109535 brokerage/ service fee

የድለላ አበል ክፍያ መጠን ከተሰጠው አገልግሎት ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን የሚገባ ስለመሆኑ በድለላ አበል መጠን ላይ በሚደረገው ክርክር እንደ ጉዳዩ ዓይነት እና የተሰጠው አገልግሎት እየተገናዘበ የሚወሰን ስለመሆኑ የን/ሕ/ቁ. 59(3)

 

የሰ/መ/ቁ.109535 የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ/ም


መዝገቡ መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰትተናል፡፡

 ፍ ር ድ

ጉዳዩ የደለላ አበል ክፍያ የተመለከተ ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራንዮ ምድብ ችሎት የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ላይ በቀረበው ክስ መነሻነት ነው፡፡ የክሱ ይዘትም የአሁነ ተጠሪ ከአመልካች ጋር በነበረው የቆየ የኮሚሸን ስራ ግንኝነት በቃል በደረጉት ስምምነት የአመልካች ንብረት የሆነው አንድ ቪላ መኖርያ ቤት ተከራይ ፈልገው እንዲያካራዩላቸው በተለመደው የኮሚሽን ክፍያ አሰራር መሰረት የአንድ ወር  የኪራይ ገቢ በኮሚሽን መልክ ለተጠሪ እንደሚከፈሉ በዚህም በተደጋጋሚ በተደረገው ጥራት ቤቱ ጰጉሜ 02 ቀን 2005 ዓ/ም የሮያል ኖረዊጂን ኤምበሲ ቤቱን ለጽ/ቤቱ አገልግሎት በወር 20,000 ዶላር ሂሳብ ኪራይ በመስማማት መስከረም 23 ቀን 2006 ዓ/ም የ10 ዓመት ኪራይ ውል ስምምነት በመፈራረም ተከራዩ የአንደኛ ኣመት ቅደመ ክፍያ 4,540,800 ብር ለአመልካች የከፈለ ሲሆን አመልካች ግን በስምምነቱ መሰረት መክፈል የሚጠበቅባቸው የአንድ ወር  ኪራይ ሒሳብ ለመክፈል ፈቃደኛ በለመሆኑ የኮሚሽን ክፍያ 378,400.00 ብር ከመስከረም  2006 ዓ/ም ከሚተሰብ 9% ህጋዊ ወለድ ወጪና ኪሳራ እንዲከፍላቸው ዳኝነት መጠየቃቸው የሚያሰይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካች የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚ እና በፍሬ ነገሩ መልስ አቅርበዋል፡፡ የመጀመሪያ መቃወሚያ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ የግዘት ስልጣን እንደሌለው ቤቱም የራሰቸው አለመሆኑን የሚገልጽ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ጉዳዩ ከኖርዋይ ኤምበሲ በተደረገው የኪራይ ውል ስምምነት ተጠሪ ሳይሆን እንግልዝኛው ዴቪድ ዊልስ የተበሉ የረዱዋቸው ስለ መሆኑ የቆየ ግንኝነት እንደልነበራቸው በመካከላቸው ውል የለም እንጅ ውል አለ ከተባለ መክፈል ያላበቸው በመቶ ሁለት ፐርሰንት (2%) ስለመሆኑ የሚገልጽ መልስ አቅርቦዋል፡፡

የስር ፍርድ ቤትም ጉዳዩ ለመመልከት ሥልጣን እንደለው ቤቱም በአመልካች የሚታወቅ የራሳቸው ስለመሆኑ በሰነድ የተረጋገጠ ነው በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ የስር ፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙ ክርክር እና ማስረጃ


መርምሮ ተገቢ ነው ያለውን ጭብጥ ከያዘ በኃላ የተጠሪ ምስክሮች በአመልከች እና ተጠሪ መካከል የድለላ ስራ ግንኝነት መኖሩን ማረጋገጣቸው የአመልከች ምስክሮች በአንፃሩ የራሱ ልጆች በመሆናቸው በተሸለ አግባብ አስረድቷል ለማለት እንደማይቻል የተጠሪ 2ኛ ምስክር የኖርዋ ኤምባሲ ሰራተኛ በመሆኑ ወገንተኝነት እንደሌለው እና ኤምባሲው እና አመልካች ያገናኛቸው ተጠሪ ስለመሆኑ ማስረዳቱን ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 686/2002 በ20/02/2006 ዓ/ም የታደሰ የድላለ ስራ ፈቃድ ያለቸው መሆኑ መረጋገጡ ክፍያ በተመለከተም በቃል ባደረጉት ስምምነት የአንድ ወር የቤት ኪራይ ክፍያ እንደሆነ ቤቱም በወር 20,000 ዶላር በመስማማት ለ20 ዓመት እንደተከራየ ኤምባሲው በበኩሉ 57,000 ብር መክፈሉ ሲታይ ከአመልከች ጋር ያገናኙዋቸው ተጠሪ መሆናቸውን እንደሚያሳይ በመግለጽ በግራ ቀኙ የቃል ውል ስምምነት መሰረት የአንድ ወር ኪራይ ሂሳብ በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር 378,400 ብር ይህ ክስ ከተመሰረተበት ከታህሳስ 16 ቀን 2006 ዓ/ም ጀምሮ ተከፍሎ እስኪያልቅ ድረስ ከ9% ሕጋዊ ወለድ ጋር ለተጠሪ ይክፈሉ በማለት ወስኗል፡፡

