118252 criminal procedure/ appeal/ stay of exectuion

በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 188/5/ መሰረት አንድ ፍርድ በተከሳሽ ላይ ከተሰጠ ተከሳሹ ለበላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ሲቀርብ የበታች ፍርድ ቤትን ውሳኔ የበላይ ፍርድ ቤቱ ማገድ የሚችልበትን አግባብ የሚያሳይ ድንጋጌ ከመሆኑ ውጪ ከሳሽ ወገን በተከሳሽ ነፃ መለቀቅ ላይ ይግባኝ ብሎ ሲሄድ ፍርዱ እንዳይፈፀም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለመስጠት መነሻ የሚያደርገው ስላለመሆኑ

 

የሰ/መ/ቁ. 118252

ቀን 24/05/2008 ዓ/ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንደሻው አዳነ ቀንዓ ቂጣታ

አመልካች፡- ሀብታሙ አያሌው - ጠበቃ አመሃ መኮንን - ቀረቡ

 

ተጠሪ፡- የፌዴራል ዐቃቤ ህግ - ዐ/ህግ ብርሃኑ ወንድምአገኘሁ - ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ አንድ በሽብር ወንጀል የተከሰሰ ሰው ከክሱ ምንም መከላከል ሳያስፈልገው በነጻ ሲሰነበት በዚሁ ብይን አቃቤ ህግ ይግባኝ ለበላይ ፍርድ ቤት አቅርቦ የስር ፍርድ ቤት የነጻ መለቀቅ ብይን እንዲታገድለት ሲያመልክት ተቀባይነት የሚያገኝበትን የህግ አግባብ የሚመለከት ነው፡፡

 

ክርክሩ የጀመረው በፊዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁኑ አመልካች ከሌሎች ዘጠኝ ግልሰቦች ጋር የተከሰሱበት የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ከሽብር ቡድን ጋር የተለያዩ ግንኙነቶች በመፍጥር የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ሊያደርግ ያሰበውን የሽብር እንቅስቃሴ በመምራት በስሩም አባላትን በመመልመል፣ ከሽብር ድርጅቱ አባልና አመራሮች ጋር ግንኙነት በማድረግ፣ የሽብር ቡድኑን ዓላማ፣ ተግባር እና ተልእኮ ለመፈጸም በመንቀሳቀሳቸው በፈጸሙት የሽብርተኝነት ድርጊት ማቀድ፣ መዘጋጅት፣ ማሴር፣ ማነሳሳት እና ሙከራ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ነው፡፡ አመልካቹ የወንጀል ድርጊቱን ክደው በመከራከራቸው አቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸው ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቶአል፡፡ ከዚህም በኃላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ አቃቤ ሕግ አመልካቹ የተከሰሱበትን የወንጀል ድርጊት ስለመፈፀማቸው እንደ ክሱ አላስረዳም በማለት አመልካቹን ምንም መከላከል ሳያስፈልጋቸው ከክሱ በነፃ እንዲሰናበቱና ማረሚያ ቤቱም   ከእስር


ወዲያውኑ እንዲፈታቸው በማለት ትዕዛዝ ሰጥቶአል፡፡ በዚህ ብይን የአሁን ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበ ሲሆን ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳዩን መርምሮ የአሁኑን አመልካች እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሳይሰጥ አመልካቹ በነፃ እንዲሰናበቱ በተሰጠው ብይን መሰረት ከእስር እንዲለቀቁ የተሰጠው ትዕዛዝ እንዲታገድ የአሁኑ ተጠሪ አመልክቶ ፍርድ ቤቱም የተጠሪን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የአመልካችን የነፃ መለቀቅ ትዕዛዝ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 188(5) ድንጋጌ መሰረት ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቶአል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤተታ የቀረበውም ይህንኑ የእግድ ትዕዛዝ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም በስር ፍርድ ቤት አመልካች በነጻ እንዲሰናበቱ የተሰጠው ትዕዛዝ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የታገደው ለጉዳዩ አግባብነት የሌለው ድንጋጌ ተጠቅሶ መሆኑን የሚዘረዝር ሲሆን አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርቦም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓአል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ትዕዛዝ እና ከግራ ቀኙ ክርክር አንጻር እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም በዚህ ችሎት እንዲታይ በሰበር አጣሪ የተያዘው ጭብጥ አመልካች በነጻ እንዲሰናበቱ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይን በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 188(5) ተጠቅሶ መታገዱ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለው በመሆኑ ከዚሁ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለው ተመልክተናል፡፡

 

በመሰረቱ ፍርድ ቤት በአንድ ጉዳይ ላይ ዳኝነት መስጠት የሚገባው በሕጉ የተዘረጋውን ስርዓት መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በሕጉ የተዘረጋውን ስርዓት መሰረት አድርጎ ዳኝነት በመስጠት ሂደት ደግሞ ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን ድንጋጌ መለየትና ተፈጻሚ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ የፀረ ሽብር አዋጅ ተጠቅሶ ክስ የቀረበበት ሰው ክርክሩ የሚመራበት አግባብ በአዋጁ አንቀጽ 36 የተመለከተ ሲሆን በዚህ ድንጋጌ መሰረት የጸረ ሽብር አዋጁን መሰረት አድርገው የሚቀርቡ ክርክሮች በአዋጁ በራሱ በተጠቀሱት የስነ ስርዓት ደንቦች እንዲሁም ከአዋጁ ጋር ተቃርኖ ከሌለ ደግሞ በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግና በ1954ቱ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሰርዓት ሕግ የሚመሩ መሆኑን ተጠቃሹ የአዋጁ ድንጋጌ ያሳያል፡፡ ከዚህ አንፃር ስንመለከተው የጸረ ሽብር አዋጅ መሰረት ክስ ቀርቦበት የአቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ከተሰሙ በኋላ አንድ ሰው በነፃ ቢሰናበት አቃቤ ሕግ በጉዳዩ ላይ ይግባኝ ብሎ የስር ፍርድ ቤት የነፃ መለቀቅ ብይንን ማሳገድ የሚችልበት አግባብ መኖር ያለመኖሩን የአዋጅ ቁጥር 652/2001 ድንጋጌዎች አያሳዩም፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 36 መሰረት የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 188/5/ ድንጋጌ ተፈፃሚ ሊሆን ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ሲነሳም ይህ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ድንጋጌ አርዕስቱ ፍርድ እንዳይፈፀም ስለማገድ የሚል ያለው ሁኖ ዘርዝሮ ይዘቱ በተለይም የድንጋጌው ንዑስ ቁጥር አምስት ሲታይ ይግባኙ ከመሰማቱ በፊት


በማንኛውም ጊዜ ወይም ይግባኙ በሚሰማበት በማንኛውም ጊዜ ፍርዱ እንዲታገድ ለይግባኝ ፍርድ ቤት ማመልከት እንደሚቻል ይደነግጋል፡፡ የዚህ ንዑስ ድንጋጌ መሰረታዊ አላማ በአንቀፁ ንዑስ አንድ ድንጋጌ ስር ያለውን ድንጋጌ ዉጤታማ ለማድረግ ነው ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን የወንጀል ጉዳይ ከሰው ልጅ ነፃነት፣ ሕይወትና ክብር ጋር እጅጉን የተቆራኘ በመሆኑ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠው ፍርድ ቢፈፀም በእነዚህ መብቶች ላይ ሊመለስ የማይችል ጉዳት ሊደርስ ስለሚችል ከወዲሁ ለመከላከል ነው ተብሎ መሆኑ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ፍርዱ በተከሳሹ ከተሰጠ ተከሳሹ ለበላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ሲቀርብ የበታች ፍርድ ቤትን ውሳኔ የበላይ ፍርድ ቤቱ ማገድ የሚችልበትን አግባብ የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 188/5/ ድንጋጌ የሚያስገነዝብ ከመሆኑ ውጪ ከሳሽ ወገን በነፃ መለቀቅ ላይ ይግባኝ ብሎ ሲሄድ ፍርዱ እንዳይፈፀም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለመስጠት መነሻ የሚያደርገው ድንጋጌ ነው ለማለት የሚያስችል ሁኖ አልተገኘም፡፡ ሆኖም አንድ ተከሳሽ በነፃ ሲሰናበት አቃቤ ሕግ ይግባኝ ብሎ ፍርዱን ለማሳገድ የሚችልበት የሕግ መሰረት የለም ማለት ግን አይደለም፡፡ የፀረ ሙስና ጉዳዩች ላይ ተፈፃሚነት ያላቸው ሕጎችና በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 63 እና 67 ስር የተመለከቱትን ድንጋጌወችን መሰረት በማደረግ በነፃ የተለቀቀ ተከሳሽ በማረሚያ ቤት ሁኖ ጉዳዩን እንዲከታተል  ማድረግ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች መኖራቸው ግን ሊስተዋል የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አመልካች በነፃ እንዲሰናበቱ የተሰጠውን የስር ፍርድ ቤትን ብይን በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 188/5/ መሰረት ያገደው ድንጋጌው ለጉዳዩ አግባብነት ሳይኖረው ሁኖ አግኝተናል፡፡

 

በሌላ በኩል ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ጉዳዩን የተመለከተው የፍርድ ቤቶች መደበኛ የስራ ጊዜ በተዘጋበት ተረኛ ችሎት በተመደበበት አግባብ ሲሆን ዋናውን ጉዳይ ሳይመረምር የስር ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ እንደሚመጣ ብሎ ከአዘዘ በኃላ የስር ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ ከመቅረቡ በፊት ስለመሆኑ ከትዕዛዙ ግልባጭ ይዘት ተገንዘበናል፡፡ የስር ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ ቀርቦ መ/ሰጪን የሚያስቀርብ የህግና የፍሬ ነገር ነጥብ ስለመኖሩ የሚያሳይ ትዕዛዙ በተረኛው ችሎት አልተሰጠም፡፡ የስር ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ ከቀረበ በኋላ በዋናው ጉዳይ ላይ ግራ ቀኙን ለማከራከር የሚያስችል የህግና የፍሬ ነገር ነጥብ መኖሩ ላይ ተገቢውን ትዕዛዝ ሊሰጥ የሚችለው መደበናው ችሎት መሆኑን ተረኛው ችሎት በ15/12/2007 ዓ/ም ከሰጠው ትዕዛዝ በኃላ ያሉት ጊዚያትና የክርክር ሂደቶች የሚያስገነዝቡት ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ዋናውን ጉዳይ ማየት የቀጠለው መደበኛ ችሎት አመልካች ጉዳዩን በውጪ ሁነው የማይከታተሉበት  ህጋዊ አግባብ መኖር ያለመኖሩ ላይ አግባብነት ያለውን ህግና ድንጋጌ በመለየት ብይን ሊሰጥበት የሚገባ መሆኑን  ተገንዝበናል፡፡  ስለሆነም  የፌዴራሉ  ጠቅላይ  ፍርድ  ቤት  ይግባኝ  ሰሚው ችሎት


በ15/12/2007 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ አግባብነት የሌለውን ድንጋጌ መሰረት ያደረገ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 117340 በ15/12/2007 ዓ/መ የተሰጠው እግድ የህግ መሰረት የለውም በማለት በድምጽ ብልጫ ሽረናል፡፡ በሌላ በኩል መደበኛው ችሎት በዋናው ጉዳይ ክርክር ቀጥሎ ከሆነ አመልካች ከእስር ውጪ ሁነው ጉዳዩን መከታተል የማይችሉበት የህግ መሰረት መኖር ያለመኖሩን ተመልክቶ ተገቢውን ትዕዛዝ ሊሰጥበት ይገባል በማለት ጉዳዩን መልሰንለታል፡፡

2.  መዝገቡ ተዘግቶአል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

 

የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

ሃ/ወ

 

 የ ልዩነት ሐሳ ብ

 

ስሜ በተራ ቁጥር ሶስት የተመዘገብኩት ዳኛ የስራ ባልደረቦቼ በሰጡት ፍርድ ባለመስማማት የልዩነት ሐሳቤዩን እንደሚከተለው አስፍሬአሎሁ፡፡

 

ለዚህ ሰበር አቤቱታ ምክንያት የሆነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተረኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 117340 ነሀሴ 15 ቀን 2007 ዓ/ም ችሎቱ የሰጠው ትዕዛዝ ሲሆን በትዕዛዝ ክፍሉም የቀረበውን ይግባኝ ቅሬታ መርምሮ ተገቢ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 158194 በ14/12/2007 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ ከመፈጸም ታግዶ እንዲቆይ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 188(5) መሰረት ትዕዛዝ መስጠቱን ከስር ፍርድ ቤት መዝገብ የውሳኔ ግልባጭ መረዳት ይቻላል፡፡

 

የአሁኑ አመልካች አቶ ሀብታሙ አያሌው ከሌሎች ዘጠኝ ግለሰቦች ጋር ከተከሰሱበት የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብር ወንጀል በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ ማሴር እና መነሳሳት ወንጀል ዐቃቤ ህግ እንደክሱ አላስረዳም ተብሎ ከክሱ በነጻ እንዲሰናበቱና ማረሚያ ቤቱም ከእስር ወዲያውኑ እንዲፈታቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመወሰኑ ምክንያት የአሁኑ ተጠሪ በጉዳዩ ይግባኝ በመጠየቅ ፍርዱ እንዳይፈጸም ዕግድ አሰጥቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ መታየት ያለበት መሰረታዊ የክርክር ነጥብ የፌዴራል ጠቅላይ  ፍርድ ቤት ተረኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ትዕዛዝ የሰበር አቤቱታ ለማቅረብ የሚያስችል ህጋዊ መሰረት አለው ወይስ የለውም? የሚል ነው፡፡


በመሰረቱ አንድ ጉዳይ ለሰበር ሰሚ ችሎት ብቁ ሁኖ ሊታይ የሚችለው ጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ስለመሆኑ በቅድሚያ ሲረጋገጥ ነው፡፡ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 80(3) (ሀ) እና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10(2) በግልጽ እንደተመለከተው አንድ ጉዳይ ለሰበር ሰሚ ችሎት ብቁ የሚሆነው አቤቱታ የቀረበበት ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ (Final court decision) ያገኘ መሆን ያለመሆኑን በቅድሚያ መረጋገጥ ያለበት መሰረታዊ  ነጥብ ስለመሆኑ የድንጋጌዎቹ ይዘትና መንፈስ ያስገነዙቡናል፡፡ በመሆኑም ሰበር ሰሚ ችሎት የመጨረሻ ፍርድ ባለገኙ ጉዳዮች ውሳኔ የመስጠት ስልጣንና ኃላፊነት ያልተሰጠው መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ አገላለጽ ለሰበር ብቁ ያልሆኑ የመጨረሻ ፍርድ ያላገኙ ጉዳዮች በሰበር ሰሚ ችሎት ሊስተናገዱ የሚችሉበት ስርዓት አይኖርም፡፡

 

አንድ ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ መሆን ያለመሆኑን ለመለየት በመመዘኛነት መታየት ያለባቸው መሰረታዊ ነጥቦች ምን ምን ናቸው? የሚለው አንኳር ነጥብ አገርቷ ከምትከተለው የህግ ስርዓት ጋር ተገናዝቦ መታየት ይኖርበታል፡፡ አንድ ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠበት ነው ወይስ አይደለም? የሚለው አከራካሪ ጭብጥ ለመፍታት እንደመነሻ ከሚወሰዱ ነገሮች በፍርድ ቤቶቻችን የዳበረው አሰራር፤ የምንከተለው የህግ ስርዓት እና ሰበር ሰሚ ችሎቱ የራሱ የሆነ የስነ ስርዓት ህግ ያልተቀረጸለት በመሆኑ በህገ መንግስቱ የተጠቀሰው “የመጨረሻ ውሳኔ” የሚለው ቃል ይዘት ከህግ አወጭው ሐሳብ በተጣጣመ መልኩ በመተርጎም እና በመደበኛ እንደሁም ከስነ ስርዓት ህጎቻቸን መሰረታዊ ድንጋጌዎች አንጻር መመልከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተያያዘ በስነ ህግ (jurisprudence) የዳበረው የአተራጓጎም ስርዓት የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ሲባል መሰረታዊ ህጋዊ መስፈረቱ ምንድነው? የሚለው እንደአግባብነቱ ለተያዘው ጉዳይ ተፈጻሚ የሚሆንበት ስርዓት ይኖራል፡፡

 

ከላይ እንደተመለከትነው አንድ ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው መሰረታዊ ነጥብ ሊመዘን የሚችለው በተያዘው ጉዳይ ምንም የተንጠለጠለ ነገር የሌለው፤ የይግባኝ ሂደቱ አማጦ የጨረሸ፣ በጉዳዩ በተያዙ አከራካሪ ነጥቦች መልሶ ማየት በማያስችል መንገድ ዕልባት የተሰጠበት መሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡ በስነ ህግ በዳበረው የአተረጓጎም ስርዓትም አንድ ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘነው የሚለው ሲታይ፡- final decision generally is one which ends the litigation on the merit and leaves nothing for the court to do but execute the judgment በማለት ትርጉም የተሰጠው ሲሆን ይህ ትርጎም በግርድፍ ወደ አማርኛ ስንመለሰው አንድ ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ አገኝቷል ለማለት የሚቻለው በሚያከራክረው ጭብጥ ላይ የመጨረሻ መቋጫ ያገኘ ሲሆን እና ጉዳዩ እንደ ፍርዱ ከመፈጸም ወጭ ሌላ አማራጭ የሌለው የውሳኔ ዓይነት መሆኑን ሲርጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በተያየዘ በመጀመሪያ መቃወሚያ ወይም ጊዜያዊ   አገልግሎት ባለው ትዕዛዝ ላይ የሰበር አቤቱታ መቅረብ እንደማይችል    በዚህ


ረገድ የዳበረው የሰነ ህግ ትርጉም ያመልከታል፡፡ (preliminary ruling and temporary injunctions may not qualify a case to be reviewed by way of cassation) ከዚህ የምንገነዘበው ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው ትዕዛዝ ትዕዛዙን በሰጠው ችሎት በራሱ ጊዜ መልሶ ሊያስተካክለው፣ ሊያሻሽለው ወይም ሊሽረው የሚችል ነው፡፡ የመጀመሪያ መቃወሚያ ወይም ጊዜያዊ አገልግሎት ያላቸው ትዕዛዞች በተከራካሪ ወገን መብት እና ነፃነት ላይ ለጊዜው ገደብ አይጥሉም ባይባልም በዚህ አግባብ የሚሰጥ ትዕዛዝ ግን የመጨረሻ ውሳኔ ነው ለማለት የሚቻል አይደለም፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ አመልካች በስር ፍርድ ቤት ከእስር እንዲፈቱ የተሰጠው ትዕዛዝ ለጊዜው መታገዱን ያከራከረ ጉዳይ አይደለም፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተረኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዕግድ የሰጠበት የህግ ድንጋጌ ተገቢ ባይሆንም የትዕዛዙ ይዘት ሲታይ ግን አመልካች ከእስር እንዲፈቱ ገደብ የተደረገው ጉዳዩ በይግባኝ እስከሚታይ እንጂ ሊታረም የማይችል በፍሬ ጉዳዩ (merit of the case) የመጨረሻ ውሳኔ መስጠቱን አያሳይም፡፡ ከላይ እንደተመለከተው አንድ ጉዳይ ለሰበር ብቁ የሚሆነው የተሰጠው ትዕዛዝ (ውሳኔ) ፍርድ ይዘትና መንፈስ ሲታይ የመጨረሻ እና ጉዳዩ በያዘው ፍ/ቤት መልሶ የማይታርም ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በያዝነው ጉዳይ በአመልካች ላይ የቀረበው የዐቃቤ ህግ ይግባኘ ፍርድ ቤቱ ሊቀበለው ወይም ላይቀበለው ይችላል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ የአመልካች በእስር ይቆይ ጥያቄ የአሁኑ ተጠሪ ያቀረበው ይግባኝ አቤቱታ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ እና የዐቃቤ ህግ ክስና ማስረጃ እንዲከላከል የሚታዘዝ ከሆነ አመልካች የተጠረጠሩበት ወንጀል ዓይነትና ክብደት መሰረት ተደርጎ የዋስትና ጉዳይ የሚታይ ይሆናል፡፡ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔን የሚያጸና ከሆነም ስርዓቱን ጠብቆ ለሰበር የሚቀርብ አቤቱታ ቢኖርም ባይኖርም ጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ የሚገያገኝ በመሆኑ የአመልካች በእስር ይቆይ ትዕዛዝ ህጋዊ ውጤት በተሰጠው ውሳኔ ምክንያት የሚያበቃ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት አመልካች ከእስር እንዳይለቀቁ የሰጠው ትዕዛዝ ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው ትዕዛዝ እንጂ የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠበት ነው ለማለት የሚቻል አይደለም፡፡ ከላይ እንደተመለከተው በአመልካች ላይ የተሰጠው ትዕዛዝ ይዘት እና ባህሪ ችሎቱ በራሱ ጊዜ መልሶ የሚያርመው ነው፡፡ በመሆኑም የአመልካች የሰበር አቤቱታ የመጨረሻ ውሳኔ ባገኘ ጉዳይ ያልቀረበ ጊዜያዊ ዕገዳ (temporary injuction) መሆኑ እየታወቀ ለሰበር ብቁ ነው መባሉ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 80 ንኡስ አንቀጽ (3) (ሀ) እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እንደተሻሻለ አዋጅ ቁጥር 25/88  አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች መሰረታዊ ይዘትና መንፈስ የተከተለ ሆኖ አልተገኘም፡፡

 

የሰበር ስርዓት የተዘረጋበት አይነተኛ ዓላማ የመጨረሻ ውሳኔ ባገኙ ጉዳዮች ላይ የተፈጸመው መሰረታዊ የህግ ስህተት ካለ በማረም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ስለመሆኑ ከአጠቃላይ   የሰበር


ጽንስ ሐሳብና ዓላማ የምንረዳው ነው፡፡ የሰበር ስርዓት መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመባቸው ውሳኔዎች በማረም በአንድ አገር በተቻለ መጠን ወጥ የሆነ የህግ አተርጓጎም እና አፈጻጸም (in order to attain uniform application and interpretation of laws throughout the nation) እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ጉዳይ በሰበር እንዲታይ እንደመሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ የሚወሰድ አስገዳጅ ህጋዊ መስፈርት ጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ መሆን ያለመሆኑን ህገ መንግስቱና ተከታይ አዋጆች መሰረት በማድረግ መመዘን ነው፡፡ ህግ አወጪው የመጨረሻ ውሳኔ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ የሚፈጸም መስረታዊ የህግ ስህተት ካለ እና ይህ ስህተት ሳይታረም እንደረጋ ወይም እንደጸና የሚቆይ ከሆነ በአንድ አገር ህዝብ፤ መንግስት እና ዜጎች መብትና ጥቅም ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የህግ የበላይነትን (rule of law) ከማረጋገጥ አንጻር ያለው ዓይነተኛ ትርጉም እና ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ታሳቢ በማደረጉ ስለመሆኑ ከህገ መንግስቱ እና ተከታይ ድንጋጌዎች (አዋጆች) የምንገነዘበው ነው፡፡ በሌላ በኩል ሰበር ሰሚ ችሎቱ መሰረታዊ ያልሆኑ የህግ ስህተቶች የማረም ስልጣን ይሁን ኃላፊነት አልተሰጠውም፡፡ የፍሬ ነገር ክርክር እና የማስረጃ ምዘና ስርዓትም ከሰበር ስልጣን ውጭ መሆኖቸው ልብ ይሏል፡፡ ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ አከራካሪ ሁኖ የቀረበው የፍርዱ ለጊዜው እንዳይፈጸም የማገድ ጉዳይ በአመልካች ላይ ለጊዜው በእርስር መቆየትን ማስከተሉ ግልጽ ቢሆንም የተረኛ ችሎቱ ትዕዛዝ የማይታረም የመጨረሻ ውሳኔ (ትዕዛዝ) ነው ለማለት የሚያስችል አንዳችም የህግ መሰረት የለውም፡፡

 

አከራካሪው ትዕዛዝ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በክርክር ጊዜ ሊያረመው የሚችል ወይም የይግባኝ ሂደቱ ካበቃ በኃላ ህጋዊ ውጤቱ የሚያበቃ ትዕዛዝ መሆኑ እየታወቀ እንደ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ መወሰዱ ተገቢነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ በእነዚህ ሁሉም ምክንያቶች የስር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት የስር ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኙ እስከሚታይ (እስከሚሰማ) ማገዱ ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው ትዕዘዝ ሰጥቷል ከሚባል በስተቀር የመጨረሻ ውሳኔ እንደሰጠ መቆጠሩ በህጉ አግባብ አይደለም፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአመልካች የቀረበው የሰበር አቤቱታ በጊዜያዊ ዕግድ ላይ የተመሰረት እንጂ የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጠበት መሆኑን ግንዘቤ በመወሰድ ጉዳዩ ለሰበር ብቁ አይደለም በማለት መዝገቡ መዝጋት ሲገባው በፍሬ ጉዳዩ ውሳኔ እንደተሰጠ ግምት በመወሰድ ውሳኔ መስጠቱ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 80(3) (ሀ) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 የተመለከተው “የመጨረሻ ውሳኔ” (Final decision) መስፈርት የማያሟላ የህግ መሰረት የሌለው በመሆኑ ለሰበር ብቁ አይደለም በማለት በልዩነት ሐሳብ ተለይቻሎህ፡፡

 

 

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