95680 Oromia family law/ common property/ private property

በኦሮሚያ የቤተሰብ ህግ መሠረት ባልና ሚስቱ በየግል ያገኟቸውን ንብረትም ሆነ ገንዘብ በግል ይዘው መቀጠል እንደሚችሉ  ሲደነገግ ይህ የግል የተባለው ንብረት የግል ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው የግል ይባልልኝ ተብሎ በፍ/ቤት ሲፀድቅ ስለመሆኑ፣

የኦሮሚያ ክልል የቤተሰብ ህግ ቁ.69/1995 አንቀፅ 741ዐ፣አንቀፅ 74/2

የሰ/መ/ቁ. 95680

 

መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- አልማው ወሌ

 

ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ ተኽሊት ይመሰል

አመልካች፡- ወ/ሮ የሺ ተሾመ ተጠሪ፡- አቶ መስፍን ኃይሉ

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥታል፡፡

 

 ፍ ር ድ

 

ይህ ጉዳይ የተጀመረው በኦሮሚያ ክልል የሎሜ ወረዳ ፍ/ቤት ሲሆን የአሁን አመልካች ከሣሽ ሲሆኑ የአሁን ተጠሪ ተከሣሽ ነበሩ አመልካች ባቀረቡት ክስ፡- ከተጠሪ ጋር የነበረው ጋብቻ የፈረሰ መሆኑን በመግለፅ በጋብቻ ውስጥ የተፈራ የጋራ ንብረት ያካፍለኝ በማለት በኤጄሬ ከተማ የሚገኝ በ198 ካ.ሜ.ላይ ያረፈ ቤትና ኩሺና፣ ዲናሞ ብቻውንና የወፍጮ ዲናሞ በንግድ ባንክ ያለ ገንዘብ በ369 ካ.ሜ. ላይ 90 ቆርቆሮ የተሠራ ቤት የሞተር ቤት 2 ክፍል በልማት የተከፈለ 80,000 ብር እና የተሸጠ የወፍጮ እና ጀኔሬተር ገንዘብ(13,000) ያካፍለኝ ብላለች በ198 ካ.ሜ.ላይ  ያረፈው ቤት በ1982 ከጋብቻ በፊት (በ17/02/82) የገዛሁትን ነው፡፡በ369 ካ.ሜ. ላይ ያለው ቤት 85 ቆርቆሮ እንጂ 90 አይደለም በመንገድ ሥራ የመኖሪያ ቤት ፈርሶ የተከፈለኝ 54,000 ባገኘሁት ካሣ ከአቶ መለሰ ጫካ ከተባለ ሰው ገንዘብ ተበድሬ የሰራሁት የግል ንብረት ነው፡፡ የካሣ ገንዘቡም ብር 80,000 ሣይሆን ብር 54,000 ነው፡፡ በናፍጣ የሚሠራ ሁለት ወፍጮና ጀኔሬተር 13,000 የተገዛ ቢሆንም 11,495.55 ተጨምሮበት በ24,495.85 ወደ ኤሌክትሪክ ተቀይሮ በሥራ ላይ የሚገኝ እንጂ በጥሬ ገንዘብ የለም፡፡ በተጨማሪም የጋራችን የሆነ የላሜራ ሱቅ ሸቀጥ ግምቱ 60,000 በከሣሽ እጅ ይገኛል፡፡ የመብራት ሀይል ዕዳ (የወፍጮ) 21,000 የጋራችን ነው በመጨረሻም በ369 ካ.ሜ. ቦታ ላይ ያለውም ቤት የግሌ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩን ያየው ፍ/ቤትም በግራ ቀኙ የተማመኑትን ንብረት በማለፍ አከራካሪ የሆኑትን ፍሬ ነገሮች በመለየት ንብረቶችን አስመልክቶ መስተዳደሩና የአካባቢ ሽማግሌዎች  እንዲያጣሩ በማድረግ ተከሣሽ (ተጠሪ) ተበደርኩ የሚለውን 60,000 አመልካች የማታውቀውና ያልተረጋገጠ ነው፡፡ባንክ ቤት አለ የተባለው ገንዘብ በአመልካች በኩል እንዲያረጋግጡ አልተደረገም በማለት  ውድቅ ካደረገው በኃላ የተቀሩትን ንብረቶች በቀረበው ማስረጃ በማረጋገጥ እኩል እንዲካፈሉ ሲል በተለይ በ198 ካ.ሜ. ቦታ ላይ ያለው ቤት የተጠሪ በግል ገንዘባቸው ገዝተው በ369 ቦታ ላይ ቤት መስራታቸውን የካሣ ገንዘብ 54,000 ይክፈሉ ሲል በ369 ላይ ያረፈውን ቤት እኩል ይካፈሉ


በማለት ወስኗል፡፡የይግባኙም ፍ/ቤት የግራ ቀኙን በማከራከር አጣርቶ ሲያፀናው በክልሉ ሰበርም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.337 ተሰርዟል፡፡

 

የአመልካች አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሣኔ ለማሳረም ነው፡፡

 

አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ በሥር ፍ/ቤት ከተጠሪ ጋር እንደባልና ሚስት ለ23 አመት ስንኖር ያፈራነውን ወፍጮ ከነ ቤቱ መኖሪያ ቤት አንድ ኩሽና አንድ ሽንት ቤት በ198 ካ.ሜ. ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ጠጅ ቤት ፈርሶ መሬቱም ሲወሰድ የተከፈለውን ካሣ ገንዘብ 54,000 ብር በ369 ካ.ሜ ቦታ ላይ የተሰራውን ቤት አመልካች 54,000 ለተጠሪ ከፍላ ቤቱን በጋራ ትካፈል መባሉ መሠረታዊ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባዋል ሲሉ አመልካች ጠይቀዋል፡፡

 

በዚህም መሠረት ይህ ችሎትም አመልካች 54,000 ብር ከፍላ በ369 ካ.ሜ.ቦታ ላይ ያረፈውን ቤት ትካፈል መባሉና በ198 ካ.ሜ ቦታ ላይ ያለው ቤት በላዩ ላይ የተተከለው ወፍጮ ቤት በግል የተሰራነው?ወይስ በጋብቻ ውስጥ? የሚለው ወደ ድርጅትነት የተለወጠው መቼ ነው?የሚለው እና ለመብራት ሀይል የተከፈለው 24,000 መቼ ነው?የሚሉት ነጥቦች እንዲጣሩ በጭብጥነት በመያዝ የግራ ቀኙ በቀረበው አቤቱታ ላይ መልስና የመልስ መልስ በመቀባበል እንዲከራከሩ አድርጓል፡፡

 

በመሆኑም የግራ ቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሣኔ እና ከህጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል፡፡

 

የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሰውን ይመስላል፡፡እኛም እንዳየነው አመልካች ጋብቻ መፍረሱን ጠቅሰው የጋራ ንብረታችን ነውና ልንካፈል ይገባል የሚሉትን የንብረት ዝርዝር በማቅረብ የጠየቁ ሲሆን የሥር ወረዳ ፍ/ቤትም በዝርዝር የቀረበለትንና የዳኝነት ጥያቄ የታመነውንና ተቃውሞ በተጠሪ የቀረበበትን ነጥብ በመለየት በማስረጃ አጣርቶ ውሣኔ አሳርፎበታል፡፡

 

እኛም በማስረጃ ረገድ ተጣርቶ ውሳኔ ያገኘውን በመቀበል በጭብጥነት በተያዙት ነጥቦችን ስናየው ተጠሪ በጋብቻ ውስጥ ከአመልካች ጋር በነበረበት ጊዜ የነበረው ወፍጮ አብረው ሲጠቀሙበት የነበረ የመብራት ኃይል የአገልግሎት ዋጋ ብር 24.000.00 መክፈላቸውን አረጋግጠው የጋራ ዕዳቸው መሆኑንና በድርሻቸው አመልካች እንዲከፍሉ ጠይቋል፡፡ የሥር ፍ/ቤትም ግራ ቀኙ በጋብቻ ውስጥ እያሉ የተጠቀሙበት መሆኑን በማረጋገጥ አመልካች ቤት በነበሩበት ወቅት የቆጠረ የመብራት ዋጋ በመሆኑ ዕዳውን ሊከፈሉ ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ እንግዲህ አመልካች ከወፍጮ ገቢ ተጠቃሚ አይደለሁም ሲሉ ባልተከራከሩበት የዕዳው ተጋሪ መሆን የለብኝም በማለት ያቀረቡት ክርክር የሕግ መሠረት የለውም በመሆኑም ይኽኛውም የውሳኔ ክፍል ባግባቡ ተጣርቶ የተወሰነ በመሆኑ ተቀብለነዋል፡፡

 

ሁለተኛውን አከራካሪውን በ198 ካ.ሜ ይዞታ አስመልክቶ ተጠሪ ከጋብቻ በፊት ገዝቼ እያለሁ በመንገድ ምክንያት ፈርሶ ያገኜሁትን ካሳ ገንዘብ 54.000 ብር በመያዝ ከአመልካች ጋር ተጋብተው በ369 ካ.ሜ ቦታ ላይ የሰፈረውን ቦታ ሰራን ፣ ስለዚህ ንብረቶቹ የግል ንብረት ነው በማለት ሲከራከሩ አመልካች በበኩላቸው ይዞታው የተገዛውና የተሰሩት አንድ ክፍል ቤት ብቻ መሆኑንና ይህ ፈርሶ ተስፋፍቶ በ369 ካ.ሜ ቤት ተሰርቶ የጠጅ ቤት ድርጅት ስንጠቀምበት የነበረና የፈረሰ በመሆኑ ከ23 አመት በኃላ ተጠሪ የግሌ ነው ሲል መከራከሪያ ሊያደርጐት አይገባም ይላሉና እኛም ተጠሪ ተቀበልኩ የሚሉትን ገንዘብ ከጋብቻ በፊት ያገኜሁት ነው ቢሉም ከአመልካች ጋር የ369 ካ.ሜ ይዞታ ላይ ቤት በመስራት አስፋፍቶ ለረዥም ዓመታት መኖራቸው


ያላከራከረ ነው፡፡ እንግዲህ በእነዚህ ባለፉት አመታት በግራ ቀኙ አስተዋጽኦ ቤቱ ከተገነባ በቀጣይነት የሚገኙት ገቢዎች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ንብረቶች መቀላቀላቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ ተጠሪ ተጠቃሹ ገንዘብ የግሌ ነው የሚሉበት ምክንያት ከጋብቻ በፊት ያገኘሁትና በዚሁ ገንዘብ በ369 ካ.ሜ ይዞታ ላይ ቤት ሰርተናል በማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የኦሮሚያ የቤተሰብ ህግ ቁ.69/1995 አንቀፅ 74/1/ መሠረት ባልና ሚስቱ በየግል ያገኟቸውን ንብረትም ሆነ ገንዘብ በግል ይዘው መቀጠል እንደሚችሉ ሲደነገግ ይህ የግል የተባለው ንብረት የግል ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው በተጠቃሹ ህግ አንቀፅ 74/2/ ስር የግል ይባልልኝ ተብሎ በፍ/ቤት ሲፀድቅ መሆኑን በግልጽ ደንግጐታል፡፡ ይህ ደግሞ በህጉ እንደዋነኛ መስፈርት የተቀመጠ ጉዳይ ነዉ፡፡ በተያዘው ጉዳይም ተጠሪ በዚህ መልኩ ተጠቃሹን ንብረት ወይም ገንዘብ አስመዝግቤያለሁ ሲሉ ያቀረቡት ክርክር አልነበረም፡፡ ይህ ሆኖ ሣለ በስር ፍ/ቤቶች አመልካች 54,ዐዐዐ ብር በመክፈል ቤቱን ይካፈሉ የሚለውን የውሣኔ ክፍል ባለመቀበል፡፡ የተቀሩትን የውሣኔ ክፍሎች ባልነካ መልኩ በ369 ይዞታ ላይ ያረፈውን ቤት 54,ዐዐዐ አመልካች ይክፈሉና ቤቱን ይካፈሉ መባሉና በየደረጃው ባሉት ፍ/ቤቶች ያለመታረሙ መሠረታዊ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተናል፡፡ በመሆኑም ተከታዩን ውሣኔ ተሰጥቷል፡፡

 ው ሣ ኔ

1.  የሉሜ ወረዳ ፍ/ቤት በመ.ቁ 34054 በቀን 23/07/05 የከፍተኛው ፍ/ቤት  በመ.ቁ

33974 በቀን 06/12/2005 እና የክልሉ ሰበር ሰሚ በመ.ቁ 173245 በቀን

28/02/2006   የሰጡት ውሣኔ ተሻሽሎ ፀንቷል፡፡

2. አመልካች አከራካሪውን ብር 54,000.00 ለተጠሪ ሣይከፍሉ የጋራ ነው የተባለውን ቤት ሊካፈሉ ይገባል ብለናል፡፡

 

3. የወጪ ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ውሣኔ በማግኘቱ ተዘግቷል፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::

 

 

እ/ኢ