102662 family law/ divorce/ common property/ period of limitation

ጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል ሊባልባቸው ስለሚችሉባቸው ሁኔታዎች ጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል ተብሎ ከሚታሰብበት ጊዜ አንስቶ በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ የንብረት ክፍፍል ጥያቄ ካልቀረበ በይርጋ የሚታገድ ስለመሆኑ

 

የሰ/መ/ቁ.102662

የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ/ም

ዳኞች፡-አልማው ወሌ ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

አመልካች፡- ወ/ሮ አልማዝ ለሼ- ጠበቃ ኤርሚያስ ደስታ ቀረቡ፡፡ ተጠሪ፡- አቶ በቀለ በላቸው- ወኪል  ትርፍነሽ በቀለ ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

 ፍ ር ድ

 

ጉዳዩ ጋብቻ ፈርሷል ሊባል የሚችልበትን አግባብ የሚመለከት ነው፡፡ጉዳዩ የተጀመረው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የደብረብርሃን ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን ክሱን ያቀረቡት የአሁኑ አመልካች ናቸው፡፡ የክሱ ይዘትም፡- ከአሁኑ ተጠሪ ጋር በአገር ባህል የጋብቻ አፈጻጸም ስርዓት ጋብቻ ፈጽመው ለአርባ አመታት ያህል አብረው መኖራቸውን፣ ይሁን እንጂ ከመስከረም 2006 ዓ/ም ጀምሮ ሊስማሙ ባለመቻላቸው በመካከላቸው ሰላም እንደሌለ ገልፅው ጋብቻው ፈርሶ የጋራ ንብረት እንዲካፈሉ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪ ለክሱ በሰጡት መልስም ከአመልካች ጋር ባልና ሚስት የነበሩ መሆኑን ሳይክዱ አመልካች ከአስራ ዘጠኝ አመታት በፊት ቤቱን ጥለው መሄዳቸውንና ተለያይተው የሚኖሩ መሆኑን ጠቅሰው ክሱ በይርጋ ሊታገድ ይገባል  በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያስቀደሙ ሲሆን በፍሬ ነገር ረገድ ደግሞ ከአመልካች ጋር ያፈሩት የጋራ ንብረት የሌለ መሆኑን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

 

የግራ ቀኙ ክርክር በዚህ መልኩ የቀረበለት የሥር ፍ/ቤትም ጉዳዩን መርምሮ በአመልካች እና በተጠሪ መካከል የነበረው ጋብቻ ከአስር አመታት በፊት ፈርሷል የሚል ድምዳሜ ደርሶ የአመልካች ክሱ በይርጋ የታገደ ነው በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡ በዚህ ብይን የአሁኗ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለሰሜን ሸዋ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡


ከዚህም በኋላ አመልካች የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበውም በጉዳዩ ላይ በተሠጠው ብይን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ተብሎ መዝገቡ ተዘግቶባቸዋል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ሲሆን ይህ ችሎት የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ተጠሪን በመጥራት ግራ ቀኙን በጽሑፍ አከራክሯል፡፡እንዲሁም የወረዳው ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ እንዲመጣ አድርጓል፡፡

 

በአጠቃላይ የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን ምላሽ ማግኘት የሚገባው የጉዳዩ ጭብጥ በተጠሪና በአመልካች መካከል ጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል ተብሎ በበታች ፍርድ ቤቶች መወሰኑ ተገቢነት አለውን? የሚለውነው፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የወረዳው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ምስክሮች ሰምቶ በአመልካችናበተጠሪ መካከልየነበረውጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል በማለት በአመልካች በኩል የቀረበውን ክርክር አልተቀበለውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ወደዚህ ድምዳሜ የደረሰው በአመልካችና በተጠሪ መካከል የነበረው የጋብቻ ግንኙነታቸው ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ ተቋርጦ ግራ ቀኙ ለየብቻ መኖር መጀመራቸው ተረጋግጧል በሚል አቢይ ምክንያት ነው፡፡ ይህ የወረዳው ፍርድ ቤት የፍሬ ነገር ማጣራትና የማስረጃ ምዘና ድምዳሜ በዚህ ረገድ ተመሳሳይ የሆነ ስልጣን ባለው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ አመልካች በዚህ ችሎት አጥብቀው የሚከራከሩት ግራ ቀኙ ሌላ ትዳር መስርተው የራሳቸውን ሕይወት የማይኖሩ መሆኑን፣ አልፎ አልፎ በጤና ምክንያት አመልካች ለፀበል ወደ ሌላ ቦታ ከመሄዳቸው ውጪ አመልካችና ተጠሪ ያልተለያዩና እስከ መስከረም 2006 ዓ/ም ድረስ አንድ ላይ የሚኖሩ መሆኑን ዘርዝረው ለጉዳዩ አግባብነት የሌለው አስገዳጅ ውሳኔ ተጠቅሶ መወሰኑ ያላግባብ ነው በሚል ነው፡፡ እኛም ጉዳዩን ይህ ሰበር ችሎት በመ/ቁ. 14290፣ 20983፣ 31891፣ 67924 እና በሌሎች በርካታ መዛግብት ከሰጣቸው አስገዳጅ ውሳኔዎች ጋር አገናዝበን ተመልክተናል፡፡

በመሰረቱ የወረዳው ፍርድ ቤት ለውሳኔው መሰረት ያደረገውና ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 31891 ሌሎች ከላይ በተጠቀሱት መዛግብት በሰጣቸው አስገዳጅ ውሳኔዎች በባልና ሚስት መካከል ያለ ጋብቻ በፍ/ቤት በተሰጠ የፍቺ ውሳኔ ፈርሷል ባይባልም የተጋቢዎች ተለያይቶ ለረጅም ጊዜ መኖር፣ በዚህም ጊዜ ሌላ ትዳር መሥርቶ መገኘት የቀድሞው ጋብቻ በሕጋዊ መንገድ ተቋርጧል ሊያስብል ይችላል በማለት በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(1) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህም ውሳኔ ይዘትና መንፈስ መረዳት የሚቻለው የጋብቻ መፍረስ በተጋቢዎች የረዥም ጊዜ መለያየት ሊከናወን የሚችል መሆኑና ፍርድ ቤቱም በዚህ አግባብ የፈረሰውን ጋብቻ እንደገና እንዲፈርስ ውሳኔ የሚሰጥበት አግባብ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ በሰ/መ/ቁጥር 67924 የተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ደግሞ በቤተሰብ ሕጉ አግባብ የመተጋገዝና የመተባበር ግዴታቸውን


ሲወጡና የነበሩና ያልተለያዩ መሆኑ ከተረጋገጠ ጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል ለማለት የማይቻል መሆኑን በመዝገቡ ከተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች በመነሳት የተወሰነ ነው፡፡

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካችና ተጠሪ በሕጉ አግባብ ጋብቻ መሰርተው ልጆችን ከወለዱ በኋላ በ1987 ዓ/ም ጀምሮ በአካል ተለያይተው ለአስራ ዘጠኝ አመታት ያህል ሳይገናኙ የኖሩ መሆኑን ከግራ ቀኙ ምስክሮች ቃል የተረጋገጠ መሆኑን የበታች ፍርድ ቤቶች ደምድመዋል፡፡ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀረበው የወረዳው ፍርድ ቤት ዋና መዝገብም  የግራ ቀኙ ምስክሮች የመሰከሩት የፍሬ ነገር ነጥብ በይዘቱ የበታች ፍርድ ቤቶች ከደመደሙት ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ተገንዝቦአል፡፡ በመሆኑም አመልካች ከተጠሪ ጋር እስከ መስከረም 2006 ዓ/ም ድረስ አልተለያየንም በማለት የሚያቀርቡት ቅሬታ በስር ፍርደ ቤት ዋና መዝገብ ውስጥ በምስክሮች ከተነገረው የምስክርነት ቃል ይዘትና ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ከደረሱበት ድምዳሜ ውጪ በመሆኑ ተቀባይነት የሚሰጠው ሁኖ አልተገኘም፡፡ በዚህ ረገድ አመልካች ያቀረቡት ቅሬታ ለዚህ ችሎት በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች አግባብ የተሰጠውን ስልጣንም ያላገናዘበ ሁኖ አግኝተናል፡፡

በመሰረቱ ጋብቻ በተጋቢዎች መካከል የመተጋገዝ፣ የመከባበርና መደጋገፍ እንዲሁም አብሮ የመኖር ግዴታን የሚጥል መሆኑን ከክልሉ የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 60 እና 61 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚሁ  አኳያ በተጠሪና በአመልካች መካከል የነበረው ጋብቻ ይህ ሰበር ችሎት አስቀድሞ በተመሳሳይ ጉዳይ ከሰጠው ውሳኔ አንጻር ተቋርጧል? ወይንስ አልተቋረጠም? የሚለውን ለመወሰን ከፍ ብሎ በአመልካችና በተጠሪ መካከል በጋብቻ ውስጥ በግራ ቀኙ የሚጠበቁ ግዴታዎች ባግባቡ ሲተገበሩ ያልነበሩና እነዚህን ግዴታዎችን ለመወጣት ደግሞ በአመልካች በኩል ያጋጠመው ሁኔታ በሕጉ የተጣሉባቸውን ግዴታቸውን ለመወጣት የማያስችል የነበረ መሆኑ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ አመልካች ከተጠሪ ጋር አልተለያየንም፣ በጤና ችግር ምክንያት አልፎ አልፎ ለፀበል ሌላ ቦታ እሄድ ነበር በማለት የሚያቀርቡት ክርክር በክርክሩ ሂደት በማስረጃ የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮችን መሰረት አድርጎ ያልቀረበ ሁኖ አግንተነዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተያዘው መዝገብና ይህ ሰበር ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠባቸው መዛግብት የያዟቸው መሰረታዊ ፍሬ ነገሮች ከዚህ መዝገብ ከተረጋገጡት እውነታዎች ሙሉ በሙሉ የተመሳሳይነት ያላቸው ሁኖ እያለ አመልካችም ሆነ ተጠሪ ሌላ ትዳር መስርተው ሕይወታቸውን በመምራት ላይ አይገኙም በማለት በሰ/መ/ቁጥር 31891 የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በመተውና ግንኙነቱ ያልተቋረጠ  ተጋቢዎችን መሰረት ተደርጎ በመ/ቁጥር 67924 የተሰጠውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ አመልካች መከራከራቸው ከአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2 (1) አተገባበር ጋር የሚጋጭ ሁኖ አግኝተናል፡፡ ስለሆነም የአመልካችና የተጠሪ ግንኙነት ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ በሁኔታ የፈረሰ


በመሆኑ እና ለጉዳዩ አግባብነት በላቸው ከላይ በተጠቀሱት መዛግብት በተሰጠው ትርጉም መሰረት የጋራ ንብረት ጥያቄም በአስር አመት ያልቀረበ በመሆኑ የተጠሪ ክስ በይርጋ የታገደ ነው ተብሎ ብይን መሰጠቱ የሚነቀፍበትን የሕግ ምክንያት አላገኘንም፡፡ ሲጠቃለልም በጉዳዪ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት ሁኖ ስላላገኘነው ተከታዩን ወስነናል፡፡

 ው ሳ ኔ

1. የደብረብርሃን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር  0108191/06  በ22/08/2006 ተሠጥቶ በሰሜን ሸዋ መስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 0114418 በ30/08/2006 ዓ/ም፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 030- 5041 ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

2. በአመልካችና በተጠሪ መካከል በአገር ባህል የጋብቻ አፈፃጸም ስርዓት ተመስርቶ የነበረው ጋብቻ ለረዥም ጊዜ ተለያይቶ በመኖር ምክንያት ፈርሷል በማለት ወስነናል፡፡

3.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

 ት ዕ ዛ ዝ

ከደብረብርሃን ከተማ ወረዳ ፍርደ ቤት የመጣ መዝገብ ቁጥር 0108191/06 በመጣበት አኳሀን ይመለስ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

ወ/ከ