105834 Labor dispute Review of decision of discipline committee

Labor dispute

Review of decision of discipline committee

Proclamation no. 377/2004 27(1)/g/ and art. 12/2/(7)

በየመስሪያ ቤቱ የሚቋቋሙ የዲሲፕሊን ኮሚቴዎች በህግ አግባብ የሚቋቋሙና የሰራተኛው ጥቅም ያለአግባብ እንዳይጎዳ ተገቢው መጣራት ተደርጎ እርምጃ እንዲወሰድ እገዛ የሚያደርጉ ናቸው ተብሎ የሚታመን ስለሆነ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ ዋጋ ሊያጣ የሚገባው ተገቢው ማስረጃ ቀርቦ ህጋዊ ያለመሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ስለመሆኑ፣ 

 

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 27 ንዑስ አንቀፅ 1/ሸ/ እና አንቀፅ 12/2/(7) 

 

 

//. 105834  

ሚያዚያ 28 ቀን 2007 .

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

ሡልጣን አባተማም

ሙስጠፋ አህመድ

ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ኮንፌደሬሽን

ጠበቃ እሸቴ ጓንጉል - ቀረቡ፡፡  

ተጠሪ፡- / እመቤት ኤርሚያስ -

መዝገቡ መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ጉዳዩ የቀረበው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአመልካች የስንብት እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመጽናቱ በውሳኔው ላይ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልካች ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 “መሰረት ያደረገ የግል የስራ ክርክር ሁኖ አንድ ሰራተኛ በስራ ላይ የዲስፕሊን ጥፋት ፈፅሟል ተብሎ ከስራ ያለማስጠንቀቂያ የሚሰናበትበትን የሕግ አግባብ የሚመለከት ነው፡፡

በስር ፍርድ ቤት የቀረበው የተጠሪ ክስ በአመልካች ማህበር ውስጥ በወር ብር 4,500.00 (አራት ሺህ አምስት መቶ) እየተከፈላቸው በሂሳብ ሰራተኝነት የስራ መደብ ከመስከረም 05 ቀን 1990 . ጀምሮ ሲያገለግሉ ቆይተው አመልካች ማህበር የዲስፕሊን ጥፋት ፈጽመዋል በሚል ምክንያት በሕገ ወጥ መንገድ ከስራ ያሰናበታቸው መሆኑን ዘርዝረው ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ የካሳ፣የስራ ስንብት፣የማስጠንቀቂያ ጊዜ እና ክፍያ ለዘገዬበት ክፍያ እንዲከፈላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን ያሳያል፡፡ የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም ተጠሪ የተለያዩ የዲስፕሊን ጥፋቶችን መፈፀማቸውን በመግለጽ ጥፋቶችም፡- ተጠሪ የስራ መደባቸው አካውንታት ሆኖ እያለ ከስራ ድርሻቸው ውጪ መጠኑ ብር 9000.00 (ዘጠኝ ሺህ ብር) የሆነ ገንዘብ ከአምስት ወራት በላይ በእጃቸው ላይ ያቆዩ መሆናቸውን፣ተጠሪ ይህን በእጃቸው ያቆዩትን ብር 9000.00 (ዘጠኝ ሺህ ብር) በስራ ላይ እንደዋለ በማስመሰል የተሳሳተ ሪፖርት ማቅረባቸውንና ይህንኑ በእጃቸው የቆየውን ገንዘብ ባንክ እንዲያስገቡ ሲታዘዙ ትዕዛዝ ያለመቀበላቸው፣የስራ አመራር ቦርድ ሳይፈቅድ የአመልካች ማህበር ተ/ዋና ስራ አስኪያጅ ለሆኑት አቶ ተሾመ ዴሬሳ በየወሩ ከሰኔ ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 2005 ዓ.ም ድረስ ብር 430.00 በድምሩ ለአራት ወራት ብር 1720.00 (አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሃያ ብር) መክፈላቸው፣ለፌዴሬሽኑ አትክልተኛ ለአቶ መዝገቡ ገላው ሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም ብር 100.00 (አንድ መቶ ብር) መክፈላቸው፣ለአመልካች ማህበር የሕዝብ ግንኙነት ሰራተኛ አቶ ደረሰ ታደሰ ከሰኔ ወር 2004 ዓ.ም እስከ መስከረም 2005 ዓ.ም ብር 130.00 በየወሩ በድምሩ 520.00 (አምስት መቶ ሃያ ብር) ጭማሪ በማድረግ መከፈላቸው፣በአመልካች የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አስተባባሪዎች እጅ ብር 9000.00 (ዘጠኝ ሺህ ብር) የያዘ ሰደን ከሚያዝያ 19 ቀን 2004 ዓ.ም እስከ ህዳር 14 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ሳያወራረድ እንዲቆይ በቃል መፍቀዳቸው፣ተጠሪ በተለያዩ ግለሰቦች ክፍያ ሲፈፅሙ ተቀናሽ የሚደረግ ዊዝሆልዲንግ ታክስ 2 %) ከሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም እስከ መስከረም ወር 2005 ዓ.ም ድረስ ብር 17,092.70 (አስራ ሰባት ሺህ ዘጠና ሁለት ብር ከሰባ ሳንቲም) በወቅቱ ለግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ገቢ ያለማድረጋቸው፣ህዳር 04 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ከአስተደደርና ፋይናንስ ኃላፊ ቢሮ በኮምፒዩተር ላይ ተሰክቶ የነበረ 4GB የፍላሽ ዲስክ ያለ አመልካች ማህበር ፈቃድ መውሰዳቸው፣የቅጥር ውል ላልተፈፀመላቸውና ላልታደሰላቸው ሰራተኞች ደመወዝ መክፈላቸው፣ግዥዎች በእቅድ ከተያዘው በጀት በላይ እንዲፈፀሙ ማድረጋቸው፣ከፋይናንስ ውጪ ሰነድ ማዘጋጀታቸው፣ከአለም አቀፍ የሥራ ድርጅት የተገኘውን ብር 184,206.00 “ወርልድ ለርኒግ” ከተባለ ድርጅት የተገኘ በማስመሰል በጀት ምንጩን በማሳሳት መመዝገባቸው፣አመልካች ድርጅት ምንም እዳ ሳይኖርበት በስራ ማስኪያጃ 19,000.00 (አስራ ዘጠኝ ሺህ ብር) ከተለያዩ ወጪዎች ብር 162,000.00 (አንድ መቶ ስልሳ ሁለት ሺህ) እዳ ያለበት መሆኑን አስመስለው መግለፃቸው፣ተጠሪ የአመልካችን ብር 500.00 እዳ እያለባቸው ለአንድ አመት ያህል ገቢ ያለማድረጋቸው ስለመሆናቸው ዘርዝሮ እና ከእነዚህ ጥፋቶች በዲስፕሊንና ኮሚቴ ውሳኔና በኦዲት ሪፖርት መረጋገጣቸውን ጠቅሶ የስራ ስንብቱ ሕጋዊ ነው በማለት ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ የፌዴሬሽን ተ/ዋና ስራ አስኪያጅና አትክልተኛ ደመወዝ እንዲጨመር ከሚመለከታቸው አካላት የደረሳቸውን የደመወዝ ዝርዝርና በአመልካች መስሪያ ቤት ይገኛል የተባለውን ሰነድ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ሰነዱ ከቀረበለትና ከተጠሪ እጅ ያለውን ቀሪ ሁሉ ከተመለከተ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪ የፈፀሙት የዲስፕሊን ጥፋት የለም ወደ ሚለው ድምዳሜ ደርሶ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው በማለት የካሳ ክፍያ፣የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣ክፍያ ለዘገዬበት ክፍያና የሁለት አመት ፈቃድ እንዲከፍላቸው፣የስራ ስንብት ግን የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚና የተከፈላቸው በመሆኑ አይከፈላቸው ሲል ወስኗል፡፡ 

