100712 criminal procedure/ RTD procedure/ right to defense

የRTD ችሎት መከላከያ የማቅረብ መብትን የማያስነፍግ ስለመሆኑ

 

 

ዳኞች፡-አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

 

አመልካች፡- አቶ ሽብሩ ጌቱ ሴንጫ - ጠበቃ ወይሸት ከበደ ቀረቡ፡፡ ተጠሪ፡- የፌዴራል አቃቤ ሕግ - የቀረበ የለም፡፡


የሰ/መ/ቁ 100712

መጋቢት 28 ቀን 2007 ዓ/ም


መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በመሰረተው ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡- በ1996 ዓ/ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 669(2)ን በመተላለፍ የማይገባውን ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በ18/02/06 ዓ/ም በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ሲሆን በኮ/ቀ/ክ/ከ/ወረዳ 02 ልዩ ቦታው ካራቆሬ ደጋማን የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት ውስጥ በስራ አስኪያጅነት ተቀጥሮ እየሰራ ባለበት የግል ተበዳይ አማረ አብርሃም የድርጅቱ ባለቤት የሆኑትን ንብረት አንድ መቶ ሃምሳ ከረጢት የጫማ ጥሬ እቃ ፕላስቲክ የአንድ ከረጢት ግምት ብር 1100.00 (አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር) የጠቅላላው ግምት ብር 165,000.00 (አንድ መቶ ስልሳ አምስት ብር) የሚያወጣውን ወስዶ ለስር 2ኛ ተከሳሽ አቶ ደረጀ ፍቃዱ የሸጠና የተያዘ በመሆኑ ከባድ የስርቆት ወንጀል ፈጽሟል የሚል ነው፡፡ አመልካችም ፍርድ ቤት ቀርቦ የአቃቤ ሕግ የክስ ቻርጅ ተነቦለት እንዲረዳው ከተደረገ በሁዋላ እምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ የወንጀል ድርጊቱን ያለመፈፀሙን በመግለጹ አቃቤ ሕግ አሉኝ የሚላቸውን ማስረጃዎች  አቅርቦ አሰምቷል፡፡

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ አመልካች ድርጊቱን ስለመፈፀሙ በአቃቤ ማስረጃዎች የተነገረበት መሆኑን ተገንዝቦ የአመልካችን የመከላከያ ማስረጃ ማሰማት መብቱን በአመልካች ፍላጎት ማለፉን ጠቅሶ አመልካችን በአቃቤ ሕግ በኩል ተጠቅሶ በቀረበበት አንቀጽ ስር ጥፋተኛ አድርጎ ቅጣቱንም ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ጋር አገናዝቦ ማየቱን ገልጾ በስምንት አመት ከአምስት ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማቱ ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በሁዋላ የስር ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ የጸና ሲሆን የቅጣት ውሳኔው ግን በማክበጃ እና በማቅለያ ምክንያቶች አያያዝ ላይ የስር ፍርድ ቤት ስህተት  መፈፀሙ የተረጋገጠበት ነው በሚል ምክንያት ስህተቶቹን ለይቶና ማረሙን ገልፆ የስር ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ መጠን ዝቅ በማድረግ አመልካች በስድስት አመት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

የአሁኑ የሠበር አቤቱታው የቀረበው ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ሲሆን የአቤቱታው መሰረታዊ  ይዘትም፡-  የስር  ፍርድ  ቤት  የአመልካችን  መከላከያ  ማስረጃ  ሳይሰማ ያለፈው


አመልካች የመከላከያ ማስረጃ አለኝ እያልኩ ነው፣የወንጀል ድርጊቱ መፈፀሙን አቃቤ ሕግ አላስረዳም፣ ተፈፀመ የተባለው የወንጀል ድርጊትና የተጠቀሰው ድንጋጌ አብረው የማይሄዱና የቅጣት ውሳኔ አሰጣጥም ተገቢነት የሌለው ነው የሚሉ ምክንያቶችን የያዘ ነው፡፡አቤቱታው ተመርምሮም የአመልካች የመከላከያ ማስረጃ ማሰማት መብት የታለፈው በአግባቡ መሆን ያለመሆኑን ለማጣራት ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪም ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም የስር ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ለሰበር ችሎት ያስቀርባል ተብሎ ሲታዘዝ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

