Federal Court Case Tracker

 • በኦሮሚያ የቤተሰብ ህግ መሠረት ባልና ሚስቱ በየግል ያገኟቸውን ንብረትም ሆነ ገንዘብ በግል ይዘው መቀጠል እንደሚችሉ  ሲደነገግ ይህ የግል የተባለው ንብረት የግል ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው የግል ይባልልኝ ተብሎ በፍ/ቤት ሲፀድቅ ስለመሆኑ፣

  የኦሮሚያ ክልል የቤተሰብ ህግ ቁ.69/1995 አንቀፅ 741ዐ፣አንቀፅ 74/2

  የሰ/መ/ቁ. 95680

   

  መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ/ም

   

  ዳኞች፡-አልማው ወሌ

   

  ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ ተኽሊት ይመሰል

  አመልካች፡- ወ/ሮ የሺ ተሾመ ተጠሪ፡- አቶ መስፍን ኃይሉ

  መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥታል፡፡

   

   ፍ ር ድ

   

  ይህ ጉዳይ የተጀመረው በኦሮሚያ ክልል የሎሜ ወረዳ ፍ/ቤት ሲሆን የአሁን አመልካች ከሣሽ ሲሆኑ የአሁን ተጠሪ ተከሣሽ ነበሩ አመልካች ባቀረቡት ክስ፡- ከተጠሪ ጋር የነበረው ጋብቻ የፈረሰ መሆኑን በመግለፅ በጋብቻ ውስጥ የተፈራ የጋራ ንብረት ያካፍለኝ በማለት በኤጄሬ ከተማ የሚገኝ በ198 ካ.ሜ.ላይ ያረፈ ቤትና ኩሺና፣ ዲናሞ ብቻውንና የወፍጮ ዲናሞ በንግድ ባንክ ያለ ገንዘብ በ369 ካ.ሜ. ላይ 90 ቆርቆሮ የተሠራ ቤት የሞተር ቤት 2 ክፍል በልማት የተከፈለ 80,000 ብር እና የተሸጠ የወፍጮ እና ጀኔሬተር ገንዘብ(13,000) ያካፍለኝ ብላለች በ198 ካ.ሜ.ላይ  ያረፈው ቤት በ1982 ከጋብቻ በፊት (በ17/02/82) የገዛሁትን ነው፡፡በ369 ካ.ሜ. ላይ ያለው ቤት 85 ቆርቆሮ እንጂ 90 አይደለም በመንገድ ሥራ የመኖሪያ ቤት ፈርሶ የተከፈለኝ 54,000 ባገኘሁት ካሣ ከአቶ መለሰ ጫካ ከተባለ ሰው ገንዘብ ተበድሬ የሰራሁት የግል ንብረት ነው፡፡ የካሣ ገንዘቡም ብር 80,000 ሣይሆን ብር 54,000 ነው፡፡ በናፍጣ የሚሠራ ሁለት ወፍጮና ጀኔሬተር 13,000 የተገዛ ቢሆንም 11,495.55 ተጨምሮበት በ24,495.85 ወደ ኤሌክትሪክ ተቀይሮ በሥራ ላይ የሚገኝ እንጂ በጥሬ ገንዘብ የለም፡፡ በተጨማሪም የጋራችን የሆነ የላሜራ ሱቅ ሸቀጥ ግምቱ 60,000 በከሣሽ እጅ ይገኛል፡፡ የመብራት ሀይል ዕዳ (የወፍጮ) 21,000 የጋራችን ነው በመጨረሻም በ369 ካ.ሜ. ቦታ ላይ ያለውም ቤት የግሌ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩን ያየው ፍ/ቤትም በግራ ቀኙ የተማመኑትን ንብረት በማለፍ አከራካሪ የሆኑትን ፍሬ ነገሮች በመለየት ንብረቶችን አስመልክቶ መስተዳደሩና የአካባቢ ሽማግሌዎች  እንዲያጣሩ በማድረግ ተከሣሽ (ተጠሪ) ተበደርኩ የሚለውን 60,000 አመልካች የማታውቀውና ያልተረጋገጠ ነው፡፡ባንክ ቤት አለ የተባለው ገንዘብ በአመልካች በኩል እንዲያረጋግጡ አልተደረገም በማለት  ውድቅ ካደረገው በኃላ የተቀሩትን ንብረቶች በቀረበው ማስረጃ በማረጋገጥ እኩል እንዲካፈሉ ሲል በተለይ በ198 ካ.ሜ. ቦታ ላይ ያለው ቤት የተጠሪ በግል ገንዘባቸው ገዝተው በ369 ቦታ ላይ ቤት መስራታቸውን የካሣ ገንዘብ 54,000 ይክፈሉ ሲል በ369 ላይ ያረፈውን ቤት እኩል ይካፈሉ


  በማለት ወስኗል፡፡የይግባኙም ፍ/ቤት የግራ ቀኙን በማከራከር አጣርቶ ሲያፀናው በክልሉ ሰበርም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.337 ተሰርዟል፡፡

   

  የአመልካች አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሣኔ ለማሳረም ነው፡፡

   

  አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ በሥር ፍ/ቤት ከተጠሪ ጋር እንደባልና ሚስት ለ23 አመት ስንኖር ያፈራነውን ወፍጮ ከነ ቤቱ መኖሪያ ቤት አንድ ኩሽና አንድ ሽንት ቤት በ198 ካ.ሜ. ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ጠጅ ቤት ፈርሶ መሬቱም ሲወሰድ የተከፈለውን ካሣ ገንዘብ 54,000 ብር በ369 ካ.ሜ ቦታ ላይ የተሰራውን ቤት አመልካች 54,000 ለተጠሪ ከፍላ ቤቱን በጋራ ትካፈል መባሉ መሠረታዊ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባዋል ሲሉ አመልካች ጠይቀዋል፡፡

   

  በዚህም መሠረት ይህ ችሎትም አመልካች 54,000 ብር ከፍላ በ369 ካ.ሜ.ቦታ ላይ ያረፈውን ቤት ትካፈል መባሉና በ198 ካ.ሜ ቦታ ላይ ያለው ቤት በላዩ ላይ የተተከለው ወፍጮ ቤት በግል የተሰራነው?ወይስ በጋብቻ ውስጥ? የሚለው ወደ ድርጅትነት የተለወጠው መቼ ነው?የሚለው እና ለመብራት ሀይል የተከፈለው 24,000 መቼ ነው?የሚሉት ነጥቦች እንዲጣሩ በጭብጥነት በመያዝ የግራ ቀኙ በቀረበው አቤቱታ ላይ መልስና የመልስ መልስ በመቀባበል እንዲከራከሩ አድርጓል፡፡

   

  በመሆኑም የግራ ቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሣኔ እና ከህጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል፡፡

   

  የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሰውን ይመስላል፡፡እኛም እንዳየነው አመልካች ጋብቻ መፍረሱን ጠቅሰው የጋራ ንብረታችን ነውና ልንካፈል ይገባል የሚሉትን የንብረት ዝርዝር በማቅረብ የጠየቁ ሲሆን የሥር ወረዳ ፍ/ቤትም በዝርዝር የቀረበለትንና የዳኝነት ጥያቄ የታመነውንና ተቃውሞ በተጠሪ የቀረበበትን ነጥብ በመለየት በማስረጃ አጣርቶ ውሣኔ አሳርፎበታል፡፡

   

  እኛም በማስረጃ ረገድ ተጣርቶ ውሳኔ ያገኘውን በመቀበል በጭብጥነት በተያዙት ነጥቦችን ስናየው ተጠሪ በጋብቻ ውስጥ ከአመልካች ጋር በነበረበት ጊዜ የነበረው ወፍጮ አብረው ሲጠቀሙበት የነበረ የመብራት ኃይል የአገልግሎት ዋጋ ብር 24.000.00 መክፈላቸውን አረጋግጠው የጋራ ዕዳቸው መሆኑንና በድርሻቸው አመልካች እንዲከፍሉ ጠይቋል፡፡ የሥር ፍ/ቤትም ግራ ቀኙበጋብቻ ውስጥ እያሉ የተጠቀሙበት መሆኑን በማረጋገጥ አመልካች ቤት በነበሩበት ወቅት የቆጠረ የመብራት ዋጋ በመሆኑ ዕዳውን ሊከፈሉ ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ እንግዲህ አመልካች ከወፍጮ ገቢ ተጠቃሚ አይደለሁም ሲሉ ባልተከራከሩበት የዕዳው ተጋሪ መሆን የለብኝም በማለት ያቀረቡት ክርክር የሕግ መሠረት የለውም በመሆኑም ይኽኛውም የውሳኔ ክፍል ባግባቡ ተጣርቶ የተወሰነ በመሆኑ ተቀብለነዋል፡፡

   

  ሁለተኛውን አከራካሪውን በ198 ካ.ሜ ይዞታ አስመልክቶ ተጠሪ ከጋብቻ በፊት ገዝቼ እያለሁ በመንገድ ምክንያት ፈርሶ ያገኜሁትን ካሳ ገንዘብ 54.000 ብር በመያዝ ከአመልካች ጋር ተጋብተው በ369 ካ.ሜ ቦታ ላይ የሰፈረውን ቦታ ሰራን ፣ ስለዚህ ንብረቶቹ የግል ንብረት ነው በማለት ሲከራከሩ አመልካች በበኩላቸው ይዞታው የተገዛውና የተሰሩት አንድ ክፍል ቤት ብቻ መሆኑንና ይህ ፈርሶ ተስፋፍቶ በ369 ካ.ሜ ቤት ተሰርቶ የጠጅ ቤት ድርጅት ስንጠቀምበት የነበረና የፈረሰ በመሆኑ ከ23 አመት በኃላ ተጠሪ የግሌ ነው ሲል መከራከሪያ ሊያደርጐት አይገባም ይላሉና እኛም ተጠሪ ተቀበልኩ የሚሉትን ገንዘብ ከጋብቻ በፊት ያገኜሁት ነው ቢሉም ከአመልካች ጋር የ369 ካ.ሜ ይዞታ ላይ ቤት በመስራት አስፋፍቶ ለረዥም ዓመታት መኖራቸው


  ያላከራከረ ነው፡፡ እንግዲህ በእነዚህ ባለፉት አመታት በግራ ቀኙ አስተዋጽኦ ቤቱ ከተገነባ በቀጣይነት የሚገኙት ገቢዎች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ንብረቶች መቀላቀላቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ ተጠሪ ተጠቃሹ ገንዘብ የግሌ ነው የሚሉበት ምክንያት ከጋብቻ በፊት ያገኘሁትና በዚሁ ገንዘብ በ369 ካ.ሜ ይዞታ ላይ ቤት ሰርተናል በማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የኦሮሚያ የቤተሰብ ህግ ቁ.69/1995 አንቀፅ 74/1/ መሠረት ባልና ሚስቱ በየግል ያገኟቸውን ንብረትም ሆነ ገንዘብ በግል ይዘው መቀጠል እንደሚችሉ ሲደነገግ ይህ የግል የተባለው ንብረት የግል ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው በተጠቃሹ ህግ አንቀፅ 74/2/ ስር የግል ይባልልኝ ተብሎ በፍ/ቤት ሲፀድቅ መሆኑን በግልጽ ደንግጐታል፡፡ ይህ ደግሞ በህጉ እንደዋነኛ መስፈርት የተቀመጠ ጉዳይ ነዉ፡፡ በተያዘው ጉዳይም ተጠሪ በዚህ መልኩ ተጠቃሹን ንብረት ወይም ገንዘብ አስመዝግቤያለሁ ሲሉ ያቀረቡት ክርክር አልነበረም፡፡ ይህ ሆኖ ሣለ በስር ፍ/ቤቶች አመልካች 54,ዐዐዐ ብር በመክፈል ቤቱን ይካፈሉ የሚለውን የውሣኔ ክፍል ባለመቀበል፡፡ የተቀሩትን የውሣኔ ክፍሎች ባልነካ መልኩ በ369 ይዞታ ላይ ያረፈውን ቤት 54,ዐዐዐ አመልካች ይክፈሉና ቤቱን ይካፈሉ መባሉና በየደረጃው ባሉት ፍ/ቤቶች ያለመታረሙ መሠረታዊ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተናል፡፡ በመሆኑም ተከታዩን ውሣኔ ተሰጥቷል፡፡

   ው ሣ ኔ

  1.  የሉሜ ወረዳ ፍ/ቤት በመ.ቁ 34054 በቀን 23/07/05 የከፍተኛው ፍ/ቤት  በመ.ቁ

  33974 በቀን 06/12/2005 እና የክልሉ ሰበር ሰሚ በመ.ቁ 173245 በቀን

  28/02/2006  የሰጡት ውሣኔ ተሻሽሎ ፀንቷል፡፡

  2. አመልካች አከራካሪውን ብር 54,000.00 ለተጠሪ ሣይከፍሉ የጋራ ነው የተባለውን ቤት ሊካፈሉ ይገባል ብለናል፡፡

   

  3. የወጪ ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ውሣኔ በማግኘቱ ተዘግቷል፡፡

   

  የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት::

   

   

  እ/ኢ

 • Family law

  Irregular union

  Condition for existence of irregular union

  Federal Family Code art. 97, 98, 99 and 106(2)

  ጋብቻ ሳይኖር እንደባልና ሚስት ለሚኖሩ ሰዎች የሚፈለገው ማስረጃ ወንዱና ሴትየዋ የተጋቡ ሰዎችን ሁኔታ ሲያሳዩና ቤተዘመዶቻቸውና ማህበረሠቡ እንደተጋቢ ሰዎች የሚኖሩ ናቸው ብለው የሚገምቷቸው መሆን ያለባቸው ስለመሆኑ፣ 

  በአንድ ወንድና ሴት መካከል ለተወሰነ ጊዜ የፍቅር ግንኙነት መኖሩ ብቻ እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ናቸው ሊያስብል የማይችል ስለመሆኑ ፣

  አዋጅ ቁጥር 213/92 አንቀፅ 97፣98፣99 እና 106/2/

  96853

 • Family law

  Contract of marriage

  Interpretation of contract of marriage

  አንድ ወንድና ሴት ሲጋቡ በጋብቻ ውላቸው ንብረትን በተመለከተ ካደረጉት ስምምነት ላይ “ከወለደች የግል የለባትም” ፣ “ ሀብትሽ ሀብቴ ነው “ ተብሎ የተፈጸመው የውል ሀረግ ካለና ልጅ ከወለዱ ከጋብቻ በፊት የነበራቸውን የግል ንብረት የጋራ ለማድረግ እንደተስማሙ የሚቆጠር ስለመሆኑ፣

  98029

 • በገጠር መሬት ላይ የሚኖረው መብት የመጠቀም መብት ሲሆን ይህንን መብት ለ3ኛ ወገን /ለሌላ/ ሰው ለረጅም ጊዜ ሰጥቶ ተጠቃሚነቱ የተቋረጠበት ባለመብት መልሶ መጠየቅ የማይችል ስለመሆኑ፣ የኦሮሚያ ክልለ የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1997 አንቀፅ 9(5)

   

  የሰ/መ/ቁ. 113973

  ቀን 21/04/2008 ዓ/ም

  ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

   

  ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

  ሸምሱ ሲርጋጋ ፈይሳ ወርቁ

  አመልካች፡- ወ/ሮ ጠጅቱ ኡርጋ - ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ገመዳ ሬባ - አልቀረቡም

  መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

   

   ፍ ር ድ

   

  ጉዳዩ የባልና ሚስት ንብረት ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የጀመረው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ሮቢ ወ/ፍ/ቤት ነው፡፡ አመልካች በዚህ ወረዳ ፍ/ቤት ባለቤታቸው በነበሩት አቶ አሰፋ ገመዳ ላይ ክስ የመሰረቱት ኤዴ ከተባለ አከባቢ የሚገኝ ሁለት የበሬ መዋያ  መሬት እና ሰምንተኛ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ግማሸ የበሬ መዋያ ይዞታ መሬታችንን እኩል እንደንካፈል ይወሰንልኝ የሚል ሲሆን ተከሳሽ በበኩላቸው የተጠቀሰው ይዞታ መሬት የጋራ ይዞታችን አይደለም ሊካፈል አይገባም ብለዋል፡፡ የአሁኑ ተጠሪ ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብተው ግራ ቀኙ የሚከረከሩበት መሬት የግል ይዞታዬ ነው በስሜ ተለከቶ የሚገኝ እና በስሜ የምግብርበት ነው ከሳሽና ተከሳሽ በዚህ መሬት ላይ አንዳችም መብት የላቸውም ብለው ተከራካረዋል፡፡

   

  ከሳሽ (የአሁኑ አመልካች) በበኩላቸው ለክርክር ምክንያት የሆነውን መሬት በ1994 ዓ/ም ከተከሳሽ ጋር ስንጋባ የተከሳሽ አባት የሆኑት ጣልቃ ገብ ሰጥተውን በጋብቻ ውላችን ላይም ተጠቅሶ ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ በይዞታችን ስር ሆኖ ስንጠቀምበት ቆይተናል፡፡ ሰሞንኛ ተብሎ ከሚታወቀው አካባቢ ባለን ይዞታ ላይ ቤት ያለን ሲሆን በመ/ቁ. 15710 እና 14792 በሆኑ መዝገቦች በዚህ ቤት ውስጥ ሆኜ ልጆችን እንደሳደግ ፍ/ቤት አዞልኛል የጣልቃ ገብ አቤቱታ ውድቅ ይደረግልኝ ብለው ተከራከረዋል፡፡


  ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙ ምስክሮችን ሰምቶ ክርክራቸው ከቀረበው ማስረጃ ጋር በማገናዘብ መርምሮ ለክርክር ምክንያት የሆነው መሬት በጋብቻ ውሉ ላይ የተመዘገበ እና ከሳሽና ተከሳሽ ይዘውት ሲጠቀሙበት የቆዩ በመሆኑ ጣልቃ ገብ የመሬቱ ይዞታ በስማቸው የሚገኝና ግብር በስማቸው የሚገብርብት ቢሆንም ከሳሽና ተከሳሽ ይዘው የሚጠቀሙበትን መሬት ጣልቃ ገብ መጠየቅ አይችሉም ለክርክር ምክንያት የሆነውን መሬት ከሳሽና ተከሳሽ እኩል ይካፈሉ በማለት ወስኗል፡፡

   

  ጣልቃ ገብ (የአሁኑ ተጠሪ) በዚህ ውሳኔ ላይ ቅሬታቸውን ለምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት አቅርበዋል፡፡ ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ ለክርክር ምክንያት የሆነውን መሬት የስር ከሳሽና ተከሳሽ ሲጋቡ ይ/ባይ (የስር ጣልቃ ገብ) የሰጠው መሆኑን የስር ከሳሽ ምስክሮች ያስረዳ ቢሆንም መሬት የሚሰጠው በቃል ሳይሆን በጽሁፍ ማስረጃ ሆኖ ስልጣን ባለው አካል መመዝገብ እንዳለበት ከገጠር መሬት አዋጅና ከፍ/ብ/ህ/ቁ. 1723 መረዳት ይቻላል፡፡ መሬቱ የጣልቃ ገብ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ለይግባኝ መልስ ሰጭ ከባለቤታቸው ጋር በህጋዊ  መንገድ የተሰጠ ስለመሆኑ ሳይረጋገጥ የጋብቻ ውሉም ለወደፊቱ ከአባታችን ላይ የምናገኛው መሬት የሚል በመሆኑ እና ከዚያ ወዲህም የተደረገ ስጦታ የሌለ በመሆኑ ክርክር ያስነሳው መሬት የይግባኝ ባይ (የስር ጣልቃ ገብ) ይዞታ ነው በማለት የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ በመሻር ወስኗል፡፡

   

  የአሁኑ አመልካች በዚህ ውሳኔ ላይ ቅሬታቸውን ለኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት በይግባኝ አቅርበው ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ በሰጠው ውሳኔ ክርክር ያስነሳውን መሬት ይ/ባይ ከስር ተከሳሽ ጋር በሚጋቡበት ጊዜ በጋብቻ ውላቸው ላይ የተገለጸ እና ከዚያ ወዲህ ይ/ባይ ከባለቤታቸው ጋር እየተጠቀሙበት የቆዩ መሆኑ ተመስከሯል የቀበሌው አስተዳደር ለወረዳ ፍ/ቤት በጻፈው ሪፖርት ላይም መሬቱን ተጋቢዎቹ በጋራ ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑን ገልጿል፡፡ የመሬት እና አካባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ለወ/ፍ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ መሬቱ በመልስ ሰጭ (በስር ጣልቃ ገብ) ስም የተለካ መሆኑን ነገር ግን እየተጠቀሙበት ያሉት ተጋቢዎቹ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ መሬቱ በጋብቻ ውል ላይ የተጠቀሰ መሆኑን ግራ ቀኙ አልተካካዱም ከዚያ ወዲህም ተጋቢዎቹ ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ መ/ሰጭ በስሙ በመመዝገቡ ብቻ እስካሁን ያልተጠቀሙበትን መሬት በስሜ ተለክቷል በማለት ያቀረቡት መከራከሪያ ተቀባይነት የለውም፡፡ ቤት የሰሩበትን መሬት ይ/ባይ ቀደም ሲል እንደኖርበት በፍ/ቤት ተውስኖልኛል ብለው ያቀረቡትን መከራካሪያ መ/ሰጭ አላስተባበሉም ክርክር ያስናሳውን መሬት ይ/ባይ ከባለቤታቸው ጋር ሊካፈሉ ይገባል በማለት የከፍ/ፍ/ቤቱን ውሳኔ በመሻር ወስኗል፡፡ የአሁኑ ተጠሪ በዚህ ውሳኔ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለማስረም ለኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ሰበር ችሎቱም የግራ ቀኙን ክርክር እና የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ በማገናዘብ መርምሮ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን መሬት ተጠሪዋ ከባለቤቷ አባት (ከአመልካች) ያገኙትና ለ9 ዓመት ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑ  በምስክሮች  ተረጋግጧል፡፡  ይሁን  እንጂ  የገጠር  መሬት  አጠቃቀም  ደንብ    እና


  ፍ/ብ/ህ/ቁ.1723 መሰረት የገጠር መሬት ስጦታ በጽሁፍ መሆንና መመዝገበ አለበት ተጠሪ መሬቱን በጋብቻ ወቅት በስጦታ ያገኙ ስለመሆኑ አግባብነት ያለው ማስረጃ አቅርበው ያላረጋገጡ በመሆኑ ክርክር ያስነሳው መሬት የአመልካች (የስር ጣ/ገብ) ይዞታ ነው በማለት ወረዳ እና የጠቅላይ ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት ውሳኔን በመሻር ወስኗል፡፡

   

  አመልካች በዚህ ውሳኔ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በመዘርዘር እንዲታረምላቸውን አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ አቤቱታው ተመርምሮ አመልካች አከራካሪውን 2 ጥማድ እርሻ መሬት ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ ከስር ተከሳሽ ጋር እስከተፋቱበት ጊዜ 2003 ዓ/ም ድረስ በጋራ ሲጠቀሙ መቆየታቸው ተረጋግጦ እያለ መሬቱን ልትካፈል አይገባም ተብሎ ጥያቄዋ በክልሉ ሰበር ችሎት  ተቀባይነት የማጣቱን አግባብነት ለመመርመር ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ ግራ ቀኙ በጽሁፍ ክርክራቸውን አቅርበዋል፡፡

   

  የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ጋር በማገናዘብ አቤቱታው እንዲመረመር ከተያዝው ጭብጥ አንጻር የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመ መሆን አለመሆኑን መርምረናል፡፡

   

  እንደመረመርነውም ክርክር ያስነሳውን መሬት አመልካች የስር ተከሳሽ ከነበሩበት  ባለቤታቸው ጋር በ1994 ዓ/ም ሲጋቡ የባለቤታቸው አባት የሆኑት ተጠሪ ሰጥተዋቸው በጋብቻ ውላቸው ላይም ተጠቅሶ ጋብቻ ከመሰረቱበት ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ ጋብቻው በፍቺ እስከፈረሰበት 2003 ዓ/ም ድረስ ተጋቢዎቹ በጋራ ሲጠቀሙበት የነበረ መሆኑ ፍሬ ነገርን ለማጣራት እና ማስረጃ ለመመዘን በህግ ስልጣን በተሰጣቸው የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ላይ ተረጋግጧል፡፡ ክርክር ያስነሳው መሬት ተመዝግቦ የሚገኘው እና ግብር የሚከፈልበት በተጠሪው ስም ቢሆንም ይህን መሬት ለአመልካቹ እና ለባለቤታቸው ሰጡ ከተባለበት ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 2003 ዓ/ም ድረስ ተጠሪ ተጠቅመውበት የማያውቁ መሆኑና ሲጠቀሙበት የቆዩት አመልካች ከባለቤታቸው (የስር ተከሳሽ) ጋር መሆኑ በስር ፍ/ቤቶች ተረጋግጧል፡፡ ማንኛውም አርሶአደር በመሬት ይዞታው የመጠቀም መብቱን በዚያ መሬት ገቢ ለሚተዳደሩ ወይም ሌላ ገቢ ለሌላቸው የቤተሰብ አባላት ወይም መሬት ለሌላቸው ልጆቹ በስጦታ ማስተላለፍ እንደሚችል በኦሮሚያ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1997 አንቀጽ 9(5) ላይ ተመልክቷል፡፡

   

  በተያዘው ጉዳይ በጽሁፍ የተደረጉ የስጦታ ውል ባይኖርም ለክርክር ምክንያት የሆነውን መሬት በተጠሪ ስም ተመዝግቦ ያለ መሆኑን ነገር ግን እየተጠቀሙበት ያሉት አመልካች  እና ባለቤታቸው መሆኑን ገልጻ ለሜታ ሮቢ ወ/ፍ/ቤት መልስ የሰጠ ሲሆን የቀበሌው አስተዳደርም ለስር ፍ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ ለክርክር ምክንያት በሆነው መሬት አመልካች ከባለቤታቸው ጋር ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑን ገልጿል፡፡ ስር ፍ/ቤት ቀርበው የተሰሙ የአመልካች ምስክሮችም


  መሬቱን ተጠሪ ሰጥተዋቸው አመልካችና ባለቤታቸው ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ተጠሪ ለከርክር ምክንያት በሆነው መሬት ላይ የነበራቸውን የመጠቀም መብት ልጃቸው የሆነው የአመልካች ባለቤት ከአመልካች ጋር ጋብቻ ሲፈጽሙ በዚህ መሬት እንዲተዳደሩ በአባትነታቸው አስልፈው ሰጥተው ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ አመልካች ከባለቤታቸው ጋር በፍቺ ውሳኔ እስከተለያዩበት 2003 ዓ/ም ድረስ ሲጠቀሙበት የቆዩ በመሆኑ በመሬቱ የነበራቸውን የተጠቃሚነት መብት ካስተላለፉ በኋላ መሬቱ ተመዝግቦ የሚገኘው እና ግብርም የሚከፈለው በተጠሪው ስም ብቻ በመሆኑ መሬቱ ለተጠሪ ሊመለስላቸው ይገባል ማለት የሚቻል አይደለም፡፡ ለክርክር ምክንያት የሆነውን መሬት እንደቤተሰብ በእኔ ስር ሆነው አመልካች ባለቤቷ ተጠቀሙ እንጂ በግላቸው ስር ሆኖ አንድም ቀን አልተጠቀሙበትም በማለት ተጠሪ ለዚህ ችሎት ባቀረቡት መልስ የተጠቀሱ ቢሆንም ይህን ስር ፍ/ቤት በነበረው ክርከራቸው አላስረዳም፡፡ በስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ላይ የተረጋገጠው መሬቱን ተጠሪ ለአመልካች ከሰጡ በኃላ ሲጠቀሙበት የቆዩት አመልካች እና ባለቤታቸው መሆናቸውን ነው፡፡ በገጠር መሬት ላይ የሚኖረው መብት የመጠቀም መብት ሲሆን ተጠሪ ይህን መብታቸውን ለአመልካችና ባለቤታቸው አሳልፈው ሰጥተው ለረጀም ጊዜ በዚህ መሬት ላይ ተጠቃሚነታቸው በተቋረጠበት ሁኔታ የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት እና የኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በጽሁፍ የተደረገ ስጦታ ውል አለመኖሩን ብቻ መሰረት በማድረግ በክርክሩ ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር ውጪ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆነ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

   

   ው ሳ ኔ

   

  1. የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍ/ፍ/ቤት በመ/ቁ. 55478 በቀን 3/03/2006 ዓ/ም በዋለ ችሎት የሰጠው ውሳኔ እና የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ/ቁ.186326 በቀን 26/08/2007 ዓ/ም በዋለ ችሎት የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

  2. በኦሮሚያ  ክልል   ምዕራብ   ሸዋ  ዞን  ሜታ   ሮቤ   //ቤት በመ/ቁ.15357   በቀን

  10/01/2006 ዓ/ም በዋለ ችሎት የሰጠው ውሳኔ እና የኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 170790 በቀን 8/11/2006 ዓ/ም በዋለ ችሎት የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ቁ.348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

  3. ለክርክሩ ምክንያት የሆነው መሬት የአመልካች እና ባለቤታቸው የነበሩተ የስር ተከሳሽ የጋራ ይዘት ነው ብለናል፡፡

   

  4. ግራ ቀኙ በዚህ ችሎት ላደረጉት ክርክር ያወጡትን ወጪ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ዕልባት ያገኘ በመሆኑ ወደ መ/ቤት ይመለሰ፡፡የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

 • ጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል ሊባልባቸው ስለሚችሉባቸው ሁኔታዎች ጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል ተብሎ ከሚታሰብበት ጊዜ አንስቶ በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ የንብረት ክፍፍል ጥያቄ ካልቀረበ በይርጋ የሚታገድ ስለመሆኑ

   

  የሰ/መ/ቁ.102662

  የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ/ም

  ዳኞች፡-አልማው ወሌ ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመሰል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ

  አመልካች፡- ወ/ሮ አልማዝ ለሼ- ጠበቃ ኤርሚያስ ደስታ ቀረቡ፡፡ ተጠሪ፡- አቶ በቀለ በላቸው- ወኪል  ትርፍነሽ በቀለ ቀረቡ

  መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

   ፍ ር ድ

   

  ጉዳዩ ጋብቻ ፈርሷል ሊባል የሚችልበትን አግባብ የሚመለከት ነው፡፡ጉዳዩ የተጀመረው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የደብረብርሃን ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን ክሱን ያቀረቡት የአሁኑ አመልካች ናቸው፡፡ የክሱ ይዘትም፡- ከአሁኑ ተጠሪ ጋር በአገር ባህል የጋብቻ አፈጻጸም ስርዓት ጋብቻ ፈጽመው ለአርባ አመታት ያህል አብረው መኖራቸውን፣ ይሁን እንጂ ከመስከረም 2006 ዓ/ም ጀምሮ ሊስማሙ ባለመቻላቸው በመካከላቸው ሰላም እንደሌለ ገልፅው ጋብቻው ፈርሶ የጋራ ንብረት እንዲካፈሉ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪ ለክሱ በሰጡት መልስም ከአመልካች ጋር ባልና ሚስት የነበሩ መሆኑን ሳይክዱ አመልካች ከአስራ ዘጠኝ አመታት በፊት ቤቱን ጥለው መሄዳቸውንና ተለያይተው የሚኖሩ መሆኑን ጠቅሰው ክሱ በይርጋ ሊታገድ ይገባል  በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያስቀደሙ ሲሆን በፍሬ ነገር ረገድ ደግሞ ከአመልካች ጋር ያፈሩት የጋራ ንብረት የሌለ መሆኑን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

   

  የግራ ቀኙ ክርክር በዚህ መልኩ የቀረበለት የሥር ፍ/ቤትም ጉዳዩን መርምሮ በአመልካች እና በተጠሪ መካከል የነበረው ጋብቻ ከአስር አመታት በፊት ፈርሷል የሚል ድምዳሜ ደርሶ የአመልካች ክሱ በይርጋ የታገደ ነው በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡ በዚህ ብይን የአሁኗ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለሰሜን ሸዋ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡


  ከዚህም በኋላ አመልካች የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበውም በጉዳዩ ላይ በተሠጠው ብይን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ተብሎ መዝገቡ ተዘግቶባቸዋል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ሲሆን ይህ ችሎት የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ተጠሪን በመጥራት ግራ ቀኙን በጽሑፍ አከራክሯል፡፡እንዲሁም የወረዳው ፍርድ ቤት ዋና መዝገብ እንዲመጣ አድርጓል፡፡

   

  በአጠቃላይ የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን ምላሽ ማግኘት የሚገባው የጉዳዩ ጭብጥ በተጠሪና በአመልካች መካከል ጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል ተብሎ በበታች ፍርድ ቤቶች መወሰኑ ተገቢነት አለውን? የሚለውነው፡፡

  ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የወረዳው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ምስክሮች ሰምቶ በአመልካችናበተጠሪ መካከልየነበረውጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል በማለት በአመልካች በኩል የቀረበውን ክርክር አልተቀበለውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ወደዚህ ድምዳሜ የደረሰው በአመልካችና በተጠሪ መካከል የነበረው የጋብቻ ግንኙነታቸው ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ ተቋርጦ ግራ ቀኙ ለየብቻ መኖር መጀመራቸው ተረጋግጧል በሚል አቢይ ምክንያት ነው፡፡ ይህ የወረዳው ፍርድ ቤት የፍሬ ነገር ማጣራትና የማስረጃ ምዘና ድምዳሜ በዚህ ረገድ ተመሳሳይ የሆነ ስልጣን ባለው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ አመልካች በዚህ ችሎት አጥብቀው የሚከራከሩት ግራ ቀኙ ሌላ ትዳር መስርተው የራሳቸውን ሕይወት የማይኖሩ መሆኑን፣ አልፎ አልፎ በጤና ምክንያት አመልካች ለፀበል ወደ ሌላ ቦታ ከመሄዳቸው ውጪ አመልካችና ተጠሪ ያልተለያዩና እስከ መስከረም 2006 ዓ/ም ድረስ አንድ ላይ የሚኖሩ መሆኑን ዘርዝረው ለጉዳዩ አግባብነት የሌለው አስገዳጅ ውሳኔ ተጠቅሶ መወሰኑ ያላግባብ ነው በሚል ነው፡፡ እኛም ጉዳዩን ይህ ሰበር ችሎት በመ/ቁ. 14290፣ 20983፣ 31891፣ 67924 እና በሌሎች በርካታ መዛግብት ከሰጣቸው አስገዳጅ ውሳኔዎች ጋር አገናዝበን ተመልክተናል፡፡

  በመሰረቱ የወረዳው ፍርድ ቤት ለውሳኔው መሰረት ያደረገውና ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 31891 ሌሎች ከላይ በተጠቀሱት መዛግብት በሰጣቸው አስገዳጅ ውሳኔዎች በባልና ሚስት መካከል ያለ ጋብቻ በፍ/ቤት በተሰጠ የፍቺ ውሳኔ ፈርሷል ባይባልም የተጋቢዎች ተለያይቶ ለረጅም ጊዜ መኖር፣ በዚህም ጊዜ ሌላ ትዳር መሥርቶ መገኘት የቀድሞው ጋብቻ በሕጋዊ መንገድ ተቋርጧል ሊያስብል ይችላል በማለት በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(1) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህም ውሳኔ ይዘትና መንፈስ መረዳት የሚቻለው የጋብቻ መፍረስ በተጋቢዎች የረዥም ጊዜ መለያየት ሊከናወን የሚችል መሆኑና ፍርድ ቤቱም በዚህ አግባብ የፈረሰውን ጋብቻ እንደገና እንዲፈርስ ውሳኔ የሚሰጥበት አግባብ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ በሰ/መ/ቁጥር 67924 የተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ደግሞ በቤተሰብ ሕጉ አግባብ የመተጋገዝና የመተባበር ግዴታቸውን


  ሲወጡና የነበሩና ያልተለያዩ መሆኑ ከተረጋገጠ ጋብቻ በሁኔታ ፈርሷል ለማለት የማይቻል መሆኑን በመዝገቡ ከተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች በመነሳት የተወሰነ ነው፡፡

  ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካችና ተጠሪ በሕጉ አግባብ ጋብቻ መሰርተው ልጆችን ከወለዱ በኋላ በ1987 ዓ/ም ጀምሮ በአካል ተለያይተው ለአስራ ዘጠኝ አመታት ያህል ሳይገናኙ የኖሩ መሆኑን ከግራ ቀኙ ምስክሮች ቃል የተረጋገጠ መሆኑን የበታች ፍርድ ቤቶች ደምድመዋል፡፡ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀረበው የወረዳው ፍርድ ቤት ዋና መዝገብም  የግራ ቀኙ ምስክሮች የመሰከሩት የፍሬ ነገር ነጥብ በይዘቱ የበታች ፍርድ ቤቶች ከደመደሙት ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ተገንዝቦአል፡፡ በመሆኑም አመልካች ከተጠሪ ጋር እስከ መስከረም 2006 ዓ/ም ድረስ አልተለያየንም በማለት የሚያቀርቡት ቅሬታ በስር ፍርደ ቤት ዋና መዝገብ ውስጥ በምስክሮች ከተነገረው የምስክርነት ቃል ይዘትና ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ከደረሱበት ድምዳሜ ውጪ በመሆኑ ተቀባይነት የሚሰጠው ሁኖ አልተገኘም፡፡ በዚህ ረገድ አመልካች ያቀረቡት ቅሬታ ለዚህ ችሎት በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች አግባብ የተሰጠውን ስልጣንም ያላገናዘበ ሁኖ አግኝተናል፡፡

  በመሰረቱ ጋብቻ በተጋቢዎች መካከል የመተጋገዝ፣ የመከባበርና መደጋገፍ እንዲሁም አብሮ የመኖር ግዴታን የሚጥል መሆኑን ከክልሉ የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 60 እና 61 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚሁ  አኳያ በተጠሪና በአመልካች መካከል የነበረው ጋብቻ ይህ ሰበር ችሎት አስቀድሞ በተመሳሳይ ጉዳይ ከሰጠው ውሳኔ አንጻር ተቋርጧል? ወይንስ አልተቋረጠም? የሚለውን ለመወሰን ከፍ ብሎ በአመልካችና በተጠሪ መካከል በጋብቻ ውስጥ በግራ ቀኙ የሚጠበቁ ግዴታዎች ባግባቡ ሲተገበሩ ያልነበሩና እነዚህን ግዴታዎችን ለመወጣት ደግሞ በአመልካች በኩል ያጋጠመው ሁኔታ በሕጉ የተጣሉባቸውን ግዴታቸውን ለመወጣት የማያስችል የነበረ መሆኑ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ አመልካች ከተጠሪ ጋር አልተለያየንም፣ በጤና ችግር ምክንያት አልፎ አልፎ ለፀበል ሌላ ቦታ እሄድ ነበር በማለት የሚያቀርቡት ክርክር በክርክሩ ሂደት በማስረጃ የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮችን መሰረት አድርጎ ያልቀረበ ሁኖ አግንተነዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተያዘው መዝገብና ይህ ሰበር ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠባቸው መዛግብት የያዟቸው መሰረታዊ ፍሬ ነገሮች ከዚህ መዝገብ ከተረጋገጡት እውነታዎች ሙሉ በሙሉ የተመሳሳይነት ያላቸው ሁኖ እያለ አመልካችም ሆነ ተጠሪ ሌላ ትዳር መስርተው ሕይወታቸውን በመምራት ላይ አይገኙም በማለት በሰ/መ/ቁጥር 31891 የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በመተውና ግንኙነቱ ያልተቋረጠ  ተጋቢዎችን መሰረት ተደርጎ በመ/ቁጥር 67924 የተሰጠውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ አመልካች መከራከራቸው ከአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2 (1) አተገባበር ጋር የሚጋጭ ሁኖ አግኝተናል፡፡ ስለሆነም የአመልካችና የተጠሪ ግንኙነት ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ በሁኔታ የፈረሰ


  በመሆኑ እና ለጉዳዩ አግባብነት በላቸው ከላይ በተጠቀሱት መዛግብት በተሰጠው ትርጉም መሰረት የጋራ ንብረት ጥያቄም በአስር አመት ያልቀረበ በመሆኑ የተጠሪ ክስ በይርጋ የታገደ ነው ተብሎ ብይን መሰጠቱ የሚነቀፍበትን የሕግ ምክንያት አላገኘንም፡፡ ሲጠቃለልም በጉዳዪ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት ሁኖ ስላላገኘነው ተከታዩን ወስነናል፡፡

   ው ሳ ኔ

  1. የደብረብርሃን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር  0108191/06  በ22/08/2006 ተሠጥቶ በሰሜን ሸዋ መስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 0114418 በ30/08/2006 ዓ/ም፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 030- 5041 ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል፡፡

  2. በአመልካችና በተጠሪ መካከል በአገር ባህል የጋብቻ አፈፃጸም ስርዓት ተመስርቶ የነበረው ጋብቻ ለረዥም ጊዜ ተለያይቶ በመኖር ምክንያት ፈርሷል በማለት ወስነናል፡፡

  3.  በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

   ት ዕ ዛ ዝ

  ከደብረብርሃን ከተማ ወረዳ ፍርደ ቤት የመጣ መዝገብ ቁጥር 0108191/06 በመጣበት አኳሀን ይመለስ ብለናል፡፡

  መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

  የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

   

  ወ/ከ

 • ሞግዚት የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ፈጽሞ ሲገኝ ሊወሰዱ ስለሚገቡ ዝርዝር ሁኔታዎች የሕግ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ሞግዚቱ ለሚፈጽማቸው ድርጊቶች፤ ወኪል የሆነ ሰው ከተሰጠው ሥልጣን በላይ በሚሠራበት ጊዜ አግባብነት ያላቸው የውክልና ሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ የሚሆኑ ስለመሆኑ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁ.213/1992 አንቀጽ 306፣277 የፍ/ብ/ሕ/ቁ.2207/1

  የሰ/መቁ.103151

  መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም

  ዳኞች፡-አልማው ወሌ

   

  ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ ቀነዓ ቂጣታ

  ሌሊሴ ደሳለኝ

   

  አመልካች፡-አቶ ግርማ ብሩ አየለ - ቀረቡ

   

  ተጠሪ፡-አቶ መርዕድ ብስራት - ጠበቃ አበበ ማስረሻ ጋር ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

   ፍ ር ድ

   

  ይህ ጉዳይ የቤት ሽያጭ ውል እንዲፈርስ የቀረበ ክስን መነሻ ያደረገ ክርክር ነው፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ፡- የሥር ከሳሽ /የአሁን ተጠሪ/ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ የወላጅ አባቴ እና የ2ኛ ተከሳሽ የጋራ ንብረት የሆነውን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 03 የቤት ቁጥር አዲስ ካረታ ቁ.3329 የሆነውን ቤት 2ኛ ተከሳሽ ከሞግዚትነት ስልጣን ተቃራኒ ሚያዝያ 23 ቀን 2000 ዓ.ም በተደረገ ሽያጭ ውል ለ1ኛ ተከሳሽ በብር 350,000 የሸጠች ስለሆነ 1ኛ ተከሳሽም /የአሁኑ አመልካች/ የከሳሽና የሌሎች ሰዎች የጋራ ንብረት መሆኑን እያወቀ ለቅን ልቡና ተቃራኒ በሆነ መንገድ ስለገዛ የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስልኝ፣ 1ኛ ተከሳሽ ቤቱን እንዲያስረክበኝ በማለት አመልክቷል፡፡

   

  ይህን ክስ በተመለከተ ተከሳሾች መልስ እንዲሰጡበት የታዘዘ ሲሆን የሥር 1ኛ ተከሳሽ /የአሁን አመልካች/መጥሪያ ደርሶት የጽሑፍ መልስ ስላልሰጠ ታልፏል፡፡ የሥር 2ኛ ተከሳሽ በሰጠችው መልስ ባለቤቴ ከሞተ በኋላ ልጆች ለማሳደግ የተቸገርኩ በመሆኑ የቤት ሽያጭ ውል ፈጽሜአለሁ፡፡ 1ኛ ተከሳሽም የቤቱን ሸያጭ ገንዘብ እንደውሉ አልከፈለኝም፤ እኔ ቤቱን የሸጥኩኝ ለከሳሽና ለሁለት ወንድሞቹ ጥቅም እንጂ ለግሌ ጥቅም አይደለም፤ ፍ/ቤቱ የመሰለውን ውሳኔ ቢሰጥ አልቃወምም በማለት ተከራክራለች፡፡ 1ኛ ተከሳሽ ክርክር በሚሰማበት ቀን ቀርቦ  ሲከራከር


  ሞግዚት የማይንቀሳቀስ ንብረት መሸጥ ትችላለች፣ እኔ በቤቱ ላይ ሰፊ ለውጥ ያደረኩ ስለሆነ ውሉ ሊፈርስ አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡

   

  ከዚህ በኋላ ፍ/ቤት ግራ ቀኙን በማከራከር፣ የከሳሽን የሰው ምስክር በመስማት በሰጠው ውሳኔ በተከሳሾች መካከል ሚያዝያ 23 ቀን 2000 ዓ.ም የተደረገው የቤት ሽያጭ ውል የልጆችን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ስለተፈጸመ ፈርሶ ተዋዋይ ወገኖች ወደ ነበሩበት ይመለሱ፣ 2ኛ ተከሳሽ ብር 60,000 ለ1ኛ ተከሳሽ ትመልስ፣ 1ኛ ተከሳሽ በገዙት ይዞታ ሲገለገሉበት በነበረው ቤት ላይ ያወጡት ወጪ ካለ ክስ አቅርቦ መጠየቅ ይችላል በማለት ወስኗል፡፡ የሥር 1ኛ ተከሳሽ ይህን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ማመልከቻውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን በማከራከር በሰጠው ውሳኔ፣ የቤቱ ሽያጭ ዋጋ በአብዛኛው ስላልተከፈለ 2ኛ ተከሳሽ ለግል ጥቅም አውላለች፣ የልጆች ቅጥም ላይ ጉዳት ድርሷል የሚያስብል ስላልሆነ፣የሽያጭ ውሉን ለማፍረስ በቂና አሳማኝ ምክንያት ስለሌለ ሊፈርስ አይገባም በማለት የሥር ውሳኔ በመሻር ወስኗል፡፡ የሥር ከሳሽ ይህን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ማመልከቻውን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን በማከራከር በሰጠው ውሳኔ፣ የቤት ሽያጭ ውሉ የከሳሽን ጥቅም የሚጎዳ ስለሆነ ውሉ ሊፈርስ ይገባል በማለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት  ውሳኔ በመሻር የፌዴራል የመጀመያ ደረጃ ፍ/ቤት ውሳኔን በማጽናት ወስኗል፡፡ የአሁን የሰበር አቤቱታም ይህን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ የቀረበ ነው፡፡

   

  የአሁን አመልካች ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም በተጻፈ አቤቱታ የተጠሪ ሞግዚትና አስተዳዳሪ የነበሩት ወ/ሮ ክብካብ አስፋው የቤት ሽያጭ ውሉን ያደረጉት ለተጠሪ እና ለሌሎች ሁለት ወንድሞቻቸው መልካም አስተዳደር ስለሆነ ውሉን የተደረገው ለልጆቹ ቅጥም መዋሉ በተጠሪም ሞግዚት በጽሑፍ እና በምስክሮች በስር ፍ/ቤት የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ ውሉ ሊፈረስ  ይገባል በማለት የተሰጠ ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው፡፡ የተጠሪ ሞግዚት ከተቀበለችው የቤት ሽያጭ ውሉ ገንዘብ የተጠሪ ድርሻ ብር 10,000 ብቻ ስለሆነ ውሉ የሚፈርስበት ምክንያት የለም፡፡ አመልካች ቤቱን ከገዛሁ በኋላ ሌላ አዲስ ሰርቪስ ቤት ክፍሎች ብር 450,000 በላይ ወጪ በማድረግ በቤቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የይዘት ለውጥ አድረጎበታል፡፡ ስለዚህ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ውሉ ፈርሶ ወደ ነበራችሁበት ተመለሱ በማለት የወሰኑት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለው ስለሆነ እንዲሻርልኝ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲፀናልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

   

  የሰበር አጣሪ ችሎትም መዝገቡን በመመርመር "በአመልካች እና በተጠሪ ሞግዚት መካከል የተደረገው የቤት ሸያጭ ውል ይፍረስ ተብሎ በሥር ፍ/ቤቶች የመወሰኑን አግባብነት ከመዝገብ ቁ.46490 አንጻር ለመርመር ሲባል አቤቱታው ለሰበር ያስቀርባል በማለት ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ


  በታዘዘው መሰረት መስከረም 7 ቀን 2007 ዓ.ም የተጻፈ መልስ አቅርቧል፡፡ የመልሱ ይዘትም፡- የተጠሪ ሞግዚት የማይንቀሳቀስ ንብረት መሸጥ አትችልም፡፡ እኔ ከቤቱ ድርሻ እያለኝ ያለ እኔ ፈቃድ ሸጣለች፡፡ የተጠሪ መብት መጣስ እና መጎዳት የሚጀምረው ከዚህ መሰረታዊ ከሆነው የባለቤትነት መብቶች አኳያ ስንነሳ ነው፡፡ እኔ በቤቱ ሽያጭ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰብኝ አስረድቼአለሁ፣ አመልካች ግን ከሽያጩ ጥቅም ያገኘሁት መሆኑን አላስረዳም፡፡ አመልካች ከቤቱ ሽያጭ ገንዘብ የከፈለው ብር 60,000 ብቻ ሲሆን ቤቱን ተረክቦ እያኖረበት ነው፣ ከጉዳት በቀር ጥቅም ሊኖር አይችልም፡፡ ተጠሪው በሽያጩ ጉዳት እንጂ ያገኘሁት ጥቅም ስለሌለ ለሰበር መዝገብ ቁ.46490 ከሰጠው ውሳኔ ጋር የማይቃረን ስለሆነ ውሳኔው እንዲፀናልኝ፣ የቀረበው አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግልኝ፡፡ አመልካች ከቤቱ ድርሻ የተጠሪ ድርሻ 10,000 ብር ብቻ ስለሆነ ሊፈርስ አይገባም በማለት ያቀረበው ክርክር የባለቤትነት መብትን የጣሰ እና ሕጉ ተቃራኒ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡ አመልካቹ በቤቱ ላይ ግንባታ ስለመካሄዱ ያቀረበው ማስረጃም የለም፣ በቤቱም ላይ የይዘትም ሆነ የቅርጽ ለውጥ አላደረገም፣ የተጠሪ ሞግዚት የቤት ሽያጩን ገንዘብ ማባከናቸውን እንጂ ለልጆች ጥቅም ያወሉት መሆኑን ያረጋገጠ ማስረጃ  የለም፡፡ ስለዚህ አመልካች ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ሆኖ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም ተብሎ እንዲፀናልኝ፣ ወጪና ኪሳራ እንዲወሰንልኝ በማለት ተከራክሯል፡፡ አመልካች ጥቅምት 04 ቀን 2007 ዓ.ም በተጻፈ የመልስ መልስ አቤቱታውን በማጠናከር ተከራክሯል፡፡

   

  የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ እንደተመለከተ ሲሆን፤ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎትም የግራ ቀኙ  ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው  የሕግ  ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ አቤቱታው ያስቀርባል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡ መዝገቡን እንደመረመርነው ተጠሪ ባቀረበው ክስ የሽያጭ ውል የተፈጸመበት ቤት ላይ ድረሻ እያለኝ የእኔን ጥቅም በሚጎዳ መልክ ሞግዚት የሆነችው ወ/ሮ ክብካብ ሣህሉ ወልደማርያም በሽጨጭ ውል ለአመልካች የሸጠች ስለሆነ ውሉ እንዲፈርስልኝ በማለት አልክቷል፡፡ የተጠሪ ሞግዚት /የሥር 2ኛ ተከሳሽ/ በጽሑፍ ባቀረበችው መልስ ቤቱን የሸጥኩት ለተጠሪ እና ለሌሎች ወንድሞቹ ቅጥም ነው በማለት የተከራከረች ቢሆንም እንደምስክር ሆነ በሰጠችው ቃል ደግሞ ከቤቱ ሽያጭ ገንዘብ ውስጥ ብር 60,000 ብቻ የተቀበለች እንደሆነና ለራሷ ትምህርት ክፍያ እንደከፈለችና ቀሪውን ለወንድሟ እንዳበደረች ገልጻለች፡፡ አመልካች በበኩሉ መጥሪያ ደርሶት የፍሑፍ መልስ ባለመስጠቱ የታለፈ ስለሆነ የጽሑፍ መልስ እና ማስረጃ በማቅረብ በማስረዳት መከራከር የነበረበትን ክርክር በተመለከተ መብት አጥቷል፡፡ ስለዚህ አልካች በጽሑፍ መከራከር የነበረበትና ማስረጃ በማቅረብ ማስረዳት የነበረበትን ፍሬ ነገር በተመለከተ አሁን ለማንሳት የሚችልበት የሕግ መሰረት የለውም፡፡ ተጠሪ ባቀረበው ክርክር አመልካች ከተጠሪ ሞግዚት  ጋር


  የቤት ሽያጭ ውሉን ሲፈጽም በቤቱ ላይ ልጆች ድርሻ ያላቸው መሆኑን ውሉ እያመለከተ ነው ቤቱን የገዛው የሚለውን፣ አመልካች ይህን ፍሬ ነገር ክዶ እየተከራከረ አይደለም፡፡ አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው በሞግዚቱ በኩል የተደረገው የቤቱ ሽያጭ ለልጆች ጥቅም ነው እንጂ ጥቅማቸውን የሚጎዳ አይደለም የሚል ነው፡፡ የተጠሪ እናት የሆነችው የሥር 2ኛ ተከሳሽ የተሻሻለው የቤተሰብበ ሕግ አዋጅ ቁ.213/1992 አንቀጽ 220/1/ መሰረት ሕጋዊ የሞግዚትነት ስልጣን እንደተሰጣቸው ከመዝገቡ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት የሥር 2ኛ ተከሳሽ ተጠሪን በመወከል ሕጋዊ ተግባሮችን ለተጠሪ ጥቅም ለመፈጸም ስልጣን የተሰጣቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ በዚሁ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 277 የሞግዚት ስልጣን በተመለከተ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከመሸጥ ጋር ተያይዞ የሚለው ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን ሕጉ ሞግዚት መሸጥ የሚችላቸውን የንብረት ዓይነቶች በመዘርዘር በማስቀመጡ፣ ከዚህ ዝርዝር ወጭ ያሉትን ንብርቶች በተመለከተ ሞግዚት መሸጥ አይችልም ቢባል እንኳን ሞግዚት የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ፈጽሞ ከተገኘ ግን ምላሸ ለማግኘት ሌላ ሕግ መፈተሽ አስፈላጊ ሆኖ ይታያል፡፡ ከዚህ አንጻር የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁ.213/1992 አንቀጽ 306 እንደሚደነግገው "የሕግ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ሞግዚቱ ለሚፈጽማቸው ድርጊቶች፤ ወኪል የሆነ ሰው ከተሰጠው ሥልጣን በላይ በሚሠራበት ጊዜ አግባብነት ያላቸው የውክልና ሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ" የሚል ነው ፡፡ በዚህ መሰረት ተወካዩ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ በመውጣት የሰራውን ስራ በተመለከተ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.2207/1/ እንደሚያመለክተው "ተወካዩ ከስልጣኑ ውጭ የሠራው ስራ በቅን ልቡና ሆኖ ሲገኝ ሥራውን ወካዩ እንዲያጸድቅለት ይገደዳል" የሚል ነው፡፡ በዚህ አግባብ የሞግዚቱ "ቅን ልቡና" መታየት ያለበት የተሰራ ስራ የልጁን ጥቅም የሚጎዳ ነው ወይስ አይደለም? ከሚል አንጻር መሆን እንዳለበት ነው፡፡

   

  የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁ.46490 መጋቢት 21 ቀን 2002 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሞግዚት የማይንቀሳቀስ ንብረት ለልጆች መልካም አስተዳደግና ጥቅም የሸጠ መሆኑ ከተረጋገጠ የሽያጭ ውል ለማፍረስ የሚያስችል በቂ ምክንያት አይደለም በማለት ወስኗል፡፡ ይህ ማለት የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭን በተመለከተ የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም የሚል ጭብጥ መታየት ያለበት ለልጆች ቅጥም መሆን አለመሆኑን በማጣራት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በተጠሪ ሞግዚት እና በአልመካች መካከል የተደረገውን የቤት ሽያጭ ውል ለተጠሪ እና ለሌሎች ወንድሞቹ ጥቅም የዋለ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ጭብጥ ሲታይ ለተጠሪ ጥቅም መዋሉን የሚያመለክት ምንም ነገር የለም፡፡ የተጠሪ ሞግዚት ከቤቱ ሽያጭ አመልካች የከፈላት ገንዘብ ብር 60,000 እንደሆነ ከዚህ ውስጥ ብር 10,000 ለትምህርት እንደከፈለች፣ ቀሪውን ለወንድሟ እንዳበደረች አረጋግጣለች፡፡  ይህ ማለት ከቤት ሽያጭ የተገኘው ገንዘብ ለተጠሪም ሆነ ለሌሎች ልጆች አለመዋሉን   ያመለክታል፡፡


  እንዲሁም ከቤቱ ሽያጭ የተገኘ ገንዘብ ለልጆቹ ጥቅም መዋሉን የሚያመለክት ማስረጃ መቅረቡን የሥር ፍ/ቤቶች ያረጋገጡት ነገር የለም፡፡ አመልካች ራሱ ከቤቱ ሽያጭ ብር 350,000 ውስጥ እስካሁን የከፈለው ብር 60,000 ብቻ ሲሆን ቀሪውን ገንዘብ ያለመክፈሉ ግራ ቀኙ የሚካከዱት ጉዳይ ስላልሆነ፣ የቤቱ ሽያጭ ውል ለተጠሪ እና ለሌሎች ልጆች ጥቅም የዋለ ነው ለማለት የሚያችል አንድም ነገር የለም፡፡ አመልካች ቤቱ የተሸጠበትን ገንዘብ አብዛኛውን ሳይከፍል እንዲያውም አነስተኛ ገንዘብ ብቻ ከፍሎ በዚህ ሽያጭ የልጆቹ ጥቅም ተጠብቆላቸዋል፣ የሽያጭ ውሉም ለልጆች ጥቅም የተደረገ ነው፤ ለተጠሪና ለሌሎች ወንድሞቹ መልካም  አስተዳደግ ውሏል በማለት የሚያቀርበው ክርክር ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አይታይም፡፡ ስለዚህ የሚያዝያ 23 ቀን 2000 ዓ.ም በተጠሪ ሞግዚትና በመአልካች መካከል የተደረገው የቤት ሽያጭ ውል ለተጠሪና ለሌሎች ወንድሞቹ ማለትም ለልጆች ጥቅም እና መልካም አስተዳደግ ያልዋለ መሆኑ ስለተረጋገጠ፣ የሸያጭ ውሉ ሌፈርስ አይገባም በማለት አመልካች ያቀረበው ክርክር በየትኛውም የሕግ መመዘኛ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡

   

