104715 criminal law/ concurrence of offenses/ notional concurrence/ senetincing

አንድ ወንጀል ከመስራት ሃሳብ የሚመነጩ የተለያዩ ድርጊቶች አንድ
ወንጀል ከመስራት ሃሳብ የሚመነጩ ናቸው በማለት ተጠቃለው እንደ
አንድ ወንጀል እንዲተገበሩ ማድረግ የህጉን አግባብ የተከተለ
ስላለመሆኑ፡-
በፅኑ እስራትና በቀላል እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች ተደራርበው
ሲገኙ የቀላል እስራት ወደ ፅኑ እስራት እንደሚለወጥ፤ስሌቱም
የሁለት ዓመት ቀላል እስራት እንደ አንድ ዓመት ፅኑ እስራት
የሚቆጠር ስለመሆኑ፡-
የወ/ሕ/ቁ/ 184 (1)(ለ)

የሰ/መ/ቁ. 104715

 

መጋቢት 02 ቀን 2007 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- መድሕን ኪሮስ

 

አልማው ወሌ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡-   እንደሻው ይልማ ዳዲ - የቀረበ የለም

ተጠሪ፡- የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ አቶ ያሬድ አየለ - ቀረቡ መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ርድ

 

ጉዳዩ የጀመረው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁኑ ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ነው፡፡ ጉዳዩ የወንጀል ክርክር የሚመለከት ሲሆን የአሁኑ ተጠሪ በአመልካች ላይ ሁለት ክሶች አቅርበዋል፡፡ አንደኛው ክስ አመልካች የወ/ሕ/ቁ 692(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ጉዳይ ፈፃሚ ነኝ የፍቺ የምስክር ወረቀት ላሰራልህ በማለት የግል ተበዳይ ወንድወሰን አራጋው እህት ለሆነችው ፍቅርተ አራጋው እና ባለቤቷ በማታለል በሁለት ጊዜ ክፍያ አርባ ሺህ ብር ከወሰደ በኃላ ለልደታ ክፍለ ከተማ ውልና ጋብቻ መዝገብ የተሰጠ በማስመሰል ሀሰተኛ የፍቺ የምስክር ወረቀት የሰጠመሆኑን፤ 2ኛ ክስ ደግሞ የወ/ሕ/ቁ 385(1)(ሀ) የተመለከተውን በመተላለፍ በሀሰት የተዘጋጀ የፍቺ ምስክር ወረቀት በማዘጋጀት ለግል ተበዳይ የሰጠ በመሆኑ፤በምስክር ወረቀቶች ላይ በሚደረግ ወንጀል መከሰሱን የሚያሳይ ነው፡፡

የሥር ፍርድ ቤትም የአመልካች የእምነት ክህደት ቃል በሕጉ አግባብ ከመዘገበ በኃላ አመልካች ክዶ በመከራከሩ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል አዳምጧል፡፡ አመልካች በቀረቡ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ድርጊቱን የፈጸመ መሆኑን በመግለጽ በመመስከራቸው ምክንያት እንዲከላከል ታዞ የመከላከያ ምስክሮችን ቃል ሰምቷል፡፡ የግራ ቀኙ ክርክር በዚህ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኃላ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙ ክርክር እና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ በዓቃቤ ሕግ በኩል የቀረቡ ምስክሮች የአሁኑ አመልካች 40 ሺህ ብር ተቀብሎ በሀሰት የተዘጋጀ የፍቺ ምስክር ወረቀት መስጠቱን የቀረቡት የሰው ምስክሮች እንዲሁም አመልካች ለፖሊስ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 27(2) በሰጠው ቃል ጭምር እንዳመነ፤በአመልካች በኩል የቀረቡ የመከላከያ ምስክሮች የዓቃቤ ሕግ ክስና ማስረጃ አላስተባበሉም በማለት በተከሰሰባቸው ሁለቱም የህግ ድንጋጌዎች በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 149(1) መሰረት ጥፋተኛ ነው በማለት ፍርድ ሰጥቷል፡፡

 

ቅጣትን በተመለከተም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከመዘገበ በኃላ አንደኛው ክስ የወ/ሕ/ቁ 692(1) የወንጀል ደረጃ፣ መነሻ የእስራት ቅጣት እና መቀጮ እርከን የወጣለት በመሆኑ የወንጀሉ ደረጃ 5 ተጓዳኝ የእስራት ቅጣት እርከን 14 መቀጮ ደግሞ 3 በመሆኑ ፍርድ ቤቱም መነሻ ቅጣቱ 2 ዓመት ከ 9 ወር እና 2,500.00 ብር መቀጮ እንዲሆን ወስኗል፡፡ 2ኛ ክስ የወንጀል


