93577 criminal procedure/ criminal trial in absentia

በወንጀል የተከሰሰ ሰው ጉዳዩን በሌለበት ለማየት ፍ/ቤቱ በመጀመሪያ
ለተከሣሹ ህጉ ያስቀመጠውን ጥብቅ መስፈርት በተከተለ መልኩ
በአግባቡ ጥሪ ሊያደርግለት የሚገባ ስለመሆኑ፣
የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 161(1)(2) እና 162

የሰ/መ/ቁ. 93577

 

ህዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል

አመልካች፡- አቶ ዘውዴ ተስፋይ ስመኝ ጉዳይ ተከታታይ ቀረቡ ተጠሪ፡- የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ዐቃቤ ህግ የቀረበ የለም

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የተጀመረው በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁኑ ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ደግሞ ተከሳሽ ነበር፡፡ተጠሪ በአመልካች እና በስር ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ በነበረው ካሳየ ጌጡ ያቀረበው ክስ ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ነው፡፡ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ መነሻ የሆነው የአሁኑ ተጠሪ ጉዳዩ የተሰማው በሌለበት በመሆኑ ከመጥሪያ አደራረስ ጋር የተያያዘ ክርክር በማቅረቡ ነው፡፡

ዓቃቤ ህግ በስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተጠሪ እና 1ኛ ተከሳሽ በነበረው ካሳየ ጌጡ ያቀረበው ክስ የወ/ሕ/ቁ.32(1)(ሀ) እና 539(1)(ሀ) የተመለከተውን በመተላለፍ ሰው ለመግደል አስበው በ19/10/1997 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ትግራይ ክልል አላማጣ ወረዳ ቀበሌ ማረዋ ሟች ሰመሀኝ አረቂ በክላሽ ኮፕ መሳሪያ አንድ ጥይት በመተኮስ ገድለዋል የሚል ነው፡፡

አመልካች ጉዳዩ ሊሰማ በተያዘው ቀጠሮ ባለመቅረቡ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.161(1) በሚያዘው መሰረት በመኖሪያ አካባቢው በተለጠፈ መጥሪያ ጥሪ ቢደረግለትም ባለመቅረቡ በሌለበት ክርክሩን ቀጥሎ የዓቃቤ ህግ ምስክሮች ከተሰሙ በኃላ የሥር ፍርድ ቤት ዐቃቤ ህግ እንደ ክሱ አቀራረብ አስረድቷል በማለት አመልካች ጥፋተኛ ነው በማለት ወስኗል፡፡ ቅጣት በተመለከተም  በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የወሰነ መሆኑ ከሥር ፍርድ ቤት መዝገብ መረዳት ይቻላል፡፡ አመልካች በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር ከዋለ በኃላ በማረሚያ ቤት በኩል በ15/09/2004 ዓ.ም. ውሳኔ ለሰጠው ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ አመልካች ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ እና በፍርድ ቤት ባደረገው ክርክር ፈጸመው በተባለው የግድያ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት መሆኑ አለማወቁን፤ በሚኖርበት አካባቢ ባህል በግድያ የተጠረጠረ ሰው ራሱ እና ቤተሰቡ ከአካባቢው ለቀው እንደሚሄድ፤ አመልካችም አካባቢው ለቆ በኦሮሚያ ክልል ሲኖር እንደነበር፤ ቀርቦ ቢከራከር እና ቢከላከል ከእሱ ጋር ተከሶ እንደነበረው ግለሰብ በነፃ ይለቀቅ እንደነበር በመግለጽ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተነስቶለት ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ መጠየቁን፤ ዐቃቤ ህግ በበኩሉ አመልካች ወደ ህግ መቅረብ ሲገባው ሆነ ብሎ ከአካባቢው በመሸሹ


በአካባቢውም ጥሪ ተደርጎለት ባለመቅረቡ በሌለበት የተሰጠው ፍርድ እና ቅጣት ሊጸና እንደሚገባ ተከራክረዋል፡፡

የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙ ክርክር በመመርመር በሰጠው ብይን አመልካች የአካባቢው ባህል መሰረት በማድረግ ከአካባቢው ለቆመሄዱ ያቀረበው ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው፤ በአንፃሩ ጉዳዩ ወደ ፍትህ አካል ቀርቦ መጨረስ ይገባው እንደነበር፤ አመልካች ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በአካባቢው የአስተዳደር ክፍል ቤተዘመዶቹ በሚገኙበት አካባቢ መጥሪያ ተለጥፎ መቅረብ አልቻለም፡፡ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካደረገኝ በኃላ ነው ፍርደኛ መሆኔን ያወኩት የሚለው ተቀባይነት የለውም፡፡ መጥሪያው በአካባቢው መለጠፉን ያውቀዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ በወ.ሕ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 197 ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት የለውም በማለት ወስነዋል፡፡

