103826 traffic violation/ execution of judgment

የትራፊክ ደንብን በመጣስ የሚተላለፍ ቅጣትን ለአፈፃፀሙ ፍ/ቤት ሊቀርብ የሚችል ስላለመሆኑ የትራፊክ ፍሰትን ለመቆጣጠር የወጣው ደንብ ቁጥር 208/2003 አንቀፅ

 

የሰ/መ/ቁጥር 103826 ቀን 25/01/2008 ዓ.ም

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ

ሌሊሴ ደሳለኝ

 

አመልካች፡- አንዋር አህመድ - አልቀረቡም ተጠሪ፡- የቤ/ጉ/ክ/መ/ፍትህ ቢሮ - አልቀረቡም

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የአፈፃፀም ክስ ሂደትን የተመለከተ ነው፡፡ ክርክሩ የተጀመረው ከፓዊ ወረዳ ፍ/ቤት ሲሆን የፓዊ ወረዳ ፍትህ ጽ/ቤት የፍርድ ባለመብት በመሆን በአመልካች ላይ ያቀረበው የአፈፃፀም ክስ ሲሆን ዝርዝሩም አመልካች ያለፈቃድ በማሽከርከር በቀን 12/6/2005 - 13/06/2005 ዓ.ም የትራፊክ ደንብ በመጣስ 5000 ብር የተቀጣ ስለሆነ በቅጣቱ መሰረት ይፈጽምልኝ በማለት አቅርቧል፡፡ አመልካችም ያለአግባብ ስለተቀጣሁ ልፈፅም አይገባም በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ የፓዊ ወረዳ ፍ/ቤት አመልካች በውሳኔው መሰረት ለመፈፀም ፈቃደኛ ስለአልሆነ በስድስት /6/ ወር/ እስራት እንዲቀጣ ገንዘቡን የሚከፍል ከሆነ ደግሞ ከእስራት እንዲፈታ በማለት ይወስናል፡፡

 

አመልካች በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሲያቀርቡ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ የሕዝብ የመንገድ ትራንስፖርት የስነ ስርዓት መቆጣጠሪያ መመሪያ ስራ ጥፋት ሪኮርድ አያያዝና ስለቅጣት ደረጃ በዝርዝር የሚገልፅ እንጅ ይህ ቅጣት ባልተፈፀመ ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት በሕጉ የተገለጸ ነገር ስለሌለ በፍ/ቤት የተሰጠ ምንም ውሳኔ ሳይኖር አመልካች እንዲፈፅም መደረጉ ትክክል አይደለም በማለት ወረዳው ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡


ተጠሪ ውሳኔውን በመቃወም ለክልሉ /የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቦ ፍ/ቤቱም በሥ/ሥ/ሕጉ ቁጥር 377 መሰረት ይግባኙን በመሰረዝ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ጉዳዩ ሲቀርብ ሰበር ችሎቱም የፓዊ ወረዳ ፍርድ ቤት በአመልካች ላይ የመንገድ ትራንስፖርት መመሪያን ደንብን በመተላለፍ የቀረበበትን የአፈፃፀም ክስ ማስፈፀሙ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ እና የከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የፓዊ ወረዳ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በማፅናት ወስኖአል፡፡

 

አመልካችም ለዚህ ሰበር ችሎት በቀረቡት የሰበር አቤቱታ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ስለአለበት ይታረምልኝ በማለት አመልክተዋል፡፡ በትራፊክ ደንብ መተላለፍ ምክንያት በአመልካች ላይ የተጣለውን ቅጣት በፍርድ ቤት የአፈፃፀም ክስ ሊቀርብበት ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ለመመርመር ሲባል ተጠሪ  መልስ እንዲያቀርብ ተደርጎአል አመልካችም የመልስ መልስ ሰጥቷል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ እና የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተገለፀ ሲሆን እኛም መዝገቡን ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርመረናል፡፡ አመልካች ላይ የቀረበው የአፈፃፀም መዝገብ በትራፊክ ደንብ መተላለፍ ምክንያት ስራን የትራፊክ ደንብን መተላለፍ የሚገዛው ትራፊክን ለመቆጣጠር  የወጣ የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 208/2003 ነው፡፡

 

በዚህ ደንብ አንቀፅ 85 ስለ ቅጣቱ እና አፈፃፀሙን የደነገገ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 85/2/ መሰረት የትራፊክ ተቆጣጣሪ የዚህን ደንብ ድንጋጌዎች ተላልፎ ያገኘው አሽከርካሪ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱን እንዲሰጠው በመጠየቅ ቅጣት እንዲፈፅም በፅሁፍ ማሳወቅ አለበት በማለት ደንግጎአል፡፡ በዚህ ደንብ መሰረት ይህን አዋጅ የተላለፈ አሽከርካሪ ቅጣት ከተጣለበት አፈፃፀሙ የትራፊክ ተቆጣጣሪው በፅሁፍ በማሳወቅ የተቀጣው አሽከርካሪ እንዲፈፅም  ማድረግ ነው እንጅ ለአፈፃፀም ፍ/ቤት የሚቀርብ ስለመሆኑ በደንቡ አልተቀመጠም፡፡  ከደንቡ እንደምንረዳው በትራፊክ ተቆጣጣሪው በዛ ሂደት እንዲቀጥል እንጂ ፍ/ቤት ለአፈፃፀም እንዲቀርብ አይደለም፡፡ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 378/1/ የተደነገገው በፍ/ቤት አፈፃፀም የሚፈፀመው ውሳኔው በፍ/ቤት የተወሰነ መሆኑን ታሳቢ የደረገ ነው፡፡ በመሆኑም የትራፊክ ፍሰትን ለመቆጣጠር ሲባል በደንብ ቁጥር 208/2003 አንቀፅ 85 መሰረት የሚጣስ ቅጣት አፈፃፀሙ በፍ/ቤት ሊቀርብ የሚችል መሆኑን የሚደነግግ ሕግ የለም፡፡ ይህ ሆኖ እያለ በተጠሪ በኩል የቀረበውን የአፈፃፀም ማመልከቻ ውሳኔው በፍ/ቤት ባልተሰጠበት ሁኔታ እንዲሁም በደንብ ቁጥር 208/2003 አፈፃፀሙ ለፍ/ቤት መቅረብ እንደአለበት ሳይደነግግ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጠቅላይ    ፍርድ


ቤት ሰበር ችሎት በትራፊክ ተቆጣጣሪ የተጣለው ቅጣት በፍ/ቤት ሊፈፀም ይገባል በማለት የወሰነው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት ብለን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመ/ቁ 05033 ሚያዝያ 27/2006 በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ የፓዊ ወረዳ ፍ/ቤት በመ/ቁ 06041 በቀን 22/09/2005 በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በማፅናት የወሰነውን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348/1/ መሰረት ተሽሯል፡፡

2. የመከተል ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 09 በቀን 28/10/2005 በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ /በአብላጫ ድምፅ/ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348/1/ መሰረት ፀንቷል፡፡

3. እዚህ ፍ/ቤት ለተካሄደው ክርክር ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 


 

 

ብ/ይ