103151 family law/ minors/ acts of minor

ሞግዚት የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ፈጽሞ ሲገኝ ሊወሰዱ ስለሚገቡ ዝርዝር ሁኔታዎች የሕግ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ሞግዚቱ ለሚፈጽማቸው ድርጊቶች፤ ወኪል የሆነ ሰው ከተሰጠው ሥልጣን በላይ በሚሠራበት ጊዜ አግባብነት ያላቸው የውክልና ሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ የሚሆኑ ስለመሆኑ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁ.213/1992 አንቀጽ 306፣277 የፍ/ብ/ሕ/ቁ.2207/1

የሰ/መቁ.103151

መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ

ሌሊሴ ደሳለኝ

 

አመልካች፡- አቶ ግርማ ብሩ አየለ - ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- አቶ መርዕድ ብስራት - ጠበቃ አበበ ማስረሻ ጋር ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ይህ ጉዳይ የቤት ሽያጭ ውል እንዲፈርስ የቀረበ ክስን መነሻ ያደረገ ክርክር ነው፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ፡- የሥር ከሳሽ /የአሁን ተጠሪ/ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ የወላጅ አባቴ እና የ2ኛ ተከሳሽ የጋራ ንብረት የሆነውን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 03 የቤት ቁጥር አዲስ ካረታ ቁ.3329 የሆነውን ቤት 2ኛ ተከሳሽ ከሞግዚትነት ስልጣን ተቃራኒ ሚያዝያ 23 ቀን 2000 ዓ.ም በተደረገ ሽያጭ ውል ለ1ኛ ተከሳሽ በብር 350,000 የሸጠች ስለሆነ 1ኛ ተከሳሽም /የአሁኑ አመልካች/ የከሳሽና የሌሎች ሰዎች የጋራ ንብረት መሆኑን እያወቀ ለቅን ልቡና ተቃራኒ በሆነ መንገድ ስለገዛ የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስልኝ፣ 1ኛ ተከሳሽ ቤቱን እንዲያስረክበኝ በማለት አመልክቷል፡፡

 

ይህን ክስ በተመለከተ ተከሳሾች መልስ እንዲሰጡበት የታዘዘ ሲሆን የሥር 1ኛ ተከሳሽ /የአሁን አመልካች/መጥሪያ ደርሶት የጽሑፍ መልስ ስላልሰጠ ታልፏል፡፡ የሥር 2ኛ ተከሳሽ በሰጠችው መልስ ባለቤቴ ከሞተ በኋላ ልጆች ለማሳደግ የተቸገርኩ በመሆኑ የቤት ሽያጭ ውል ፈጽሜአለሁ፡፡ 1ኛ ተከሳሽም የቤቱን ሸያጭ ገንዘብ እንደውሉ አልከፈለኝም፤ እኔ ቤቱን የሸጥኩኝ ለከሳሽና ለሁለት ወንድሞቹ ጥቅም እንጂ ለግሌ ጥቅም አይደለም፤ ፍ/ቤቱ የመሰለውን ውሳኔ ቢሰጥ አልቃወምም በማለት ተከራክራለች፡፡ 1ኛ ተከሳሽ ክርክር በሚሰማበት ቀን ቀርቦ  ሲከራከር


ሞግዚት የማይንቀሳቀስ ንብረት መሸጥ ትችላለች፣ እኔ በቤቱ ላይ ሰፊ ለውጥ ያደረኩ ስለሆነ ውሉ ሊፈርስ አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡

 

ከዚህ በኋላ ፍ/ቤት ግራ ቀኙን በማከራከር፣ የከሳሽን የሰው ምስክር በመስማት በሰጠው ውሳኔ በተከሳሾች መካከል ሚያዝያ 23 ቀን 2000 ዓ.ም የተደረገው የቤት ሽያጭ ውል የልጆችን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ስለተፈጸመ ፈርሶ ተዋዋይ ወገኖች ወደ ነበሩበት ይመለሱ፣ 2ኛ ተከሳሽ ብር 60,000 ለ1ኛ ተከሳሽ ትመልስ፣ 1ኛ ተከሳሽ በገዙት ይዞታ ሲገለገሉበት በነበረው ቤት ላይ ያወጡት ወጪ ካለ ክስ አቅርቦ መጠየቅ ይችላል በማለት ወስኗል፡፡ የሥር 1ኛ ተከሳሽ ይህን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ማመልከቻውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን በማከራከር በሰጠው ውሳኔ፣ የቤቱ ሽያጭ ዋጋ በአብዛኛው ስላልተከፈለ 2ኛ ተከሳሽ ለግል ጥቅም አውላለች፣ የልጆች ቅጥም ላይ ጉዳት ድርሷል የሚያስብል ስላልሆነ፣የሽያጭ ውሉን ለማፍረስ በቂና አሳማኝ ምክንያት ስለሌለ ሊፈርስ አይገባም በማለት የሥር ውሳኔ በመሻር ወስኗል፡፡ የሥር ከሳሽ ይህን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ማመልከቻውን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን በማከራከር በሰጠው ውሳኔ፣ የቤት ሽያጭ ውሉ የከሳሽን ጥቅም የሚጎዳ ስለሆነ ውሉ ሊፈርስ ይገባል በማለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት  ውሳኔ በመሻር የፌዴራል የመጀመያ ደረጃ ፍ/ቤት ውሳኔን በማጽናት ወስኗል፡፡ የአሁን የሰበር አቤቱታም ይህን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ የቀረበ ነው፡፡

 

የአሁን አመልካች ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም በተጻፈ አቤቱታ የተጠሪ ሞግዚትና አስተዳዳሪ የነበሩት ወ/ሮ ክብካብ አስፋው የቤት ሽያጭ ውሉን ያደረጉት ለተጠሪ እና ለሌሎች ሁለት ወንድሞቻቸው መልካም አስተዳደር ስለሆነ ውሉን የተደረገው ለልጆቹ ቅጥም መዋሉ በተጠሪም ሞግዚት በጽሑፍ እና በምስክሮች በስር ፍ/ቤት የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ ውሉ ሊፈረስ  ይገባል በማለት የተሰጠ ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው፡፡ የተጠሪ ሞግዚት ከተቀበለችው የቤት ሽያጭ ውሉ ገንዘብ የተጠሪ ድርሻ ብር 10,000 ብቻ ስለሆነ ውሉ የሚፈርስበት ምክንያት የለም፡፡ አመልካች ቤቱን ከገዛሁ በኋላ ሌላ አዲስ ሰርቪስ ቤት ክፍሎች ብር 450,000 በላይ ወጪ በማድረግ በቤቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የይዘት ለውጥ አድረጎበታል፡፡ ስለዚህ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ውሉ ፈርሶ ወደ ነበራችሁበት ተመለሱ በማለት የወሰኑት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለው ስለሆነ እንዲሻርልኝ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲፀናልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

 

የሰበር አጣሪ ችሎትም መዝገቡን በመመርመር "በአመልካች እና በተጠሪ ሞግዚት መካከል የተደረገው የቤት ሸያጭ ውል ይፍረስ ተብሎ በሥር ፍ/ቤቶች የመወሰኑን አግባብነት ከመዝገብ ቁ.46490 አንጻር ለመርመር ሲባል አቤቱታው ለሰበር ያስቀርባል በማለት ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ


በታዘዘው መሰረት መስከረም 7 ቀን 2007 ዓ.ም የተጻፈ መልስ አቅርቧል፡፡ የመልሱ ይዘትም፡- የተጠሪ ሞግዚት የማይንቀሳቀስ ንብረት መሸጥ አትችልም፡፡ እኔ ከቤቱ ድርሻ እያለኝ ያለ እኔ ፈቃድ ሸጣለች፡፡ የተጠሪ መብት መጣስ እና መጎዳት የሚጀምረው ከዚህ መሰረታዊ ከሆነው የባለቤትነት መብቶች አኳያ ስንነሳ ነው፡፡ እኔ በቤቱ ሽያጭ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰብኝ አስረድቼአለሁ፣ አመልካች ግን ከሽያጩ ጥቅም ያገኘሁት መሆኑን አላስረዳም፡፡ አመልካች ከቤቱ ሽያጭ ገንዘብ የከፈለው ብር 60,000 ብቻ ሲሆን ቤቱን ተረክቦ እያኖረበት ነው፣ ከጉዳት በቀር ጥቅም ሊኖር አይችልም፡፡ ተጠሪው በሽያጩ ጉዳት እንጂ ያገኘሁት ጥቅም ስለሌለ ለሰበር መዝገብ ቁ.46490 ከሰጠው ውሳኔ ጋር የማይቃረን ስለሆነ ውሳኔው እንዲፀናልኝ፣ የቀረበው አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግልኝ፡፡ አመልካች ከቤቱ ድርሻ የተጠሪ ድርሻ 10,000 ብር ብቻ ስለሆነ ሊፈርስ አይገባም በማለት ያቀረበው ክርክር የባለቤትነት መብትን የጣሰ እና ሕጉ ተቃራኒ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡ አመልካቹ በቤቱ ላይ ግንባታ ስለመካሄዱ ያቀረበው ማስረጃም የለም፣ በቤቱም ላይ የይዘትም ሆነ የቅርጽ ለውጥ አላደረገም፣ የተጠሪ ሞግዚት የቤት ሽያጩን ገንዘብ ማባከናቸውን እንጂ ለልጆች ጥቅም ያወሉት መሆኑን ያረጋገጠ ማስረጃ  የለም፡፡ ስለዚህ አመልካች ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ሆኖ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም ተብሎ እንዲፀናልኝ፣ ወጪና ኪሳራ እንዲወሰንልኝ በማለት ተከራክሯል፡፡ አመልካች ጥቅምት 04 ቀን 2007 ዓ.ም በተጻፈ የመልስ መልስ አቤቱታውን በማጠናከር ተከራክሯል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ እንደተመለከተ ሲሆን፤ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎትም የግራ ቀኙ  ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው  የሕግ  ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ አቤቱታው ያስቀርባል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡ መዝገቡን እንደመረመርነው ተጠሪ ባቀረበው ክስ የሽያጭ ውል የተፈጸመበት ቤት ላይ ድረሻ እያለኝ የእኔን ጥቅም በሚጎዳ መልክ ሞግዚት የሆነችው ወ/ሮ ክብካብ ሣህሉ ወልደማርያም በሽጨጭ ውል ለአመልካች የሸጠች ስለሆነ ውሉ እንዲፈርስልኝ በማለት አልክቷል፡፡ የተጠሪ ሞግዚት /የሥር 2ኛ ተከሳሽ/ በጽሑፍ ባቀረበችው መልስ ቤቱን የሸጥኩት ለተጠሪ እና ለሌሎች ወንድሞቹ ቅጥም ነው በማለት የተከራከረች ቢሆንም እንደምስክር ሆነ በሰጠችው ቃል ደግሞ ከቤቱ ሽያጭ ገንዘብ ውስጥ ብር 60,000 ብቻ የተቀበለች እንደሆነና ለራሷ ትምህርት ክፍያ እንደከፈለችና ቀሪውን ለወንድሟ እንዳበደረች ገልጻለች፡፡ አመልካች በበኩሉ መጥሪያ ደርሶት የፍሑፍ መልስ ባለመስጠቱ የታለፈ ስለሆነ የጽሑፍ መልስ እና ማስረጃ በማቅረብ በማስረዳት መከራከር የነበረበትን ክርክር በተመለከተ መብት አጥቷል፡፡ ስለዚህ አልካች በጽሑፍ መከራከር የነበረበትና ማስረጃ በማቅረብ ማስረዳት የነበረበትን ፍሬ ነገር በተመለከተ አሁን ለማንሳት የሚችልበት የሕግ መሰረት የለውም፡፡ ተጠሪ ባቀረበው ክርክር አመልካች ከተጠሪ ሞግዚት  ጋር


የቤት ሽያጭ ውሉን ሲፈጽም በቤቱ ላይ ልጆች ድርሻ ያላቸው መሆኑን ውሉ እያመለከተ ነው ቤቱን የገዛው የሚለውን፣ አመልካች ይህን ፍሬ ነገር ክዶ እየተከራከረ አይደለም፡፡ አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው በሞግዚቱ በኩል የተደረገው የቤቱ ሽያጭ ለልጆች ጥቅም ነው እንጂ ጥቅማቸውን የሚጎዳ አይደለም የሚል ነው፡፡ የተጠሪ እናት የሆነችው የሥር 2ኛ ተከሳሽ የተሻሻለው የቤተሰብበ ሕግ አዋጅ ቁ.213/1992 አንቀጽ 220/1/ መሰረት ሕጋዊ የሞግዚትነት ስልጣን እንደተሰጣቸው ከመዝገቡ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት የሥር 2ኛ ተከሳሽ ተጠሪን በመወከል ሕጋዊ ተግባሮችን ለተጠሪ ጥቅም ለመፈጸም ስልጣን የተሰጣቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ በዚሁ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 277 የሞግዚት ስልጣን በተመለከተ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከመሸጥ ጋር ተያይዞ የሚለው ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን ሕጉ ሞግዚት መሸጥ የሚችላቸውን የንብረት ዓይነቶች በመዘርዘር በማስቀመጡ፣ ከዚህ ዝርዝር ወጭ ያሉትን ንብርቶች በተመለከተ ሞግዚት መሸጥ አይችልም ቢባል እንኳን ሞግዚት የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ፈጽሞ ከተገኘ ግን ምላሸ ለማግኘት ሌላ ሕግ መፈተሽ አስፈላጊ ሆኖ ይታያል፡፡ ከዚህ አንጻር የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁ.213/1992 አንቀጽ 306 እንደሚደነግገው "የሕግ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ሞግዚቱ ለሚፈጽማቸው ድርጊቶች፤ ወኪል የሆነ ሰው ከተሰጠው ሥልጣን በላይ በሚሠራበት ጊዜ አግባብነት ያላቸው የውክልና ሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ" የሚል ነው ፡፡ በዚህ መሰረት ተወካዩ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ በመውጣት የሰራውን ስራ በተመለከተ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.2207/1/ እንደሚያመለክተው "ተወካዩ ከስልጣኑ ውጭ የሠራው ስራ በቅን ልቡና ሆኖ ሲገኝ ሥራውን ወካዩ እንዲያጸድቅለት ይገደዳል" የሚል ነው፡፡ በዚህ አግባብ የሞግዚቱ "ቅን ልቡና" መታየት ያለበት የተሰራ ስራ የልጁን ጥቅም የሚጎዳ ነው ወይስ አይደለም? ከሚል አንጻር መሆን እንዳለበት ነው፡፡

 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁ.46490 መጋቢት 21 ቀን 2002 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሞግዚት የማይንቀሳቀስ ንብረት ለልጆች መልካም አስተዳደግና ጥቅም የሸጠ መሆኑ ከተረጋገጠ የሽያጭ ውል ለማፍረስ የሚያስችል በቂ ምክንያት አይደለም በማለት ወስኗል፡፡ ይህ ማለት የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭን በተመለከተ የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም የሚል ጭብጥ መታየት ያለበት ለልጆች ቅጥም መሆን አለመሆኑን በማጣራት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በተጠሪ ሞግዚት እና በአልመካች መካከል የተደረገውን የቤት ሽያጭ ውል ለተጠሪ እና ለሌሎች ወንድሞቹ ጥቅም የዋለ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ጭብጥ ሲታይ ለተጠሪ ጥቅም መዋሉን የሚያመለክት ምንም ነገር የለም፡፡ የተጠሪ ሞግዚት ከቤቱ ሽያጭ አመልካች የከፈላት ገንዘብ ብር 60,000 እንደሆነ ከዚህ ውስጥ ብር 10,000 ለትምህርት እንደከፈለች፣ ቀሪውን ለወንድሟ እንዳበደረች አረጋግጣለች፡፡  ይህ ማለት ከቤት ሽያጭ የተገኘው ገንዘብ ለተጠሪም ሆነ ለሌሎች ልጆች አለመዋሉን   ያመለክታል፡፡


እንዲሁም ከቤቱ ሽያጭ የተገኘ ገንዘብ ለልጆቹ ጥቅም መዋሉን የሚያመለክት ማስረጃ መቅረቡን የሥር ፍ/ቤቶች ያረጋገጡት ነገር የለም፡፡ አመልካች ራሱ ከቤቱ ሽያጭ ብር 350,000 ውስጥ እስካሁን የከፈለው ብር 60,000 ብቻ ሲሆን ቀሪውን ገንዘብ ያለመክፈሉ ግራ ቀኙ የሚካከዱት ጉዳይ ስላልሆነ፣ የቤቱ ሽያጭ ውል ለተጠሪ እና ለሌሎች ልጆች ጥቅም የዋለ ነው ለማለት የሚያችል አንድም ነገር የለም፡፡ አመልካች ቤቱ የተሸጠበትን ገንዘብ አብዛኛውን ሳይከፍል እንዲያውም አነስተኛ ገንዘብ ብቻ ከፍሎ በዚህ ሽያጭ የልጆቹ ጥቅም ተጠብቆላቸዋል፣ የሽያጭ ውሉም ለልጆች ጥቅም የተደረገ ነው፤ ለተጠሪና ለሌሎች ወንድሞቹ መልካም  አስተዳደግ ውሏል በማለት የሚያቀርበው ክርክር ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አይታይም፡፡ ስለዚህ የሚያዝያ 23 ቀን 2000 ዓ.ም በተጠሪ ሞግዚትና በመአልካች መካከል የተደረገው የቤት ሽያጭ ውል ለተጠሪና ለሌሎች ወንድሞቹ ማለትም ለልጆች ጥቅም እና መልካም አስተዳደግ ያልዋለ መሆኑ ስለተረጋገጠ፣ የሸያጭ ውሉ ሌፈርስ አይገባም በማለት አመልካች ያቀረበው ክርክር በየትኛውም የሕግ መመዘኛ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

ሌላው አመልካች ባቀረበው ክርክር ተጠሪ ከቤቱ ያለው ድርሻ አነስተኛ መሆኑን በመግለጽ ለውሉ መፍረስ መክንያት ሊሆን አይችልም የሚለው ሲታይ ተጠሪ ከቤቱ ድርሻ እስካለው ድረስ የጋራ ንብረቱ ከሱ ፈቃድ ውጭ መሸጥ የሌለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከልጆች መብት አንጻር የአመልካች ክርክር ተቀባይነት የለውም፡፡ በሌላ በኩል አመልካች ቤቱን ከገዘሁ በኋላ በቤቱ ላይ ግንባታ አካሄጃለሁ ያለውን በተመለከተ ተጠሪ ምንም ዓይነት ግንባታ አልተደረገም በማለት ክዶ የተከራከረ ሲሆን፣ አመልካች ደግሞ የጽሑፍ ክርክር በማቅረብ በማስረጃ ስላላስረዳ፣ በሥር ፍ/ቤት በማስረጃ ያላስረዳውን ክርክር ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንደቅሬታ ነጥብ ማቅረቡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.329/1/ መሰረት ተቀባይነት የለውም፡፡ በአጠቃላይ የሥር ፍ/ቤቶች የሽያጭ ውሉ የልጆችን ጥቅም የሚጎዳ ስለሆነ ውሉ ፈርሶ ግራ ቀኙ ወደ ነበሩበት ሊመለሱ ይገባል፣ አመልካች በቤቱ ላይ ያወጣ ወጪ ካለ ከሶ መጠየቅ ይችላል በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተተ የሌለው በመሆኑ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁ.201566 በ07/08/2005 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ፣ እንዲሁም የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁ.137501 ታህሳስ 22 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠውን ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለው  በመሆኑ በመሻር የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁ.98101 በ22/09/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሌለው በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348/1/ መሰረት ጸንቷል፡፡


 

2.  የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይድረስ ብለናል፡፡

3. ግራ ቀኙ በዚህ ችሎት የደረሰባቸውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ በውሳኔ ስለተዘጋ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

ማ/አ