አመልካች ቅጣት በተመለከተ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት በማግኘቱ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት በማሻሻል በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

አመልካች በሌለበት የተሰማው ጉዳይ ሊሻር ይገባል በማለት ወደ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታውን አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎትም በወ.መ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 162(ሀ) እንደተመለከተው የጋዜጣ ጥሪ አስፈላጊ መሆኑ አስገዳጅ ድንጋጌ ቢሆንም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (ለ) እንደተደነገገው ፍ/ቤቱ ለተከሳሽ ሊደርሰው ይችላል ብሎ በገመተው አግባብ ጥሪውን ማስተላለፍ እንደሚችል ስለሚገልጽ በአመልካች መኖሪያ አድራሻ መለጠፉ ስለተረጋገጠ የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚነቀፍ አይደለም በማለት በማጽናት ወስነዋል፡፡

የሰበር አቤቱታ የቀረበውም የስር ከፍተኛ እና ጠቅላይ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ለማስለወጥ ነው፡፡ አመልካች በስር ፍርድ ቤቶች ተፈጸመዋል ያላቸውን ስህተቶች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘቱ፡- የተጠረጠረበት ወንጀል ከተፈጸመ  በኃላ ከአካባቢው ርቆ መሄዱ፤ በአካባቢው ባህልም የተለመደ መሆኑ፤ የተከሰሰ መሆኑ አለማወቁን፤ በአካባቢውም መከሰሱን ሊነግረው የሚችል ቤተሰብ አለመኖሩን፤ ሕጉም ጥሪ በጋዜጣ እንደሚደረግ እያዘዘ በአካባቢው በተለጠፈው ጥሪ ብቻ መጥሪያ ደርሶታል መባሉ በአግባቡ አለመሆኑን፤ ቀርቦ ባለመከራከሩ የመከላከል መብቱ መታለፉ በመግለጽ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሻር አመልክቷል፡፡

ዐቃቤ ህግ የበኩሉን መልስ አቅርበዋል፡፡ ዐቃቤ ህግ የሰጠው መልስ ዋና ፍሬ ነገሩ፡- የስር ፍርድ ቤት ህጉ በደነገገው አግባብ በተሰጠው አማራጭ ጥሪ ማስተላለፉ፤ አመልካች በአካባቢው በተደረገለት ጥሪ አለመቅረቡን፤ በገጠር አካባቢ በጋዜጣ የሚወጣ ጥሪ እንደማይነበብ የተሻለ የሚሆነው በአካባቢው መጥሪያው መለጠፍ መሆኑ፤ የስር ፍርድ ቤትም ይህንን አማራጭ በመውሰድ ለአመልካች የተላለፈው ጥሪ በአግባቡ ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ሊጸና ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም ጉዳዩ ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች እና ጉዳዩን ለሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምረናል፡፡

ጉዳዩ እንደመረመርነው በአመልካች እና ተጠሪ መካከል ያለው መሰረታዊ የክርክር ጭብጥ በወንጀል ጉዳይ የተከሰሰ ሰው በሌለበት ነገሩ እንዲሰማ ሲታዘዝ የመጥሪያ አደራረስ ሥርዓቱ ምን መምሰል አለበት? የሚል ነው፡፡ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት መፍትሔ የሚሻው ጭብጥ የስር ፍርድ ቤቶች አመልካች የተከሰሰበት የግድያ ወንጀል በሌለበት እንዲታይ ሲወስኑ መጥሪያው ተከሳሹ ይኖርበት ነበር በተባለው ቀበሌ እና አካባቢ ብቻ መለጠፍ በወ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 162 የተመለከተው ድንጋጌ መሰረታዊ ይዘት በአግባቡ ያገናዘበ ነው ወይስ አይደለም?  የሚል ነው፡፡


