94713 civil procedure counter claim procedure for counter claim

civil procedure

counter claim

procedure for counter claim

 

 

 

 

የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ የፍትሐብሔር ሥነ- ስርዓት ህጉ በሚያዘው መሰረት ሥርዓቱን ጠብቆ ያልቀረበ ከሆነ ዳኝነት ሊሰጥበት የማይችል ስለመሆኑ፣

 

 

የፍ/ሥ/ሥ/ሕ.ቁ 234(1)፣(2)

 

የሰ/መ/ቁጥር 94713

 

መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ

ተኽሊት ይመሰል

 

አመልካቾች፡- 1. ህጻን ሲኢድ ዘውዴ

 

2. ህጻን ኑሩ ሁሴን ዘውዴ   ሞግዚት ወ/ሮ ሙሉ ሞሳ - ጠበቃ ሆነልኝ ዋለ -

 

3. ህጻን አዲሱ ዘውዴ       ቀረቡ

 

ተጠሪ፡-  1.ወ/ሮ ጥሩሰው ሞሳ        6. ሞሚና አግማስ     የ1ኛ፣2ኛ፣3ኛ፣5ኛ-8ኛ ጠበቃ 2. ሶፊያ አግማስ 7. ጥጋቡ አግማስ                   አዲስ መንግስት ቀረቡ፡፡

3. ፋንታ አግማስ           8. በላይ አግማስ

 

4. አስጋርጅ አግማስ         9. አለሚቱ ታደሰ            ታልፏል፡፡

 

5.ብርቄአግማስ

 

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ ከውርስ ንብረት ግምት ክፍያ ጋር ተያይዞ የቀረበ ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው ያሁኑ ተጠሪዎች በአሁኑ አመልካቾች ሞግዚት ላይ በአማራ ብሔራዊ ክልልዊ መንግስት በደብረ ታቦር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻነት ነው፡፡ የአሁኑ አመልካቾች ሞግዚት ተከሳሽ፣ አሁን ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ስምንት የተጠቀሱት ተጠሪዎች ከሳሾች፣9ኛ ተጠሪ ደግሞ ጣልቃ ገብ ነበሩ፡፡

 

የክሱ ይዘትም፡-ከተጠሪዎች መካከል ከተራ ቁጥር ሁለት ጀምሮ ያሉት ከወላጅ አባታቸው ከሟች አቶ አግማስ አምባው ላይ በውርስ ያገኙትንና አዋሳኙ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን በ369 ካ/ሜትር ያረፈውን ቤት ከሟች ባለቤት ከወ/ሮ ጥሩሰው ሞሳ ጋር እኩል ተካፍለው ከይዞታው ውስጥ 184.57 ካ/ሜ ከወ/ሮ ጥሩሰው ሞሳ ድርሻ ውጪ ያለው ግማሹን በወ/ሮ ሙሉ ሞሳ ተይዞ እንደሚገኝ፣ይህንኑ ቤትና ቦታ የወ/ሮ ሙሉ ሞሳ ባለቤት አቶ ዘውዱ አግማስ እንደስር ከሳሾችና ሌሎች የሟች ወራሾች ሁሉ የሟቹ ልጅ በመሆናቸው በቤቱ ላይ ወርሃዊ ኪራይ ክፍያ


እየከፈሉ ይዘው ቆይተው አቶ ዘውዱ አግማስ በመስከረም ወር 2001 ዓ/ም ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ በኋላ ወ/ሮ ሙሉ ሞሳ ቤቱን ያለ ክፍያ ይዘው የተቀመጡ መሆኑን ዘርዝረው ከጥቅምት ወር 2001 ዓ/ም ጀምሮ የቤቱን ጥቅም በተመሳሳይ ቤት በአካባቢው ያሉ ቤቶች  በሚያስገኙት ዋጋ መጠን እንዲከፍሉና ቤቱንም እንዲለቁ ይወሰንልን በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

 

የአሁኑ አመልካቾች ሞግዚት ለክሱ በሰጡት መከላከያ መልስም ጉዳዩ ቀድሞ በፍርድ ማለቁንና ጥያቄው ውርስ ሳይጣራ የቀረበ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም የሚሉ ነጥቦችን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት አንስተው በፍሬ ነገሩ ደግሞ አውራሹ ሳይሞቱ የነበረው ሙሉ ቤትና ቦታ በአንድ በኩል ከሞቱ በኋላ ለሁለት የተከፈለው ቤትና ቦታ ተይዞ ሁለቱ ቤትና ቦታዎች በገንዘብ እያንዳንዳቸው ያለመገመታቸውን፣ የቤት ኪራይ ውል በጽሑፍ ሳይኖር የክፍያ ጥያቄ መቅረቡ ያላግባብ መሆኑን፣ ቤቱን የያዙትም ባለቤታቸው አቶ ዘውዱ አግማስ የአውራሹ ልጅና ወራሽ በመሆናቸውና የአሁኑ አመልካቾችን የወለዱላቸው በመሆኑ አመልካቾች በተተኪ ወራሽነት በቤቱ ላይ መብት ያላቸው መሆኑን፣ ስለቤቱ ከአውራሹ ሞት በኋላ የተሰጡ የምስክር ወረቀቶችን በተመለከተ መጋቢት 24 ቀን 2000 ዓ/ም የተሰጠውን የሚስማሙበት ሆኖ የካቲት 15 ቀን 2001 ዓ/ም የተሰሩትን ግን ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ የተሰሩ፣ ነገር ግን የእርሱ ስም የተጠቀሰባቸው የተተኪዎችን ጥቅምና መብት የማያስከብሩ በመሆናቸው ተቀባይነት ሊሰጣቸው እንደማይገባና ሊሰረዙ የሚገባቸው መሆኑን፣ የውርሱ ጉዳይ ስለቤቱ ብቻ ሳይሆን ስለሌሎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችም ጭምር በመሆኑ በአጣሪ ሊጣራ እንደሚገባ፣ የእርቁ ጉዳይን ለማረጋገጥ የቀረበው ሰነድም ባለቤታቸው ተስማሚ ያልሆኑበት ሰነድ በመሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ፣ ክሱ የቀረበበት ቤት ሟች ባለቤታቸው ከአባታቸው ከአቶ አግማስ አምባው ለጎጆ መውጫ እንዲሆናቸው የተሠጣቸው መሆኑን፣ የውርስ ሃብት ክፍፍል ይደረግ ከተባለውም ተከሳሽ እና ሌሎች ወራሾች እየተጠቀሙበት ያለው የአቶ አግማስ አምባው ንብረቶች በአጣሪ ተጣርተው ሊካፈሉ ይገባል እንጂ ተከሳሽ የያዙትን ቤት ብቻ የሚያካፍሉበት አግባብ ያለመኖሩን ዘርዝረውና በውርሱ ሊካተቱ ይገባል ያሏቸውን የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን አይነታቸውና ግምታቸውን ጠቅሰው ክፍፍሉ ሊደረግ ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የወረዳው ፍ/ቤትም ጉዳዩን መርምሮ በተከሳሽ የቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎችን ውድቅ አድርጎ ከአለፈ በኋላ ፍሬ ነገሩ  ላይም ግራ ቀኙን በቃል ከአከራከረና ተገቢ ነው ባለው መንገድ ሁሉ ከአጣራ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ክርክር የተነሳበትን ቤት ተከሳሽ ይልቀቁ፣ ከአስሩ የሟች አቶ አግማስ ልጆች ጋር የተከሳሽ ልጆችበአባታቸው አቶ ዘውዱ እግር ተተክተው ተጠቃሚ ይሁኑ፣ ከጥቅምት 01 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር 2002 ዓ/ም ድረስ ያለውንተከሳሽ ቤቱን ይዘው የተጠቀሙ በመሆኑበወር አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ቤቱ እንደሚከራይ በአካባቢው ግምት መነሻ ተረጋግጧል ብሎ ይህንኑ ስሌት መሰረት አድርጎ እስከ ታህሳስ ወር 2002 ዓ/ም ድረስ ያለውን የኪራይ ገንዘብ ብር 21,000.00 አንድ አስረኛ ድርሻ ትተው ተከሳሽ ለከሳሾች እንዲከፍሉ፣ጣልቃ ገብም አንድ አስረኛ ከቤቱም ሆነ ከኪራዩ ገንዘብ እንዲያገኙ፣ የዳኝነት ገንዘቡን በተመለከተም ተከሳሽ ለከሳሾች  እንዲተኩ ሲል ወስኗል፡፡

የአሁኑ አመልካቾችም በተሰጠው ውሣኔ ቅር በመሰኘት የይግባኝ አቤቱታቸውን ለደቡብ ጎንደር መስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ቤት ያልተከፋፈለ የሟች አግማስ አምባው ንብረት በመሆኑ ወራሾች ባሉበት ሁኔታ ለመካፈል ካልተስማሙ በጨረታ ተሸጦ አንድ አስረኛ ድርሻ ለአሁኑ አመልካቾች ሁኖ ቀሪውን ተጠሪዎች በድርሻቸው እንዲከፋፈሉ፣ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስን


በተመለከተም ተጠሪዎች አመልካች የዳኝነት አልከፈሉም ከማለት በስተቀር ሌላ ክርክር አላቀረቡም፣ በይግባኝ ሰሚው ችሎት ያቀረቡት የይርጋ ክርክርም ተቀባይነት የሌለው ነው በሚል ምክንያት አርባ ሺህ የተገመተ አይነታቸው ሃያ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ተጠሪዎች ለአመልካቾች በድርሻቸው እንዲከፍሉ በማለት በአብላጫ ድምጽ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪዎች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የአመልካቾች የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ በአመልካች መከላከያ መልስ ጋር በአማራጭ መልስነት የቀረበና ዳኝነት የተከፈለበት ስለመሆኑ የማያሳይ እና ክሱ ስርዓቱን ጠብቆ ያልቀረበ ሁኖ እያለ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሳሽ ከሳሽነት ክስን ራሱ ከይግባኝ ክርክር ጋር ተቀብሎ ተጠሪዎች የሚንቀሳቀሱ ንብረቶቹን ግምት ለአመልካቾች ድርሻቸውን እንዲከፍል በማለት የሰጠው ውሳኔ ስነ ስርዓታዊ አይደለም፣ የቤት ኪራዩንም አመልካች የሚከፍሉበት የሕግ አግባብ የለም በሚል ምክንያት በዚህ ረገድ የተሰጡትን የውሳኔ ክፍሎች የሻራቸው ሲሆን በአመልካቾች ሞግዚት ተያዘ የተባለውን ቤት በተመለከተ ግን እንዲለቀቅና ለወራሽ ልጆች እንዲያስረክቡና አከፋፈሉን በተመለከተም በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1272 እና ተከታዩቹ መሰረት የሚፈጸም ሁኖ በበታች ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው በማለት አጽንቶታል፡፡የዳኝነት ገንዘቡን በተመለከተ የተሰጠውን የውሳኔ ክፍልንም አጽንቶታል፡፡ የአሁኑ አመልካቾች ሞግዚት በዚህ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በሰጠው የውሳኔ ክፍል ቅር በመሰኘት የሠበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡-- አከራካሪውን ቤት እንዲለቁ መወሰኑ ከህፃናት መብትና ጥቅም አንፃር ተገቢ ያለመሆኑን፣ በጉዳዩ ላይ ያነሱት ይርጋ መታለፉም ያላግባብ መሆኑን፣ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስም ስርዓቱን ጠብቆ ስልጣን ላለው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበ ሁኖ እያለ ውድቅ መደረጉ ያላግባብ መሆኑን፣ ባልተከፋፈለ የጋራ ሃብት ላይ በቀረበ ክስ ረቺና ተረቺ በሌለበት ሁኔታ የዳኝነት ገንዘብ እንዲከፍሉ መደረጉም ከህግ ውጪ መሆኑን ዘርዝረው በጉዳዩ ላይ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተሰጠው ውሳኔ ሊለወጥ ይገባል በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ስርዓቱን ጠብቆ የቀረበ አይደለም ተብሎ ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ዳኝነት ሳይከፈል ክሱ ቀርቦ ከታየ በኋላ ፍርድ ቤቱ ሊከተለው ስለሚገባው ስርዓት ይህ ችሎት ከሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አንፃር ለመመርመር ተብሎ ለዚህ ችሎት የቀረበ ሲሆን ከ9ኛ ተጠሪ በስተቀር ሌሎች ተጠሪዎች ቀርበውም ግራ ቀኙ  በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሣኔና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሯል፡፡ በዚህም መሰረት በጭብጥነት የተያዘው ጉዳይ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ውድቅ የመደረጉን አግባብነት የሚመለከት በመሆኑ የአመልካቾች ሞግዚት ቤቱን እንዲለቁ፣ በቤቱ ላይ ያነሱት የይርጋ መቃወሚያ፣ እንዲሁም የዳኝነት ገንዘብ እንዲከፍሉ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ያቀረቡት የሰበር ቅሬታ በዚህ ችሎት እንዲታይ ያልተደረገ ከመሆኑም በላይ አመልካቾች በወረዳው ፍርድ ቤት ያቀረቡት የይርጋ መቃወሚያ ታልፎ ቤቱን እንዲለቁ፣ የዳኝነት ገንዘቡንም እንዲከፍሉ ተወስኖባቸው ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት የይግባኝ ክርክርም በዚህ ረገድ በወረዳው ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ፀንቶባቸው ወደ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት  የይግባኝ  ማመልከቻ  ያቀረቡት  የአሁኑ  ተጠሪዎች  መሆናቸውን  የክርክሩ   ሂደት


ስለሚያሳይ እና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት ደግሞ አመልካች በዚህ ረገድ መስቀለኛ ይግባኝ ወይም የመቃወሚያ ክርክር ያቀረቡ ስለመሆኑ ውሳኔው  ስለማያሳይ በዚህ ችሎት በእነዚህ ነጥቦች ላይ የሚያቀርቧቸው ክርክሮች ተቀባይነት የሚያገኙበት የስነ ስርዓት ሕግ አግባብ የለም፡፡በመሆኑም በዚህ ረገድ የቀረቡትን የአመልካቾችን የክርክር ነጥቦች ስርዓቱን ጠብቀው ያልቀረቡ በመሆኑ አልፈናቸዋል፡፡

ስለተከሳሽ ከሳሽነት የቀረበውን ቅሬታ በተመለከተ ከክርክር ሂደቱ መገንዘብ እንደሚቻለው ተከሳሽ የነበሩት የአሁኑ አመልካቾች ሞግዚት ከፍ ሲል እንደተገለፀው ዳኝነት ጠይቀው እየተከራከሩ ያለው አከራካሪ ከሆነው ቤት ጭምር ሌሎች የሚንቀሳቀሱ የውርስ ንብረቶች መኖራቸውን ገልጸውና የንብረቶችን አይነት፣ብዛትና ግምታቸውን ዘርዝረው እነዚህ ንብረቶች የውርሱ አካል ተደርገው ክፍፍሉ ሊፈፀም ይገባል በማለት ሲሆን ይህን የዳኝነት ጥያቄ በወረዳው ፍርድ ቤት ያቀረቡት ግን ተጠሪዎች ባቀረቡባቸው ክስ የመከላከያ መልስ ሲያቀርቡ በአማራጭ መልስነት ስለመሆኑ የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን የመራበት ሁኔታም ጉዳዩ በይግባኝ ቀርቦለት ግራ ቀኙን በስር የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ላይ ስለመሆኑ የውሳኔው ግልባጭ ያስገነዝባል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አመልካቾች የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ አቀራረብ ስርዓት በሕጉ የተቀመጠውን አግባብ ያለመከተሉን በአቢይ ምክንያትነት ጠቅሶ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔውን መሻሩን ከውሳኔው ተገንዝበናል፡፡አመልካቾች በዚህ የሰበር ክርክር ደረጃ አጥብቀው የሚከራከሩት ደግሞ በወረዳው ፍርድ ቤት በነበረው ክርክር የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ስርዓቱን ጠብቆ የቀረበ ነበር ሳይሉ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክርክሩ እንዲቀጥል ተደርጎ የንብረቱ ግምትም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስረ ነገር ስልጣን እንዲኖረው የሚያደርግ በመሆኑ ክርክሩ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከይግባኝ ክርክር ጋር እንዲታይ ተደርጓል በሚል ነው፡፡ ሆኖም አመልካቾች በስር ፍ/ቤት ተከሳሾች እንደመሆናቸውና እነሱም በበኩላቸው ከተጠሪዎች የሚጠይቁት መብት ካላቸው በህጉ አግባብና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 234/1/ /ረ/ መሰረት ከመከላከያ መልሳቸው ጋር የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 215/2/ ስር እንደተመለከተው በመፈፀም በተከሳሽ ከሳሽነት ክስ የተጠቀሱት የሚንቀሳቀሱት ንብረቶች ግምት እንዲከፈላቸው በሚል የቀረበ የዳኝነት ጥያቄ የለም፡፡ በዚህ አግባብ ተሟልቶ የቀረበ የዳኝነት ጥያቄ በሌለበት ደግሞ ዳኝነቱ ሊሰጥ አይችልም፡፡ አመልካቾች በተከሳሽነታቸው በተሰጣባቸው ውሳኔ ይግባኝ ብለው በሄዱት ክርክር ላይ በስር ፍርድ ቤት በሕጉ አግባብ ያልቀረበ የተካሳሽ ከሳሽነት ክስ እንዲቀርብ ተደርጎ ከይግባኙ ጋር የሚወሰንበት አግባብ የለም፡፡ እንዲህ አይነት የክርክር አመራር የተከራካሪ ወገኖችን የመሰማት መብትም የሚጎዳ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 17352 የሠጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሚመለከተው ተገቢው ዳኝነት ክፍያ ሳይፈፀም በፍርድ ቤት በቀጠለ ክርክር ስለሚፈፀም ስርዓት እንጂ ከመነሻው የክስ አቀራረብ ስርዓትን ሳይከተል የቀጠለውን ክርክር ሁኖ የሚመለከት አይደለም፡፡

ሲጠቃለል ከፍ ሲል በተገለፁት ምክንያቶች የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አመልካቾች የዳኝነት አገልግሎት ፈፅመው የተከሳሽ ከሳሽ ዳኝነቱንም በስርዓቱ ባላቀረቡበት ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን ግምት በተመለከተ ተጠሪዎች የአመልካቾችን ድርሻ እንዲከፍሉ ሊገደዱ አይገባም፣ አመልካቾች በሕጉ አግባብ ክስ ሊያቀርቡ ይገባል በማለት የሰጠው ውሳኔ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመፅናቱ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት አላገኘንም፡፡ በመሆኑም ተከታዩን ውሣኔ ሰጥተናል፡፡


 

 ው ሣ ኔ

1. የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መ/ቁ 31215 ሰኔ 05 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት መ/ቁ 33634 ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ/ም በዋለው ችሎት በትእዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348/1/ መሰረት ፀንቷል፡፡

2. የአመልካቾች የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ስርዓቱን ጠብቆ የቀረበ አይደለም ተብሎ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በተሰጠውና በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በፀናው የውሳኔ ክፍል የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል፡፡ በሌሎች ነጥቦች ላይ የተሰጠው ውሳኔም አልተነካም፡፡

3.  ለዚህ የሰበር ክርክር ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

 

 ት ዕ ዛዝ

 

በዚህ መዝገብ ህዳር 04 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል፡፡ ለሚመለከታቸው አካላት ይጻፍ፡፡

 

መዝገቡ ተዘግቷል፣ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የ/ማ                                   የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