99900 commercial law/ partnership

በውል መሰረት ከተቋቋመ የሽርክና ማህበር ውስጥ አንድ የማህበር አባል ከማህበሩ ሊወጣበት ስለሚችልበት አግባብ

 

የሰ/መ/ቁ. 99900

 

መስከረም 25 ቀን 2008 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ረታ ቶሎሣ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ

ሌሊሴ ደሣለኝ

 

አመልካች፡- አቶ ኃይሉ መንግስቱ - ቀረቡ ተጠሪዎች፡-      1. አቶ ሬገን መሐመድ - አልቀረቡም

2. አቶ ጌታሁን ገሰሰ አልቀረቡም፡፡

 

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ  ር ድ

 

ጉዳዩ የሽርክና ማህበር በማቋቋም የተዋጣው ገንዘብ ይመለስልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሆኖ ክርክሩም የጀመረው የአሁኑ አመልካች በአፋር ክልል ገቢረሱ ከፍተኛ ፍ/ቤት በተጠሪዎች ላይ በመሰረተው ክስ መነሻነት ነው፡፡ የክሱ ፍሬ ነገርም በአጭሩ ከተጠሪዎች ጋር በነበራቸው የሽርክና ውል መሰረት የእርሻ ስራ መጀመራቸውን ገልፆ በመካከሉ ግን አመልካች ከማህበሩ መውጣት መፈለጉን ተከትሎ ያዋጣው ገንዘብ ብር 38,900 አመልካች እንዲመለስለት በጠየቀው መሰረት ተጠሪዎች ገንዘቡን በሁለት ዙር ክፍያ ሊከፍሉ ከተስማሙ በኃላ ያለመከፈላቸውን ጠቅሶ በውሉ መሰረት ሊከፍሉ የተስማሙበትን ብር 38,900ና ብሩ ተከፍሎ እስኪያልቅ ድረስ  ከሚታሰብ ህጋዊ ወለድ ጋር እንዲሁም በውሉ መሰረት ባለመፈፀማቸው ቅጣት/ ገደብ ብር 5000 እና ወጪና ኪሳራን ጨምሮ እንዲከፈልኝ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ሲሆን የስር 1ኛ ተከሳሽ የሆነው የአሁኑ 1ኛ ተጠሪም በበኩሉ ቀርቦ ለክሱ በሰጠው መከላከያ መልስ ፡- ከአመልካች ጋር በሽርክና በጋራ ስራ ለመስራት ገንዘብ ማዋጣቸውን አምኖ ሆኖም ግን አመልካች የዋጣውን ገንዘብ ለመመለስ አለመስማማቱን ወይም ውል አለመፈረሙንና አመልካች የውል ስምምነት ነው ብሎ ያቀረበው ሰነድም 2ኛ ተጠሪን ብቻ በሽማግሌዎች አማካኝነት    በመደለልና


አታሎ ያስፈረመው ውል እንጂ እኔን ጭምር ያካተተ ባለመሆኑ ውሉ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጾ ይልቁንም በሽርክና ውላችን መሰረት የከዚህ ቀደሙን ኪሳራ አመልካች ከእኛ ጋር ከተጋራ በኃላ በቀጣዩም አብረን እንድንሰራ ተብሎ ይወሰንልን በማለት ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት ፍ/ቤትም በበኩሉ የግራ ቀኙን ቃል ክርክር ካአዳመጠ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች አስቀድሞ ያዋጣው የገንዘብ ይመለስለት በሚለው ሰነድ ላይ 1ኛ ተከሳሽ (የስር 1ኛ ተጠሪ ) ባይፈርምም በሁለቱ ተከሳሾች መካከል የወካይና ተወካይ ግንኙነት መኖሩንና እንዲሁም የስር 1ኛ ተከሳሽም በራሱ በውሉ ላይ ባይፈርምም በውሉ መስማማቱን ግን ከቀረበው ክርክር ለመረዳት መቻሉን ካሰፈረ በኃላ ተከሳሾች በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1675 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሰረት በገቡት ውል መሰረት ዋናውን ገንዘብ ብር 38,900 ክስ ከተመሰረተበት ቀን አንስቶ ከሚታሰብ 9%ወለድ ጋርና እንዲሁም ብር 5000 ገደብ ጭምር በአንድነትና በነጠላ ለስር ከሳሽ ይከፈሉ ሲል  ወስኗል

፡፡ በአሁኑ ተጠሪዎች የይግባኝ ቅሬታ መነሻነት ጉዳዩን በይግባኝ በተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በበኩሉ ግራ ቀኙን ተከራከሪ ወገኖች አስቀርቦ እንዲከራከሩ ካደረገ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ በግራ ቀኙ ተከራካሪ ወገኖች መካከል የሽርክና ውል መኖሩን መረጋገጡን ከገለፀ በኃላ ከዚኅ ውል ለመውጣትም ሆነ የሽርክና ውሉን ለማፍረስ የፈለገ አባል ካለ ጥያቄውን ማቅረብ ያለበትም ሆነ ጉዳዩ ታይቶ ተገቢው ውሳኔ ሊሰጥበት የሚገባው ጉዳዩን በተለይ በሚገዛው ንግድ ህጉ መሰረት መሆን አለበት እንጂ ስለ ውሎች በጠቅላላው የሚመለከተው የፍ/ብ/ህጉ ድንጋጌዎች መሠረት ባለመሆኑ የህንኑን ተከትሎ ተፈጸሟል የተባለው የውል ሰነድም በዚሁ ምክንያት ተፈፃሚነት የለውም በማለት የስር ፍ/ቤቱን ውሳኔ ከተቸ በኃላ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348(1) መሰረት ሽሮታል ፡፡አሁን የቀረበው በሰበር አቤቱታም ይህንኑ በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ሲሆን አቤቱታውም ተመርምሮ ለሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ ሊታይ ይገባል በመባሉ ተጠሪዎች ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተጠቀሰውን የሚመስል ሲሆን እኛም በበኩላችን ይህ ሰበር አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን በጭብጥነት ይዘን ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል መዝገቡን እንደተመለከትነውም በአመልካችና ተጠሪዎች መካከል አስቀድሞ የተቋቋመ የሽርክና ማህበር ውል መኖሩን ፣በዚህ ውል መነሻነትም አመልካች የበኩላቸውን ድርሻ ብር 38,900 ገንዘብ ማዋጣቱን በሽርክና ውሉ መሠረትም የእርሻ ስራ በጋራ መስራት መጀመራቸውም ፣ይህ በእንዲህ እንዳለ 2ኛ ተጠሪ በ23/11/2004 ዓ.ም በተደረገ ስምምነት መሰረት አመልካች በማህበር አባልነቱ አስቀድሞ ያዋጣውን ገንዘብ በሁለት ዙር የክፍያ አፈጻጸም ጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለመክፈል በራሱና 1ኛ ተጠሪን በመወከል ውል መፈረሙን አመልካችም ይሄው ገንዘብ በአንድነትና በነጠላ በተጠሪዎች እንዲከፈለው የጠየቀው ይህንኑን


ውል መሰረት በማድረግ መሆኑን ፣ነገር ግን 1ኛ ተጠሪ ለ2ኛ ተጠሪ የሰጠው ውክልና ስልጣን አለመኖሩን ፣1ኛ ተጠሪም በዚሁ መሰረት በአመልካች ጥያቄ አለመስማማቱንና እንዲሁም  ካለ 1ኛ ተጠሪ ፈቃድ ውጭ ሁለቱ አባላት ብቻቸውን ይህንኑ አመልካች አስቀድሞ ያዋጣውን መዋጮ ይዞ ከማህበሩ ይውጣ በማለት መወሰንም የማይችሉ መሆኑን ገልፆ የሚከራከሩ መሆኑን ከክርክሩ ሂደት ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

 

እንግዲህ በግራ ቀኙ ተከራካሪ ወገኖች መካከል በውል መሰረት የተቋቋመ የሽርክና ማህበር አለ ከተባለ ከዚህ ማህበር ለመውጣት የፈለገ አባል እንዴት እና በምን አግባብ መውጣት እንደሚችል በንግድ ህጉ አንቀጽ 227 እና ተከታዮቹ ጠቅላላ ድንግጌዎች በሚመለከተው መሰረት ስለመሆኑ መገንዘብ ይቻላል ፡፡ በእርግጥ አመልካች የራሱን መዋጮ ይዞ ከማህበሩ ይውጣ በሚለው ሀሳብ ላይ ሁሉም የማህበሩ አባላት ቢስማሙበት ኖሮ አመልካች ይህንኑ በውሉ መሰረት እንዲሰጠው መጠየቅ እንደሚችል ከንግድ ህጉ አንቀጽ 233(1) ድንጋጌ ይዘትና ሌሎችም ተከታይ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል ፡፡ይሁንና ከማህበሩ አባላት አንዱ የሆነው 1ኛ ተጠሪ በዚህ ነጥብ ላይ መስማማቱን አመልካች አላስረዳም ፡፡ እንዲሁም 2ኛ ተጠሪም ቢሆን ከ1ኛ ተጠሪ የተሰጠውን ውክልና ስልጣን መሠረት በማድረግ ለአመልካች መዋጮው እንዲመለስለት የሚለውንና በ 23/11/2004 ዓ.ም ተደርጓል የተባለውን የውል ስምምነቱ ስለመፈረሙም በፍሬ ነገር ደረጃ በማስረጃ አልተረጋገጠም እንዲህ ከሆነ ደግሞ 1ኛ ተጠሪ በዚህ ረገድ ለ2ኛ ተጠሪ የሰጠው የውክልና ስልጣን ከሌለና 1ኛ ተጠሪም በራሱ በ 23/11/2004 ዓ.ም ተደርጓል በተባለው ስምምነት ሰነድ ላይ አለመፈረሙ ከተረጋገጠ አመልካች ይህንን ውል በሰነድ መሠረት በማድረግ አስቀድሞ የዋጣው መዋጮ እንዲከፈለው /እንዲመለስለት /መጠየቅ የሚችልበት የህግ አግባብ አይኖርም ፡፡ ስለሆነም አመልካች ሁሉም የማህበሩ አባላት ያልተስማሙበትን የውል ስምምነት ሰነድ( በ23/11/2004 ዓ.ም ተደርጓል የተባለውን) መሠረት  በማድረግ  አስቀድሞ ለማህበሩ አዋጥቶ የነበረውን መዋጮ ብር 38,900 እንዲመለስለት መጠየቁ ለጉዳዩ በተለይ አግባብነት ያለው የንግድ ህጉን ድንጋጌዎች መሠረት ያላደረገ በመሆኑ የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የዞኑን ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔን መሻሩ በውጤት ደረጃ በአግባቡ ነው ከሚባል በስተቀር መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ ስላላገኘነው ተከታዩን ውሳኔ ሰጥቷል፡፡


 

 

 ው ሳ ኔ

 

1.  የአፋር  ብ/ክ/መንግስት  ጠ/ፍ/ቤት  ይግባኝ  ሰሚ  ችሎት  በፍ/ይ/መ/ቁጥር  2752 በ

14/5/2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348(1) መሠረት በውጤት ደረጃ ፀንቷል፡፡

2.  የአመልካች ሰበር አቤቱታ ተቀባይነት አላገኘም

3.  አመልካች በንግድ ህጉ መሰረት መብቱን ከማስከበር ይህ ውሳኔ አይከለከለውም ፡፡

4. ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