አመልካች ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው፡፡ የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈል ተብሎ በተወሰነው የውሳኔ ክፍል ቀጥተኛ የይግባኝ አቤቱታ፣ተጠሪ ደግሞ በድርጅቱ ከአስራ አምስት አመት በላይ አገልግለው ለሰባት አመታት ለአገለገሉት ጊዜ የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ መሆናቸው ለቀሪዎቹ አመታት የሥራ ስንብት ክፍያ እንዳገኙ መደረጉና የአመት ፈቃድም ሲተላለፍ የቆየ ሁኖ እያለ የሁለት አመት ብቻ ታስቦ እንዲከፈላቸው ተብሎ መወሰኑ ያላግባብ ነው  በሚል መስቀለኛ የይግባኝ አቤቱታ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አጽንቶታል፡፡

የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ሲሆን የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ተጠሪ ስራቸውን ሲሰሩ ከአስራ አምስት በላይ የዲስፕሊን ግድፈት የፈፀሙ ስለመሆኑ በሰነድ ማስረጃዎች ተረጋግጦ እያለ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮም ተጠሪ በስራቸው ላይ ጥፋት የፈፀሙ ስለመሆኑ በኦዲት ሪፖርትና በአመልካች መስሪያ ቤት የዲስፕሊን ኮሚቴ ተጣርቶ ተረጋግጦ ሳለ የሥር ፍርድ ቤቶች ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው በማለት የተለያዩ ክፍያዎች ለተጠሪ እንዲከፈሉ የመወሰናቸውን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርበውም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም የስር ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ 

ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም ጉዳዩን ከግራ ቀኙ ክርክር፣ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አንጻር ጉዳዩ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አኳያ እንደሚከተለው መርምረናል፡፡

ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች ተጠሪን አሰናበትኩ የሚለው አስራ አምስት ያህል የዲስፕሊን ግድፈቶችን ተጠሪ ስለመፈጸማቸው ተረጋግጧል በሚል ምክንያት ሲሆን ይህንኑ ለማስረዳትም የፌዴሬሽኑ የአስተዳደር ማኑዋል በሚያዘው መሰረት የተቋቋመው የዲስፕሊን ኮሚቴ የሰጠውን ውሳኔና የኦዲት ሪፖርት ሰነድ በማስረጃነት አቅርቧል፡፡ የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ሆነ ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአመልካች በኩል የቀረቡትን እነዚህን የሰነድ ማስረጃዎች የማስረጃነት ዋጋ ሳይሰጡ አልፈዋል፡፡ የበታች ፍርድ ቤቶች የዲስፕሊን ኮሚቴውን የውሳኔ ሰነድ ያልተቀበሉት ተጠሪ ሰነዱን ባለማመን ፍርድ ቤት ክስ ማቅረባቸውን በመጥቀስ ሲሆን የኦዲት ሪፖርቱን ደግሞ የስራ ስንብቱ ከተደረገ በኃላ የተጠቃለለ በመሆኑ የተጠሪ የዲስፕሊን ግድፈት መኖሩ ታውቆ ስንብቱ ተደርጓል በማለት የሚያስችል አይደለም የሚለውን አብይ ምክንያት ከአሰፈሩ በኃላ በተጨማሪነት የኦዲት ሪፖርቱ ከቀድሞ ሰራተኛ ያልተሰራ ስራ መኖሩን ገልጾ በተተኪ ሰራተኛ ሊሰራ እንደሚገባ መገለጹ ከሂሳብ አሰራር ጉድለት ጋር ተያያዥ የሆኑትን ሰራተኛ ማንነት የማይገልጽና የማያብራራ ነው፣ኦዲት ሪፖርቱ በተራ ቁጥር 4.8፣4.3 እና 4.9 የተዘረዘሩት ካልሆነ በስተቀር ቀሪዎቹ የኦዲት ሪፖርት ይዘቶች ከቀረቡት መከራከሪያ ነጥቦች ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ተያያዥነት የሌላቸው ናቸው፣የኦዲት ሪፖርት ተራ ቁጥር 5 ስር የሂሳብ ሰራተኛዋ የብቃት ችግር ያለባቸው መሆኑን መግለጹም ለስንብቱ ምክንያት የተባለው የዲስፕሊን ጉድለት በመሆኑ አግባብነት የሌለው ነው የሚሉትንና የደመወዝ ጭማሪ አከፋፈል በተመለከተ ደግሞ ተጠሪ በሚመለከተው አካል ተፈቅዶ የፈፀሙት መሆኑን አረጋግጠዋል የሚሉ ምክንያቶችን አስፍሮ ነው፡፡ 

በመሰረቱ አንድን ፍሬ-ነገር ለማስረዳት በተከራካሪ ወገኖች ተቆጥሮ የቀረበ የሰነድ ማስረጃ በህጉ ተቀባይነት የለውም (inadmissible) ወይም ከተያዘው ፍሬ-ነገር ጭብጥ ጋር አግባብነት የለውም እስካልተባለ ድረስ ሰነዱ በማስረጃነት ተመርምሮ እንዲሁም ከሌሎች ማስረጃ አይነቶች ጋርም በአንድነት ታይቶና ተመዝኖ የሚገባው ዋጋ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 138 ስር እንደተመለከተው በህግ አግባብ የተቆጠረው ማስረጃ በዝምታ የሚታለፍበት ወይም ከሕግ ውጪ የማስረጃነት ዋጋ ሳይሰጥ ውድቅ የሚሆንበት አግባብ የለምና፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ይህንኑ በፍትሐብሄር ስነ ስርዓት ሕጉ የተመለከተውን የማስረጃ አቀራረብና አቀባበል ደንብ ያለፈው በአመልካች በኩል የቀረበው የዲስፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ የሰነድ ማስረጃ በተጠሪ እምነት ያላገኘና ፍርድ ቤት ክስ ያቀረበበት ጉዳይ ነው በሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ አመልካች ያቀረበው ይኼው ሰነድ የፌዴሬሽኑ የአስተዳደር ማኑዋል በሚያዘው መሰረት በተቋቋመው ኮሚቴ ተጠሪ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡበት ተደርጎና ተገቢነት አላቸው የሚሏቸው ማስረጃዎች ቀርበው በተጠሪ ተፈጸሙ የተባሉትን ጥፋቶች መኖራቸውን፣ተጠሪም በዲስፕሊን ኮሚቴው ጥፋቶችን ማመናቸውን በማረጋገጥ የተሰጠ መሆኑን የሰነዱ ይዘት በግልፅ ያሳያል ፡፡ ይህ ማስረጃ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው  ማስረጃ ሲሆን የማስረጃነት ዋጋ ሊያጣ የሚችለው ተጠሪ በፍርድ ቤት ክስ በማቅረባቸው ወይም ሰነዱን ባለማመናቸው ሳይሆን ሰነዱ በፌዴሬሽኑ የአስተዳደር ማኑዋል መሰረት ባልተቋቋመ የዲስፕሊን ኮሚቴ የተዘጋጀ፣ወይም ዲስፕሊን ኮሚቴው ከሕግ ውጪ ማስረጃውን በመስማትና በመመዘን ያልተገባ ድምዳሜ ይዞ የሰጠው ውሳኔ መሆኑን ተጠሪ በፍርድ ቤት ላይ በሚያቀርቡት ክርክርና ማስረጃ የአመልካችን ማስረጃ ሲያስተባብሉ እንጂ እንዲሁ በደፈናው ማስረጃውን አላመኑም፣ፍርድ ቤት ክስ አቅርበዋል በሚል ምክንያት አይደለም፡፡ በየመስሪያ ቤቱ የሚቋቋሙ የዲስፕሊን ኮሚቴዎች በሕግ አግባብ የሚቋቋሙና የሰራተኛው ጥቅም ያላግባብ እንዳይጎዳ ተገቢው መጣራት ተደርጎ እርምጃ እንዲወሰድ እገዛ የሚያደርጉ ናቸው ተብሎ የሚታመን ሲሆን የዲስፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ በማስረጃነት ዋጋ ሊያጣ የሚገባው ተገቢው ማስረጃ ቀርቦ ሕጋዊ ያለመሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካች መስሪያ ቤት ያቀረበውን የዲስፕሊን ኮሚቴ የውሳኔ ሰነድ የማስረጃነት ዋጋ ያሳጡት ተጠሪ ተገቢውን ማስረጃ አቅርበው ሰነዱ ሕገ ወጥ መሆኑን ሳያስረዱና ይህንኑ ለማስረዳትም በሕግ አግባብ የቆጠሩት ማስረጃዎች ሳይኖር ስለመሆኑ የስር ፍርድ ቤትን ዋና መዝገብ አስቀርበን ከጠቅላላ የግራ ቀኙ የክርክር ሂደት ተገንዝበናል፡፡

የኦዲት ሪፖርቱን በተመለከተም ኦዲት የተደረገው እ.ኤ.አ ከጃንዋሪ 1/2011 እስከ ኦክቶበር 31/2012 ድረስ ያለው የአመልካች ማህበር ዝርዝር ሂሳብ ሁኖ ሪፖርቱ በተጠቀሱት 22 ወራት ውስጥ የታዬውን የሂሳብ አያያዝ ችግር ከዝርዝር ከማስቀመጡ በፊት የ2012 በቀድሞዋ የሂሳብ ሰራተኛ ያልተሰራ መሆኑ፣በተተኪው ሰራተኛ ሊሰራ የሚገባ እና ይህም የተጀመረ መሆኑን በመግቢያው ላይ ያሰፈረ መሆኑን ሰነዱ ያሳያል፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ የተጠቃለለው በእርግጥ ጥር 14 ቀን 2005 ዓ.ም ስለመሆኑ ሰነዱ የሚገልጽ ሲሆን ስንብቱ የተከናወነው ደግሞ ጥር 10 ቀን 2005 ዓ.ም መሆኑን የስንብት ደብዳቤው ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ኦዲት በተደረገበት ጊዜ የሂሳብ ስራው  የሚመለከተው ተጠሪን ስለመሆኑ አመልካች በክሱ የጠቀሰ ሲሆን ተጠሪም ቢሆኑ የኦዲት ስራው ራሳቸውን የሚመለከት ሁኖ በውጤቱ ግን ተጠያቂ ያላደረጋቸው መሆኑን ጠቅሰው አመልካች አለኝ የሚለው ይሄው የሰነድ ማስረጃ በፍርድ ቤት እገዛ እንዲቀርብላቸው በማስረጃ ዝርዝር መግለጫቸው ላይ የጠቀሱ መሆኑን የስር ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ ውስጥ ያሉት ሰነዶች የሚያሳዩት ሐቅ ሲሆን የስንብት ደብዳቤው መሰረት ያደረገው የዲስፕሊን ኮሚቴውን ውሳኔ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሲታይ በዚህ ውሳኔ መሰረት ተጠሪ በ17 የዲስፕሊን ክሶች ተከሰው በ15ቱ ጥፋተኛ ሁነው የዲስፕሊን ኮሚቴ ማግኘቱን፣ጥፋቶቹም ከባድ መሆናቸውን ጭምር የሚገልጽ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ተጠሪ በአመልካች መስሪያ ቤት ላይ ክስ ያቀረቡት መጋቢት 09 ቀን 2005 ዓ.ም እንደመሆኑ መጠን አመልካች ስንብቱ ሕጋዊ ነው የሚልባቸውን ምክንያቶች በዲስፕሊን ኮሚቴው ውሳኔና ይህንኑ የሚደግፋትን ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን በማስረጃነት ቢያቀርብ ከስንብቱ በኃላ የተገኘ ማስረጃ ነው ተብሎ የማስረጃነት ዋጋ የሚያጣበት የማስረጃ አቀራረብና አቀባበል ደንብ የለም፡፡ አንድ ማስረጃ ለአንድ ጉዳይ ሊቀርብ አይገባም ተብሎ ውድቅ መደረግ ያለበት ለጉዳዩ አግባብነት የሌለው ሁኖ ሲገኝ ወይም በሕጉ ለማስረጃነት እንዲቀርብ ተለይቶ የተቀመጠ የማስረጃ አይነት መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው የበታች ፍርድ ቤቶች የተጠሪን የዲስፕሊን ኮሚቴ ውሳኔን እና የኦዲት ሪፖርት ማስረጃዎችን ውድቅ ያደረጉት ተገቢውን የማስረጃ አቀራረብና አቀራረብ ስርዓት ተከትሎ ያለመሆኑን ተገንዝበናል፡፡ እነዚህ ማስረጃዎች የማስረጃነት ዋጋ አላቸው ከተባሉ ደግሞ በማስረጃዎቹ የተረጋገጡት የዲስፕሊን ጥፋቶች ከባድ መሆናቸውንና የተደጋገሙ መሆኑን የሚገልፁና ተጠሪ ስራቸውን በአግባቡ የማይወጡ የነበሩ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡

ተጠሪ ከባድ የዲስፕሊን ግድፈቶች ሲፈጽሙ የነበረ ከሆነና ጥፋቶችም ተደጋጋሚ መሆናቸው ግልጽ ከሆነና አመልካች በተጠሪ የስራ ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት ስራው በአግባቡ ያልተሰራለት፣በገንዘብ ጥቅሙ ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ከተረጋገጠ በአመልካች ማህበር የገንዘብ ጥቅም ላይ ጉዳት ያለመደረሱን የማስረዳት ግዴታ የተጠሪ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ግን ተጠሪ የአመልካች የሠነድ ማስረጃዎች የተጠሪን ጥፋት የሚያረጋግጡ አይደሉም ከማለት ውጪ ይህንኑ የሚያስረዳ ማስረጃ ያለማቅረባቸውን የሥር ፍርድ ቤትን ዋና መዝገብ በማስቀረብ ከክርክሩ ሂደት ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ተጠሪ የፈፀሙት ጥፋት በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1// የሚሸፈንና የተጠሪን የሥራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የሚያስችል በቂ ምክንያት ሆኖ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች በተጠሪ የተፈፀመ ጥፋት የለም በማለት ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ሲሉ የሰጡት ውሣኔ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27/1// እና አንቀጽ 12(2) (7) ድንጋጌዎች መሠረታዊ ይዘት፣መንፈስ አላማ ያላገናዘበ ሆኖ  አግኝተነዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካች የተጠሪን የሥራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጡ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1()) እና 12(2)(7) ድንጋጌዎች መሰረት ሕጋዊ እንጂ ሕገ ወጥ ተግባር ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች የተጠሪን የሥራ ውል ያቋረጠው ከሕግ ውጭ ነው በማለት የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለአገኘነው ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 

ፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 42383 ህዳር 19 ቀን 2006 . ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 139394 ሐምሌ 30 ቀን 2006 . ውሳኔ በፍ/////ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2.    የአመልካች እርምጃ ሕጋዊ ነው፣አመልካች ለተጠሪ ካሳም ሆነ የሥራ ስንብት ክፍያ፣የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ሊከፍል አይገባም ብለናል፡፡

3.    የዓመት እረፍት 57 ቀናት ወደ ገንዘብ ተቀይሮ ብር 8,550.00 (ስምንት ሺህ አምስት መቶ ሃምሳ ብር) እና ይህንኑ ክፍያም ያላግባብ ያዘገዬ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ መሰረት የአንድ ወር ደመወዝ ብር 4,500.00 (አራት ሺህ አምስት መቶ) ይክፈል ብለናል፡፡

4.    ለክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

ጥቅምት 26 ቀን 2007 . ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል፡፡ ይፃፍ፡፡

መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