106610 Labor dispute Payments termination of contract of employment

Labor dispute

Payments

termination of contract of employment

Proclamation no 377/96 art. 27/1/b, 25

 

አንድ አሰሪ ሰራተኛው ያቀረበውን የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ተቀብሎ ሰራተኛውን ካሰናበተ በኋላ የተለያዩ የክፍያ ጥያቄዎች በሰራተኛው ሲቀርብለት ወደኋላ ተመልሶ የስራ ውል ማቋረጫ ምክንያት አግኝቻለሁ በማለት ሌላ ደብዳቤ በመጻፍ ለሰራተኛው የሚገባውን ክፍያ አልፈፅምም ማለት አግባብነት የሌለው ስለመሆኑ፣ 

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 27/1/ለ/፣25 

 

//106610

ግንቦት 14 ቀን 2007

ዳኞች - አልማው ወሌ

ዓሊ መሀመድ

ሱልጣን አባተማም

ሙስጠፋ አህመ

ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- አቶ ካብራክ ተኮላ - ጠበቃ ጋር ቀረበ

ተጠሪ -የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት ሎጆስቲክስ/ ቀረበ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ ነበሩ፡፡ አመልካች ባቀረቡት ክስ በተጠሪ ድርጅት ከታህሳስ 26/2000 - ጥር 29/2005 . ድረስ 5 አመት 1 ወር ስሰራ ቆይቼ ስራዬን በራሴ ፍቃድ ብለቅም፤ የስንብት፤ ለዘገየበት እና አበል አልተከፈለኝም በማለት እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተጠሪም በሰጠው መልስ አመልካች ያለደሞዝ የወሰዱት እረፍት ከተጠናቀቀ ከህዳር 17/2005 / ጀምሮ ወደ ሥራ ያልገቡ መሆኑን በመረዳቱ ከህዳር 17 /2005 / ጀምሮ ውላቸው መቋረጡን እና 5 አመት ያልሞላቸው በመሆኑ ያለማስጠንቀቂያ ስለሆነ ስንብት አይገባቸውም፤ ይገባቸዋል ከተባለም የማስጠንቀቂያ ግዜ 1 ወር ደሞዝና የቦንድ መግዣ ተቀንሶ ሊከፈላቸው ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን  ያየው ፍርድ ቤትም ተጠሪ የአመልካችን የስራ መልቀቅ ጥያቄ 29/6/2005 ጀምሮ ከተቀበለ እና ካሰናበታቸው በኋላ የስራ ውል ማቋረጫ ምክንያት መፈጸሙን አረጋግጫለሁ በማለት ሌላ ደብዳቤ በመጻፍ ክፍያ አልፈጽምም የሚልበት ምክንያት አይኖርም በመሆኑም 5 አመት 1 ወር የስንብት ክፍያ የቦንድ ተቀንሶ ተጠሪ ሊከፍል ይገባል በማለት ወስኗል፡፡ በቀጣይነት ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤትም ተጠሪ አመልካችን የመልቀቂያ ጥያቄ ተቀብሎ ቢያሰናብተውም፤ ድርጊቱ ስህተት ነው ብሎ ካመነበት ስህተቱን ለማረም ይችላል፤ አመልካችም ከህዳር 17 ቀን 2005 ጀምሮ በስራ ላይም አልተገኙም፤ በመሆኑም ተጠሪ ውል ማቋረጫ ምክንያት አግኝቻለው በማለት የስንብት አልከፍልም ማለቱ ባግባቡ ነው፤ በማለት የስር ውሳኔን ሽሮታል፡፡ የአመልካች አቤቱታም የቀረበው ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡ በመሆኑም አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ ቅሬታቸውን ሲገልጹ፤ ስራዬን የለቀቅኩት በጥር 29/2005 በጻፍኩት ደብዳቤ ሲሆን ተጠሪም የስንብት ደብዳቤ በሚያዝያ 11/2005  ሰጥቶኛል፡፡ ይሁን እንጂ በ17/03/2005 ነበር ወደ ስራ መመለስ የነበረብህ፤ ግንቦት 8/2005 ስህተት መፈፀሜን ተረዳሁ በማለት ጥር 29/2005 ያስገባውን ደብዳቤ አልቀበልም  በማለት ከእረፍት በኋላ ወደስራ አልገባህም በማለት ከ ህዳር 17/2005 ጀምሮ ነው፤ መባሉ አግባብ አይደለም፡፡ የተጠቀሰውም የሰበር ውሳኔ ቁ 45889 ከተያዘው ጉዳይ አይመሳሰልም፡፡ ሰራተኛውና አሰሪው የስራ ውላቸው ጸንቶ ባለበት የሚደረግ እርምት እንጂ፤ ከስራ በገዛ ፍቃዱ ለለቀቀ ሰራተኛ ኪሊራንስ ተሰጥቶት ከ4 ወር በኋላ ስህተትን ማረም አይደለም፡፡ በመሆኑም በፍቃዴ ከተሰናበትኩ በኋላ ግንቦት 8/2005 የተጻፈውን፤ የተጠሪን ደብዳቤ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተቀብሎት፤ አመልካች ከህዳር 17/2005 በኋላ ወደስራ ያለመግባቱ ተረጋግጦ እርማት መደረጉ ባግባቡ ነው በማለት የስር ፍርድ ቤት መሻሩ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ጠይቋል፡፡

በዚህም መሰረት ችሎቱም አመልካች የሥራ መልቀቂያ ለተጠሪ ሚያዝያ 11/2005 ዓ.ም ከሰጠው በኋላ፤ እንደገና ያለደሞዝ የወሰድከው ዕረፍት የተጠናቀቀው በ17/3/2005 ሆኖ ወደሥራ አልገባህም በማለት ከዚሁ ግዜ ጀምሮ የስራ ውሉን ማቋረጡ፤ እና ጥር 17/2005 ክሊራንስ እንዲያዞር ከመፍቀዱ አኳያ ስንብቱ ህጋዊ ነው መባሉን በጭብጥነት በመያዝ የግራቀኙ በጽሁፍ መልስና የመልስ መልስ እንዲቀባበሉ በማድረግ አከራክረዋል፡፡

ተጠሪ በሰበር መልሱ የሚከራከረው፡- አመልካች እረፍታቸውን ጨርሰው ካልተመለሱ ማስታወቂያ በማውጣት ጥሪ በማድረግ ካልመጡ ውል ማቋረጡ የተሻለ ይሆን ነበር፤ ይህ ያለመደረጉ ምንም መብት አይፈጠርላቸውም እንጂ፤ ሌላው ኪሊራንስ የተሰጣቸው አስተዳደሩ ስራ ላይ ነበሩ በሚል እምነት ነው፤ አመልካች ወደ ስራ መመለስ ከነበረባቸው 17/3/05 ጀምሮ እስከ ጥር 30/2005 ድረስ ወደስራ አልተመለሱም፤ በአዋጅ 377/96 አንቀጽ 27/1/ ለ መሠረት ከ5 ቀን በላይ ስለቀሩ መሰናበታቸው ባግባቡ ነው፤ በመሆኑም ተጠሪ የፈጸመውን ስህተት ባወቀበት ጊዜ ማረሙና አመልካችን ማሰናበቱ አግባብነት ያለው በመሆኑ ስንብቱ ህጋዊ ነው መባሉ የሚነቀፍ ባለመሆኑ ሊጸና ይገባል በማለት ይከራከራል፡፡ አመልካች በበኩሉ፡- ከተጠሪ ጋር በአዋጅ 377/96 አንቀጽ 25 መሰረት በስምምነት የስራ ውላችንን ካቋረጥን በኋላ እና ተጠሪ ጥያቄዬን ተቀብሎ፤ ክሊራንስ አዞሬ እንድወጣ ከፈቀደና ውሉ ከተቋረጠ ወድያ የሚታረም ነገር አይኖርም በማለት የስር ክርክሩን በማጠናከር የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ሊሻር ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

ባጠቃላይ የክርክሩ አመጣጥ ከላይ የተገለጸውን ይመስላል፡፡ እኛም የግራቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌ አንጻር መዝገቡን መርምረናል፡፡

በመሆኑም ከተያዘው ጭብጥ አንጻር የክርክሩን አጠቃላይ ሂደትና የስር ውሳኔዎችን እንዳየነው አመልካች በራሳቸው ፍቃድ የስራ መልቀቂያ በመጠየቅ ተጠሪም በጥያቄው መሰረት እንዲፈጸም ፈቅዶና አመልካችን ካሰናበተ በኋላ፤ ያለማስጠንቀቂያ የሚያሰናብት ምክንያት አገኘሁ በማለት አስፈላጊውን ክፍያ አልከፍልም በማለቱ ነው፡፡ እንግዲህ ተጠሪ የሚለው አመልካች እረፍት 17/2/2005 ወስደው ወደስራ መመለስ የነበረባቸው 17/3/2005 ሆኖ ሳለ በቦታው ተገኝተው ስራ ባለመጀመራቸው  እና በስህተት በጥር 30/2005 የቀረበውን የአመልካች መልቀቂያ ጥያቄ ተቀብለን ሚያዝያ 11/2005 እንዲፈጸም ብናደርግም ስህተት መሆኑን በመረዳታችን ከህዳር 17/2005 ጀምሮ ማሰናበታችን ባግባቡ ነው የሰበር ሰሚው ውሳኔ 45889 አሰሪው ስህተቱን ማረም የሚችል መሆኑን ወስኗል በማለት ተከራክረዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ጉዳዩን ያየው ፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአመልካችን የስራ መልቀቂያ ተቀብሎ ካሰናበተው በኋላ ሌላ ምክንያት አገኘሁ በማለት ድጋሜ ደብዳቤ መጻፍ ተገቢነት የለውም በማለት የስንብት ክፍያ ለአመልካች እንዲከፈላቸው ቢወስንም፤ የከፍተኛው ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ካየው በኋላ ተጠሪ ስህተቱን ማረም ይችላል ሲል የአመልካች ስንብት ባግባቡ ነው በማለት የስር ውሳኔን ሽሮታል፡፡ በዚህም መሰረት ተጠሪ ሊያርሙት የሚችሉት ስህተት የትኛውን አይነት ስህተት ነው የሚለውን ስናይ የሰበር ውሳኔ . 45889 ከተያዘው ጉዳይ የማይገናኝ በመሆኑ መከራከሪያ ሊሆን አይገባም፡፡ በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ የአመልካችን የመልቀቂያ ጥያቄ ተቀብሎና ለአግባብነቱም ምላሽ ሰጥቶ ካሰናበታቸው እና የክፍያ ጥያቄ ሲቀርብለት ከወራት በኋላ ወደኋላ ተመልሶ ስህተት መፈጸሜን ተረዳሁ ማለቱ ባለቀ ጉዳይ ስህተት ማፈላለግ ካልሆነ በቀር፤ ተጠሪን የመሰለ ድርጅት አስተዳደራዊ ስራውን ባግባቡ ባለመወጣት በፈጸመው ጉዳይ የአዋጁን 377/96 አንቀጽ 27/1/// ጠቅሶ ለመከራከር መሞከሩ አግባብነት የለውም፡፡ ምክንያቱም ተጠሪ እረፍት የሰጠውን ሰራተኛ በተባለው መመለሻ ጊዜ ካልገባ ምን ሊደረግ እንደሚገባ ሳያውቅ የአመልካችን መልቀቂያ ያስተናግዳል ተብሎም የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ባጠቃላይ የመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት የአመልካችን ጥያቄ በፍሬ ነገር ደረጃ በማረጋገጥ ክፍያ እንዲከፈላቸው የወሰነው ውሳኔ በከፍተኛው ፍርድ ቤት አግባብነት የሌለው አሰሪ ስህተቱን ማረም ይችላል ተብሎ የተወሠነው አስገዳጅ ውሣኔ ተጠቅሶ መሻሩ ሊታረም የሚገባው ነው ብለናል፡፡

በመጨረሻም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከስንብት በኋላ የተሰጠውን የውል ማቋረጫ ምክንያት በመቀበል ተጠሪ ስህተቱን ማረም ይችላል በማለት የስር ውሳኔን መሻሩ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

1.    የፌዴራል የከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ..139381 በቀን 13/12/06 / የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ. 09937 ህዳር 16/2006 የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የሰጠው ውሳኔ ተሽሯል፡፡

2.    የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለአመልካች የስንብት ክፍያ ብር 7,540.50 ይከፈላቸው በማለት የወሰነው ጸንቷል፡፡

3.    የግራቀኙ የወጪ ኪሳራቸውን ይቻቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ውሳኔ በማግኘቱ ተዘግቷል፡፡

ማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት