103458 pension/ scope of public pension law

የመንግስት ሰራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2003 የተፈፃሚነት ወሰን

 

የሰ/መ/ቁ 103458 ቀን 27/01/2008 ዓ.ም

ዳኞች፡-  ተገኔ ጌታነህ

 

ተሻገር ገ/ስላሴ ተፈሪ ገብሩ ሹምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

አመልካች፡- አቶ ጋረድ ለበሰ

 

ተጠሪ፡- የመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የጡረታ መብትን የሚመለከት ሲሆን አመልካች በተለየዩ መ/ቤቶች ለ17 ዓመት እና በአ/ብ/ክ/መንግስት ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኃላፊ ሆነው ለ1ዐ አመት አገልግለው በራሳቸው ጥያቄ ከሹመት የተነሱ መሆኑን በአዋጅ ቁ 714/2003 አንቀፅ 19/5/ መሰረት ከአንድ የምርጫ ዘመን ያገለገሉና ዕድሜያቸው ከ5ዐ አመት በላይ በመሆኑ የጡረታ መብታቸው እንዲከበርላቸው አሰሪ መ/ቤታቸውን ጠይቀው የተሰጣቸው ምላሽ ፍትሐዊ አለመሆኑን ገልፀው ቅሬታቸውን ለሰሜን/ምዕ/ሪጅን ማ/ዋ/ኤጀንሲ አቅርበው ኤጀንሲው አመልካች ስራቸውን የለቀቁት በራስ ፈቃድ በመሆኑ በአ/ቁ 714/2003 አንቀፅ 19/3/ መሰረት ዕድሜያቸው 55 አመት ሲሞላ ከየካቲት 1/2010 ጀምሮ የጡረታ አበል የሚወሰንላቸው መሆኑን ኮሚቴው የወሰነ ሲሆን፡-

 

በዚህ ውሳኔ አመልካች ቅሬታቸውን ለማህበራዊ ዋሰትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የይግባኝ አቤቱታ አቀርበው የመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋሰትና ኤጀንሲ የሰጠው ውሳኔ በአግባቡ ነው በማለት ያፀናው መሆኑን ከቀረበው የአመልካች አቤቱታ እና ውሳኔዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

 

አመልካች በዚህ ውሳኔ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት በይግባኝ አቀርበው ይግባኝ የተባለበት ውሳኔ ጉድለት የለበትም ተብሎ በፍ/ብ/ስ/ስ/ቁጥር 337 የዘጋው ሲሆን አመልካች በዚህ ውሳኔ ተፈፀመ ያሉትን ስህተት በመዘርዘር በዚህ ሰበር ችሎት እንዲታረምላቸው አቅርበዋል፡፡


የአመልካች አቤቱታ ለሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀርባል የተባለው ከአማራ ክልል አዋጅ ቁጥር 172/2002 አንቀፅ 3/1//ሀ/ አንፃር አመልካች የጡረታ ይከበርልኝ ጥያቄ ውድቅ መደረጉ በሰበር ለመመርመር ነው፡፡

 

የአመልካች አቤቱታ ይዘት የስር ፍ/ቤቶች ለውሳኔያቸው መሰረት ያደረጉት አዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀፅ 19/3/ ለመንግስት ተሿሚዎች የሚያገለግል ሣይሆን ከሹመት ውጭ በመንግስት ሰራተኞች ሲያገለግሉ ለነበሩ ሰራተኞች ነው የተጠቀሰው አንቀፅ በፌዴራል ልዩ የተሿሚዎች አዋጅ ቁጥር 653/2001 እና በአማራ ክልል ዝክረ ሕግ አዋጅ ቁጥር 172/2002 በተለየ ሁኔታ መብት የተሰጣቸውን የመንግስት ኃላፊዎች የማይመለከት በመሆኑ ይህ ድንጋጌ ከዝክረ ሕግ አዋጅ ቁጥር 172/2 አንቀፅ 3/1//ሀ/ ጋር ተጣምሮ ሊተረጎም የማይገባው ሆኖ ሣለ የስር ፍ/ቤቶች የሰጡት የሕግ ትርጉም መሰረታዊ ስህተት ስላለበት ይታረምልኝ የሚል ነው፡፡

 

ተጠሪ በበኩሉ የአማራ ክልል አዋጅ ቁጥር 172/2002 አንቀፅ 3/1//ሀ/ ከመንግስት ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ ቁ. 714/2003 አንቀፅ 62/2/ መሰረት የሚቃረን ስለሆነ ተፈፃሚነት የለውም፡፡ በአዋጅ ቁ. 714/2003 አንቀፅ 2/1/ የመንግስት ሰራተኛ ማለት የመንግስት ተሿሚዎችንም የሚያካትት መሆኑ ተመልክቷል የጡረታ መብትና ጥቅምን በተመለከተ የክልሉ  አዋጅ ተፈፃሚነት የለውም፡፡ ተፈፃሚነት ያለው አዋጅ ቁ. 714/2003 ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ አመልካችም አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡ እንደመረመርነውም የመንግስት ሰራተኞች ጡረታን በተመለከተ ስራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 714/2003 ሲሆን በዚህ አዋጅ ትርጓሜ አንቀፅ 2/1/ ላይ የመንግስት ሰራተኛ በመንግስት መ/ቤት በቋሚነት በመቀጠር ደመወዝ እየተከፈለው የሚሰራ ሰው ሲሆን የመንግስት ተሿሚዎች፣ የምክር ቤት አባላትንና የመከላከያ ሰራዊት አባላትን እንደሚጨምር ተመልክቷል፡፡ በአንቀፅ 2/2/ “ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊ” ማለት ሚኒስቴር፣ሚኒስቴር ዳኤታ ወይም ተመሳሳይ  ደረጃ  ያለው የመንግስት ኃላፊ ነው በሚል የተመለከተ ሲሆን በአንቀፅ 2/6/ “መንግስት” ማለት በኢፌዴሪ መንግስት እና የክልል መንግስታትን እንደሚያጠቃልል በአንቀፅ 2/7/ ደግሞ “ክልል” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ከኃላፊነት የተነሱ የሀገርና የመንግስት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች መብትና ጥቅም ለመጠበቅ በወጣው አዋጅ ቁጥር 653/2001 አንቀፅ 12 እና 21 የጡረታ መብትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በአዋጅ 714/2003 አንቀፅ 62/1//ሐ/ የተሻሩ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 2 ይህን አዋጅ የሚቃረኑ ማናቸውም ሕጎች ወይም የአሰራር


ልምዶች ይህን አዋጅ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚ አይሆኑም በማለት ተመልክቷል፡፡ የአ/ብ/ክ/መ/አዋጅ ቁጥር 172/2002 ቀደም ብሎ የወጣ ነው፡፡ ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ የአመልካች የጡረታ መብት ጥያቄ መታየት ያለበት የጡረታ መብትን አስመልክቶ በወጣው ልዩ ሕግ በመንግስት ሰራተኞች የጡረታ ሕግ አዋጅ ቁ. 714/2003 እንጅ በአ/ብ/ክ/መ/በወጣው ዝክረ ሕግ አዋጅ ቁጥር 172/2002 አይደለም፡፡

 

በአዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀፅ 19/5/ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊን ወይም የምከር ቤት አባልን የሚመለከት ሲሆን ለከፍተኛ የመንግስት ኃላፊ ወይም የምክር ቤት አባል በአዋጅ ትርጓሜ ክፍል ከተሰጠው ትርጉም አንፃር አመልካች ይህን የሚያሟሉ ባለመሆኑ በአዋጅ አንቀፅ 19/3/ መሰረት በስር ፍ/ቤት የተሰጠው ውሳኔ በአግባቡ በመሆኑ የሰበር ፍ/ቤት በዚህ ረገድ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ፈፅሟል የሚባል አይደለም ብለናል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በሰሜን ምዕ/ሪጅን ማ/ዋ/ኤጀንሲ በቀን 8/6/2005፣ የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ በቁጥር ጡ/ይ/1/1/92/2006 በቀን 17/08/2006 የሰጡት ውሳኔ እና የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በፍ/ብ/ይ/መ/ቁ 100266 በቀን 11/09/2006 ዓ.ም በዋለ ችሎት የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ቁ 348/1/ መሰረት ፀንቷል፡፡

2. ግራ ቀኙ በዚህ ሰበር ችሎት ላደረገው ክርክር ያወጡትን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ የተዘጋ በመሆኑ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

ብ/ይ