99447 contract/ contract of carriage/ damage

በማጓጓዝ ውል ግንኙነት በደረሰ የሕይወት ሕልፈት የሚከፈል ካሣ በንግድ ህጉ መሰረት ስለመሆኑ

 

የሰ/መ/ቁ.99447

.ጥቅምት 26 ቀን 2008 ዓ.ም.

 

ዳኞች:- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች:- አቶ ተፈራ ጣሰው - የቀረበ የለም ተጠሪ:- ወ/ሮ ፈንታዬ በንቲ - የቀረበ የለም

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

 

 ፍ  ር ድ

 

ጉዳዩ በተሸከርካሪ መገልበጥ ምክንያት ከደረሰ የሞት አደጋ ጋር ተያይዞ የተነሳ የጉዳት ካሳ ክፍያ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ በተጀመረበት የምዕራብ ሸዋ ዞን ከ/ፍ/ቤት ከሳሽ በመሆን ክሱን የመሰረቱት ተጠሪ ናቸው፡፡ ተጠሪ ክስ የመሰረቱት በአሁኑ አመልካችና አቶ አስማማው ደረጀ በተባሉ ግለሰብ ሲሆን ክሱም በ15/03/2003 ዓ.ም. አዘጋጅተው ያቀረቡት ነው፡፡ የክሱ ይዘት ባጭሩ፡- ንብረትነቱ የተከሳሾች የሆነና የሰሌዳ ቁጥሩ 3-30038 አ.አ. የሆነ አይሱዚ ተሽከርካሪ በ04/05/2002 ዓ.ም. በደረሰ አደጋ በመገልበጡ ከጌዶ ወደ አዲስ አበባ ተሳፍረው ሲጓዙ በነበሩት የከሳሽ ባለቤት አቶ እንዳሉ ባይሳ ላይ የሞት አደጋ እንደደረሰ፣ ባለቤታቸው በንግድ ስራ ያገኙት ከነበረው ገቢ ከሳሽን እንዲሁም የ 4 እና የ 2 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ሁለት ልጆቹን ያስተዳድር እንደነበረ እና በሞቱ ምክንያት በመተዳደሪያ ረገድ ጉዳት እንደደረሰባቸውና በጉዳቱ ጊዜ ደግሞ ወጪ ያወጡ መሆኑን የሚገልጽ ሆኖ በድምሩ ብር 349,192.61(ሶስት መቶ አርባ ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ ዘጠና ሁለት ብር ከስልሳ አንድ ሳንቲም)፣ የጠበቃ አበል 10% እና ለክሱ የወጣውን ወጪና ኪሳራ ተከሳሾች እንዲከፍሉ  ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው፡፡ 2ኛ ከሳሽ የነበረውን ግለሰብ ከተጠሪ ጋር በእርቅ በመጨረሳቸው ምክንያት ከክሱ ውጪ የሆኑ ሲሆን የአሁኑ አመልካች ግን ወደ ክርክሩ ተጠርተው በሰጡት መልስ ጉዳዩ ከስር 2ኛ ተከሳሽ ከነበሩት የመኪናው የጋራ ባለሃብት ጋር በእርቅ በማለቁ ክስ


ሊቀርብበት እንደማይገባ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ከአስቀደሙ በኋላ በፍሬ ነገር ደረጃ ደግሞ ሟቹ ተሽከርካሪውን ባለው ግንኙነት ለምኖ በነጻ የተሳፈረና የሄደ በመሆኑ ለጉዳቱ ኃላፊነት እንደሌለባቸው፣ የሟቹ ገቢ መጠንም ተቀባይነት እንደሌለውና የተቋረጠ ገቢ የሌለ መሆኑን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የስር ፍርድ ቤትም የአሁኑ አመልካች ያቀረቡትን መቃወሚያ ውድቅ አድርጎ በፍሬ ነገሩ ላይ ግራ ቀኙንና ማስረጃዎቻቸውን ከሰማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካችን ለክሱ ኃላፊ ያደረጋቸው ሲሆን የኃላፊነቱን መጠን በተመለከተም በትክክል ሟቹ ያስገኙ የነበረው የቀን ገቢ በተጠሪ ምስክሮች እንደተገለፀው ያለመሆኑን ደምድሞ መካከለኛ ያለውን የቀን ገቢ በብር 20.00 ፍርድ ቤቱ ይዞ እና ሟች ለ15 አመታት ሊሰሩ ይችሉ ነበር በማለት በድምሩ 100,800.00(አንድ መቶ ሺህ ስምንት መቶ ብር ) ለተቋረጠ ገቢ ወስዶና በአደጋው ምክንያት የወጣውን ወጪ ደግሞ ብር 6000.00(ስድስት ሺህ)፣የሞራል ካሳ ብር 1000.00 በመያዝ በድምሩ ብር 107,800.00(አንድ መቶ ሰባት ሺህ ስምንት መቶ ብር) አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍሉ ውሳኔ ሰጥቶአል፡፡

 

የአሁኑ አመልካች በዚህ ውሳኔ ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ አመልካች ለክሱ ኃላፊ መባላቸው በአግባቡ መሆኑን፣የኃላፊነት መጠንን በተመለከተ ግን በተጨባጭ ይገኝ የነበረው ገቢ የሚያስቸገር መሆኑንና ተጠሪ ከስር 2ኛ ተከሳሽ ከነበሩት የመኪናው የጋራ ባለሃብት ጋር ባደረጉት የእርቅ ስምምነትም ብር 14,000.00 የተከፈላቸው መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባትና በርትዕ መወሰን ተገቢ መሆኑን ገልጾ ብር 56,000.00 (ሃምሳ ስድስት ሺህ) እንዲከፈላቸው በማለት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አሻሽሎ ወስኗል፡፡ከዚህም በኋላ የአሁኑ አመልካች የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ችሎቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ በአመልካችና በተጠሪ መካከል የነበረው ግንኙነት የትራንስፖርት ግንኙነት መሆኑን፣ ግንኙነቱ የትራንስፖርት ቢሆንም በዚህ ረገድ ያለው ሕግ ስለ ካሳ የሚደነግገው ሁኔታ ያለመኖሩን ጠቅሶ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2095 ድንጋጌ መሰረት ካሳው መሰላት እንደአለበት፣ በዚህ አግባብ ሲሰላም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው የካሳ መጠን ውሳኔ መኪናው የጋራ ባለሃብትነት የተቋቋመበት መሆኑን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተሰጠ መሆኑን መገንዘቡን ዘርዝሮ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አፅንቶታል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የተጠሪ ባለቤት  የሆኑት ሟች ከአመልካች ጋር የጥቅም ግንኙነት የነበራቸው ስለመሆኑ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ አመልካች ለሞት አደጋው ኃላፊ መደረጋቸው ያላግባብ መሆኑን፣የትራንስፖስርት ግንኙነት ነበር ከተባለም የካሳ መጠን በንግድ ሕጉ መወሰን ሲገባ ከውል ውጪ ኃላፊነትን መሰረት አድርጎ መወሰኑ ያላግባብ መሆኑን፣ እና አደጋውን አደረሰ የተባለን መኪና አመልካች ከስር 2ኛ ተከሳሽ ጋር በጋራ


ያፈሩት መሆኑና ይኼው የጋራ ባለሃብት ደግሞ ከተጠሪ ጋር በአደረጉት እርቅ መሰረት ብር 14,000.00 ከፍለው እያለ ክሱ መቀጠሉ ያላግባብ መሆኑን፣ ክሱ መቀጠሉ ተገቢ ነው ከተባለም አመልካች ኃላፊ ሊሆኑ የሚችሉት በድርሻቸው መጠን መሆኑን ዘርዝረው የበታች ፍርድ ውሳኔ እንዲታረምላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪም ቀርበውም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጎአል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በክርክሩ እልባት ማግኘት የሚገባው ጭብጥ የስር ፍ/ቤቶች የአመልካቹን ኃላፊነት እና የኃላፊነት መጠን ለመወሰን ከውል ውጪ ኃላፊነትን የሚመለከቱ የፍትሐብሔር  ሕጉን ድንጋጌዎች መሰረት ያደረጉት በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚል ነጥብ መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩን ከዚሁ ጭብጥ አንፃር መርምረናል፡፡

 

በዚህም መሰረት የአመልካችና የስር 2ኛ ተከሳሽ የጋራ ንብረት የሆነው አይሱዙ ተሸከርካሪ ተገልብጦ በስር በተጠሪ ባለቤት ላይ ለደረሰው የሞት አደጋ ምክንያት የሆነው ተሽከርካሪ የጭነት ማመላለሻ መሆኑ እና ሟችም የእህል ነጋዴ ሁነው በተሽከርካሪው ሲጓዝ የነበሩት ከመኪናው የጋራ ባለሃብቶች ጋር የጥቅም ግንኙነት ሳይኖር ስለመሆኑ በአመልካች በማስረጃ ያልተረጋገጠ መሆኑን ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ባላቸው የክልሉ የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የተሽከርካሪው የጋራ ባለሃብት የሆኑት የአሁኑ አመልካች ሟቹ ከእህል ንግድ ጋር ተያይዞ በነበራቸው የመጓጓዣ ውል መግባታቸውን የሚያመለክት ሲሆን የማጓጓዝ ውል ማለት  አጓዥ ዋጋ በመቀበል ሰውን፣ ጓዝን እና ዕቃዎችን ከተወሰነ ስፍራ ለማድረስ ግዴታ የገባበት ስምምነት ማለት መሆኑ በን.ሕ.ቁ. 561 ተመልክቷል፡፡ የዚህ ዓይነቱን ውል የገባ አጓዥ መንገደኛው በመንገድ ላይ ስለሚደርስበት መዘግየት፣ እንዲሁም በጉዞው ጊዜ ወይም በሚሳፈርበትና ወይም በሚወርድበት ጊዜ በአደጋ ምክንያት ለሚደርስበት መቁሰል ወይም የአካል መጉደል ወይም የሕይወት ማለፍ ኃላፊ መሆኑ በን.ሕ.ቁ.595 የተመለከተ ሲሆን በን.ሕ.ቁ. 599 በተመለከተው መሰረት ጉዳቱ የደረሰው አጓዡ በፈጸመው ተግባር ወይም ባደረገው ጉድለትና እንዲሁም ይህ ተግባርና አደጋ ጉዳት ሊያደርስ ወይም ሊፈጥር የሚችል መሆኑን እያወቀ በጥንቃቄ ጉድለት መሆኑ ካልተረጋገጠ በቀር የተጎዳው ማንኛውም ዓይነት መንገደኛ ቢሆን አጓዡ በኃላፊነት ለአንድ መንገደኛ የሚከፍለው የካሳ መጠን ከብር 40,000 እንደማይበልጥ በዚሁ ሕግ በቁጥር 597(1) ተደንግጓል፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ ባቀረቡት ክስ ተሽከርካሪው ተገልብጦ በባለቤታቸውን እና በልጆቻቸው አባት ላይ የሞት አደጋ ማድረሱን ከመግለጽ በስተቀር ለመገልበጡ በምክንያትነት የሚጠቀስ


በአሽከርካሪው ወይም በተሽከርካሪው ባለቤት የተከሰተ ጥፋት፣ ቸልተኝነት ወይም የጥንቃቄ ጉድለት ስለመኖሩ የገለጹት ነገር ያለመኖሩን የመዝገቡ ግልባጭ  ያመለክታል፡፡ በመሰረቱ ለደረሰው አደጋ ካሳው በንግድ ሕጉ ከተመለከተው ጣሪያ ከፍ ብሎ ሊወሰንልኝ ይገባል የሚል ከሳሽ አደጋው የደረሰው በአጓዡ ወይም የአጓዙ ሰራተኛ በሆነ ሰው ጥፋት ወይም የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን ማስረዳት የሚጠበቅበት ሲሆን በተያዘው ጉዳይ ግን አደጋው የደረሰው በአጓዡ ወይም በሰራተኛው ጥፋት ወይም ጉድለት ምክንያት ስለመሆኑ የተጠሪ የክስ ማመልከቻ አይገልጽም፡፡ ስለሆነም የአመልካችና የተጠሪ ባለቤት ግንኙነት የመጓጓዣ ውልን መሰረት ያደረገ ነው ከተባለና በን/ሕ/ቁጥር 599 አግባብ አደጋው መድረሱ እስካልተረጋገጠ ድረስ በዚህ አይነት ግንኙነት ለሚደደርሰው የሞት አደጋ የካሳ መጠን ከውል ውጪ ኃላፊነትን በሚገዛው የህግ ክፍል የተመለከቱት የካሳ አተማመን ድንጋጌዎች መሰረት ሊሆኑ የሚችሉበት ሕጋዊ አግባብ የለም፡፡፡

 

የካሳው መጠን መወሰን የሚገባው በንግድ ህጉ በተመለከተው ጣሪያ ነው፡፡ቀደም ሲል በውሳኔው ላይ እንደተገለጸው በንግድ ሕጉ በቁጥር 597 ድንጋጌ መሰረት የአመልካች የኃላፊነት ጣሪያ በብር 40,000 የተገደበ ሲሆን በስር ፍ/ቤት 2ኛ ተከሳሽ የነበረው ግለሰብ የመኪናው የጋራ ባለሃብት ነው፡፡ አመልካችና እኚህ ግለሰብ በመኪናው ላይ ያላቸው ድርሻ የሚበላለጥ ስለመሆኑ የክርክሩ ሂደት የማያሳይ በመሆኑ ሃላፊነቱ እኩል ሊካፈሉት የሚገባ ነው፡፡ የስር 2ኛ ተከሳሽ ከተጠሪ ጋር ያደረጉት እርቅ አመልካች ስምምነታቸውን የሰጡ ስለመሆኑ ባልተረጋገጠበት  ሁኔታ ለአመልካችም ተፈፃሚ የሚደረግበት አግባብም የለም፡፡ እንዲህ ከሆነ አመልካች ለተጠሪ ሊከፍሉ የሚገባው የካሳ መጠን ብር 20,000.00(ሃያ ሺህ) ነው፡፡

 

ይሁን እንጂ ተጠሪ ከአደጋው ጋር ተያይዞ ያወጡት ወጪ በማስረጃ የተረጋገጠውን ገንዘብ ብር 6000.00 ግማሹን ብር 3000.00(ሶስት ሺህ) አመልካች ለተጠሪ ሊተኩላቸው የሚገባ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

 

ሲጠቃለልም በአመልካች በተጠሪ መካከል ያለው ግንኙነት የመጓጓዣዣ ውል  ተብሎ ከተደመደመ በኋላ የካሳው መጠን ሊሰላ የሚገባው በንግድ ሕጉ መሰረት ሳይሆን ከውል ውጪ ኃላፊነትን በሚመለከቱ የፍትሐብሔር ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ነው በማለት እና ከሳውንም በዚሁ መሰረት በማስላት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበትና ሊታረም የሚገባው በመሆኑ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡


 

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 140813 በ13/03/05 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ. 158714 በ26/05/2006 ዓ.ም ምክንያቱ ተለውጦ የፀናው ውሳኔ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 348(1) መሰረት ተሻሽሎአል፡፡

2. ተሽከርካሪው የጭነት ማመላለሻ ቢሆንም ሟች ከነበራቸው የንግድ ስራ ጋር በተያያዘ የመጓጓዣ ውል ግንኙነት ከአመልካች ጋር የነበራቸው በመሆኑና የመገልበጥ አደጋ የደረሰበትም በአጓዡ ወይም በሰራተኛው ጥፋት ወይም የጥንቃቄ ጉድለት ስለመሆኑ ከሳሽ ወገን ክርክርም ሆነ ማስረጃ ያላቀረበበት በመሆኑ ለካሳ  መጠን አወሳሰኑ አግባብነት ያለው የፍትሐብሔር ሕጉ ሳይሆን የንግድ ሕጉ ነው በማለት ወስነናል፡፡

3. በተጠሪ ባለቤት እና የልጆች አባት ላይ ለደረሰው የሞት አደጋ በጉዳት ካሳ ረገድ የአመልካቹና የስር 2ኛ ተከሳሽ የኃላፊነት መጠን ጣሪያ በንግድ ሕግ በቁጥር 597(1)ድንጋጌ መሰረት ብር 40,000 ነው በማለት ወስነናል፡፡በዚህም  መሰረት አመልካች ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ግማሹን ብር 20,000.00(ሃያ ሺህ ብር) ለሞት አደጋው ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል በማለት ወስነናል፡፡ በአደጋው ምክንያት  ተጠሪ ከአወጡት ወጪ ደግሞ ብር 3000.00 እንዲሁም ለሞራል ካሳ ብር 500.00 አመልካች ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል ብለናል፡፡

4. የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ተዘግቶአል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት