109383 civil procedure/ jurisdiction/ local jurisdiction

ፍ/ቤቱ የግዛት ስልጣን የለውም በማለት ለሚቀርብለት መቃወሚያ የሚሰጠው ውሳኔ ፍትህን የሚያጓድል ካልሆነ በቀር ይግባኝ ሊቀርብበት የማይችል ስለመሆኑ

የፍ/ሥ/ሥ/ቁ. 10(2)

የሰ/መ/ቁ. 109383

የካቲት 2 ቀን 2008 ዓ.ም

 

 

ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

 

አመልካች - ሳሊሆም ከፍተኛ ክሊኒክ - ተሾመ ጉታ ቀረቡ

ተጠሪ - ዶ/ር ዘመኑ ዮሃንስ  - ቀረቡ፡፡

 

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 

 ፍ ር ድ

በዚህ መዝገብ ለተያዘው ክርክር መነሻ የሆነው የአሁን ተጠሪ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአመልካች ላይ ያቀረቡት ክስ ሲሆን አላግባብ ከስራ መሰናበታቸው ህገወጥ ነው ተብሎ ልዩ ልዩ ክፍያ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡ አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስ ድርጅቱ የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ ቀበሌ 02 በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለውም የሚል የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ እና በፍሬ ገዳዩም ስንብቱ ህጋዊ ነው እንዲባል የበኩላቸውን መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ግራቀኙ ተከራካሪዎች በተለያየ ክልል ነዋሪዎች ስለሆኑ የፌዴራል ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው በማለት መቃወሚያውን በብይን አልፎ በፍሬ ጉዳዩ የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ የስራ ዉሉ በአመልካች የተቋረጠው ከህጉ ውጭ ነው፤ ስለሆነም ለተጠሪ የካሳ፤ የስንብት እና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ በድምሩ ብር 104,730.00 (አንድ መቶ አራት ሺህ ሰባት መቶ ሰላሳ) እንዲሁም በክርክሩ ምክንያት በተጠሪ ላይ ለደረሰው ወጪ እና መጉላላት በቁርጥ ብር 500.00 (አምስት መቶ) እንዲከፍል ወስኗል፡፡ ይህን ውሳኔ በመቃወም አመልካች በይግባኝ ተጠሪ ደግሞ በመስቀለኛ ይግባኝ ቅሬታቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ክርክራቸውን ሰምቶ የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለማየት ስልጣን አለኝ ማለቱና ስንብቱ ህገወጥ ነው በማለት የደረሰበት መደምደሚያ በአግባቡ መሆኑን፤ ወጭና ኪሳራን በተመለከተ ተጠሪ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል በማለት ወስኗል፡፡


የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ አመልካች ጥር 20 ቀን 2007 ዓ.ም ያቀረቡት የሰበር ማመልከቻ ተመርምሮ ተጠሪ በስር ክሳቸው በአመልካች ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር ገልፀው ክስ ማቅረባቸው ተረጋግጦ እያለ የስር ፍርድ ቤት ግራቀኙ በተለያየ ክልል ነዋሪዎች ስለሆኑ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው ማለቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ነው? አይደለም? የሚለው ነጥብ እንዲጣራ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ክርክራቸውን በጽሁፍ ተለዋውጠዋል፡፡

 

ከላይ ባጭሩ የገለፅነው የጉዳዩን አመጣጥ ሲሆን ክርክሩን ቅሬታ ካስነሳው ውሳኔ እና ተገቢነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማያያዝ መርምረናል ፡፡ አመልካች ባቀረቡት የሰበር ቅሬታ ተጠሪ ተቀጥረዉ ሲሰሩ የነበረበት ድርጅት የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ ቀበሌ 02 በመሆኑ፤ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 138(1) እና በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 22(1) መሰረት ጉዳዩን አይቶ የመወሰን ስልጣን ያለው ድርጅቱ በሚገኝበት ቦታ ያለው የክልሉ ወረዳ ፍርድ ቤት (ሰበታ ሀዋስ ወረዳ ፍርድ ቤት)  በመሆኑ፤ በአዲስ አበባ እና ድሬድዋ ያሉ የፌዴራል ፍርድ  ቤቶች የስራ ክርክርን ለማየት ስልጣኑ የተሰጣቸው ቢሆንም በሁለት ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ተከራካሪዎች በመሆናቸው በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 5(2) መሰረት ጉዳዩን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የማየት ስልጣን አላቸው ተብሎ የክስ መቃወሚያው ውድቅ መደረጉ የስራ ክርክርን አስመልክቶ የተከራካሪ ወገን ማንነት ወይም የሚኖርበት ክልል ከግምት ውስጥ ሳይገባ የክልል ፍርድ ቤቶች ስልጣን እንዲኖራቸው ታስቦ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በግልፅ የተደነገገውን የሚቃረን በመሆኑ የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ምድብ የስራ ክርክር ችሎት ጉዳዩን አይቶ የመወሰን ስልጣን የለውም ተብሎ ውሳኔው እንዲሻር ፤ እንዲሁም በፍሬ ነገሩ የስራ ውሉ እንዲቋረጥ የተደረገው የአመልካች የስራ እንቅስቃሴ እየቀዘቀዘና ትርፉም እየቀነሰ በመሄዱ ምክንያት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው በመሆኑ ስንብቱ ህገ ወጥ ነው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ ተሸሮ ለጠሪ የሚከፈል ክፍያ የለም ተብሎ በነፃ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡

 

ተጠሪ በበኩላቸው ክሊኒኩ ህጋዊ ሰውነት የሌለው በመሆኑና ክሱም የቀረበው ስራ አስኪያጅ እና ባለቤት አቶ ተሾመ ጉታ ተብሎ በመሆኑ፤ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 5(2) መሰረት ከሳሽና ተከሳሽ መደበኛ መኖሪያችን በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ መሆኑ መነሻ ተደርጎ ክሱ መቅረብ ያለበት በፌዴራል ፍርድ ቤት ስለመሆኑ ብይን መሰጠቱ የሚነቀፍ ባለመሆኑ፤ አዋጅ ቁጥር 377/1996 የስራ ክርክርን አስመልክቶ የፌዴራል እና የክልል በማለት ለይቶ ያላስቀመጠ በመሆኑና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 20 እና 23 መሰረት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የስራ ክርክሮችንም እንደሚመለከቱ ስለሚደነግግ የተሰጠው ብይን የሚነቀፍ አይደለም ተብሎ የአመልካች ቅሬታ ውድቅ እንዲደረግ ተከራክረዋል፡፡


እንደመረመር ነው በክርክሩ ምላሽ ማግኘት የሚገባው ጭብጥ የስር ፍርድ ቤት ስልጣን (የግዛት ክልል) የለውም ተብሎ በሚቀርብለት መቃወሚያ ላይ በሰጠው ውሳኔ ይግባኝ (የሰበር አቤቱታ) መቅረቡ ህጉን መሰረት ያደረገ ነው ወይስ አይደለም? በፍሬ ጉዳዩ ስንብቱ ህገወጥ ነው ተብሎ ልዩ ልዩ ክፍያ እነዲከፈል በመወሰኑ የተፈፀመ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለ ወይስ የለም? የሚሉት ናቸው በዚሁ ቅደም ተከተል መሰረት መርምረናል፡፡

 

ቀዳሚውን ጭብጥ በተመለከተ ከክርክሩ እንደተረዳነው አመልካች ያቀረቡት የስልጣን መቃወሚያ ስረ ነገርን የተመለከተ ሳይሆን የግዛት ክልል ስልጣንን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ግራ ቀኙ እንደገለፁት በአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ያሉ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የስራ ክርክርን ለማየት የስረ ነገር ስልጣኑ በህግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አመልካች እየተከራከሩበት ያለው የግዛት የዳኝነት ስልጣን በዋነኛነት መሰረት የሚያደርገው ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ጉዳይ  የተፈጠረበትን ቦታ፤ለተከራካሪ ወገኖች የሚኖረውን አመቺነት እና መሰል ሁኔታዎችን ሲሆን የስረ ነገር ስልጣን መሰረት የሚያደርገው ግን ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ይዘት፣የተከራካሪ ወገኖችን መብትና ጥቅም ክብደት እናመጠን፤የጉዳዩን የውስብስበነት ደረጃ እና መሰል ነጥቦችን በመሆኑ በጉዳዮች አመራር ስርዓት ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ለስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን ነው፡፡ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 9 እና 10 ድንጋጌዎች ተገናዝበው ሲታዩም ሕጉ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ከግዛት ስልጣን ይልቅ ለስረ ነገር ስልጣን መሆኑን መገንዘብ የሚያስችሉናቸው፡፡ በተለይ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 10(2) ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው ፍርድ ቤቱ የግዛት ክልል ስልጣን የለውም በማለት ለሚቀርብለት መቃወሚያ የሚሰጠው ውሳኔ ፍትህን የሚያጓድል ካልሆነ በቀር ይግባኝ ሊቀርብበት እንደማይችል ተደንግጓል፡፡ በተያዘው ጉዳይ የአመልካቾች ቅሬታ በስር ፍርድ ቤት የተላለፈው ውሳኔ ፍትህን የሚያጓድል ነው በማለት የቀረበ አይደለም፡፡ ፍትህን የሚያጓድል ውሳኔ ስለመተላለፉ የቀረበ ክርክር በሌለበት ደግሞ የስር ፍርድ ቤት የግዛት ክልል ስልጣን የለውም ተብሎ በቀረበው መቃወሚያ ላይ ባሳለፈው ብይን ይግባኝ እና የሰበር አቤቱታ መቅረቡ ህጉን የተከተለ ሆኖ አላገኘነውም ፡፡ ስለሆነም ምንም እንዃ ነዋሪነታቸው በተለያዩ ክልሎች በሆኑ ተከራካሪ ወገኖች መካከል የሚነሳ ክርክርን የማየት ስልጣን የፌዴራል ፍ/ቤቶች መሆኑበአዋጁ 25/1988 አንቀጽ 5(2) ስርመደንገጉ የግዛት ክልል ስልጣንን ሳይሆን የስረነገር ስልጣንን የሚመለከት በመሆኑ የስር ፍርድ ቤቶች ይህን ምክንያት በመጥቀስ የስልጣን ክርክሩን መወሰናቸው ተገቢ ሆኖ ባናገኘውም በግዛት ክልል ስልጣን ረገድ በተሰጠ ውሳኔ ይግባኝ (የሰበር አቤቱታ) መቅረቡ የስነ ስርአት ህጉን የተከተለ ባለመሆኑ አልተቀበልነውም፡፡

 

ሁለተኛውን ጭብጥ በተመለከተ የስር ፍርድ ቤቶች ፍሬ ነገሩን ለማጣራት እና ማስረጃ ለመመዘን በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት ክርክርና ማስረጃውን ተመልክተው የስራ ውሉን ለማቋረጥ አመልካች እንደሚሉት ባጋጠማቸው የገቢ ማሽቆልቆል የተነሳ ሰራተኛን ለመቀነስ


የሚያስችል አስገዳጅ ሁኔታ ስለመፈጠሩ ያላረጋገጡ በመሆኑ፤ ቅነሳውም በህጉ የተዘረጋውን ስርዓት የተከተለ ስለመሆኑ የቀረበ መከራከሪያና ማስረጃ አለመኖሩን በማረጋገጥ የስራ ስንብቱ ህገወጥ ነው በማለት መወሰኑ እና በሕጉ የተመለከቱ ክፍያዎች ይከፈሉ ማለታቸው የሚነቀፍ አይደለም ፡፡ በዚህ ረገድ የተፈጸመ የህግ ስህተት የለም ብለናል ፡፡

 

 

 ው ሳ ኔ

1. በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/ 32414 ታህሳስ 11/2006 ዓ.ም ተወስኖ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ 139491 ህዳር 25/2007 ዓ.ም የተሻሻለው ውሳኔ በፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ 348(1) መሰረት በውጤት ደረጃ ፀንቷል ፡፡

2. በስር ፍርድ ቤት የተጀመረው አፈፃፀም ታግዶ እንዲቆይ የተሰጠው ትዕዛዝ ተነስቷል ፡፡ ይፃፍ

3. በዚህ ችሎት ስለተደረገው ክርክር ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገቡ እልባት ያገኘ ስለሆነ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ፡፡

 

የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 የ ል ዩነ ት ሐሳብ

 

በዚህ መዝገብ ለክርክር በቀረበው ጉዳይ ተጠሪው ሲሰሩበት የነበረው ተቋም የሚገኝ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን በሰበታ ሃዋስ ወረዳ ውስጥ መሆኑ፣ የስራ ውሉ የተደረገውም ሆነ ሲፈጸም የነበረው በዚያው ወረዳ ውስጥ መሆኑ አላከራከረም፡፡ በክልል ውስጥ የሚነሳ የግል የስራ ክርክር ጉዳይን አይቶ የመወሰን ስልጣን ደግሞ በአዋጅ ቁ. 377/1996 አንቀጽ 138(1) ስር የተሰጠው ለክልል ወረዳ ፍ/ቤት ነው፡፡ የግዛት ስልጣን የሌለው አንድ ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ፍትሕን የሚያጓድል ካልሆነ በቀር ተቀባይነት እንደማያጣ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ አንቀጽ 10(2) ስር የተመለከተ ቢሆንም በመሰረቱ ቀደም ሲል አሃዳዊ የመንግስት አወቃቀርን መሰረት አድርገው የወጡት እና አሁን ድረስ በስራ ላይ ያሉት ሕጎች መተርጎም እና ተግባራዊ መደረግ የሚገባቸው በአሁኑ ጊዜ ያለው ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ስርዓት ካስከተላቸው ለውጦች ጋር ተጣጥመው ነው፡፡ በአሁኑ የመንግስት አወቃቀር ስርዓት መሰረት የፍርድ ቤቶችን የስረ ነገር ስልጣን ለመወሰን እንደመስፈርት ከሚወሰዱት ነጥቦች አንዱ ደግሞ ጉዳዩ የተነሳበት ስፍራ ወይም ግዛት በመሆኑ በተያዘው ጉዳይ ክሱ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የስራ ክርክር ችሎት ተስተናግዶ ውሳኔ  ማግኘቱ የሚያስነሳው የስረ ነገርን ሳይሆን በስነ ስርዓት ሕጉ አንቀጽ 10(2) ድንጋጌ መሰረት የግዛት


ስልጣን ጥያቄን ብቻ ነው ወደሚል መደምደሚያ የሚያደርስ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ የስነ ስርዓት ሕጉ አንቀጽ 10(2) ድንጋጌን በዚህ አግባብ መተርጎም በአንድ ክልል ወረዳ ፍ/ቤት ቀርቦ መታየት ያለበት ጉዳይ ትይዩ ስልጣን ባለው በማንኛውም የሌላ ክልል ወረዳ ፍ/ቤት ታይቶ ቢወሰን ጉዳዩ የሚያስነሳው የስረ ነገር ሳይሆን የግዛት ስልጣን ጉዳይን ነው እንደማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የፍርድ ቤቶች ስልጣን በአሁኑ ጊዜ በፌዴራል እና በተለያዩ ክልሎች በተደለደለበት ሁኔታ ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የሚያስነሳው የስረ ነገር ሳይሆን የግዛት ስልጣንን ጥያቄ ነው ሊባል ይችል የነበረው ክሱ ተስተናግዶ ውሳኔ ያገኘው በዚያው ክልል በሚገኝ ሌላ ወረዳ ፍ/ቤት ቢሆን ኖሮ ነው፡፡ በክልል ወረዳ ፍ/ቤት ቀርበው መስተናገድ የሚገባቸውን የግል የስራ ክርክር ጉዳዮች የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የስራ ክርክር ችሎት ተቀብሎ የማየት የስረ ነገር ስልጣን የሌለው ስለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁ. 100950 አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሰጠ ሲሆን የስራ ክርክር ጉዳዮችን አስመልክቶ በመዝገብ ቁ. 113339 እና 113675 የተሰጡ ገዥ ውኔዎችም ቢሆኑ ለጉዳዩ አግባብነት የላቸውም ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የስረ ነገር ስልጣንን አስመልክቶ በተከሳሽ ወገን የቀረበለት መቃወሚያ ባይኖር ኖሮ እንኳ የቀረበለትን ጉዳይ አስተናግዶ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል የስረነገር ስልጣን ያለው መሆኑን በቅድሚያ የማረጋገጥ ግዴታ ያለበት ሲሆን ስልጣን የሌለው በሆነ ጊዜም በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁ. 9(1) እና 231 (1) (ለ) መሰረት ጉዳዩን ዘግቶ ማሰናበት ይጠበቅበታል፡፡

 

በመሆኑም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ በስልጣን ምክንያት ሊሻር ይገባው ነበር በማለት ስሜ በተራ ቁ. ሁለት የተመለከተው ዳኛ የልዩነት ሃሳቤን አስፍሬአለሁ፡፡

 

 

 

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

መ/ይ