አመልካች ጥፋተኛ የተባለው ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ማስረጃዎች የመከላከያ ማስረጃ የለኝም በማለት በቃልና በፅሑፍ ለስር ፍርድ ቤት አረጋግጧል ተብሎ ስለመሆኑ ከስር ፍርድ ቤት የውሳኔ ግልባጭ ተገንዝበናል፡፡ አሁን በዚህ የሰበር ክርክር ደረጃ ደግሞ አመልካች ይህ የሥር ፍርድ ቤት አገለላጽ ከፍላጎታቸው ውጪ መመዝገቡንና የመከላከያ ማስረጃ ላሰማ ጥያቄ አቅርበው የነበረ መሆኑን ገልጸው ተከራክረዋል፡፡

በመሰረቱ የተከሰሱ ሰዎች በሕግ ከተጠበቁላቸው መብቶች አንዱ የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸውን ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት ስለመሆኑ በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 20(4) የተደነገገ ሲሆን ይህ መብት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(4) ድንጋጌ አግባብ የአገሪቱ የሕግ አካል በሆኑት የአለም አቀፍ ስምምቶችም ጥበቃ ያገኘ ስለመሆኑ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን 14(3(ለ)) ድንጋጌን በመመልከት የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎች ስር የተመለከተው የተከሳሽ መብት የሚያስገነዝበው አንድ ተከሳሽ ተገቢ ባልሆነ ማስረጃ ጥፋተኛ  እንዳይባልና በከሳሹ ወገን ማስረጃ ቀርቦ ከሆነም በበኩሉ ምንም ጥፋት ያልፈፀመና ንፁህ መሆኑን የማስረዳት ሁኔታዎችን ማመቻቸት የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም ለቀረበበት ክስ መከላከያ ለማዘጋጀት አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮችንና በቂ ጊዜ ማግኘት እንደሚገባው ሕጉ ያስገነዝባል፡፡ ተከሳሹ ይህንኑ በሕገ መንግስቱ ጥበቃ ያገኘውን የመከላከል መብት በአግባቡ እንዲጠቀም ማድረግ የፍርድ ቤት ኃላፊነት መሆኑንም ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 13(1) እና (2) ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ የተከሳሽ ክስን የመከላከል መብት ሊታለፍ የሚገባው ተከሳሹ መብቱን የማይጠቀምበት መሆኑን በግልፅ ለፍርድ ቤቱ ሲያረጋግጥለት ብቻ መሆኑን ከድንጋጌዎች መንፈስ የምንገነዘበው ነው፡፡ ተከሳሹ መብቱን ስለመተው ባልተረጋገጠበት አግባብ ግን የተከሳሽን የመከላከል መብት ተከሳሹ ትቷል የሚል አገላለፅ በፍርድ ሐተታው ላይ በማስፈር ብቻ ዳኝነት መስጠት ተገቢነት የሌለው አካሄድ ነው፡፡

 

የጉዳዮችንመራዘምለማስቀረትየተቀየሰውየተፋጠነየወንጀልአሰጣጥ (RTD) መሰረታዊ ኣላምምበማስረጃደረጃውስብስብነትየሌላቸውንጉዳዮችበቀላሉለመወሰንአዲስአሠራር ለመዘርጋት ማስቻል ከሚሆን በስተቀር በሕገ መንግስቱና በሌሎች ተፈጻሚነት ባላቸው ሕጎች የተጠበቁትን የተከሳሽን መብቶች በሚጎዳ አኳኃን ለመተግበር አለመሆኑ ይታወቃል፡፡በመሆኑም በሕጉ የተጠበቁት መብቶችና የዳኝነት አካሄዶች በሕጉ አግባብ ተተግብረው ዳኝነት ከሚሰጥ በስተቀር አንድ ጉዳይ የተፋጠነየወንጀልአሰጣጥን (RTD) መሰረት አድርጎ በመቅረቡ ብቻ ቀሪ    የሚሆኑ


አይደሉም፡፡ የተፋጠነየወንጀልአሰጣጥ (RTD) አሰራርን መሰረት አድርጎ የሚታይ  ጉዳይ የተከሳሹን የመከላከል መብት ለመተው የሚያስችለው ተከሳሹን ይህንኑ መብቱን በማሻያማ አኳኃን የተወው መሆኑን ሲያረጋገጥ ነው፡፡

 

ወደ ተያዘው ጉደይ ስንመለስ የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን ያየው የተፋጠነየወንጀልአሰጣጥ (RTD) አሰራርን ተከትሎ ሲሆን አመልካችን ጥፋተኛ ያደረገው ተከሳሽ ድርጊቱን መፈፀሙ በዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ተነግሮበት የመከላከያ ምስክር እንዳለው ተጠይቆ የመከላከያ ማስረጃ "አለኝ በማለት በችሎት በፅሑፍ በቃል ያረጋገጠ" ስለሆነ ነው በሚል ምክንያት ስለመሆኑ ከውሳኔው ይዘት ተመልክተናል፡፡ ይህ የስር ፍርድ ቤት አጻጻፍ በአንድ በኩል አመልካች በቃልም ሆነ በፅሑፍ የመከላከያ ማስረጃ "አለኝ" ያለ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ድምዳሜው አመልካች የመከላከያ ማስረጃ የሌለው መሆኑን መግለፁን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይህን ግልጽነት የጎደለውን የስር ፍርድ ቤትን አጻጻፍ ትክክለኛነቱን ለመረዳት ይቻል ዘንድም ዋና መዝገቡን አስቀርበን ተመልክተናል፡፡ የስር ፍርድ ቤትን መዝገብ እንደተመለከትነውም የሥር ፍርድ ቤት አመልካች እንዲከላከል ጥቅምት 28 ቀን 2006 ዓ/ም በዋለው ችሎት ብይን ሲሰጥ ብይኑ ቀድሞ የተዘጋጀውን ቅጽ/ፎርም/ በመሙላት የተሰጠ ሲሆን በይዘቱም አመልካች መከላከያ ማስረጃ "የለኝም" በማለት መግለፁን፣ ይህንኑ የገለፀው ደግሞ በችሎት በፅሑፍና በቃል መሆኑን የሚጠቅስ ቢሆንም አመልካች በቃል የገለጸ ስለመሆኑ ከብይኑ ውጪ በእለቱ የችሎቱ የወረቀት ስራ ያልተመዘገበ፣ "በፅሑፍ አረጋግጧል" የሚለው አባባልም ከመዝገቡ ውስጥ ካሉት ሰነዶች ሲታይ ሰነዱ የሌለ መሆኑን ይህ ችሎት ተገንዝቧል፡፡ በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤት ቀድሞ የተዘጋጀውን የብይንና የፍርድ ፎርም ሲሞላ በአማራጭ የተቀመጡትን ቃላትና ሐረጎችን በእስክርቢቶ እየሰረዘ አመልካች የመከላከያ ማስረጃ የለኝም ብሎ በቃልና በፅሑፍ አረጋግጧል በማለት የመከላከያ ማስረጃ መስማትን ያለፈ ቢሆንም ይህንኑ የሚያረጋገጥ ማስረጃ ያለመኖሩን ከስር ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ ተረድተናል፡፡ ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው አመልካች በሕጉ የተጠበቀላቸውን የመከላከያ ማስረጃ ማሰማት መብት የስር ፍርድ ቤት ያለፈው አመልካቹ በግልጽ በመብቱ የማይጠቀምበት መሆኑን ሳያረጋገጥ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም  ምክንያት ተከታዩን ወስናል፡፡

 

 ው ሣ ኔ

 

1. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 34797 ጥቅምት 28 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 144019 የካቲት 14 ቀን 2006 ዓ/ም ተሻሻሎ የፀናው ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 195(2(ለ-1)) መሰረት ሙሉ በሙሉ ተሸሯል፡፡

2. የአመልካች የመከላከያ ማስረጃ የማሰማት መብት የታለፈው ያላግባብ ነው ብለናል፡፡ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት ክርክሩን በመ/ቁጥር 34797 ቀጥሎ የአመልካችን የመከላከላያ ማስረጃ በሕጉ አግባብ ሰምቶ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ዳኝነት እንዲሰጥበት ጉዳዩን መልሰን ልከንለታል፡፡ይጻፍ፡፡

3. የስር ፍርድ ቤት አመልካችን የብር 10,000 (አስር ሺህ) ዋስ እንዲጣራና ጉዳዩን  በውጪ ሆኖ እንዲከታተል እንዲደረግም ብለናል፡፡ይጻፍ፡፡

 ት ዕ ዛዝ

የስር ፍርድ ቤት መዝገብ በአስቸኳይ ይመለስ ብለናል፡፡

 

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡         የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት