102056 civil procedure/ opposition/ appeal procedure

በክርክሩ ተካፋይ ያልሆነውን ወገን የሚጎዳ ውሳኔ የተላለፈው ጉዳዩን በተዋረድ ባየው የሰበር ችሎት በሚሆንበት ጊዜ ይህ በክርክሩ ተካፋይ ያልሆነው ወገን አለኝ የሚለውን መብት ለማስከበር ይችል ዘንድ መብቴን ተጋፍቷል በሚለው ሰው ላይ በስሙ ቀጥታ ክስ በመመስረት መብቱን ከማስከበር ውጪ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.358 መሰረት ተቃውሞውን ለሰበር ችሎቱ ሊያቀርብ የሚችል ስላለመሆኑ

የሰ/መ/ቁ. 102056

ታህሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም


 

 

 

 

 

አመልካች፡- አቶ ሳምሶን ካሳዬ - የቀረበ የለም


ተኽሊት ይመስል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ


ተጠሪ፡- 1. ወ/ሮ መሰረት ግርማ - ተወካይ ኃይሉ ቦሰት ቀረቡ 2. አቶ ሳሙኤል ካሳዬ

3. አቶ ኢሳያስ ካሳዬ     ቀረቡ

4. ወ/ሮ ሜላት ካሳዬ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ር ድ

ጉዳዩ የውርስ ንብረት ይለቀቅልኝ ጋር ተያይዞ የተሰጠው ውሳኔ ላይ የቀረበውን የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች በአደአ ወረዳ ፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ነው፡፡ አመልካች በዚህ ፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ በ17/04/2006 ዓ/ም የተፃፈ ሁኖ 1ኛ ተጠሪ ተከሳሽ፣ የአሁኑ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ተራ ያሉት ተጠሪዎች ደግሞ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረው በመ/ቁጥር 24515 በ16/10/2002 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ ከእናቴ ከወ/ሮ ፀሐይ ገብሬ በውርስ ሊተላለፍልኝ በሚገባ ንብረት ላይ የተሰጠና መብቴን የነካ ነው በሚል ምክንያት ውሳኔ ተነስቶ የክርክሩ ተካፋይ ልሆን ይገባል የሚል ሲሆን የአሁኑ ሥር ፍርድ ቤትም ለፍርዱ መሰረት የሆነው ንብረት ላይ የተሰጠው ውሳኔ የተፈጸመ ነው በሚል ድምዳሜ የአመልካች የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ በመዝገቡ ሊስተናገድ እንደማይችል፣ ሆኖም አመልካች መብታቸውን ቀጥታ ክስ አቅርበው ማስጠበቅ የሚችሉ መሆኑን ጠቅሶ የአመልካችን አቤቱታ ውድቅ አድርጎባቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ የአሁኑ አመልካች ይግባኛቸው ለምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የአሁኑ ከተራ ቁጥር 2 እስከ 4 ያሉት ተጠሪዎች በአሁኗ 1ኛ ተጠሪ ላይ የውርስ ንብረት ይለቀቅልን ክስ አቅርበው የወረዳው ፍርድ ቤት ክርክር ያስነሳው ይዞታና ንብረት ለከሳሾች እንዲለቀቅላቸው መወሰኑን፣ ይህ ውሳኔ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፀንቶ የነበረ ቢሆንም የአሁኗ 1ኛ ተጠሪ የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎትም በመ/ቁጥር 11115 በ03/03/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የበታች ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት


ያለበት ነው በሚል ምክንያት ሙሉ በሙሉ በመሻር ክርክር የተነሳበት ይዞታና ንብረት የ1ኛ ተጠሪ ነው በማለት የወሰነ መሆኑን፣ ይህ ውሳኔ በመሰጠቱ ምክንያትም 1ኛ ተጠሪ የተወሰደባቸው ንብረት እንዲመለስላቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 349(1) ድንጋጌ  መሰረት አቤቱታ አቅርበው ፍርድ ቤቱም ከ2ኛ እስከ 4ኛ ተጠሪዎች ባሉት ተጠሪዎች የ1ኛ ተጠሪ ቤት ፈርሶ ስለነበር በአሁኗ 2ኛ ተጠሪ ስም ያለው ቤት ተሽጦ ለ1ኛ ተጠሪ ግምቱ እንዲከፈል ጨረታ እንዲወጣ አድርጎ በሂደት እንደሚገኝ፣ የወረዳው ፍርድ ቤት በዚህ አግባብ አፈጻጸሙን እየመራ ያለው የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 11115 የሰጠውን ውሳኔ መነሻ አድርጎ ስለመሆኑና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት የፍርድ መቃወሚያ ሊቀርብ የሚገባው ደግሞ ፍርዱን ለሰጠው ፍርድ ቤት መሆኑን ጠቅሶ የአሁኑ አመልካች የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ አቀራረብ ስርዓት ስርዓቱን የተከተለ አይደለም በሚል ድምዳሜ የሥር ፍርድ የአመልካችን አቤቱታ ውድቅ ማድረጉን ተገቢ ነው በማለት ወስኖአል፡፡ ከዚህም በኋላ አመልካች የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የወረዳው ፍርድ ቤት እያስፈጸመ ያለው የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 11115 የሰጠውን ውሳኔ ሁኖ እያለና በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎትም ሆነ በበታች ፍርድ ቤቶች ክርክሩ መኖሩን አመልካች ባላወቁበት ሁኔታ እንዲሁም የ1ኛ ተጠሪ አፈጻጸም ሂደት ላይ ስለመኖሩ ክርክሩ እያሳየ ፍርዱ ተፈጽሟል ተብሎ የፍርድ መቃወሚያው በወረዳው ፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉም ሆነ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሠጠው ውሳኔ በወረዳ ፍርድ ቤት የፍርድ መቃወሚያ ሊቀርብበት የሚችል አይደለም በማለት መወሰኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 ድንጋጌ አላማ ውጪ የሆነ እና የአመልካችን የውርስ መብት የጎዳ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ  ሲሆን ተጠሪዎች ቀርበውም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጎአል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች እና የአሁኑ ተጠሪ ከተራ ቁጥር 2 እስከ 4 የተጠቀሱት ተጠሪዎች የወ/ሮ ጸሐይ ገብሬ ወራሽ መሆናቸውን፣ የአሁኑ አመልካች ከተራ ቁጥር 2 እስከ 4 የተጠቀሱት ተጠሪዎች  ከወ/ሮ ጸሐይ ገብሬ በውርስ የሚተላለፍልን ቤትና  ይዞታ በ1ኛ ተጠሪ ከሕግ ውጪ ተይዞ ይገኛል በሚል በተጠሪዋ ላይ ክስ መስርተው በወረዳው ፍርድ ቤት ንብረቱ እንዲለቀቅላቸው ተወስኖላቸው በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ፀንቶ የነበረ ቢሆንም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግን የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተሽሮ አከራካሪው ቤትና ይዞታ የ1ኛ ተጠሪ ነው ተብሎ መወሰኑን፣ በዚህ ሂደት ግን የስር ከሳሾች በ1ኛ


ተጠሪ ቤት ላይ ጉዳት አድርሰው/አፍርሰው/ ስለነበር ተጠሪዋ የፈረሰው ቤታቸው ግምቱ እንዲከፍላቸው አፈጻጸሙን በወረዳው ፍርድ ቤት ቀጥለው ባሉበት ሁኔታ የአሁኑ አመልካች በዋናው ጉዳይ የተሰጠው ፍርድ የውርስ መብቴን የነካ ነው በሚል የፍርድ መቃወሚያ ያቀረቡና ተቀባይነት ያጡ መሆኑን ነው፡፡

የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በግልፅ የሚያሳየው አመልካች የፍርድ መቃወሚያ  ያቀረቡበት ውሳኔ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 11115 የተሰጠና ፍርዱ ከተፈፀመ በኃላ የቀረበ መሆኑን ነው፡፡ አመልካች መቃወሚያው የቀረበበት ፍርድ አልተፈፀመም፤ በሂደት ላይ ያለ ነው የሚሉት 1ኛ ተጠሪ ቤታቸው በሌሎች ተጠሪዎች የፈረሰባቸው በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 349(1) መሰረት የቤቱን ግምት ሊከፍሉኝ ይገባል በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ መነሻ አድርጎ የስር ፍርድ ቤት ይህንኑ አቤቱታ ለማስፈፀም በ28/04/2006 ዓ/ም የሰጠውን ትዕዛዝ መሰረት በማድረግ ስለመሆኑ ከወረዳው ፍርድ ቤት መዝገብ ግልባጭ ተመልክተናል፡፡

በእግርጥ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 358 መሠረት የሚቀርበው አቤቱታ የሚስተናገደው ለመቃወሚያው መነሻ የሆነውን ውሳኔ ለሰጠው ፍ/ቤት ነው፡፡ አቤቱታው የሚጣራው ወይም የሚስተናገደው ማንኛውም ክስ በሚስተናገድበት ሥርዓት በመሆኑ እና ይህም ማስረጃ መስማትንና ማስረጃውን መዝኖ ውሳኔ መስጠትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ስለሆነም ታህሳስ 17 ቀን 2006 ዓ/ም ለወረዳው ፍርድ ቤት የቀረበው የተቃዋሚ ማመልከቻ ወይም ክርክር በማስረጃ ተጣርቶ የሚወሰን ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ የፍርድ መቃወሚያ የቀረበበትን  ውሳኔ የሰጠው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ነው፡ የሰበር ችሎቱ ፍሬ ነገሮችን በማስረጃ የማጣራትም ሆነ ማስረጃን የመመዘን ሥልጣን የለውም፡፡ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ደግሞ ፍሬ ነገርን የሚያጣራበት ወይም የማስረጃ ምዘናን ክርክርና ቅሬታ የሚመለከትበት ሥልጣን የሌለው መሆኑን የኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ለ))፣ ከክልሉ ሕገ መንግስት  አንቀፅ 64 (2(ሐ)) እና የክልሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 141/2000 አንቀጽ 31 ድንጋጌዎች ያስገነዝባሉ፡፡ በመሆኑም በሕግ አተረጓጎም ረገድ የተፈጸመውን ስህተት ለማረም በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ለ)) ከክልሉ ሕገ መንግስት አንቀፅ 64(2(ሐ)) እና የክልሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 141/2000 አንቀጽ 31 ድንጋጌዎች መሰረት ስልጣን በተሰጠው በክልሉ ሰበር ችሎት የሚታይ አይሆንም፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ክርክሩ የተጀመረው በወረዳው ፍርድ ቤት እንደሆነ መቃወሚያው መቅረብ ያለበት ለዚሁ ፍ/ቤት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን የወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ የተሻረው በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ነው፡፡ በመሆኑም የወረዳው ፍርድ ቤት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በፍርድ መቃወሚያ መነሻ አይቶ እንዲሽር ማድረግ ከፍርድ ቤቶች የስልጣን ተዋረድ አንጻር ሲታይ ያልተፈለገ ውጤትን ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ የወረዳው ፍርድ ቤት የፍርድ መቃወሚያውን እንዲመለከትና ዳኝነት እንዲሰጥ ማድረግ የሚመረጥ አይሆንም፡፡  በሌላ


በኩል ግን ተቃዋሚው መብታቸውን የሚያስከብሩበትን መድረክ ሊያገኙ የሚገባ መሆኑ ሲታይም ይኸው ሊታይላቸው የሚገባው በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አይደለም፡፡ የክርክሩ ሂደት እንደሚያሳየው ከወረዳው ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ተቃዋሚ የክርክሩ ተካፋይ አልነበሩም፡፡ ከዚህ የተነሳም በክልሉ ሰበር ችሎት የተሰጠው ውሳኔ ተቃዋሚውን የሚያስገድድ አይሆንም፡፡ ከዚህም የምንገነዘበው ተቃዋሚ አለኝ የሚሉትን መብት ለማስከበር ይችሉ ዘንድ መብቴን የሚነካ ውሳኔ ሰጥቷል በሚሉት ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን ከሚያቀርቡ ወይም መብቴን ተጋፍቶአል በሚለው ሰው ላይ በስሙ ቀጥታ ክስ መመስረት መብታቸውን ከሚያስከብሩ በስተቀር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 መሰረት ለወረዳ ፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ስርዓቱን የጠበቀ ነው ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም፡፡ 1ኛ ተጠሪ በሌሎች ተጠሪዎች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 349(1) መሰረት ያቀረቡት አፈጻጸም በሂደት ላይ መሆኑም የወረዳው ፍርድ ቤት የአመልካችን የፍርድ መቃወሚያ እንዲያስተናገድ የሚያስችለው አይደለም፡፡ ምክንያቱም በዋናው ክርክር ላይ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 11115 የተሠጠው ውሳኔ የ1ኛ ተጠሪን በይዞታውና በቤቱ ላይ ሙሉ መብት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ እስከሆነ ድረስ ይሄው መብታቸው የሚለወጥ መሆኑን አመልካች በቅድሚያ በቀጥታ ክስ ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡ ሲጠቃለልም የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካችን የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ ውድቅ ማድረጋቸው ከክርክሩ ሂደት እና ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ አንፃር የሚነቀፍ ሁኖ ስላልተገኘ በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ በውጤት ደረጃ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም በማለት ተከታዩነ ወስነናል፡፡

 ው ሣ ኔ

1. በአደአ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 24515 በ10/04/2006 ዓ/ም ተሰጥቶ  በምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ.036604 በ19/09/2006 ዓ/ም፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 185034 በ4/10/2006 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1)መሰረት ጸንቷል፡፡

2. አመልካች አለኝ የሚሉትን መብት በሌላ አግባብ ከማስከበር ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም ብለናል፡፡

3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና  ኪሳራ  የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡


 

 

 

 

 

 

ብ/ይ


       

በ24/10/2006 ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል፡፡ ለሚመለከታቸው አካላት ይጻፍ፡፡  መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