  ሌላው አመልካች ባቀረበው ክርክር ተጠሪ ከቤቱ ያለው ድርሻ አነስተኛ መሆኑን በመግለጽ ለውሉ መፍረስ መክንያት ሊሆን አይችልም የሚለው ሲታይ ተጠሪ ከቤቱ ድርሻ እስካለው ድረስ የጋራ ንብረቱ ከሱ ፈቃድ ውጭ መሸጥ የሌለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከልጆች መብት አንጻር የአመልካች ክርክር ተቀባይነት የለውም፡፡ በሌላ በኩል አመልካች ቤቱን ከገዘሁ በኋላ በቤቱ ላይ ግንባታ አካሄጃለሁ ያለውን በተመለከተ ተጠሪ ምንም ዓይነት ግንባታ አልተደረገም በማለት ክዶ የተከራከረ ሲሆን፣ አመልካች ደግሞ የጽሑፍ ክርክር በማቅረብ በማስረጃ ስላላስረዳ፣ በሥር ፍ/ቤት በማስረጃ ያላስረዳውን ክርክር ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንደቅሬታ ነጥብ ማቅረቡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.329/1/ መሰረት ተቀባይነት የለውም፡፡ በአጠቃላይ የሥር ፍ/ቤቶች የሽያጭ ውሉ የልጆችን ጥቅም የሚጎዳ ስለሆነ ውሉ ፈርሶ ግራ ቀኙ ወደ ነበሩበት ሊመለሱ ይገባል፣ አመልካች በቤቱ ላይ ያወጣ ወጪ ካለ ከሶ መጠየቅ ይችላል በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተተ የሌለው በመሆኑ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

   

   ው ሳ ኔ

   

  1. የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁ.201566 በ07/08/2005 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ፣ እንዲሁም የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁ.137501 ታህሳስ 22 ቀን2006 ዓ.ም የሰጠውን ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለው  በመሆኑ በመሻር የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁ.98101 በ22/09/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሌለው በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348/1/ መሰረት ጸንቷል፡፡


   

  2.  የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይድረስ ብለናል፡፡

  3. ግራ ቀኙ በዚህ ችሎት የደረሰባቸውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ በውሳኔ ስለተዘጋ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡

  የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

   

  ማ/አ

 • በተሻሻለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የቤተሰብ ህግ መሰረት ባልና ሚስት የጋራ ንብረታቸውን እኩል የማስተዳደር መብት ያላቸውና የጋራ ስምምነት ሳይኖር ንብረትን ለሌላ 3ኛ ወገን በአንደኛው ተጋቢ ፍቃድ ብቻ የተላለፈ ከሆነና ይህንን ስምምነቱን ያልሰጠው ተጋቢ በህጉ በተፈቀደለት ጊዜ ገደብ ውስጥ የይፍረስልኝ ጥያቄውን ካላቀረበ የተፈፀመው ተግባር እንደፀና የሚቆይ ስለመሆኑ አዋጅ ቁ.213/92 አንቀፅ 68፣69

   

  የሰ/መ/ቁ. 103721

  የካቲት 03 ቀን 2008 ዓ.ም

   

   

  ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

  ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ

  ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

   

  አመልካች፡-  ወ/ሮ ሰሚራ ጀማል ከጠበቃ ሰለሞን ታደሰ ቀረቡ ተጠሪ፡- 1ኛ. አቶ ጀማል እንዲሪስ ከጠበቃ መሰረት ስዩም ጋር ቀረቡ

  2ኛ. ወ/ሮ ሉላ አረፈ አልቀረቡም

  3ኛ.አቶ ሀጎስ አብዱራህማን በመዝገብ ቤት በኩል እንዲሰሙ ተናግሯል፡፡

  መዝገቡ ተመርምሮ ተገቢውን ዳኝነት ለመስጠት ለየካቲት 01 ቀን 2008 ዓ/ም ቀጠሮ የያዘ ሲሆን በዚህም መሰረት መዝገቡን መርምረን በአዳሪ በዚሁ እለት የሚከተለውን  ፍርድ ሰጥተናል፡፡

   ፍ ር ድ

  ይህ የሰበር ጉዳይ በአሁን አመልካችና 1ኛ ተጠሪ መካከል የነበረው ጋብቻ በፍ/ቤት የፍቺ ውሳኔ መሰረት መፍረሱን ተከትሉ በአሁን አመልካች የጋራ ንብረት ድርሻ ጥያቄ መነሻ የስር ፍ/ቤቶች የጋብቻ ውጤት በሆነው የንብረት ክርክር ላይ የሰጡትን ዳኝነት በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ክርክር ካስነሳው የውሳኔ ክፍል አንፃር ተመልክቶ የውሳኔውን አግባብነት ከግራ ቀኙና ክርክሩ የሚመለከተው ሆኖ የተገኘው 3ኛ ተጠሪም ካቀረቡት ክርክር ጋር በማገናዘብ አስፈላጊውን ዳኝነት ለመስጠት በሚል የቀረበ ነው፡፡

   

  የጉዳዩም አመጣጥ ባጭሩ እንደሚከተለው ነው በአሁን አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ መካከል ሚያዚያ 21  ቀን 1987 ዓ/ም ተደርጎ የነበረው ጋብቻ ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ/ም  በፍ/ቤት የፍቺ ውሳኔ መፍረሱን ተክትሎ የአሁን ተጠሪ ሀምሌ 27 ቀን 2003 ዓ/ም ተሻሽሎ ባቀረቡ ማመልከቻ የጋራ ንብረት ናቸው ያሏቸውን ናቸው የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረቶች በመዘርዘር ድርሻቸው ተለይቶ ይወሰንላቸው ዘንድ ተገቢ የነበሩትን የአሁን 1ኛ ተጠሪን እና የ1ኛ ተጠሪ ሌላ ሚስት የሆነችን የአሁን 2ኛ ተጠሪን በተከሳሽነት ላይ ደመወዝ በዚሁ የጋብቻ ውጤት በሆነው የንብረት ድርሻ ጥያቄ ላይ፣ እንደዚህም 1ኛ ተጠሪ የጋራ ንብረትን ሲያስተዳድር የደረሰው፣  ጉዳት ሲታወቅ በኃላ ተገቢውን የካሳ ለአመልካች እንዳይከፍል ይወሰንልኝ   በማለት


  ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ እንደክርክራቸው ያስረዳልናል ያሏቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃም አያይዘው አቀርበናል፡፡

   

  የአሁን 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የጋራ ንብረት ናቸው በሚል በአሁን አመልካች የክስ ማመልከቻ ላይ ከተዘረዘሩት ንብረቶች የጋራ ንብረት የሆኑትን በማመን፣ በጋራ ሀብትነት የማይታወቁትን፤ የሚያገኙትን ደግሞ በመካድ በአመልካች ክስ በተዘረዘረው የንብረት ዝርዝር አንፃር መልስ የሰጡ ሲሆን፤ በንብረት አስተዳደር ረገድ ያደረስኩት ጉዳት የሌላ በመሆኑ የሰጠው  ጥያቄ አይመለከተኝም በማለት ክርክራቸውን አቅርቧዋል፡፡ ለክርክሩም ድጋፍ ያላቸውን ማስረጃዎች አያይዘው አቅርበዋል፡፡

   

  የአሁን 3ኛ ተጠሪም የጋራ ንብረት ነው በሚል በአሁን አመልካች ከተጠቀሱት ንብረቶችና መካከል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍል ከተማ ወረዳ 3 ክልል በቤት  ቁጥር 2545  የሚታወቀውን ቤት በውል አዋዋዩ ክፍል ዘንድ ጂ. ኤስ. ኤ.ጄኔራል ትሬድንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር ከተባለው ድርጅት የገዙት ስለሆነ የአመልካችን ጥያቄ ውድቅ ለማድረግ ይወሰንልኝ በማለት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብተውም ተከራክረዋል፡፡ ለዚህም ክርክራቸው ለማስረጃነት ሰነዶችን እንዳቀረበም የመዝገቡ መልሰን ያስረዳል፡፡

   

  እኚሁ ጣልቃ ገብ ያቀረቡትን ክርክር አስመልክቶ የአሁን አመልካች ጣልቃገብ ፍ/ቤቱ በንብረቱ ላይ የእግድ ትእዛዝ በሰጠበት ንብረት ላይ ግዥ የፈጸሙ ስለሆነ የሽያጭ ውሉ ከጅምሩ ፈራሽ ስለሆነ ጥያቄው ተቀባይነት የለውም በማለት ተከራክረዋል፡፡

   

  የአሁን 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ይህንኑ በቁጥር 2545 ተመዝግቦ የሚታወቀውን ቤት አስመልክቶ ንብረቱ በማናቸውም ስም ተመዝግቦ የሚታወቅ የጋራ ንብረት ባለመሆኑ እንጂ የጋራ ንብረት ተቆጥሮ መቅረቡ ተገቢ አይደለም በማለት አመልካች ባቀረቡት ክስ ቀጥተኛ መልስ የሰጡ ከመሆኑም በላይ በጣልቃ ገብ በኩል የቀረበው ክርክር አስመልክቶ ደግሞ ተቃውሞ የሌለባቸው መሆኑን ገልጸናል፡፡

   

  ሁሉም ወገኖች ከላይ ባጭሩ ለይዞታ ደረጃ የተገለጸውን የጹሁፍ ክርክር ካደረጉ በኋላ ለጉዳዩም ላይ የቃል ክርክር እንዳደረጉ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

   

  የስር ፍ/ቤትም ከግራ ቀኙ ክርክር በመነሳት በአከራካሪነታቸው በጭብጥነት ተይዘው ከማስረጃ አንፃር ለማየት ዳኝነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በማለት ከሙግት ደረጃ ደርሶ ለማስረጃ ሰምቶ ዳኝነት ካሳረፈባቸው ንብረቶች መካከል በአከራካሪያቸው ከዚህ ሰበር ደረጃ ዘልቀው ከደረሱት መካከል አንዱ በቤት ቁጥር 2545 የተመዘገበውን ቤት አስመልክቶ


  የአሁን አመልካች በጋብቻ ዘንድ የተፈራውን ይህንኑ ንብረት ከእኔ ለማሸሽ ሲል ያለ እኔ ፈቃድ ጀ. ኤስ.ኤ አጄኔራል ትሬድንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር ወደ ተባለው ድርጅት በመዋጨነት አስገምቶ አሽሽቶ የሰጠ በመሆኑ፤ እንዲሁም ይህን ንብረት የአሁን 3ኛ ተጠሪ ፍ/ቤቱ በንብረቱ ላይ የእግድ ትእዛዝ ከተሰጠበት በኋላ እንዲገዙት የተደረገ ስለሆነ ንብረቱ የጋራ ሀብት መሆኑ ታውቆ በድርሻዬ ልከፍል ይገባል በማለት የተከራከሩ ቢሆንም በኢፊድሪ የፍትህ ሚንስተር የሰነዶች ማረጋገጫና ከዘገባ ጽ/ቤት በቀን 10/3/2002 ዓ/ም በተፈረመ የጂ ኤስ ኤ ጄነራል ትሬድንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር የመመስረቻ ጽሁፍ ይዘው በቤት ቁጥር 2545 ተመዝግቦ የሚታወቀው  በ1ኛ ተጠሪ  አማካኝነት በመጭነት  የተመዘገበ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

   

  ሚያዚያ 16 ቀን 2002 ዓ/ም በተካሄደ የጂ ኤስ ኤ.ኤጀኔራል ትሬድንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር ለሂሳብ 1ኛ ተጠሪ በማህበሩ የየራሳቸውን አክስዮን በብር 240,000.00 /ሁለት መቶ አርባ ሺህ ብር/ ሽጠው የተሰራበት መሆኑ በኢፈደሪ የፍትህ ሚኒስቴር ማስረጃ ማረጋገጫ ምዝገባ ጽ/ቤት ማህተም በተረጋጠ ሰነድ ተረጋግጧል ጂ. ኤስ ጄኔራል ትሬድንግ ኃ/የተ/ የግል ማህበር ግንቦት 17 ቀን 2003 ዓ/ም በተፃፈና በሰነዶች ማረጋገጫና መዝገብ ጽ/ቤት በተመዘገበ የሽያጭ ውል ይህንኑ የቤት ቁጥር 2545 የሆነው በብር 240,000.00 /ሁለት መቶ አርባ ሺህ ብር/ ለጣልቃ ገብ ለአሁን 3ኛ ተጠሪ አብዱራህማን አህመድ የተሸጠ ስለመሆኑም በጣልቃ ገብ አማካኝነት በቀረበው የጽሁፍ ማስረጃ ተረጋግጧ በመሆኑም ይኸው ቤት ከ1ኛ ተጠሪ እጅ ሙሉ በሙሉ ወጥቶ በጂ ኤስ. ኤ.ተራ ደንብ ኃ/የተ/የግል ማህበር ተጠቃሎ ተላልፏል የተስፋፋውም የአመልካችና 1ኛ ተጠሪ ጋብቻ እንዳይፈርስ የፍቺ ጥያቄ ለመቅረቡ በፊት እና ለፍ/ቤት የእግድ ትእዛዝ በፊት ስለመሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡

   

  የጋራ የሆነውን ንብረት ያለ ሁለተኛው ተጋቢ ፈቃድ በአንደኛው ተጋቢ አማካኝነት ተላልፎ የተገኘ እንደሆነ በአዋጅ ቁጥር 213/92 አንቀፅ 68/ሀ/ እና 69 እንደተደነገገው ፈቅደን ባልሰጠው ተጋቢ ጥያቄ መሰረት ንብረቱ የተላለፈበት ግዴታ እንዲፈርስ ካልተደረገ በቀር በተፈጸፀመው የንብረት ማስተላለፍ ስምምነት ውስጥ ተጋቢዎች እንደታሰበው ግምት እንደሚሰጡ ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሰረት አመልካች በዚህ በመ/ቁ 2545 የተደረገውን የሽያጭ ስምምነት  በመቃወም በፍ/ቤት ጥያቄ አቅርበው ያስወሰኑት የለም፡፡ ስለሆነም ንብረቱን ከእኔ ለማሸሽ ሲል ለኢኤስኤ ትሬድንግ ኃ/የተወሰነ የግል ማህበር በመውጫ ሰጥቷል የፍ/ቤቱን ዕግድ በመጣስ  ሸጦታል በማለት ያቀረቡት ክርክር ራሱ ችሎ መቅረብ የነበረበት ክርክር እንጅ በዚህ አሁን በቀረበው ክርክር ሊታይ የማይችል ከመሆኑም በላይ ንብረቱ ወደ ማህበሩ የተዛወረው በአመልካች በኩል የፍቺ ጥያቄ ለመቅረብና የዕግድ ትዕዛዝ ከመተላለፉ በፊት ስለሆነ የመ/ቁጥር  2545 የሚታወቀው ቤት የአመልካችና የተጠሪዎች የጋራ ሀብት ሳይሆን ጣልቃ ገብ በግዥ ያገኙት ንብረት ነው በማለት ወስኗል፡፡ እንዲሁም በዘምዘም ባንክ አ/ማህበር በተጠሪዎች ስም  የአከሲዮን


  ድርሻ የለም፣ በባንክ ስማችን የተቀመጠ ገንዘብ የለም በማለት ተጠሪዎች ቢከራከሩም ፍ/ቤቱ ስላቀረበው ማስረጃ ጭምር የተረጋገጠ ሆኖ ተገኝቷል በማለት ተረጋግጧል ባለው የገንዘብ መጠን መሰረት የአሁን አመልካች ድርሻ እንዳላቸው ገልፆ ዳኝነት ሰጥቶበታል በሌላ በኩል ጋብቻው ፀንቶ በነበረበት ወቅት ንብረት በማስተዳደር በኩል የፈፀሙት ጉድለት ያለመሆኑ ያለ መሆኑ ተጣርቶ ከተረጋገጠ በኋላ ለማ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡ ይሁን እንጅ ተጋቢዎች በጋብቻቸው ዘመን የጋራ ንብረታቸውን በጋራ እንዲያስተዳድሩ በሕጉ ግምት የሚወስድ ሲሆን ይህን ግምት ማፍረስ የሚቻለው አንደኛው ተጋቢ የሌለውን መብት የሚጎዳ ተግባር ፈፅሞ ስለመገኘቱ የማረጋገጥ ማስረጃ የቀረበ እንደሆነ በሕጉ አንቀፅ 87 ተደንግጓል 1ኛ ተጠሪ  ንብረት ሲያስተዳድሩ ፈፀሙ በሚል በማስረጃ የተረጋገጠና ተለይቶ የታወቀ ጉድለት ያልተገኘ በመሆኑ ፍ/ቤቱ ጥያቄውን አልተቀበለውም የሚለውን ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ፍ/ቤቱ ለሰጠው ዳኝነት በምክንያትነት ያሰፈረውን ሐተታ እና የሰጠውን የዳኝነት ዓይነት ከዚህ በላይ ባሰፈረው አኳኋን በሰጠው የፍርድ ክፍል ላይ ከገለፀው በኋላ በፍርድ መሰረት የተረጋገጠውንና ሊረጋገጥ ያልቻለውን ምስክር አስመልክቶ የፍርድ ተከታይ በሆነው የውሳኔ ክፍል ላይ

   

  በቂርቆስ ክ/ከተማ በቀሌ 02/03 ክልል በቤት ቁጥር 297 ተመዝግቦ የሚገኘውን ቤት በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የሚገኘውን ቤት አመልካችና ተጠሪዎች በጋራ ያፈሩት ንብረቶች ስለሆነ የክፍፍሉንም መንገድና ስልት ከመጥቀስ ጋር ሶስቱም እኩል እንዲከፈሉ በን/ስ/ላፍ/ክፍለ ከተማ በመ/ቁጥር 2545 የግልግል ሀብት ነው፤

   

  1ኛ ተጠሪ በቴክኖሎጅ ሲስተም ኃ/የተ/የግ/ማህበር ያላቸውን ሸር፣ በፒስ ደልለን ኃ/የተ/የማህበር ውስጥ ያለው ሸር 2ኛ ተጠሪ በዘምዘም ባንክ አ/ማህበር ያላቸው በሁለተኛ ተጠሪ ስም በዳሽን ባንክ ስለ አካባቢ ቅርንጫፍ በ1ኛ ተጠሪ ስም በወጋገን ባንክ ተ/ኃይማኖት ቅርንጫፍ በ1ኛ ተጠሪ ስም በዳሽን ባንክ ስለ አካባቢ ያስቀመጠውን ገንዘብ ከእነ መጠኑ በመግለፅ ሶስቱም እኩል እንዲካፈሉ በማለት በኮ/መ/ቁ 61875 በቀን 13/10/2004 ዓ.ም ወስኖ ግራ ቀኙን አሰናብቷል፡፡

   

  በዚህ ውሳኔ የአሁን አመልካች ቅር ተሰኝተው ባቀረቡት የይግባኝ ቅሬታ መነሻ ይግባኝ ሰሚው ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ 125893 ሁሉንም ወገኖች ከክርክር በኋላ

   

  የቤት ቁጥር 2545 አስመልክቶ የቀረበውን ጉዳይ በሚመለከት በዚሁ ቤት ላይ የስር ፍ/ቤት የካቲት 16/2003 ዓ.ም የዕግድ ትዕዛዝ ከመስጠቱ በፊት ቤቱ በ1ኛ አማካኝነት በመውጫነት ወደ ጅ.ኤስ.ኤ ጀኔራል ትሬድግግ ኃ/የተ/የግል ማህበር ገብቶ የነበረ እና 1ኛ ተጠሪ በማህበሩ ውስጥ የነበራቸውን 4127/4/ለ/2002 በቀን 12/9/2002 መተላለፉን የሰነዶች ማረጋገጫ ፅ/ቤት ለስር ፍ/ቤት በቀን 20/4/2004 ዓ.ም ከላከው ማስረጃ አረጋግጧል፡፡ እንዲሁም የዚሁ ቤት ስመ-


  ሀብትነት ወደ ጅኤስኤ ጀኔራል ትሬድንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በቀን 04/8/2002 በቁጥር ን/ስ/ቀ/05/83/3805/02 የተላለፈ ስለመሆኑ የን/ስ/ላ/ክ/ከተማ መሬት አስተደደርና ግንባታ ፅ/ቤት የካቲት 14 ቀን 2003 ዓ.ም በተፃፈና ለስር ፍ/ቤት ከላከው ሰነድ ተረጋግጧል፡፡

   

  ቤቱ ወደ ሶስተኛ ወገን በተላለፈበት ጊዜ ግንቦት 1/2002 ዓ.ም ግራ ቀኙ በጋብቻ ውስጥ የነበሩ ስለመሆኑ የስር ፍ/ቤት ግንቦት 24 ቀን 2002 ዓ.ም የሰጠው የፍቺ ውሳኔ ያረጋግጣል፡፡ በመሆኑም ይኽው ንብረት በጋብቻ ጊዜ ወደ ሶስተኛ ወገን ሲተላለፍ መተላለፉን አላወቀም ነበር የሚሉ ሲሆን አሁን ለዚህ ችሎት ውሉ እንዲፈርስ ስልጣን ባለው ፍ/ቤት ጥያቄ አቅርበው እየተከራከሩ እንደሚገኙ በገለፁት መልኩ ይኽው ውል በማስፈረስ መብታቸውን ከሚያስከብሩ በቀር በጠየቁት ዳኝነት አኳኋን ሊስተናገድ የሚችል አይደለም በማለት የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ሲያፀናው በ1ኛ ተጠሪ እና በ2ኛ ተጠሪ ስም የሚገኘውን የሼር ሀብት መጠንን በሚመለከት ማህበሮቹ ለስራ ተሰማርተው ያገኙትን ትርፍ ሁሉ አጠቃሎ መወሰን ሲገባው ማህበሮች በተቋቋሙበት ጊዜ በተደረገው መነሻ ይካተታል መጠን ላይ መወሰኑ አግባብ አለመሆኑን እንዲሁም በልዩ ልዩ በባንኮች በእነዚሁ ተጠሪዎች ስም አንፃር ይገኛል የተባለውን ሀብት መጠን አስመልክቶ ፍ/ቤቱ ገንዘብ ስለመኖሩ በጠየቀበት ጊዜ በባንኮች ተቀምጦ ተገኝቷል የተባለውን የገንዘብ መጠን ሳይሆን በትዳር በነበሩበት ጊዜ አንደኛዉ ወገን ብቻ በማውጣት ለግል ጥቅም ተጠቅሞበታል ከሚያሰኝ በቀር ለጋራ ጥቅም እንደዋለ አያስቀጥርም በማለት መነሻ ሊሆን ከሚችለው ጊዜ ጋር በማስተያየት በባንኮች ካላቸው ሂሳብ እንቅስቃሴ  በመነሳት መሠረት የሚገባዉ መሆኑን ጠቅሰን በዚሁ መሠረት እራሱ ይግባኝ በከካሽ ፍርድ ቤት ጉዳዮን ተመልክተ የገንዘቡን መጠን በፍርዱ የውሣኔ ክፍፍል በተገለፀው አኳኋን ከፍ አድርጎ በሚሻሻል መወሰን ፤

   

  በሸር ድርሻ ላይ የተወሰነውን የድርሻ መጠንን ከላይ በተመለከተው መሠረት ከውሳነ በኃላ የክፍፍል ማስረጃን በሚመለከት 1ኛ መልሰ ሰጭ በሀብቱም ማህበሮች የተወሰነላቸውን የአክስዮን ድርሻ ለተቻለ እና ተጠሪዎች የሚስማሙ ከሆነ በአባልነት እንዲቀጥሉ ይህ ካልተቻለ ተሽጦ የሽያጩን ድርሻ ይከፈላቸው የአከስዮኖች አሻሻጭም በንግድ ህግ አንቀጽ 523 እና ተከታዮች ድንጋጌዎች እንደዚሁም የሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.57288 በሰጠው የህግ ትርጉም መሠረት ሆኖ ድርሻቸው እንዲሰጣቸውና እንዲሁም በቤት ቁጥር 2545 ውስጥ/ የተሰጠውን ዕቃ በሚመለከት ቀርቧል በተባለው የወንጀል ክስ ምርመራ ውጠት መሠረት የአሁኑ አመልካች ጥያቄ የማቅርብ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን ከዚህ በላይ ከተገለፁት በቀር ሥማቸው በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ የፀና መሆኑን ለመግለፅ በሥር ፍ/ቤት የተሰጠውን ውሣኔ በማሻሻል የወሰነ መሆኑን ከፍርዱ ግልባጭ ተረድተናል ፡፡


  የአሁን አመልካች በዚህ የሰበር ሰሚ ችሎት ሊታረም ይገባል በማለት ለቅሬታቸው መሠረት ያደረጉት የቤት ቁጥር 2545 የሆነው ቤት የባልና ሚስት የጋራ ሀብት ነው ወይስ የአሁን 3ኛ ተጠሪ የሚለውን ለይቶ በመወሰን ረገድ፤እንዲሁም በሥር ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሣኔ የተረጋገጠባቸውን የአክስዮን ድርሻዎ የክፍፍሉን መንገድ በሚመለከት የአክስዮን ድርሻዎች በሚገኙበት ማህበር በአባልነት እንድቀጥል በማድረግ መወሰን ስገባው ማህበሩ ለተስማማ በሚል ተገልፆ የህግ መሠረት የለውም ለሚሉት መወሰኑ ነጥቦች ላይ ፡፡

   

  ተጠሪዎችም በበኩላቸው ክርክር በሚመለከታቸው ክርከር አንፃር በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ዳኝነት መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት አይደለም የሚሉበትን ምክንያት በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡

   

  እንግዲህ የጉዳዮ አነሳስ፤የክርክሩ ይዘትና የሥር ፍ/ቤቶች በየደረጃው የሰጡት ዳኝነት ፤የዚህን ዳኝነት አግባብነት በሚመለከት ወገኖች በዚህ ሰበር ችሎት ያቀረቡት ክርክር በይዘት ደረጃ ከላይ ከፍ ሲል ባጭር ባጭሩ የተመለከተው ሲሆን ፤እኛም ጉዳዮን እንደሚከተለው መርምረናል ፡፡ ተመልክተናል ፡፡

   

  ጉዳዮን እንደመረመርነውም በቤት ቁጥር 2545 የተመለከተውን ቤት አስመልከቶ የአሁን አመልካች ከሥር ፍ/ቤት ጀምሮ ለክርክራቸው መሠረት ያደረጉት ንብረቱ በሽያጭ ወደ አሁን 3ኛ ተጠሪ የተላለፈው ፍ/ቤቱ በዚሁ ንብረት ላይ ዕግድ ከሰጡበት በኃላ የፍ/ቤቱ ዕግድ ተጥሶ ስለሆነ የሽያጭ ተግባሩ ዋጋ አልባ ስለሆነ ሊፈርስ ይገባል የሚለውን አንደኛው የክርክር ነጥብ ሲሆን የዚህኑ ክርክር አግባብነት ለዚሁ ጉዳዮ በሥር ፍ/ቤቶች በነበረው የክርክር ሂደት በማስረጃ ከተረጋገጠው የፍሬ ነገር ጉዳይ በመነሳት ተመልክተናል ፡፡

   

  የአሁን አመልካች ለዚህ የሰበር ጉዳይ መነሻ የሆነውን ክስ ከቀረቡ በኃላ የክርክሩ ውጤት እስክታወቅ በሚል ይኽው ቤት በማናቸውም መንገድ ቢሆን ወደ ሶስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ የዕግድ ትእዛዝ የሰጡት የካቲት 16 ቀን 2003 ዓ.ም መሆኑና ይኽው ቤት በአሁን 1ኛ ተጠሪ አማካኝነት በዓይነት በመወጫነት ወደ ጂ.ኤስ.ኤ ጀኔራል ትሬድንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የገባውና ስመ ሀብትነቱም ወደ ዚሁ ማህበር ስም የተላለፈው ይኽው የወሰነበት የዕግድ ትእዛዝ ከመስጠቱ በፊት ስለመሆኑ በሥር ፍ/ቤት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ የአንድ ንብረት ባለሀብት ማን ነው የሚለው የሚወሰነው ደግሞ ንብረት ከአንዱ ወደ ሌላው ለማስተላለፍ የሚያስችለው እንደ ሽያጭ ስጦታ ወዘተ የመሳሰሉት ህጋዊ ተግባሮች በህግ ፊት በሚፀና አኳኋን ተፈፅመው እንደሆነ እና በዚሁ አኳኋን በተፈፀመው ህጋዊ ተግባር የተነሣ በንብረቱ ላይ የባለቤትነት መብት ያገኘ ሰው ንብረቱን ካስተላለፈዉ ተፈጥሯዊም ሆነ የህግ ሰው ባሻገር ማናቸውንም 3ኛ ወገን ለመመለስ የሚያስችለውን የስመ ሀብት ዝውውር ሥርዓት ሁሉ ታከናውኖ እንደሆነ በፍ/ብ/ህግ ቁጥር


  1678 ፣1731፣1184፣1195 ተደንግጓል፡፡ አሁን የተያዘውን ጉዳይ ከእነዚህ ድንጋጌዎች አንፃር ስነየው ክርክር ያስነሰው ንብረት በ1ኛ ተጠሪ እና ጀ አስ ኤ ጀኔራል ትሬዲንግ መካከል በተደረገ ስምምነት መሠረት ይኽው ንብረት በዓይነት በመወሰኑ ወደ ከማህበሩ ገብቶ፤ ማህበሩ በዚሁ ንብነት ላይ መብትና ግዴታ ያቋቋመ ሲሆን ከዚሁ ንብረት ወደ ማህበሩ መግበት የተነሰ ለአስተላለፈውም ግዴታ ፈጥሮለታል ይህ በህግ የተፈቀደ ንብረት ሊተላለፍ የሚችለበት አንዱ ህጋዊ ተግበር ሲሆን ማህበሩ በዚሁ ንብረት ላይ የእኔ በይ በመጣ ለመመለስ ዋስትና የሆነውን የስመ ሀብት ዝውውር ሥርዓት ሁሉ ፈፅሟ፡፡ በዚህም መሠረት የዚሁ ንብረት የበላቤትነት መብት ያለው ይኽው ማህበር እንጂ ሌላ ማናቸውም ወገን ሊሆን አይችልም ይህን በንብረት ላይ ያለን የበለሀብትነት መብት ማህበሩ ያቋቋመው ፍ/ቤቱ በንብረቱ ላይ የዕግድ ትዕዛዝ ከመስጠቱ በፊት ነው ከዚህ በንብረቱ ላይ የበለቤትነት መብት ከቋቋመ በኃላ በዚህ በህግ ከቋቋመው ላይ የበለቤትናት መብቱ ተጠብቆም በንብረቱ ላይ የማዘዝ ወደ ሌላ 3ኛ ወገን የመስተልለፍ መብት ያለው ሲሆን ሌላ ማየናቸውም 3ኛ ወገን ይህንኑ ንብረት ለሚመለከት ከመህበሩ ጋር በሚያደረገው ህጋዊ ተግበር ወደ እራሱ ያዛወረው ከሆነ ንብረቱን ለማዘወር መብትና ስልጣን ከለው ወገን ያገኘ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመለየት ማህበር ንብረቱን በሸጠበት ጊዜ በንብረቱ ላይ የተመለከተውን ስመ ሀብትነት ምዝገባ የሚከተል እንጂ 3ኛ ወገን ከማህበሩ ጋር ግብይት የፈፀመበት ጊዜ ሊሆን አይችልም ከዚህ በላይ ንብረት ከንደኛው ወገን ወደ ሌላው ሊተላለፍ የሚችልበትን መንገድ በሚመለከት በተጠቀሱት ድንጋጌዎች የተቀመጡት ሁለት ቋሚ መሟያዎች ማናቸውም በንብረት ላይ ሊኖር የሚችለው ግብዓት በህግ ዋስትና ተሰጥቶት በህ/ሰብ ደረጃ ያለስጋት የሠለጠ ኢኮኒሚያዊ ግንኙት ለመፍጠር እንዲያስችል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የአሁን አመልካች የፍ/ቤቱ የዕግድ ትዕዛዝ ከተለለፈ በኃላ 3ኛው ተጠሪ ከማህበሩ ጋር የሽያጭ ውል ያደረገበትን ጊዜ ተንተርሰው የሚያቀረቡት ክርክር የህግ መሠረት ያለው ሆኖ አላገኘነውም ፡፡

   

  ከዚህም በቀር የማይንቀሳቀስ ንብረት በዓይነት ለመውጫ ወደ አክሲሆን ማህበር ወይም ወደ ኩባንያ ስለመዘወሩ በመመስረቻ ፅሑፍ ሰፍሮና በዚህ መስረጃ መዝገብ ጽ/ቤት ተመዝግቦ በማንቀሰቀስ ንብረት በመዝገብ ውስጥ መመዝገቡ ከተረጋገጠ የ3ኛ ወገኖችን ላይ ለመመለስ የሚያስችለው ሥርዓት መሟለቱን እንደሚያመለክት ይህ ለሰበር ሰሚ ችሎት ከዚህ ቀርቦ ተመሰሰይ በሆነው በሰበር መ/ቁ.. 27869 ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ በመሆኑም ጭምር ከዕግድ ትዕዛዝ ጋር በተያየዘ የአሁን አመልካች የሚያቀርብበት ክርክር በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ዳኝነት መሠረተዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት መሆኑን የሚያመለክት ህጋዊ መሰረት የለው ክርክር አይደለም ሌላውና ይህንኑ በቤት ቁጥር 2545 የተመለከተውን ቤት  አስመልክቶ የአሁን አመልካች ያቀረቡት ክርክር በዋጅ ቁጥር 2/3/92 ስለጋራ የበልና ሚስት ሀብት አስተዳደርና ጥበቃ በህጉ የተቀመጠውን  የተጋቢዎች የጋራ ስምምነትን አስፈላጊነት በመጥቀስ ነው፡፡


  የጋራ ሃብት የሆነን ንብረት አንደኛው ተጋቢ ያለ ሌላኛው ተጋቢ ስምምነት ለሌላ ሶስተኛ ወገን በሽያጭ ማስተላለፍ እንደማይችል በዚሁ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 68 የተደነገገ ሲሆን፤ ይህ ድንጋጌ በይዘቱ የጋራ በሆነ ንብረት ላይ ተጋቢዎች እኩል መብት ያላቸው መሆኑን በህገ- መንግስቱ አንቀጽ 34(1) የተመለከተውን ህገ-መግስታዊ ድንጋጌ ተከትሎ የተደነገገ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በአገር በማህበረሰብ ውስጥ ንብረትን አስመልክቶ የሚደረገው ግብይት ያለማነቆ በሰለጠ አኳኋን እንዲፈጸም ካልተደረገ በአገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን እንቅፋት በማየት ይህ ከላይ የተመከተው የጋራ ስምምነት አስፈላጊነት በሁኔታ ላይ እንዲመረኮዝ በማስፈለጉ ተከታይ በሆነው አንቀጽ 69 እንደተመለከተው አንደኛው ተጋቢ ያለፈቃዱ ንብረቱ በአንደኛው ተጋቢ ብቻ መሸጡን በተረዳ ጊዜ ይህ የሽያጭ ተግባር በህጉ የተሰጠውን መብት የጣሰ መሆኑን መነሻ አድርጎ በክስ አማካኝነት ማስፈረስ እንደሚቻል፤ ይህንኑ የማስፈረስ ተግባሩን ካልተጠቀመ፤ ወይም በህጉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የማስፈረስ ጥያቄው ስልጣን ባለው ፍ/ቤት ካልቀረበ ግን አንደኛው ተጋቢ ብቻውን የፈጸመው ህጋዊ ተግባር እንደጸና እንደሚቀር እንጂ የጋራ ስምምነት ባለመኖሩ ምክንያት ብቻ ንብረቱ የተላለፈበትን ግብይት ወይም የሽያጭ ውል በዘፈቀደ በማናቸውም ጊዜ መቃወም እንደማይቻል ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም የስር ፍ/ቤቶች በዚህ ረገድ የሰጡት ዳኝነት የህጉን ትክክለኛ አፈጻጸም የተከተለ እንጂ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመ አይደለም፡፡

   

  የአሁን አመልካችም ይህንኑ ተገንዝበው ክርክራቸው በይግባኝ ደረጃ ለደረሰበት ጊዜ በዚሁ ስርዓት መሰረት በንብረት ላይ ያላቸውን መብታቸውን ለማስከበር ስልጣን ባለው ፍ/ቤት ክስ አቅርበው በክርክር ላይ የሚገኙ መሆኑን የገለጹ በመሆኑና ይህ ችሎም ለትክክለኛ ፍርድ አሰጣጥ ይህንኑ የተባለውን በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የቀረበውን የኮ/መ/ቁ. 194776 የሆነውን መዝገብም አስቀርበን እንደተመከትነው ጥያቄውን በዚያው አግባብ ማቅረባቸውን ተገንዝበናል፡፡ ይኸው ፍ/ቤትም ጉዳዩን ለጊዜው የዘጋው የፌዴራል ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ. 125895 የቀረበለትን የይግባኝ ጉዳይ መርምሮ የመጨረሻ ዳኝነት እስኪሰጥበት ጊዜ  ድረስ በማገዱ ምክንያት በመሆኑና ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ዳኝነት የሰጠበት ጉዳይ ስለሆነ የስር ፍ/ቤቶች በፍርዳቸው ላይ እንደገለጹት መብታቸውን ከሚያስከብሩ በቀር በዚህ የጋራ ንብረት መሆኑ ተረጋግጦ የጋራ ሃብትን ለማከፋፈል እንዲቻል በቀረበው መዝገብ ላይ ወደ ሶስተኛ ወገን በሽያጭ አማካኝነት ተላልፎ የባልና ሚስት የጋራ ሃብት መሆኑ ያልተረጋገጠውን የቤት ቁጥር 2545 እንደጋራ ሃብት ሊቆጠር ይገባል በማለት የሚያቀ ርቡት ክርክር ተቀባይነት ያለውም አይደለም፡፡

   

  ሌላውና ለዚህ የሰበር ጉዳይ የክርክር ምክንያት የሆነው ለአሁን አመልካች ይግባኝ ሰሚ ከፍተኛው  ፍ/ቤት  አሻሽሎ  በወሰነላቸው  የአክሲዮን  ሼር  ድርሻ  ላይ  ያላቸውን     ሀብት


  የሚያገኙበትን ተጠቃሚ የሚሆንቨትን መንገድ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሚስማማ ከሆነ በአባልነት እንዲቀጥሉ ይህ ካልሆነም ተሽጦ የሸያጭ ድርሻ እንዲያገኙ በማለት በንግድ ህግ ቁጥር 523 እና ተከታዮቹ የተመለከተውን መሠረት በማድረግና በሰበር ሰሚው ችሎት በሰበር መ/ቁ.57288 የተሰጠውን ትዕዛዝ በመከተል የሰጠውን ዳኝነት አግባብነቱን አስመልክቶ ግራ ቀኙ ክርክር ያደረጉበት ጉዳይ ነው፡፡

   

  ይህንንም ጉዳይ እንደተመለከትነው በማናቸውም ምክንያት በፍ/ቤት በሚሰጥ  ፍርድ የሚረጋገጠው መብት ከተብ ወይም ከውል የመነጨውን መብት መኖርና አለመኖር አስመልክቶ እንዲህጉ አነጋገር ለማስረዳት የቀረበውን ክርክርና ክርክሩን አነጋገር ለማስረዳት የቀረበውን ክርክርና ክርክርን ለማስረዳት የቀረበውን መብት ወደ ተግባር ይህንኑ ከህግ እንዲያስችል ለመብት ምንጭ የሆነውን ህግ መሠረት በማድረግ ነው፡፡

   

  ከዚህም አንፃር ጉዳዩን አግባብነት ካለው ህግ ጋር ተገናዝቦ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡

   

  አግባብነት ካላቸው ህጎች አንዱ ይኸው የአክቢዮን ድርሻ ግራ ቀኙ በጋብቻ ዘን በነበሩበት ጊዜ የተፈራ የጋራ ሀብት እንደመሆኑ መጠን በሀብቱ የባለእኩልነት ድርሻቸውን የሚቃረጋግጠው አዋጅ ቁጥር 213/92 አንቀጽ 62 አንዱ ሲሆን እንዲሁም ከዚሁ የጋራ ሀብት ነው፡፡ ከተባለው የሀብት ዓይነት አንፃር ሲታይ ደግሞ የዚህ የጋራ ሀብት የክፍፍል ሁኔታ የሀብቱን ጉዳይ ምክንያት በማድረግ በሚደነግገው በንግድ ህጉ አንቀጽ 523 የተመለከተው ድንጋጌ ደግሞ ሌላው ነው፡፡ ስለሆነም የዚህኑ ክፍፍል ሥርዓት የሚደረግበትን መንገድ በሚመለከት የሥር ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በንግድ ህጉ አንቀጽ 523 ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ መሠረት ማድረግ የሚያነቀፍ አይደለም፡፡ ሆኖም ይህንኑ ድንጋጌ እንደሙሉ ይዘቱ አይነት ተፈፃሚ በማድረግ ስለሆነም የአሁኑ አመልካች በፍርድ በተረጋገጠላቸው የአክሲዮን ድርሻ ቫት መብት ላይ ከንግድ ህጉ አንቀጽ 523 አንፃር አየቶ መብቱን ለማረጋገጥ መነሻ ለሆኑ ከሚገባቸው የህጉ ክልሎች መካከል በንግድ ህጉ አንቀጽ 523/2/ እንደተመለከተው የአክሲዮን ማህበር መመሥረቻ ፅሑፍ የይዙቱ የአሁን አመልካች በማህበሩ አባልነት ተካተው በአባልነት ይህንኑ ለፍርድ በተረጋገጡባቸው የአክሲዮን ድርሻ ሀብት መገልገል የሚቻሉ መሆኑንና አለመሆኑን አስመልክቶ ምን እንደሚል ከመመስረቻ ፅሑፍ ጋር አገናዝቦ ከታየ በኋላ ሊታይ የሚገባው እንጂ ሆና እያለ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሰጠው ዳኝነት በዚህ ረገድ የተባለ ሆኖ አላገኘነውም ስለሆነም በዚሁ የነግድ ህግ ቁጥር 523/2/ ድንጋጌ ተትክከለኛ አፈፃፀሙን ተከትሎ ፍርድ በመስጠት  ረገድ የታየው ጉድለት ሊታረም የሚገባው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

   

  በዚህ ሁሉ ምክንያት የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥተናል፡


   ው ሣ ኔ

   

  1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ.61875በቀን 13/10/2004 ዓ5ም የሰጠውን ፍርድ እንዲሁም ይግባኝ ሰሚው ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ12559 ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠውን ፍርድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 325/1/ መሠረት አሻሽለን ወስነናል፡፡

  2. በን/ስ/ላ/ከተማ ወረዳ 03 ክልል ውስጥ በመ/ቁጥር 2545 ተመዝገቦ የሚታወቀው  ቤት ላይ የባለቤትነት መብት ያለው የአሁን 3ኛ ተጠሪ አቶ ሐገስ አብዱራህማን ናቸው መባሉ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡

  3. ለአሁን አመልካች በፍርድ በተረጋገጡላቸው የአክሲዮን ድርሻና መጠን ላይ ባላዠው የሀብት መብት ላይ መገልገል የሚቻልበት ማበህበሩ አባልነት ተካተው በአባልነት ነው ወይስ በአባልነት መገልገሉ የሚቻሉበት ህጋዊ ምክንያት ታይቶ በሐራጁ ተሽጦ ይህንኑ ሀብት እንደያገኙት ነው?የሚባለው ጭብጥ ከማህበሩ መመስረቻ ፅሑፍ ይዘት እና ከንግድ ህጉ አንቀጽ 523/2/ አንፃር ታይቶ ይወሰልን ዘንድ ብቻ መዝገቡን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ.343/1/ መሠረት ወደ ሥር ፈ/ቤት መልሰናል፡፡

  4. የዚህ ክርከር ውጤት እሰኪታወቅ ድረስ በሚል በዚህ የስር መዝገብ ቁጥር 103721 ተሰጥቶ የነበረው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል ይፃፍ፡፡

  5. የዚህ የሰበር ክርክር ጉዳይ ስላስከተው ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሳቸው ይቻሉ፡፡ ብለናል፡፡

  መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት መልሰናል፡፡

  የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

   

   

  መ/ተ

 • አንድ ጋብቻ ሲፈርስ ንብረት ክፍፍልን በሚመለከት በእርቅ ውል ስምምነት በሽማግሌ የተደረገው እርቅ በፍ/ቤት ተመዝግቦ ከተዘጋ በኋላ እንደገና እንደ ባልና ሚስት አብረን እየኖርን ስለነበር በድጋሚ የንብረት ክፍፍል ይደረግ የሚል ጥያቄ አግባብነት ያለው ስላለመሆኑ፣

   

  የሰ/መ/ቁ. 105054

  ታህሳስ 22 ቀን 2008ዓ/ም

  ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ

   

  ሙስጠፋ  አህመድ ተፈሪ ገብሩ

  ሸምሱ ሲርጋጋ አብርሃ መሰለ

  አመልካች፡- ወ/ሮ ጌጤ እጅጉ -ቀርበዋል ተጠሪ፡-አቶ ብርሃኑ ተሰማ   -ቀርቧል

  መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

   

   ፍ ር ድ

   

  ጉዳዩ የባልና ሚስት አፈፃፀም የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ የተጀመረው በሌሙና ቢልቢሎ ወረዳ ፍርድ ቤት ተጠሪ ባቀረቡት የአፈፃፀም ክስ ነው፡፡ የአቤቱታውን ይዘትም ባጭሩ በመ/ቁ.343/96 በቀን 21/8/1996 ዓ/ም የነበረው ጋብቻ ሲፈርስ ንብረት ክፍፍል በሚመለከት በእርቅ ውል ስምምነት በሽማግሌ የተደረገው እርቅ በፍርድ ቤት ተመዝግቦ ተዘግተዋል፡፡ በዚሁ መሰረትም አንድ ወፍጮ ቤት፤ አንድ የዘይት መጭመቂያ ቤት እና አንድ ፒፒሻ ሽጉጥ የተጠሪው እንደሆነ ፍርድ ቤት በውሳኔው አረጋግጠዋል፡፡ ከውሳኔ በኃላ ታርቀን በባልና ሚስት ሆነን ስንኖር የዲገሉና ጢጆ ወረዳ ፍርድ ቤት መ/ቁ.19963 በቀን 9/8/ 2005ዓ/ም እና የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.6054 በቀን 19/10/05ዓ/ም በመ/ቁ. 343/96 በሆነው መዝገብ ላይ የተሰጠ የንብረት ክፍፍል እንዳይነካ ሲል ተወስነዋል፡፡ ስለዚህ የወፍጮ ቤት የነበረው አሁን የእንጨት መሰንጠቂያ የሆነው እና የዘይት መጭመቂያ ቤት ስም ይዛወርልኝ ፒፒሻ ሽጉጥ ታስረክበኝ ወይም ግምቱ 26,000 ብር እንዲከፈለኝ ሲሉ አፈፃፀም መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካችም በሰጡት መልስ በ1996 ዓ/ም ባልና ሚስት መሆናችን የማይካድ እውነት ነው፡፡ ትዳር ሲፈርስ ለኔ የተሰጠኝ የያዝኩት እንጂ የተጠሪ አይደለም፡፡ ያልተወሰነበት የሚፈፅምበት ነገር የለም፡፡ በእጄ የሌለውን ነገር ለመፈፀም አልገደድም፡፡ ጋብቻ ከፈረሰ የሰራሁት በስሜ ካርታ አውጥቼ የሚሰራበት ነው በማለት መልሳቸውን አቅርበዋል፡፡


  የስር ፍርድ ቤትም የግራቀኙን ማስረጃ በመመዘን በውላቸው መሰረት መፈፀም አለበት በማለት የዘይት መጨመቂያና የወፍጮ ቤት የነበረ ወደ እንጨት መሰንጠቂያ የተቀየረው ወደ ተጠሪ ስም እንዲዛወር እና ሽጉጥ እንዲያስረክቡ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡

   

  በዚሁ ትእዛዝ ላይ ከአሁኑ አመልካች ይግባኝ የቀረበለት የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በሽጉጥ የተሰጠው ትእዛዝ በማሻሻል በሌሎቹ ንብረቶች ላይ የስር ፍርድ ቤት በማፅናት ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡ በመቀጠል ለኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቅሬታ በአመልካች በመቅረቡ የግራ ቀኙ ክርክር ከሰማ በኃላ የዘይት መጭመቂያ በተመለከተ የተሰጠው ትእዛዝ በማፅናት፤ ወፍጮ ቤት የነበረው ወደ እንጨት መሰንጠቂያ ቤቱ የተጠሪ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ እንጨት ድርጅት ሲቀየር ማሽኖቹና መሳሪያዎቹ የተገዙት እንደ ባልና ሚስት በአንድ ቤት  በሚኖርበት ጊዜ ስለሆነ ማሽኖቹና ዕቃዎቹ በባለሙያ ተገምቶ ግምቱ ወይም በጨረታ በመሸጥ እኩል እንዲካፈሉ በማለት በመሻሻል ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የተፈፀመ መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የለበትም ሲል አቤቱታው ሳይቀበለው በትእዛዝ ዘግቶታል፡፡

   

  የሰበር አቤቱታ የቀረበውም የስር ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ የሰጡት ዳኝነት መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት ስለሆነ ሊታረም ይገባል በማለት ነው፡፡ አቤቱታው  በሰበር ችሎት እንዲታይ የተያዘው ጭብጥ የእንጨት ድርጅት የተቋቋመው ወፍጮ ቤት የነበረው በ1996ዓ/ም በስምምነት ከተካፈሉ በኃላ እንደገና እንደባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ መሆኑ ባልተካደበት በተደረገው የንብረት ከፍፍል ስምምነት መሰረት ቤቱ የተጠሪ ነው ተብሏል በሚል መነሻ አመልካች በአፈፃፀም መዝገብ ላይ ለተጠሪ እንድትለቅ የተሰጠው ትእዛዝ ህጋዊ የክርክር አካሄድና አመራርን የተከተለ መሆን አለመሆኑን ለመመርመር ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮ ለሰበር ችሎቱ ሊታይ የሚገባ ነው ተብሎ በመታዘዙ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡ አመልካችም የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

   

  የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ እንደተገለፀው ሲሆን በዚህ መሰረትም በጭብጥነት በተያዘው ነጥብ ከግራ ቀኝ ወገኖች ክርክር፤ አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና ከሕጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል፡፡ ጉዳዩ የአፈፃፀም ከስ ስለሆነ በዋናው ጉዳይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረት እንዲፈፀም መደረግ አለበት፡፡ በግራ ቀኙ የተማመኑበት ጉዳይ በመሐከላቸው የነበረው ጋብቻ በፍቺ ሲፈርስ የንብረት ክፍፍል በስምምነት በማድረግ በፍርድ ቤት ተቀባይነት አግኝቶ የፀደቀ ነው፡፡ ከፍቺ በኃላም እንደባልና ሚስት አብረው እየኖሩ እንደነበር በስር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ፍሬ ነገር ነው፡፡ በ2005ዓ/ም የአሁኑ ተጠሪ የፍቺ ክስ ለፍርድ ቤት አቅርበው ነገር ግን ጋብቻ የለም ግንኙታቸው


  እንደ ባልና ሚስት አብረው እንደሚኖሩ ሰዎች የሚባል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ አብረው ያፈሩት ንብረት የጋራ እንዲሆንና በ1996 ዓ/ም የተደረገው ክፍፍል የተጠበቀ መሆኑን ውሳኔ ተሰጥተዋል፡፡

   

  ውሳኔው ይህ ከሆነ አፈፃፀሙን የዘይት መጭመቂያና የወፍጮ ቤት ለተጠሪ የደረሰው መሆኑን አመልካችም የራስዋ ድርሻ እንደያዘች ከስር መዝገብ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከፍቺ በኃላ አብረው መኖር ከጀመሩ ያፈሩት ንብረት መኖር አለመኖሩን ለማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባለቸው የስር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ወፍጮ ቤት የነበረው ወደ የእንጨት ድርጅት ሲቀየር የተለያዩ ማሽኖችና ዕቃዎች አብረው ያፈሯቸው እንደሆነ ነው፡፡ በዚህ መሰረትም አብረው ያፈሩት ማሽኖችና እቃዎች እኩል አንዲካፈሉ፤ ቤቱ ደግሞ ለተጠሪ እንዲሆን በማለት የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስሕተት ያለበት ሆኖ አልተገኘም፡፡ በዚሁ መሰረትም የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

   

   ው ሳ ኔ

   

  1. የኦሮሚያ ጠ/ ፍ/ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.181913 በቀን 12/10/2006 ዓ/ም የስር

   

  ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በማሻሻል ሰጠው ውሳኔ እና የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.185727 በቀን 22/11/2006ዓ/ም የሰጠው ትእዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ.348/1/ መሰረት አጽንተናል፡፡

   

  2. በዚህ ችሎት ተሰጥቶ የነበረው የእግድ ትእዛዝ ተነሰተዋል ለሚመለከተው አካል ይተላለፍ፡፡

   

  3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ወጭና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገብ ተዘግተዋል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

   

   

  የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

   

   

  መ/ይ

 • የጋብቻ የምስክር ወረቀት ተገቢውን ስርዓት ተከትሎ የተሰጠ አይደለም ተብሎ መሰረዝ ጋብቻ አልነበረም ለማለት የሚያስችል ስላለመሆኑ፣

  Download Cassation Decision

 • ባል ወይም ሚስት የጡረታ አበል ተጠቃሚ ሆነው ባሉበት ፍቺ ቢከሰት የጡረታ መብት ተጠቃሚ የሆነው ባል ወይም ሚስት የጡረታ አበል ለባል ወይም ለሚስት ሊያካፍል የሚገባ ስላለመሆኑ ፣ የመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 345/95 አንቀጽ 35

  Download Cassation Decision

 • የገጠር መሬት እንደሌላው ንብረት በመቁጠር ከቤተሰብ ህጉ አንጻር የሚታይ ስላለመሆኑ ፣ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በአንድ ተጋቢ ስም ተዘጋጅቶ ከተሰጠ በኋላ ጋብቻ ቢፈፀምና ተጋቢዎቹ መሬቱን የጋራ ለማድረግ ሊስማሙ የሚችሉ ስለመሆኑ፣ የአማራ ክልል የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ ቁ. 133/1999 አንቀጽ 24/3/ ደንብ ቁ. 151/1999 አንቀጽ 20/6/

  Download Cassation Decision

 • በአባት በኩል ያለን መወለድ መቃወም የሚቻለው የልጁ አባት ነው ተብሎ በህግ ግምት የሚሰጠው ሰው እሱ የሞተ ወይም ችሎታ ያጣ እንደሆነ ከተወላጆቹ አንዱ የመካድ ክስ በማቅረብ መቃወም የሚችል ስለመሆኑ፣ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁ. 213/1992/አንቀጽ 167፣174 እና 179

  Download Cassation Decision

 • እድሜው ያልደረሰ ልጅ የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመሸጥ የሚያስችል የሞግዚት ስልጣን ይሰጠኝ ጥያቄ ፍ/ቤቶች የህፃንን መብትና ድህንነት ቅድሚያ እንዲሰጠው በማደረግ ሲወሰኑ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቀረበውን መሰረታዊ ጥያቄ እና አማራጭ መፍትሔ መኖሩን አለመኖሩን በማጣራት መወሰን ያለበት ሰለመሆኑ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሰት 36 (2) ፣ ፍ/ብ/ሕ/ቁ 280 እና 289(1) የቤተሰብ ህግ አዋጅ 213/1992 አንቀፅ 43

  Download Cassation Decision

 • ባልና ሚስት የጋራ የሆነውን የንግድ ድርጅታቸውን መልካም ስም የማከራየት መብትና በቤቱ ውስጥ የሚገኘውን የንግድ ዕቃ የመከፋፈል መብት ያላቸው ስለመሆኑ፣ የን/ሕ/ቁ. 127

  Download Cassation Decision

 • የመጀመሪያ ሚስት በንብረትዋ ላይ ስምምነት ባላደረገችበት ፤ባል ሁለተኛ ሚስት ሲያገባ መቃወሚያ አላቀረበችም በማለት በንብረትዋ ላይም ስምምነት አድርጋለች በማለት በመደምደም ፤ሁለተኛ ሚስት እኩል እንድትካፈል በማለት የሚሰጥ ውሳኔ ህጋዊ ስላለመሆኑ

  Download Cassation Decision

 • የባልና ሚስት የጋራ ንብረት ነው የተባለ ንብረትን አፈፃፀምን በተመለከተ የንብረቱ ሕጋዊነት ላይ የሚመለከተው አስተዳደር አካል አግባብ ያለው ውሣኔ እስኪሰጥ ድረስ መሸጥ መለወጥ ባይቻልም ባለበት ሁኔታ የግራ ቀኙን እኩል ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አግባብ በጋራ የሚያስተዳድሩበት ወይም ተከፋፍለው የሚጠቀሙበት ወይም አከራይተው ጥቅሙን እኩል የሚከፋፈሉበት ሁኔታ መመቻቸት ያለበት ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ 386/2/

  Download Cassation Decision

 • በሌላ አገር ህግ እና በኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ መካከል እንደባልና ሚስት አብረው በመኖር ግንኙነት ውስጥ የተፈራ ንብረት የጋራ እንዲሆን ለመወሰን በሁለቱም ህጎች መካከል ግጭት መኖር ያለመኖሩን የሌላኛው አገር ህግ እንዲቀርብ በማድረግ መወሰን የሚገባው ስለመሆኑ በዓለም አቀፍ የግለሰብ ህግ /Private International law/ መሠረት በዘርፉ እውቀት ያለ ወይም ምሁር /Scholar/ የሰጠውን አስተያየት በማስረጃነት ሲቀርብ የቀረበውን አስተያየት እንደማንኛውም ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን አስተያየቱ የቀረበለት ፍርድ ቤት ስለመሆኑ የኢ.ፊ.ድ.ሪ ቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/92 አንቀጽ 5፤102 /1/

  Download Cassation Decision

 • ጋ ብቻ ሳይፈጸም እንደባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነትን ለማስረዳት የቀረበ ማስረጃ ግንኙነቱን የማሳየት ብቃት ያለው መሆኑ ከተረጋገጠ የግንኙነቱን ያለመኖር በማንሳት የሚከራከረው ሌላኛው ወገን በህግ ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ ግንኙነት ስላለመኖሩና ንብረቶችም የግል ስለመሆናቸው የማስረዳት ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ፣ አዋጅ ቁ. 75/1995 117/4/ እና 114 እና 97 አንቀጽ 109፣110፣113 እና 117

  Download Cassation Decision

 • ጋብቻ የተፈጸመው በአንድ ክልል ውስጥ እና በዚያው ክልል ሕግ መሰረት ሆኖ ክስ በቀረበበት ጊዜ ተጋቢዎቹ የሚኖሩት በተለያዩ ክልሎች ውስጥ መሆኑ ቢረጋገጥ እንኳ ከፍቺ እና መሰል ጥያቄዎች ጋር ተይይዘው የሚነሱ ጉዳዮችን የማስተናገድ የስረ ነገር ስልጣን በክልሉ ሕግ መሰረት ጉዳዩን የማየት ስልጣን የተሰጠው የክልሉ ፍርድ ቤት እንጂ ተጋቢዎቹ መደበኛ ነዋሪነታቸው በተለያዩ ክልሎች ውስጥ እንደሆነ ተቆጥሮ ጉዳዩ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን ስር የሚወድቅ ስላለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 25/1988 (እንደተሻሻለ) አንቀጽ 5 (2)

  Download Cassation Decision

 • በፌደራል የቤተሰብ ህግ መሰረት በአባት በኩል ያለን መወለድ የመካድ ክስ በማቅረብ መቃወም ስለሚችሉ ሰዎች የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 177/1-3

  Download Cassation Decision