ከስር ፍርድ ቤት የክርክር ሂደት መገንዘብ እንደተቻለው አመልካች በከባድ የግድያ ወንጀል ክስ ቀርቦበት ጉዳዩ ሊሰማ በተቀጠረበት ቀን ባለመቅረቡ በሌለበት ክርክሩን ተካሂዶ ጥፋተኛ ተብሎ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡ የስር ፍርድ ቤት አመልካች እንዲቀርብ የሰጠው ትዕዛዝ ተፈፃሚ ባለመሆኑ መደበኛ መኖሪያው ነው በተባለው እና በአካባቢው  አስተዳደር መጥሪያ በመለጠፍ በሌለበት ጉዳዩን እንዲሰማ አዟል፡፡ አመልካች ከስር ፍርድ ቤት ጀምሮ አጥብቆ የሚከራከረው የተከሰሰ ስለመሆኑ አለመሰማቱ፤ በአካባቢው ባህል በወንጀል የተጠረጠረ ሰው ቀየውን ለቆ የሚሄድ መሆኑ እና የስር ፍርድ ቤትም ህጉ ያስቀመጠውን በጋዜጣ የመጥራት አስገዳጅ ድንጋጌ በአግባቡ አለመተርጎሙን ነው፡፡

በመርህ ደረጃ የወንጀል የክርክር ሂደት ተከሳሾች ባሉበት እንደሚደረግ በልዩ ሁኔታ ደግሞ የፈጸሙት ወንጀል ቀርበው መከራከር የማይፈለጉና ከፍትህ ስርዓቱ የሸሹ ግለሰቦች በፍትህ ስርዓቱ መጠየቅ ያለባቸው በመሆኑ በሌሉበት ነገሩ ሊሰማ እንደሚችል ከወ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 161(1) እና (2(ሀ) ድንጋጌ መሰረታዊ ይዘት ንባብ የምንረዳው ነው፡፡ ፍርድ ቤቱም አንድን ጉዳይ ተከሳሽ በሌለበት ለማየት እንዲችል ተከሳሹ በቀጠሮ ቀን ያለ በቂ ምክንያት መቅረቱን ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑ የዚህ ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ 1 በግልጽ ያመለክታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በሌለበት ነገሩ ለመስማት ትዕዛዝ ከሰጠ ጥሪው ተደራሽ በሆነ አግባብ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል፡፡ በወ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 162 እንደተመለከተው ፍርድ ቤቱ የሚያስተላለፈው ጥሪ ተከሳሹ ስለተጠረጠበት ጉዳይ ዝርዝር መግለጫ የያዘ እና ጥሪውም በጋዜጣ  እንዲወጣ መታዘዝ እንዳለበት ከድንጋጌው ይዘት የምንገነዘበው ነው፡፡ በሌላ በኩል ፍ/ቤቱ የተሻለ አማራጭ ካገኘም የመጥሪያ ማስታወቂያው በሌላ መንገድ ማስተላለፍ እንደሚችል የዚህ ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ያሳያል፡፡

በስር ፍርድ ቤት የክርክር ሂደት እንደተገለጸው የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች እንዲቀርብ በጋዜጣ ጥሪ አለማድረጉን ነው፡፡ የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን  እንዳሰፈረው አመልካች የአካባቢውን ባህል መሰረት በማድረግ መሸሹን ተቀባይነት የለውም በመኖርያ ቤቱ አካባቢ እና በአካባቢ አስተዳደር የተለጠፈው መመጥሪያ ጉዳዩ በሌለበት እንደሚታይ የሰማ መሆኑ ግምት ይወስዳል በማለት ከድምዳሜ ላይ መድረሱን በውሳኔው አስፍራው አምልካች የተጠረጠረበት ወንጀል ተፈጸመ ከተባለበት በኃላ ከአካባቢው ለቆመሄዱን በየትኛውም መልኩ መከሰሱን አለማወቁን እየተከራከረ ነው፡፡ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምልካች የተከሰሱበት ጉዳይ በሌለበት ለመስማት ትዕዛዝ ሲሰጥ በጋዜጣ የጥሪ ማስታወቂያ ለማስተላለፍ ያልቻለበት ሁኔታ ምን እንደነበር በውሳኔው ግልጽ አላደረገም ፡፡በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ማስረጃ ቀርበው የመከላከል መብት ያላቸው መሆኑ በሕገ መንግስቱ እና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የተረጋገጠ ስለመሆኑ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 (1)እና(4)እና የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አካል የሆነው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች አለማቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 14(3)(ለ) እና (መ)መሠረታዊ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ እና ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው የሰብአዊ መብት  ድንጋጌዎች የተረጋገጠው ፍትሐዊ የዳኝነት መብት በየትኛውም መልኩ ሳይሸራረፍ በፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ሊሆን ይገባል፡፡ በእጃችን ወደ አለው ጉዳይ ስንመጣ አመልካች ጉዳዩን በሌለበት የታየው የጥሪ ማስታወቂያ በመደበኛ መኖርያ ቤት እና የአካባቢ አስተዳደር በመለጠፍ ብቻ ነው፡፡ በወ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ162(1) እንደተመለከተው ተከሳሽ በሌለበት የሚደረገው ክርክር የመጥሪያ ማስታወቂያ በቅድሚያ በጋዜጣ መደረጉ ሲረጋገጥ ነው፡፡ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች የተከሰሰበት ጉዳይ ቀርቦ እንዲከራከር በጋዜጣ ጥሪ ለማድረግ ያልቻለበት ምክንያት ግልፅ