የአሁኑ አመልከች በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም ተቀባይነት አለገኘም፡፡ የህ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ የአመልካች አቤቱታ ተመርምሮ ለሰበር ይቅረብ በመባሉ ግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር አደርጓአል፡፡ አመልካች ሰፊ የሰበር ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን እንኳን ይዘቱ ከተጠሪ ጋር የድለላ ስምምነት እንዳልነበረ ይከፈል የተበለው የገንዘብ መጠንም ከፍተኛ በመሆኑ ሊቀንስ እንደሚገባ የሚጠይቅ ነው፡፡ ተጠሪ በበኩለቸው በአመልካች ጋር ስምምነት የነበራቸው ስለ መሆኑ ማስረዳታቸው የክፍያ መጠኑም አመልካች በ20 ዓመት ያገኙታል ተብሎ ከሚጠበቀው የኪራይ ገቢ አንጻር እና ተጠሪ ከሰጡት የድለላ አገልግሎት ሲታይ ተመጣጠኝ ነው በዝቷል ሊባል አይገባም የሚል ክርክር አቅርበዋል፡፡ የመልስ መልስም ቀርበዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለጸ ሲሆን ይህ ችሎትም ግራ ቀኙ በጽሑፍ ያደረጉት ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና ጉዳዩ ለሰበር ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ የተያዘው ጭብጥ የደላለ አበል ክፍያ መጠን በተመለከተ በዚህ መዝገብ የተሰጠው ውሳኔ ከንግድ ሕግ አንቀጽ 59(3) አንፃር ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ነው የሚል ነው፡፡

ከክርክሩ መገንዘብ የተቻለው የስር ፍርድ ቤቶች በፍሬ ነገር ደረጃ በአመልካች እና ተጠሪ መካከል የድለላ ስራ ግንኝነት መኖሩን ማረጋገጣቸው ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤት የአመልከች እና ተጠሪ ምስክሮች ቃል የሰነድ ማስረጃ መርምሮ የተጠሪ ምስክሮች ክሱን በተሸለ አግባብ ማስረዳታቸውን ከድምዳሜ ላይ መደረሱን መዝገቡ ያሳያል፡፡ የስር ፍርድ ቤት የአሁን ተጠሪ ባደረጉት ጥራት አመልካች አንድ ቪላ ቤት ለኖርዌይ ኤምባሲ ለ20 ዓመት ማከራየታቸው እና ክፍያም በወር


20,000 ዶላር ስለመሆኑ የከራከረ ጉዳይ አይደለም፡፡ የአሁኑ አመልካች ከተጠሪ ጋር የድለላ ስራ ግንኝነት የለንም በሚል በአጽንኦት የተከራከሩ ቢሆንም የስር ፍርድ ቤት ግንኙነት መኖሩን ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤት የፍሬ ነገር ማጠራት እና ማስረጃ ምዘና እና ድምዳሜ በዚህ ችሎት በድጋሚ የሚመዘን ሆኖ አልተገኘም፡፡ ምክንያቱም የሰበር ሰሚ ችሎት በሕግ ተለይቶ የተሰጠው ሥልጣን መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም ስለመሆኑ ከኢፌዴሪ ህግ መንግስት አንቀጽ 80(3)(ሀ) እና አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 10 መሠረታዊ ድንጋጌዎች ይዘት መንፈስ የምንገነዘበው ነው፡፡ በመሆኑም አመልከች በፍሬ ነገር ክርክር እና ማስረጃ ምዘና ላይ ያቀረቡት ክርክር በአጠሪ ችሎት በጭብጥ ከለመያዙ በተጨማሪ ከዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ሥልጣን ውጪ በመሆኑ አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረቡት ክርክር የህግ መሠረት የለውም ብለናል፡፡

