107805 jurisdiction/ government procurement

ከመንግስት ገዥና አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚነሳ ክርክር በመጀመሪያ ስልጣኑ የማየት መብት ያለው የመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ ቅሬታ ሰሚ ቦርድ እንጂ የመደበኛ ፍ/ቤት ስላለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀፅ 75(1) አዋጁን ለማስፈፀም የወጣው መመሪያ አንቀፅ 49(1)

 

የሰ/መ/ቁ. 107805

 

ጥቅምት 04 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ

 

ተሻገር ገ/ስላሴ ብርሃኑ አመነው ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

 

 

አመልካች፡-   ጄዳው አማካሪ አርክተክቶችና መሐንዲሶች ባለቤት አቶ ዳንኤል አሰፋ ጠበቃ አለሙ ገበየህ - ቀረቡ

ተጠሪ፡- 1ኛ. የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ነገረ ፈጅ አቶ ፋሲል ተሰማ - ቀረቡ 2ኛ. የኢፌዲሪ ፍትህ ሚኒስቴር - አልቀረቡም

መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን፤ መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ይህ የሰበር ጉዳይ በአስተዳደር አካል የተወሰነ ጉዳይ በመደበኛ ፍ/ቤት ቀርቦ ሊታይ የሚችልበትን የአቤቱታ አቀራረብ ሥርዓትና ቅሬታውን ተቀብሎ የማየትና የመወሰን ሥልጣን ያለው በየትኛው ደረጃ የተዋቀረው ፍ/ቤት ነው? የሚለውን አስመልክቶ ግራ ቀኙ ከተከራከሩበት ጉዳይና ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ህጎች ጋር በማገናዘብ ለይቶ ለመወሰን በሚል የቀረበ ነው፡፡

 

የጉዳዩም መነሻ የአሁን አመልካች በአሁን 1ኛ ተጠሪ ላይ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በቀጥታ ያቀረበው ክስ ሲሆን የክሱም ይዘት ተከሳሹ ለብሔራዊ ስታድየም ግንባታ የሚሆን የዲዛይን ሥራ ፈልጎ ባወጣው የጨረታ ውድድር መሠረት ተወዳዳሪ አሸናፊ ሆኛለሁ በጨረታ ሰነዱ (በዝክር ተግባሩ) መሠረት ሥራው ለ2ኛው ዕጩ ተወዳዳሪ ሊሰጥ የሚችለው አሸናፊው በእርሱ ምክንያት ሥራውን ለማከናወን አለመቻሉ የተረጋገጠ እንደሆነ ብቻ መሆኑ ተገልፆ እያለ ተከሳሹ በህገ-ወጥ መንገድ ጨረታ እንደገና እንዲደረግ የሚያስችል ተግባር በሚከናወን በሁለተኛ ደረጃ ለተሰየመው ተወዳዳሪ ሰጥቶ በዚሁ መሠረት እያከናወነ ስለሚገኝ ይህንኑ ተግባሩን አቁሞ በአሸናፊነቴ ቴክኒካል ፕሮፖዛል እንዲቀርብ እና የቴክኒካል ፕሮፖዛል ድርድር እንዲያደርግ ይወሰንልኝ የሚል ነው፡፡


ተከሳሽ የነበረውም የአሁን 1ኛ ተጠሪ ከሳሽ በጨረታው የአሸናፊነት ደረጃ አልደረሰም የሚልበትን ዝርዝር የክርክር ነጥብ በመጥቀስ በውድድሩ ሂደት ከሳሽ ለዲዛይን ሥራው ብቁ የሚያደርገውን መስፈርት አላሟላም፤

 

እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 75(1) መሠረት የመንግሥት ግዥን በሚመለከት የሚቀርቡ ቅሬታዎች ሥልጣን ባለው የመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ ቅሬታ ሰሚ ቦርድ ቀርበው እንዲታዩ በማድረግ ሥልጣኑን የቦርዱ እንጂ የፍ/ቤቱ አይደለም ስለሆነም ክሱ ሊዘጋ ይገባል የሚለውንም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ክርክር አቅርቧል፡፡

 

ከሳሽም ጉዳዩን ለዚሁ ቦርድ አቅርቦ ማስወሰኑን ይህ ቦርድ የሚሰጠውም ውሳኔ የመጨረሻና አስገዳጅ ነው ተብሎ በአዋጅ አልተደነገገም ይልቁንም አዋጁን ተከትሎ በወጣው መመሪያ አንቀደጽ 49 (1) መሠረት በቦርዱ ውሳኔ ቅሬታ ያለው ሰው አቤቱታውን አግባብ ባለው ፍ/ቤት ማቅረብ እንደሚቻል ስለተደነገገ ፍ/ቤቱ የቀረበለት ክስ ተቀብሎ ለማየት ሥልጣን አለው በማለት ተከራክሯል፡፡

 

ክሱ የቀረበለት ፍ/ቤትም ለክርክሩ መነሻ የሆነው ጉዳይ በቀጥታ ተቀብሎ በማስተናገድ ሥልጣን አለው ወይስ የለውም? የሚለውን አከራካሪ ነጥብ በሚመለከት አግባብነት ያለወን የአዋጁንና የመመሪያውን ድንጋጌዎች በመጥቀስ የጉዳዩ አቀራረብ ሥርዓቱን ጠብቆ ሥልጣን ባለው ፍ/ቤት የቀረበ ነው የሚል ዳኝነት የሰጠበት ሲሆን፤

 

ይግባኝ ሰሚው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በበኩሉ ጉዳዩ በይግባኝ ደረጃ የይግባኙን ጉዳዩ ለማየት ሥልጣን ላለው ፍ/ቤት ከማቅረብ በቀር የሥር ፍ/ቤት ጉዳዩን በቀጥታ ተቀብሎ ለማየትና ለመወሰን የሚያስችል የህግ የመነጨ ሥልጣን የለውም ሲል ሽሮ ወስኗል፡፡

 

በሁለተኛ ደረጃ ይግባኝ ጉዳዩ የቀረበለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በየደረጃው የተሰጡትን ውሳኔዎች ተመልክቶ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በይግባኝ ተመልክቶ የሰጠው ውሳኔ በአግባቡ መሆኑን አትቶ በመወሰን የአሁን አመልካችን አሰናብቷል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ታይቶ ትርጉም የሚያስፈልገው ሆኖ ከተያዘው አከራካሪ ነጥብ አንፃር ባጭሩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም ጉዳዩን እንደሚከተለው ተመልክተናል፡፡

 

የአሁን 1ኛ ተጠሪ ግራ ቀኙ የተከራከሩበትን ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 649 /2001 አንቀጽ 75 (1) መሠረት አይቶ ለመወሰን ሥልጣን የተሰጠው ለመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ ቅሬታ ሰሚ ቦርድ እንጂ በመደበኛ ፍ/ቤት ቀርቦ ሊታይ የሚችል አይደለም በሚል ያቀረበው ክርክር


ይህንኑ አዋጅ ለማስፈፀም በሠጠው መመሪያ አንቀጽ 49 (1) ድንጋጌ ሥር በግልፅ እንደተመለከተው ይኸው ቅሬታ ሰሚ ቦርድ በሰጠው ውሳኔ ያለው ወገን አግባብ ላለው ፍ/ቤት አቤቱታ ማቅረብ የሚቻል በመሆኑ ጉዳዩ በማናቸውም ምክንያት ለመደበኛ ፍ/ቤት ቀርቦ ሊታይ የሚችል አይደለም የሚለው ክርክሩ ህጋዊ መሠረት ያለው አይደለም፡፡

 

አከራካሪ ሆኖ የተገኘው በዚሁ ቅሬታ ሰሚ ቦርድ በሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው ወገን አቤቱታውን “አግባብ ባለው ፍ/ቤት ማቅረብ ይችላሉ ተብሎ ከተደነገገው ይህ አግባብ ያለው ፍ/ቤት የትኛው ነው? የመጀመሪያ ደረጃ ክስን በጉዳዩ ዓይነት ወይም በገንዘቡ መጠን መሠረት ተቀብሎ ጉዳዩን በቀጥታ የክስ ደረጃ የሚያየው ፍ/ቤት ወይስ የቦርዱን ውሳኔ አግባብነት እንደገና ተመልክቶና ክስ በይግባኝ ዳኝነት ለመስጠት ሥልጣን ላለው ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት? የሚለው ነው፡፡

 

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 79 የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው በሚል የተደነገገውን በዚሁ ህገ-መንግስት የፍ/ቤቶችን የሥልጣን ወሰን ለሚያመለክተው ከአንቀጽ 37 ጋር አጣቅሶ ማየት እንደሚቻለው ማንኛውም ጉዳይ ያለገደብ በመደበኛ ፍ/ቤት ቀርቦ ሊታይ የማይችል መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይልቁንም በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 37 የተቀመጠው የሥልጣን ክፍፍል ወሰን እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል እና ጉዳዩንም አይቶ ለመወሰን ከመደበኛ ፍ/ቤት ውጭ በሌላ የዳኝነት ሰጭ አካል ያልተሰጠ መሆኑ ከተረጋገጠ ይህንኑ በፍርድ ሊያልቅ የሚችለውን ጉዳይ ለማየትና ለመወሰን ብቸኛ ሥልጣን ያላቸው (exclusive Jurisdiction jurisdiction ) ያላቸው ፍ/ቤቶች መሆናቸውን ለማስገንዘብ ሲባል በአንቀጽ 79 መደንገጉን መረዳት ይቻላል፡፡

 

ስለሆነም መደበኛ ፍ/ቤቶች የቀረበላቸው ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል መሆኑን  በማረጋገጥ ላይ ብቻ ላይወሰኑ በህገ- መንግስቱ አንቀጽ 37 መሠረት ይኸው ጉዳይ ከመደበኛ ፍ/ቤት ውጭ ለሌላ በህግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል ቀርቦ የሚታይ መሆኑንና አለመሆኑን በቀጥታ የመመርመር ግዴታ አለባቸው፡፡

 

ከዚህ አንፃር አሁን የተያዘውን ጉዳይ ስንመለከት በፍሬ ነገር ደረጃ እንደተረጋገጠውና   ግራ ቀኙም እንደተማመነበት ሁለቱም ወገኖች ያለያያቸው ጉዳይ በአዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 75(1) መሠረት ጉዳዩ ለመደበኛ ፍ/ቤት ቀርቦ ከመታየቱ በፊት በመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ ቅሬታ ሰሚ ቦርድ መቅረብ እንዳለበትና በዚሁ የቅሬታ ሰሚ ቦርድ ውሳኔ ማግኘት አለበት በዚህም መሠረት ጉዳዩ በዚሁ አካል ቀርቦ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ ነው በዚህም አኳኃን በዚሁ የአስተዳደር አካልም (ከፊል የዳኝነት ሰጭ አካል) ታይቶ የተሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ሆኖ የሚቀር ሳይሆን በውሳኔው ላይ ቅር የተሰኘ ወገን ቅሬታውን አግባብ ላለው ፍ/ቤት አቅርቦ


አቤቱታውን ማቅረብ እንደሚችል አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ አንቀጽ 49(1) ተደንግጓል፡፡ ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው በአዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 75(1) በህገ- መንግስት አንቀጽ 37 እንደተደነገገው ይህንኑ ጉዳይ በቀዳሚ ተቀብሎ ለማስተናገድ ሥልጣን ያለውን የዳኝነት አካል (ከፊል የዳኝነት አካል) ለይቶ ካስቀመጠ በኃላ እንደገና ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍ/ቤት ለማቅረብ የጉዳዩን አሰማምሮ አወሳሰን በሚመለከት በአስተዳደራዊ ክፍል የዳኝነት ሰጭ አካል እና በመደበኛ ፍ/ቤት መካከል ያለውን ቁርኝት በሚመለከት ይህንኑ በአዋጅ አንቀጽ 75(1) የተቀመጠውን ድንጋጌ ለማስፈፀም በሠጠው መሠረት አንቀጽ 49(1) በግልፅ ተመልክቷል፡፡ እንግዲህ በከፊል የዳኝነት ሰጭው አካልና በመደበኛው ፍ/ቤት መካከል ያለውን ቁርኝነት በተገለፀበት መመሪያ አንቀጽ 49(1) “በቦርዱ ውሳኔ ቅሬታ ያለው ሰው አግባብ ላለው ፍ/ቤት አቤቱታውን ማቅረብ ይችላል፡፡” በሚል ከተገለፀው ቅሬታው አስቀድሞ በተሰጡ የቦርድ ውሳኔ ላይ የተመሠረተ ከመሆኑ፤ ቅሬታ የሚለውም ቀጥተኛ ትርጉም በአንድ አካል በተሰጠ ውሳኔ ላይ ያልተስማማ ወገን አለመስማማቱን የሚገልፁበት ቃል መሆኑን በዚህም ድንጋጌ የእግሊዘኛ ቅጂ “Review of complaint by the coyrt” በሚል ከተገለጸው “Review” የሚለው አስቀድሞ በተወሰነ ውሳኔ ላይ ተመርኩዞ በዚሁ ውሳኔ ላይ ቅር ተሰኝቶ ከቀረበው ቅሬታ ጋር በማዛመድ ጉዳዩን እንደገና በዳኝነት ሰጭ አካል የሚታይ መሆኑን የሚያመለክት በመሆኑ በህገ - መንግስቱ አንቀጽ 37 ሆነ በአዋጅ አንቀጽ 75(1) የመደበኛ ፍ/ቤቶችን የዳኝነት ሥልጣን ወሰን ካስቀመጠ በኃላ በማስፈፀሚያው መመሪያ አንቀጽ 49(1) የተቀመጠው ከመደበኛ ፍ/ቤቶች ጋር ያለው ቁርኝት መገለጫው በይግባኝ ሥርዓቱ አማካኝነት ውሳኔውን በይግባኝ ሰሚነቱ ሥልጣን መሠረት በቦርዱ የተሰጠውን ውሳኔ አግባብነት ካለው ህግና መመሪያ አንፃር በማየት መመርመር እንዲቻል እንጂ ጉዳዩን እንደ አዲስ በመቀጠር ተከራካሪ ወገኖች በጉዳዩ ላይ ክርክር በአዲስ መልክ የሚያከናውኑበትን ሥርዓት የሚመለክት አይደለም፡፡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አግባብ ያለው ፍ/ቤት ጉዳዩን ከህግ አንፃር ብቻ መመልከት እንዲቻል ሆኖ አልተቀረፀም ይባል እንጂ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የተሰጠበትና በዚህም ውሳኔ ላይ ቅሬታ ማቅረብ እንደሚቻል በመመሪያ የተፈቀደ በመሆኑ ጉዳዩን በክለሳ “Review” መልክ የሚያየው ፍ/ቤት የህግም ጥያቄ ሁሉ መመልከት የሚችል መሆኑ በውስጠ ታዋቂነት ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባ ነበር እንጂ ጉዳዩ በቀጥታ ክስ አማካኝነት ሊቀርብ ይገባል የሚለው ወደሚለው በቂ የውሳኔ መነሻ ትችትና ሊያደገውም አይገባም ነበር፡፡

 

በሀገራችን የህግ ሥርዓቱ በልዩ ልዩ ህጎች እንደተመለከተው በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 37 በአስተዳደርና፣ በከፊል የዳኝነት ሰጭ አካል እንጂ በመደበኛ ፍ/ቤቱ አስቀድመው ሊታዩ የማይችሉን ጉዳዮች ከተመለከቱ በኃላ ፍትህ የማግኘት መብትን ይበልጥ ለማረጋገጥ ሲባል ከፍ/ቤቱ ጋር ቁርኝት ሊኖራቸው እንደሚገባና ቁርኝቱም ለይግባኝ ሥርዓቱ  አማካኝነት    ጉዳዩ


በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት አማካኝነት እንዲታዩ በማድረግ የተደነገጉ እንጂ እንደገና እንደ አዲስ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ (of first instance ) አቅርቦ አዲስ ክርክርን በሚጋብዝ ደረጃ የተቀረፀ አይደለም፡፡

 

በዚሁ ሁሉ ምክንያት በይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍ/ቤት የተሰጠው የመጨረሻ ዳኝነት መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አላገኘነውም፡፡

 

 

 ው ሳ ኔ

1. የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በይግባኝ ሰሚነቱ ሥልጣን ላይ መ/ቁ 103961 ህዳር

17/2007 ዓ.ም በአብላጫ ድምፅ በትዕዛዝ የሰጠው የመጨረሻ ዳኝነት ፀንቷል፡፡

2. አመልካች በመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ ቅሬታ ሰሚ ቦርድ ውሳኔ  ቅሬታ ካለው ቅሬታውን በይግባኝ አቤቱታ አቀራረብ ደንብን ሥርዓት መሠረት ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ላለው አግባብ ላለው ፍ/ቤት ከሚያቀርብ በቀር በቀጥታ ክስ አቀራረብ ሥርዓት የጉዳዩን ዓይነትም ሆነ የገንዘብ መጠኑን መሠረት በማድረግ ጉዳዮች በቀጥታ ደረጃ በሚታዩበት ሥርዓተ መሠረት ማቅረቡ ሥነ-ሥርዓታዊ አይደለም ብለናል፡፡

3. በዚህ ሰበር ደረጃ ግራቀኙ ባደረጉት ክርክር ሳቢያ ለወጣው ወጭና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

የ/ማ

 
 
 

Google Adsense