አላደረገም ፡፡ የወ.መ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ 161(ሀ) መሠረታዊ ይዘት እና አላማ እንደተመለከተው አንድ ተከሳሽ በሌለበት ነገሩ ሲሰማ በፍ/ቤት ትዕዛዝ የሚሰጥ ከሆነ የመጥሪያ ማስታወቂያ በጋዜጣ እንዲወጣ ፍርድ ቤቱ ማዘዝ ያለበት መሆኑ በአስገዳጅነት የተደነገገበት አግባብ ሰፊ ስርጭትና ተደራሽነት ባለው ጋዜጣ የሚደረግ ጥሪ፤ጥሪ የሚደረግለት ተከሳሽ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩን ለመከታተል የሚያስችለው እንዲሆን ነው፡፡

የሥር ፍርድ ቤቶች የአመልካች ፍርድ ተሸሮ ጉዳዩ ድጋሜ ይታይልኝ ጥያቄ ውድቅ ሲያደርጉ ያሰፈሩት ምክንያት የወ.መ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ.162(ለ) ፍርድ ቤቱ መጥሪያው  ለተከሳሹ ሊደርስ ይችላል ብሎ በገመተው አግባብ ማስተላለፍ እንደሚችል ፤በዚህ የሕግ ድንጋጌ ትርጉም መሠረትም ተከሳሽ እንዲቀርብ በአካባቢው አስተዳደር እና መኖሪያ ቤቱ መጥሪያ እንዲለጠፍ አማራጭ መውሰዱን በመግለጽ ነው፡፡ በወ.መ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 162(ሀ) እንደተመለከተው ተከሳሹ በሌለበት ጉዳዩ እንዲታይ ከታዘዘ የመጥሪያ ማስታወቂያ በጋዜጣ እንዲወጣ ማዘዝ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በወ.መሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 162(ለ) የተመለከተው አገላለጽ ለተከሳሹ የሚደርሰ መስሎ ከታየው መጥሪያው የሚደርስበት ሌላ መንገድ ፍርድ ቤቱ ማዘዝ ይችላል  “የሚለውን ፍሬ ነገር በንኡስ አንቀጽ “ሀ”ላይ ከተመለከተው የጥሪ አደራረስ ሥርዓት በተሻለ አግባብ እንዲሆን ከማድረግ ውጭ ከዚህ ያነሰ መብት ለመስጠት ታስቦ የተደነገገ ስለመሆኑ ከአጠቃላይ የድንጋጌ ይዘትና ዓላማ የምንረዳው ሆኖ አልተገኘም፡፡ የመጥሪያ አደራረስ ሥርዓት በፍርድ ቤቱ እይታ የጥሪ ማስታወቂያው በጋዜጣ ከሚደረግ ጥሪ ለተሻለ አግባብ የሚደርስ ስለመሆኑ እርግጠኛ ከሆነ ነው እንጂ ሰፊ ስርጪት እና ተደራሽነት ካለው የጋዜጣ ጥሪ የጠበበ አማራጭ እንዲጠቀም የወ/መ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 162(ለ) የሚፈቅድ አይደለም ፡፡

በአመልካች መኖሪያ አካባቢ ወይም በአስተዳደር አካባቢ የሚደረገው ጥሪ በወሰን ቋሚ አድራሻ የሚደረግ እንጂ እንደ ጋዜጣ አገራዊ /አካባቢያዊ ስርጭት እና ተደራሽነት ያለው አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ተከሳሽ በሌለበት ነገሩ የሚታይበት የሙግት ሥርዓት ሕጉ ለይቶ በደነገጋቸው ጉዳዮች ብቻ የሚደረግ ሆኖ የአጠቃላይ መርሁን ልዩ ሁኔታ ነው፡፡ ከፍትሕ ሥርዓቱ ሸሽተው የሚደበቁ ተከሳሾች በሌሉበት ሁኔታም ጉዳያቸው የሚታይበት ሥርዓት መዘርጋት የወንጀል ሕጉ ዓላማና ግብ ለማሳካት ተገቢ ቢሆንም ተከሳሽ በሌለበት የሚደረገው ክርክር የተከሳሽ የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚያጣብብ  እንዳይሆን የመጥሪያ አደራረስ ሥርዓት ሕጉ የዘረጋውን ድንጋጌ በጥብቅ በመተግበር ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 20(4) እና የሲቭልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 14(3) (ለ) እና(መ) የተደነገጉት ቀርቦ የመከራከር እና የመከላከል መብት ማስከበር ፍትሐዊ የወንጀል ፍትህ ሂደት እንዲኖር  የሚደረግ ነው፡፡

አመልካች ከሚኖርበት አካባቢ ከቤተሰብ ጋር ቀየውን ለቆ ስለመሄድ በሥር ፍርድ ቤት ከቀረበው ክርክር መረዳት ይቻላል፡፡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለውም በኦሮሚያ ክልል መሆኑ እየተከራከረ ነው፡፡ አመልካች ራሱን ቤተሰቡን ከአካባቢው ለቆ መሄዱ በሚከራከሩበት በሚኖርበት ቀበሌ/አስተዳደር መጥሪያ መለጠፍ ለአመልካች በተሻለ አግባብ ጥሪ ተደርጎለታል ለማለት አይችልም፡፡ ከላይ እንደተመለከተው የወንጀል ጉዳይ የሙግት ሥርዓት ፍትሐዊ የክርክር ሂደት ያከበረ መሆን ይገባል፡፡ ፍትሐዊ የወንጀል ሙግት ሥርዓት ደግሞ በወንጀል ለተጠረጠረው ግለሰብ ቀርቦ ጉዳዩ እንዲከላከል በአግባቡ ጥሪ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር የስር ፍርድ ቤቶች በአመልካች መደበኛ መኖሪያ ቤት እና ቀበሌ አስተዳደር ጥሪ መደረጉ በቂ ነው በማለት አቤቱታው ውድቅ ማድረጋቸው በወ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 162 የተመለከተውን አገላለፅ መሠረታዊ ይዘትና ዓላማ ያላገናዘበ ነው፡፡ የሥር ፍርድ ቤቶች አመልካች እንዲቀርቡ ጥሪ የተደረገበት ሥርዓት ሕጉ ያስቀመጠው ጥብቅ መስፈርት ያልተከተለ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት


የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የሥር ፍርድ ቤቶች አመልካች የተከሰሰበት የወንጀል ጉዳይ ቀርቦ እንዲከራከሩ ሕጉ በዘረጋው ሥርዓት አግባብ የመጥሪያ ማስታወቂያ በጋዜጣ ሳያወጡ ተከሳሹ በሌለበት የክርክር ሂደቱን አጠናቅቀው አመልካች ጥፋተኛ ነው በማለት በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰናቸው መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ በመገኘቱ ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

 

1. የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ/መ/ቁ. 03870 በ24/09/2004 የሰጠው ብይን፤ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ. 58544 በ03/12/2005 ዓ.ም የሰጠው ብይን ተሽሯል፡፡

2. አመልካች ሕጉ በዘረጋው የመጥሪያ አደራረስ ሥርዓት መጥሪያ ማስታወቂያ በጋዜጣ ሳይሰማ ክርክር ተካሄዶ መወሰኑ በአግባቡ አይደለም ብለናል፡፡

3. በአመልካች የቀረበው የወንጀል ክስ ግራ ቀኙ በተገኙበት የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 202(1) በሚያዘው መሠረት በአካባቢው ባለው ሌላ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማለትም የደቡብዊ ምስራቅ ከፍተኛ ፍርድ ቤት/በተመሳሳይ ደረጃ ባለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት/ ዐቃቤ ህግ  ክሱን በማቅረብ ክርክሩን እንዲቀጥል አዘናል፡፡ ይፃፍ፡፡

4. የስር ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ብይኖች የተሻሩ ስለመሆናቸው ለሁለቱም ፍ/ቤቶች ይድረሳቸው ብለናል፡፡ ይፃፍ፡፡

5. ለአመልካችም የፍ/ቤቱ ውሳኔ ግልባጭ በትግራይ ክልል ማይጨው ማረሚያ ቤት በኩል ይድረሰው፡፡ ይፃፍ፡፡

6. ለተጠሪም የፍ/ቤቱ ውሳኔ በትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ በኩል ይድረሰው ብለናል፡፡ ይፃፍ፡፡ ጉዳዩ ውሳኔ ያገኘ በመሆኑ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

እ/እ