አንድ የትራፊክ ባለሙያ የሚሰጠው ሙያዊ አስተያየት የማስረጃ ዋጋ
የማይሰጠው አስተያየቱ ተገቢውን የሙያ ደንብ ተከትሎ ያልተሰጠና
ያልቀረበ፣በጊዜውና በቦታው ከነበሩት የአይን ምስክሮች ቃል ጋር
ተነፃፅሮ ሲታይ በመሰረታዊ ነጥቦች ላይ ልዩነት ያለበት መሆኑ
ሲረጋገጥ እንጂ በጭፍጫፊ ነጥቦች ላይ ልዩነት ተከስቷል ተብሎ
ሊሆን እንደማይገባ፣
የልዩ አዋቂዎች ምስክሮች ቃላቸውን ገለልተኛ ሆነው መስጠት እንደ
አለባቸውና ቃላቸው ያለበቂ ምክንያት ልዩ አዋቂ ያልሆኑ ሰዎች
በሚሰጡት የምስክሮች ቃል ውድቅ መሆን የሌለበት መሆኑን
ተቀባይነት ያላቸው የማስረጃ ህግ ደንቦች የሚያስገነዝቡ ስለመሆኑ
የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 141፣142፣194
የወንጀል ህግ ቁጥር 24፣59፣239(2)፣57፣543(2)
የሰ/መ/ቁ. 92141 መስከረም 3ዐ ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም
ዳኞች፡- አልማው ወሌ
ሱልጣን አባተማም መኮንን ገ/ሕይወት ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመስል
አመልካች፡- የደ/ብ/ብ/ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትፍትሕ ቢሮ አቃቤ ሕግ ተጠሪ፡- አቶ አለማየሁ አስፋው
መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡
ፍ ር ድ
ጉዳዩ ወንጀል ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች በአሁኑ ተጠሪ ላይ በጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም፡- ተጠሪ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 543/2/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በሾፌርነት ሙያቸው የሌላውን ሰው ሕይወትና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ እያለባቸው መጋቢት ዐ2 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም ከቀኑ 5፣3ዐ ሲሆን ንብረትነቱ የድርባ ደፈርሻ የመንገድ ስራ ተቋራጭ የሆነውን፤ የሰሌዳ ቁጥሩ 3-
25709 ኦሮ የሆነውን ቶዮታ ሃይሉክስ መኪና ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ አርባ ምንጭ መሰመር በከፍተኛ ፍጥነት እና የራሳቸውን መስመር በመልቀቅ በማሽከርከር ላይ እያሉ በምዕራብ አባያ ወረዳ ብርብር ከተማ የሰሌዳ ቁጥሩ 2-ደ/ሕ 11444 የሆነችውን ባለሁለት እግር ባጃጅ ሞተር ሲያሽከረክር የነበረውን ንጋቱ ሉቃስ የተባለውን ሰው በመግጨት የገደሉት በመሆኑ በፈፀሙት በቸልተኝነት ሰው መግደል ወንጀል ተከሰዋል የሚል ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪም የክስ ማመልከቻ ደርሷቸው ክሱን እንዲረዱት ከተደረገ በኋላ ስለእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቁ በክሱ ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው የገለፁ ሲሆን የድርጊቱን አፈፃፀም በተመለከተም ድርጊቱ መፈፀሙን አምነው አፈፃፀሙ ግን እንደ አቃቤ ህግ ክስ ያለመሆኑን ዘርዝረው የክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ከዚህም በኋላ ተጠሪ የወንጀል ድርጊቱን ሰለመፈፀማቸው ሟች በደረሰባቸው አደጋ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ መሆኑን አቃቤ ህግ በማስረጃዎቹ ያስረዳባቸው መሆኑ በስር ፍርድ ቤት ታምኖበት ይህንኑ እንዲያስተባብሉ የተጠሪ የመከላከያ ማስረጃ ማሰማት መብታቸው ተጠብቆላቸው ተጠሪ አንድ የሰው መከላከያ ማስረጃዎችን አሰምቷል፡፡ ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ በሟች ላይ የሞት አደጋ የደረሰው በሟች ጥፋት መሆኑን ከማስረጃዎቹ መረዳቱን ገልፆና በአቃቤ ህግ ማስረጃዎችም ልዩነት መከሰቱን ዘርዝሮ ተጠሪ የአቃቤ ሕግ ማስረጃዎቹን በመከላከያ ማስረጃቸው አስተባብለዋል በሚል ድምዳሜ ከክሱ በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙንና የሰበር አቤቱታውን እንደየቅደም ተከተላቸው ለክልሉ
ጠቅላይፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ሰሚ ችሎቶች ቢያቀርብም ቅሬታው በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 195(1) መሠረት ተሰርዞበታል፡፡የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ አመልካች ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ ሁለት ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚልባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ፡- ተጠሪ ድርጊቱን የፈፀሙት ከጥንቃቄ ጉድለትና በከፍተኛ ፍጥነት ሲያሽከረክሩ ሆኖ እያለ በስር ፍርድ ቤቶች የሟች ጥፋት አለ ተብሎ የተጠሪ የወንጀል ተጠያቂነት የለባቸውም ሲባል መታለፋ ያላግባብ መሆኑን፣የትራፊክ ባለሙያዎች የሰጡት የትራፊክ ኘላንና የአደጋ መግለጫ የሰነድ ማስረጃዎች ውድቅ የተደረጉት ተገቢውን የማስረጃ ሚዛን ባለመከተል መሆኑን ዘርዝሮ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተሽሮ በተጠሪው ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲሰጥ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው፡፡አቤቱታው ተመርምሮ ተጠሪ በነጻ የመለቀቃቸውን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪም በሕጉ አግባብ ጥሪ ተደርጎላቸው ባለመቅረባቸው በፅሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸዉ ታልፏል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡
በመሠረቱ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ወንጀሉን የሚቋቋሙት ሕጋዊ፣ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑን በአዋጅ ቁጥር 414/1996 የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 239(2) በግልጽ ደንግጓል፡፡እንግዲህ አንድን ድርጊት ወንጀል ነው ብሎ ለመወሰን ሕጋዊ፣ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ተጣምረው መገኘት የግድ ይላል፡፡ሕጋዊ ፍሬ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ ለጉዳዩ አግባብነት አለው ተብሎ የተጠቀሰውን ድንጋጌ ለማቋቋም ሙሉ በሙሉ መሟላት ያለባቸውን ነጥቦች ሲሆን ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ እንደየቅደም ተከተላቸው ከድርጊቱ ማድረግ ወይም አለማድረግና ከሐሳብ ክፍል ጋር በሕጉ የተመለከቱትን ሁኔታዎች የሚመለከቱ ናቸው፡፡በምክንያትነትና በውጤት መካከል ደግሞ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 24 በተመለከተው አግባብ ግንኙነት መኖሩ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ወንጀሉ በተከሳሹ የተፈፀመ መሆኑን ከሳሽ የሆነው ወገን አሳማኝ እና በቂ በሆነ ሁኔታ የማስረዳት ሸክም ያለበት መሆኑን ከወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 141፣142 እና 194 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡
በተያዘው ጉዳይ ከላይ እንደተገለፀው ተጠሪ ሲያሽከረክሩት የነበረው ተሽከርካሪ እና ሟች ሲያሽከረክር የነበረውን ተሽከርካሪ ተጋጭተው ሟች ላይ መጋቢት 02 ቀን 2004 ዓ.ም ጉዳት ደርሶ በዚሁ ጉዳት ምክንያት ሟቹ ለህልፈት የተዳረገ መሆኑ የተካደ ጉዳይ አይደለም፡፡ተጠሪ የሚከራከሩበት ነጥብ በወቅቱ ራሳቸው የሚያሽከረክሩትን መኪና በተገቢው ፍጥነትና ጥንቃቄ በተሞላበትሁኔታ ሲያሽከረክሩ እንደነበር ጠቅሰውና ይህንኑ አይተዋል ተመልክተዋል የሚሏቸውን አንድ የሠው መከላከያ ምስክራቸው አስረድተዋል ሟች የሞቱት በራሳቸው ጥፋት ምክንያት ነው የትራፊክፕላኑ አደጋው የደረሰው በተጠሪ ጥፋት ነው በሚል የቀረበው ተጠሪ ያልፈረሙበት በመሆኑ ተቀባይነት ሊሰጠው አይገባም የሚሉ ነጥቦችን በማንሳት መሆኑን ከስር ፍርድ ቤት የውሳኔ ግልባጭና ከዋናው መዝገብ ከሰፈሩት የክርክር ሂደቶች ተገንዝበናል ፡፡ የሥር ፍርድ ቤትም ይህንኑ የተጠሪን መከራከሪያ ነጥብ የተቀበለው ሲሆን የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ቃል ልዩነት ያለበት መሆኑን፣የትራፊክ አደጋ ፕላኑና የአደጋው መግለጫ ሰነዶች የማይታመኑ መሆኑና የተጠሪ መከላከያ ማስረጃ ግን የሚታመኑ መሆኑን በውሳኔ ላይ ጠቅሷል
፡፡ ይሁን እንጂ የሥር ፍርድ ቤት ለጉዳዩ ቀጥተኛና አግባብነት ያለውን የባለሙያ የምስክርነት አስተያየት በአደጋው ቦታ የተነሳውን ፕላንና የግራ ቀኙን ምስክሮች ቃል መዝኖ ተጠሪ ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርጉ ቀርተው አደጋው መድረሱን የዐቃቤ ህግ የሠውና የሰነድ ማስረጃዎች ያረጋገጡትን ፍሬ ነገር ውድቅ ያደረገው መሰረታዊ ነጥቦች ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል ልዩነት ማሳየቱን ፣የባለሙያ ምስክርነት ቃልም በተገቢው ማስረጃ የተስተባበለ መሆኑን በግልጽ ጠቅሶ ያለመሆኑን ከውሳኔው ግልባጭና ከዋናው መዝገብ ላይ ከሰፈረው የአቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል እንዲሁም ከሰነድ ማስረጃዎች ይዘት ለመረዳት ችለናል፡፡ የአሁኑ ተጠሪ በአመልካች የተከሰሰው ሲያሽከረክሩት የነበረውን መኪና በከፍተኛ ፍጥነት እና የራሳቸውን የቀኝ መስመር በመልቀቅ ወደ ግራ መስመር በመግባት በጥንቃቄ ጉድለት ሟችን ገጭተዋል በሚል ምክንያት ሲሆን አመልካች ይህንኑ የድርጊት አፈፃፀም በተመለከተ በጊዜው እና በቦታው የነበሩትን የሰው ምስክሮች ስለአደጋው ሙያዊ አስተያየት መስጠት የሚችሉትን የትራፊክ ፖሊሶች የሰጡትን ሙያዊ መግለጫ ለማስረጃነት አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ ከመስማቱ በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ የትራፊክ ፖሊሶች ችሎት ቀርበው ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡበትም አድርጓል ፡፡ በአቃቤ ህግ በኩል የተሰሙት ሁለት ምስክሮች ተጠሪ ሲያሽከረክሩት የነበሩውን መኪና ፍጥነት ከሙያ አንፃር ሊመሰክሩ ይችላሉ ተብሎ የማይወሰዱ ቢሆንም ሟች በወቅቱ የነበረበትን ሁኔታና የደረሰበትን ጉዳት ከመመስከራቸውም በላይ ድርጊቱ ሲፈጸም የተጠሪ መኪና በከፍተኛ ፍጥነት ሁኖ ወደ ሟች ግራ መስመር አጥብቦ በመግባት ሟችን እንደገጨውና የተጠሪ መኪና የቆመበትን አጠቃላይ ሁኔታ እንደግንዛቤአቸው መጠን የገለጹ ሲሆኑ በምስክሮች ቃል ተከስቷል የተባለው ልዩነት ሟቹ ሲያሽከረክር የነበረው ባጃጅ ተሽከርካሪ ወደ ዋናው መንገድ የፊት ጎማው የገባ መሆን ያለመሆኑ እና የተጠሪ መኪና ከግጭቱ በኃላ የቆመበትን አግባብ የሚመለከት ነው፡፤ ስለጉዳዩ ሙያዊ አስተያየት በሰነድ ማስረጃዎቹ ላይ ያሰፈሩት የትራፊክ ፖሊሲዎች የተጠሪ የመኪና ማሽከርከር ሁኔታ የትራፊክ ደንቡን ተከትሎ የተከናወነ ያለመሆኑን ሟች ለግጭቱ መከሰት ያደረገው አስተዋጽኦ ያልነበረ መሆኑን በሚያስገነዝብ መልኩ የመሰከሩ ሲሆን የእነዚህ ምስክሮች ቃል በስር ፍርድ ቤት ክብደት ሳይሰጠው የታለፈው የአደጋ ቦታ ፕላኑ ረቂቁ የአደጋ መነሻ ቦታ ላይ ምልክት ያለበት ሁኖ ዋናው ግን ይኼው ምልክት የለውም የሚለውንና ለመርማሪ ከሳሽ ሲላኩ የሰነዶቹን የገጽ ብዛት ፍርድ ቤት ከቀረበው ጋር የተለያዩ መሆናቸውን የሚገልፁ ምክንያቶች በማስፈር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዋናው የአደጋ ቦታ ፕላን የትራፊክ አደጋ የሚነሳበትን ደንብ መሰረት አድርጎ ያልተነሳ መሆኑን በተጠሪ ማስተባበያ ክርክርና ማስረጃ ያልቀረበበት ከመሆኑም በላይ ተጠሪ በወቅቱ ያሽከረክሩት የነበረውን መኪና ከተገቢው ፍጥነት በላይ እና ከተገቢው መስመር በመውጣት ሲያሽከረክሩ የነበሩ መሆኑን ሰነዶቹ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚገልፁት መሆኑን የሰነዶቹ ይዘት በግልፅ ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ በተጠሪ በኩል የቀረቡት ምስክር የተጠሪ መኪና ፍጥነት የለውም ብለው የሰጡት ምስክርነት የባለሙያዎችን የምስክርነት ቃል ሊያስተባብል የሚችልበት አግባብ የሌለ መሆኑን ከክርክሩ ሂደት ተገንዝበናል፡፡ አንድ የትራፊክ ባለሙያ የሚሰጠው ሙያዊ አስተያየት የማስረጃነት ዋጋ የማይሰጠው አስተያየቱ ተገቢውን የሙያ ደንብ ተከትሎ ያልተሰጠና ያልቀረበ፣ በጊዜውና በቦታው ከነበሩት የአይን ምስክሮች ቃል ጋር ተነጻፅሮ ሲታይ በመሰረታዊ ነጥቦች ላይ ልዩነት ያለበት መሆኑ ሲረጋጥ እንጂ በጭፍጫፊ ነጥቦች ላይ ልዩነት ተከስቷል ተብሎ ሊሆን አይገባም፡፡
በመሰረቱ ፍርድ ቤቱ የልዩ አዋቂዎችን የምስክርነት ቃል ጉዳዩን ለማብራራት ወይም ለክርክሩ ውሣኔ አሰጣጥ ተገቢ ነው ካለ ወይም ተከራካሪ ወገኖች ክርክራቸውን ለማስረዳት በሕጉ አግባብ
