉ ባላገናዘበ መልኩ ማስረጃ ይቅረብ ማለት ስላለመሆኑ፡-

 

ለአንድ ጉዳይ አግባብነት ያላቸው  ማስረጃዎች  መቅረብ ያለባቸው ለህጉ የተዘረጋውን ሥርዓት ጠብቀው ሊሆን የሚገባ ስለመሆኑና ተገቢውን የማስረጃ አቀራረብ ሥርዓት ሳይጠብቅ የሚቀርብ ማስረጃ ግን ዋጋ ሊሰጠው የማይገባና ውድቅ ሊደረግ የሚገባ ስለመሆኑ፣

 

የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 137(3) እና 256

 

የሰ/መ/ ቁጥር 97217

 

መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶ ባካፋ አንለይ  -- ራሳቸው ቀረቡ፡፡

 

ተጠሪ፡- አቶ ቴዎድሮስ አንለይ  - ጠበቃ ጌትነት አየለ ቀረቡ፡፡ መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ  ር ድ

 

ጉዳዩ ያለአግባብ የተያዘ የመኖሪያ ቤት ይለቀቅልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአሁን ተጠሪ በአመልካች ላይ በመሠረተው ክስ መነሻነት ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡- በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 08 ክልል ውስጥ የሚገኘውን፣ በካርታ ቁጥር 10/00/93 የሚታወቀውንና በ660 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሰፍሮ በስማቸው ተመዝግቦ ያለውን መኖሪያ ቤት ተከሳሽ ምንም መብት ሳይኖራቸው  ከህዳር ወር 1998 ዓ.ም ጀምሮ በመያዝ እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ገልፀው ቤቱ እንዲለቀቅላቸውና ያላግባብ ቤቱን ለተጠቀሙበት ጊዜ ደግሞ በወር ብር 2000.00(ሁለት ሺህ) ኪራይ ታስቦ እንዲከፈላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

 

ተከሳሽ የሰጡት የመከላከያ መልስም፡- ከሳሽ ቦታውን የተመራበት ካርኒ አላቀረበም፡፡ ቤቱ በ1963 ዓ.ም የተሠራ ሲሆን ውሃና መብራት የገባው በወላጅ አባታችን በደጃዝማች አንለይ ኃይሌ ስም በመሆኑ ቤቱ የአባታችን ቤት ነው፡፡ በአባታችን ስም የተከፈተው የማህደር ቁጥር 1224 የአባታችን ቤት መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ማህደሩ በሙሉ ተዘርፏል፡፡ ግብርበአባታችን ስም የተገበረ ለመሆኑ የባህር መዝገብ ቁጥር 202 ስለሚያስረዳ ቀርቦ መታየት ይችላል፡፡ ቤቱ ከአባታችን ሞት በኋላ ከእናታችን ጋር የምንገለገልበት እንጅ ተከራይቶ አያውቅም፡፡ ከሳሽ ከአከራካሪው ቤት ጐን በሊዝ የተመራውን ቦታ አንድ ላይ በማድረግ የሟች አባታችንን  ቤትና ቦታ አጠቃሎ ካርታ እና ፕላን አወጣበት እንጅ የእሱ አይደለም፡፡ ስለዚህ የወራሽነት ድርሻውን ከሚጠይቅ ውጪ የግሌ ነው በማለት ያቀረበው ክርክር ሐሰት ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡

 

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከሰማ በኋላ አከራካሪው ቤት የከሳሽ ለመሆኑ ከተከሳሽ በተሻለ አስረድተዋል በማለት በአብላጫ ድምጽ ተከሳሹ ቤቱን ለከሳሽ ሊያስረክብ ይገባል በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ባለመስማማት  ይግባኛቸው  ለክልሉ  ጠቅላይ  ፍርድ  ቤት  ይግባኝ  ሰሚ    ችሎት፣የሰበር


አቤቱታቸውን ደግሞ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት ሲያጡ ጉዳዩን ለዚህ ችሎት አቅርበው ይህ ችሎትም ግራ ቀኙን በመ/ቁጥር 55907 አከራክሮ የበታች ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ውሳኔ በመሻር ጉዳዩ በአግባቡ ተጣርቶ ሊወሰን ይገባል ሲል ሊጣሩ የሚገባቸውን ነጥቦች ለይቶና ሊቀርቡ የሚችሉትን ማስረጃዎችን ጭምር ጠቁሞ ጉዳዩን ለስር ፍርድ ቤት መልሶ ልኮለታል፡፡

