civil procedure
appointment of auditor
compromise agreement
finality of compromise agreement
ተከራካሪ ወገኖች ለፍ/ቤት የሒሳብ አጣሪ ይሾምልን የሚል አቤቱታ ሲያቀርቡ በሒሳብ አጣሪዎች ሪፖርት አለመስማማት ቢኖር እንኳ ጉዳዩ የንግድ ህጉንና የፍትሐብሔር ሥነ-ስርዓቱን መሠረት በማድረግ ውሣኔ በዛው በኩል እንደሚሠጥ በግልጽ ከተስማሙ ይህ ግልጽ ስምምነት ባለበት ሁኔታ የሒሳብ አጣሪዎች የስራ ክንውን ግድፈት አለበት በማለት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የሚያቀርቡበት ህጋዊ ምክንያት የሌለ ስለመሆኑ፣
የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 277(1)(2) ፣የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 3312
የሰ/መ/ቁጥር 93239
ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም
ዳኞች፡- አልማው ወሌ
ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኸሊት ይመሰል
አመልካቾች ፡- የአቶ አበበ ክብረት ሚስትና ወራሾች እነ ወ/ሮ ብርሃኔ መኰንን 10 ሰዎች ጠበቃ አቶ አምሳሉ ባየ ቀረቡ
ተጠሪ፡- አቶ ነጋ ቦንገር ዶ/ር ሸዋረጋ አስራት ቀረቡ
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው ክርክር የተጀመረው በሥር የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አመልካቾች ባቀረቡት አቤቱታ በኮ/መ/ቁ 06187 በ 13/07/2005ዓ.ም የተሰጠው ትዕዛዝ ነው፡፡አመልካቾች እና ተጠሪ የነበራቸውን ክርክር በስምምነት ለመጨረስ ያቀረቡት አቤቱታ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.277 መሠረት በፍ/ቤት የተመዘገበ መሆኑ መዝገቡ መዘጋቱን በሥር ፍ/ቤት መዝገብ የተገለጸ ሲሆን በስምምነቱ መሠረት የተሾሙት የሂሳብ አጣሪዎች ሪፖርት ፍ/ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅ በአሁኑ አመልካቾች ግንቦት 09 ቀን 2004ዓ.ም አቤቱታ ቀርቧል፡፡
የሥር ፍርድ ቤቱም የግራቀኙ የስምምነት ይዘት አጠር ባለመልኩ ከጠቀሰ በኃላ የግራ ቀኙ ጥያቄ ወይም ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ ሂሣብ አጣሪ ይሾምልን የሚል እንደነበር፤የሂሳብ አጣሪዎች ከተመረጡ በኃላ ሂሳቡ በምን መንገድ ተሠራ ወደ ሚለው ፍሬ ጉዳይ በመግባት የሂሣብ ሪፖርቱ የሚመረመርበት ህጋዊ ምክንያት አለመኖሩን ፤የፍ/ቤቱ ሥልጣን የሂሳብ አጣሪ ኮመሾም የዘለለ አለመሆኑና ሥልጣኑ አጣሪ ከመሾም የዘለለ ነው የሚባልቢሆን እንኳ ግራቀኙ በስምምነታቸው መሠረት የሂሣብ አጣሪው ውሳኔ እንደሚቀበሉ በስምምነታቸው ተራ ቁጥር 4(3)መመልከቱን ፣የሂሳብ አጣሪ በፍ/ቤት ትዕዛዝ መነሻነት ከሂሳብ አጣሪነት ሊነሳ እንደሚችል
፤ይሁንና በተያዘው ጉዳይ ሂሣብ ከተጣራ በኃላ የሂሣብ አጣሪዎች ሪፖርት ይፅደቅ ወይም አይፅደቅ ወደ ሚል ክርክር ውስጥ መግባት ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚሰጡበት አግባብ አለመኖሩን በመጥቀስ አቤቱታውን ውድቅ በማድረግ በትዕዛዝ ክፍሉ ግራቀኙ በስምምነቱ መሠረት ያልፈፀመ ወገን ካለ የአፈፃፀም ጥያቄ ማቅረብ እንደሚቻል አስፍሯል፡፡
አመልካች የሥር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመቃወም ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበዋል ፡፡ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱም ግራቀኙ ያደረጉት ስምምነት ህግና ሞራል የማይቃረን
መሆኑ ተረጋግጦ የተመዘገበ እና በይግባኝ ያልተሻረ ነው፡፡ የሥር ፍ/ቤት የአመልካቾች ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ በአግባቡ ነው በማለት በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 337 መሠረት ይግባኙን ሰርዞታል፡፡
አመልካቾች በሥር የመጀመሪያ እና ከፍተኛ ፍ/ቤቶች ተፈጽሟል ያሉትን ስሕተት በመዘርዘር የሰበር አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ የሰበር አቤቱታቸው መሠረታዊ ይዘት በሂሣብ አጣሪዎች ተፈጽሟል ያሏቸውን ግድፈቶች ከዘረዘሩ በኃላ በግራቀኙ የተደረገው እና በፍ/ቤት የተመዘገበው ስምምነት ይዘት የሂሳብ አጣሪዎችን ምርጫ ብቻ እንደሚመለከት የሁለቱም ወገኖች መብትም ሆነ ግዴታ የሚመለከት ጉዳይ በስምምነቱ ሰነድ አለመካተቱን ፣የሂሳብ አጣሪዎች የሚያቀርቡት ሪፖርትም የስምምነቱ አካል አለመሆኑን፤የሥር ፍ/ቤቶች ጉዳዩ አስቀድሞ በስምምነት አልቋል ሲሉ የደረሱበት ድምዳሜ ትክክል ባለመሆኑ እንዲሻር እና በሂሣብ አጣሪዎች የቀረበው ሪፖርት ፍ/ቤቱ አሻሽሎ እንዲያፀድቀው ጠይቋል፡፡ተጠሪ በበኩላቸው መልስ ሰጥተዋል፡፡ ዋና ፍሬ ነገሩ በአመልካቾች የቀረበው አቤቱታ የግራቀኙ ስምምነት አለማገናዘቡን ፤የሂሳብ አጣሪዎችም ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ ግዴታቸውን የተወጡ ስለመሆናቸው የግራቀኙ ስምምነት በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 3312 መሠረት ሊነካ የማይችል እና ይግባኝ አልባ ውሳኔ መሆኑ ተረጋግጦ የሥር ፍ/ቤቶች ውሳኔ በውሳኔ እንዲፀና አመልክቷል፡፡ በአመልካቾች የቀረበው የመልስ መልስ አቤቱታቸውን የሚያጠናክር ነው፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራቀኙ ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል ፡፡
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ግራቀኙ ጉዳያቸው በግልግል ስምምነት ለመጨረስ ይችሉ ዘንድ ሂሳብ አጣሪዎች በመሾም ስልጣን እና ተግባራቸውን በመወሰን ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጋቸው ነው። በሥር ፍ/ቤት ግራቀኙ ያቀረቡትን የእርቅ ስምምነት ህግና ሞራልን የማይቃወም በመሆኑ ተቀብሎ ማፅደቁ ከመዝገቡ ጋር የተያያዘው ማስረጃ ያሳያል በዚህ ጉዳይ ለክርክሩ መሠረት የሆነው በግራቀኙ የተደረገው የግልግል ስምምነት የሂሣብ አጣሪዎች ሪፖርት በተመለከተ የሚነሱ ክርክሮች በፍርድ ቤት እየታዩ መፅደቅ አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚል ነው ፡፡አመልካቾች አጥብቀው የሚከራከሩት በሂሳብ አጣሪዎች ተፈጸመ የተባለው ግድፈት በፍርድ ቤት ስሕተቱ እንዲታረም ማድረግ እንደሚችሉ ሲገለጽ ተጠሪ በበኩላቸው የሂሣብ አጣሪዎች ውሳኔ የመጨረሻ እና ይግባኝ የማይጠየቅበት መሆኑን ነው፡፡
የግራቀኙ መሠረታዊ የልዩነት ነጥብ ለክርክሩ መሠረት የሆነውን የሂሣብ አጣሪዎች ሪፖርት ተገቢነት በመደበኛ ፍርድ ቤት ሊታይ የሚችል ነው ወይስ አይደለም የሚል ነው፡፡ ይህንን መሠረታዊ የክርክር ነጥብ ይዘት በአግባቡ ለመረዳት በግራቀኙ የተደረገው ስምምነት ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያለው የስምምነቱ ክፍል ማየቱ ተገቢ ይሆናል ፡፡ ግራ ቀኙ ሰኔ 17 ቀን 2000 ዓ.ም ተስማምተው የተፈራረሙት ሰነድ እንደሚያመለክተው በጋራ ማህበር ያቋቋሙት የናዝሬት የምግብ ዘይትና ሳሙና ኢንዱስትሪና የእህል ንግድ ማህበር ስለፈረሰ ሂሳቡን በአጣሪዎች ለማጣራት መስማማታቸውን ፤የሂሳብ አጣሪዎች በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት ከ1990 ዓ.ም ወዲህ ያለውን ሂሣብ አጣርተው ዕዳ ጠያቂዎች የሚያቀርቡት ማስረጃ መርምረው ዕዳውን በመቀበል ወይም ስላለመቀበል ውሳኔ እየሰጡ በመጨረሻም የማህበሩ ንብረት በመሸጥ እዳውን ከከፈሉ በኃላ ቀሪው ለተገልጋይ ወገኖች እንደ አክስዮን መጠን እንዲያከፋፍሉ መስማማታቸው፤ሂሣብ አጣሪዎች የሂሳብ መጣራቱን በሚያካሂዱበት ወቅት ከተገልጋይ ወገኖች
የሚቀርቡ ሂሳቦች ቢኖሩ እንደሚቀበሉ፤ጉዳዩም በስምምነት ለመጨረስ ጥረት እንደሚያደርጉ፤ ጥረቱ ፍሬያማ ካልሆነ ግን በንግድ እና የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጎች መሠረት የራሳቸውን ውሳኔ በማድረግ ሥራቸውን በትክክል አከናውነው ከፍጻሜ እንደሚደርስ መስማማታቸውን በስምምነቱ ተራ ቁጥር 4.2 እና 4.3 በግልጽ ተመልክቷል፡፡
ግራ ቀኙ ካደረጉት የግልግል ስምምነት መገንዘብ እንደተቻለው የሂሳብ አጣሪዎች ጉዳዩን በስምምነት ለመጨረስ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ይሁንና በስምምነት መቋጨት ካልተቻለ ግን የበኩላቸውን ውሳኔ እንዲሰጡ ነው፡፡አመልካቾች የሂሳብ አጣሪዎች የሥራ ክንውን ግድፈት አለበት በማለት ይከራከራሉ፡፡ በአንፃሩ ተጠሪ የሂሳብ አጣሪዎች ሪፖርት ግራቀኙን የሚያስገድድ ይግባኝ የሌለበት ውሳኔ መሆኑን ይገልፃሉ ፡፡ የሥር ፍርድ ቤት የግራቀኙን ስምምነት አፅድቆታል ፡፡ በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንደሰፈረው የአመልካቾች ጥያቄ በፍ/ቤት ትዕዛዝ የተሾሙ የሂሳብ አጣሪዎች ከኃላፊነት ይነሱልን ጥያቄ አይደለም ፡፡ የሂሳብ አጣሪዎች ተገቢ ነው ያሉትን ተግባር አከናውነው ለግራቀኙ አቅርበዋል ፡፡ ግራቀኙ ከመጀመሪያውኑ ጉዳዩ ከፍርድ ቤት ውጭ በስምምነት ለመጨረስ ተስማምተዋል ፡፡ በግራቀኙ ስምምነት መሠረትም የሂሳብ አጣሪዎች ሥራቸውን አከናውነው ውጤቱ ለሚመለከታቸው ባለ ጉዳዬች ማቅረባቸው በሥር ፍርድ ቤት መዝገብ ተመልክቷል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ስምምነት ከመዘገበ በኃላ መዝገቡን ዘግቶታል ስምምነቱ ህግና ሞራልን የማይቃረን መሆኑ በፍ/ቤት ታምኖበት ከተመዘገበ በኃላ ያለው ሕጋዊ ውጤት እንደማንኛውም ፍርድ እንዲፈጸም አቤቱታ ሊቀርብበት የሚችል መሆኑን ከፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ.277(1)እና(2) እንዲሁም ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 3312 ይዘትና የሕጉ መንፈስ የምንገነዘበው ነው፡፡ አመልካቾች በሥር ፍርድ ቤት ክርክራቸው የሂሣብ አጣሪዎች የግራ ቀኙ ስምምነት የጣሱ ስለመሆናቸው ወይም ከስምምነቱ ውጭ መሠረታዊ እና የሥነ ሥርዓት ሕጎች በሚቃወም አግባብ ስለመሥራታቸው የቀረበ ነገር የለም ፡፡ በአንፃሩ የሂሣብ አጣሪዎች ጉዳዩን በስምምነት መቋጨት ካልተቻለ የንግድ ህግና የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ህጐች ተፈፃሚ በማድረግ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጡ በግራቀኙ ስምምነት አንቀፅ 4.3 ተመልክቷል ፡፡ ይህ ግልፅ ስምምነት ባለበት ሁኔታ የሂሳብ አጣሪዎች የሥራ ክንውን ግድፈት አለበት በማለት ጉዳዩን በድጋሚ ወደ ፍርድ ቤት የሚያቀርቡበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም፡፡ አመልካቾች የሂሳብ አጣሪዎችን የመጨረሻ ውሳኔ መሠረት በማድረግ ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ ይግባኝ ከሚጠይቁ በስተቀር የግራቀኙ ክርክር በሥር ፍርድ ቤት በተገለጸበት ሁኔታ የሂሳብ አጣሪዎች የሥራ ክንውን ሪፖርት በፍርድ ቤት እንዲሻሻል ያቀረቡት አቤቱታ ከግራቀኙ ስምምነት ውጭ ነው፡፡ ስለሆነም አመልካቾች የሂሳብ አጣሪዎች ሪፖርት ተገቢነት በፍርድ ቤት ይታይልን በማለት ያቀረቡት ጥያቄ በሥር ፍርድ ቤቶች ውድቅ መደረጉ በአግባቡ ነው ብለናል
፡፡ አመልካቾች ያቀረቡት አቤቱታ የግራቀኙ አስገዳጅ ስምምነት ይዘትና መንፈስ ያልተከተለ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት የስር ፍ/ቤቶች የአመልካቾች የሂሳብ አጣሪዎች ሪፖርት ተገቢነት ተመርምሮ ይሻሻልልን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው መሠረታዊ የህግ ስሕተት ያለበት ነው ለማለት አልተቻለም ፡፡ በዚህ ምክንያት ተከታዩን ወስነናል ፡፡
ው ሳ ኔ
1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በኮ.መ.ቁ.06187 በ 13/07/2005 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ.መ.ቁ 137138 በ 5/10/2005 ዓ.ም የሰጡት ትዕዛዝ ጸንቷል፡፡
2. አመልካቾች የሂሳብ አጣሪዎች ሪፖርት ተገቢነት በፍ/ቤት ተመርምሮ ይሻሻልልን በማለት ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ብለናል ፡፡ ይሁንና አመልካቾች በስምምነቱ መሠረት ያልፈፀመ ወገን ካለ የአፈፃፀም ጥያቄ የማቅረብ መብት የተጠበቀ ነው ፡፡
3. የዚህ ፍ/ቤት ወጭና ኪሳራ ግራቀኙ የየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ውሳኔ ያገኘ በመሆኑ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡
ት/ጌ የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