ደረጃ እና የእስራት ቅጣት መነሻ እርከን ያልተዘጋጀለት በመሆኑ የወንጀሉ ደረጃ መካከለኛ ደረጃ በመመደብ አንድ ዓመት ቀላል እስራት በመነሻነት ይዟል፡፡ ሁለቱም መነሻ ቅጣቶችን በመደመር በእርከን 17 ሥር በመክተት ፍቅድ ሥልጣኑ 3 ዓመት ከ 3 ወር እስከ 3 ዓመት ከ 11 ወር ፅኑ እስራት እና 3000,00 ብር መሆኑን በመግለጽ በዓቃቤ ሕግ በኩል የቅጣት ማክበጃ ምክንያት አልቀረበም፡፡ በአመልካች በኩል ሦስት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች በመቀበል በእርከን 14 ሥር 2 ዓመት ከ 9 ወር እና ብር 600.00 እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

አመልካች የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝ ቅሬታ ተቀባይነት የለውም ተብሎ ውድቅ ተደርጓል፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንን በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ያስቀርባል የተባለ በመሆኑ ግራቀኙ የጽሑፍ ክርክር ያደረጉ ሲሆን አመልካች በሰበር ቅሬታው የጠቀሰው መሠረታዊ ነጥብ የወንጀል ድርጊት በሁለት የህግ አንቀጾች የሚያስጠይቅ አይደለም፤ የቅጣት አወሳሰን ሥርዓቱም ቀላል እስራት ወደ ጽኑ እስራት ሳይለወጥ የተደመረ በመሆኑ የወ/ሕ/ቁ 184(1)(ለ) ያገናዘበ አይደለም የሚል ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው መልስ የማታለል እና የሀሰት ምስክር ወረቀት ማዘጋጀት ሁለቱም ድንጋጌዎች እራሳቸው የቻሉ እና አንደኛው ሌላኛውን የላካተተ በመሆኑ በሁለቱም የህግ አንቀጾች ጥፋተኛ መባሉ በአግባቡ ነው፡፡ ቅጣት በተመለከተ የጽኑ እና ቀላል እስራት በወ/ሕ/ቁ 184 (1) (ለ) መሰረት ያልተሰራ በመሆኑ በህጉ አግባብ ተስተካክሎ በእርከን 12 ሥር ተሰልቶ ቢወሰን ተቃውሞ እንደሌለው አመልክቷል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት የሥር ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል፡፡ እንደመረመርነውም በዚህ ችሎት መታየት ያለባቸው መሰረታዊ ጭብጦች፡- አንደኛ አመልካች ተጠሪ በቀረበው ክስ የተጠቀሱ የህግ ድንጋጌዎች ሥር በሁለቱም ጥፋተኛ መባሉ በሕጉ አግባብ ነው ወይስ አይደለም?ሁለተኛ የጥፋተኝነት ውሳኔው በአግባቡ ከሆነ የቅጣት አወሳሰን ሥርዓቱስ የወ/ህ/ቁ 184(1) (ለ) እና የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2005 ያገናዘበ ነው ወይስ አይደለም የሚሉ ናቸው፡፡

የመጀመርያው ጭብጥ በተመለከተ፡- በመሰረቱ አንድ ድርጊት አንድ ወንጀል ከመሥራት ሐሳብ የመነጨ መሆኑ በሕጉ አገላለጽ የተረጋገጠ ከሆነ በአንድ ድንጋጌ ሥር ጉዳይ የሚታይ ስለመሆኑ ከወ/ሕ/ቁ 61 መሰረታዊ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ነው፡፡ በሌላ በኩል ተደራራቢ ወንጀሎች መፈጸማቸው ሲረጋገጥ ደግሞ ለሁለት እና ከሁለት በላይ  ለሆኑ ድንጋጌዎች አጥፊው በሕጉ አግባብ የሚያስጠይቀው ስለመሆኑ በወ/ሕ/ቁ 60፣63 ተመልክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንድ ወንጀል ከመሥራት ሐሳብ የሚመነጩ ድርጊቶች ሕግ አውጪው ራሳቸው ችለው ወንጀል እንደሚያቋቁሙ ለወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል የደነገገ ከሆነም ወንጀል ፈፃሚው በሁለቱም የሕግ አንቀጾች እንደሚቀጣ ግልጽ ነው፡፡ ወደተያዘው ጉዳይ ስንመጣ አመልካች በአንደኛው ክስ የማታለል ወንጀል በ2ኛ ክስ ደግሞ ሐሰተኛ የምስክር ወረቀት ለግል ተበዳዮች መስጠቱን የሚገልጽ ነወ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በማታለል ድርጊቱ መቀጣቱ እንደተጠበቀ ሁኖ በ2ኛ ክስም በተደራቢነት ሊጠይቅ እንደሚገባ በወ/ሕ/ቁ 699 በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም አመልካች ሁለቱም ድርጊቶች በአንድ ድንጋጌ ሥር የሚጠቃለሉ ናቸው በማለት ያቀረበው ክርክር የህግ መሰረት የለውም፡፡