 

ጉዳዩ የተመለሰለት የምዕራብ ጐጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም እንደገና ግራ ቀኙን በመጥራት አለኝ የሚሉትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ አስቀርቦ በመስማትና ለጉዳዩ አግባብነት አላቸው ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎችን ከሚመለከታቸው አካለት እንዲቀርቡና ማብራሪያም እንዲሰጥበት ጭምር ከአደረገ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ከ660 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ ውስጥ በ440 ካ/ሜትር ክልል ውስጥ ያለው ቤት የአሁኑ ተጠሪ አይደለም፣ 220 ካ/ሜትር ቦታ ግን ተጠሪ በሊዝ የገዙት በመሆኑ የአሁኑ አመልካች ለቀው ሊያስረክቡ ይገባል በማለት ወስኗል፡፡

 

የአሁን ተጠሪ በዚህ ውሣኔ ቅር በመሠኘት ጉዳዩን በይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አቅርበው ችሎቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ 440 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ የአሁን ተጠሪ ስለመሆኑ በሰውም ሆነ በሰነድ ማስረጃ ከአሁኑ አመልካች ክርክርና ማስረጃ በተሻለ መልኩ ተረጋግጧል የሚል ድምዳሜ ይዞ የአሁን አመልካች ቤትና ቦታውን ሙሉ በሙሉ ለቀው ለተጠሪው ሊያስረክቡ ይገባል፣ ያላግባብ ለተጠቀመበት የቤት ኪራይም በወር 2000.00 ታስቦ በድምሩ ብር 62,000 /ስልሳ ሁለት ሺህ ብር/አመልካች ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በኋላ የአሁኑ አመልካች ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኛቸውን አቅርበው ችሎቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ አመልካች 440 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ ጭምር እንዲለቁ መወሰኑ ባግባቡ ነው፣ የኪራይ ገንዘቡን በተመለከተ ግን ለተጠሪ ቀድሞ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያልወሰነው እና ጉዳዩ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሲመለስም እንዲጣራ ያልታዘዘ በመሆኑ አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍሉ የሚወስንበት የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓት የለም ብሎ በጉዳዩ ላይ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተሰጠውን ውሳኔ አሻሽሎ ወስኗል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- አከራካሪው ቤትና ቦታ የሟች አባታችን ለመሆኑ በተገቢው መንገድና ማስረጃ ተረጋግጦ እያለ የተጠሪው ነው ተብሎ እንዳስረክብ የተወሰነው ያለአግባብ ነው፣ተጠሪው አለኝ ያሉት የኑዛዜ ሰነድም የማስረጃ አቀራረብ ስርዓትን ተከትሎ ያልቀረበና ሕጋዊ አይደለም፣በጉዳዩ ላይ ዳኝነት የተሠጠው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲጣሩ የተለዩት ነጥቦችንና ጉዳዩ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከተመለሰ በኋላ ከሚመለከታቸው አካላት የቀረቡትን የሰነድ ማስረጃዎችን ባለገናዘበ መልኩ ነው የሚል ሁኖ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ እንዲሻር ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የሰበር አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከለተው መልኩ መርምሮታል፡፡  እንደመረመረውም አመልካች 440    ካ/ሜትር


ቤትና ቦታ ለተጠሪ ሊለቁ ይገባል ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባው ሁኖ አግኝተናል፡፡

 

በቅድሚያ ተጠሪ ጉዳዩ የፍሬ ነገር ክርክር ነው በማለት ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ተመልክተናል፡፡ በአመልካችና በተጠሪ መካከል ያለው ክርክር ከማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ጋር የተያየዘ ሲሆን በዚህ ችሎት ጉዳዩ የቀረበው ጉዳዩ በሕጉ አግባብ ተጣርቶ የተወሰነ መሆን ያለመሆኑንና የማስረጃ አቀራረብ ስርዓትን እንዲሁም የምዝና መርሁን ባገናዘበ መልኩ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ጭብጥ የፍሬ ነገር ማጣራት ወይም የማስረጃ ምዘና ጉዳይ ባለመሆኑ በዚህ ችሎት የማይታይበት አግባብ ስላላገኘን በዚህ ረገድ የቀረበውን የተጠሪን ተቃውሞ አልተቀበልነውም፡፡