ከቆጠሩ ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ያላቸውን ልዩ አዋቂዎች ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ሊያደርግ እንደሚችል ስለማስረጃ አቀራረብና አቀባበል ከተደነገጉት ድንጋጌዎች መረዳት የምንችለው ጉዳይ ነው፡፡ የልዩ አዋቂዎች ምስክሮች ቃላቸውን ገለልተኛ ሆነው መስጠት እንደአለባቸውና ቃላቸው ያለበቂ ምክንያት ልዩ አዋቂ ያልሆኑ ሰዎች በሚሰጡት የምስክርነት ቃል ውድቅ መሆን የሌለበት መሆኑን ተቀባይነት ያላቸው የማስረጃ ሕግ ደንቦች የሚያስገነዘቡን ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የልዩ አዋቂዎች የምስክርነት ቃል በገለልተኛነት ሊሰጥ እንደሚገባ አዋቂ ያልሆኑ ሰዎች የሚሰጡት የምስክርነት ቃል ከልዩ አዋቂዎች የምስክርነት ቃል የተሻለ ክብደት ሊሰጠው የሚገባው ፍርድ ቤቱ በቂ የሆነ ምክንያት ሲያገኝ በመሆኑ የልዩ አዋቂዎች የምስክርነት ቃል እንደ ማንኛውም ማስረጃ በጥንቃቄ ሊመዘን የሚገባው እንጅ ሁል ጊዜ ክብደት ሊሰጠው የሚገባ የማስረጃ አይነት አይደለም፡፡ የትራፊክ ፖሊስ የአደጋ ፕላን ሪፖርትም የባለሙያ ሙያዊ አስተያየትን በወረቀት ላይ ስዕላዊ በሆነ መንገድ የሚያስቀምጥ በመሆኑ በባለሙያ የሚረጋገጥ ሰነድ በመሆኑ እንደ ማንኛውም የልዩ አዋቂ የምስክርነት ቃል በተገቢው መንገድ ሊመዘን የሚገባው የማስረጃ አይነት እንጅ ሁልጊዜ ድምዳሜ ማስረጃ (Conclusive Evidence) ያለመሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
በተያዘው ጉዳይም የትራፊክ ሰነዱ ይዘትና የትራፊክ ባለሙያዎች አስተያየት ተገቢውን የትራፊክ ደንብ ተከትሎ ያልተሰራ መሆኑ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ልዩ አዋቂ ባልሆኑት በተጠሪ መከላከያ ምስክር ቃል ተስተባብሏል ተብሎ በበታች ፍርድ ቤቶች መወሰኑ በክርክሩ ሂደት የተረጋገጡትን መሰረታዊ ነጥቦችን ያላገናዘበና የማስረጃ አቀባበልና ምዘና ስርዓትን ያልተከተለ ሁኖ ተገኝቷል፡፡ በአንድ ጉዳይ የቀረበን የሰነድ ማስረጃ ይዘት ሙሉ በሙሉ ሳይመዘን በመተው በጭፍጫፊ ነጥቦች ላይ ብቻ በማተኮር ማስረጃን ክብደት ሳይሰጡ ማለፍ ደግሞ የማስረጃ ምዘና መርህና የዳኝነት አካሄዱ የማይፈቅዱት በመሆኑም የመሰረታዊ ህግ ስህተት መመዘኛን የሚያሟላ ነው፡፡ አንድ ፍ/ቤት በህግ በኩል የቀረቡትን ማስረጃዎቹን ውድቅ ሊያደርግ የሚገባው በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠውን ነገር ሙሉ በሙሉ ይዞ ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን የማስረጃ ምዘና መርህ ይዞ ማስረጃውን በመመዘን እንጂ ከማስረጃዎቹ ውስጥ ጭፍጫፊውን ወይም የተወሰነውን ፍሬ ነገር ብቻ በመያዝ ሊሆን እንደማይገባው ተቀባይነት ያላቸው የማስረጃ ህግ ጽንሰ ሀሳቦች የሚያስገነዝቡን ሐቅ ነውና፡፡ በመሆኑም የስር ፍ/ቤት የዐቃቤ ህግ ማስረጃዎች ተጠሪ ጥፋት የፈጸመው መሆኑን አላረጋገጡም ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው ተጠሪ እንዲከላከሉ ትዕዛዝ ከሰጠ በኃላ ሁሉም የዐቃቤ ህግ ምስክሮች የሰጡትን የምስክርነት ቃል እና በሰነድ ማስረጃዎች የሰፈረውን ይዘት አንድ ባንድ ባለማየትና የልዩ አዋቂዎች ሙያዊ አስተያየትን ውድቅ ለማድረግ ለሚያስችል በቂና ህጋዊ ምክንያት ሳይኖር ነው፡፡በመሆኑ ተጠሪ የሹፍርና ሙያ የሚጠይቀውን ጥንቃቄ ባለማድረግ የወንጀል