አመልካች ለተጠሪ እንዲከፈል የተወሰነው የአንድ ወር የቤት ኪራይ ሒሣብ ብር 378,400.00 ከ9% ወለድ ጋር በዝቷል የሚል ክርክር አቅርበዋል፡፡ አመልካች አከራከሪው ቤት ለ20 ዓመት በወር 20,000 ዶለር ለኖርዌይ ኤምባሲ ማከራየታቸው የተካደ ጉዳይ አይደለም፡፡ የድለላ ኣባል ክፍያ መጠን በግራ ቀኑ ስምምነት የሚወሰን ሲሆን ፍርድ ቤቱ የድለላ አበል በዝቷል የሚል እምነት ከያዘ ሊቀንስ እንደሚችል በንግድ ህግ አንቀጽ 59 (3) ሥር ተመልክቷል፡፡ በመሰረቱ የድለላ አበል ክፍያ መጠን ከተሰጠው አገልግሎት ጋር ተመጠጣኝ ሊሆን እንደሚገባ የሚታመን ቢሆንም ግራ ቀኙ የአበል ክፍያ መጠን ሲወሰኑ ታሰቢ ያደርጓቸው ነገሮች ግምት ውስጥ መግባት አለበቸው፡፡ በተያዛው ጉዳዩ አከራካሪ የሆነው ጭብጥ ለተጠሪ የሚከፈለው የደለላ አበል ክፍያ መጠን በዝቷል? ወይስ አልበዛም? የሚል ነው፡፡ ከላይ እንተመለከተው ግራ ቀኙ ፈቅደው ያደረጉት ስምምነት ስለመሆኑ የስር ፍ/ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ አረጋግጧዋል፡፡ አመልከች የድለላ አበል መጠን 2% መሆን አለበት በማለት የተከራከሩ ቢሆንከም የዚህ ክርክር ሕጋዊ መሰረት ማሳየት አልቻሉም፡፡ የቤት ኪራይ ውሉ ለ20 ዓመት የሚቆይ መሆኑ ሲታይ የስር ፍርድ ቤት ለተጠሪ በስምምነታቸው መሰረት የአንድ ወር ኪራይ ሒሳብ እንዲከፈል መወሰኑ የግራ ቀኑ ስምምነትና አጠቃላይ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የወሰነው መሆኑን ከመቀበል ውጭ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለመሆኑ የሚያሰይ ነገር አልቀረበም፡፡ የቤት ኪራይ ውል ለ20 ዓመት መደረጉን በፍሬ ነገር ደረጃ ተረጋግጦ በአመልከች እና ተጠሪም የድላለ ስራ ስምምነት መኖሩን የስር ፍ/ቤት በተቀበለበት ሁኔታ የድለላ አበል ክፍያ መጠን በዝቷል ወይም አንሰዋል በሚል በመጠኑ ላይ የሚደረገው ክርክር አጠቃላይ ሁኔታዎች መመልከት የሚጠይቅ እንጂ አንድ ወጥ መስፈርት መሰረት ተደረጎ የሚወሰን ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ  ደግሞ በድለላ አበል መጠን ላይ በሚደረገው ክርክር እንደጉዳዩ ዓይነት እና የተሰጠው አገልግሎት እየተገናዘበ የሚወስን ከመሆኑ አንፃር የስር ፍ/ቤት የደረሰበት ድምዳሜ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት አልተቻለም፡፡ በዚህ ሁሉ   ምክንያት የስር ፍርድ ቤት የድለላ   ስምምነት


መኖሩን በፍሬ ነገር ደረጃ አረጋግጦ ተጠሪ ለሰጡት አገልግሎት የአንድ ወር ኪራይ ሒሰብ 378,4000.00 ከ9% ወለድ ጋር እንዲከፈለቸው መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈጸሙን አያሰይም፡፡ በዚህም ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ. 35650 በ21/02/2007 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ. 162863 በ15/05/2007 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ ጸንቷል፡፡

2. በአመልካች እና ተጠሪ የድለላ ስራ ስምምነት መኖሩን ተረጋግጦ የቤቱ የአንድ ወር ኪራይ ብር 378,400.00 ከ9% ወለድ ጋር እንዲከፈል መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡

3.  የዚህ ፍ/ቤት ክርክር ያስከተለው ውጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸው ይቻሉ ብለናል፡፡

 ት ዕ ዛ ዝ

በዚህ ፍ/ቤት መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ/ም የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል፡፡

መዝገቡ   ወደ መ/ቤት ይመለሰ

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 
 
 

Google Adsense