109206 civil procedure/ admission

ተከሳሽ የተከሰሰበትን ነገር በሙሉ ወይም በከፊል የሚያምን መሆኑን የገለፀ እንደሆነ በእምነቱ መሰረት ይገባኛል የሚለው ማናቸውም ዳኝነት እንዲሰጠው አመልካች(ከሳሽ) ሊጠይቅ የሚችል ስለመሆኑ

የሰ/መ/ቁ. 109206

 

የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም.

 

ዲኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

 

አመልካች - አቶ ፍስሃ እርቅ ይሁን ተጠሪ - አቶ ኪሮስ ስዩም

 

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

ጉዳዩ የገንዘብ ክርክር ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች በተጠሪ ላይ በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ ነው ፡፡ የክሱ ይዘት ግራቀኙ በነበረን የንግድ ግንኙነት ጀንፈል ቡና በጋራ ገዝተን አስበጥረን ለማእከላዊ ገበያ አቅርበን በመሸጥ ትርፉን ለመከፋፈል ባደረግነው ስምምነት መሰረት ለጀንፈል ቡና መግዣ ብር 122,000.00 (መቶ ሃያ ሁለት ሺህ) ሰጥቸው ቡናው ተገዝቶ አስበጥረን እና በከሳሽ ፈቃድ ማእከላዊ ገበያ ተልኮ በከሳሽ የቡና ሽያጭ ወኪል በአቶ ዘላለም ጥላሁን አማካኝነት ተሸጦ ገንዘቡ በንግድ ባንክ በኩል የተላከልኝ ሲሆን ይህን ገንዘብ አውጥቼ ትርፉን ተሳስበን እስክንከፋፈል ድረስ ሙሉ ገንዘቡን ለተከሳሽ የሰጠሁት ቢሆንም ሂሳብ ተሳስበን ገንዘባችንን ሳንካፈል በመካከላችን አለመግባባት ስለተፈጠረ በ 10/07/2006 ዓ.ም በሽማግሌ ዋና ገንዘቤንና ትርፉን እንዲሰጠኝ አስጠይቄው ቡና መግዣ ብር 122,000.00 (መቶ ሃያ ሁለት ሺህ) እንደሰጠሁት አምኖ ከዚህ ገንዘብ ብር 41,000.00 (አርባ አንድ ሺህ) የሰጠኝ ሲሆን ቀሪውን ብር 81,000.00 (ሰማንያ አንድ ሺህ) ዛሬ ነገ በማለት ሊሰጠኝ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ዋና ገንዘቤንና ትርፉ ታስቦ እንዲከፍለኝ በማለት ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪም ለክሱ መልስ ሰጥተዋል፡፡

 

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማና የሰነድ ማስረጃዉን ከመረመረ በኋላ ተከሳሽ በምስክሮች ለመክፈል ተስማምቷል የተባለውን ቀሪ ገንዘብ ብር 81,000.00 (ሰማንያ አንድ ሺህ) ለከሳሽ እንዲከፍለው ወስኗል፡፡ ይግባኙን የተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበኩሉ የይግባኝ ክርክሩን ሰምቶ የባንኩ ሰነድ  ገንዘቡ


የተላከ ለከሳሽ ስለመሆኑ ከሚያስረዳ በቀር ለተከሳሽ ስለመላኩ ስለማያስረዳ፤ ከሳሽ ገንዘቡን ከባንክ አውጥቶ ለተከሳሽ ስለመስጠቱ የሚያስረዳ አንዳች የሰነድ ማስረጃ ስላልቀረበ፤ የተሰሙት ምስክሮችም ገንዘቡን ሲሰጥ አይተናል በማለት ስላልመሰከሩ፤ እንዲሁም ተከሳሹ ገንዘቡ ያለበት መሆኑን በሽማግሌዎች ፊት ተስማምቷል ለተባለውም ስለመስማማቱ የቀረበ የስምምነት ሰነድ ስለሌለ ተከሳሽ ኃላፊነት የለበትም ገንዘቡንም ሊከፍል አይገባም በማለት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን ሽሯል፡፡ አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር ተሰኝተው ጉዳዩን ለክልሉ ሰበር ችሎት ቢያቀርቡም ቅሬታቸው ተቀባይት ሳያገኝ አያስቀርብም ተብሎ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበው ይህንን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

አመልካች ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ 4/አራት/ ገፅ የሰበር ማመልከቻ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ችሎቶች ውሣኔና ትዕዛዝ መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ፡-ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት ክሱን በዝርዝር ክደው መልስ ያልሰጡ በመሆኑ በመሸሽ ክሱን እንዳመኑ የሚያስገምት በመሆኑ፤ ገንዘቡ በብድር የተሰጠ ባለመሆኑ በሰው ምስክር ማስረዳት እየተቻለ የሰነድ ማስረጃ አላገኘንም ተብሎ መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት በመሆኑ፤ እንዲሁም የስር ፍርድ ቤት ዳኝነት የተጠየቀበትን ከቡና ሽያጭ የተገኘን ትርፍ ሂሳቡ እንዲጣራ አስደርጎ አለመወሰኑ እና የወለድ ጥያቄውን ማለፉ የህግ ስህተት በመሆኑ እንዲታረም መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም የተፃፈ 4 /አራት/ ገፅ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም ከብር 500.00 (አምስት መቶ) በላይ በሆነ የገንዘብ ክርክር በፅሁፍ ማረጋገጫ ካልተደገፈ ተቀባይነት የለውም ተብሎ መዝገቡ እንዲዘጋ፤ በሽማግሌዎች ፊት ተጠሪ ገንዘብ ስለመውሰዱ አምኖልኛል የሚለው መከራከሪያም ከእውነት የራቀ ከመሆኑም በላይ የተቆጠሩት ምስክሮች የሰጡት ቃል እርስ በርሱ የሚጋጭና ገንዘቡን ሰጥቶኛል ብሎ ነግሮናል የሚል አመሰካከር በመሆኑና ገንዘቡን አመልካች ለተጠሪ ሲሰጥ አይተናል የሚል ባለመሆኑ የፍታብሄር ስነ ስርዓት ህጉን አንቀፅ 242 እና 128 ድንጋጌዎች አፈጻጻም ያልተከተለ ምስክርነት አሰጣጥ በመሆኑ፤ ያለሰነድ ተሰጠ ለተባለው ገንዘብ ተጠሪ ኃላፊነትም ተጠያቂነትም የለበትም ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት አልተፈፀመበትም ስለሆነም ሊጸና ይገባል የሚል ነው ፡፡ አመልካችም ሰኔ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በፃፈት 2/ሁለት/ ገፅ የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር የሰበር አቤቱታ ከቀረበበት ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው የህግ ዴንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመርነው ተጠሪ በሽማግሌዎች ፊት አምነው ለመክፈል ስለመስማማታቸው የሰነድ ማስረጃ አልቀረበም በማለት ገንዘቡን   መክፈል   ኃላፊነት


የለባቸውም ተብሎ መወሰኑ ተገቢ መሆን አለመሆኑ በጭብጥነት ተይዞ ሊታይ የሚገባው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

እንደሚታወቀው የፍትሃብሔር ግዴታ ከውል ወይም ከህግ ከሚመነጭ ግንኙነት  ላይ የሚመሰረት ሲሆን ክስ አቅራቢው ወገን የግዴታውን ምንጭ በመግለጽ የሚጠይቀውን ዳኝነት በዝርዝር የማቅረብ ግዴታ አበለት፡፡ ተከሳሹም በክሱ የተጠቀሰን ግንኙነት አስመልክቶ ዝርዝር በልሱን እንዲያቀርብ ይጠበቃል፡፡ በዚህ መልኩ ግንኙነቱ ተለይቶ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን የህጉን ድንጋጌዎች በመመልከት ግንኙነቱን ለማስረዳት ሊቀርብ ስለሚችለው ማስረጃ አይነት እና የማስረዳት ሸክሙ ስለሚያርፍበት ወገን በህጉ አግባብ ሊወሰን የሚገባ ይሆናል፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተፈጠረው የንግድ ግንኙነት ጀንፈል ቡና በጋራ ገዝተው አስበጥረው ለማእከላዊ ገበያ በማቅረብ ትርፉን ለመከፋፈል ስለመሆኑና የሚጠይቁትን ዳኝነት ገልፀው አመልካች ክስ ያቀረቡ ሲሆን በማስረጃነትም ጉዳዩን በሽምግልና አይተዋል የተባሉ ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡ ተጠሪ በሰጡት መልስ የተጠቀሰው ግንኙነት መኖሩን ሳይክዱ ከሳሽ ራሱ የቡና ሽያጭ ገንዘቡን ከባንክ የተቀበለ መሆኑን በክሱ ስላመነ ክስ ማቅረብ አይችልም ተብሎ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ፤ እንዲሁም ከብር 500.00 በላይ ያለሰነድ ማስረጃ መክሰስ አይችልም የሚሉ መቃወሚያወች እና በአማረጭም ከሳሽ ባቀረበው ሰነድ መሰረት ከባንከ ከተረከበው የድርሻቸውን ገንዘብ እንዲከፍል የሚጠይቅ መልስ አቅርበዋል፡፡

 

ከተደረገው ክርክር የግራቀኙ ግንኙነት በፅሁፍ ያልተረጋገጠ የሽርክና የንግድ ግንኙነት ስለመሆኑ ተገንዝበናል፡፡ በእንዲህ አይነቱ ግንኙነት ተቃራኒ ስምምነት ከሌላቸው በቀር ግራ ቀኙ ገቢ ላደረጉት መዋጮ ባለሀብትነቱን እንደያዙ ይቆያሉ፡፡ ተጠሪ በመከላከያ መልሱም ባይሆን በሌላ በማናቸውም መንገድ የተከሰሰበትን ነገር በሙሉ ወይም በከፊል የሚያምን መሆኑን የገለፀ እንደሆነ በእምነቱ መሰረት ይገባኛል የሚለው ማናቸውም ዳኝነት እንዲሰጠው አመልካቹ ሊጠይቅ እንደሚችል፤ በእንዲህ አይነቱ ሁኔታ የታመነውን ለማስረዳት የጽሁፍ የስምምነት ሰነድ ሊያቀርቡ ይገባል በሌላ አይነት ማስረጃ ሊያስረዱ አይችሉም የሚባልበት የህግ ምክንያት እንደሌለ ክርክሩ ከሚመራበት የስነ ስርዓት ህግ ድናጋጌዎች እና ከማስረጃ ፅንሰ ሃሳብ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለሆነም አመልካች ክሱን ለማስረዳት ያቀረቧቸው ማስረጃዎች ተቀባይነት የላቸዉም የሚባልበት የህግ ምክንት ባለመኖሩ፤ ይልቁንም ባቀረቡዋቸው ማስረጃዎች ተጠሪ ገንዘቡ እንዳለበቸውና ለመክፈል መስማማታቸውን ማስረዳታቸውን በማረጋገጥ የስር ፍርድ ቤት ያሳለፈው ውሳኔ የሚነቀፍበት ምክንያት የለም፡፡ በአንጻሩ የሰነድ ማስረጃ አልቀረበም ተብሎ ተጠሪ ኃላፊነት የለበትም ገንዘቡንም ሊከፍል አይገባም በማለት ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔውን መሻሩ እና የሰበር ችሎቱም ይህን ሳያርም ማለፉ ህጉን የተከተለ ሆኖ አላገኘንውም፡፡ ስለሆነም የክልሉ


ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ችሎቶች የሳለፉት ውሳኔ እና ትዕዛዝ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ብለናል፡፡

 

በሌላ በኩል አመልካች በቅሬታቸው የስር ፍርድ ቤት ዳኝነት የተጠየቀበትን ከቡና ሽያጭ የተገኘን ትርፍ ሂሳቡ እንዲጣራ አስደርጎ አለመወሰኑ እና የወለድ ጥያቄውን ማለፉ የህግ ስህተት ነው ተብሎ እንዲታረም የጠየቁ ቢሆንም በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የበኩላቸውን ይግባኝ ወይም መስቀለኛ ይግባኝ አቅርበው በየደረጃው ውሳኔ የተሰጠበት ባለመሆኑ አልተቀበልነውም፡፡

 

 ው ሣ ኔ

1. የጋምቤላ ብ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍ/ይ/መ/ቁ 01686/07 ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ያሳለፈው ውሳኔ፤ እንዲሁም የክልሉ ሰበር ችሎት በፍ/ሰ/መ/ቁ 00396/07 ህዳር 8 ቀን 2007 ዓ.ም ያሳለፈው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 348 (1) መሠረት ተሽሯል፡፡

2. የማጃንግ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍ/መ/ቁ/ 01978/06 ጳጉሜ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ያሳለፈው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 348 (1) መሠረት ፀንቷል፡፡

3. በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ፊት ስለተደረገው ክርክር ያወጡትን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

 

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