117076 labor dispute/ manager

አንድ ሠራተኛ የሥራ መሪ ሆኖ የሚቆጠረው እንደ ድርጊቱ የሥራ ፀባይ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንጻር መታየት ያለበት ስለመሆኑ፣

አዋጅ ቁጥር 377/96 አዋጅ ቁጥር 494/1998 አንቀጽ 3/2/ሐ/

የሰ/መ/ቁ.117076

ጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም.

ዳኞች፡-ተሻገር ገ/ሥላሴ

 

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ተብሩ ሸምሱ ሲርጋጋ

አብርሃ መሰለ

 

አመልካች፡- በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት የቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ  ነ/ፍጅ    ብሩክ ታፈነ ቀረቡ ወክልና አያያዝ

 

ተጠሪ፡- አቶ ዮሐንስ ብዙነህ   ቀረቡ

 

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የስራ ስንብት ክፍያ ጥያቄን አስመልክቶ የተነሳ ክርክርን የሚመለከት  ሲሆን የተጀመረውም ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ በሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተከሳሽ በነበረው የአሁኑ አመልካች ላይ ባቀረቡት ክስ ነው፡፡ከሳሽ በ14/02/2007 ዓ.ም. ያቀረቡት ክስ ይዘትም ባጭሩ፡-በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ ከ17/08/2005 ዓ.ም. ጀምሮ በወር ብር 4,699 እየተከፈላቸው በሳይት መሀንዲስነት በመስራት ላይ እያሉ ተከሳሽ ድርጅት የስራ ውላቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ ያቋጠባቸው መሆኑን የሚገልጽ ሆኖ ሕገ ወጥ የስራ ስንብት እርምጃ የሚያስከትላቸው እና ተዛማጅ ክፍያዎች አግባብነት ባላቸው በአዋጅ ቁጥር  377/1996 ድንጋጌዎች መሰረት በድምሩ ብር 77,219 (ሰባ ሰባት ሺህ ሁለት መቶ አስራ ዘጠኝ ሺህ) እንዲከፍላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው፡፡

 

ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ በ08/03/2007 ዓ.ም. በሰጠው መልስ ከሳሽ የስራ መሪ በመሆናቸው ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት እና በስራ ክርክር ችሎት ሊስተናገድ የሚገባው አይደለም የሚል የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ካስቀደመ በኃላ በፍሬ ጉዳዩ ረገድም የስራ ውሉ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ እና በየሶስት ወሩ የሚታደስ መሆኑን፣እያንዳንዱ ወገን የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ በመስጠት ውሉን ማቋረጥ እንደሚችል በውሉ የተመለከተ መሆኑን፣ውሉ የተቋረጠውም ከሳሽ በተከሳሽ ድርጅት ጥቅም ላይ ጉዳት ያደረሱ በርካታ  ጥፋቶቸን መፈጸማቸውን ተከሳሽ ገምጋሚ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ በማረጋገጡ መሆኑን  በመግለጽ ክሱ


ውድቅ እንዲደረግ ተከራክሯል፡፡ ፍርድ ቤቱም የመቃወሚያ ነጥቡን በብይን አልፎ እና በፍሬ ጉዳዩ ላይ ክሱን እና የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ በኃላ የስራ ውሉ የኮንትራት ውል መሆኑን፣የስራው ባህርይም የሚያልቅ መሆኑን እና ከሳሽ ስራቸውን በአግባቡ እንደማያከናውኑ የተከሳሽ ምስክሮች ያስረዱ መሆኑን ገልጾ የስራ ውሉ በሕግ አግባብ የተቋረጠ በመሆኑ ተከሳሽ ድርጅት ለከሳሽ የሚከፍለው ክፍያ የለም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን ዘግቶ ያሰናበተው ሲሆን ጉዳዩን በመጨረሻ የተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የስር ከሳሽ የስራ መሪ ስለመሆናቸው ተከሳሽ ድርጅት በማስረጃነት ያቀረበው የስራ መዘርዝርም ሆነ የስራ ውል የሚያረጋግጡ ባለመሆኑ በተከሳሽ የቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በስር ፍርድ ውድቅ የተደረገው በአግባቡ መሆኑን፣የስራ ውሉ የተደረገው ለተወሰነ ጊዜ ስለመሆኑ ተከሳሽ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 10 (1) ድንጋጌ መሰረት ያላስረዳ መሆኑን እና በከሳሽ ተፈጽመዋል የተባሉት ጥፋቶቸ በአዋጁ አንቀጽ 28 (1) ስር የሚሸፈኑ ካለመሆኑም በላይ ተከሳሽ ድርጅት ለእነዚህ ጥፋቶች እርምጃ ሲወስድ የነበረ ስለመሆኑ የተገለጸ ነገር አለመኖሩን ገልጾ ተከሳሽ ድርጅት የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ በመስጠት የወሰደው የስንብት እርምጃ ሕገወጥ ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ በመድረስ በስር ከሳሽ የተጠየቀውን የክፍያ ዓይነት እና መጠን አጣርቶ እንዲወስን ጉዳዩን ወደ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመመለስ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው ይዘቱ ከላይ የተመለከተው የክልሉ ሰበር ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ ተጠሪው የስራ መሪ ናቸው በማለት አመልካች ያቀረበው መቃወሚያ ተቀባይነት የማጣቱን አግባብነት ከተጠሪው የስራ መዘርዝር አንጻር ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በጉዳዩ እልባት ማግኘት የሚገባቸው፡-

 

1. ተጠሪው የስራ መሪ በመሆናቸው ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት እና በስራ ክርክር ችሎት የተስተናገደው አላግባብ ነው በማለት አመልካች ያቀረበው እና ለክርክሩ በጭብጥነት የተያዘው የክርክር ነጥብ በዚህ ችሎት ሊስተናገድ የሚችልበት ስነ ስርዓታዊ አግባብ የለም በማለት ተጠሪው ያቀረቡት ክርክር ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ነው ወይስ አይደለም?

2. ተጠሪው የስራ መሪ በመሆናቸው ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት እና በስራ ክርክር ችሎት ሊስተናገድ የሚገባው አይደለም በሚል አመልካች ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ ተደረገው በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም?


የሚሉ ነጥቦች መሆናቸውን በመገንዘብ አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ከእነዚሁ ነጥቦች አንጻር መርምረናል፡፡

 

የመጀመሪያውን ነጥብ በተመለከተ ተጠሪው የስራ መሪ በመሆናቸው ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት እና በስራ ክርክር ችሎት የተስተናገደው አላግባብ ነው በማለት አመልካች ያቀረበው እና ለክርክሩ በጭብጥነት የተያዘው የክርክር ነጥብ በዚህ ችሎት ሊስተናገድ የሚችልበት ስነ ስርዓታዊ አግባብ የለም በማለት ተጠሪው በሰበር መልሳቸው ተከራክረዋል፡፡በመሰረቱ አመልካቹ ይህንን የክርክር ነጥብ ለዚህ ሰበር ችሎት ሊያቀርብ የቻለው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በጭብጥነት ይዞ ውሳኔ ያሳረፈው በዚህ የክርክር ነጥብ ላይ ጭምር በመሆኑ ነው፡፡ተጠሪው የስራ መሪ አይደሉም ተብሎ በወረዳ ፍርድ ቤት በተሰጠው ብይን ላይ አመልካች በወቅቱ ያቀረበው ይግባኝ ሳይኖር ተጠሪው ባቀረቡት አቤቱታ ሳቢያ አመልካች ይህንን የክርክር ነጥብ በክልል ሰበር ደረጃ ማንሳቱ ስነ ስርዓታዊ አይደለም የሚሉ ከሆነ ተጠሪው የዚህ ዓይነት መከራከሪያ ማቅረብ የነበረባቸው በክልሉ ሰበር ችሎት እንጂ በዚህ የሰበር ደረጃ አይደለም፡፡የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር መልስ አቅርቦ የተከራከረ አንድ ተከሳሽ ወገን መቃወሚያው ውድቅ ተደርጎበት ነገር ግን ክርክሩን በሚሰማው ፍርድ ቤት በሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ተጠቃሚ ከሆነ አቅርቦት የነበረው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ በመደረጉ ብቻ ይግባኝ ሊያቀርብ የሚቸልበት አግባብ ካለመኖሩም በተጨማሪ ከሳሽ ወገን ለበላይ ፍርድ ቤት በሚያቀርበው ይግባኝ እና አቤቱታ ላይ መልስ በሚሰጥበት ጊዜ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውድቅ የተደረገበትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በተጨማሪ መከራከሪያነት ከማቅረብ የሚከለክለው ነገር ባለመኖሩ ተጠሪው የስራ መሪ ናቸው የሚለውን የመከራከሪያ ነጥብ አመልካች በዚህ ሰበር ደረጃ አንስቶ ሊከራከር የሚችልበት ስነ ስርዓታዊ አግባብ የለም በማለት ተጠሪው ያቀረቡት መከራከሪያ ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

ሁለተኛውን ነጥብ በተመለከተ አዋጅ ቁጥር 377/1996 ተፈጻሚነት የሚኖረው በአዋጁ አንቀጽ 2 ስር የተመለከቱትን ሳይጨምር በአሰሪና ሰራተኛ መካከል በሚደረግ በቅጥር ላይ በተመሰረተ የስራ ግንኙነት ላይ ስለመሆኑ በአንቀጽ 3 (1) ስር የተደነገገ ሲሆን የአዋጁ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ የሚደረጉበት የስራ ውል ተቋቁሟ የሚባለውም ማንኛውም ሰው ደመወዝ እየተከፈለው በአሰሪው መሪነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ወይም የተወሰነ ስራ ለአሰሪው ለመስራት በተስማማ ጊዜ ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 2 (3) እና 4 (1) ድንጋጌዎች ያመለክታሉ፡፡

 

በሌላ በኩል የአዋጅ ቁጥር 377/1996 ተፈጻሚ ከማይሆንባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የስራ መሪን አስመልክቶ በሚደረግ የስራ ውል ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 (በአዋጅ ቁጥር


494/1998 እንደተሻሻለ) በአንቀጽ 3 (2 ) (ሐ) ስር የተመለከተ ሲሆን በዚህ ድንጋጌ በተሰጠው ትርጉም መሰረትም የስራ መሪ ማለት በሕግ ወይም እንደ ድርጅቱ የስራ ፀባይ በአሰሪው በተሰጠ የውክልና ስልጣን መሰረት የስራ አመራር ፖሊሲዎችን የማውጣት እና የማስፈጸም ከነዚሁ በተጨማሪ ወይም እነዚህኑ ሳይጨምር ሰራተኛን የመቅጠር፣ የማዛወር፣ የማገድ፣የማሰናበት፣የመመደብ ወይም የስነ ስርዓት እርምጃ የመውሰድ ተግባሮችን የሚያከናውን እና የሚወስን ግለሰብን የሚመለከት እና እንዲሁም እነዚህን የስራ አመራር ጉዳዮች አስመልክቶ የአሰሪውን ጥቅም ለመጠበቅ አሰሪው ሊወስድ ስለሚገባው እርምጃ በራሱ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ የሕግ አገልግሎት ኃላፊንም የሚጨምር ነው፡፡ጉዳዩን በመጀመሪያ  ደረጃ የተመለከተው የወረዳው ፍርድ ተጠሪው የስራ መሪ ስለሆኑ ጉዳያቸው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 እና በስራ ክርክር ችሎት የሚታይ አይደለም በማለት አመልክች ያቀረበውን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በብይን ውድቅ የተደረገበትን ምክንያት  በውሳኔው ላይ ያልገለጸ ቢሆንም የክልሉ ሰበር ችሎት ግን በዚህ ረገድ አመልካች ያቀረበውን መቃወሚያ ሳይቀበል የቀረው የተጠሪው የስራ መዘርዝር እና የግራ ቀኙ የስራ ውል ይዘት ተጠሪው የስራ መሪ ናቸው የሚያሰኝ የስራ ኃላፊነት የተሰጣቸው መሆኑን አያመለክትም በማለት ነው፡፡

 

ተጠሪ በመሰረቱት ክስ ላይ የስራ መደባቸው ሳይት መሀንዲስ እንደሆነ አድርገው የገለጹ ቢሆንም በቀጣይ የክርክር ሂደት ሳይት መሀንዲስ ሳይሆኑ አመልካች ድርጅት በሆሳዕና ከተማ የሚያከናውናቸውን አራት ፕረጀክቶች በበላይነት የመምራት የስራ ኃላፊነት ያላቸው የፕሮጀክት መሀንዲስ መሆናቸው ተረጋግጦአል፡፡ተጠሪነታቸውም ለአመልካች ድርጅት የኮንስትራክሽን መምሪያ መሆኑን የስራ መዘርዝራቸው ያመለከታል፡፡ የተጠሪው የስራ መዘርዝር በስሪ መሪ የሚከናወኑ ተግባራትን የማከናወን የስራ ኃላፊነት እንዳላቸው የሚያመለክት አይደለም የሚባል ካለመሆኑም በተጨማሪ በድርጅቱ የስራ መመሪያ መሰረት ተጠሪው የፕሮጀክቶቹ ማኔጅመንት ኮሚቴ የበላይ ኃላፊ በመሆን የሰው ኃይል፣የፋይናንስ፣የንብረት ግዢ እና አስተዳደር ጉዳዮችን በበላይነት የማስተዳደር እና የመምራት፣የባንክ ሂሳብ የማንቀሳቀስ፣ ለፕሮጀክቶቹ አስፈላጊ የሆነውን የሰው ኃይል የመቅጠር፣ማገድ እና የማሰናበት ስራዎችን ጨምሮ በስራ  መሪ የሚከናወኑ ናቸው የተባሉትን ተግባራት የማከናወን ኃላፊነት የነበራቸው ስለመሆኑ አመልካች በሰበር አቤቱታው ላይ በዝርዝር ላቀረበው ክርክር ተጠሪው በሰበር መልሳቸው ያቀረቡት ግልጽ የማስተባበያ ክርክር አለመኖሩን ተገንዝበናል፡፡አንድ ሰራተኛ የስራ መሪ ሆኖ የሚቆጠረውም የሚያከናውናቸው ተግባራት እንደየድርጅቱ የስራ ፀባይ እየታየ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 (በአዋጅ ቁጥር 494/1998 እንደተሻሻለ) በአንቀጽ 3 (2 ) (ሐ)  ስር ተመልክቷል፡፡ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት በማከናወን ተጠሪነታቸው ለአመልካች ድርጅት የኮንስትራክሽን መምሪያ ሆኖ ድርጅቱ በሆሳዕና ከተማ የሚያከናውናቸውን አራት    ፕሮጀክቶች


በበላይነት የሚመሩ መሆኑ የተረጋገጠ እስከሆነ ድረስ ደግሞ ተጠሪው ከላይ በተጠቀሰው ድንጋጌ መሰረት የስራ መሪ ናቸው ሊባሉ የማይችሉበት ሕጋዊ ምክንያት የለም፡፡የስራ መሪ ከሆኑ ደግሞ ተጠሪው ያቀረቡት ክስ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት እና በስራ ክርክር ችሎት ሊስተናገድ የሚገባው አይሆንም፡፡

 

ሲጠቃለል በአመልካቹ የቀረበውን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ አድርገው ተጠሪው ያቀረቡትን ክስ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት እና በስራ ክርክር ችሎት በማስተናገድ በስር ፍርድ ቤቶች በአንድ ወይም በሌላ አግባብ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 29077 በ02/07/2007 ዓ.ም. የተሰጠው ውሳኔ፣በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 17538 በ30/07/2007 ዓ.ም. የተሰጠው ትዕዛዝ እና በደቡብ  ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 65144 በ01/12/2007 ዓ.ም. የተሰጠው ውሳኔ በሙሉ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348 (1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. ተጠሪው የስራ መሪ በመሆናቸው ክሱ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት እና በስራ ክርክር ችሎት የተስተናገደው በአግባቡ አይደለም በማለት ወስነናል፡፡

3.  በዚህ መዝገብ ተሰጥቶ የነበረው የአፈጻጸም እግድ ተነስቷል፡፡

4.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

5.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡


 

 

መ/ተ


የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