 

ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስም፡- ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ይህ ችሎት ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሲመልስ ሊጣሩ የሚገባቸውን ነጥቦችን የለየ መሆኑን ነው፡፡ይህ ችሎት ጉዳዩን ወደ ታች ሲመልሰው ለክርክሩ መነሻ የነበረውን ይዞታ ማነው የተመራው ፣ ቤቱን ማነው የሰራው፣በማን ገንዘብ ተሰራ የፅሁፍ ማስረጃዎችን በተመለከተ ካርታ በከሳሽ (የአሁን ተጠሪ) ስም የተሰጠ መሆኑ ከማስረዳት ባለፈ የከተማው  አስተዳደርየቤቱንና የይዘታውን አመጣጥ በአግባቡ ያውቃል ተብሎ ስለሚገመት በስር ፍርድ ቤቱ በኩል ታዞ ተጨማሪ ማብራሪያዎችንእንዲሰጥበት ሊደረግ እንደሚገባ፣ ማብራሪያ ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች መካከልም በከተማ አስተዳደሩ የነበረውን የማህደር ቁጥሩ 1224 የሆነውና በደጃዝማች አንለይ ሃይል ስም የነበረው/ የተከፈተው ለየትኛው ይዞታና ቤት ነበር የውሃና መብራት ውል በስማቸው ሊዋዋሉ የቻሉበትን አግባብ እንዴት እንደነበር፣ ከማህደሩ ውስጥ ጠፍቷል የተባሉት ገፆች እንዴት ሊጠፉ እንደቻሉ ፣ጠፍተውም ከሆነ መጥፋታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የጠፉት ገፆች ይዘታቸው ምን እንደነበር ያሁን ተጠሪ ካርታ 660 ካሬ ሜትር ላይ የወጣላቸው በአንድ ጊዜ ነው ወይስ አሁን ክርክር ካስነሳው ይዞታ ጎን የነበረውን 220ካሬ ሜትር ከተመሩ በኋላ ነው፣ አሁን ክርክር የተነሳበት ይዞታ ከ220 ካሬ ሜትር ጋር ተጠቃሎ የተሰራ ነው ወይስ አይደለም፣ ሒደቱስ እንዴት ነበር የሚሉት ነጥቦች ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ናቸው በማለት ዘርዝሯል እንዲሁም ሰበር ችሎቱ የግብር አከፋፈል ሂደቱ በተካራካሪዎች አባት ሲከፈል የነበረበትና በተጠሪም ሲከፈልበት የነበረበት አግባብ ሊጠራ የሚገባው ነጥብ መሆኑን በመግለፅ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በባህርዳር ከተማ ገቢ ፅ/ቤት የባህር መዝገብ ተራ ቁጥር 202 በአባታቸው ስም ይገበር የነበረ በመሆኑ ቀርቦ ይታይልኝ በሚል ጥያቄ ቀርቦ ፍ/ቤቱ ስለማየቱ በፍርዱ ውስጥ የተባለ ነገር ባለመኖሩ ማስረጃው ቀርቦ ሊታይ እንደሚገባ ለስር ፍርድ ቤት መመሪያ ሰጥቷል፡፡ከዚህ በተጨማሪ ቤቱ ተሰራ ከተባለበት ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ ግራ ቀኙም ሆኑ ሌሎች የቤተሰብ አባላት በተለይም እናትና አባት ከቤቱ ጋር ያላቸውና የነበራቸው ቁርኝት መታየትና መጣራት እንዳለበትም በውሳኔው ላይ አስፍሮ ጉዳዩን ለስር ፍርድ ቤት የመለሰለት መሆኑን ተረድተናል፡፡

 

ከላይ የተመለከቱት ነጥቦች ይህ ችሎት በስር ፍርድ ቤት እንዲጣሩ የለያቸው ሲሆን የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩ ከተመለሰለት በኋላ ፍሬ ነገሩን ያጣራበትን መንገድ መመልከቱ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

 

የስር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ምስክሮች የሰማ ሲሆን በሥር ፍ/ቤት የተሠሙት የተጠሪ ምስክሮች ቤቱን ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1965 ድረስ ባለው ጊዜ ተመርቶ የሠራው ተጠሪ መሆኑን፣ ቤቱን ሲሰራም ከተለያዩ ሰዎች ገንዘቡን ተበድሮ መስራቱን የሚያውቁ መሆኑን አስረድተው ቤቱን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲሄድ አባቱ እንዲኖሩበት  ፈቅዶላቸው


ይኖሩበት እንደነበር፣ በዚሁ ሁኔታ ውሀና መብራት በእሳቸው ስም መግባቱን መስክረዋል፡፡ ባንቺ ዓለም አንለይ የተባለችው የግራ ቀኙ እህት በሰጠችው ምስክርነትም ቤቱ የታላቅ ወንድማችን የቴዎድሮስ አንለይ ነው፣ አባታችን በሕይወት እያሉ ሁሉን ነገር ያንቀሳቅሱ የነበሩ እሳቸው ናቸው፣ በኑዛዜያቸውም ቤቱን የተጠሪ መሆኑን ገልፀዋል፣ እሳቸው በ1990 ዓ.ም ከሞቱ በኋላ ቤቱ በብር 2000 ተከራይቶ ነበር፣ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ቤቱ በአሁኑ አመልካች ይዞታ ስር መቆየቱንም ሁሉም ምስክሮች አስረድተዋል፡፡ የአመልካች ምስክሮች በበኩላቸው ቤቱን የሠሩት የግራ ቀኙ አባት ደጃዝማች አንለይ ኃይሌ ናቸው፣ ቦታውን የተመሩት ደግሞ በተጠሪው ስም ነው፣ ግብር ይከፈል የነበረው ደግሞ በደጃዝማች አንለይ ስም ነበር በማለት መመስከራቸውን የውሳኔው ግልባጭ ያሳያል፡፡

 

ከክፍሉ ማዘጋጃ ቤት የቀረበው የሙያ ምስክር የሰጠው ምስክርነትም የደጃዝማች አንለይ በልጃቸው ቴዎድሮስ አንለይ ስም ቦታ ተመርተው በራሳቸው ስም ሲገብሩ ቢኖሩም በኋላ ግን ቦታው በስሙ በተመራው ልጃቸው /በተጠሪ ስም/ ግብሩ ተስተካክሎ ሲገበር መቆየቱን፣ በፊት የነበረው ቦታ 440 ካሬ ሜትር ሲሆን በኋላ 220 ካሬ ሜትር ቦታ ሊዝ ገዝቶ ጨምሮበት 660 ካሬ ሜትር ቦታ በተጠሪ ስም ተጠቃሎ መስጠቱን መግለጹን የስር ፍርድ ቤት መዝግቧል፡፡

 

የስር ፍርድ ቤት በሰነድ ማስረጃነት ያስቀረበው የባህር ዳር ከተማ አስተዳዳር ገቢዎች ጽ/ቤት ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ ቁጥር አዘል ደብዳቤ በባህር መዝገብ ቁጥር 202 በሆነ ግብር በተጠሪው ስም የማይገበር መሆኑንና መዝገቡ በደጃዝማች አንለይ ኃይሌ ስም መሆኑን የሚያሳየውን ሰነድ፣ በባህር ዳር ከተማ ውሀና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት ጥቅምት 10 ቀን 2004 ዓ.ም. በተፃፈ ቁጥር የያዘ ደብዳቤ ውሀ የገባው በደጃዝማች አንለይ ኃይሌ ስም መሆኑንና በመሥሪያ ቤቱ አሠራር ውሀ በስም ለማስገባት የሚቻለው ባለይዞታ መሆኑን ገልፆ በወቅቱ ደጃዝማች አንለይ ባለይዞታ ስለሆኑ ውሃው የገባላቸው መሆኑን በማረጋገጥ  የሰጠው ሰነድ፣በባህር ዳር ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ጥቅምት 10 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የማህደር ቁጥር 1224 የሆነውን በደጃዝማች አንለይ ኃይሌ ስም የነበረው ቦታ የሚያሳየው የተለያዩ ቦታዎችን ከሰዎች መግዛታቸውን፣ ይሁን እንጂ እነዚህ ቦታዎች የተወረሱባቸውና በተለያየ ምክንያት የፈረሱ መሆኑን፣ ህዳር 19 ቀን 1984 ዓ.ም በፃፉት ማመልከቻ ቦታ እንዳሌላቸውና በልጃቸው በቴዎድሮስ አንለይ ቤት በጢሰኝነት እንደሚኖሩና ቦታ እንዲሰጣቸው ያመለከቱበት ማመልከቻ መኖሩንና አቶ ቴዎድሮስ ፋይል ላይ ደግሞ ግንቦት 11 ቀን 1992 ዓ.ም በተዘጋጀ ሳይት ፕላን ባህር ዳር ከተማ 08 ቀበሌ የ440 ካሬ ሜትር ቦታ እንደነበራቸውና 220 ካሬ ሜትር ቦታ በሊዝ ጠይቀው ከሚያዚያ 24 ቀን 1993 እስከ ግንቦት 02 ቀን 1993 ዓ.ም እንዲወስዱ ተወሰኖላቸው የ660 ካሬ ሜትር ቦታ ካርታ መውሰዳቸውን የሚገልፅ ሰነድ ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በባህር ዳር ዲስትሪክት ቁጥር 2 አገልግሎት ማዕከል ጥቅምት 06 ቀን 2004 ዓ.ም የተፃፈ ደብዳቤ መብራት በደጃዝማች አንለይ ኃይሌ ስም መግባቱን የሚያሳይ ሰነድ፣ የባህር ዳር ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ጥቅምት 26 ቀን 2001 ዓ.ም የፃፈው ደብዳቤ በደጃዝማች አንለይ ኃይሌ ስም ይገበርበት የነበረ ምንም ዓይነት ካርታና ፕላን የለም ሲል የገለጸበት ሰነድ፣የባህር ዳር ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ጥቅምት 07 ቀን 2001 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ አከራካሪው ቤትና ቦታ በአቶ ቴዎድሮስ አንለይ ስም በካርታ ቁጥር 10100/93 በፋይል ቁጥር 291 ተመዝግቦ የሚገኝ መሆኑን እንደሚያሳይ የገለፀበት ሰነድ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የሰነድ ማስረጃዎች በተጨማሪ የስር ፍርድ ቤት በማስረጃነት የያዘው ሰነድ የአሁኑ ተጠሪ ጉዳዩ ወደ ስር ፍርድ ቤት ከተመለሰ በኋላ አገኘሁ ብለው በተጨማሪ ማስረጃነት እንዲታይላቸው ያቀረቡት


ሰነድ ሲሆን ይህም ሟች ደጃዝማች አንለይ ኃይሌ መስከረም 06 ቀን 1984 ዓ.ም. አደረጉ የተባለው ኑዛዜ ሁኖ ለጉዳዩ አግባብነት አለው የተባለው የኑዛዜው ክፍል ሟቹ "…..አሁን ያለንበት መኖሪያ ቤት በልጄ በቴዎድሮስ አንለይ ስም የተሠራ ነው፣ቤቱም የተሠራበት ቦታ በራሱ ስም የተገኘና የተያዘ ሥለሆነ ቤቱን ከነቦታው መረከብ ይችላል…."  በማለት ማስፈራቸውን ያሳያል ተብሎ በስር ፍርድ ቤቶች ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ የሰውና ሰነድ ማስረጃ መገንዘብ የሚቻለው በአከራካሪው ቤትና ቦታ ውሀና መብራት በደጃዝማት አንለይ ኃይሌ ስም መግባቱንና በቤቱም ውስጥ እየኖሩ ግብር በህይወት እስከነበሩ ድረስ በእሳቸው ስም ይገበሩ የነበረ መሆኑን ሲሆን የቤቱን ካርታ እና ፕላን ግን በእሳቸው ስም የተመዘገበ አለመሆኑንና በተጠሪው ስም የተመዘገበ መሆኑን ነው፡፡በተጠሪው ስም የተመዘገበበት ጊዜ በ1993 ዓ/ም ስለመሆኑ ክርክር የቀረበበት የፍሬ ነገር ነጥብ አይደለም፡፡ይህ ምዝገባ የተከናወነው ቦታው በተጠሪው ስም የተመራ ነው በሚል ምክንያት ስለመሆኑ ማዘጋጃ ቤቱ የሚከተለውን  አሰራርን መሰረት በማድረግ ለስር ፍርድ ቤቱ ማብራሪያ እንደሰጡ የቀረቡት ሰራተኞች ከሰጡት የምስክርነት ቃል መገንዘብ የሚቻል ቢሆንም በቤቱ ማህደር ውስጥ ሰነዶች እንደነበሩ ሳይካድ ሰነዶቹ የጠፉት ህጋዊ ምክንያት ግን በማስረጃ ያለመረጋገጡን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡ ማዘጋጃ ቤት  ያለው የቤቱ ማህደር የአመልካችን አባት ስም የማይጠቀስ ነው የተባለ ቢሆንም ተመሳሳዩን ቤትና ቦታ በተመለከተ በግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ይገኛል የተባለው ማህደር ደግሞ የአሁኑን ተጠሪ ስም የማይገልፅ፣ይልቁንም የሟች ደጃዝማች አንለይ ኃይሌን ስም የሚገልፅ መሆኑን የሚመለከተው አካል ለፍርድ ቤቱ አረጋግጦ ልኳል፡፡ይህ ማህደር ሰነዶቹ የጠፉት ስለመሆኑ በተጠሪ ክርክር ያልቀረበበትና ሕጋዊ ተቀባይነቱም ጥያቄ ውስጥ ያልገባ  የሰነድ  ማስረጃ መሆኑን ክርክሩ በግልጽ ያሳያል፡፡

 

በመሰረቱ አንድ ሰው በፍ/ብ/ህ/ቁ 1195 ድንጋጌ መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነትን በማወቅ በአስተዳደር ክፍልየምስክር ወረቀት ሲሰጥ የምስክር ወረቀቱን ያገኘው ሰው የማይንቀሳቀሰው ንብረት ባለሃብት ሁኖ ሊገመት እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡ ይህ ድንጋጌ በግልጽ የሚያሳየው በአስተዳደር አካሉ የሚሰጥ ማስረጃ የመብቱ ባለቤት የሆነውን ሰው ለመለየት ግምት የሚወስድበት እንጂ አሳሪ ወይም ድምዳሜ ማስረጃ /conclusive evidence/ ያለመሆኑን ይልቁንም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1196 ስር በተመለከቱት ውስን ምክንያቶች አግባብ ሊሰተባበል የሚችል ሕጋዊ ግምት /rebuttable legal presumption/ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም በፍ/ብ/ህ/ቁ 1195 ስር የተመለከተው የህግ ግምት ፍጹም የሆነ ወይም ድምዳሜ ማስረጃ ሳይሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1196 ስር የተመለከቱት ሁኔታዎች ስለመኖራቸው በማናቸውም ማስረጃ በማረጋገጥ ሊስተባብል የሚችል የሕግ ግምት ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ስው በአስተዳደር አካል የተሰጠ ካርታ በመያዙ ብቻ በካርታው የተጠቀሰው የማይንቀሳቀስ ንብረት ህጋዊ ባለሃብት እንደሆነ ህጉ ግምት ቢወስድለትም ይህ ግምት ግን ካርታው የተሰጠበትን አግባብ ከደንቡ ከአስራሩና ከሰልጣኑ ውጪ እንዲሁም በማይረጋ የምስከር ወረቀት መሰረት ማስረጃው ተሰጥቶ ከሆነ ይህንኑ በማናቸውም ማስረጃ በማረጋገጥ የህጉን ሕሊናዊ ግምት ማፍረስ እንደሚቻል ፍ/ብ/ሕ/ቁ 1196 ድንጋጌ በግልጽ ያሳያል፡፡ ይህንኑ የህጉን ይዘትና መንፈስ ካርታው ከመሰረዝ ጋር አስተሳስረን ስንመለከተውም አንድ የአስተዳደር አካል በሕጉ አግባብ የተሰጠን የባለቤትነት ማስረጃ በሕጉ የተመለከቱት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ዋጋ አልባ የሚያደርገው ሕጋዊ አግባብ የሌለ መሆኑን በቀላሉ የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሰው በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የባለቤትን መብት አቋቁሟል ለማለት የሚቻለው በህግ አግባብ የተገኘውን ማስረጃ መሰረት አድርጎ የመፋለም ክስ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት አቅርቦ በጉዳዩ የሚቀርቡት ማስረጃዎች በሕጉ


የተዘረጋውን የማስረጃ አቀራረብ ስርዓት ተከትለው ሲቀርቡና ማስረጃዎቹ ለጉዳዩ ተፈጻሚነት ባለው የማስረጃ ምዘና መርህ መሰረት ክሱን ማስረዳታቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡

 

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ ተጠሪ በ1993 ዓ/ም ከአስተዳደር አካሉ የባለቤትን ማረጋገጫ ደብተር አግኝተዋል ተብሎ ማስረጃው መቅረቡ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1195 መሰረት ማስረጃው የተሰጠበትን ንብረት ባለሃብት ናቸው ተብሎ የሚገመቱት ተጠሪ ናቸው ተብሎ ግምት ለመውሰድ የሚያስችል ቢሆንም የክርክሩ ልዩ ባህርይ ሲታይ በተለይም የአከራካሪው  ቤት ማህደር ውስጥ ነበሩ የተባሉ ሰነዶች ከጠፉ በኋላ ማስረጃው ለተጠሪ መሰጠቱ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ ተጠሪ አለኝ በማለት ያቀረቡት ይኼው የባለቤትነት የምስክር ወረቀት ሕጋዊ ተቀባይነት እንዲሰጠው የማያደርገው ሁኖ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች ይህንን ለማስተባበል በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1196 በተደነገገው አግባብ ለተጠሪውየተሰጠው የባለቤትነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ከደንብ ውጪ በሆነ አሠራር ወይም ሥልጣን በሌለው አስተዳዳር ክፍል ስለመሆኑ በሰውም ሆነ በሰነድ ማስረጃው ያስረዱት ነገር የለም በማለት መደምደማቸው በክርክሩ ሂደት የቀረቡትን ሁሉንም ማስረጃዎች ያገናዘበ ሁኖ አልተገኘም፡፡ ሟች ደጃዝማች አንለይ ኃይሌ ግብር በስማቸው መገበራቸው ወይም ውሃና መብራት በስም ማስገባታቸው ከሚመለከታቸው አካላት በቀረቡት ማስረጃዎች የተረጋገጠ ሲሆን እነዚህ  ማስረጃዎች  በአመልካችና በተጠሪ መካከል አይነት በተነሳው ክርክር የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነትን ለማረጋገጥ አይችሉም ተብሎ ማስረጃዎቹ ውድቅ የሚሆኑበት የማስረጃ ምዝና መርህ የለም፡፡ የበታች ፍርድ ቤቶች የባህር ዳር ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት ውሃ በስም ሊገባ የሚችለው የይዞታ ባለቤትነት ሲረጋገጥ ነው በማለት የሰጠውን የሰነድ ማስረጃም በደፈናው በምን እንዳረጋገጠው የገለፀው ነገር ባለመኖሩ የሰጠው ማረጋገጫ ተቀባይነት አለው ብሎ ለመውሰድ የሚቻል አይደለም በማለት ከማለፋቸው በስተቀር የመስሪያ ቤቱ የተለመደ አሰራር አለመሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲቀርብ ያላደረጉ በመሆኑ ማስረጃው ተቀባይነት ያጣበት አግባብ ሕጋዊ ምክንያትን መሰረት አድርጎ አለመሆኑን ተገንዝበናል፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩት ቤትና ቦታው የሟች አባታችን ነው በማለት ሲሆን ሟች አባታቸው መስከረም 06 ቀን 1984 ዓ.ም ባላደረጉትና ስርዓቱን ጠብቆ ባልቀረበው የኑዛዜ ሰነድ ክርክር ያስነሳው ቤት የተጠሪ ነው መባሉ ያላግባብ ነው በሚል ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች ይህ የኑዛዜ ሰነድ ለማስረጃነት የቀረበበትን አግባብ በውሳኔውአቸው ላይ በግልጽ ባያሰፍሩም የአሁኑ ተጠሪ በዚህ የሰበር ደረጃ በዚህ ረገድ የሚያቀርቡት ክርክር ሰነዱ ቀድሞ ሊገኝ ባለመቻሉ የቀረበና ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለስር ፍርድ ቤት ሲመልስም ጉዳዩ አግባብነት ባላቸው ሌሎች ማስረጃዎች ጭምር እንዲጣራ ብሎ ስለአዘዘ ማስረጃው መቅረቡ ተገቢ ነው በሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ችሎት የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን አግባብነት ባላቸው ማስረጃዎች ሁሉ አጣርቶ እንዲወስን በማለት የሰጠው ውሳኔ ስለማስረጃ አቀራረብ በህጉ የተመለከቱትን ድንጋጌዎችን ሁሉ ባላገናዘበ መልኩ ማስረጃው እንዲቀርብ በማሰብ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚገባ አይደለም፡፡ በመሆኑም ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸው ማስረጃዎች መቅረብ ያለባቸው በሕጉ የተዘረጋውን ስርዓት ጠብቀው ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ተጠሪ አለኝ የሚሉትን የኑዛዜ ሰነድ በተመለከተ ለማስረጃነት ያቀረቡት ጉዳዩ ከዚህ ችሎት ከተመለሰ በኋላ ሲሆን ሰነዱ በማስረጃነት እንዲቀርብ የጠየቁበት አግባብም ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 137(3) እና 256 ድንጋጌዎች ይዘት ጋር የተገናዘበ መሆኑን ያረጋገጡት ነገር የሌለ መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡ የተጠሪ ምስክር የሆኑት እህታቸው ቀድሞ ክርክሩ ላይ የምስክርነት ቃላቸውን   የሰጡ


ሲሆን በዚህ ጊዜ ስለኑዛዜ ሰነዱ የሰጡት የምስክርነት ቃል ሳይኖር ጉዳዩ ወደ ዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲመለስ ቤቱ የተጠሪ መሆኑን ሟች ደጃዝማች በኑዛዜ አረጋግጠውላቸዋል የሚለው ምስክርነታቸው ቀድሞውንም ኑዛዜ መኖሩ ይታወቅ የነበረ መሆኑን የሚያሳይ ምስክርነት ነው ሊባል የሚችልና ተጠሪ ሰነዱን በጊዜው ተገቢውን ጥረት አድርገው ማቅረብ ይችሉ የነበረ፣ ማቅረብ የማይችሉበት ምክንያት ካለውም ይህንኑ ለፍርድ ቤቱ ማሳወቅና በሌላ አግባብ ማስረዳት ይችሉ የነበረ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በመሆኑም የኑዛዜው ሰነድ ለማስረጃነት የቀረበበት አግባብ ከተጨማሪ ማስረጃ አቀራረብ ስርዓት ውጪ ነው፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች ሰነዱን ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው ሟቹ በኑዛዜው ላይ ቤቱ የልጅ ቴዎድሮስ አንለይ በስሙ ቦታ ተመርቶ የሠራው ስለሆነ ቤቱ ከነቦታው መረከብ ይችላልብለው ማስፈራቸውን፣የኑዛዜው ቃል ይዘት ቤቱ የሟች ነው ተብሎ አሁን የተከሰተው ዓይነት ክርክር እንዳይፈጠር አስቀድመው አስበው ያደረጉት መሆኑን ነው በሚል ምክንያት ሰነዱ የማስረጃነት ዋጋ መስጠታቸው ተገቢነት የሌለውን የማስረጃ አቀራረብ ስርዓት ተፈጻሚ በማድረግ የደረሱበት ድምዳሜ በመሆኑ በሕግ ተቀባይነት ሊሰጠው የማይገባ ሁኖ አግኝተናል፡፡

 

ሲጠቃለልም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አከራካሪው 440 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ የተጠሪ ሃብት ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ ጉዳዩ እንዲጣራ ሲመለስ በክርክሩ ላይ በህግ አግባብ የቀረቡትን የሰነድ ማስረጃዎችን ይዘት ከክርክሩ ልዩ ባህሪና ተገቢነት ካለው የማስረጃ ምዘና መርህ ጋር ባለማገናዘብ ሁኖ ስለአገኘው በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት  ሁኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስናል፡፡

 

              

 

1.  የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 34051 የካቲት 20   ቀን

2005 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተሰጥቶ በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት  ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 88365 ታህሳስ 02 ቀን 2006 ዓ/ም ተሻሽሎ የጸናው ውሣኔ በፍ/ብ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ. 348/1/ መሠረት ተሻሽሏል፡፡

2.  የምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 25679 ግንቦት 30 ቀን

2004 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

3. አመልካች 440 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ ለተጠሪ ሊያስረክቡ ይገባል የተባለው የውሳኔ ክፍል ተሽሯል፡፡ አመልካች ብር 62,000 /ስልሳ ሁለት ሺህ ብር/ የቤት ኪራይ ለተጠሪ ሊከፍሉ አይገባም፣ 220 ካ/ሜትር ቦታ ሊለቁ ይገባል ተብሎ የተሠጠው የውሳኔ ክፍል ፀንቷል፡፡

4.  ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

5. ተጠሪ በውርስ አግባብ አለኝ የሚሉትን መብት ከመጠየቅ ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም ብለናል፡፡

 ት ዕ ዛ ዝ

በዚህ ችሎት መጋቢት 08 ቀን 2006 ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረው የአፈፃፀም ዕግድ ተነስቷል፡፡ ይፃፍ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት