97760 contract/ commercial law/ contract of carriage

በአጓዥ ጥፋት በደረሰ አደጋ ምክንያት በተጓዡ(መንገደኛው) ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሳ ለመወሰን ልንከተላቸው ስለሚገቡ የካሳ አከፋፈል መርሆች የን/ሕ/ቁ. 599፣ የፍ/ሕ/ቁ. 2091 እና 2092

 

 

የሰ//.97760 ታህሳስ 19 ቀን 2008 ዓ/ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- ወ/ሮ ንግስቲ አትክልቲ  -ጠበቃ ሙሉዓለም ፈጠነ ቀረቡ፡፡ ተጠሪ፡- አቶ አበባው ሽፈራው                    -የቀረበ የለም፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ  ር ድ

 

ጉዳዩ የአካል ጉዳት ካሳ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኗ አመልካች እና አቶ በረከት ተስፋዬ ላይ በመሰረቱት ክስ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡ ንብረትነቱ የአመልካች በሆነውና በስር 2ኛ ተከሳሽ በነበሩት በአቶ በረከት ተስፋዬ ይሽከረከር በነበረው ኮድ 3- 58098 አ.አ ተሸከርካሪ ከአለታ ወንዶ ከተማ ወደ ሐዋሳ ከተማ ብር 22.00 ከፍለው በመጓጓዝ ላይ እንዳሉ መኪናው በከፍተኛ ፍጥነት ይሸከረከርና ሹፌሩም ሞይባል ያናገር ስለነበር ከተራራው ጋር ተጋጭተው በአካላቸው ላይ  50% የአካል ጉዳት  የደረሰባቸው መሆኑን፣በዚህም ምክንያት  ገቢ ያጡና ለሕክምና ወጪ ያወጡ መሆኑንና ሹፌሩም በወንጀል የተቀጡ መሆኑን ዘርዝረው  በድምሩ ብር 497,105.97(አራት መቶ ዘጠና ሰባት ሺህ አንድ መቶ አምስት ብር  ከዘጠና ሳንቲም) ባልተነጣጠለ ኃላፊነት የመኪናው ባለቤትና ሹፌሩ እንዲከፍሉ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጡት መከላከያ መልስም ጉዳቱ የጥቅም ግንኙነት በሌለው ሁኔታ ስለመሆኑ፣ ተጠሪ በጉዳቱ ምክንያት የተቋረጠባቸው ገቢ ወይም ጥቅም የሌለ መሆኑንና የጉዳት ካሳ መጠኑም የተጋነነ መሆኑን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡ የሥር 2ኛ ተከሳሽ የነበሩት ግለሰብ ባለመቅረባቸው ጉዳዩ በሌሉበት እንዲታይ ተደርጎአል፡፡


ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶ አመልካችን ኃላፊ በማድረግ ብር 376,226.00 (ሶስት መቶ ሰባ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ስድስት ብር) በአንድነትና በነጣላ እንዲከፈላቸው ወስኖአል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለደቡብ ብ/ብ/ሕ/ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን እንዲከራከሩ እና አማካይ እድሜን በተመለከተ ከሚመለከተው አካል ማስረጃ እንዲቀርብ ከአደረገ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ላይ የተሰጠውን የኃላፊነት ውሳኔ ተቀብሎ የጉዳት ከሳ መጠኑን ግን ከአማካይ እድሜ ጋር በማመጣጣን አስልቶ በድምሩ ብር 284,280.00( ሁለት መቶ ሰማንያ አራት ሺህ ሁለት መቶ ሰማንያ ብር) አመልካችና የስር 2ኛ ተከሳሽ በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ሲል ወስኗል፡፡ ከዚኅም በኋላ አመልካች የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

 

የአመልካች ጠበቃ የካቲት 04 ቀን 2006 ዓ/ም ጽፈው ባቀረቡት አራት ገፅ የሰበር አቤቱታ በታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ፡-አመልካች ለጉዳቱ ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ መወሰኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2081፣2086(2) እና 2089 ድንጋጌዎች ጋር እና የጥቅም ግንኙነት በሌለበት ሁኔታ የተሸከርካሪው ባለቤት ተጠያቂነት የለበትም ተብሎ ከተወሰነው የዚህ ሰበር ችሎት አስገዳጅ ውሳኔ ጋር ያልተጣጣመ መሆኑን፣ ተጠሪ ክሱን ከውል ውጪ ሃላፊነትን በሚገዙ ድንጋጌዎች መሰረት ማቅረባቸው ተገቢነት የሌለው መሆኑንና የካሳ መጠኑንም በጉዳቱ ምክንያት የተቋረጠ የተጠሪ ጥቅም በሌለበትና የተጠሪ ገቢ በአግባቡ ባልተጣራበት ሁኔታ በተጋነነና ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2090 ይዘትና መንፈስ ውጪ የተወሰኑ መሆኑን ዘርዝረው ውሳኔው ሊታረም የሚገባው ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ የፁሑፍ ክርክር አድርገዋል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድነጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዙት ጭብጦች አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ የተያዙት ጭብጦች፡-

1. በተጠሪ ላይ ለደረሰው ጉዳት አመልካች ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ በበታች ፍርድ ቤቶች መወሰኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2089 ድንጋጌ እና ከሰ/መ/ቁጥር 38457 አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አንጻር ተገቢ መሆን ያለመሆኑን፣

2. የአጓዥ ተጓዥ ውል መኖሩ ሳይካድ ከውል ውጪ ሃላፊነት ተብሎ የቀረበው ክስ ተገቢ  መሆን ያለመሆኑን እና


3. ተጠሪ በጉዳቱ ምክንያት ያጡት ጥቅም እንደተቋረጠባቸው ባላስረዱበት ለተጠሪ ካሳ እንዲከፈላቸው የተወሰነው የካሳ መጠን ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ነው፡፡

የመጀመሪያውን ጭብጥ በተመለከተ፡- አመልካች ከተጠሪ ጋር የጥቅም ግንኙነት የለኝም በማለት የሚከራከሩት ጉዳት አደረሰ የተባለውን ተሸከርካሪ በወቅቱ Populationa Service International(PSI) ለተባለ ድርጅት አከራይቼ ከመኪናው ጥቅም ሲያገኝ የነበረው ይኼው ድርጅት ነው በሚል አቢይ ምክንያት መሆኑን ተገንዝናል፡፡ የስር ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ ማስረጃ እንዲቀርብ አድርጎ የኪራይ ውል ሊቀርብ ባለመቻሉ መኪናው ተከራይቶ የነበረ ነው ለማለት እንዳልቻለ ግልጾ ያለፈው ስለመሆኑ ከውሳኔው ግልባጭ ተገንዘብናል፡፡ በመሆኑም አመልካች መኪናውን አከራይተው ያልነበሩ መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ በስር ፍርድ ቤት የተረጋገጠ  ሲሆን ፍሬ ነገሩን ለማጣራትና ማስረጃን በመመዘን ረገድ ተመሳሳይ የሆነ ስልጣን ያለው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ይህንኑ ፍሬ ነገር የተቀበለው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ስናው ይህ ችሎት አመልካች መኪናውን አከራይተው ነበር ወይስ አልነበረም? የሚለውን የፍሬ ነገርና የማስረጃ ምዘና ነጥብ የሚመረምርበት አግባብ የለም፡፡ ምክንቱም ለዚህ ችሎት በአ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 80(3(ሀ) እና በአዋጅ ቁጥር 25/88  አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ተለይቶ የተሰጠው ስልጣን ፍሬ ነገርን ለማጣራት ወይም ማስረጃን ለመመዘን ሳይሆን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ማረም ብቻ ነውና፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ በአመልካች በኩል የቀረበው ቅሬታም ሆነ በሰበር አጣሪ ችሎቱ በጭብጥነት የተያዘው ነጥብ ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠውን ፍሬ ነገርና የዚህን ችሎት ስልጣን ያላገናዘበ በመሆኑ የምንቀበለው ሁኖ አልተገኘም፡፡

 

 ሁ ለተ ኛ ውን ጭብጥ በተ መለከተ፡ - ተጠሪ በአመልካች መኪና ክፍያ ፈጽመው ሲጓጓዙ የነበሩ መሆኑ ያልተካደና በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ግንኙነቱ ውልን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ውልን መሰረት ያደረገ የመጓጓዣ ግንኙነት በን/ሕ/ቁጥር 588 እና ተከታይ ድንጋጌዎች አግባብ ሊታይ የሚገባ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በን/ሕ/ቁጥር 588 ድንጋጌ ይዘት ሲታይ አጓዡ መንገደኛውን በመልካም ይዞታና ጥበቃ እንደዚሁም ስለ ምቾቱና ስለ ጉዞው በውሉ የተወሰነውን ጊዜ አክብሮ እንደተወሰነው እመድረሻ ስፍራ የማድረስ ግዴታ እንዳለበት በሓይለ ቃል አስቀምጦ እናገኛለን፡፡ የዚህ ድንጋጌ መሠረታዊ ይዘት የአጓዡን የትራንስፖርት መኪና በሀላፊነት ተረክቦ መኪናውን ደህንነትና ብቃት አረጋግጦ የትራፊክ ደንብና ሥርዓትን አክብሮ የማሽከርከር ሀላፊነት ያለበት አሽከርካሪ /ሹፌር/ ረዳቱና ሌሎች ሰራተኞች መንገደኛውን መልካም ይዞታና ጥበቃ እንደዚሁም ምቾት በመጠበቅ በሰላም ወደሚፈለግበት ቦታ የማድረስ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስቻል ሲሆን ይህንኑ በሕግ የተጣላባቸውን ግዴታ ካልተወጡ ደግሞ


መንገደኛው በጉዞው ላይ ስለሚደርስበት መዘግየትና በጉዞው ጊዜ ወይም በሚሣፈርበት ወይም በሚወርድበት ጊዜ በአደጋ ምክንያት ለሚደርስበት መቁሰል ወይም የአካል ማጉደል ወይም የህይወት ማለፍ አጓዡ ሀላፊ እንደሚሆን በንግድ ህግ አንቀጽ 595 ስር  በግልጽ ተደንግጓል፡፡የዚህ ድንጋጌ አጓዡ መንገደኛው በጉዞ ጊዜ በሚሣፈርበትና በሚወርድበት ጊዜ በአደጋ ምክንያት ለሚደርስበት መቁሰል ወይም የአካል መጉደል ወይም ህይወት ማለፍ አጓዡ በሀላፊነት የሚጠየቅ መሆኑን በመሠረታዊ መርህነት የሚያስቀምጥ ሲሆን ፣ አጓዡ ከሀላፊነት ነጻ የሚሆንባቸዉን ልዩ ሁኔታዎች የሀላፊነቱን መጠንና አጓዡ በህግ ከተደነገገው መጠን በላይ በሀላፊነት ሊጠይቅ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች የሚደነግጉ ልዩ ድንጋጌዎች አካቶ ይዟል፡፡ በንግድ ህግ አንቀጽ 595 ከተደነገገው ሀላፊነት አጓዡ ነጻ የሚሆንበትን ሁኔታ የሚደነግገው የንግድ ህጉ አንቀጽ 596 ሲሆን በንግድ ህግ አንቀጽ 596 አጓዡ በመንገደኛው ላይ የአካል መጐዳት ወይም የሞት አደጋ የደረሰው ከአቅም በላይ በሆነ ከፍተኛ ሀይል መሆኑን ፣ ወይም ጉዳቱ የደረሰው በሶስተኛ ሰው ጥፋት መሆኑን ወይም በመንገደኛው ጥፋት መሆኑን ያስረዳ እንደሆነ አጓዡ ከሀላፊነት ነጻ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ የካሳ መጠኑን በተመለከተ የቀረበውን ቅሬታ ስንመለከተውም አጓዡ በንግድ ህግ ቁጥር 596 መሠረት አደጋው የደረሰ መሆኑን ለማስረዳት ካልቻለ በመንገደኛው ላይ ለደረሰው ጉዳት በሀላፊነት የሚጠየቅ መሆኑን የንግድ ሕግ ቁጥር 597 ድንጋጌ ያሳያል፡፡ የሀላፊነት መጠን በተመለከተ ደግሞ ለአንድ መንገደኛ ከብር 40,000 /አርባ ሺ ብር/ እንደማይበልጥ የንግድ ህግ አንቀጽ 597 በግልጽ ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ በንግድ ህግ አንቀጽ 597 የተደነገገው የሀላፊነት መጠን አጓዡ በንግድ ህግ አንቀጽ 596 የተደነገጉትና ከሀላፊነት ነጻ የሚያደርጉት ሁኔታዎች መኖራቸውን ለማስረዳት ባልቻለበት ሁኔታና መንገደኛው በንግድ ህግ አንቀጽ 599 በሚደነገገው መሠረት አጓዡ አደጋ ሊያደርስ የሚችል መሆኑን እያወቀ በፈጸመው ተግባር ወይም ጉድለት ምክንያት አደጋው የደረሰ መሆኑን ለማስረዳት ባልቻለበት ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆን ድንጋጌ ነው፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ ግን የአመልካች ንብረት የሆነውን ተሽከርካሪ ያሽከረክር የነበረው የአመልካች ሰራተኛና የመኪናው ሹፌር የሆነው ለአደጋው ምክንያት ስለመሆኑ ተረጋግጦ በወንጀልም ክስ ተመስርቶበት ጥፋተኛ ተብሎ የተቀጣ መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡ አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረቡት ግልጽ የሆነ ክርክርና ማስተባበያም የለም፡፡ በንግድ ህግ ቁጥር 588 በሚደነግገው መሠረት የመንገደኛውን መልካም ይዞታ ደህንነትና ምቾት በመጠበቅ መንገደኛውን የማጓጓዝ ሀላፊነቱን ሊወጡ የሚገባቸውን ወገኖች የመኪና ባለቤት፣ ሹፌር፣ረዳቱና ሌሎች ሰራተኞች ሊሆኑ የሚችሉበት አግባብ መኖሩን፣ በንግድ ህግ አንቀጽ 599 “አጓዡ የተፈፀመው ተግባር ወይም ጉድለት” የሚለው ሀረግ አጓዡ በግሉ የፈጸመውን ተግባር ወይም ጉድለት የሚመለከት ሣይሆን የአጓዡ ሰራተኞች አደጋ ሊያደርስ ወይም ሊፈጠር እንደሚችል እያወቁ የፈጸሙትን


ተግባር ወይም ጉድለት የሚያካትት ስለመሆኑ በሰ/መ/ቁጥር 67973 በሆነው መዝገብ ላይ በቀረበው ጉዳይ በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በማናቸውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያሰገድድ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ በዚህ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተያዘው ጉዳዩ ሲታይም አደጋው የደረሰው የ2ኛ አመልካች መኪና ሲያሸከረክር የነበረው ሹፌር ባጠፋው ጥፋት ስለመሆኑ በበታች ፍርድ ቤቶች የክርክር ሂደት የተረጋገጠ በመሆኑ ለጉዳዩ ተፈጻሚነት ያለው የን/ሕ/ቁጥር 599 መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ እንዲህ ከሆነ  አመልካች  በተጠሪው ላይ ለደረሰው የአካል ጉዳት በግንድ ህግ አንቀጽ 597 ከተደነገገው በላይ ካሣ የመክፈል ሀላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም አመልካች በንግድ ህግ አንቀጽ 597 ከተደነገገው የሀላፊነት መጠን በላይ ለተጠሪ ካሣ የመክፈል ሀላፊነት እንደአለባቸው የንግድ ህግ አንቀጽ 599 ድንጋጌ የሚያስገነዝበን ነው፡፡ በን/ሕ/ቁ 599 ድንጋጌ መሠረት ለመንገደኛው ካሣ የመክፈለ ሀላፊነት ያለበት አጓዥ ለመንገደኛው የሚከፍለው የካሣ መጠን ለመወሰን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2091 እና 2092 የተደነገጉት የካሳ አከፋፈል መርሆች አግባብነት ያላቸው ስለመሆናቸውም ይህ ችሎት ከላይ በተጠቀሰው የሰበር መዝገብ አሰገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አግባብ ጉዳዩ ሲታይም ክሱ መቅረብ ያለበት ከውል ውጪ ሃላፊነትን በሚገዙ ድንጋጌዎች በመሆኑ ተጠሪ በዚህ አግባብ ክስ ማቅረባቸውና የበታች ፍርድ ቤቶች ይህንኑ ክስ ተቀብለው ከውል ውጪ ኃላፊነትን በሚገዙ ድንጋጌዎች መሰረት መወሰናቸው የሚንቀፍበትን ሕጋዊ ምክንየት አላገኘንም፡፡

 

ሶስተኛውን ጭብጥ በተመለከተ፡- ተጠሪ በመኪናው ግጭት ምክንያት በአካላቸው ላይ 50% ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ፣ ከጉዳቱ የተነሳ ለተለያዩ ወጪዎች የተዳረጉ መሆኑንና ከጉዳቱ በፊት በሲዳማ ቡና አብቃይ ገብሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ይሰሩ እንደነበርና በጉዳቱ ምክንያትም የስራ ብቃታቸው እና ሲያገኙ የነበረው የገቢ መጠንን ፍሬ ነገርን ለማጣራትና  ማስረጃን ለመመዘን ስልጣን ባላቸው የስር ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች በጉዳቱ ምክንያት ወደፊት ተጠሪ የሚቀርባቸውን ገቢና ከጉዳቱ ጋር ተያይዘው የወጡትን ወጪዎች በመለየት የካሣ መጠኑን ወስነዋል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በተለይ ካሳውን ሊወሰን የቻለው የተጠሪን እድሜና በአከባቢው በጊዜው የታወቀውን አማካይ እድሜ ስንት እንደሆነ በመለየት ስለመሆኑ ውሳኔው በግልጽ ያሳያል፡፡

በመሰረቱ ካሳ የሚከፈለው ጉዳት መኖሩ ሲረጋገጥ ሲሆን የካሳ አተማመን ፣መጠንና አከፋፈልን በተመለከተ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2090፣2091፣2092 ፣ 2095 እና በሌሎች ድንጋጌዎች የተቀመጠ ሲሆን ከእነዚህ ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚቻለውም ካሳው በተቻለ መጠን ከጉዳቱ ጋር መመጣጠን ያለበት መሆኑን ነው፡፡የበታች ፍርድ ቤቶች በሚሰጡት የካሳ መጠን ላይ ይግባኝ የሌለው መሆኑ በመርህ ደረጃ በፍ/ብ/ሕ/ቁር 2152 ስር የተመለከተ ሲሆን ይግባኙ በልዩ ሁኔታ  የሚፈቀድባቸው


ሁኔታዎች ደግሞ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2153 ስር ተገልጸዋል፡፡ በተያዘው ጉዳይ በአመልካች በኩል የቀረበውን ቅሬታ መሰረት ስናደረግ በካሳ አተማመኑ ላይ በሕጉ የተመለከቱት ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ ሳይገቡ በበታች ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ስለመሠጠቱ የሚያሳይ ነገር ያለ ሁኖ አልተገኘም፡፡ ተጠሪ አካላቸው በሕገ መንግስቱም ጥበቃ የተደረገላቸው ሲሆን ካሳው ሲወሰንም ይህንኑና ጉዳቱ በአመልካች የወደፊት ኑሮ ላይ ሊያስከትለው የሚችለው አጠቃላይ ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት ሊወሰን የሚችል ነው፡፡ ከውል ውጪ ኃላፊነትን በተመለከተ የሚገዙት የፍትሓብሔር ሕጋችን ድንጋጌዎች መንፈስ የጉዳትን ጠቅላላ ባህርይና የካሣ ልክ አተማመን ሁኔታዎችን ያስገነዝቡናል፡፡ በዚህም መሠረት ጉዳት በሰው ጥቅም ላይ ችግር የሚያደርስ መሆኑን፣ ይህም ጥቅም ማቴሪያሊዊ /በሰው አካል ወይም ንብረት የደረሠ/ ወይም ሞራሊዊ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡ የተጎዳ ሰው ደግሞ መካስ እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ የካሣውን አተማመን በተመለከተም መጠኑ በተበዳዩ ላይ ከደረሰው ጉዳት ጋር እኩል ሁኖ መመዘን ያለበት መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2091 ድንጋጌ ያሣያል፡፡ የጉዳት ካሣ ከደረሰው ጉዳት ጋር እኩል ሆኖ ሲመዘንም በተጎጂው ላይ በእርግጠኝነት መድረሱ የታወቀ /actual damage/ ወይም ወደፈት ሊደርስ የሚችል ጉዳትን/future damage/ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት የግድ የሚል መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2091/1/ እና 2092 ድንጋጌዎች መንፈስ ያስረዳል፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት የጉዳት ካሣ ሊተመን የሚገባ መሆኑን ሕጉ በግልጽ ከማስቀመጡም በተጨማሪ የአተማመኑ ሥርዓትም እንደጉዳቱ ዓይነትና ማስረጃ አቀራረብ ውስብስብነት ሊለያይ የሚችል መሆኑን የሕጉ መንፈስ ያስገነዝባል፡፡ በዚህም መሠረት የጉዳት ካሣ መጠን አጥጋቢና በቂ ማስረጃን ወይም ርትዕን መሠረት በማድረግ ሊወሰን የሚገባው መሆኑን የካሣ አከፋፈሉን ልክ በሚደነግገው የሕጉ ክፍል የተቀመጡ ድንጋጌዎች ያስገነዝባሉ፡ በሌላ በኩል የካሣ አተማመን ሥርዓት ጠቅላላ የመሥራት አቅም /General utility/ ሣይሆን ልዩ ጠቀሜታ/specific utility/ መርህን ቢከተል ፍትሓዊነት ያለው አሠራር መሆኑ ይታመናል፡፡ ይህም አሠራር በተጨባጭ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ የካሣውን ልክ ያላግባብ ከማጋነንና ከመቀነስ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በመሆኑም ጉዳት መድረሱ በማስረጃ ከተረጋገጠና ጉዳቱም በተጎጂው የወደፊት ሕይወት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሣዳሩ እንደማይቀር ምክንያታዊ እርግጠኝነት ያለው መሆኑ ከተረጋገጠ ካሣ መወሰን ከአጠቃላይ የሕጉ ዓላማና ከፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2091 እና 2092 ድንጋጌዎች መንፈስ አኳያ አግባብነት ያለው ነው፡፡ መጠኑን በተመለከተ በሕጉ ለዳኞች በተሰጠው ሥልጣን ወይም በጉዳዩ ላይ በቀረበው ማስረጃ መሠረት በመተመን ለተጎጂው መፍርድ የሚቻልበት ሁኔታ በሕጉ መኖሩን ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎችና የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2101 እና 2102 ድንጋጌዎች ያስገነዝባሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ጉዳቱ መድረሱ እየታወቀ የአሁንና የወደፊት ቁሣዊ ጉዳት /material damage/ ስለመኖሩ    ተጎጂው


አላስረዳም ተብሎ የመካስ መብት ማጣት ከአጠቃላይ ከውል ውጪ ኃላፊነትን ከሚገዛው ሕግ አላማ ጋር አንድ ላይ የሚሄድ አይሆንም፡፡

ወደያዝነው ጉዳይ ስንመለስም ተጠሪ  በአመልካች መኪና ተሳፍረው ሲሄዱ በደረሰው  ከተራራ ጋር የመጋጨት አደጋ በአካላቸው ላይ ጉዳት መድረሱ በሚገባ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳቱ ወደፊት ሊጠፋ የሚችል ስለመሆኑም የተገለፀ ነገር የለም፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ በአመልካች የቀረበው ቅሬታም ሆነ በአጣሪ ችሎቱ በጭብጥነት የተያዘው ነጥብ በበታች ፍርድ ቤቶች በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠውን ነጥብ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2090፣2141 እና 2153 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ጋር ያላገናዘበ ሁኖ አግኝትናል፡፡ በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት የሚያስችል ህጋዊ ምክንያት ስላለገኘን ተከታዩን ወስነናል፡፡

 

 ው  ሣ ኔ

1. በሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 1656 ሚያዚያ 03 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 594440 በ10/01/2006 ዓ/ም የተሻሻለውና ይህንኑ የተሻሻለውን ውሳኔ የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ ያፀናው የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 94784 በ30/04/2006 የሠጠው ትዕዛዝ  በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1)መሰረት ፀንቷል፡፡

2. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

መ/ይ