ሁለተኛው ጭብጥ በተመለከተ፡- አመልካች በሁለት የህግ ድንጋጌዎች ጥፋተኛ ተብሏል፡፡ የሥር ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለመጀመሪያው ክስ የጽኑ እስራት አማራጭ የተወሰደ ሲሆን ለሁለተኛ ክስ ደግሞ የአንድ ዓመት ቀላል እስራት ወስደዋል፡፡ በጽኑ እስራት እና ቀላል እስራት የሚያስቀጡ   ወንጀሎች   ተደራርበው   ሲገኙ   የቀላል   እስራት   ወደ   ጽኑ    እስራት


እንደሚለወጥ፤ስሌቱም የሁለት ዓመት ቀላል እስራት እንደ አንድ ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚቆጠር በወ/ህ/ቁ 184 (1) (ለ) ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አንፃር የሥር ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሁለተኛው ክስ (ወ/ሕ/ቁ 385) የአንድ ዓመት ቀላል እስራት የወሰነ ቢሆንም ወደ ጽኑ እስራት ሳይለወጥ የሁለቱም ድንጋጌዎች መነሻ ቅጣት በመደመር መወሰኑ የወንጀል ሕጉ እና የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ያላገናዘበ ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሥር ፍርድ ቤት በሥር ፍርድ ቤት የተፈፀመው የሕጉን አተገባበር ስህተት ሳያርም ማጽናቱ  መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በእነዚህ ሁለቱ ምክንያቶች በሥር ፍርድ ቤቶች የተፈጸመው የሕግ አተገባበር ስህተት በከፊል መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈጸሙን የሚያሳይ በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ በመሆኑም ከላይ በተመለከተው የህግ ድንጋጌ መሰረት የሁለቱም ድንጋጌዎች መነሻ ቅጣት ሲደመር 3 ዓመት ከ 3 ወር ጽኑ እስራት እንደሚሆን ከቅጣት አወሳሰን መመሪያው የቅጣት ስሌት የምንረዳው ነው፡፡ በወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያው አንቀጽ 26(3) መሰረት መነሻ ቅጣቱ በመወሰንና በመደመር በቅጣት እርከኑ ሠንጠረዥ የሚያርፍበት የቅጣት እርከን መለየት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህ መሰረት መነሻ ቅጣቱ በእርከን 15 የሚካተት ሲሆን በአመልካች በኩል በሥር ፍ/ቤት ተቀባይነት ያገኙ ሦስት የቅጣት ማቅለያዎች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ በቅጣት አወሳሰን መመሪያው አንቀጽ 23 (1) መሰረት በእያንዳንዱ ማቅለያ ምክንያት እርከን አንድ ወደታች ይቀንሳል፡፡ እንዲህ በመሆኑም ቅጣቱ በእርከን 12 ከተመለከተው ከ2 ዓመት እስከ 2 ዓመት ከ 6 ወር ባለው ፍቅድ ሥልጣን ፍርድ ቤት የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡

ቅጣቱ ሲወሰን የወንጀል ሕጉ ዓላማ ግብ በአንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ የወንጀል ፈፃሚው ግላዊ ሁኔታዎች፤ የወንጀል አፈፃፀም ሁኔታ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በተያዘው ጉዳይ በአመልካች ላይ የሚወሰነው ቅጣት የሚያስጠነቅቀው፤ የሚያስተምረው፤ሌላ ወንጀል እንዳይፈፅም የሚያደርገው መሆን አለበት፡፡ በሌላ በኩል ማሕበረሰቡም በቂ ትምህርት በመውሰድ ከወንጀል ድርጊት እንዲርቅ የሚያደርገው መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም ከላይ የገለጽነው አጠቃላይ የቅጣት አወሳሰን መርሆዎች መሰረት በማድረግ አመልካች በዚህ ጉዳይ ከአሁን በፊት የታሰረበት ካለ በቅጣቱ የሚካተት ሆኖ በ 2 ዓመት ጽኑ እስራት እና 600.00 ብር መቀጮ እንዲቀጣ ወስነናል፡፡

 ው ሳኔ

 

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 143927 በ5/06/2006 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወ/ደ/መ/ቁ 102208 በ 30-10-2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 195(2) (ለ) (2) ተሻሽሏል፡፡ ይፃፍ፡፡

2. አመልካች በተከሰሰባቸው ሁለቱም ድንጋጌዎች ጥፋተኛ መባሉ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡ በዚህ ረገድ የሥር ፍ/ቤቶች የሰጡት የውሳኔ ክፍል ጸንቷል፡፡

3. የሥር ፍርድ ቤቶች በአመልካች ላይ የወሰኑት እስራት ቅጣት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ.ቁ 195 (2) (ለ) (2) በማሻሻል በሁለት ዓመት ጽኑ እስራት እና 600.00 ብር መቀጮ እንዲቀጣ ወስነናል፡፡ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤትም በዚህ ችሎት በተሻሻለው ቅጣት መሰረት ተቆጣጥሮ እስራቱን  እንዲያስፈጽም ታዟል፡፡ ይፃፍ፡፡

 

4. መዝገቡ ውሳኔ ያገኘ በመሆኑ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡ የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