ድርጊቱን በቸልተኝነት ያደረጉ መሆኑ በዓቃቤ ህግ የአይን ምስክሮች እና በትራፊክ ፖሊሶች ሙያዊ አስተያየት ተረጋግጦባቸው እያለ በማስረጃ የተረጋገጠውን ፍሬ ነገር በመተው ተጠሪውን የስር ፍ/ቤት በነጻ ማሰናበቱም ሆነ በክልሉ የበላይ ፍ/ቤቶች አለመታረም መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 57 በግልጽ እንደሰፈረው “ለድርጊቱ ኃላፊ ሊሆን የሚገባው ሰው አስቦ ወይም በቸልኝተኝነት አንድ ወንጀል ካላደረገ በቀር በወንጀል ጥፋተኛ አይሆንም በአንጻሩ አንድ ሰው “የፈጸመው ድርጊት በህግ የሚያስቀጣ ቢሆንም ምንም ጥፋት ሳያደርግ ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ኃይል ምክንያት ወይም በድንገተኛ አጋጣሚ ነገር የተፈጸመ ወይም የደረሰ ሁኖ ሲገኝ በወንጀል ህግ ሊፈረድበት አይገባም በማለት የወንጀል ህጉ አንቀጽ 57/2/ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ የህጉ አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻለው በአንድ ድርጊት ምክንያት አንድን ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ነው ለማለት ከሳሽ የሆነው ዐ/ህግ ድርጊቱ የተፈጸመው ሆነ ተብሎ
ወይም በችልተኝነት መሆኑን ማስረዳት የሚጠበቅበት መሆኑን ነው፡፡ድርጊቱ ሆነ ተብሎ ወይም በቸልተኝነት የተፈጸመ መሆኑን ማስረጃ የሚጠበቅበት መሆኑን ነው፡፡ ድርጊቱ ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት የተፈጸመ መሆኑ ማስረጃ ካልቀረበ ወይም ድርጊቱ ከአቅም በላይ ወይም በድንገተኛ አጋጣሚ የተፈጸመ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ በተከሳሽ በኩል ከቀረበ የተከሰሰውን ሰው በወንጀል ህግ ጥፋተኛ ብሎ መፍረድ ከህጉ መንፈስ ውጪ ነው፡፡ በወንጀል የተከሰሰ ሰው ቸልተኛ ነበር? ወይስ አልነበረም? የሚለው ጥያቄ በወንጀል ህግ በአንቀጽ 59 የሰፈረውን ድንጋጌ መሰረት በማድረግ የሚወሰን ነው፡፡ የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አንድ አሁን ለተያዘው ጉዳይ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው በመሆኑም የህጉን ይዘት እንዳለ ማስቀመጡ ጠቃሚ ነው፡፡ ይኸው፡- ማንም ሰው በቸልተኝነት የወንጀል ተግባር አድርጓል የሚባለው ፡-
/ሀ/ ድርጊቱ በወንጀል ህግ የሚያስቀጣ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል
እያወቀ አይደርስም የሚል ግምት ወይም ባለማመዘን፣ ወይም (ለ) ድርጊቱ በወንጀል የሚያስቀጣ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ማወቅ አለበት ወይም እንዳለበት ባለመገመት ወይም ባለማሰብ ድርጊቱን የፈፀመ እንደሆነ ነው፡፡
በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ሰው በቸልተኝነት ወንጀል ፈፅሟል የሚባለው ውጤቱን እያወቀ ውጤቱ አይደርስም ከሚል መነሻ ድርጊቱን የፈፀመ እንደሆነ ወይም ደግሞ የወንጀል ውጤት የሚያስከትል መሆኑን ባያውቅም ውጤቱን ማወቅ ነበረበት ወይም ጥረት ቢያደርግ ውጤቱን ማወቅ ይችል ነበር ማለት ሲቻል ነው፡፡ በመሆኑም ቸልተኝነት አለ ለማለት ሕጉ የሚጠቀምበት ዋነኛ መስፈርት የተከሰሰው ሰው በድርጊቱና በውጤቱ መካከል ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ያለው ወይም ሊኖረው የሚገባው ግንዛቤ ነው፡፡ ድርጊቱን የፈፀመው ሰው የነበረው ዕውቀትና ግንዛቤ ወይም ሊኖረው የሚገባው ዕውቀትና ግንዛቤ የሚመዝነው የሰውዬው እድሜ ያለው የኑሮ ልምድ የትምህርት ደረጃው፣ ሥራውና የማህበራዊ ኑሮ ደረጃው ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም የሕጉ አንቀጽ 59(1) ይደነግጋል፡፡
ወደ ተያዘው ጉዳይ ስመለስም ተጠሪ በሙያቸው አሽከርካሪ ሆነው እያለና በአሽከርካነት ሙያቸው ደግሞ የሌላውን ሕይወትና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ እያለባቸው የሰሌዳ ቁጥሩ 3- 25709 ኦሮ የሆነውን ቶዩታ ሃይሉክስ መኪና ከዲስ አበባ ከተማ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ እያሽከረከሩ ተገቢውን ጥንቃቂ ከማድረግ ጉድለት መኪናው ሟች ሲያሽከረክር የነበረውን ባጃጅ በመግጨት ሟች የሞተ በመሆኑ ተጠሪ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543(2) ስር የማይጠየቁበትን ሕጋዊ ምክንያት አላገኘንም፡፡ ስለሆነም ተጠሪ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23፣24፣57፣59(ለ) እና 543(2) ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ አንፃር ሲታይ ለወንጀሉ ኃላፊ ሊባሉ የሚገባ ሆኖ ስለአገኘነው ተጠሪ ላይ የተሰጠውን የነፃ መለቀቅ ውሣኔ በወ/መ/ሕ/ስ/ስ/ቁጥር 195(2(ሀ)) መሰረት በመሻር ተጠሪ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543(2) ሰር የተመለተውን ድንጋጌ በታወቀ ቸልተኝነት የተላለፈ ጥፋተኛ ነው ብለናል፡፡
ይህ ከተባለ በኋላ አመልካች ባለመቅረቡ የቅጣት አስተያየት መቀበል አልተቻለም፡፡
ት ዕ ዛዝ
አመልካች የሚቀርብ ከሆነ አስተያየቱን ለመቀበልና ተገቢውን ለመከተል ለ11/02/07 ዓ.ም ተቀጠረ፡፡
የማይነበብ የአምሰት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡
የሰ/መ/ቁ 92141
ጥቅምት 14 ቀን 2007 ዓ/ም
ዳኞች፡-አልማው ወሌ ሱልጣን አባተማም መኮንን ገ/ህይወት ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል
አመልካች፡- የደቡብ ክልል ዐ/ህግ ተጠሪ፡- ዓለማየሁ አስፋው
መዝገቡ የተቀጠረው የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ነው፡፡ በዚህም መሰረት መዝገቡን መርምረን ተከታዩን የቅጣት ውሳኔ ሰጥተናል፡፡
ቅ ጣ ት
1. አንድ ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ሁኖ ከተገኘ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ያለበት ሲሆን ቅጣቱ የሚወሰነው ደግሞ ስራ ላይ በዋለው በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ታይቶ፡፡ ተጠሪ ጥፋተኛ የተባሉበት ድንጋጌ የሚያስቀጣው ከአንድ አመት እስከ አምስት አመት ሊደርስ በሚችል ቀላል እስራት ሁኖ የገንዘብ መቀጮ ደግሞ ከብር 3000.00 (ሶስት ሺህ ብር) እስከ 6000.00 ( ስድስት ሺህ) ብር ነው፡፡
እንደ ቅጣት መመሪያው መወሰን እንዲቻል ደግሞ በተጠሪ ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔከግራ ቀኙ ቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ምክንያቶች ጋር ተገናዝቦ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ በዚህ አግባብ ቅጣቱ ከመሰላቱ በፊት ግን ተጠሪ ጥፋተኛ የተባሉበት ድንጋጌ ክሱ ሲመሰረትም ሆነ በበታች ፍርድ ቤቶች ክርክሩ ሲካሄድ ደረጃ ያልወጣለት ቢሆንም በዚህ ችሎት ጉዳዩ በመታየት ላይ እያለና የጥፋተኛነት ውሳኔ በተሰጠበት ጊዜ በስራ ላይ ያለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 በመሆኑ በዚሁ መመሪያ መሰረት የወንጀል ህጉ አንቀጽ 543 ደረጃ ድንጋጌ ነው፡፡ ተጠሪ ድርጊቱን የፈጸሙት በታወቀ ቸልተኝነት ከመሆኑም በላይ የሟች አስተዋጽኦ ስለሌለና ተጠሪም በሙያቸው ሹፌር በመሆናቸው የወንጀሉ ደረጃ አራት ሆኖ የእስራት ቅጣት መነሻ እርከን 16 ነው፡፡ በዚህ እርከን የፍርድ ቤቱ የተተወው ፍቃደ ስልጣን ከሶስት አመት እስከ ሶስት አመት ከሰባት ወር ነው፡፡ መነሻ ቅጣቱም በዚሁ ሬንጅ ውስጥ የሚያዝ ሲሆን ተጠሪ ላይ መጨረሻ ላይ የሚጣለው የቅጣት መጠን የሚታወቀው ግን የማክበጃ እና የማቅለያ ምክንያቶች ታይተው ስሌቱ ከተሰራ በኃላ ነው፡፡ በዚህም አግባብ የቅጣት መጠኑን ማስላት የግድ ሲሆን በተጠሪ ላይ በዓቃቤ ህግ በኩል የቀረበ የቅጣት ማክበጃው ምክንያት የለም።
አቃቤ ህግ ጥፋተኝነት ውሳኔ ሲሰጥም ሆነ የቅጣት አስተያየቱን የማቅረብ እድሉን ለመጠበቅ ቀጠሮ ሲያዝለት አልቀረበምና፡፡ በሌላ በኩል ተጠሪ ሪኮርድ ያልቀረበባቸው መሆኑን የክርክሩ ሂደት ማሳየቱ ይኼው ምክንያት በማቅለያነት እንዲያዝላቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ማቅለያ ምክንያት ደግሞ በመመሪያው አንቀጽ 23(4) ድንጋጌ መሰረት በተጠሪ ላይ የሚጣለውን ቅጣት ከእርከን 16 ወደ እርከን 15 ዝቅ የሚደረገው ነው፡፡ በዚሁ መጨረሻ እርከን ስር የተመለከተው የቅጣት ዓይነትና የእስራት መጠን ሬንጅ ከሁለት አመት ከዘጠኝ ወር እስከ ሶስት አመት ከስምንት ወር በመሆኑ በዚሁ ለፍ/ቤቱ በተሰጠው ፈቃድ ስልጣን መሰረት የአሁኑ ተጠሪ ለፈጸመው ጥፋት በሁለት አመት ከዘጠኝ ወር ቀላል እስራት ሊቀጣ የሚገባ ሆኖ ስለገኘነው ተጠሪ በጉዳዩ ላይ የታሰረው ካለ ማናቸውም ጊዜ የሚታሰብለት ሁኖ በሁለት አመት ከዘጠኝ ወር ቀላል እስራት ሊቀጣ ይገባል ብለናል፡፡
1. የገንዘብ መቀጮን በተመለከተ ደግሞ ተጠሪ ሊቀጡ የሚገባው ብር በእርከን 4 ሁኖ ስለአገኘነው በብር 3500.00 (ሶስት ሺህ አምስት መቶ ብር) ነው ብለናል፡፡
2. በአመልካች የሰበር አቤቱታ ላይ የተጠሪ መኖሪያ አድራሻ አዲስ አበባ መሆኑ ስለተጠቀሰ የፌዴራል ፖሊስ ከደቡብ ክልል ፖሊስ ጋር በመሆን ተጠሪን አፈላልጎ በመያዝ ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ፣የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤትም ተጠሪን ተረክቦ በዚህ ችሎት ውሳኔ መሰረት ቅጣቱን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ብለናል፡፡ ይጻፍ፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል ፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