102652 family law/ divorce/ company shares/ partition of shares

በጋብቻ ጊዜ የተፈራ የባልና ሚስት የጋራ የሆነ የአክስዮን ድርሻ በፍቺ ጊዜ በአይነት ሊከፋፈል የሚችል ስለመሆኑ፣

 

የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ  91 እና 92

የሰ/መ/ቁ.102652 መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም.

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ዓሊ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡-ወ/ሮ ሀቢባ መካ -ከጠበቃ ዘውዱ ተሾመ ጋር ቀረቡ ተጠሪዎች፡-

1.  አቶ ደሊል ሁሴን - ቀረቡ

2.  ኢትዮ የአሽከርካሪዎች እና መካኒኮች ማሰልጠኛ ማዕከል ኃ. የተወሰነ የግል ማህበር

- ጠበቃ ስንታየሁ ብርሃኑ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ የፍቺ ውሳኔን ተከትሎ በጋብቻ ውስጥ የተፈራ የአክሲዮን ድርሻ በተጋቢዎቹ መካከል የሚከፋልበትን ስርዓት አስመልክቶ የተነሳ የአፈጻጸም ክርክርን የሚመለከት ነው፡፡

 

የጉዳዩን አመጣጥ በተመለከተ የፍቺ ውሳኔን ተከትሎ በአመልካች እና በ1ኛ ተጠሪ መካከል በነበረው የንብረት ክፍፍል ክርክር በ2ኛ ተጠሪ ማህበር ውስጥ በ1ኛ ተጠሪ ስም ተመዝግቦ የሚገኘው 162 የአክሲዮን ድርሻ በጋብቻ ውስጥ የተፈራ የጋራ ንብረት መሆኑ ተረጋግጦ እኩል እንዲካፈሉ በስረ ነገሩ ውሳኔ የተሰጠ መሆኑን፣ይህንኑ ውሳኔ ለማስፈጸም አመልካች ባቀረቡት የአፈጸጸም ክስ ላይ የአሁኑ 2ኛ ተጠሪ የፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 418 ድንጋጌን ጠቅሶ መቃወሚያ አቅርቦ የነበረ መሆኑን፣ፍርድ ቤቱም መቃወሚያው ወደፊት የሚታይ ነው በማለት የጋራ ናቸው የተባሉትን ሌሎች ንብረቶች በተመለከተ አፈጻጸሙን መቀጠሉን፣ከዚህ በኃላ የአክሲዮን ድርሻውን በተመለከተ እንደ ፍርዱ እንዲፈጸምላቸው አመልካች አቤቱታ ማቅረባቸውን፣ፍርድ ቤቱም የአክሲዮን ድርሻው የሚገኝበት ማህበር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ለአፈጻጸሙ ያመች ዘንድ በአፈጻጸም ጥያቄው ላይ ማህበሩ አስተያየት እንዲሰጥ ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎ ከቀድሞ ተጋቢዎች መካከል  አንዳቸው ለሌላኛው ድርሻውን ለቆ አንደኛው ወገን በማህበሩ አባልነት መቀጠል የሚችል ከመሆኑ ውጪ ሁለቱን ወገኖች በአንድነት በማህበሩ ውስጥ የማይፈልጋቸው መሆኑን ገልጾ አስተያየት ማቅረቡን፣ግራ ቀኙ የዋጋ ግምቱን ተቀብለው አንዳቸው ለሌላኛው ድርሻውን ለመልቀቅ መስማማት ያልቻሉ መሆኑን እና የማህበሩ አባላት ባልተስማሙበት ሁኔታ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ሌላ ሰው በማህበሩ ውስጥ አባል እንዲሆን መወሰን የማይችል መሆኑን ገልጾ የአክሲዮን ድርሻው


ተሽጦ ገንዘቡን አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ እኩል እንዲከፋፈሉ ትዕዛዝ መስጠቱን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል፡፡

 

አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን ዘግቶ በማሰናበቱ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ ለክርክሩ መነሻ የሆኑት አክሲዮኖች በዓይነት መካፈል የሚችሉ ሆነው የ2ኛ ተጠሪ መተዳደሪያ ደንብም ሳይከለክል አክሲዮኖቹ በሐራጅ ተሸጠው ክፍፍሉ እንዲፈጸም የመወሰኑን አግባብነት ተጠሪዎቹ ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት የስር ፍርድ ቤቶች የአፈጻጸም ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል፡፡

 

በዚህም መሰረት በ2ኛ ተጠሪ ማህበር ውስጥ በ1ኛ ተጠሪ ስም ተመዝግቦ የሚገኘው 162 የአክሲዮን ድርሻ በጋብቻ ውስጥ የተፈራ የአመልካች እና የ1ኛ ተጠሪ የጋራ ንብረት መሆኑ በስረ ነገሩ ፍርድ ተረጋግጧል፡፡ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት የአክሲዮን ድርሻው በሐራጅ ተሽጦ ክፍፍሉ በገንዘብ እንዲደረግ ውሳኔ ሊሰጥ የቻለው ከቀድሞ ተጋቢዎች መካከል አንዳቸው ለሌላኛው ድርሻውን ለቆ አንደኛው ወገን በማህበሩ  አባልነት መቀጠል የሚችል ከመሆኑ ውጪ ሁለቱን ወገኖች በአንድነት በማህበሩ ውስጥ የማይፈልጋቸው መሆኑን ገልጾ 2ኛ ተጠሪ ማህበር አስተያየት አቅርቦአል በማለት ነው፡፡አመልካች ከስር ጀምረው የሚከራከሩት ደግሞ አክሲዮኖቹ በዓይነት ሊካፋፈሉ የሚችሉ በመሆኑ ሕጻናት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጭምር እንዲረዳቸው የአክሲዮኖቹ ክፍፍል በዓይነት እንዲደረግ በመጠየቅ ነው፡፡በመሰረቱ የጋብቻ መፍረስን ተከትሎ የጋራ ሀብት እንዲከፋፈል የሚደረገው እያንዳንዱ ተጋቢ ከጋራ ሀብቱ የተወሰነ ንብረት እንዲደርሰው በማድረግ ስለመሆኑ እና ክፍፍሉ በሽያጭ ሊደረግ የሚችለው ንብረቱ ለክፍፍል የማያመች ወይም ለማከፋፈል የማይቻል ሆኖ ንብረቱ ከሁለት ለአንዳቸው እንዲሰጥ ባልና ሚስቱ ሳይስማሙ በቀሩ ጊዜ  ስለመሆኑ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በአንቀጽ 91 እና 92 ስር በዝርዝር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

 

በተያዘው ጉዳይ 2ኛ ተጠሪ ማህበር ከአመልካች እና ከ1ኛ ተጠሪ መካከል አንዳቸውን እንጂ ሁለቱን በማህበሩ ውስጥ አልፈልጋቸውም ከማለት በቀር አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ አክሲዮኖቹን በየድርሻቸው በዓይነት በመከፋፈልየማህበሩ አባላት መሆን የማይችሉበት ሕጋዊ ምክንያት ስለመኖሩ በስር ፍርድ ቤት ያቀረበው ክርክር እና ማስረጃ የለም፡፡በሰበር ደረጃም ቢሆን አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ አክሲዮኖቹን በዓይነት ተከፋፍለው በአባልነት ይቀጥሉ መባሉ በማህበሩ ውስጥ ብርቱ ጭቅጭቅን እና አለመግባባትን የሚያስከትል ነው ከማለት ውጪ የዚህ ዓይነት ሁኔታ ሊከሰት ስለሚችልበት ምክንያት ያቀረበው አሳማኝ መከራከሪያ የለም፡፡ የአክሲዮኖቹ በዓይነት የመከፋፈል ጉዳይ የሚመለከተው በመሰረቱ አመልካችን እና 1ኛ ተጠሪን እንጂ 2ኛ ተጠሪን ባለመሆኑ አክሲዮኖቹ ሊከፋፈሉ የሚገባቸው በሽያጭ ነው በማለት 2ኛ ተጠሪ መቃወሚያ አቅርቦ ለመከራከር የሚያስችል መብት እና ጥቅም አለው ለማለትም የሚቻል አይደለም፡፡

 

ሲጠቃለል በ2ኛ ተጠሪ ማህበር ውስጥ በ1ኛ ተጠሪ ስም ተመዝግቦ የሚገኘው 162 የአክሲዮን ድርሻ በጋብቻ ውስጥ የተፈራ የአመልካች እና የ1ኛ ተጠሪ የጋራ ንብረት መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ የአክሲዮን ድርሻውን አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ በዓይነት እንዲከፋፈሉ ለመወሰን የሚከለክል ሕጋዊ ምክንያት ባልቀረበበት ሁኔታ 2ኛ ተጠሪ ማህበር የሰጠውን አስተያየት   ብቻ


መሰረት በማድረግ የአክሲዮን ድርሻው ክፍፍል በሽያጭ አማካይነት እንዲፈጸም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተሰጥቶ በይግባኝ ሰሚው ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትዕዛዝ የጸናው የአፈጻጸም ትዕዛዝ የተሻሻለውን የቤተሰብ ሕግ በአንቀጽ 91 እና 92 ድንጋጌዎች መሰረት ያላደረገ እና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

 

 ው ሳ ኔ

 

1. በ2ኛ ተጠሪ ማህበር ውስጥ በ1ኛ ተጠሪ ስም ተመዝግበው የሚገኙት 162 የአክሲዮኖች ለአመልካች እና ለ1ኛ ተጠሪ ሊከፋፈል የሚገባው በሐራጅ ሽያጭ ነው በሚል በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 206322 በ25/07/2006 ዓ.ም. ተሰጥቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 150907 በ30/08/2006 ዓ.ም. በትዕዛዝ የጸናው የአፈጻጸም ትዕዛዝ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2. በ2ኛ ተጠሪ ማህበር ውስጥ በ1ኛ ተጠሪ ስም ተመዝግበው የሚገኙት 162 አክሲዮኖች በዓይነት ሊከፋፈሉ የማይችሉበት ሕጋዊ ምክንያት ባለመኖሩ እነዚህን  አክሲዮኖች አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በአንቀጽ 91(1) ድንጋጌ መሰረት እያንዳንዳቸው 81 አክሲዮኖችን በዓይነት ሊከፋፈሉ ይገባል በማለት ወስነናል፡፡

3. የዚህ ውሳኔ ግልባጭ በውሳኔው መሰረት እንዲያስፈጽም ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ እንዲያውቀው ደግሞ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይላክ፡፡

4.  የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

5.  ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

 

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::